ቁሞ ዬሚጠብቅ (stagnant) ዬሆነ ዬአመክንዮ ድንጋጌ – ዓለም አስተናግዳ አታውቅም! – ከሥርጉተ ሥላሴ

ከሥርጉተ ሥላሴ 23.12.2016 (ዙሪክ – ሲዊዘርላንድ) 
 
በሰዎችና፡ በመላእክት፡ ልሳን፡ ብናገር፡ ፍቅር፡ ግን፡ ከሌለኝ፡ እንደሚጮኽ፡ ናስ፡ ወይንም፡ እንደሚንሽዋሽ፡ ጽናጽል፡ ሆኜአለሁ። ትንቢትም፡ ቢኖረኝ ፥ ምሥጢርን፡ ሁሉና፡ እውቀትን፡ ሁሉ፡ ባውቅ፡ ተራሮችንም፡ እስካፈልስ፡ ድረስ፡ እምነት፡ ሁሉ፡ ቢኖረኝ፡ ፍቅር፡ ግን፡ ከሌለኝ፡ ከንቱ፡ ነኝ። ድሆችንም፡ ልመግብ፡ ያለኝን፡ ሁሉ፡ ባካፍል፥ ሥጋዬንም፡ ለእሳት፡ መቃጠል፡ አሳልፌ፡ ብሰጥ፡ ፍቅር፡ ግን፡ ከሌለኝ፡ ምንም፡ አይጠቅመኝም። (ዬሐዋርያው ዬቅዱስ ጳውሎስ መልዕክት ወደ ቆረንቶስ ሰዎች ምዕራፍ ፫ ቁጥር ከ፩ እስከ ፫) 
 
እፍታ።
 

ሥርጉተ ሥላሴ

 
እፍታን በትምህርተ ጥቅስ አላስገባሁትም። ስለምን? ከ2005 እስከ 2008 መጨረሻ ድረስ እ.አ.አ. እዚህ ሲዊዘርላንድ ዉስጥ በሰራሁበት አንድ ዬኮሚኒቲ ዬራዲዬ ፕሮግራም በሚዲያ ዬዋና መምሪያ ደረጃ እፍታ – ጠብታ – ዬወግ ገበታ ዬሚሉ ስያሜዎችን ያፈለቀው ዬሥርጉተ ሥላሴ መንፈስ ነበር፤ ስለዚህም ሃብቴን በፈለኩበት ጊዜ ዬመጠቀም ሙሉ መብት ይኖረኛል ማለት ነው።

ዬሰው ልጅ ህልውናውን ሊመራበት ዬሚያስችለው ዬራሱ ዬሆነ ገዢ መንፈስ አለው። ውስጡን ዬሚመራበት – ዬሚያስተዳድርበት – መክሊት። እንደ ተፈጥሮው በረቂቅ ንጥረ ቅኝት – ዬተቀመረ። ቅል ብቻ ነው ተቀዶ – ሆድ ዕቃው ወጥቶ – ለሰው ልጅ አንዳሻው አገልግሎት ዬሚሰጠው። ወይንም ጭቃ ተጠፍጥፎ ወይንም ተንቦልቡሎ – ተፈጥሮውን ለውጦ – በእሳት ጋይቶ ሸክላ ዬሚሆነው። ከፍ ሲል እንስራ ዝቅ ሲል ስባሪው ለእሳት መጫሪያ በገልነት አገልግሎት ዬሚውለው። ዬሰው ልጅ መንፈስ ቁስ አይደለም በክብ፤ በጋድም፤ በማዕዘን በዲዛይን ተጠፍጥፎ በስባሪ ሽርፍራፊ ጥርቅምቅም ቁስ ዬሚሰራ። ተፈጥሯዊ ዬሆነ ሰማያዊ ህግጋቶች አሉት፤ ህግጋቶቹ ሲጠቁለት ብቻ ነው አድማጭም፣ ተሳታፊም፣ አጋርም – አድናቂም ዬሚሆነው፣ በስተቀር ሊጫንበት ዬታለመውን ጫን – ተደል ዕሳቤ አያስጠጋውም። ልብስን እንጂ ልብን ማዋስ አይቻልምና። በሰው ልጅ ልብ ውስጥ በብሎን ዬሚጠባብቅ፤ ወላልቆ ዬሚገጣጠም መጤ ማንነት ሊኖር አይችልም።

መንሹ።

በትዕዛዝ ዬሚታፈስ ሰብል ዬለም። ሰው ለደረሰበት ማህበራዊ ንቃተ ህሊና ዬሚመጥን ዬመንፈስ ልዕቅናን ይጠይቃል። ዬህዝቡ ማህበራዊ ንቃተ ህሊና ከመሪዎች ዬመቅደም አቅም በላይ ከሆነ፤ ለቀደመው – ለላቀው መርህ መሪዎች ሊገዙ ግድ ይላቸዋል። ይህን አሻም ካሉ ድርጅታቸው ሆነ በሥራቸው ያሉት ተቋማት ሳይቀሩ ከባህር ዬወጣ አሳ ይሆናሉ።

ማህበራዊ ንቃተ ህሊና እዳሪ በቅሎ መንገድ አዳሪ አይደለም። ማህበራዊ ንቃተ ህሊና ዬታቆረ stagnant ቆሞ ዬሚጠብቅም አይደለም። ማህበራዊ ንቃተ ህሊና መሰረቱ ቀድሞ ሊመጡ በሚችሉ አሉታዊ ሆነ አዎንታዊ ዕሴቶች በበቂ ዬቀደመ ዬህሊና መሰናዶ – ዬህዝብን ወቅታዊ ዬትንፋሽ አቅም ኃብታትን ወደ ዬሚፈልገው አቅጣጫ መምራት ዬሚያስችል – ሙሉ አካልን ዬመግራት አቅም ያለው – ለነቃው ዬህሊና ክፍል አሸናፊ  ዬምህንድስና ርቁቅ፤ ሥልጡን ክስተት ነው። ከሁሉም በላይ ዬአንድን ማህበረሰብ ማህበራዊ ንቃተ ህሊና መራሹ ዓምድ ወቅት ብቻ ነው።

ስለሆነም ዬማህበራዊ ንቃተ ህሊና ጭራ ላለመሆን ቁልፉ ወቅት ሁነኛዬ ብሎ ዬሚያነሳቸውን አዳዲስ ሃሳቦችን ሳይፈሩ፤ ወይንም ሳይሸሹ፤ ወይንም ሳያብሎ፤ ወይንም ሳያዳግሙ፤ ዬህዝብን አዳዲስ original ዬሃሳብ አቅርቦት  – ዕለታዊ ፍላጎቶችን ማዳመጥ ይጠይቃል – በአክብሮት። በዝግ ስብሰባ ዬህዝብን አዳዲስ original ዬሃሳብ አቅርቦት ረመጥ ሊተናገድ አይገባም። ህዝብ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች በፕሮፖጋንዳ ወይንም በዕብለት ያልተሞሸረ ግልጥነትና ቀጥተኝነት ይፈልጋል። ዬጎበጡ  – ገዳዳ – ግልጽነቶች ትርፋቸው ድካም ብቻ ነው ዬሚሆነው። ዬነቃው ዬማህበረሰብ ህሊና ያልቀናውን መንገድ ሳያቀርበው ሊያስፈነጥረው ወይንም ሊሸሸው ይችላል። ወቅት ዬወለዳቸው ህዝባዊ እሳቤዎች ዬእኛ አካል ብሎ ማስጠጋት ካልተቻለ – ፍንዳታ ሊያስከትሉ ይችላሉ። ዬፍንዳታዎቹ ዬጉዞ መስመር ደግሞ አቅጣጫ ዬለሽ ከሆኑ፤ ማረፊያቸው ሆነ ወሳኙ በለስ ሊሆን ይችላል። ይህ ደግሞ ጠቃሚም አይሆንም።

አብሶ ዬማህበራዊ ንቃተ ህሊና ሃብት በህዝብ ከራሱ መከራ ዬበቀለ ከሆነ፤ በሁለት ወይንም፤ በሦስት ወይንም ከዛ ሊበልጡ በሚችሉ ዕውቅና ያልተነፈጉ ዬግለሰቦች ውክልና ሆነ ፊት ለፊት በማውጣት ብቻ መንፈሳዊ ዕሴቱን – ሃብቱን በቁጥጥር ሥር ማዋል አይቻልም። መዋቅራዊ በሆኑም አካሎች ቢሆኑ ሃብቱን ለመፍጠር ያፈሰሱት ማዕዋለ መንፈስ ካልኖረ በስተቀር፤ – እንደ መስኖ ዉሃ በተፈለገው አቅጣጫ እንዲፈስ ዬሚያደርግ ዬገኃዱ ዓለም ቃለ ምህዳን አቅመ ቢስ ነው ዬሚሆነው። አቅመ ቢስነቱ ደግሞ ሌላ ዬሚፈጥረው ዬግጭት ዓውድ ይኖረዋል። ግትርነትን መርህ ማድረግ፤ አፈንጋጭነትን ዬተካነ ማናህሎኝነት፤ እንዲሁም ፋክትን አለመቀበል። ፋክትን በእንጡሩብ በማናህሎኝነት ዘሎ ዬማህበራዊ ንቃተ ህሊናን ዕሴት ባለቤት መሆን አይቻልም። ፈጽሞ!

እንዲያውም ስበትና ግጭቱ በሚኖራቸው ፍትጊያ፤ በእጅ ያሉ ሃብቶችም ዬማፈንገጥ ዕድል ሊገጥማቸው ይችላሉ። ለዚህ ምሳሌ ዬሚሆነው ዬእኔና ዬቢዢን ኢትዮዽያ አፍቅሮተ – ተስፋ አመክኒያዊ  ዬመንፈስ ሰንሰለት ዬተበጠሰው ዬእዮር አደባባይ ይመስል ዬአንዲት ተጨማሪ ደቂቃ ተማህጽኖ ምላሹ ኮሳሳ መሆኑ ዬፈጠረው ግድፈት ነበር። አንዱ በመሪነት ሌላው በተጠማኝነት፤ አንዱ ቤተኛ ሌላው ባይታዋር፤ አንዱ ልጅ ሌላው እንጀራ ልጅ፤ በሰፋ ዬደረጃ ልዩነት ዬትውልዱን ዬሥነ  – ልቦና  ጫን ፤ ዬሚዛናዊነት ዝበት ንዝረት ቁልጭ ያለ  ስውር (abstract discrimination) ሆኖ ስላገኘሁት –  በዛች ቅጽበት ልቤም መንፈሴም ሸፈተ። ውስጤ ተሰበረ። ዬውስጤ ተስፋ ነኮተ። አመመኝ። ነገን ለነገዎች በእኩል ዓይን ለማስረከብ አንዱ ዬቀስተዳመና መንፈስ ባለ ድልዳሌ ንጉሥ – ሌላው ብትን አፈር ለምኖ መንገድ አደሪ ሲሆን ማዬት – ህሊናን ሞግቶ ትክክለኛ ሚዛን ያስጨብጣል። እኔ ድቃቂ ትቢያ ላይ ያለሁ ሴት ነኝ። አምላኬ ዬፈጠረኝ እንደ ሰው አድርጎ ስለሆነ – ቢያንስ ፈጣሪዬ ዘንበል ብሎ ዕንባዬን – ያዳምጣል። ሳልፍም ወደ እኩልነት ቤታችን – መሬት።

አንደኛው ዬተጋድሎ ምዕራፍ – መራኽ ።

ተያያዥ ዕይታዎች ….. በማከያነትም ይኖራሉ ….

መራኺነት እራስን መምራት ነው። ለመምራት – መመራትም እንዳለ ማወቅ ይጠይቃል። ለመሪነት ብቁ አድማጭነት ስኬቱ ነው። ማሸነፍ እንዳለ ሁሉ መሸነፍም ይኖራል። መሸነፍን መፍቀድ ብልህነት ነው። ነባሩ ሃሳብ አሸናፊውን አዲስ ሃሳብ እንደ ባላንጣ ወይንም እንደ መጤ ማዬት ዕዳን ከሜዳ መናፈቅ ነው። በተሸናፊነት ጽንስ ውስጥ ማንህሎኝነት ከተከሰተ ደግሞ ተሸናፊው ሃሳብ አገግሞ ዬመነሳት አቅሙ እስከ ወዲያኛው ሙት መሬት ዕጣ ፈንታው ሊሆን ይችላል። ዬተሻለው ነባሩ ሃሳብ ዬተሸነፈበትን ሃሳብ አክብሮ፣ መሸነፍን ያስከተሉትን ነገሮች – ቁጭ ብሎ በማጥናት – ቀጥተኛው አውራ መንገዱ ቢያደርግ ቢያንስ መሃል ላይ ያሉ፣ ጥግ ያልያዙ አቅሞችን ዬመሰብሰብ ዕድል ይኖረዋል። ውስጥ ያለው ኃይልም ቋፍ ላይ እንዳይሆን ይረዳዋል። አለኝ ለሚለው ኃይሉም ቢሆን መረጋጋትን ፈጥሮ ዬውስጥ ሰላሙን ያሰክንለታል። ያተርፋል።

ተሸናፊው ሃስብ በቅኑ መንፈስ በአሸናፊው ሃሳብ ውስጥ ያሉ ንጥረ ነገሮችን ከልብ ሆኖ ለመመርመር ሲናሪዮ ወይንም ፕሮቶኮል አያስፈልገውም። ይህም ማለት ዬንጥረ ነገሮችን ዬልብ ትርታ በተደሞ አቅሮቦ – ዬእኔ ማለትን ይጠይቃል። ዬእኔ ዬሚባለው ንጥረ ነገር በለበጣ ሚዜነት መሆን አይገባውም። ይልቁንም ሆኖ በመገኘት በልብ ፊርማ መረጋገጥ አለበት። ዬሚታይ ዬጭብጥ ፍሬ ነገር መኖር አለበት። ጉዳዩ አመክኗዊ ነው ይህውም ….

ዬመጀመሪያው አመክንዮ ለምሳሌ .. ከ10 ዓመት በኋላ ዬቅንጅትን ዬመራራ ስንብትን መንፈስ ለማምጣት „ቅንጅት ዬሚል ፓርቲ ቢፈጠር፣ ትንሳኤ ዬሚል ዬራዲዮና ዬቴሌቢዢን ፕሮግራም ቢጀመር – ቅንጅት ዬሚል ግብረ ኃይል ቢዋቀር“ – ለዛ መንፈስ ዳግማዊ ህልውና አይሰጠውም። ዬሞተው፤ ዬተሰዋው እያለ ምስጋናው – ሙሉዑ ክብሩ ለውጩ ደጋፊ ነበር። እስር ቤት ውስጥ በገፍ በቅንጅት ምክንያትነት በሁሉም ዬኢትዮዽያ መሬቶች ወገኖቻችን ነበሩ። ዬሆነ ሆኖ በዛን ጊዜ ከፖለቲካ ውሳኔዎቹ በላይ ዬህዝብን መንፈስ ዬጎዳው – እኔ እንደሚመስለኝ አጽናኝ መንፈስ ይሻ ዬነበረው ንዑድ መንፈስ መሬት ላይ ዬነበረ – ዬምልዕት ጎስቋላ መንፈስ ግማዱን እንደ ተሸከመ – በተስፋ ቢስነት እንዲቀጥል መበዬኑ፣ ይፋዊ ዬሆነ አይዞህን፤ እናመስግናለን ስለ ተነፈገ ነው። ሙሉ አመኔታው ጥግ አጣ። እኔ እራሴም ብሆን  በዘመነ ቅንጅት በትንሳኤ ራዲዮ በድምጽ ሥሰራም – ስጽፋቸው ዬነበራቸውን መንፈሶች ዛሬ ላምጣ ብል ከራስ ጋር መጣላት ነው ዬሚሆነው።

ሁለተኛው „ወቅት“ እራሱ ከህዝቡ ጋራ ስለሚኖር፤ ዬህዝብን ወቅታዊ ጥያቄ፤ ለዛች ዬወቅት ዬጊዜ ማዕቀፍ ብቻ ስለሚያቀርብ – ዬወቅት ጥያቄ ሕዝብን ማነቃቃትና ማንቀሳቀስ  mobilized ዬማድረግ አቅሙ ከጠሐይ ጉልበት በላይ መሆኑ ነው። አዲስ ድርጁ ኃይል „ወቅት“ እራሱ ይፈጥራል። አዲስ መሪዎችን „ወቅት“ ይወልዳል። በነባሩና በአዲሱ መንፈስ ያለው ዬግጭት ሂደትም ይሄው ነው። ሊሆን ግድ ስለሚል። ዬሚበጀው ነባሩ አዲሱን ቡቃያ ለማቀጨጭ ከመታግል ይልቅ – ተወራራሽና ተከታታይ ባህሪ እንዲኖር ለማድረግ እራሱን መግራት ብቻ ነው ያለው አማራጭ። በአዲስ ዬአያያዝ ጥበብ ክህሎት ውስጥን መቅጣት። ስህተት እዳይሰራ በልዩ ቅብዕ ዬተፈጠረ ምድራዊ ሰው ዬለም። ወቅትን ሳያዳምጥ አሸናፊ ሆኖ ዬወጣ መሪ ሃሳብም ኖሮ አያውቅም። ይሄ እንደገና መወለድን renaissance ይጠይቃል። በስተቀር አዲሱ እዬጣለው ስለሚያልፍ – ዬነባሩ ሃሳብ ጥግ አልቦሽ ሆኖ ከባህር ዬወጣ ዓሳ ከመሆን አይድንም። ይሄንን ዬሚያው አሁን ሳይሆን ጨርሶ ከወደቀ በኋላ ሊሆን ይችላል።

ለዚህ ዬአሜሪካው ዬ2016 ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ታላቅ ዬተመክሮ ት/ ቤት ነው – ዲሞክራቶች ወጣቱ ያቀፈውን አማራጭ ተወዳዳሪ – ያልታዬ፣ አዲሳዊ fresh ጻዕዳ መንፈስን – ተፎካክሮ ማሸነፍ ዬሚያስችል አቅምን – ብክለት ዬሌለበትን ዬብቃት ቃናን ገፋ አድርገው – አቅማቸውን ሁሉ በውጥረት ቀውስ ግጭት በጎሸው መንፈስ ላይ ማፍሰሳቸው ለሪፓፕሊካኑ ተፎካካሪ ዕጣ ወጣላቸው። ዓለምም እንዳማጠች ቀረች። ዬተፈጥሮ አስገዳጅ ነገር ካልመጣ አራት ዓመት ከዛም ለሚበልጥ ጊዜ ዓዲሱን ባለ ራዕይ ወቅት ሸልሟል። ወቅት እራሱን ዬሚያስተዳድርበት ያልተጻፈ  ህግጋት አለው። አሸናፊም ነው። ስለዚህ ነባሩ ነፃነት ፈላጊ ሃሳብ ስብከትን ተግ ማድረግ ይገባዋል። በፖለቲካ ስብከት ሀገር አይገነባም። ዬህዝብን ህሊናዊ ቀልብም መግዛትም አይቻልም።

ሌላው ያዬነው ዬጎንደር ዬአብዮቱ መንፈስ ዬማህበራዊ ንቃተ ህሊና ደረጃ ከላይ ወደ ታች ሳይሆን – መሬት ላይ በራሱ ጊዜ ነው ዬፈነዳው። ከላይ ወደ ታች ዬወረደ ዬማዕከላዊነት ሰንሰለት ዬለውም። ስለዚህም ሽቅብ ዬሚያስጠብቀው ምንም አይነት ዬአመክንዮ ግዴታ ስለለበት፤ ማዕከላዊነትን ማስተናገድን – አይፈቅድም። ይህም ማለት በዚህ ህያው ዬለውጥ መንፈስ ውስጥ ከላይ ወደ ታች ፍላጎትን በትእዛዝ መልክ ማስተላለፍ transfer ማድረግ አይቻልም። ሌላም እጅግ አስጊ ምልክት አለው – ይሄ ምናባዊ ምኞት በራሱ ነገም በማዕከላዊነት መርዘን ምች ዬምትታመም ኢትዮዽያን ህልመኝነት ያመለክታል። አንባገነናዊ መንፈስም ማጫ እዬተመታለት ስለመሆኑ ፍንጭ ይሰጣል። ይህንን ዬሚፈቅድ ዬነፃነት ራህብተኛም ማግኜት ይቸግራል። ሁሉ ዬራሱ ጌታ ነውና።

ይልቅ ከዚህ ተንሳፋፊ ምኞታዊነት ነባሩ ነፃነት ፈላጊ ሃሳብ በመውጣት – ዬከፈለው ዬቀደመው መስዋዕትነት ዕሴት በዋጋ አልቦሽ እንዳይደመደም – ወቅቱን በጭብጥ ጆሮነት – በሃቅ ዓይናማ አመክንዮ ማድመጥ ግድ ይለዋል። በስተቀር ወንዝ ሲወስድ እያሳሳቀ ነው“ ዬሚለው ብሂል ለራዕዩ ተደራሽ መሆኑ አይቀሬ ይሆናል። እንደ 1960ዎቹ „አማራ ጨቁኖህ ስለኖረ – ለራሴ መግደያ ገመድ ከእኔ ባልተወለድከው መሪ ሃሳብ ሥር ሁኜ – እንዳሻህ እንድታደርገኝ ፈቅጃለሁ“ ብሎ – ለኢህአፓ ዓላማ፤ ለማሌሊት ዓላማ፤ ለሻብያ ዓላማ ዬሚሞት ዬአማራ ትውልድ ዛሬ ሊኖር ይችላል ብሎ ማሰቡ ራሱ ላጥ ያለ ገደል ነው። መንገዱ ዬተናደ ነው። በሞኝ ክንድ ዘንዶ ተለክቶበት አይቷልና። በዚህ ውልግድ መንገድ ቅንጣት ደቂቃ ዬሚያጠፋ ዬብዙኃን ዬአማራ መንፈስም አይኖርም። በዚህ ክህሎታዊ አመክንዮ መገባባት ካልተቻለ፤ አንዲት ጋት ዬኮቲ ማረፊያ ማሳ በህሊና ለማግኘት ጋዳ ነው። ሰባዕዊ መብት ሙሉ ዬነፃነት መሬት እንጂ ዬጉልማ መሬት ውራጅ ለመሆን አይፈቅድም።

ላቂያነት – በልባምነት።

„ማን ያርዳ ዬቀበረ፣ ማን ይናገር ዬነበረ።“ ጎንደር ላይ አዬር ላይ ሆኖ አባል መመልመል፣ መዋቅር መዘርጋት ቀርቶ መሬት ላይ ተገኝቶም ይከብዳል። ዬማይቻል ነገር ነው። ይህንን ደግሞ እዛው ዬተፈጠርን እንዲሁም ደረጃውን በጠበቀ ዬማደራጀት ሙያተኝነት በውስጡ ዬኖርን ሰዎች አለን – በህይወት። በተጨማሪም በራስ አነሳሽነት በማደራጀት ተግባር ሳንኮችና ፍሬዎች ላይ ለመነሻነት ዬሚያገለግሉ ዬጥናትና ዬምርምር ሥራዎችም ስሜን ጎንደር ላይ ለናሙና ተሰርቶ ነበር። በጥናቱ feedback ልቦናን ዬመያዝ ዬአቅም ርቀቱን ተፈጥሮና ዬማህበረሰቡ ዬውስጥነት ርቁቅ መንፈስ እኔ በዛን ጊዜ ተመልክቼበት ነበር። ዬጥናቱን ሪፖርትም እስከ ማዕከላዊ ኮሜቴ ድረስ መላኩን አውቃለሁ፤ ኃላፊነቱ ዬእኔ ስለ ነበር።

ጎንደር ላይ ብዙ ዬማይሰሩ በሌላ ኃይል መንፈስ ውስጥ ዬተጸነሱ፣ ተንሳፈው ሊቀሩ ዬሚችሉ አሉ። ዬሞቅታ ግልቢያዎች – ዕውነት ለመናገር ግጣሙ አይደለም። ጎንደር ውስጡ ካልፈቀደ ያፈሰዋል። ማንነታቸው ዬመንፈስ ሚዛን ዬሚደፋ መሆኑ ሳይረጋገጥ እንደ ወረደ ቅቡል ዬሚሆን ምንም ዓይነት ጉዳይ ዬለም ጎንደር መሬት ላይ። ለዚህም ነበር ጎንደር ላይ በነበረው ህዝባዊ ስብሰባ ኮሜቴውን „ዬዬትኛው ዬፖለቲካ ድርጅት አባል ናችሁ?“ ብሎ በአጽህኖት ዬጠዬቀው። ሳይጣራ ዘው ዬለም በጎንደሮች ቤት። ዬተከደኑ ተፈጥሮዎች አሉት – ጎንደር። „ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ“ እንዲሉ ወያኔም ህሊናው ዬጎንደርን ዬበቃ ውስጥ መተርጎም አቅቶት ነው „በአሸባሪነት“ ዬፈረጀው – ዬቀይ መስመርም ክልል ያደረገው። በአደባባይ ተናግሯል እኮ „ወያኔ እንጂ እኛ ዬሻብያ ተላላኪ አይደለነም“ ሲል። ለወያኔ „ሻብያን አንተ አሸባሪ ካልከው – ለአንተ ነው ዬሚቀርብህ – አንተ ነህ አሸባሪው ማለት ነው ያለው። እኛን አታነካካን ብሎታል – በእድምታ። ስለ ጎንደር በጥቂቱ በአራት ክፍል በ2015 በተከታታይ ዬጻፍኩትን በዘሃበሻ ድህረ ገጽ ትብብር ወጥቶ ነበር። ግርድፍ ዕይታን ለመግራት አስቤ ነበር ዬጻፍኩት። ከትርጓሜ ስህተትም ይታደግ ነበር። ለነገሩ ማስተዋል ለሁለቱም ጎራ ተበጥብጦ አይጋት ነገር።

ጥቁር ዕጣ።

ዬህዝብን ማህበራዊ ንቃተ ህሊና መምራት ዬሚቻለው አጋጣሚ ሰጥቷቸው ዬሚበቅሉ አበባዎችን ተራ – በተራ በተናጠል መልቀም ትንፋሽ ማሳረፊያ ቢሆን እንጂ – ዘላቂ መፍትሄ አይደለም። ጥገናዊ ዘዴ ነው። ብልህ ዬፖለቲካዊ አስተሳሰብም አይደለም – ለእኔ። አቅምን መጥኖ መነሳት ብቻ ነው መካቹ ጉዳይ። „ልክን ማወቅ ከልክ ያደርሳል“ ይላል ጎንደሬ ሲተርት። ይልቁንም ነባሩ ሃሳብ ማዳዳጡን ትቶ፤ ዘመን ጠገብ ዬአቅም ዬአያያዝ ዬሰፋ ዬክህሎት ክሳት ክፍተት ስላለ – እሱንም ባሊህ ማለት ያለበት ይመስለኛል። መጠጊያ አጥቶ እንደ ጊዜያዊ መጠለያ አድርጎት ዬቆዬው ኃይልም ቢሆን – ከወቅቱ መንፈስ ጋር እንዲሄድ ዬቆዬውን አቋሙን ሊያስክዱት ዬሚያስገድዱት ፋክቶች ከኖሩ፤ እሱንም ዬማጣት ጥቁር ዕጣ ሊኖር ይቻላል። ባዶ እጅ ዬመቀረት። ይህም ሌላው በአግባቡ ዬለውጡን መንፈስ ከመያዝ ስስ ዬአቅም አያያዝና አስተዳደር ዬመነጨ ነዳላ ገጠመኝ ነው። እኔ እማዬው እንደዛ ነው።

በተጨማሪም በግርግሩ ዬራሱን ዬቁርሾ ምት ዬሚስከነዳም ቂመኛ መንፈስም አለ፤ ይሄም ሌላው ቀይ መስመር ነው። ብልህነትና ብልጥነት በፍጹም ሁኔታ ዬተለያዩ ናቸው። በግርድፋ ለፖለቲካ አመራር ምራቁን ዬዋጠ ብልህነት አትራፊ ሲሆን፤ ብልጥነት ለሌላ ዘርፍ በአፍላው ሊሰራ ይችል ይሆናል፤ ተደጋጋሚ ከሆነ ግን ለሌላ ዘርፍም ቢሆን አትራፊነቱ ዕድለ ቢስ ነው። አብሶ ለፖለቲካ ትርፍነት ብልጥነትን በድግግሞሽ ዬህልውናው መሰረት በማድረግ ብልህነትን ከተጫነው፤ በሁሉሙ ዘርፍ መሬት ዬያዙ ቅምጥ ኃብቶችን ሳይቀረ ዬተነቃነቀ ጥርስ ሊያደርጋቸው ይችላል። ዬተነቃነቀ ጥርስ ደግሞ አውልቆ ካልተገላገሉት ዬውስጥን ሰላምን ያውካል። ይህ ከሚሆን ለፖለቲካዊ ተግባራት መርህን ብልጥነት ከማድረግ ይልቅ፤ ጨዋ ብልህነት እንዲመራ መፍቀድ ዬሃሳብን ትንፋሽ ሊያሰነብት ይችላል። ዛሬ መሬት ላለው ከፍተኛ ደረጃ ላይ ለደረሰው ግዙፍ ዬማህበራዊ ንቃተ ህሊና ከፍታዊ ደረጃ፤ ዬብልጥነት ዳታዊ ቀመር ብዙም አጋዥ አይመስለኝም። ይልቁንም ኪሳራን ይሸልማል።

ከዚህ ጋር ማንሳት ዬምፈልገው በነፃነት ትግል ውስጥ ዬሚስጥር ጥበቃና አያያዝ ብርቱ ጥንቃቄ ያልተፈጠረልን መሆኑ ነው። በዘረክራካ ዬመረጃ ቅብብሎሽ ወገኖቻችን ለፋሽት ጥቃት መሸለም ብቻም ሳይሆን፤ ወቅትን ያላደመጠ መሆን ዬብልጥነት ኮቴ ተከትለው ዬሚመጡ ዬመጠራቅቅ ቀለበቶች – እራሳችን ጠልፎ እንዲጥል ፈቅደንለታል። አብሶ በሰብዕዊነት አምክንዮ ውስጥ ጭልጥ ባለ ዬፕሮፖጋንዳ ብልጥነት መሬት ላይ ያለው ወገን ዬጋለ ምጣድ ስጦ እንዲሆን ተገዶበታል። በርካታ ቤተሰብ ቤቱ ተፈቷል።

ይህ በጥሞና ተመርምሮ መታረም ያለበት ጉዳይ ይመስለኛል። ለፋሺስት ጭካኔ ሥጋ ቀላቢዎች እኛው እራሳችን ሆነናል። በሌላ በኩልም ዬምንተዳዬ ጉዞ ዬደጋፊ መንፈስን ልብ ዬማሸፈት አቅሙ አንቱ ነው። ዬህዝብ እንግልትና ሞት ዬካራንቡላ ጨዋታ አይደለም። እንኳንስ ዬሰው ልጅ ዬእርሻ ሰብል በአንድ ጀንበር ማስበል አይቻልም። ስለሆነም ብልህነት ከጥንቃቄ ጋር ቢሆን ከፍላጎት እርከን ለመድረስ ማገር ዬሚሆን ይመስለኛል።

ሁለተኛው ዬተጋድሎ ምዕራፍ – ዬደም ታሪክ 

መሰረታዊውን ጭብጥ ሳይንሳዊ ዬመፍትሄ ሃሳብ አመንጭቶ ከመፍታት ይልቅ፤ እንደ አልባሌ ማዬትም ሆነ ዬረጅም ቀጠሮ አጀንዳ ማድረግ አዋጭ መንገድ አይደለም። ዬደም ተጋድሎ ታሪክ ሸቀጥ አይደለም – በፕሮፖጋንዳ ተገዝቶ ለልደት ዬሚሸለም።  – ወይንም ዬልደት ኬክ አይደለም – ተቆራርሶ ለድሎተኞች ዬሚታደል። ሃብቱ ዬደም ታሪክ ነው። ታሪኩን አሳልፎ ላለመስጠት ሁለተኛው ዬተጋድሎ ምዕራፍ እዬሆነ ይታያል። ዬሚበጀው ክብሩንና ታሪኩን ለባለታሪኩ ባለቤት መተው ነው። ሊደነቅ፣ ሊከበር፣ በቂ ዕውቅና ሊሰጠው ዬሚገባውም ለተጋድሎው ባለቤት ለህዝብ መሆን ይገባዋል።

ቀሪውን ረጅሙን መራራ ጊዜ በተመለከተም ቢሆን በንቀት፣ በትዕቢት፣ ሳይሆን በመከባበር ጉዞን አህዱ ማለት ይሻላል – ባልዘበጠ አቋም። ይሄም ቢሆን ውስብስብ ዬኢትዮዽያን ችግር ለ40ዓመት በጦርነት እሳት እዬነደደ ያለው ዬጎንደር ብቻ ግዴታ አይደለም። ዬመቶ ሚሊዮን ህዝብ ኃላፊነት እንዲሸከም መጫንም ጎንደርን ሲሪያ ከማድረግ ለይቼ አላዬውም። ዬፋሲል ግንብ ጉዳይም አለ። ምን አደረገ ይሄ ህዝብ? እኮ ምን በደለ ይህ ዬአብርኃም በግ? ሁልጊዜ ለግራ ቀኝ ማገዶነት ዬሚታጨው። ሁሉም መስዋዕትነትን መከፋፈል ያስፈልጋል። ይህንን ዬታመቀ ጉዳይ ዬትም ቦታ ዬሚኖሩ ዬጎንደር ልጆች ፊት – ለፊት ወጥተው ዘብ መቆም አለባቸው። ነገምም ይቀጥላል በበላይ መንደር። አማራ ዬደም መገበሪያ መሬት መሆን ብቻውን ዬለበትም። ዬበፊቱ – ይበቃዋል።

ዬአማራ ተጋድሎ „ዬኢትዮዽያ ሀገራዊ ንቅንቄ“ ተልዕኮ ዬማስፈጸም ግዴታም፣ አቅም ሊሆን ይገባል ተብሎ መታሰቡ እራሱ ፍቺ ያልተሰራለት ጉዳይ ነው። ስለምን? ገና ለጋ ለሆነ ተጋድሎ ይህን ያህል ኃላፊነት መጫን ምን ሊባል እንደሚችል አላውቅም። አራስ ህፃንን 13,000 ኪሎ ብረት ተሸከም እንደ ማለት ይመስለኛል። ኢትዮዽያ ዬሁሉ እንጂ ዬእሱ ብቻ ሀገር አይደለችም። ዬድርድር ፍንጭ ከተገኜ ደግሞ አቋጣሪ እንደሌለው ካለፈውም – አሁን ካለውም ዕውነት መማር ይገባዋል። እሱ እንደ ተጠመደ እነ አቤቶ ሹልክ አይቀሬ ነው። ዬቆዬሰው ይዬው። „አያያዙን አይቶ ሸክሙን ይቀሙታል።“ ተጋድሎውን በሥሙ መጥራት እንኳን መድፈር አልተቻለም።

ይህን አሳዛኝ ትዕይንት ማስተባባያ ዬማይቀርብበት – ምድሪቱ ዬምታውቀው ዬሃቅ እንክብል ስለሆነ እንዳሻ መረማመጃ ሆኖ እያዬን ነው። ይህነን ሃቅ ያልደፈረ ዬነገ ዬታሪክ ግድፈት ነው እያዬን ያለነው። ለዛውም አውሮፓ ኮሚሽን ፓርላሜንት ላይ መስዋዕትነቱ በምን ሁኔታ እንደ ቀረበ ዬሚታወቅ ነገር ዬለም። ከኢትዮዽያዊው ማንዴላ ከፕ/ መራራ ጉዲና ጋር ሆላንድ ላይ በተደረገው ውይይትም ለቀረበው ጥያቄ አውሮፓውያኖቹ ጊዜ በመስጠት – ለማድመጥ ፈቃደኝነታቸው ልግስና እንዳለው ብቻ ነበር ዬተናገሩት። እንደ ፖለቲካ ሊቅነታቸው ጥበቃ እንዳይለዬው ዬፈለጉት፣ ግን ዬታዘቡት ዕውነት እንዳለ እያንዳንዷን ነጠላ ነገር ጉዳዬ ብሎ ለሚከታተለው መንፈሴ ልዩ መልዕክት ነበረው። ዬቅኔ እጭጌ ብላቴ ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን በቅኔው ለዛ እንደተቃኘው „አብረን ዝም እንበል“  እንደ ማለት ይሆን? ዬሆነ ሆኖ ዬተብራራ መልስ ለመስጠት መቸገራቸውን አስተውዬበታለሁ። እርግጥ ዬብልህነት ዬቅራኔ አያያዝ መንገድ ነው፤ መጠቃቱ ለሳቸውም ዬቀረ ባይሆንም። ዬሃሳብ ጦርነቱም ዬታሪክና ዬተጋድሎ ዘረፋውን አቤት ወዴት ብላችሁ ተሽቆጥቆጡለት – እጅ ንሱለት፣ ተነጠፋለት – ተጎዝጎዙለት ነው። ይህ ደግሞ በጓዳ ከነጮች ጋር እንጂ፤ ለእውነት ራህብተኛው ዬመንፈስም፣ ዬተስፋም ዬአሜኔታ ልግስና አቅም አይኖረውም። አክብሮትን ይቆራርጣል፤ አመኔታን ይሸነሽናል። ትዕግስትን ይሸበሽባል። ዕውነትና ህሊናን ስለሚያፋጥጥ። ዘላቂ ምራቁን ዬዋጠ ዕውቅና ዬሚገኘው በዕውነት ማሳ ብቻ ነው።

ዬሆነ ሆኖ ዬዚህ ግትር ዕይታ ዕጣ ፈንታ ወደፊት ተደፋሪ መስምር ነው ዬሚሆነው። ተከብሮ ዬመቆዬት ወይንም በተቀባይነት ዬመዝለቅ አቅሙ ዬነፈሰበት ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም በገላጣ መሬት ላይ ዬተከወነ ዬአማራ ህዝብ ዬተጋድሎ ደማቅ ገድል፤ ጉልበቱ እራሱ ዬሚፈጥረው አጓጒና ሳቢ ሂደቶች ስላሉት። ሃቁ እራሱ ወታደር ነው። ሃቁ እራሱ ገበሬ ነው። በዬትኛውም ሁኔታ ያለውን ዬሃቅ አርበኛ ሰብል ዬማሰባሰብ አቅም አለው። ዬተፈናቀለን ዬአማራ ሰብዕና መንፈስን፤ ዬተሰበረን ዬአማራ ቅስም ትንሳኤውን ዬጎንደር አብዮት ዓዉጇል። ለኢትዮዽያውያን ምንዱባንም አይዟችሁን አልብሷል። ይህንን ዬተስፋ መንገድ ነጥቀን መልሰን እንቀብረዋለን ዬሚል ዕሳቤ ዕድሉ ራዕድ ነው። መሬት እዬከዳው ይሄዳል። ሁኔታዎችን በጥሞና አጥንቶ መጣኝ መፍትሄ ካልተፈለገ፤ „ዬዝብሪት ቤት ሳይዘጋ ያድራል“ እንደሚባለው ድካሙ ሁሉ ፈሶ እንዳይቀር በተለይ ዬታሪክ አጋጣሚ አደራ ዬሰጣቸው ባደብ ቢመክሩበት መልካም ነው። አትራፊውን ዬመቀበል አቅምን መፍጠር በእጅጉ ዬሚያስፈልግ ይመስለኛል።

ህግ ተላላፊነት።

„ህግ ተላላፊዎችን ጠላሁ“  አለ ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት ———– ራዕይ፤ ፍላጎት፤ ተስፋ ማቀድ፤ ዬሰው ልጅ መብት ነው። በሞፈር ዘመት ራዕይ አይተለም-ም፤ ለራዕይ ትልም ሰጪም ነሺም ከአንድ አምላክ በስተቀር ማንም – በማንም ላይ መጫን አይችልም። እንዲጠራበት ዬሚፈልገውን ሥያሜ፣ ዓርማ፤ ዓላማና ተግባር ዬሚወስነው ራዕዩን ያቀደው አካል ባለቤቱ እንጂ ራዕይ በሞግዚት ሆኖም አያውቅም። ወይንም በማደጎ ልጅነት ሆኖ አያውቅም። በውክልና ራዕይ አይታሰብም። ለራዕይ baby sitter አያስፈልገውም። ወይንም ጎረቤቱ ሊሆን አይችልም። ለራዕዩ መነሻም መድረሻም ሆነ ፈቃድ ሰጪም – ፈቃድ ነሺም ባለቤቱ ነው። ዬመብት ፍርፋሪ መልቀም ሰፊ ራዕይና ዬትውልድን ተልዕኮ ይዞ ዬተነሳ ኃይል ሊሆን አይችልም። በራዕይ ጉዞ ዬጌታና ዬሎሌ ቅኝ ተገዢነት ዬለም። እንኳንስ ዛሬ በመይሳው ዘመንም አልሠራም። በባላይ ዘመንም ቢሆን አፍንጫህን ላስ ነው ዬተባለው። ቲፒዲኤምን ዬተቀበለ መንፈስ ዬአማራን ህልውና ዬተጋድሎ መንፈስ መቀበል ግድ ይለዋል። አልቀበልም ማለትም ይችላል። መጪውን – ከቻለ። ቅዱሳን፣ ደናግል አቮም ለግፋዕን ዬጸሎት አጥር ቅጥር ይገነባሉ። መገለል ከአንጀት ዬሚቀመጥ አመክንዮ ነው። ባይታዋርነት ዬርህርህና ሽልማትን ከቅንነት መንደር ያፍሳል። ለመጋፋት ሰብዕዊነትን ዬሚቀነቅኑ ሩህሩህ ዬዓለም ህዝብ ሳይቀር ከልብ ያዳምጠዋል። በሌላ በኩልም  ብዙኃኑን መንፈስ መጋፋት ጊዜ እዬጠበቀ ዬሚፈነዳ ቦንብ እንዲኖር ሊደርግም ይችላል። አቅም በአግባቡ እንዲሁም በአክብሮት ከተያዘ ብቻ ነው ልቡን ማግኘት ዬሚቻለው። በስተቀር ትእግስት ሲያልቅ ፍቅር ይሰደዳል። መመካት በህዝብ ፍቅር ብቻ ነው። መከታ፣ ጥግ፣ ዋሻ፣ መጠለያ፣ ዬህዝብ ንጹህ ፍቅር ብቻ ነው። ዬምልዐት ዬፍቅር አማጬ ከንጹህ መንፈስ ዬታጨ ዬምልዕት ንዑድ ልብ ብቻ ነው።

አማራነት ይከበር!“

„አማራነት ይከበር!“ ይህ በኽረ ጥያቄ ለአንድነት ኃይሉ ከአንድ ጎጆ ቤት እንደምትመዘዝ ቀንጣ እሳር ነው ዬሚታዬው። ባለቤት ዬለውም። ሌላው ቀርቶ በአዉራው ፖርቲ ውስጥ በመደበኛ ሙያው ዬጥናትና ዬምርምር ብቃት፤ ዬሙያ ልቅና ያለው ወርቅ ሰብዕና  በኢትዮዽያ አገራዊ ንቅናቄ፤ ውይይትና ዬፊርማ ሥርዓት ላይ አዬነውን? እስከዛሬ በታዩ ጉልህ አገራዊ ጉባኤዎች ብሄሩ አማራ ዬሆነ በሙያው ሊቅ-  ጎልቶ ያዬነው አንድም ቦታ ዬለም። ይታዘቡኛል – አለማለት። ያውም ዬወጣበት ቤተሰብ ቤተ – ዘደቂቀ ቅኔ ነው። ያ ሊቅ እንደ እኔ እንደ ማህይሟ ዬጉልበት ሠራተኛ ነው። ስለዚህ ባለቤት ለሌላቸው መንፈሶችና ነፍሶች ጥግ ያስፈልጋቸዋል። ዬኪዳን  ቤት ያስፈልጋቸዋል። ለድርድርም መቅረብ አይኖርበትም። ለዚህም ነው በአውራ ፓርቲ ያሉ ሊቃናት ሲዘረዘሩ እንኳን ያ … ዬሀገር ሃብት በዝርዝር እጮዎች ውስጥ ዬማይታዬው። ዬነፃነት ኃይሉ ከእሱ መንፈስ ጋር እንዲተዋወቅ ጥረቱ ዝግ ነው። ሌሎችንማ እያዬን እዬሰማን ነው።

እኔም ያወቅኩት በ2008 ልክ ይሄን ሰሞን ነበር ኮፐን ሀገን ዴንማርክ ላይ ዬG20 ዬሀገር መሬዎች ስብሰባ ላይ ሟቹ ጠ/ ሚር. ሄሮድስ መለስ ዜናዊ ይገኙ ስለነበር፤ ዬዴን ኢትዮዽውያን ባሰናዱት ዬተቃውሞ ሰልፍና ህዝባዊ ስብሰባ ላይ ነበር። ለዚህ ብቁ ልዩ ዬሐገር አንጡራ ኃብት ፍጹም ዬሆነ ታላቅ አክብሮት አለኝ። ለእኔ ለሥርጉተ ሥላሴ ትውልድ ሊተካቸው ከማይችሉት ምርጥ ዬሐገሬ ዬኢትዮዽያ ሃብቶች አንዱ ነው። በሁለመናው አንቱ ነው። ላቂያ! ዘደቂቀ አዳም። ሰፊ ክፍተት ነው ያለው። ይህን  ክፍተት ቢያንስ ለማቀራረብ ችግሩን ባሊህ ማለት ወቅት እራሱ ለራሱ ዬሸለመው አመክንዮ ነው።

ዬሆነ ሆኖ ዳግማዊ መአህድ ከኢሳት ጋር  ዬሦስትዮሽ ውይይት ሲያደርግ በክፍል አንዱ ክፍለ ጊዜ ያዳመጥኩት ቃለ ምልልስ ነበር። ገድለኛው ዬአማራ ዬህልውና ተጋድሎ አብዮት ላይ አማራነትን ዬሚገልጽ ጎልቶ ዬወጣ ድምጽ አልተሰማም“  ዬሚል ሞጋች ዕይታ አዳምጫለሁ። በወቅቱ ኧረ! ነበር መሉው ስላልወጣ ነው“ ዬሚል መልስ ተሰጥቶበታል። በመጀመሪያ ነገር ይህ ቃለ ወንጌል ዬጎንደር አብዮት ዬተነሳበት ዓናት አመክንዮ ገላጭ ነው። ወልቃይት አንቺን ብረሳሽ ቀኜ ትርሳሽ“  ከጎንደር እስከ ጎጃም ጠረፍ ድረስ ዬሚሊዎኖች ድምጽ ሆሳዕና ነበር። ስለሆነም በተደሞና በአንክሮ ዬበለፀገው ህዝበ – ድምጽ አሁን ላለው አጠቃላይ ዕውነትን አዛንፎ ወይንም ጥለቱን ዘቅዝቆ ዬመልበስ ሂደት መልስ በሆነ ነበር። ዬአውሮፖዎቹ ዬሥልጣኔ ዬምርምር ማዕከሉ ቅኔ ቤት – ድጓ ቤት፤ ፆመ ድጓ ቤት፤ ቤተ – ዜማ፤ ቤተ  – ንባብ፤ ቤተ – አቋቋም ዬሁሉም ዕልፍኝ ዬሆኑ አቨው አጠገብ ስላሉ፤ እንደ እኛ በቁሙ ስላልሆነ ዬሚያነቡት፤ ትርጓሜውና ሚስጢሩን በአንድምታ እንዲገልጡ ቢጠዬቁ – መጠሐፍ ይጥፋበታል። ዬወንጌላውያኑን ዬሐዋርያትን ገድል መጸሐፍት በአንድምታ እንዳመሳጠሩበት። በነገራችን ላይ አንድ ቅዱስ አባት ከሞቱ በኋላ ታትሞ ዬሚወጣ መጸሐፍ ጽፈዋል፤ ሞታቸውን በትዕግስት ይጠብቃሉ። ሊቅነቱ ሆነ ጥልቅነቱ እስከዚህ ድረስ ነው።

በፋሽስት ግፍ እንደተፈጸመበት እንደ ሌላው ወገኑ ሁሉ ዘብሄረ አማራ ዬ26 ዓመት ሞቱ ልደቱ ወይንም ዬተዳረበት –  ዬተኳለበት እንዳልሆነም ይታወቃል። አማራው በፖሊሲ ደረጃ ነው በመዶሻ ዬተቀጠቀጠው። ባለቤት አልባ ብቻውን ያሳለፈው ጊዜ ለዚህ ዬተጋድሎ መንፈስ ሊያበቃው አይችልም ብሎ ማሰብ በራሱ ዬጭብጥ ጭንቅላትን መተላለፍ ይመስለኛል። ዛሬ አማራ በመሆኑ ብቻ፤ ሌላው ቀጥ ባለ ዬህይወት መጓጓዣ እዬተጓዘ፤ እሱ ጫካ ለጫካ ዬሚንከራተትበትን ዘመን ምክነት ዬመግለጽ አቅሙ በበቂ ሁኔታ አማራው ይኖረዋል ብዬ አስባለሁ። ለዚህም ነው በሰፋ ህዝባዊ ተጋድሎ እሳት እዬረገጠ ዬሚችለውን በማድረግ ላይ ዬሚገኘው። ዬአማራ አዲስ ትውልዱ ከእኛ ዬተሻለ ዘመኑን ዬሚመጥን ዬመንፈስ አቅም አለው። ትውልዱ ኑሮው ዬማድመጥ አቅሙ ዬሚመነጨው ከመከራው ጋራ ስለሚኖር አስተርጓሚ፤ ወይም ለፍዳው ማከያ አጋፋሪ አይሻውም። አሳርን ተንፍሶ፣ ፍዳን ተጎንጭቶ፤ ስቃይን ተመግቦ እዬኖረው ነው። አማራ ሆኖ መጸነስ ውጪም፣ ሀገርም ፍዳ መሆኑን ዬማመሳጠር አቅሙ ቤተ – ቅኔ ዘጉባኤው ነው። ነፍሱ ዬተፈጠረችው በቅኔ እፍታ ነውና። ሌላው ቪዲዮ እስኪመጣ ድረስም አያስጠብቅም። ይሄው …..

አማራነት ይከበር!“

እና ዬአማራ ወጣቶች ዬህዝብን ድምጽ አቀንቃኝ ቢሆኑ ሊደነቅ ሲገባው ስለምን ይወገዛሉ። ዬሁሉም እምነት በውስጡ አለ። መሬት ካለው መሰረታዊ አመክንዮ መነሳት፣ ለህዝብ አንጡራ ፍላጎት ቀድሞ መሰለፍ ቢያስመሰግን እንጂ ዬሚያስወቅስ ሊሆን አይገባም። እንዲያውም ለህዝብ ዬተጋድሎ ምዕራፍ ዬተስፋ ጥግ ነው ዬሚሆነው። ይህ በራሱ ዬአቅም ቤተኝነትን ዬሚያፋፋ፤ ተጨማሪ አዳዲስ ንቁ ኃይል ፈጣሪ ነው ዬሚሆነው።  ደግሞም ብልህነት ነው። ያው አማራ ዬሚለው ዬብዙኃን ማህበረሰብ ወላዊ መጠሪያ ጎልቶ በመውጣቱ ህመም ካልሆነ በስተቀር። ወቅት እራሱ በራሱ ጊዜ ዬሚያነሳቸው ዬተለያዩ ጉዳዮች ይኖሩታል። ስለምን? ቁሞ ዬሚጠብቅ (stagnant) ዬሆነ ዬአመክንዮ ድንጋጌ – ዓለም አስተናግዳ ስለማታውቅ! „ድምፃችን ይሰማ“ ፈልጎት፤ አቅዶት ነበርን?

ያንጊዜም ጫፍ ዬረገጡ ወጀቦች ነበሩ። ለእኔ ለራሱ ከማልጠብቃቸው ሰዎች በጎ ዕይታያ እንዳቆም ያልሆኑ ስንክሳሮችን ዬደረቱልኝ ነበሩ። ግን እስከ እልፈቴ ድረስ ዬመንፈሴ ጌታ እኔ እንጂ፤ ሌላ እንዲሆን ባለመፍቀዴ በጸና ዬድጋፍ አቋሜ ቀጠልኩ። „ድምፃችን ይሰማ“ አክራሪነትን አቀንቃኝ እንዳልነበረ ሁሉ፤ ዬአማራ ህዝብ ዬህልውና ተጋድሎም ማንነትን ዬማስከበር ወላዊ ዬትግል መስመር እንጂ፤ ዬአክራሪነት መንገድ በፍጹም አይደለም።  „ድምጻችን ይሰማ“ ኢትዮጵያን ዬእስልምና እምነት ተከታይ ሀገር ለማድረግ ዬነበረ ዬእምነት ተጋድሎ ሳይሆን፣ ዬሃይማኖት ዬእኩልነት ዬመብት ንፁህ ተጋድሎ እንደነበረው ሁሉ፤ ዬአማራ ህዝብ ዬህልውና ተጋድሎ እንደ ዜጋና እንደ ህዝብ ዬመኖር ዋስትና ዬእኩልነት ንጹህ ተጋድሎ እንጂ በኢትዮዽያና በኢትዮዽያዊነት ላይ ሰይፍ ዬመዘዘ እኩይ መስመር ፈጽሞ አይደለም።

„ዬድምፃችን ይሰማ“ ንዑድ መንፈስ ዬደገፈ – ያቀነቀነ – በአክቲቢስትነት ዬበኩሉን ድርሻ ዬተወጣ ወገን ወቅት ላሰናደለት ዬትግል ምዕራፍ ይሁንታን ዬሸለመ እንጂ፤ ዬነጻነት ትግሉን ወደ ሌላ አቅጣጫ ለመዘወር እንዳላሰበ ሁሉ፤ ዛሬም ዬአማራ ህዝብ ጥያቄን አጉልተው ዬወጡ ወጣት ዬአማራ ህዝብ ዬተጋድሎ አክቲቢስቶች በወቅት አስገዳጅነት ስለመሆኑ ዕውቅናው በተገባው መልኩ ሊሰጣቸው ይገባል። በእናት ኢትዮዽያ ያልተበደለ ዬሃይማኖት ተቋማት ፈጽሞ ዬለም። በአንድም በሌላም። እንዲያውም በዓዋጅ ደረጃ „አማራንና ኦቶዶክሰን እንዳይነሳ አድርገን አርቀን ቀብረነዋል“ ሁላችንም ያዳመጥነው በተግባርም ያዬነው ነው። እንደዚህ ዘመንም ዬተዋህዶ ቅዱሳን አባቶች በገፍ ተሰደው አያውቁም። ይህም ሆኖ ዬኢትዮዽያ እስልምና እምነት ዬደረሰበትን ጥቃት ለመመከተ ከተነሳው ህዝባዊ እንቅስቃሴ „ከድምፃችን ይሰማ“ ጋር አብረን ቆምን እንጂ፤ ሌሎችም ሃይማኖቶችም እንደ እስልምና እምነት ሃይማኖት እኩል ተጨቁነዋል – „ዬድምፃችን ይሰማ“ ዬእናንተ ጥያቄ አብላጫ ዬለውም፤ ተለይታችሁ አልተጨቆናችሁም፤ አርፋችሁ ተቀመጡ – ማንም አላለም። ዬእናንተ ጥያቄ ዬዘወትር ዬሌላው ዬክት አልተባለም። ሚዛን ለራስ ነው። ይህ youtube ብቻ ዬተለጠፈም አይደለም መድረስ ካለበት ቦታ ሁሉ ዬተላከ ነው። አፍቅሮተ ማኒፌስቶን ሳይሆን ሰው መሆንን ብቻ ይጠይቅ ስለነበር።

https://www.youtube.com/watch?v=FmeGfeOaM_I

አሁን ያለው ዝንባሌ ለራሱ ለድምፃችን ይሰማ መምህራዊ አኃታዊ ጽኑዑ ዬተጋድሎ መስመር መልካም አይመስለኝም። በአማራ ተጋድሎ ውስጥ ዬእስልምና እምነት ተከታዮች አሉና። በብሄራቸው ዬጥቃቱ ሰለባ በመሆናቸው። ከተማ ብቻ ሳይሆን ገጠርም ቀላል ዬማይባል ኃይል አለ። እኔ እራሴ እማስታውሰው ጭልጋ ወረዳ 6 ምክትል ወረዳዎች ነበሩት። ሦስቱ ምክትል ወረዳዎች ቆላማ ናቸው። ዳዋ – ጫቆ – አዳኝ አገር ይባላሉ።  ከሦስቱ ውስጥ አንዱ ጫቆ ምክትል ወረዳ ሙሉ በሙሉ እስከሚያሰኝ ድረስ ዬእስልምና እምነት ተከታዮች ናቸው። ቆለኛ ደግሞ ጥቃትን ለማንበርከክ አይበገሬ ነው። እኔ ሥፍራውን በእግሬ ተጉዤ በጫቆ ብቻ ከ20 ያላነሱ ዬገበሬ መንደሮችን ተመልክቻለሁ። እርግጥ እንኳንስ ከተማ ተውልዶ ላደገ ሴት ለወንድም ከባድ ነበር ፈተናው። ሁሎችም እጅግ አስቸጋሪ ዬመሬት አቀማመጥ ነው ያላቸው።

ዬሆነ ሆኖ ጉዳትንም ጥቅምን ማመዛዘን ዬሚቻለው መጣኝ ክስተት ሲኖር ብቻ ነው። አማራነት እንደ ሌላው ብቻ ነው ዬተበደለው ማለት ለፖለቲከኞች ማኒፌስቶ ሊመች ይችል ይሆናል። ሰውን ማዕከሉ ላደረገ ቅን ግን ዬዘር ጥፋትን genocide ሰው ዬሆነበት ሚስጢር መገለጫው ዬጠፋ ስለሆነ ለንጽጽር ዬሚቀርብም አመክንዮ አልነበረም። „the deliberate killing of a large group of people, especially those of a particular nation or ethnic group“ በአማራው ላይ ይህ አልተፈጸመም? ብሄራቸው አማራ ሆነው ዬእስልምና እምነት ተከታዮች ሲጠፋ ከቶ ይሄ እምነቱንም ጭምር አላጠፋውም ሊባል ይሆን?

ዬእስልምና አማኙ ሲጣፋ በዕምነቱ ውስጥ ያሉ ዬዶግማ ዕሴቶች ሁሉ አብረው ይደመሰሳሉ። ዬት እንደ ደረሰ ከማይታወቀው 2.4 ሚሊዮን ዬአማራ ህዝብ ውስጥ በእምነታቸው ሳይሆን አማራ በመሆናቸው ብቻ በዘራቸው ምክንያት በርካታ ዬእስልምና እምነት ተከታዮችም ጠፍተዋል። ከፊት ለፊት ያለውን ዬማንፌስቶ ልዕልና ሳይሆን፤ በጥልቀት ሰው ዬመሆንን ሚስጥር በተደሞና በአንክሮ መመርመሩ ሃይማኖትንም ከጥፋት ለመታደግ፤ ዓራት ዓይናማው መንገድ ነው። በመርህ ደረጃ ሰው አልባ ሃይማኖትም፤ ሰው አልባ  አገርም ዬለም። እንኳንስ ዬዴሞክራሲ ህልመኝነት።

ሰው መሆን መፈጠር ነው። ሰውነት ፍጥረትነት ነው። ዬኃይማኖት ዕምነት ግን ዬሰው ልጅ ከተወለደ በኋላ ዬሚመጣ፤ ለአቅመ አዳም ከደረሰ በኋላ ሆነ፣ ለአቅመ ህያውን ከደረሰ በኋላ ሊለውጠው ወይንም ሊጸናበት ዬሚችል ሲሆን፤ ሰው ግን እንቁላልና ዘር በእናት ማህጸን ማደር ከጀመረ ጊዜ ጀምሮ ነው ሰውነቱ። ዬሰው ልጅ ለአቅመ አዳም ሲደርስ ሆነ፣ ለአቅመ ህያውን በስጋም ምድርን እስኪለይ ድረስ ሰው ነው። አይለወጥ፣ አይሻሻል፣ አይቀዬር። ዬመኖር ዕሴቶች ሁሉ ሰው ነው ማዕከላቸው። ኃይማኖት በጋብቻም፤ በመኖሪያ አካባቢ ተጽዕኖም፦ ወይንም በሌላ ዬኑሮ አስገዳጅነት ይቀዬራል። ሰው መሆን ግን አካባቢም፤ ጋብቻም ሆነ ሌላ አስገዳጅ ነገር ሰው መሆኑን ሊለውጠው ከቶውንም አይችልም። መምሸት መንጋትን ከፈጣሪ በስተቀር መቀዬር ዬሚችል ምድራዊ ኃይል አለን? http://www.zehabesha.com/amharic/archives/70312

ከዚህ ሌላ የፋሽስቱ ዬትግራይ ነፃ አውጪ ግንባር ማንፌስቶ ለትግል ዬተነሳበትን መሰረታዊ ዓላማ አስኳሉን ቁጩ ብሎ፤ ከልብ ሆኖ መማር ያስፈልግ ይመስለኛል። መሰረታዊ ችግሩ ላይ ተነስተን ዬመፍትሄ ጉዞውን ስላልጀምርን ነው 26 ዓመት ሙሉ ለአውሬ ድርጅት ግብር በማቅረብ ብቻ ስንዳክር ዬኖርነው። አማራጭ መንገድ አልዘረጋነም። ለአንድነት ኃይሉም ዬትግራይ ነፃ አውጪ ግንባር ዬአማራ ህዝብ ፍልሰት ቁርሾ ከሥሩ ለመንቀል ዬማንፌስቶው ዓላማ አንኳሩ አድርጎ በዚህ ዙሪያ ዬሰራበት ምንም ዬፖለቲካ ክንውን ስላልነበረው ተስፋን በዘላቂነት ማቆም አልተቻለውም። አቅም ያነሰው ከህዉሓት ከጭንቅላቱ ከግማቱ መነሳት ባለመቻሉ ነው። እንዲያውም በአስታማሚነትና በሽፋን ሰጪነት ሲድበሰበስ ነው ዬተኖረው። ስለሆነም ዛሬ አዲስ መንገዶችን ወቅት ቀይሷል፤ አቅም ያለው በዛ መሰለፋ አማራጭ ዬመዳኛ መስመር ነው። ዬአማራ ተጋድሎ ዕውቅና መነፈጉ ትናንት በጥንካሪያቸው ልዩ አክብሮትና ጸጋ ላጎናጸፍናቸው ዬእውነት አርበኞች ጉዳይ መሆን ሲገባው፤ እንዲህ ሆኖ ማዬትና መስማት ለነገ መልካም ስንቅ አይሆንም። ዬሆነ ሆኖ ለዚህ ተጨማሪ ህመማዊ አመክንዮም ማጠናከሪያ ጭብጥ ማቅረብ እሻለሁ። በጥቂቱ  ….

ፍጥጫ።

አራባ ዓመት ያስቆጠረ ድርጅት ተቀብሎ – አዲሱን አልቀበልም ማለት በአርባ ዓመት ውስጥ ዬተወለደ ልጅ – ያደገ ልጅ ዬለም እንደ ማለት ነው። ዬዕድገት ሂደትን መቃረን ዬተገባ አይመስለኝም። ዬአማራ ትውልድ ለዘመናት ዬለም ማለትም ነው። ይህ ዬታቆረ stagnant ንድፈ ሃሳብ ዝቅ ሲል ዬማህበረሰብ ሥነ – ህይወታዊ፤ ተፈጥሯዊ ድንጋጌ ከፍ ሲል ብዙ ተባዙ ምድሪቱንም ሙሏት ቃለ እግዚአብሄርን ይፈታተናል። በሌላ በኩል አማራ ዬሚባል ነገር ዬለም¡ በሌለ ነገር ዬሚወከል ነገር ዬለም¡ ዬለም¡ „ ዬሚለውን ዬተከበሩ ፕ /መስፍን ወ/ ማርያም ግዑዝ መንፈስ ስልብነትን ያመለክታል። ይህ ደግሞ አይቀሬ ነው። በአልሞት ባይ ተጋዳይነት ያለው ዬእሳቸው ጭንጋፍ ጽንስ ዕሳቤ ነውና። መስራች ናቸው ለአማራ ዬለም ሂትለራዊ ዓውራ መንገድ። በዚህ ውስጥ ዬእስልምና እምነት ተከታዮች አማራዎችም አሉ፤ ለዚህ ሥነ – ልቦናዊ ግድለት ዬተጋለጡ።

https://www.youtube.com/watch?v=CmdgqTwSkQY

ዬጥላቻም አለው ዓይነት  „ነገር“ አስተውሉ ቅኖች ወገኖቼ „ነገር“ እንጂ ነገድ አላሉም። እኛ እንደ እሳር – እንደ ቅጠል- እንደ ዬቤት ውስጥ ቁሳቁስ ነው ዬታዬነው። እንደ ዬቤት ውስጥ ለማዳ እንሰሳዎች እንኳን ሊዩን አልፈቀዱም፣ እንኳንስ እንደ ሰው። ዬእሳቸው ጭንጋፍ ጽንስ ጥንስስ መንፈስ ባለበት ማናቸውም ተቋም ይሄ ገዳይ ትልልፍ ይኖራል። ዬእሳቸው ግዑዝ ዕሳቤ ለዘብሄረ አማራ ህዝብ ሂትለሪዝም ነው። አንድም ዬሌላ ብሄረሰብ ሙሁር ይህንን ጉዑዝ መንፈስ አደባባይ ወጥቶ ዬሞገተ ዬለም። ሌላው ቀርቶ ከአማራ ጋር ተጋብተው ዘር ዬተኩት አባና እማ ወራዎች ልጆቻቸው ከእንሰሳ በታች መታዬታቸው አላቀጠላቸውም። አላርመጠመጣቸውም። ልጆቻቸው ከትውልደ – ኢትዮዽያዊነት ማዕቀፍ መፋቃቸው አብራካቸውን ሆነ ማህጸናቸውን ዬጥቃቱ ቋያ አላርመጠመጠውም። ኢትዮዽያዊነት በዚህ ፍዳ ዉስጥ ነው ያለው።

ከቶ ዬወላጅ ለልጅ ዬሚሰጠው ፍቅር እንዴት ይገለጽ? ከዘብሄረ አማራ ዬተፈጠርክ ግን ዬሌላ ብሄርና ብሄረሰብ ደም ያለህ ውስጥህ ሲፈጠር አንዱ በአነት ሌላው በአልቦሽነት ነው። ግማሽ ነህ ማለት ነው። ከሌላው ብሄርና ብሄረሰብ በደምህ ዬወረስከው ብቻ አንድ ኩላሊት፣ ግማሽ አዕምሮ፤ ግማሽ ትንሽና ትልቅ አንጀት፤ ግማሽ ግማሽ ሳንባና ጉበት፣ ግማሹ ደምህ ሆነ ፕላዝማህ ግማሹ ዬሰው ዓይነት ሌላው ዬቅጠል ወይንም ዬሳር ነህ፤ ሴትም ከሆንሽ ዬእንቁላል ቤትሽ አንድ ነው ወንድም ብትሆን ዘር ማፍሪያህ እንዲሁ፣ ይህን ጸረ ሰብ ፍልስፍና አንድ ልጅን ጸንሳ ለምትወልድ እናት ከበደሉ ሁሉ እጅግ ዬከፋ እናታዊ ሰማያዊ ጸጋዋን ዬሰረዘ፣ በሥነ – ልቧናዋ ላይ ጢባ ጢቦ ዬተጫወተ፣ ትውልድን አምካኝ ዬናዚዚም ቅርሻም ፍልፍስፍና ነው። ለዚህም ነው ተጋድሎው ዬህልውና ሊባል ዬሚገባው። ተወደደም ተጠላም ተጋድሎው ዬአማራ ህዝብ ዬህልውና ተጋድሎ ነው!

ሃቅን አትፍሩ!

ሃቅን አትፍሩ። ሊያስማማ ዬሚችለው ዬሃቅ ድልድይ ብቻ ነው። ይህ ሃቅ ተፈልፍሎ፣ ተብጥሮ ምርምር ላይ መዋል ካልቻለ – አደጋው ሰፊ ነው። ባሳለፍናቸው ዬነፃነት ትግል ዘመናት ሁሉ ያለአንዳች ዬማዕቀብ – እገዳ በሉን በሚባለው ስም ሁሉንም እንደ ፍላጎቱ ዬት ነህ? ወዴት ነህ? ማነህ? ሳንል በሥሙ ስንጠራ ኑሮናል። ኢዲሃቅ፣ ኢአግ፣ ኦነግ፣ አግ7፣ መድህን፣ መኢህድ፣ ኦዴፍ፣ ኢህአፓ፣ መአህድ፣ ህብረት፣ መድረክ፣ አርዱፍ፣ ቀስተ ዳመና፣ ኢዲአፓ፣ ቅንጅት፣ አንድነት፣ ሰማያዊ፣ መኢሶን፣ ህውሓት፣ ደቡብ ህዝቦች፣ ኦፌኮ፣ አረና፣ ቲፒዲኤም፤ ሸንጎ፣ ትዴት ጥምረት፣ ግንባር፣ ሀገር አድን፤ ሀገራዊ ንቅናቄ፣  … ወዘተ …  ወዘተ …  ወዘተ …

ዬምሳሳላችሁና ዬምናፍቃችሁ ዬሀገሬ ልጆች ….

አንዱ ዞግ ከስድስት ያላነሰ ዬፖለቲካ ድርጅት ስለአለው ዬማስታውሳቸውን ብቻ ነው ለናሙና ዬጻፍኩት። ስለሆነም ያልፃፍኩት ከጻፍኩት ስለሚበረክት እንደማትከፋብኝ አስባለሁ። ይቅርታ መጠዬቅ ካለብኝም ይሄው ዝቅ ብዬ ይቅርታ ጠዬኩኝ። ዬሲቢክስ ድርጅቶችም ዬዚያን ያህሉ በርካታ ናቸው። ሁሉሙ ጥሩን ባሉት ሥም ሲጠሩ ኖሩ። ከአማራ ተጋድሎ በኋላ ዬተፈጠረው ሀገራዊ ንቅናቄ ዕውቅና አግኝቶ በነፃነት እዬተንጎራደደዬአማራ ተጋድሎ ዬከፋኝ ሠራዊት ለማለት አቅም ከዬት ይሸመት? አቅም ከዬት ይምጣ? ግርም ዬሚያደርግ ጉድ። ከተግባራዊ ዬታሪክ ዓውድ ጋር ግብግብ። ስለምን መሬት እዬደበደብን ዬሃሳብ ጦርነት በዬዓመቱ እንዲህ እንደምንናፍቅ አይገባኝም። ይህን ቅራኔ በአግባቡ ማስተዳደር፥ መምራት ያቃተን ዬሁሉም ዬችግር ዓይነት መሞከሪያ ጣቢያ ዬሆነችው ዬሃገራችን ዬኢትዮዽያ ዬፍዳ መፍቻ አስገኝ አቅምን ከዬት ልንሸምት እንዳሰብን አይገባኝም።

ዬብልህነት – ፍድሰት።

ለህልውና ዬሚደረግ ተጋድሎ እንደ ሰው መፈጠርን ብቻ ነው ዬሚጠይቀው። ይሄን ተቀብለው ቅን ዬሶሊዳሪቲ ስንቅ ዬሆኑ ዬኦሮሞ ማህበረሰብ ንቁ አክቲቢስቶች ወገኖቻችን ዬሚሰጡት ዕውቅና ዬመንፈስ ስንቅነቱ በአውታንዊነት – በፍቅራዊነት መንፈስ ሊስተናገድ ሲገባ፤ ዬአማራ ወጣቶች ሳይቀሩ ትልቁን ዬፖለቲካ ትርፍ ሲጠምዝዙት ይታያሉ። ይሄ መሬት ላይ ዬተደመጠውን ዬደም አጋርነት ውል በንቀት መጠቅጠቅ ነው። ከሊቅ እስከ ደቂቅ ያለው መታመስ መሰረቱ ወቅትን ያለማዳመጥ ዬፈጠረው ዬአስተሳሰብ ድህነት ነው።

ኋላቀርነት ማለት ዬኤኮኖሚ እድገት አለመመጣን ብቻ አይደለም። በሁሉም ዘርፍ ያልተመጣጠነ ዬአስተሳሰብ እድገት ድህነት ማለት ነው። ዬህዝቡ ማህበራዊ ንቃተ ህሊና አለቃነት እና እኛ ወቅትን አንብቦ ዬመረዳት አቅማችን ገና አልተፈጠረም ልበል ይሆን? እንዴት ከጎንህ ነኝ ያለን ተናፋቂ – ዬተሰበሰበ ዕምቅ ኃይል ለራስ ጥቅም ዬታሰበ (hayjac) ተብሎ በዚህ ተልካሻ ጥርጣሬ እንዲጠቀለል ይፈለጋል?

ሌላው ዬትልቅ አካል ውክል ቤቱ ድረስ ሄዶ ዬመደጋገፍ መስመር ለመዘርጋት ይማስናል፤ ለአማራ ተጋድሎ ደግሞ በማቅረብ ቅን መንፈስ፤ በራስ አነሳሽነት ቤት ድረስ ዬመጣን ወርቅ በማጣጣልና በማቃለል ማፍሰስ። በሞትና በህልውና መካከል ያለውን መንፈስ ዕውቅና መስጠት ሰባዕዊነት እንጂ hayjac አይደለም። ዬሁለቱም ግዙፍ ማህበረሰቦች ዬኦሮሞ ዬአማራና ኮንሶ ሌሎችንም አክሎ አዲስ ቀንበጥ ትውልድ ጥፋት እዬተፈጸመበት ነው። ያገናኛቸው ዬጋራ መከራ ዬዕንባ ምጥ እንጂ ዬታሪክ ቀረመትነት በፍፁም አይደለም። አልነበረም። እኛ እኮ ችግራችን ይሄው ነው። በጎ ለሚያስብ ምስጋና ቀርቶበት መብጠልጠሉ ቢቀርበት ምንኛ ዕድለኝነት በሆነ ነበር። ዬአማራ ዬነፍስ ግቢ ውጪ ተጋድሎ መከራ ላይ ሆኖ ዘመናይነት? ትርፉ ለማን?  ወደ አብሮነት ዬሚያመጣው ቀጥተኛ መንገድ ስለምን ተፈሪም – አሉታዊ ለጠፍም እንደምናበረክትበት ግራ መንገድ ነው።

እስኪ ምን አለ አክቲቢስት ጆዋር? እኔ ወደ 9 ጊዜ አዳምጨዋለሁ። አማራ ዬራሱን ሀገር መመስረት አለበት አለን? ስለ አማራ አደረጃጀቱ ቀመረ? ስለ ታክቲክና ስትራቴጂ ለአማራ ማህበረሰብ ንድፍ ቀዬስ? እኮ! ምን አለ ጆዋር? በፖለቲካ ቋንቋ ዬአማራ ተጋድሎው መሬት ላይ ያለበትን ተጨባጭ ሁኔታ ነው ዬገለጸው። መገፋቱን እኮ ይሄው እኔም በተከታታይ እዬፃፍኩት ነው። ለሌላው ትናንት እንደ አደረኩት ሁሉ።

አክቲቢስት ጆዋር? ተደማጭነቱን ያስገኘው በጭብጣዊ ዕሴቱ በአቅሙ ነው ዬገነባው፤ በተመሳሳይ መንገድ ተሂዶ ሆነ ተሻለ በሚባለው መንገድ ተጉዞ ተደማጭነትን ማብቀል ይቻላል። ኢትዮዽያ ያለባት መከራ ዕልፍ ስለሆነ አንዱን ዘርፍ ሳያረገርጉ ሞጥሮ ይዞ ዬሚመጥን አቅም መፍጠር ሲቻል፤ ውሃ በቀጠነ ዬቃላት ቃታ ስበት ዬራዕይ ገዳይ ይመስለኛል – ለእኔ። ለውድድር ዬሚያበቃ አቅም አምጦ መውለድ፤ አትራፊ መንገድ ቀይሶ ተደማጭነትን ማጽደቅ። ችሎታው ካለ።

ባለፈው ዓመት ዬኦሮሞ ፕሮቴስት አክቲቢስት ጆዋር መሃመድ ዬመንፈስ ሃብት እንዲሆን እንዲሁም ተቀባይነቱም እንዲጎላ ሰፊ ዘመቻ ነበር። በዐውራው ፓርቲ መሪዎችም ሆነ ሚዲያ፤ ዘንድሮም ያዬነውን አይተናል  – አዳምጠናል። ዛሬ አክቲቢስት ጆዋር መሃመድ እንደማንኛውም ኢትዮዽያዊ ዬፖለቲካ ፍሬ ነገር ደፍሮ ወጥቶ በአማራ ጉልበታም ተጋድሎ ዙሪያ ፖለቲካዊ ትንተና መስጠቱ፤ በተለይ ዬአማራ ተጋድሎ አቀንቃኞች ሊያከብሩት ሲገባ – በተጻራሪነት ቁሞ ተቃርኗዊ ዘመቻ መክፈት መሬት ላይ ያለውን ዬህዝብ ፍላጎት ከመርገጥ ለይቼ አላዬውም። ለመሆኑ ምንድን ነው ዬሚፈለገው?

… ለነገሩ በተለምዶ ፖለቲካ ዬቅራኔ አያያዝ፤ አፈታት፤ አስተዳደር፤ ዬዓላማ ስልትና ስትራቴጅ ቅኝት፤ ዬውሳኔ አቅም ፍላጎትና አቅርቦት – መምራት፤ ዬአቅም ዕውቅና እና ስምሪት ሳይንስነት ከሜዳ አይታፈስ ነገር። ሳይንሱን በተፈጥሮ መክሊት ወይንም በዕድሜ ጠገብ ተመክሮ ወይንም በቀለም ዕውቀት ካልተገራ ብስል ከጥሬ መሆኑ ሳይታለም ዬተፈታ ነው። አዳጋሚ ሸጎሪያዊ መከራ። አቅምን ከሚያቀጭጩ አሳማ ዕሳቤዎች ብንታረም መልካም ነው። ለትግሉ በጭራሽ ቤሳ ቤስቲ ጥቅም ዬለውም።

ሰማያዊ መፍቻ።

ፋሽስቱን ወያኔ ጨምሮ ዬአብዛኞቹ ሊሂቃን መስጥረው፣ ከብክበው ያቆዩት መተንፈሻ ቧንቧ ነበራቸው። ዬዘብሄረ አማራና ዬዘብሄረ ኦሮሞ ዬትውልድ ዬታሪክ ትርምስ። ዬነፍስ ቃጠሎ፤ ዬአብሮነት መንፈስ መፈንቅለ እኩይ ግዞት። ከሰማይ ሰማያት መፍቻ እንሆ ተላከ። ዬኢትዮዽያ አምላክ ብይኑን ሰደደ። ሰው ሰራሹን ዬጥፋት ዘመን እና ክሰሎችን ነጎድጓዱ – ደመሰሰ። ይህን ጻድቅ ዬሰማይ ድምጽ ጆሮ ያለው ሰማ። „ዬኦሮሞ ወገኔ „ ተናጠላዊ አልነበረም።  ዬኦሮሞወገናችን ደም ዬእኛም ደምነው።“  „በኦሮምያ ዬሚፈሰው ደም ይቁም!“  ፖለቲከኛው አቶ አንዷዓለም አራጌ እያለ – እስር ቤት ዬሚማቅቁትን ዬአብራክ ክፋይና ዬማህጸን ፍሬ እጅግ በርካታ ዬአማራ ልጆቹን ብቃትና ክህሎት አሳምሮ እያወቀ፤ ያስቀደመው „መሪዬ በቀለ ገርባ ነው አለን። ከድንቅ በላይ አልማዛዊ – ማስተዋል። ይህ እኮ ዬደነደነው ዬሁላችንንም ዬድንጋይ ልብሱን ልብ መንፈስ – ፍርክክስ አድሮጎ ትቢያ ነው ያረገው። ከምፅዋ እስከ ካናዳ ዬተዘረጋውን ጋኔላዊ መንፈስም ድራሹን ነው ያጠፋው። አዎና!  በቃ! ለዚህ መጣፊያ ጨርቅ ድሪቶ አያስፈልገውም። ሲያናክስ ዬኖረው ሁሉ ደብቁኝን ዬሙጥኝ አለ። „ዬቡርቃ ዝምታ“ ዬ16ኛውና -17ኛውና ክፍለ ዘመን ዬኢትዮጵያ ርዕሰ መዲና ላይ ጋዬች። ሥርዬቱ ዬእዮር ሆነ። ዬልጅ ተክለሚኬኤል አበበ ዬሰሞናቱ ብዕርና ብራና ዬግርሻ እብደትም ይሄው ነው። ነገም ዬሁለቱ ማህበረሰቦች ውጊያ ተናፋቂ ነበር። እሳቱን እዬቆሰቆሱ – እያነደዱ ሌላው ማገዶ፤ ፖለቲከኞቻችን ደግሞ ዬግል ሌጋሲን ሀውልት መገንባት። ቁምጥ ይባልለት ዬነበረውን እኩይ ህልም ወቅት አፈር ድሜ አስጋጠው። ተመስገን።

ብልሆች ተደሞውን ከውስጣቸው ሆነው አድምጠው ከአዲሱ ዬለውጥ አብዮት ጋር እዬተጓዙ ነው። ትርፋም ሀገራዊ ነው። ፍቅር ብቻ ነው ዬራዕይ ልዩ ወታደር – ለእኔ። ህሊናቸው ዬብልህነት አዝመራ – ገብ ለሆኑት ዕንቁ ነው። ዘብም ይቆሙለታል። ሥጦታው በሰው እጅ አልተጠፈጠፈም። ሃምሳ ዓመት ከእንግዲህ ወዲያ ቢደከም ይህን መሰል ቅዱስ ሰብል ተንበርክኮ ማፈስ አይቻልም። ለዛውም በእኛ ነቀል ተከል ዬፖለቲካ አቅም። ዬህሊናን ብቃት በፖለቲካ አስተሳሰብ መሰረት በማስያዝ እረገድ ከቶ ዬትኛውን አመክንዮ ይሆን በተከታታይ ዬሰራንበት?? አለን? አፍ ሞልቶ ዬሚናግር ተግባር? ሌላው ቀርቶ በጥናትና በዕውቀት ላይ ዬተመሠረተ፣ ዬትኛውንም ዬወጀብ ዓይነት መቋቋም ዬሚያስችል ለአባላቱ ሰሚናር፤ ወርክሾፕ ያዘጋጀ ድርጅት እኔ ሰምቼ አላውቅም። ዬማከብራችሁ እናንተስ ሰምታችሁ ታውቃላችሁን?

ከእኛ ይልቅ መሬት ላይ ያለው ጎምዛዛ መከራ ዬደከመበትን ብቁ ፍሬ አፍሶበታል። አሁን ዬሚታዬው ጦርነቱም መከራውን አዬር ላይ ከአንተ በላይ በርቀት አድምጫለሁና ምርጥ ዘሩ ለእኔ ይገባኛል ነው። ራፖሩም ይሄው ነው። ዬሰማዩን መፍቻ ለሚረገጡ ሁሉ ልብ ይስጣችሁ እንላለን እኔና ብዕሬ። ኢትዮዽያ ወደ እግዜብሄር እጇን ዬዘረጋችበት ዬህማማት ዘመኗ ዬመጀመሪያው መፍቻም ነበር። ማስተዋሉን – ቢሰጠን። በእያንዳንዱ ዬገጠር መሬት „በቃኝ!“ እንዲህ ሲሰማ ለእኔ በህይወቴ ዬመጀመሪያው ነው። ትንግርት!

መምህሩ ወቅት ነው። ነብዩም ወቅት ነው። ሐዋርያውም ወቅት ነው። ወቅትን ማድመጥ ዬተሳነው መንፈስ እዬተንጠባጠበ በዬፌርማታው ይቀራል። ከወቅት ጋር መጓዝ ያሰኘውም ደግሞ ዳዋን እዬጣስ ዬመንፈስ ማርና ቅቤ ከምታስገኘው ማማ በአሸናፊነት ይደርሳል። ይህ ዬሂደት ሥጦታ እንጂ ዬቀንጣ ነፍስ ልዩ በረከት አይደለም። ዬብዙኃን ተጋድሎ ያስገኘው ኃብት። ልዩ ዬነፃነት ሥጦታ ነበር። ብናውቅበት።

ዕውነት ለወቅት አናባቢ vowel ናት።

ወቅት በነፍሱ ትንፋሹ ዕውነት ነው። ስለሆነም ዕውነት ለወቅት ፈርጡ ናት። እውነት አትማርትም  – ትነጥራለች። ዕውነት ዘበኛ አያሻትም፤ ለራሷ ዘብ ዬመቆም ኃያል አቅም አላት። እውነት ዓራት ዓይናማ ተናጋሪ፣ ገሪ አደብ ዬገዛች ብቁ አድማጭም ናት። እውነት አታረጅም፤ እያሸተች ዬምትሄድ ዬድርጊት አርበኛ ናት፤ ዕውነት ተሸንፋ አታውቅም – ዬምታሸንፈው በአደባባይ በገላጣ ነው። ዕውነት ሽፍንፍን – ሽጉጥጉጥም አይደለችም፤ ዬአደባባይ – ጠኃይ ናት። ዕውነት ችሎት ናት – ሚዛን። ዕውነት ርትህ ናት – አድሎ ዬሌለባት። ዕውነት ብልጥ አይደለችም ዬፍቅራዊነት ሩኃዊ አደራጅ ስልት እንጂ። ዕውነት ፊደል ናት መምህር። ዕውነት ለወቅት አናባቢው vowel ናት – ቋንቋ!  ዕውነት ፈርኃ እግዚአብሄር አላት – መጋቢዋ ቃለ አምላክ ነውና!

 

አትቀመሽ ኃይለኛ ነሽ ——ሽ

አትጠጪ መራራ ነሽ፣

አትዋጭም ጎምዛዛ ነሽ፣

ዕውነት ደፋር ካላገኘሽ

ቃና ዬለሽ ትሆኛ-ለሽ-ሽ-ሽ-ሽ-ሽ-ሽ-ሽ-ሽ-ሽ-ሽሽሽሽሽ ….

 

መቋጫ።

ራዕይን በርስትነት ለመያዝ ማሰብ ሃቅን ያልደፈረ፣ ዬሰውን ልጅ ዬማሰብ ጸጋውን ዬሚጠቀጥቅ ህግ አልቦሽ መንፈስ ዬወለደው ዬኢጎ፤ ዬግል ሌጋሲ ዕዳ ነው።  ሰውስ ቢያንስ – ቢያንስ ምን አለ ለወቅት ይሉኝታ ቢኖረው? ወቅት እራሱን ዬሚገልጸው ለአድማጬ ብቻ ነው። ወቅት ዕውቅና ዬሚሰጠውም ለአክባሪው ብቻ ነው። ወቅት ትርፋማ ዬሚያደርገውም ለአፍቃሪው ብቻ ነው። ወቅት ውስጡን ዬሚሸልመው እሱን ሊተረጉሙት ለፈቀዱ ቅኖች ብቻ ነው። ዬወቅት ዬማስረጃ ሰነዱ ህዝብ ብቻ ነው። ከህዝብ ውስጥነት ላለመውጣት ልዩ ጥረት ማድረግ ይገባ – ይመስለኛል። ከወቅት ሥህነ – ህይወት ጋር መተላለፍ ለሁሉም አይበጅም።

ኃላፊነት ዬሁሉም ኃላፊነት ነው!

ለዬኔታ ጊዜ ለጥ ብዬ ምስጋና አቅርቢ ልሰናበት –  መሸቢያ ጊዜ።

እግዜብሄር ይስጥልኝ።

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.