የ ዶ/ር መረራ እስር – ኤልያስ አህመድ

ዶ/ር መረራ

መረራ ገና በልጅነቱ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለ ነበር የኢትዮጲያ ተማሪዎች ትግልን የተቀላቀለዉ፡፡ በአከባቢዉ የሚመለከተዉ ፍትህ አልባነት፤ ጭቆናና በተለይም በአርሶ አደሩ ላይ የሚፈፀመዉ ግፍ ወደ ትግሉ ጎራ እንዲቀላቀል አድርጎታል፡፡ ብዙዎች የጀመሩትን ትግል እስከወዲያኛዉ ሲቀጥሉበት ባይታይም ቆፍጣናዉ መረራ ግን ዛሬም ከ 50 ዐመታት በኋላም ከፊት ለፊት በመሆን ትግሉን እየመራ ይገኛል፡፡ ቢሆንም ግን ትግሉን ባለፈባቸዉ ሁሉም ስረዓቶች እንግልት አልተለዩትም፡፡ በሶስቱም ስርአቶች እስር ቤቶችን ጎብኝቷል፤ ተሰቃይቷል፡ ተንገላቷል፡፡ ዛሬም ቢሆን ይህ ጀግና እስር ቤት ነዉ ያለዉ፡፡ እስቲ ወደ ኋላ መለስ ብለን የእስር ታሪኩን እንመልከት፡፡

የመጀመሪያዉ አጋጣሚ ገና የ12ኛ ክፍል ተማሪ እያለ ትምህርቱን በሚከታተልበት አምቦ ከተማ ነበር የተከሰተዉ፡፡ በወቅቱ የነበረዉን የአፄዉን አገዛዝ በመቃወም የአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና የአለማያ እርሻ ኮሌጅ ተማሪዎች ሰፊ የተማሪዎች ንቅናቄ የሚያደርጉበት ወቀት እንደመሆኑ ይህ የተማሪዎች ንቅናቄ በየክልሉ ባሉ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶችም ይስተዋል ነበር፡፡ ከነዚህ ት/ቤቶች አንደኛዉ መረራ ይማርበት የነበረዉ አምቦ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ነበር፡፡ በወቅቱም በ ት/ቤቱ የአምቦ ተማሪዎች ንቅናቄ ይካሄድበት ነበር፡፡ ታዲያ መረራም በጊዜዉ የነበረዉ የአፄዉ ስርዓት ከኢትዮጲያ ህዝቦች ጫንቃ እስካልተወገደ ድረስ ከጨለማዉ ዘመን ልንወጣ አንችልም ብሎ ያስባል፡፡ ወጣቱ መረራ በዚያ ስርዓት እኩልነትም ሆነ ፍትህ ሊኖር እነደማይችል ከተገነዘበ በኋላ የኢትዮጲያ ተማሪዎች ንቅናቄን መጀመሪያ ወደማክበሩ ከዚያም ከልብ ወደመሳተፉ ገባ፡፡ በኋላ በአመራር ደረጃ ድረስ በሰፊዉ ለተማሪዉ ንቅናቄ የራሱን አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡ በዚህም ወቀት ነዉ መረራ የመጀመሪያ እስሩን የተጋፈጠዉ፡፡ አጋጣሚዉ እንዲህ ነበር:: ለ ሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና እየተዘጋጁ ባሉበት ሰሞን በት/ቤታቸዉ አንድ የሚያናድድ ነገር ይሰማሉ፡፡ በአርበኝነቱ ስለሚመካ ለንጉሱም አየታዘዝም የሚባልለት ራስ መስፍን ስለሺ ለንፁኅ የመጠጥ ዉሃ ማስገቢያ ተብሎ ከአምቦ ህዝብ በተሰበሰበሰ ገንዘብ ለሚያከራዩት ቤቶች ከፍልዉሀ ቧንባ መዘርጋታቸዉ ነበር፡፡

ተማሪዉም በመተባበር አንድ ዉሳኔ ከወሰነ በኋላ የፅዳት ዘመቻ ስለምናደርግ ብለዉ በነጋታዉ ሁሉም የቻለዉን አካፋና ዶማ ይዞ እንዲመጣ አደረጉ፡፡ ተማሪዉንም ለ ሁለት ከፍለዉ አሰማሩ፡፡ ዶማና አካፋ የያዙትን ወደ ራስ መስፍኑ የፈረንጅ መኖሪያ ቤታቸዉ የተዘረጋ የዉሃ ቧንባ ቆፍሮ እንዲያወጡ አሰማሩ፡፡ የተቀረዉን ተማሪ ፖሊስ ጣቢያና በህዝብ ሀብት የገባዉን ቧንባ የዘረጋዉን ማዘጋጃ ቤት እንዲይዝ አደረጉ፡፡የማዘጋጃ ቤቱ ሹም ሸሽቶ ሲያመልጣቸዉ፤ ዘዉዴ ዘለቀ የሚባል ግዙፍ ተማሪ ከብዙ ተማሪዎች ጋር ተጋግዞ ትልቅ ድንጋይ በማዘጋጃ ቤቱ ሹም መቀመጫ ላይ አኖረ፡፡ ስራዉ በፍጥነት እንደተጠናቀቀ ወሬዉ ተሰማ ራስ መስፍን ከ አ/አ የፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ ይዞ በመምጣት የአምቦ ከተማን አስወረረ፡፡ የተማሪ መሪዎች ታድነዉ እንዲያዙ ጥብቅ ትዕዛዝ ተሰጠ፡፡

በዋናናት ጉዳዩን ያስተባበረዉ ሳሙኤል ብርሃኑና በማዘጋጃ ቤቱ መቀመጫ ላይ ድንጋይ በማኖሩ ልዩ ሚና የተጫወተዉ ዘዉዴ ተይዘዉ ታሰሩ፡፡ በመቀጠልም የመረራ ሚና የታሰሩትን ልጆች ለማስፈታት ተማሪዎችን ማስተባበር ሆነ፡፡ በእነሱ የቀጠሮ ቀን ተማሪዎችን ወደ አዉራጃዉ ፍርድቤት በመምራት ላይ እንዳለ መረራም ተይዞ ታሠረ፡፡ ይህ የዘመናት ታጋይ የመጀመሪያዉን እስር አስቂኝ በሆነ አጋጣሚ ሳያድርና ክስ ሳይመሠረትበት እንዴት ተፈታ? ቀጣዩ እስርስ መች ሆነ?
ይቀጥላል

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.