የሰንደቅ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ተሻሽሎ በቀረበበት ክሥ: ፓትርያርኩን በምስክርነት ጠራ

ሐራ ዘተዋሕዶ

የሰንደቅ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ፣ ተከሣሽ ጋዜጠኛ ፍሬው አበበ

“ሙስና እና ስውር የኑፋቄ እንቅስቃሴ የታመነበት የቤተ ክህነቱ ችግር ነው”
“ጽሑፉ፣ ገንቢ ሒስ ወይም ትችት እንጂ የስም ማጥፋት ተግባር አይደለም”
የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቱን፣ የመልስ መልስ ለመስማት ለነገ ተቀጥሯል
የሳምንታዊ ሰንደቅ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ተሻሽሎ በቀረበበት የስም ማጥፋት ክሥ ጉዳይ፣ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስን በምስክርነት ቆጠረ፡፡

ጋዜጣው መጋቢት 21 ቀን 2008 ዓ.ም. ያተመው የዲያቆን ዳንኤል ክብረት ጽሑፍ፣ “የፓትርያርክ አቡነ ማትያስን ስም ያጠፋ ነው” በሚል በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ለቀረበው ክሥ፣ ችሎቱ፡- “ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ፓትርያርኩን ወክሎ የስም ማጥፋት ክሥ ማቅረብ አይችልም” በሚል ክሡ ተሻሽሎ እንዲቀርብ በሰጠው ብይን መሠረት፣ ከሣሽ አሻሽሎ ለአቀረበው ክሥ፣ ተከሣሽ፥ ባለፈው ሰኞ ታኅሣሥ 3 ቀን ለዋለው የፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቂርቆስ ምድብ 2ኛ ፍትሐ ብሔር ችሎትየመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ እና መልስ የሰጠ ሲኾን፤ እንደ መልስ አቀራረቡ እንዲያስረዱለት ከቆጠራቸው አራት ምስክሮች መካከል ፓትርያርኩ እንደሚገኙበት ታውቋል፡፡

ተከሣሹ በማስረጃነት ካቀረባቸው ሰነዶችም ውስጥ፤ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ከላይ እስከ ታች ባለው መዋቅር፥ ሙስና፣ ብልሹ አሠራር፣ የመልካም አስተዳደር ችግር ስለመኖሩ ፓትርያርኩ በተደጋጋሚ ያሰሟቸው ቃለ ምዕዳኖች፤ አማሳኞችና የተሐድሶ መናፍቃን በቤተ ክርስቲያኒቱ ህልውና እና አገልግሎት ላይ የጋረጡትን አደጋ ለመቋቋምና ለማስወገድ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ያወጣቸው መግለጫዎች በአስረጅነት መካተታቸው ተመልክቷል፡፡

ቤተ ክህነቱ÷ በመናፍቃን ስውር እንቅስቃሴ ችግር ውስጥ ስለ መግባቱም ኾነ በአማሳኞች ተዘረፈ ስለ መባሉ፤ የቤተ ክህነቱ መሪዎችና አስተዳደሮች በተደጋጋሚ መግለጫ የሰጡበትና በሰነድ ማስረጃ ጭምር የተደገፈ መኾኑን ተከሣሹ አብራርቶ፤ በጋዜጣውም ላይ፥ ከችግሮቹ ስፋትና ጥልቀት አንፃር አስቸኳይ መፍትሔ አልተሰጠም፤ መባሉ ገንቢ ሒስ እንጂ የስም ማጥፋት ተግባር ባለመኾኑ ክሡ ሊሰረዝ የሚገባው ነው፤ ሲል ተከራክሯል፡፡

አያይዞም፣ “ይህ በግልጽ የታወቀ፣ ቤተ ክህነቱ አምኖ የተቀበለውና ለማሻሻልም በየጊዜው ቃል የሚገባበትን እውነታ በማስረጃ በተደገፈ መልኩ በሰንደቅ ጋዜጣ ላይ ቢጻፍና ቢታወቅ፤ ጋዜጣው በማስረጃ ተደግፎ፣ ሚዛናዊነቱን ጠብቆ የሠራው መደበኛ ሥራው በመኾኑ የሚወደስ እንጂ በጥፋት ተቆጥሮ ስም አጥፍቷል ሊባል የሚገባው ባለመኾኑ ክሡ ውድቅ ሊደረግ ይገባል፤” ሲል ጠይቋል፡፡

ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ አሻሽሎ ባቀረበው ክሥ፣ በቀደመው ክሥ ያልተካተቱ አዳዲስ ፍሬ ነገሮች መጨመራቸው፣ የክሥ ማሻሻል መሠረታዊ ዓላማን ያላገናዘበና ሥነ ሥርዓታዊ አለመኾኑን ዋና አዘጋጁ በመቃወሚያው ጠቅሷል፤ በአቀራረቡም፣ የፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕጉ የሚጠየቀውን ፎርም(ለፍርድ ቤት የሚቀርብ ክሥ የሚኖረውን ቅርፅና ይዘት) ሳይከተልና ቅድመ ኹኔታዎቹን ሳይጠቅስ እንደ ተራ ደብዳቤ ተጽፎ መቅረቡን በመተቸት ውድቅ እንዲደረግለት አመልክቷል፡፡

ተከሣሽ በሰጠው የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያና መልስ ላይ፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን የመልስ መልስ ለመስማት፣ ችሎቱ፣ ለነገ፣ ታኅሣሥ 10 ቀን 2009 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን(ፍትሕ መንፈሳዊ)፣ ካህን በፍርድ ቤት ለምስክርነት አይጠራም፡፡ በሥጋዊ ነገር ዋስ፣ ተያዥ፣ ምስክር አይኾንም፡፡ ይህም በምሥጢረ ንስሐ፣ የተነሳሒውን ንስሐ(በወንጀል የሚያስጠይቅ ቢኾን እንኳን) በምሥጢር እንዲይዙ ካለባቸው ክህነታዊ ግዴታ ጋር የተያያዘ እንጂ፣ እንደ ግለሰብ፣ በሌሎች አስተዳደራዊ ጉዳዮች ሊኖር የሚችልን የሕግ ተጠያቂነት እንደማይመለከት ተጠቁሟል፡፡

“ፓትርያርኩ ለኢትዮጵያ የደኅንነት፣ ለምእመናን የድህነት ስጋት” በሚል ርእስ የቀረበውና ለክሡ ምክንያት የኾነው የዲያቆን ዳንኤል ክብረት ጽሑፍ፤ ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ይልቅ ፓትርያርኩን እንደ ግለሰብ በመጥቀስ ሓላፊነታቸውን ያለመወጣታቸውን የሚተችና ችግሩ እንዲፈታ፡- “መድረክ ይከፈትልን፤ በግልጽ እንነጋገር” በማለት የመፍትሔ አቅጣጫ የሚጠቁም የግለሰብ አስተያየትና ሒስ እንደኾነ ተከሣሹ በመልሱ አስፍሯል፡፡

ጽሑፉ በጋዜጣው የተስተናገደውም፣ የሕዝብ አስተያየት በሚቀርብበት “የእኔ ሐሳብ” በሚለው ዓምድ ሥር በመኾኑ፣ የጸሐፊው ወይም የዓምደኛው ሐሳብ እንጂ የኤዲቶሪያሉን አቋም እንደማያንጸባርቅ በግልጽ ሰፍሮ እንደሚገኝ ዋና አዘጋጁ በምላሹ አስረድቷል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.