ኢትዮጵያዊነትን ከአማራው ሕዝብ አእምሮ የማጥፋት ዘመቻ አዲሱ የወያኔ ስልት – ሰርጸ ደስታ

ወያኔ አጋሯ ከሆነው ኦነግ ጋር ቅድሚያ ሰጥታ የሰራችው ነገር ቢኖር የኦሮሞን ሕዝብ ከኢትዮጵያዊ ማንነቱ ማምከን ነበር፡፡ ይህ ካልሆነ ግን አደለም መሀል ኢትዮጵያ አዲስ አበባ አሁን እያከናወነ ያለውን ድርጊት እየፈጸመ  ከተነሳችበት ደደቢትም ቦታ እንደማይኖራት ጠንቅቃ ታውቀዋለች፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ ሙሉ ኢትዮጵያዊነት  ይዞ እነኳንስ እንደልብ መፈንጨት አንገትን ቀና አድርጎ ሕዝብን መገላመጥ እንኳን  ለወያኔ ባልተቻላት ነበር፡፡ የሆነው ሁሉ ግን ያሳዝናል ያሳፍራል፡፡ ዛሬ ወያኔ ራሷ ጠፍጥፋ የሰራችው ትውልድ እንዳፈራች ስለምታውቅ የኦሮሞው ጉዳይ ብዙም አላሳሰባትም፡፡ አደገኛ ስጋት የሆነባት ከ25 ዓመት የጎሳና የጎጥ መከፋፈል ሥራዋ በኋላ የኢትዮጵያዊነትና አንድነትን ወኔ በብዙዎች ዘንድ የቀሰቀሰው እንደ ጎንደሬዎቹ አይነት ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ ጎንደሬዎቹ የኦሮሞ ሕዝብ ደም ደማችን ነው ብለው በመሀል ታሪካዊ ከተማቸው አደባባዮችና መንገዶች የኦሮሞ ሕዝብ የነጻነት እውነተኛ ታጋይ የሆኑትን የበቀለ ገርባን ምስል ከፍ አድርገው ያነሱባት ነበረች ወያኔን ከምንም በላይ ያስደነገጠቻት፡፡ ልብ በሉ፡፡ ወያኔን ብቻ አደለም ብዙ የዘረኝነት ልክፍት የተጠናወታቸውን የኦሮሞ ኢሊቶችንና ድርጅቶችንም አስደንግጧል፡፡ ለኦሮሞ ሕዝብ ዛሬ አቅመቢስ መሆንና ማንነቱን አጥቶ የባዘነ ማንም እንደልቡ የሚዘውረው ለማድረግ የኦሮሞ ነን በሚል ሽፋን የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶችና እንዲሁም ግለሰቦች ምክነያት እንደሆኑ አስተውሉ፡፡ የኦሮሞን ሕዝብ የኢትዮጵያዊ ወኔ መሠረቱን ከሥሩ ለማጥፋት ደግሞ የተጠቀሙበትን ሂደት አስተውሉ፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ የኢትዮጵያዊ ማንነት ባለቤትነቱን ለማጥፋት የሚኒሊክን ታሪክ ኢላማ ማድረግ ነበረባቸው፡፡ ይህ ታሪክ በእርግጥም በዘመናዊቷ ኢትዮጵያ የኦሮሞ ሕዝብ የበላይነት የነበረውና ትልቁን ሥልጣን የተቆጣጠረበት ነበር፡፡ በአንጻሩ  ይህ ታሪክ  ወያኔ የእኔ የምትለውን የአጼ ዮሐንስን ስልጣን የቀማ ብላ ስለምታስብ ይህን ኦሮሞዎች የበላይ የሆኑበትን ታሪክ አትወደውም፡፡ ከዚያ በላይ ኢትዮጵያዊያንን ሁሉ አንድ ያደረገ ልዩ የአንድነት መንፈስ ያለው ታሪክ ስለሆነ ወያኔን ያስፈራታል የሚኒሊክ ሥም ሲጠራ ያስበረግጋታል፡፡  ይህን ታሪክ ልክ ወያኔዎችን እንደሚያስፈራቸው በኦሮሞውም ሕዝብ አእምሮ የእነሱን ፍራቻና ጥላቻ በማሳደር የአሮሞን ሕዝብ ከዚህ ታሪክ ማላቀቅና ኢትዮጵያዊነቱን አምክኖ ዛሬ እንደሚዘውሩት ለማድረግ ይረዳቸው ዘንድ አጋር ያስፈልጋቸው ነበር፡፡ ለዚህ ኦነግ ሁነኛ አጋራቸው ሆኖ አብሯቸው የኦሮሞን ሕዝብ ከኢትዮጵያዊ ማንነቱ ማላቀቅና ማምከን በመጨረሻም አቅመቢስ ሆኖ ተገዥ ለማድረግ 25 ዓመት አብሯቸው ሰርቷል፡፡ አሁንም ኦነግና ኦነጋውያን እያደረጉት ያለው ይሄንኑ ነው፡፡ ኦነግና ኦነጋውያን ለወያኔ አስበው ሳይሆን እነሱም የራሳቸው ሴራ በዚህ ሕዝብ ላይ ስላላቸው ነው፡፡ በመሠረታዊ ዓላማ ከወያኔ ጋር አንደ ናቸው፡፡ በመሆኑም በይፋና በድብቅ እስካሁን ሲተባበሩ ቆይተዋል፡፡

ስለዝህ ጉዳይ በቀደሙ በርከት ያሉ አስተያየቶቼ ብዙ ስላልኩ ብዙ አልልም፡፡  መነሻ ወደ አደረኩት የአማራን ሕዝብ እንደኦሮሞው ሁሉ ከኢትዮጵያዊ ማንነቱ አምክኖ እንደልብ ለመዘወር አሁን እየተደረገ ያለውን ጥረት እመጣበታለሁ፡፡ ለማስተዋል ይረዳ ዘንድ ግን እንዴት ሊሆን ይችላል ብላችሁ ማመን እስከሚያቅታችሁ ድረስ የሚሰሩ ሴራዎችንና ድራማዎችን ልጠቁም፡፡ ወያኔ ለድራማዋ እንዲያመቻት የራሷን ሰዎች ብዙ ዓመት ሳይቀር በእስር አቆይታ በኋላ ተቃዋሚ በማስመሰል በሕዝብ ዘንድ ወዥንብር ለመፍጠር የምትጠቀምባቸው አያሌ ግለሰቦችና የድርጅት መሪዎች እንዳሉ ብዙዎች ያውቃሉ፡፡ አሁን ትልቁን የወያኔን ሥራ እየሰሩ ያሉት እነዚህ ግለሰቦች ናቸው፡፡ ከዚያም በላይ ግን የሚደረግ ድራማ አለ፡፡ የሶማሌው የአልሸባብ ድራማ አንዱ ነው፡፡ ልብ በሉ፡፡ ለኢትዮጵያ ሶማሌ ችግር እንደሆነች አልዘነጋሁትም፡፡ እንደውም የኦነግና ኦነጋውያን የወደፊት ሕልምና ዛሬም የሚሰሩት ሴራ በዚሁ በሱማሌ በኩል የእስልምና ጽንፈኝነትን ወደኢትዮጵያ ማስገባት ነው፡፡ ኦሮምያ ለኦሮሞዎች የሚለው ቡድን ዋነኛ አላማው ይሄ ነው፡፡ ይሄን ከ1960ዎቹ መጨረሻ የሶማሌ ወረራ ጀምሮ የቀጠለ ሂደት ነው፡፡ ዛሬ ወያኔ የአሸባሪ ቡድን የመከላከል አጋር የሆነችበት ሂደት ግን መሠረታዊ አላማው አሸባሪን ለመዋጋት ሳይሆን የራሷን እድሜ ለማራዘም ነው፡፡  ይሄ ለብዙዎች ግልጽ ነው ልዝለለው፡፡ ለብዙዎች እንቆቅልሽ የሆነው ግን የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ጉዳይ ነው፡፡ ብዙዎች እንደሚመስላቸው እውነተኛ ጦርነት አልነበረም፡፡ የዛን ሁሉ ሕይወት የቀጠፈው በዘመናችን አሳቃቂ የተባለው እንደዚያ ያለው ጦርነት ድራማ ነበር ቢባል ማን ሊያምን ይችላል፡፡ ያ ጦርነት የመለስና የኢሳያስ መሪተዋናይነት ሥብሐት ነጋ የደረሰው ድርሰት ድርሰት እንደነበር ማመን ያስቸግራል፡፡ በዚያ ጦርነት የሆኑትን ክስተቶች መለስ ብለን ስናስተውል ግን እውንም ድራማ እንደነበር እንረዳለን፡፡  በዚያ ጦርነት የኢትዮጵያ ሠራዊት  ኢሳያስን ለመያዝ የሚችልበት እድልና አቅም በአገኘበት ወቅት ወደ ኋላ እንዲመለስ ትዕዛዝ መሠጠቱ ሳያንስ ሲመለስ ሆን ተብሎ እንዲያልቅ ተደርጓል፡፡  በዛው ጦርነት አሰብን መያዝ የሚያግድ ነገር አልነበረም፡፡ ኋላም ወያኔዎች እንደሚሉት ሳይሆን አሰብን ለደሕንነት ሲባል መያዝና በኢትዮጵያ ቁጥጥር ሥር ማቆየት አንዳችም አለም ዓቀፋዊ ሕግን ማፍረስ አልነበረም፡፡ የዓለም አቀፉም ማሕበረሰብም ቢሆን በዚህ ጉዳይ ኢትዮጵያ ላይ ጫና የሚፈጥርበት አንዳችም ምክነያት አይኖረውም፡፡ ይልቁንም ከኢትዮጵያም በአለፈ ለቀጣናው በሙሉ የደህንነት ሥጋት መረጋጋት ሲባል በኢትዮጵያ እጅ አሰብ መቆየቱ የብዙዎችን ድጋፍ ባስገኘም፡፡  አልሸባብን በመዋጋት የአሸባሪነት መከላከል ተባባሪ ለመሆን በተሻለ ትልቅ ፖለቲካዊ ዕድልንም በፈጠረ ነበር፡፡ በአሰብ ምትክ ማንነቷን የማናውቃት በእርግጥም ኢትዮጵያ ትሁን ኤርትራ የማትታወቀው ባድሜ ትልቅ መደራደሪያ ሆና ዛሬም የደራማው ዋና ገጸ ባሕሪ ሆና ቀጥላለች፡፡ ይህ እንግዲህ ማስተዋል ባለመቻላችን እየሆነ ያለው ለሴራቸው መሳካት ሲሉ ሴረኞች አስከምን ድረስ እነድሚሄዱ የሚያሳየን ድራማ ነው፡፡  ዛሬ ብዙዎች በየአገሩ የወያኔ ተቃዋሚ በሚመስል ለወያኔ ዋነኛ አገልጋይ እንደሆኑ ማስተዋል ካልቻልን ለወያኔ የድራማውን ድረሰት እያቀለልንለት ነው፡፡

ከዚሁ ጋር በተገናኘ በውጭ ለሚኖረው ዲያስፖራ ሁሉ የተወሰኑ ጥያቄዎችን ላንሳ፡፡ ለመሆኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጫፍ እስከጫፍ ተነስቶ ወያኔን ትንፋሽ ባሳጣበት ወቅት በየአደባባዩ ሰላማዊ ሰልፍ እያለ ሲጮሕ የነበረው ዲያስፖራ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ አስቸኳይ በሚል የክተት አዋጅ በይፋ ታውጆበት ሲገደልና ሲታሰር እነዚያ የዲያስፖራ ሰልፎች ወዴት ገቡ? እውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ለማገዝና ወያኔንስ ከሕዝብ ላይ ለማራገፍ ከሆነ የበለጠ ጫና የሚፈጥሩና ተሰሚነትም የሚኖራቸው ሰላማዊ ሰልፎች መደረግ የነበረባቸው በአስቸኳይ ጊዜው መታወጅ ምክነያት አልነበረም? ነው አሜሪካም በኮማንደ ፖስቱ ሥረ ነች? የኦሮሞና አማራ ሕዝብ አንድ መሆን ያስደነገጠው ወያኔን ብቻ ነበር? ይልቁንም ይህ አንድነት እንዳይቀጥል ወዥምብር ለመፍጠር በዲያስፖራው አካባቢ ምን ያህል ሩጫ እንደነበር አስተውላችኋል? ወያኔ አበቃለት በሚል ለቻርተርና ለሌላ ድርድር በየቀኑ የነበረው ሥብሰባ የኢትዮጵያን ሕዝብ ትግል ማዘናጋት ወይስ ለመደገፍ? የኦሮሞ ነን የሚሉ በለንደን እና በአትላነታ የተደረጉ ስብሰባዎች ዋነኛው መክነያት የኦሮሞ ሕዝብ ከአማራ ጋር አንድ እየሆነ ስለመጣ ለዘመናት የሰራንው የመለያየት ሥራችን ከሸፈብን የኦሮሞም ሕዝብ ወደ ኢትዮጵያዊነቱ ተመልሶ ሊያመልጥን ነው በሚል ሥጋት አልነበረም? የእነዚህ ቡድን መሪ ተዋናዮች ለምን የአማራ ብሔረተኛ ነኝ የሚለውን ቡድን ለመደገፍ ቀዳሚ ሆኑ? ጥያቄዬ በሌሎችም ይቀጥላል፡፡ በትልቁ ግን የማነሳው ግንቦት 7 የተባለው ቡድንስ ማን ነው? እውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ተጋድሎ ለመደገፍ ኤርትራ ታስፈልገዋለች? እስከ ጠረፍ ሱዳን ድረስ ወያኔን እየተፋለሙ ባሉ ገበሬዎች እያሉለት ኤርትራ ውስጥ መመሸግን ለምን መረጠ? በአረባምንጭ አደጋ አደረስሁ ያለው ቡድን ኢትዮጵያ በሙሉ ወያኔን በሚታገሉ ሕዝብ ከዳር እዳር በተንቀሳቀሱበት ወቅት የት ነበር? የአርባ ምንጭን አደጋ የፈጠረው ግንቦት 7 ነኝ ካለ ለምን አስፈለገ? ነው ለወያኔ ፕሮፓጋንዳ እንዲመች፣ ለዘመናት የኦሮሞ ሕዝብ በኦነግ ሥም እንደታረደ ሁሉ በግንቦት 7ም ሥም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይም አማራ የተባለውን ለማረድ ምስክር ለመፍጠር? ኦነግ የወያኔ አጋር ሆኖ የኦሮሞ ሕዝብ የሚያለቅበት አይነተኛ የፕሮፓጋንዳ መሣሪያ እንደሆነ እናውቃለን፡፡ ግንቦት ሰባትስ የወያኔ ተባባሪ አይደለም ትላላችሁ? ለዚህ መሪው ነኝ የሚለውን የብርሐኑ ነጋን፣ ኢሳያስ አፈወርቂን፣ የኢሳያስ ልዩ ሰው የስብሐት ነጋ እህት አበራሽ ነጋን፣ ስብሀት ነጋን፣ ደብረጽንንና ሌሎች ወያኔዎችን መረብ አጥኑት!!!

 

የአማራ ብሄረተኛ ነን የሚሉትስ ታዲያ ከየት መጡብን? ጎደሬው፣ ጎጃሜው፣ ወሎው፣ሸዌው አኮ አገር ቤት እየታገለ ያለው በኢትዮጵያዊነቱ ነው፡፡ የአማራን ሕዝብ በደል አግዝፈው ሊያሳዩን ይሞክራሉ፡፡ ሁሉንም እስከቦታው ድረስ የምናውቀው እውነት ነው፡፡ የአማራ ሕዝብ ወያኔን ከምንም ነገር በላይ ያስፈራታል፡፡ የሚያስፈራት ዋናው ምክነያቱ ደግሞ አማራነቱ ሳይሆን ኢትዮጵያዊነቱ ነው፡፡ ወያኔ ኢትዮጵያዊነትን ከአማራው ሕዝብ ለማጥፋት ትኩረት ሳትሰጠው ቀርታ ሳይሆን ሌሎችን ከኢትዮጵያዊነት ካመከነች አማራው ብቻውን ይቀራል የሚል ዕቅድ ስለነበራት ነው፡፡ ይህ ሕዝብ በሌሎች ላይ ተጽኖ በመፍጠር ኢትዮጵያዊነትን እንዳያቆይ ከፍተኛ ሥራ ሰርታለች፡፡ ወያኔ የመጀመሪያ ካደረገችው ሥራዋ አንዱ የአማራ ምሁራንን ከዩኒቨርሲቲ ማባረር እንደነበር እናስተውል፡፡ አማራ እንደ ኦሮሞ ከሚኒሊክ ታሪክ የሚላቀቅ አልነበረም፡፡ የኦሮሞን ሕዝብ ከሚኒሊክ ታሪክ ለማላቀቅ ከወያኔ በፊትም ከኃይለስላሴ ዘመን ጀምሮ ሲሰራበት የቆየ በመሆኑ ቀላል ነበር፡፡ ይህን ሂደት ብዙ ጊዜ ስላቀረብኩት አልመለስበትም፡፡ ሂደቱም ውስብስብ ነውና፡፡  ዛሬ የተነሱ የአማራ ብሔረተኛ ነን የሚባሉትን ለመፈብረክ ወያኔ የሄደችበት ብዙ ርቀት አለ፡፡ የጉራ ፈርዳና ሌሎችም አካባቢዎች በአማራው ሕዝብ ላይ የተፈጸሙ ግፎች ወያኔ በአማራው ላይ ያላትን ጥላቻ ለመግለጸ የሰራችውም ከመሆኑ በላይ የዛሬዎቹን ብሔረተኛ ነን የሚሉትን ቡድኖች ለድራማቸው የሚሆን ድረሰት እያዘጋጀችላቸው ነበር፡፡ እውነታው ይሄ ነው፡፡ የአማራን ሕዝብ ለመታደግ ግን የሚነሳ የትኛውም ቡድን ወያኔ ከምንም በላይ ቅድሚያ ሰጥታ የምታጠፋው ነው፡፡ የፕሮፌሰር አስራት ወልደየስን ቡድን እዚህ ጋር አስታውሱ፡፡ ልብ በሉ የእነ ፕሮፌሰር አስራት የአማራ ቡድን መሆን በራሱ አልነበረም የወያኔ ትልቁ ስጋት፡፡ የዚያ የአማራ ቡድን በውስጡ የያዘው ወያነን እንደጦር የሚያስፈራው ኢትዮጵያዊነት እንጂ፡፡ ይህ አይነቱ እውነት ነው በተመሳሳይ ዛሬ የእነ ፕ/ር መረራን ቡድን በወያኔ ጥርስ ውስጥ የከተተው፡፡ አሁንም ልብ እንድታደርጉ እፈልጋለሁ፡፡ እስከዛሬ በሌሎች ኢትዮጵያን በሚጠሉ ኦነግና መሰል ቡድኖች ከኢትዮጵያዊነቱ በመከነው የኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ ትልቅ ቦታ ስላላቸው የእነ መረራ ቡድን ለወያኔ ብዙም ሥጋት አልነበረም፡፡ ግን ይህን ቡድን ወያኔ በጥንቃቄ ነበር የምትከታተለው፡፡ ብዙም ጊዜ በሰርጎ ገቦች ስታፈረሰው ተመልሶ ሲገነባ ቆይቷል፡፡ ዛሬ ግን የዚህ ቡድን መሪዎች  በሕዝብ ዘንድ እየታወቁና ሕዝብም ወደማንነቱ እየመጣ መሆኑን ስለተረዳች ነበር ወያኔ በዚህ ቡድን መሪዎች ላይ አሁን የምናየውን ግፍ የምታደርስባቸው፡፡ ይህ ቡድን እንደ አስራት ወልደይስ ሁሉ በኢትዮጵያዊ ማንነቱ ላይ እንደማይደራደር ወያኔ አሳምራ ታውቀዋለች፡፡ ከዚህም በላይ በዚህ ቡድን ውስጥ የዘመናዊቷ ኢትዮጵያ መሥራቾች  ኦሮሞዎች ናቸው መሪያቸውም ሚኒሊክ ነው  የሚል ፍልስፍና እንዳለ ወያኔ አሳምራ ታውቀዋለች፡፡  ይህ ደግሞ ወያኔን ከምንም በላይ ያስፈራታል፡፡ ምን አልባትም ጎንደሬዎቹ የዚህን ቡድን መሪ የሆኑት በቀለ ገርባን ምስል በአደባዮቻቸው ከፍ አድርገው የማቅረባቸው ነገር ጎንደሬዎቹ የእነ በቀለ ቡድን በውልም የገባቸው መሆኑ ወያኔን እጅግ አስደንግጧታል ባይ ነኝ፡፡  ወያኔን የቀደማት ከዚህ በላይ የሆነ በሕዝብ ዘንድ ያለ ሚስጢር አለ፡፡ አውቀዋለች ግን ይሄንን ሚስጢራዊ የሆነውን የኦሮሞና የአማራው ሕዝብ ግንኙነት እንዴት ልትበጥሰው እንደምትችል ዛሬ ላይ ራስ ምታት ሆኖባታል፡፡  ይህ ሂደት ቀደም ብሎ እንደተጀምረም ታውቀለች፡፡ እና የአማራ ብሔረተኛ ነኝ የሚለውን ቡድን መፈብረክ አንዱ ስልቷ ነበር፡፡  አሁን አደጋው አንድ ነን የሚለው ከአማራው ብቻም ሳይሆን ለዘመናት ተሸውዶ ከነበረውም ከኦሮሞው ሕዝብ ዘንድ በይፋ እየተነገረ መምጣቱን ነው፡፡ የዛኑ ያህል ወያኔ፣ ኦነግና መሰሎቹ ከመቼው በላይ ያለ የሌለ ጉልበታቸውን እየተጠቀሙ ነው፡፡ ለዚህ የአማራ ብሔረተኛ ነኝ የሚለውን ቡድን በቻሉት ሁሉ ለመደገፍና አቅም አግኝቶ አንዲወጣ ትልቅ ጥረት እያደረጉ ነው፡፡  በኦሮሞ ሕዝብ ላይ የእስላማዊ መንግስትን ለማቋቋም ሕልም ያደረገው የኦነግና ኦነጋውያን ቡድን ሰሞኑን ለአማራው ብሔረተኝነት መጠናከር ድጋፉን መግለጹ የጥረቱ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ አሊያማ በምን ሂሳብ ነው የኦነግና ሊያውም እስላማዊ ጽንፈኝነትን በውስጡ የጠነሰሰው ቡድን የአማራ ተቆርቋሪ የሆነው?

 

የአማራ ቤሔረተኛው ቡድን ሌላው አላማው አማራ የሚል ቡድን ካለ በአማራው ክልል ውስጥ ያሉ የተለያዩ ሕዝቦችን እነሱም እኛም በማለት እንዲነሱ ሆን ተብሎ የሚሰራ ቡድን ነው፡፡ የዚህ ቡድን መፈብረክ ታሪክም ቡድኑ እንደሚለው ከአማራው ሕዝብ ግፍ ጋር በተያያዝ ሳይሆን የቅማንትን ሕዝብ ከሌላው የአማራ ሕዝብ ለመለየት የተደረገው የወያኔ ሴራ ከመክሸፉ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ልብ በሉ ቅማንት ጎንደሬ ነው፣ አገው ጎጃሜ ወይም ወሎዬ ነው፡፡ አማራ ግን አይደለም፡፡ እየተሄደበት ያለውን ሴራ ሁሉም ያስተውል፡፡ የአማራ ብሔረተኝነትን በማጉላት  ሌሎች በአማራው ክልል  የሚኖሩ ሕዝቦች ሁሉ የማንነት ጥያቄ በማንሳት እርስ በእርስ ሕብረት እንዳይኖራቸው ለሩቅ ጊዜ የታቀደ ሴራ መሆኑን አስተውሉ፡፡ ወልቃይቴዎቹ ሌላ የሚጠይቁበት እድል ስለሌላቸው አንጂ ወያኔ የወልቃይቴዎቹ ጥያቄ የጎነድሬነት ጥያቄ እንደሆነ አሳምራ ታውቀዋለች፡፡ ይሄ ከምንም በላይ ወያኔን ያስፈራታል፡፡ መላ ራያና አላማጣ ወሎ እንደሆነ ነው እንጂ ዛሬ ከ25 ዓመት በኋላ ትግራይ እንደሆነ አልተቀበለውም፡፡ በምን ምክነያት እንደሆነ ባላውቅም ትግርኛ ተናጋሪ ቢሆን አንኳን ታሪካዊ አሰፋፈሩ ከድሮው ትግራይ ውጭ ያለው ሕዝብ ትግራይ ውስጥ መካተትን አይፈልግም፡፡ በወልቃይት እንደማያቆም ወያኔ አሳምራ ታውቀዋለች፡፡ የጸለምትን ሕዝብ ብትጠይቁት ትግራይ መባልን አይፈልግም፡፡ በእርግጥም ሕዝቡ የራሱ የሆነ ባሕልና እሴት አለው፡፡ ሌላው ቀርቶ የተምቤን ትግርኛ ተናጋሪዎች ከእነአደዋና አክሱም ጋር ሕብረት ከሚፈጥሩ ከቤጌምድሮች ጋር ያላቸው ትስስር ይበልጥባቸዋል፡፡ ምን አልባትም በትግራይ ወያኔ ከማትወደው ሕዝብ አንዱ ተምቤን ነው፡፡ ተምቤን ግን የወያኔ ነጻ ቀጣና ምሽግ ሆና ለብዙ ዘመን አገልግላ ነበር፡፡ ተምቤኖች ግን በኢትዮጵያዊነታቸው የማያፍሩ በመሆኑ ወያኔን ያስሯታል፡፡

 

ዛሬ የአማራ ብሄረተኛ ነኝ የሚለው ቡድን ዓላማው ኢትዮጵያዊነትን ከአማራው ሕዝብ አእምሮ በማምከን እንደኦሮሞው ሕዝብ የባዘነ ለማድረግ ነው፡፡ የኦሮሞው ሕዝብ አሁን አሁን እየነቃ የመጣበት መሆኑ የአማራ ብሔረተኛ  ካለ የአሮሞውን አዲስ እያቆጠቆጠ ያለውን ኢትዮጵያዊነት ለማዳፈን ቀላል ነው፡፡ ወያኔ አሁን ያሰማራቻቸውም በቅንጅት ነው፡፡ የኦነግንና ኦነጋውያን የአማራው ቡደን ነኝ የሚለውን እንዲያበረታታ የአማራ ቡድን ነኝ ባዩም የኦነጋውያን አበረታች እንዲሆን፡፡  ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚል ሁሉ ግልጽ ሊሆንለት ይገባል፡፡ አሁን ያለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ትግል የጎሳን መዋቅር የሚፈልግ አይደለም፡፡ የጎሳ መዋቅሩን ሕዝቡ አፍርሶታል፡፡ እዚህ ለዘመናት አንደወጣ ያለ ዲያስፖራ ካልገባው ዝም እንዲል ከገባው ደግሞ እውነታው የሕዝቦች ወድ ኢትዮጵያዊነት መምጣት እንደሆነ ትልቁ የወያኔ ውድቀት ይህንኑ ተረድቶ በዚህ ቢሳተፍ፡፡ የሴረኞቹ አባል ከሆነ ግን ምርጫው ነው፡፡  አሁን ለወያኔ አደጋ የሆኑበት በአማራ ክልል የተነሳው የኢትዮጵያዊነት አቀንቃኝ በጦር ሳይቀር ሊፋለመው ዱር የወጣው ቡድን እንጂ ግንቦት 7 አደለም፡፡ የኦሮሞን ሕዝብ ቀስ በቀስ ወደ ኢትዮጵያዊነት እየሳበው ያለው የእነ መረራ ቡድን እንጂ በለንደን፣ በአተላንታ የአሮሚያን ቻርተር የሚያዘጋጀው ቡድን አይደለም፡፡ ኢትዮጵያዊ ነኝ የምትል ዱር የወጡትን ታጋዮች ደግፍ፡፡ ለእስር የተዳረጉትን መረራንና አጋሮችን ከእስር እንዲፈቱ ለአለም በሰላማዊ ሰልፍም ይሁን በተገኘው አጋጣሚ አሳውቅ፡፡ ለመሆኑ ሌሎችም ብለውታል የመራራ መታሰር ሰላማዊ ሰልፍ ለመውጣት ለዲያስፖራው አንሶበት ነው?  ከየትኛውም አጋጣሚ በላይ ዓለም አቀፍ ተደማጭነት ያለውን ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ የመራራ መታሰር ትልቅ ጉዳይ ነው፡፡ በእርግጥም የአለም አቀፉ ማሕበረሰብ በእኝህ ሰው መታሰር የወያኔን ማንነት የበለጠ ያወቀበት ክስተት ነው፡፡ አውቃለሁ ኦነግና ኦነጋውያን መረራ ጠላታቸው ነው፡፡ ሌላውስ ኢትዮጵያዊ ነኝ የምትል፡፡ መረራ ኦሮሞ እንጂ ኢትዮጵያዊ አደለም? ጎንደሬዎቹ ዛሬ የመረራን መፈታት ለመጠየቅ አደባባይ እንዳይወጡ የሞት አዋጅ ታውጆባቸዋል፡፡ ነው ኮማድ ፖስቱ ለዲያስፐራው ነው የታወጀው? በአጠቃላይ የዲያስፖራው ማሕበረሰብ በወዥንብር ለኢትዮጵያ ጠላት ለሆኑት ኦነግና ኦነጋውያን፣ አሁን የመጣው አማራ ቡድን ተብዬውና ሌሎች አጫፋሪ ከመሆኑም ባላይ ገንዘቡንና ዕውቀቱን እየሰጠ እያጠናከራቸው ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ ነኝ የምትል ሁሉ ቢያንስ ለኢትዮጵያ ጠላቶች የገንዘብና የሞራል አቅም በመሆን አገርህንና ሕዝብህን አትበድል፡፡ ከቻልክ ግን እውነተኞቹን የሕዝብና አገር ነጻነት ታጋዮቹን ደግፍ፡፡

 

አቤቱ ማስተዋልን ስጠን! እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይጠብቅ!

ሰርጸ ደስታ

አሜን

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.