በአምቦ የተነሳውን ተቃውሞ ተከትሎ ከተማዋ ለሁለተኛ ቀን ውጥረት ሰፍኖባት ዋለ

ታኅሣሥ ፲፫ (አሥራ ሦስት)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-
የአምቦ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ትናንት ትምህርት በማቆም በእስር ላይ የሚገኙ ተማሪዎች እንዲፈቱ እንዲሁም በተማሪዎች ላይ ጉዳት ያደረሱት ለፍርድ እንዲቀርቡ ሲጠይቁ ከዋሉ በሁዋላ፣ የአጋዚ ወታደሮች ወደ ግቢው በመግባት በተማሪዎች ላይ ከፍተኛ ድብደባ ፈጽመዋል። በርካታ ተማሪዎችንም ይዘው አስረዋል።Image may contain: one or more people, people standing, people walking and crowd

ዛሬ ሃሙስ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የአጋዚ ወታደር ወደ ከተማዋ በማምራት ሁሉንም ትምህርት ቤቶች ከቦ ያረፈደ ሲሆን፣ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ከትምህርት ቤት እንዳይወጡ እና የወጡትም እንዳይገቡ ታድርጓል። ተማሪዎቹ ዶ/ር መረራ ጉዲና ፣ አቶ በቀለ ገርባና ሌሎችም በእስር ላይ የሚገኙ ጓደኞቻቸው እንዲፈቱ ጠይቀዋል። ባለፈው ተቃውሞ ወቅት በድብደባ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት የነበረውና አሁንም ድረስ የአልጋ ቁራኛ የሆነውና በሞት እና ህይወት መካካል የሚገኘው  የተማሪ ወሊሶ ደብዳቢዎች ለፍርድ እንዲቀርቡም ተማሪዎች ጠይቀዋል።
ተማሪዎቹ የህወሃት ድርጅት የሆነውን የትራንስ ኢትዮጵያ ተሳቢ የጭነት ተሽካሪዎች ላይ ድንጋይ በመወርወር መስታውቶችን አርግፈዋል። ስለአካባቢው ሁኔታ ጥያቄ ያቀረብንለት የከተማው ነዋሪ፣ ከተማዋ በወታደሮች መወረሩዋን ተናግሯል ። ገዢው ፓርቲ ከ9 ሺ በላይ ሰዎችን መልቀቁን እያስታወቀ ባለበት ሰአት አሁንም በኦሮምያ የተለያዩ ቦታዎች ወጣቶችን ይዞ እያሰረ ነው።
በሌላ በኩል አላጌ እስር ቤት ውስጥ የነበሩት በሺዎች የሚቆጠሩ እስረኞች ተፈትተው ወደ መኖሪያ አካባቢያቸው ሲመለሱ፣ ህዝቡ መንገድ ላይ ወጥቶ እጁን እያጣመረ ለወጣቶች ያለውን ድጋፍና በአገዛዙ ላይ ያለውን ተቃውሞ ገልጿል። አንድ ዛሬ ሃሙስ የተለቀቀ ወጣት፣ ህዝቡ መሃል መንገድ ላይ እየገባ ድጋፉን በመግለጽ ለመጓዝ  ሁሉ ተቸግረን ነበር ብሎአል። የሻሸመኔ፣ ቡልቡልና ነገሌ  ከተሞች ወጣቶች ባሳዩዋቸው  ድጋፍ ልቡ መነካቱንም ገልጿል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ትናንት ታህሳስ 12፣ በቡሌ ሆራ ትልቁ ገበያ በሚውልበት ቀን አንድ መኪና ኮንትሮባንድ ጭኖ አልፏል በሚል ወታደሮች በተኮሱት ጥይት የአንድ ወጣት ህይወት አልፏል። የከተማው ነዋሪዎች እንደሚሉት ወጣቱ ሆን ተብሎ ተገድሏል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.