አዳነች ዘ ወዲ ፍሰሃዬ ኦፍ ዘ ቪኦኤ! [ኄኖክ የሺጥላ]

የቪኦኤ ጋዜጠኛ ወ/ሮ አዳነች ፍሰሃዬ ዶ/ር አለምአንተ ገብረስላሴን፥ ዶ/ር ገላውዲዮስ አርዓያን እና ዶ/ር ብርሃኑ መንግስቱን ጋብዛ አነጋግራ ነበር ። ዝግጅቷን ስትጀምር ያቀረበችው የመጀመሪያ ጥያቄ ይህንን ይመስላል ። መስመሩን ለወዲ ፍሰሃዬ ልልቀቅ

ኄኖክ የሺጥላ

« እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ውስጥ ፌደራላዊ ስርዓት ከተመሰረት 25 አመት አልፈዋል እስከ አሁን ባሉ ጊዜ ደህና መስሎ ቆይቶ አሁን ግን በአንዳንድ የአማራ ክልል ቦታዎች ከወልቃይት ጋ ተያይዞ አንዳንድ ችግር እየታዩ ናቸውና እስቲ ስለዚህ ፌደራላዊ አወቃቀር ያላችሁን አመለካከት ብትነግሩን ?»
እንግዲህ ከመጀመሪያ ጥያቄዋ ስንነሳ የሚከተሉትን እምነቶቿን በጥያቄዋ ውስጥ አስርፃለች ( እስቀምጣ ነው የተነሳችው )

1ኛ በኢትዮጵያ ያለው ፌደራላዊ ስርዓት ለ 25 አመታት ደህና ስርዓት ነው ( ወይም ይመስላል)
2ኛ አሁን ይህንን ስርዓት የሚፈትን ችግር እየታየ ነው ( አሁን ነው ያለችው!)
3ኛ ይህ ችግር የሚታየው በአንዳንድ የአማራ ክልሎች ነው ( እደግመዋለሁ በአንዳንድ የአማራ ክልሎች ነው ) ብላ ካለች በኋላ ለ ታጋባዥ እንግዶቹ ጥያቄዋን ትወረውራለች ።
ሁለተኛ እና እንኳር ጥያቄዋ የሚከተለውን ይመስላል

« ወልቃይት እንደሚታወቀው በመጠኑ አይቸዋለሁ ህዝቡ የሚናገረው ትግረኛ ነው ፥ አማርኛም እንደሚናገር የታወቀ ነው ፥ ምክንያቱም ጎንደር አካባቢ ነው የነበረው ፥ ዳር ነው ያሉት ፥ የሁለቱንም ቋንቋ ይናገራሉ ፥ ግን በብዛት ትግርኛ ይናገራሉ ፥ በዚያም ላይ የቦታቸው ስም ሁሉ ትግርኛ ነው ፥ እና አሁን የሚታየው ነገር ትንሽ ግራ የሚያጋባው የወልቃይት ህዝብ እኔ እንደሚመስለኝ ፍላጎቱ ከሆነ እና አብዛኛው ህዝብ እንደዚያ ከሆነ እና ድሮ ወደነበርንበት ወደ ጎንደር አስተዳደር መግባት ነው የምንፈልገው ቢሉ መብታቸው ይመስለኛል እኔ በበኩሌ ፥ ግን አቀራረቡን ስናየው ከባድ የሚያረገው « እኛ ትግሬዎች አይደለንም ፥ እኛ አማሮች ነን » የሚለው ቃል፥ ለምሳሌ ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ የሚባሉት የዚያ የኮሚቴ አንድ ሃላፊ ናቸው እንደዚህ ፥ እሳቸው አሁን የቲፒኤልኤፍ ህወሓት ታጋይ እንደነበሩ ነው የሚነገረው አማራ ከሆኑ ለምን ከሕወሓት ጋር ታገሉ ? በማለት ትጠይቃለች ።

በዚህ ጥያቄዋ ውስጥ ፥ በመጀመሪያ የወልቃይት ህዝብ ትግርኛ ተናጋሪ ነው አማርኛም እንደሚናገር ይታወቃል ነው ያለችው ። የወልቃት ህዝብ ትግርኛ እና አማርኛ ተናጋሪ ህዝብ ነው አላለችም ። ይህንን በቀላሉ ለማስረዳት « አበበ የባህል ምግቡ እንጀራ ነው ፥ ዳቦም ግን ይበላል » እንደማለት ነው ። የወልቃይት ህዝብ ፍላጎቱ ከሆነ ጎንደሬ መሆን መብቱ ነው አካሄዱ ግን ግራ የሚያጋባ ነው ስትል ፥ በትግል ሳይሆን በምርጫ ነበር መሆን ያለበት ለማለት ፈልጋ ነው ። ይህንንም ሃሳብ ለማንፀባረቅ የፈለገችበት አብይ ምክንያቷ ፥ በአሁኑ ሰዓት ወልቃይት ጠገዴ በሚባለው ቦታ ላይ ከነባሩ የወልቃይት ህዝብ ይልቅ ከትግራ በመጡ የራሷ ዘመዶች አካባቢው የተያዘ ስለሆነ ፥ ምርጫ ቢደረግ ( ማንም እንዳለው ) ድሉ የትግሬ እንደሚሆን ስለገመተች ነው ።

በዚሁ ጥያቄዋ ውስጥ ኮ/ል ደመቀ የሚባሉት የዚያ ኮሚቴ ሃላፊ ነኝ ይላሉ ፥ ግን ደሞ የህወሓት ታጋይ የነበሩ ሰው ናቸው ታዲያ ጎንደሬ ከሆኑ እንዴት ለህውሃት ታገሉ ትለናለች ። የሷ ጥያቄ ለኔ ሌላ ጥያቄ አጫረብኝ ፥ ባንቺ አስተሳሰብ ኮ/ል ደመቀን ትግሬ የሚያደርገው ለህውሓት መታገሉ ነው እንበል ። ታዲያ ጥያቄን በጥያቄ ስንመልስ ፥ በረከት ስምዖን ከበአዴን ጋ የታገለው አማራ ስለነበር ነውን ? ኢሳያስ አፈወርቂ ከኤርትራ ጎን ቆሞ የታገለው ኤርትራዊ ስለሆነ ነውን ? አባዱላ ገመዳ ( በትክክለኛ ስሙ ምናሴ ኤፍሬም) የኦህዴድ ጋ የታገለው ኦሮሞ ስለሆነ ነውን ? እነ ህላዊ ዮሴፍ እና ሌላም ብዙ ጠቅሰን እና ዘርዝረን የማንጨርሳቸው ታጋዮች ፥ እራሱ መለስ ዜናዊን ጨምሮ የታገሉት የታገሉለትን ህዝብ በደም 100% ስለሚወክሉ ነውን ?
ሌላኛው ጥያቄዋ ደሞ ይህንን ይመስላል

« አሁን እንደምንመለከተው ኮሚቴው ጎንደር ሄዶ ነው የሚንቀሳቀሰው ፥ መሃል ወልቃይት አይደለም ፥ የወልቃይት ህዝብ ደሞ እነሱን ተከትሎ ወደ ጎንደር ሲሄድ አላየንም ፥ ይህንን ሁሉ እንግዲህ ምን ያህል እንደሆነ መለየት ያለብን ይመስለኛል ፥ ምን ያህል ህዝብ ነው እንደዚያ መሆን የሚፈልገው ወይስ የተወሰኑ ናቸው ? » በማለት ትጠይቃለች
እንግዲህ ከዚህኛው ጥያቄ ደሞ የምንረዳው የወልቃይትን ጥይቄ የያዙት የወልቃይት ወክሎች የወልቃይትን ህዝብ አስከትለው እየተንቀሳቀሱ አይደለም ፥ ጉዳዩም መሃል ጎንደር ላይ እንጂ ወልቃይት ላይ እየታየ አይደለም ይህም የጥቂቶች ሃሳብ እንጂ የወልቃይት ህዝብ ሃሳብ አይመስለኝም ፥ የሚል እንድምታን ለማስተላለፍ ነው የሞከረችው ብዬ ለማለት እደፍራለሁ።
እስኪ ልጠይቅሽ
ሃይሌ ገብረስላሴ ኢትዮጵያን ወክሎ በኦሎምፒክ ሲሮጥ ፥ የኢትዮጵያን ህዝብ ውክልና ስለማግኘቱ ለማረጋገጥ 97 ሚሊዮን ህዝብ አብሮት አቴንስ መሄድ ነበረበት ማለት ነው ? ውክልና ማለት በመጀመሪያ ምን ማለት ነው ?
የወልቃይት ህዝብ ጉዳዩን ጎንደር ሄዶ እንዲመለከት የሆነበት ፥ ጉዳዩን በወልቃይት እንዲህ ያለውን የህግ ጉዳይ ሊያይ የሚችል የፍርድ ቤት አካል ስለሌለ ነው ። የማታውቂ ከሆነ ልንገርሽ እንደውም ••• የነ ኮ/ል ደመቀን የህግ ጉዳይ ወያኔ ትግራይ ነው መታየት ያለበት ሲል ምክንያቱ እኮ የትግራይ አካሎች ናቸውና ትግራይ ይምጡልን ማለት ነበር ። እነርሱ ደሞ እኛ የትግራይ አካል አይደለንም ፥ አማሮች ነን በክልላችን እንዳኛለን ነው ። ይህ ጠፍቶሽ እንዳልጠየቅሽ ቢገባኝም ፥ አካሄድሽ ለህዝቡ እንዲገባው እና ለማስረዳት ስለምሻ ነው ።
እስኪ አሁንም ለወዲ ፍሰሃዬ መስመሩን ልልቀቅ
« ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚታወቀው ከሰማኒያ በላይ ብሄር ብሄረሰቦች እንዳሉ ነው የሚያወቀው ፥ አሁን ግን ምንድን ነው እየተባለ ያለው በተለይ በተቃዋሚዎች የሚሰማው ነገር ፥ አማሮች እና ኦሮሞዎች አብረው መስራት አለባቸው ይባለል ፥ ከዚህ ሁሉ ተመርጠው ፥ ከዚህ ሁሉ ተመርጠው አማሮች እና ኦሮሞዎች የሚሰሩበት ምክንያት ምንድን ነው፥ ለፖለቲካ ፍጆታ ነው ወይስ ታምኖበት ነው ?» ትላለች ። መቼም ለምንጠየቅሽ አይባልም ፥ ግን ወይዘሮ አዳነች ለምን ይመስልሻል አብረው ይስሩ የሚባለው ?
ዶ/ር አለምዓንተ የትግሬው ኮሙኒቲ በጎንደር የትግራይ ቤቶች ተቃጠሉ ሲባል አብዛኛው የትግራይ ህዝብ ተቆጥቷል ፥ ታዲያ ይህ ከሆነ ትግሬዎች ለምን ለሌላው ዘር አልጮኹም ብለው ወ/ሮ አዳነችን ይጠይቃሉ ። አዳነች እንዴ ሌሎቹ ኢትዮጵያዊያኖች የትግሬዎች ቤት ጎንደር ሲቃጠል ለምን ብለው ተቆጥተዋል ወይ ትላልቸ። እውነቱ ግን ጎንደር ውስጥ ከተቃጠሉት 17 ቤቶች ውስጥ 13ቱ የአማራ ቤቶች መሆናቸውን ምን ያህል እናውቅ ይሆን ?
አሁንም ለወዲ ፍሰሃዬ መስመሩን ልስጥ
« አንድ ግን እዚህ ላይ ይሄ ወያኔ ነው የሚገዛው የሚባለው ፥ በመጀመሪያ የህውሓት የበላይነት ወይም መሪነት እንደነበረ ምንም የሚያጠራጥር ነገር አይደለም ፥ አሁን ግን ቀስ በቀስ ሁኔታውን ስናየው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወላይታ ናቸው ፥ መከላከያ ሚኒስትሩ ኦሮሞ ናቸው ፥ ሁለት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮች አንዱ የትግራይ አንዱ የአማራ ነው ፥ ‘ኢሄን ነገር እንዴት ነው የምናየው? »
ይህንን ጥያቄ እንዲህ እንመልሰው
የመከላከያ ሚኒስትሩ ኦሮሞ ነው ፥ ከስሩ ስንት ኦሮሞ ጀነራሎች ፥ ስንት ኦሮሞ ኮ/ሎች እና ንዑስ አዛዦች አሉ ? ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወላይታ ነው ፥ ከሃይለማሪያም ሌላ በሃይለማሪያም ካቢኔ ውስጥ አንድ ሌላ ወላይታ አለ ወይ ? ሁለት ጠቅላይ ሚኒስትር ለምን አስፈለገ ብለን ሳንል ፥ የደመቀ እና የደብረፂዮንን ሚና የሚተካ አቅም ያለው አንድ ኢትዮጵያዊ ጠፍቶ ነው ወይ? ( ከየትም ብሄር ይምጣ!)
ባጭሩ ሲደመደም ፥ እነ አዲሱ ጥሩ ስራ እየሰሩ ባሉበት በአሁኑ ሰዓት ፥ እንዲህ የዘሬን ቢተው ያንዘርዝረኝ የሚሉ ጋዜጠኞችን አቅፎ በመያዙ ቪኦኤ ቪኦኤ ካገገመብት ኢ ተአማኒነት ተመልሶ ባፍጢሙ ሊደፋ ያሰበ ይመስላል ።
የድርጅቱ ሰራተኞች ፥ እንዲህ ያለውን እና በግልፅ የሚታይን አይን ያወጣ ወገኝተኝነት ሊቃወሙ ግድ ይላል ! አሁንም የምንፈልገው ነፃ ጋዜጠኞችን ነው !

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.