ሁሉም ታሪክ በየፈርጁ ይታወሳል (ከይገርማል)

ታሪክ ማለት በአንድ ወቅት ግለሰቦች: ሕዝቦች: ሀገሮች: – – – የነበራቸው: ያደረጉትና ያሳለፉት እውነተኛ ሕይወት ማለት ነው:: በታሪክ ውስጥ ብዙ ጥሩና መጥፎ: ጎጅና ጠቃሚ የሆኑ ድርጊቶች ይታወሳሉ:: ያም ሆኖ ታሪክ በራሱ መጥፎ ወይም ጥሩ ሆኖ አያውቅም:: የታሪክ ድርሻ የተፈጸሙ ድርጊቶችን እንደሁኔታቸውና እንዳፈጻጸማቸው መመዝገብ ነው::
ታሪክን አዛብተው የሚጽፉ ሰዎች በሁሉም ነገር ላይ ጥፋት የፈጸሙ የመጨረሻወቹ መጥፎወቹ ናቸው:: እንዲህ አይነት ሰዎች በባለፈው ላይ በደል የፈጸሙ ብቻ አይደሉም:: ይልቁንም ባስቀመጡት የሀሰት ሰነድ ሕዝብን በማሳሳት ከትውልድ ወደትውልድ ለሚሸጋገር ማቆሚያ ለሌለው ጥፋት የሚዳርጉ የዝንታለም ሀጢያተኞች ናቸው:: በህይወት እያሉ በሕግ: ከሞት በኋላ ደግሞ በታሪክ ሊጠየቁ የሚገባቸው የሁልጊዜ ወንጀለኞች ናቸው::
እውነተኛ ታሪክ ያለፈውን ጊዜ በሀሳብ ወደኋላ ተጉዘን እንድናይ የሚረዳና ከተጓዝንበት ስንመለስ ደግሞ የወደፊቱን ለመቀየስ ትምህርት የምንወስድበት ሆኖ ያገለግላል:: ታሪኩን የማያውቅ ሰው መነሻውን የሳተ ነው:: መነሻ የሌለው ነገር ደግሞ መድረሻው ይቸግረዋል:: በታሪክ ውስጥ ሁሉም በየፈርጁ ይታወሳል::
አድማሱ ያፈረሰው ጊዜ
ለመንግሥት አልገዛም ብሎ ሸፈተ ብለው ንጉስ ኃ/ሥላሴ የንግሥት ዘውዲቱን ባለቤት ራስ ጉግሳን ከንግስቲቱ ፍላጎትና እውቅና ውጪ ጦር አስልከው በማስገደላቸው ንግስቲቱ በከባድ ሀዘን ወድቀው ብዙም ሳይቆዩ ታመው ስለሞቱ (በንጉሱ ትዕዛዝ አነር በሚባል ሀኪም ተገድለው ነውም ይባላል:: ለዚያም ነው ሕዝቡ ‘አይወዱም ነበረ ድመት በቤታቸው ንግሥት ዘውዲቱን አነር ገደላቸው’ የተባለው::) ንጉሥ ኃ/ሥላሴ በአጼነት ንጉሠ-ነገሥት ዘኢትዮጵያ ተብለው ነገሱ::
ከአያታቸው ከአጼ ሚኒሊክ በአዋጅ የተረከቡትን ስልጣን ለማስመለስ እና አባታቸው ንጉስ ሚካኤል በሰገሌ ጦርነት የደረሰባቸውን ሽንፈት ለመበቀል በወሎና በትግራይ አካባቢ ጦር ሲያደራጁ የነበሩት ልጅ እያሱ በትግራዩ ገዥ ተይዘው ወደአዲስ አበባ ተልከው ከታሰሩ በኋላ አጼውን የሚፎካከር ሌላ የስልጣን ባላንጣ አልነበረም::
የጎጃሙ ገዥ የራስ ኃይሉ ተ/ሐይማኖት ልጅ ወ/ሮ ሰብለወንጌል የልጅ እያሱ ባለቤት ስለነበሩ የልጅ ኢያሱ ከስልጣን ወርዶ ለእስር መዳረግ የጎጃምን ግማሽ መንግስት ከማሳጣቱም በላይ ውርደት እንደሆነ ታምኖ ስለነበር ያ ጊዜ ጎጃሞች በእጅጉ የተከፉበት ጊዜ ነበር:: ልጅ ኢያሱ ፍቼ መታሰራቸውን የሰሙት ሰብለወንጌል
“የበላሁት ሥጋ ሆዴን አመመው:
ኧረ እንዴት አድርጌ ተፍቼ ላውጣው”
ብለው ብሶታቸውን በግጥም እንደገለጹ ይነገራል::

የጎጃሞችን የጥቃት እንጉርጉሮ የተረዱት ኃ/ሥላሴ ‘ይህን እያደገ በመምጣት ላይ ያለውን የሕዝብ ስሜት ለማብረድ መሪውን መጨበጥ መፍትሄ ይሆናል’ ከሚል ድምዳሜ በመድረስ ራስ ኃይሉን አታለው በመያዝ የጎጃሞችን እንቅስቃሴ ለማዳፈን መላ መቱ:: ይህን ዕቅዳቸውን በሆዳቸው የያዙት ንጉሰ-ነገሥት ራስ ኃይሉን ለስብሰባ አስመስለው በወዳጅነት ጠርተው አዲስአበባ እንዲመጡ ካስደረጉ በኋላ “ከጣሊያን ጋር በመተባበር ልጅ እያሱን ከእስር ቤት ለማስመለጥ ዶልተሀል” በማለት ወንጅለው በፍርድ ቤት ተከሰው በክርክር ሳይረቱ በራሳቸው ትዕዛዝ ከአዲስ አበባ እንዳይወጡ ከልክለው የቁም እስረኛ አድርገው ሲያበቁ በግዛታቸው ጎጃም ራስ እምሩ ኃ/ሥላሴን የጠ/ግዛቱ እንደራሴ አድርገው ሾሙ::
የእኔ አይደለም በሚሉት ሰው መተዳደር ያልለመዱት ጎጃሞች በራስ ኃይሉ ልጅ በሆኑት አድማሱ ኃይሉ በመመራት በ1925 ዓ.ም አመጽ አስነስተው ግምጃቤቱ በሙሉ ተዘረፈ:: ባዕድ ከሚወስደው አንተ ብላው የተባለው ሀገሬው ተዝቆ የማያልቀውን የራስ ኃይሉን ወርቅና ገንዘብ ለመዝረፍ በፈጸመው ተግባር ጉዳት ተከስቷል:: ባልተደራጀ መልኩ የሚደረገው ዘረፋ መጠላለፍን የፈጠረ ስለነበር የተጎጅው መጠን በጣም ብዙ ነበር:: አንዳንዱ ከመንገድ አድፍጦ ሌላው ደክሞ ያመጣውን ገድሎ የሚቀማበት: ብዙ ህይወት የጠፋበት እና ንብረት የወደመበት ያ ጊዜ “አድማሱ ያፈረሰው ጊዜ” በመባል ይታወቃል::
የጋሌ ጊዜ
ጣሊያን ኢትዮጵያን ስትወር ጤናና ዕድሜ ጉልበቱንና ብርሀኑን ያልከዱት ጐጃሜ ማንም ሳያስገድደው ነበር እየሸለለ በፊታውራሪወችና በደጃዝማቾች ስር ተሰባስቦ በራስ እምሩ አዝማችነት በጎንደር አድርጎ ወደሽሬ ያመራው:: ጦሩ ጎንደር ላይ እረፍት ባደረገበት ጊዜ በራስ ኃይሉ የቁም እስረኛ መሆን እና የጎጃም በራስ እምሩ አስተዳደር ስር መዋል የተቆጩት ደጃዝማች በለው “የጎጃምን ሱሪ የማስመልሰው አሁን ነው” ብለው አዘናግተው ጥቂት ወታደሮቻቸውን አስከትለው ሾልከው ወደጎጃም መመለሳቸው ታወቀ:: ይሁንና የማይቀሩበት ትልቁ ቀጠሮ ከጣሊያን ጋር የሚደረገው ጊዜ የማይሰጠው ጦርነት በመሆኑ የደጃዝማች በለውን ወደኋላ መመለስ በተመለከተ ለበላይ እንዲገለጽ ተደርጎ ወደትግራይ የሚደረገው ጉዞ ቀጠለ::
ንጉሠ-ነገሥት ኃ/ስላሴ ዋናውን ጦር መርተው ወደ ማይጨው ዘምተው ስለነበር ደጃዝማች በለውን እንዲቀጣ የመንግስት ኃይል እንዲላክ የተደረገው ሀገሩን እንዲያረጋጉ አዲስአበባ ከቀሩት ራሶች እና ከእቴጌ መነን ነበር:: ያ ከማእከላዊው መንግሥት የተላከው መቺ ኃይል ሙሉ በሙሉ የኦሮሞ ጦር ነበር::
ደጃች በለው የአካባቢውን ሕዝብ ጠርተው የመቃ ላይ ግብር እያበሉ ሳለ ሳይታሰብ የደረሰው የኦሮሞ ጦር በሰላማዊ ኗሪው ላይ ሳይቀር እጅግ ዘግናኝ ግፍ መፈጸሙን የሚመሰክሩ አሁንም በህይወት ያሉ የእድሜ ባለጸጋ እናት አባቶች አሉ:: በወቅቱ ዘመናዊ ይባል የነበረውን የጦር መሳሪያ የያዘው ከማእከላዊ መንግሥት የተላከው የኦሮሞ ጦር ሳይታሰብ በድንገት ደርሶ ከግማሽ በላይ ምንም ትጥቅ ያልነበረውን ጀሌ ወታደርና ግብር ለመብላት የታደመውን ሰላማዊ ዜጋ በጥይት ረፍርፏል:: ይባስ ብሎ ለሌላው መቀጣጫ ይሆናል በማለት ከቀበሌ ቀበሌ: ከወረዳ ወረዳ እየተዘዋወረ በቤት ለቤት አሰሳ የተገኘውን ሁሉ ሴት ወንድ: ትንሽ ትልቅ ሳይል ፈጅቷል:: በሽሬ ግምባር ተሰልፎ ከሰማይ የመርዝ ጋዝ እየፈሰሰበት: ከምድር የመድፍና የመትረጌስ ጥይት እየተርከፈከፈበት ያለው የጎጃም አርበኛ ልጆቹና አቅመደካማ ወላጆቹ በወገን ሰራዊት እየረገፉ እንደሆነ የሚያውቅበት መንገድ አልነበረውም::
የጎጃም አርበኛ የጠላትን ምሽግ እየደረማመሰ ወደፊት ይገሰግስ በነበረበት ወቅት በማይጨው ግምባር ተሰልፎ የነበረው በንጉሱ የሚመራው ዋናው ሰራዊት ተበታትኖ ንጉሱ የስደት ጉዟቸውን እያመቻቹ እንደሆነ በመሰማቱ “ጦርነቱ አለቀ” ተብሎ በሽሬ ግምባር ተሰልፎ ይዋጋ የነበረው የጎጃም አርበኛ በውጊያ አስለቅቆ የያዘውን መሬት ትቶ ወደኋላ እንዲመለስ ታዘዘ (“ትዝታየ” የሚለውን የአቶ ሀዲስ ዓለማየሁን መጽሀፍ ለዋቢነት ያንብቡ):: በጦርሜዳ ያጣቸው የትግል ጓዶቹ ሀዘን ያልወጣለት አርበኛ ወደየቀዬው ተመልሶ በቤተሰቦቹ የደረሰውን ግፍ ሲያይ ሊሰማው የሚችለውን ስሜት መገመት እጅግ ይከብዳል::
ጎጃምን እንዲቀጣ በተላከው የኦሮሞ ጦር የተፈጸመው ገደብ የለሽ ጭፍጨፋ የተገታው ባልተደራጀ መልኩ ሁሉም በያገኘው አጋጣሚ በወሰደው የአጸፋ እርምጃ ነበር:: ሮጠው የማያመልጡት ተለማምጠው የማይድኑት ቢሆን በአልሞት ባይ ተጋዳይ ሴቱም ወንዱም ከእጁ በገባው ነገር ሁሉ ተከላክሎ መልሶ በማጥቃት የመንግስቱን ጦር ለወሬ ነጋሪ አንድ እንኳ ሳያስተርፍ ከዚያው አስቀርቶታል:: ያ የእልቂት ዘመን “የጋሌ ጊዜ” በመባል የሚታወቅ ሲሆን ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ የሚጠሩ የቦታ ስሞች አሁን ድረስ አሉ:: በደጃዝማች በለው ርምጃ የተበሳጩትና ጎጃምን አይቀጡ ቅጣት ቀጥቶ እንዲመለስ በተላከው የኦሮሞ ጦር መደምሰስ ያዘኑት እቴጌ መነን እና ራሶች “ጎጃምና ተልባ እያደረ ሸርተት ይላል”: ማለትም ጎጃም እንደተልባ ስፍር እያደረ ይጎድላል: ባስቀመጡበት አይገኝም በማለት ሽሬ ላይ ከንጉሱ ዘመናዊ ሰራዊት በእጅጉ የበለጠ ገድል የፈጸመውን አርበኛ የሚያረክስ: ተግባሩን የማይገልጥ ስም አውጥተው ሰድበው ለሰዳቢ ሰጡት::
በዚህ አልበቃ ብሎ በመማሪያ መጻህፍት ውስጥ ጎጃሞች ዕምነት የማይጣልባቸው እንደሆኑ ተደርጎ እንዲታወስ ተጽፎ ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ ቆይቷል:: በኮሌጅ የእንግሊዝኛ መጽሀፍ ውስጥ ዕውነት ያልሆኑ አነጋገሮችን (fallacy) ለማስተማር እንደምሳሌ ከተጠቀሱት መሀል አንዱ ይኸው የጎጃሞች አለመታመን ጉዳይ ነበር::
ታሪክ ሁሉ ትዝ ላይል ይችላል: ትዝ የሚል ነገር ሁሉ ግን ታሪክ ነው:: አዎ ትዝታ ታሪክ ነው:: ስህተት የሆኑ አባባሎች ናቸው ተብለው በምሳሌነት የቀረቡትን ሁለት አረፍተነገሮች እስቲ እንመልከት::
All Gurages are hard working!
All Gojames are dishonest!
እኒህ ሁለቱ የfallacy ምሳሌወች የኮተቤ መምህራን ት/ኮሌጅ የእንግሊዝኛ መምህር የነበረውን እቁባዝጊ በኮሌጁ ይማሩ ከነበሩት የጎጃም ልጆች ጋር አላትመውታል:: ማንም ሊገነዘበው እንደሚችለው All Gurages are hard working! የሚለው አባባል ሀሰት ቢሆንም ቀና (positive) ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል:: ሁሉም የጉራጌ ሕዝብ ጠንካራ ሰራተኛ ነው ብሎ መውሰድ የማያስሄድ አባባል ነው:: በጤናም ይሁን በፍላጎት ማጣት ወይም በሌላ በሆነ ምክንያት ከብዙሀኑ (norm) ያፈነገጡ ሰዎች መኖር የሚጠበቅ ነው:: ስለዚህ All Gurages are hard working! የሚለው ምሳሌ በምንም ይሁን በምን ጠንካራ ያልሆኑ ጥቂቶች ሊኖሩ ቢችሉም ብዙሀኑ ግን ጠንካራ ሰራተኛ ነው የሚል መልዕክት የሚሰጥ አገላለጽ ያለው በመሆኑ ብዙሀኑን አወዳሽ ነው:: የሁለተኛው ምሳሌ ብዙሀኑን የሚያወድስ ሳይሆን የሚሰድብ ነቃፊ (negative) አቀራረብ ነው:: All Gojames are dishonest! የሚለው አባባል ሀሰት ነው ብሎ በምሳሌነት ማቅረብ ጥቂቶች ታማኞች አይጠፉም የሚለውን መልዕክት የሚያስተላልፍ ነው:: መምህር እቁባዝጊ በfallacy አስተምህሮ ሁለቱም ውሸት ናቸው ብሎ ሊከራከር ሞክሮ የነበረ ሲሆን የኮሌጁን የጎጃም ተማሪወች ወክለው የተገኘኙትን ሊያሳምን ባለመቻሉ ማምለጥ የቻለው ምሳሌወችን የወሰዳቸው ከመማሪያ መጽሀፍ መሆኑን አስረድቶ መማሪያ መጽሀፉን በማሳየቱ ነበር:: ያም ሆኖ “ብታምንበት ይሆናል እንጅ እንደዚህ አይነት ህዝብ-አዋራጅ ምሳሌ መጽሀፍ ላይ ስለተጻፈ ብቻ አታቀርብም ነበር” ተብሎ ተወቅሶ “ሁለተኛ አይለምደኝም ብሎ ሂሱን አምኖ ተቀብሏል:: ከዚያ በኋላ ስለሆነው የመጽሀፉ ሁኔታ የሚያውቅ ይኖር ይሆን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.