በአማራው ክልል በሕዳር ወር የተከሰቱ ግጭቶች – #ግርማ_ካሳ

Amhara– በመቶዎች የሚቆጠሩ የአገዛዙ ታጣቂዎች ተገድለዋል።

– በወልቃይት ፣ በጠገዴም በሁመራ ካፍቲያ፣ በወገራ ፣ በታች አርማጭሆ፣ በመራብ አርማጭሆ ሕዝቡ ከሕወሃት ታጣቂዎች ጋር ከፍተኛ ጦርነት እያደረገ ነው።

ጦርነት አገርን አወዳሚ ነው።ወደ ጦርነት እንዳይኬድ ፣ በአገራችን ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር እንዲኖር፣ የሰላማዊ ፓርቲዎች ለማጠናከር በመሞከር ብዙዎቻችን ማድረግ የምንችለውን አድርገናል። ሆኖም ሕወሃቶች የሰላማዊ ታግዮችን እያፈኑ ነው። የሕወሃት ግትር ፖለቲካ ቀስ በቀስ ወደ ከፋ ደረጃ እያደረሰን ነው።፡

ሕወሃት ነገሮችን አድበስብሶ ፣ ምንም ችግር እንዳልተፈጠረ ሊነግረን ይሞክራሉ። ግን በሽታንን ከደበቅን በሽታን መጨረሻ ይገድለናል። አገራችን በአሁኑ ወቅት ታማለች። ጦርነት ዉስጥ ነው ያለችው። ከበሽታዋ ትድን ዘንድ፣ አስቸኳይ መፍትሄ ይገኝ ዘንድ፣ ያለዉን ሁኔታ መዘገብና ለሕዝብ ማሳወቅ አስፈላጊ ነው።

አገዛዙ የምናቀርበውን ዘገባ ዉሸት ነው ብሎ ሊያጣጥለው ይችላል። “አታካብዱ፣ ነገሩ ቀላል ነው። በቀላሉ ልንቆጣጠረው እንችላለን” ሊሉ ይችላሉ። ግን እየሰማን ያለነው በመቶዎች የሚቆጠሩ የአገዛዙ ታጣቂውዎች እየወደቁ እንዳለ ነው።

ምንም እንኳን የመሳሪያ ሃይል የበላይነት ቢኖራቸውም፣ ጦርነት ጦርነት ነው። በተቻለ መጠን ጦርነት ትንሽም ብትሆን የሚወገድበትን መንገድ መፈለግ ይሻላል። ጦርነት እንዲወገድ ደግሞ፣ በተለይም ህዝብ መሮት ከተነሳ፣ በምንም አይነት መልኩ ከሕዝብ ጋር ካልተስማሙና የሕዝብን ጥያቄ ካላከበሩ በቀር መፍትሄ እንደሌለ ተረድተው ከህዝብ ጋር መታረቅ ብቻ ነው መፍትሄው።

በአማራው ክልል ስላለው የአለመረጋጋት ሁኔታ ስንመለስ ችግሩ በዋናነት የተቀሰቀሰው በወልቃይ ዙሪያ እንደሆነ ለማስታወስ እንወዳለን።

ቀድሞ የጎንደር ክፍለ ሃገር አካል የነበሩ በርካታ ወረዳዎችን ወደ ትግራይ ክልል ሕወሃት መቀላቀሉ ይታወቃል። ጠመንጃና ሃይል ያለው እርሱ በመሆኑ ከሕዝብ ፍላጎት ውጭ ያደረገው ነበር። ከነዚህ ወረዳዎች መካከል ወልቃይት፣ ጠገዴም ሁመራ የመሳሰሉት ይገኙበታል። በወልቃት ጠገዴ ሕዝቡ ለዘመናት ትግሬ፣ አማራ ሳይባባል በሰላም የኖረ ህዝብ ነው። እንደ ወልቃይቴ። ህዝቡ ተዋልዷል። ሆኖም ሕወሃት መርዛማ የዘር ፖለቲካ ረጭቶ በወልቃይት በሰላም የኖሩትን መከፋፈል ጀመረ። የአካባብዊ አብዛኛ ነዋሪዎችን በግድ “ትግሬ ናችሁ” ማለት ጀመረ። ሕዝቡ ትግሪኛም፣ አማርኛም ስለሚናገር፣ በሁለትም ቋንቋዎችን አገልግሎት ቢሰጠው ምንም ችግር አልነበረም። ሆኖም ሕዝቡ በአማርኛ አገልግሎት እንዳያገኝ ተደረገ ። አድሎ ይደረግበት፣ ከመሬቱም ይፈናቀል ጀመረ።

ሕዝቡ መሰረታዊ የመብትና የማንነትን ጥያቄ በማንሳት “እኛ ትግሬ አይደለንም” በሚል ወደ አማራው ክልል መጠቃለል ይቻል ዘንድ ፣ ኮሚቴዎችን በማቋቋም ሰላማዊና ሕጋዊ በሆነ መንገድ ጥያቄዎችን አቀረበ። ሆኖም የሕዝቡን ሰላማዊ ጥያቄ ሕወሃት በጉልበት ለመጨፍለቅ ሞከረ። እንደ ኮሎኔል ደመቀ ያሉ የኮሚቴ አባላትን አሰረ። ከዚህም የተነሳ በዚያ አካባቢ ተቃዉሞ የበለጠ ተጠናከረ። በወልቃይት የተጀመረው እንቅስቃሴ መላው ጎንደርና ጎጃምን አጥለቀለቀ። ጥያቄው ከወልቃይት ጥያቄ አልፎ በመሄድ መሰረታዊ የስርዓት ለዉጥ ጥያቄነት ተሸጋገረ።

አገዛዙ የሕዝብን ጥያቄ አክብሮ ለተነሱ ችግሮች ሰላማዊ መፍትሄዎች እንዲሰጥ ለብሄራዊ እርቅ እንዲዘጋጅ ቢጠየቅም፣ አሻፈረኝ ብሎ፣ በጎንደር እና በጎጃም ያለውን ተቃዉሞ በሃይል ለመጨፍለቅ ወሰነ። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ በአማራው ክል ሕዝብ ላይ ጦርነት አወጀ። የታሰበው በሃይልና በጉልበት ነገሮች ዘጥ ረጭ ለማድረግ ነበር። ሆኖም ግን ነገሮች እየተባባሱ መጡ።

ከዚህ በመቀጠል ላለፉት ሶስት ሳምንታት የተከሰቱ ግጭቶችን ዘርዝረን በማቅርብ ምን ያህል በአማራው ክልል ሁኔታዎች እየተባባሱ እንደሆነ ለማሳየት እንሞክራሉ።

ይሄን መረጃ ያጠናቀርነው አንድ በአማራው ተጋድሎ ዙሪያ መረጃዎች ሲያቀሩ ከነበሩ፣ ብዙ ጊዜ የሚያቀርቡት ዘገባዎች ትክክለኛ ሆነው ካገኘናቸው ጋዜጠኖች፣ በአካባቢው ካሉ ወገኖች ከሚደርሱን መረጃዎች በመነሳት ነው።

ሕዳር 7 እና 8 ቀን 2009 – ቆላ ቃብቲያ ሁመራ ፡
=========================
የሕወሃት ታጣቂዎች በገበሬው ላይ በከፈቱት ጦርነት ቁጥራቸው በዉል የማይታወቅ የሕወሃት ታጣቂዎች ተገድለዋል። “ጣእመ” በሚል ስም የሚታወቅ የሕወሃት የጸረ-ሽምቅ ሃላፊን በነበረው ዉጊያ ተገድሏል። በዚህ ወቅት በአማራው ክልል ያሉ የአማራው ተጋድሎ ታጣቂዎች “ከፋኝ” በሚል ስም እንደሚንቀሳቀሱ ይፋ አድርገዋል።

ሕዳር 10 አዲ ገሹ (ወልቃይት ጠገዴ)
==========================
በወልቃይት ጠገዴ በአዲ ገሹ ከተማ የከፋኝ ጦር ከሕወሃት ታጣቂዎች ጋር ከፍተኛ ዉጊያ ያደረገ ሲሆን፣ በወቅቱም የከፋኝ ወጣት ተዋጊዎች የአዲ ጎቹን ከተማም ሙሉ ለሙሉ ተቆጣጥረዋት ነበር።

ኅዳር 14 ታች አርማጭሆ
==================
ታች አርማጭሆ ወደ ሳንጃ የሄዱ ሶስት የሰሜን ምእራብ አካባቢ የመብራት ሃይል ሰራተኞች መኪናቸው ተቃጥሎ ግለሰቦቹ ተማርከዋል። አገዛዙ በታጣቂዎች ጥቃት እንዳይደርስበት ከመከላከያ መኪናዎች ዉጭ ባሉ ሌሎች መኪናዎች ታጣቂዎችን የማመላሰ ልማድ ስላለው ነው የመብራት ሃይል መኪና ለጥቃት የተጋለጡት።

ኅዳር 16 አርማጭሆና ጠገዴ
===============
በወልቃያት ጠገዴ የተለኮሰው ዉጉያ ወደ አርማጭሆ በመዞር በዚያም የከፋኝ ታጋዮች ከሕወሃት ታጣቂዎች ጋር ከፍተኛ ጦርነት ሲያደረጉ ነበር። ህወሃት ያሰማራቸው በርካታ ሚሊሻዎች አገዛዙን በመክዳት ከፋኝን ተቀላቅለዋል።
በአርማጭሆና በጠገዴ በተደረገው ዉጉያ ከ70 በላይ የሕወሃት ታጣቂዎች የተገደሉ ሲሆን፣ በርካታ ቀላልና ከባድ የጦር መሳሪያዎች ተማርከዋል። ከከፋኝ ታጋዮች መካከል ሁለት እንደሞቱ መረጃዎች ጠቁመዋል። ከነዚህ መካከል አርበኛ ሞላ አጃው የተባለ በ2008 ዓ.ም፣ በጎንደር ባዕታ አካባቢ ከነበረው ማረሚያ ቤት፣ ቃጠሎ በተነሳበት ወቅት ከወያኔ እስር አምልጦ በአርማጭሆና በጠገዴ አካባቢ ከወያኔ ጦር ጋር ጀብድ ሲሠራ የቆየ አርበኛ ነበር።

ኅዳር 17 እና 18 – ወገራ
==================
በሰሜን ጎንደር የተጀመረው የሕወሃት ጠብ ጫሪነት አድማሱን እያሰፋ በተለያዩ ቦታዎች ዉጊያዎች እየተከሰቱ ነው። ጦርነቱ ከወልቃይት ጠገዴና አርማጭሆ በማለፍ ወደ ወገራ ተሸጋግሯል። የአገዛዙ ታጣቂዎች ሕዝቡን ትጥቅ እናስፈታለን በሚል ባደረጉት ትንኮሳ በሰሜን ጎንደር ወገራ ወረዳ የእንቃሽና የጃኖራ ቀበሌ ገበሬዎች ራሳቸውን ለመመከት ባደረጉት ሙከራ በርካታ የሕወሃት ታጣቂዎች ተገድለዋል። የቆሰሉና የተማረኩም አሉ። በነጋታው ሌላ የታጠቀ ሃይል ቢሰማራም ፣ በገበሬዎቹ ሊደመሰስ ችሏል። ገበሬዎቹ ቀላልና ከባድ መሳሪያዎችም በእጃቸው እንደገባም መረጃዎች ጠቁመዋል።

ህዳር 18 ታችና ምእራብ አርማጭሆ
==================
ከአገዛዙ የተገደሉ ወደ መቶ ይጠጋሉ። በታችና በመራብ አርማጭሆ ዉጊያዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል። በርካታ የመከላከያ ሰራዊት እስከነ ትጥቃቸው አገዛዙን እየከዱ የከፋኝን ጦር እየተቀላቀሉ ነው።

ኅዳር 24 – ጃኖራ/ወገራ
============
በጃኖራ በነበረው ውጊያ ዐሥራ ሁለት የሕወሃት ታጣቂዎችን ይዞ በአንድ መስመር ሲዋጋ የነበረ የወያኔ ጦር፣ ከጋንታ መሪ ውጭ ያሉት አስራ አንዱም ሲገደሉ፣ መሪው ቆስሎ በአንዱ የጎበዝ አለቃ እጅ ወድቆ ሳለ፣ የጎበዝ አለቃው ‹‹አንተን መግደል ለእኔ ቀላል ነው፤ ነገር ግን እኛ መገዳደልን አልመረጥንም፤ ብገድልህም ብተውህም ለእኔ ለውጥ የለውም፤ የምትድን ከሆነ ሒድ ታከም›› በማለት ያሰናበተው ሲሆን፣ የከፋኝ ጦር የሕወሃት አገዛዝ ግፍ ስላንገፈገፈው ከፍትህ ብሎ እየተዋዋጋ ያለ እንጅ በቂም በቀልና በጥላቻ ላይ የተመሰረተ እንዳልሆነ የጎበዝ አለቃው በተግባሩ አስመስክሯል።
በሌሎች መስመሮች የተደረጉ ዉጊያዎች የሞቱ የሕወሃት ታጣቂዎችን በተመለከተ አስተያየት የሰጡ አንድ የጎበዝ አለቃ ‹‹የወያኔ ወታደሮች አስከሬን በየቦታው ወዳድቋል፤ ከ50 በላይ የሚሆን የጠላት ጦር ዶጋ አመድ ሆኗል›› ሲል፣ ህወሃት ነገሮችን ቢሸፋፍንም ታጣቂዎችይ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰባቸው እንደሆነ ገልጿል።

ኅዳር 25 – እንቃሽ/ወገራ
=================
የሕወሃት ጦር በእንቃሽ ቆላማ ነብር ጠማጅ በተባለ አካባቢ ሒዶ፣ ከገበሬዎች ጋር ውጊያ ገጥሟል፡፡ የከፋኝ የጎበዝ አለቆችን ከሕጻን እስከ አዛውንት በመቀላቀል ተጋድሎውን እየደገፉ ሲሆን፣ የስሙ ሕግ አስከባሪ ነን የሚሉ ወያኔ ታጣቂዎች ዒላማቸውን በግለሰቦች መኖሪያ ቤትና ንብረት ላይ አድርገዋል፡፡ የገበሬዎችን አዝመራም በከባድ መሣሪያ ያወድሙም ነበር።
ሆኖም በእንቃሽ የተንቀሳቀሰው የአገዛዙ ጦር ሙሉ ለሙሉ እንደተደመሰሰ መረጃዎች እየጠቆሙ ነው። ዛሬ እኩለ ሌሊት ላይ ውጊያው በገበሬዎች ተጋድሎ ድል አድራጊነት የተደመደመ ሲሆን እስካሁን አንድም ሰው ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት አለመድረሱን ለማወቅ ተችሏል፡፡ አቶ ፈለቀ አለበል የተባለ የአካባቢው ተወላጅና የመንግሥት ታጣቂ፣ ወታደሮችን እየመራ ሂዶ እንዲመለስ በዘመድ አዝማድ ቢጠየቅም ባለመስማቱ ሊገድሉ ከሔዱ ወታደሮች ጋር አብሮ ተገድሏል፡፡

(የዘገብነው ለጊዜው መረጃ የደረሰን በነዚህ ቢታዎችን ቀናት የተደረጉ ግጭቶችን እንጅ ሁሉንም አይደለም። በጎጃም፣ና በሌሎች የተለያዩ አካባቢዎች የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እንዳሉ መታወቅ አለበት)

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.