በቁሉቢ ቅዱስ ገብርኤል: ይፈጸማል የተባለው “ኃይለኛ ሙስና” ተጣርቶ ርምጃ እንዲወሰድ ተጠየቀ

ሐራ ዘተዋሕዶ

 • ገዳሙ፣ “አቤቱታ አቅራቢዎቹ ስም የሌላቸውና በወንጀል የሚፈለጉ ናቸው፤” ይላል
 • በኹለቱ ዓመታዊ ክብረ በዓላት፣ ከ23 ሚሊዮን ብር በላይ የስዕለት ገቢ ተሰብስቧል
 • በወርኃዊ በዓላት የሚሰበሰበው ጥሬ ገንዘብ እና ንዋያተ ቅድሳት ለምዝበራ ተጋልጧል
 • ማሠልጠኛዎች እንዲገነቡ እና የማኅበራዊ ልማት ተሳትፎው እንዲጠናከር ተጠይቋል
 • ለረጅም ጊዜ የቆዩት ሓላፊዎች፡- ሙስናን በሚጸየፉ፣ በተማሩና በነቁ አገልጋዮች ይተኩ

*                 *              *

(አዲስ አድማስ፤ ቅጽ 16 ቁጥር 884፤ ቅዳሜ፤ ታኅሣሥ 15 ቀን 2009 ዓ.ም.)በቁሉቢ ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ውስጥ፣ እየተፈጸመ ነው በሚል ከምእመናን በተደጋጋሚ የቀረበው የሙስና አቤቱታ፣ ተጣርቶ አስፈላጊው ርምጃ እንዲወሰድ፣ የምሥራቅ ሐረርጌ ዞን መስተዳደር ጽ/ቤት አሳሰበ፡፡

የመስተዳድሩ ጽ/ቤት ማሳሰቢያውን ያቀረበው፣ ባለፈው ወር መጀመሪያ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ቢሮ በጻፈው ደብዳቤ ነው፡፡ በዞኑ ሜታ ወረዳ ቁሉቢ ከተማ በሚገኘው የደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ውስጥ፣ “ኃይለኛ ሙስና እየተፈጸመ” መኾኑን በመጥቀስ ጉዳዩ እንዲጣራ የአጥቢያው ምእመናን ለቤተ ክርስቲያን ጥያቄ ሲያቀርቡ፣ ለመስተዳድሩም በግልባጭ አስታውቀው እንደነበር ጽ/ቤቱ አስታውሷል፡፡

አቤቱታውን ለማጣራት፣ ከገዳሙ አስተዳደርም ይኹን ከምሥራቅ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ እንዳልተደረገ፣ ከምእመናኑ በድጋሚ መረዳቱን የጠቀሰው የዞኑ መስተዳድር፤ “ለሕዝበ ክርስቲያኑ ክብር አለመስጠትን ያመለክታል፤” ሲል ተችቷል፡፡

“ጉዳዩ ወደ ሌላ አቅጣጫ እንዳያመራ”፣ በገዳሙ እየተፈጸመ ነው ስለተባለው ሙስና፣ በቤተ ክርስቲያን አመራር በተገቢው መንገድ ተጣርቶ አስፈላጊው ርምጃ እንዲወሰድና ለሕዝበ ክርስቲያኑ እንዲገለጽ የፓትርያርኩን ቢሮ ጠይቋል፡፡

kulubi-st-gabriel-church
ጉዳዩ፣ በመንግሥት ደረጃ የፓትርያርኩ ቢሮ እስኪጠየቅ ድረስ ቸል መባሉ፣ በእጅጉ ቅር እንዳሰኛቸው የገለጹት የአጥቢያው ምእመናን፦ የስብከተ ወንጌል አገልግሎቱ መዳከሙን፤ በገዳሙ የተከናወነ ተጠቃሽ አካባቢያዊ ማኅበራዊ ልማት አለመኖሩን፤ የአገልጋዮች ደመወዝ የገቢውን ያኽል አለመሻሻሉንና ካህናቱ ከሚያሳዩት ትጋት ውጭ መንፈሳዊ አገልግሎቱን ለማጠናከር በአስተዳደሩ የሚደረገው ጥረት እዚኽ ግባ የማይባል መኾኑን፤ ሙስናን ብልሹ አሠራርን በመቃወም ከአስተዳደሩ የተለየ አቋም የሚይዙ ሠራተኞች በየምክንያቱ እንዲርቁ መደረጋቸውን አስረድተዋል፡፡

በየዓመቱ ታኅሣሥ 19 እና ሐምሌ 19 ቀን ለገዳሙ በስዕለት ከሚገባው ጥሬ ገንዘብ እና የተለያዩ ዓይነት ንዋያተ ቅድሳት ውጭ ባሉት ወርኃዊ በዓላትም ከፍተኛ ገቢ እንደሚገኝ ምእመናኑ ይናገራሉ፡፡

የኹለቱ ዓመታዊ ክብረ በዓላት ገቢ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤትና በዞኑ መስተዳድር አካላት ጥብቅ ቁጥጥር የሚደረግበትን ያኽል በሌሎቹም ወራት አለመደረጉ፣ ለከፍተኛ ሙስና አጋልጦታል፤ የሚሉት ምእመናኑ፤ በየዓመቱ ለክብረ በዓል በሚጎርፉት በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ተሳላሚዎች፡- የጸበል ቦታው እንዲታወቅ፣ ማረፊያዎችንና መጸዳጃዎችን ማመቻቸቱ እንኳ ትኩረት አልተሰጠውም፤ ሲሉ ቅሬታቸውን ይገልጻሉ፡፡

[የደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ገዳም በሚገኝበት በቁሉቢ ከተማ ዙሪያና በወረዳው ቀበሌዎች፦ እንደ ቀርሳ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ኮረሜ ቅድስት ማርያም፣ ወተር ኪዳነ ምሕረት እና ላንጌ ቅዱስ ራጉኤል ያሉት ችግረኛ የገጠር አብያተ ክርስቲያናት ከሐረርና ከድሬዳዋ በሚጓዙት ምእመናን የሚረዱ እንጂ ከገዳሙ የሚያገኙት ድጋፍ አለመኖሩም ጠቁመዋል፡፡]  

የገዳሙ አስተዳዳሪ መልአከ ኃይል አባ ወልደ ጊዮርጊስ በበኩላቸው፤ የዞኑን ጥያቄ በተመለከተ ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጋር መወያየታቸውንና የተሰጠውን ምላሽም ትላንት ለመስተዳድሩ ማድረሳቸውን አዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡ “ጉዳዩ መታየት ያለበት በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ነው፤” ያሉት አስተዳዳሪው፣ የሙስና አቤቱታ አቅርበዋል የተባሉት ሰዎች ራሳቸው፣ በወንጀል የሚፈለጉ መኾናቸውን ጠቅሰው፣ ለሕግ እንዲቀርቡ ጠይቀናል፤ ብለዋል፡፡

የገዳሙ ሒሳብ ሹሙ ወ/ሪት ወይንሸት ግርማም፣ አቤቱታ አቅራቢዎቹ ማንነታቸውን አለመግለጻቸውን ጠቅሰው፣ አቤቱታ የቀረቡባቸውን ጥያቄዎች ከሀገረ ስብከቱ ጋር ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ በአካል አቅርበን በደብዳቤ የተሰጠውን ምላሽ ደግሞ፤ አዲስ አበባ ለሚገኘው ክልላዊ ቢሮና ለምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ጽ/ቤት መስጠታቸውን አስረድተዋል፡፡

[ቀደም ሲል፣ ከምእመናኑ የቀረቡ አቤቱታዎችን መሠረት በማድረግ፣ አስተዳዳሪውን ጨምሮ የጽ/ቤቱ ሓላፊዎች፦ ከደለበ የባንክ ተቀማጭ ጀምሮ በተለያዩ የንግድ ተቋማት ባለአክስዮኖች መኾናቸውን፤ በድሬዳዋና በአዲስ አበባ ውድና ዘመናዊ የመኖርያ ቤቶችን መግዛታቸውን እንደ ማሳያ በመጥቀስ ገዳሙን እየመዘበሩ እንዳሉ መዘገቡ ይታወሳል፡፡]  

ገዳሙ፣ በገቢረ ተኣምራቱ ያለውን ታዋቂነትና የገቢ መጠኑን ያኽል፣ መንፈሳዊ አገልግሎቱን ለከተማው ምእመናን ተደራሽ በኾነ አኳኋን እንዲያስፋፋ፤ ቀድሞም የነበሩት የካህናት ማሠልጠኛ እና የአብነት ት/ቤቶች በተደራጀ መልኩ እንዲከፈቱ፤ እንደ ድሬዳዋና ሐረር ባሉት ከተሞች ተጨማሪ ገቢ የሚያስገኙ የራስ አገዝ ግንባታዎችን በማካሔድ ማኅበረሰባዊ አገልግሎቱን የሚያጠናክርበት አቅም እንዲፈጥር፤ ጠቁመዋል፤ ምእመናኑ፡፡ ለዚኽም ገዳሙ፣ “ለረጅም ጊዜ ከቆዩት ሓላፊዎች ይልቅ፡- ሙስናን የሚጸየፉ፣ የተማሩና የነቁ አገልጋዮች ያስፈልጉታል፤” ይላሉ፤ ምእመናኑ፡፡

በዓመት ኹለት ጊዜ ለሚከበረው የቅዱስ ገብርኤል ክብረ በዓል፣ ከሀገር ውስጥና ከውጭ ወደ ገዳሙ ከሚጓዙ ተሳላሚዎች፣ ከ23 ሚሊዮን 587 ሺሕ ብር በላይ በስዕለት መግባቱን የሐምሌ 19 ቀን 2007 እና የታኅሣሥ 19 ቀን 2008 ዓ.ም. የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሪፖርት ያመለክታል፡፡

ይኸው ገቢ፣ በጠቅላይ ጽ/ቤቱ የበጀት ዕቅድ እየወጣለት፥ ለቤተ ክርስቲያኒቱ የነገረ መለኰት ኮሌጆች፣ ለአብነት መምህራን፣ ለሰባክያነ ወንጌልና ለሠራተኞች ደመወዝ የሚከፈል ሲኾን፤ የሙከራ ሥርጭት እያካሔደ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቴሌቭዥን ጣቢያ የ9 ሚሊዮን ብር አስተዋፅኦ ማድረጉም በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

በስዕለት የሚሰበሰቡትን የተለያዩ ዓይነት ንዋያተ ቅድሳት፣ ዋጋ አጥንቶና ተማኝ ኮሚቴ አቋቁሞ የሚያሰራጭ የማደራጃ መምሪያ፣ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የተቋቋመ ሲኾን፤ ተጨማሪ ገቢ ማስገኛ ሕንፃ ለማሠራትም ዕቅድ መያዙን ማደራጃው በሪፖርቱ አስታውቋል፡፡

የኦርቶዶክሳውያን አገልጋዮች መረዳጃ ዕድር ተቋቋመ፤ “ብር ከመሰብሰብና አስከሬን ከመሸኘት የላቀ መረዳዳትና ቤተ ክርስቲያንን የመጥቀም ዓላማ አለን”/ኮሚቴው/

 • ዕድሩ፥ ቤተ ሳይዳ ተብሏል፤ ዓላማውን የሚደግፉቱ በመመዘገብ ላይ ናቸው
 • በአገልጋዮች እና በሠራተኞች መካከል ወዳጅነትንና ቤተሰባዊነትን ያጠናክራል
 • ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ሲያጋጥም ለመረዳዳትና ለመተሳሰብ ያስችላል
 • ተደራጅቶ በጋራ በመሥራት ራስንና ቤተ ክርስቲያንን የመጥቀም ዓላማ አለው
 • ፖለቲካን በተመለከተ ከየትኛውም አካል ጋር ግንኙነት አያደርግም

*                 *            *

 • አገልጋዩ፥ የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን የአባልነት መታወቂያ ያለው ሊኾን ይገባል
 • ኦርቶዶክሳዊ ዶግማንና ቀኖናን በመጠበቅ ከሚያስነቅፉ ተግባራት መራቅ አለበት
 • በማጽናኛ መርሐ ግብር ላይ፣ ቤተ ክርስቲያንን ለማስተዋወቅ አተኩሮ ይሠራል
 • ከዕድሩ ዕድገትጋ ተያይዘው ከሚመጡ ጥቅሞች ኹሉ የመጋራት መብት አለው
 • የአዲስ አባላት መግቢያ ብር 500 እና መደበኛ ወርኃዊ ክፍያ ብር 50 ተወስኗል

*               *                *

yeagelgayoch-meredaja-edir_2

ከመረዳጃ ዕድሩ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት በከፊል(ከግራ ወደ ቀኝ)፡- መጋቤ ሥርዓት ደስታ ጌታሁን፣ ወ/ሪት ፌቨን ዘሪሁን፣ ዘማሪ ይትባረክ ተገኝ፣ መምህር ዐቢይ መኰንን፣ መምህር ሱራፌል ታደሰ፣ ቀሲስ ዮናስ ነጌሶ፤

“ቤተ ሳይዳ” የተሰኘ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች እና ሠራተኞች መረዳጃ ዕድር ምሥረታ ተካሔደ፡፡

ባለፈው ወር፣ ኅዳር 15 ቀን 2009 ዓ.ም. በዐዲስ አበባ የተመሠረተው የመረዳጃ ዕድሩ፣ በቁጥር ከ70 ያላነሱ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችና ሠራተኞች በተገኙበት መቋቋሙ ታውቋል፡፡

የመረዳጃ ዕድሩ፦ ፆታ፣ ቀለምና ጐሣ ሳይለይ በጥቂት ወንድሞችና እኅቶች የራስ አነሣሽነት መቋቋሙ የተጠቀሰ ሲኾን፤ በመተዳደርያ ደንቡ የሰፈረውን ዓላማ የሚደግፉ ኦርቶዶክሳውያን አገልጋዮችና ሠራተኞች ኹሉ የመግቢያ ግዴታዎችን በማሟላት መመዝገብ እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡

በምሥረታ ጉባኤው ላይ፣ 27 አንቀጾች ያሉት የመረዳጃ ዕድሩ መተዳደርያ ደንብየማቋቋሙን ተነሣሽነት በወሰዱትና አገልጋዩና ሠራተኛው በመረጣቸው የኮሚቴ አባላት በንባብ ቀርቦ ተደምጧል፡፡ ከተደረገው ሰፊና ግልጽ ውይይት በተገኙ በርካታና ጠቃሚ የማሻሻያ ሐሳቦችም፣ ዳብሮና ተቃንቶ መዘጋጀቱ ተመልክቷል፡፡

በቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችና ሠራተኞች መካከል ቤተሰባዊነትንና ወዳጅነትን ማጠናከር፥ መተዳደርያ ደንቡ በቀዳሚነት ያሰፈረው የመረዳጃ ዕድሩ ዓላማ ነው፡፡ በዚኽም፦ በሐዘንና በደስታ ጊዜ በመረዳዳት በማንኛውም ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳይ ለመተሳሰብ ያስችላል፤ በሀገሪቱ ሕጎችና ደንቦች መሠረትም፣ በጋራ ተደራጅቶ ሥራ በመፍጠር ራስንና ቤተሰብን እንዲኹም ሀገርንና ቤተ ክርስቲያንን የመጥቀም ዓላማ ይኖረዋል፤ ተብሏል፡፡

ከአባላቱ የሚበዙት፣ በምእመኑ የሚታወቁ የሕዝበ ክርስቲያኑ አገልጋይ እንደመኾናቸው፣ “ቢሞቱ የሚሸኛቸውና የሚቀብራቸው አያጡም፤” ያሉት የምሥረታ ጉባኤው ተካፋዮች፣ ዕድሩ በሕይወት ሳሉ በጋራ እየሠሩ በመደጋገፍ ዓላማ ላይ እንዲያተኩር አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

“ብር መሰብሰብ፣ ንፍሮ መቀቀልና አስከሬን መሸኘት ብቻ ሳይኾን፣ አገልጋዩና ሠራተኛው በጋራ ተደራጅቶ ኑሮውን የሚያሻሽልበት፤ ሀገሩንና ቤተ ክርስቲያኑን የሚጠቅምበት አስቻይ ኹኔታ የሚፈጠርበት ነው፤” ብለዋል – መተዳደርያ ደንቡን ያብራሩ የኮሚቴ አባላት፡፡

“አገልጋይ ሲባል ማን ነው?” የሚለው ነጥብ፣ መሥራቾችን በስፋት ያወያየና ያከራከረ ጉዳይ ነበር፡፡ ዕድር ማኅበራዊ መረዳጃ ቢኾንም፣ በአባልነት መስፈርቱ የእምነት አቋምን ከማስረገጥ ጀምሮ በጥንቃቄ ተጠንቶ በደንቡ መስፈር እንዳለበት ስምምነት ተደርሶበታል፡፡

የአባላትን ቁጥር መወሰን እንደ ሐሳብ ቢጠቆምም፣ ኦርቶዶክሳዊ ዶግማንና ቀኖናን መጠበቅና እንዲኹም የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን መታወቂያ መሠረታዊ የአባልነት አንቀጾች ኾነው ተቀምጠዋል:: የአባላት ቁጥርም ሳይወሰን፣ መተዳደርያ ደንቡን የተቀበለ በየትኛውም የዓለም ክፍል የሚገኝ ኦርቶዶክሳዊ አገልጋይና ሠራተኛ ተመዝግቦ መግባት እንደሚችል ተጠቅሷል፡፡

አባሉ፣ በደንቡ በተዘረዘሩ ኹኔታዎች ወቅት የገንዘብና ሌሎች ማበረታቻዎች የማግኘት፤ በአጠቃላይ አካሔዶች ላይ በተገቢው መንገድ ሐሳብ የመስጠት፤ በሥራ አስፈጻሚነት ተመርጦ የማገልገል፤ ከዕድሩ ዕድገት ጋር ተያይዘው ከሚመጡ ጥቅሞች ኹሉ የመጋራት መብት ይኖረዋል፡፡

በአንፃሩ፣ ቤተ ክርስቲያንን ከሚያስነቅፉ ተግባራት የመራቅ፤ የማጽናኛ መርሐ ግብሮችን ጨምሮ በጠቅላላ ጉባኤና በሥራ አስፈጻሚው በሚጠሩ ሌሎች ስብሰባዎች የመሳተፍ፤ በደንቡ የተቀመጠውን የመግቢያና ወርኃዊ ክፍያ በተወሰነው ጊዜ የመክፈል፤ በሚመደብባቸው መርሐ ግብሮችና ሓላፊነቶች የማገልገል ግዴታዎች አሉበት፡፡

ye-eotc-aglegayoch-meredaja-edir

የመረዳጃ ዕድሩ ሥራ አስፈጻሚ አስመራጮች በሥራ ላይ(ከግራ ወደ ቀኝ)፤ መምህር ተስፋዬ ሞሲሳ፣ መጋቤ ምሥጢር ቡሩክ አሣመረ፣ ሊቀ ትጉሃን ደረጀ ነጋሽ(ደረጀ ዘወይንዬ)፤

በአባሉና በተመዘገቡ ቤተ ሰዎቹ የደስታና የሐዘን ወቅቶች የሚኖሩ ማኅበራዊ መድረኮች፣ ቤተ ክርስቲያንን የበለጠ የማስተዋወቅ ፋይዳም እንዳላቸው ግንዛቤ ተወስዶ፣ ለመርሐ ግብሮቹ ዝግጅት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚያስፈልግ በውይይቱ ላይ ተመልክቷል፤ በዚኹም መግባባት፣ የመርሐ ግብር ዝግጅት ራሱን ችሎ እንዲዋቀር መደረጉ ታውቋል፡፡

መረዳጃ ዕድሩ፦ ዋና ሰብሳቢውን፣ ምክትል ዋና ሰብሳቢውንና ጸሐፊውን ጨምሮ ዘጠኝ ኮሚቴዎች ያሉት ሲኾን፤ በምሥረታ ጉባኤው ተካፋዮች በተቋቋመ ሦስት አባላት ያሉት አስመራጭ ኮሚቴ አማካይነት፣ የሥራ አስፈጻሚ አባላት ምርጫ ተካሒዷል፡፡ በዚኽም መሠረት፡-

 1. መጋቤ ሥርዓት ደስታ ጌታሁን – ዋና ሰብሳቢ
 2. መምህር በላይ ወርቁ – ምክትል ዋና ሰብሳቢ
 3. መምህር ዐቢይ መኰንን – ጸሐፊ
 4. መምህር ሱራፌል ታደሰ – ተቆጣጣሪ
 5. መምህር ደስታ በዛብህ(አባቴ ኃይለ ጊዮርጊስ) – ሕግ አገልግሎት
 6. ዘማሪ ይትባረክ ተገኝ – የመርሐ ግብር ዝግጅት
 7. ቀሲስ ዮናስ ነጌሶ – ሒሳብ ሹም
 8. ዘማሪት ቅድስት አረጋ – ግምጃ ቤት
 9. ዘማሪ ፈቃዱ አማረ – ገንዘብ ያዥ
 10. ወ/ሪት ፌቨን ዘሪሁን – የሕዝብና የአባላት ግንኙነት ኾነው ተመርጠዋል፡፡

የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ለአንድ ዓመት በሓላፊነት ይቆያል፤ በሥራ እንቅስቃሴውም፣ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ተቋማት እና የልማት ድርጅቶች እንዲኹም መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልኾኑ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት እንደሚያደርግና ፖለቲካን በተመለከተ ከማንኛውም አካል ጋር እንደማይገናኝ፤ በፖሊቲካና ፖሊቲካ ነክ ጉዳዮችም ጣልቃ እንደማይገባ በደንቡ ተደንግጓል፡፡

copy-of-ye-eotc-aglegayoch-meredaja-edir

የመረዳጃ ዕድሩ መሥራች ጉባኤ ተሳታፊዎች በከፊል

የመረዳጃ ዕድሩ አባላት በሙሉ የሚገኙበት ጠቅላላ ጉባኤ በየአራት ወሩ የሚጠራ ሲኾን፤ የመጀመሪያው ጠቅላላ ጉባኤው ጥር 1 ቀን እንደሚካሔድ ሥራ አስፈጻሚው አስታውቋል፡፡ ይኸው ጠቅላላ ጉባኤው እስከሚደረግ ድረስ ባለው ጊዜ በአባልነት የሚገቡ አገልጋዮችና ሠራተኞች፣ ብር 300 በመክፈል በመሥራችነት ይመዘገባሉ፤ ከዚያ በኋላ የሚገቡ አዲስ አባላት ብር 500 የሚከፍሉ ሲኾን፣ መደበኛ ወርኃዊ ክፍያውም ብር 50 እንዲኾን ተወስኗል፡፡

በጥቅምት 2007 ዓ.ም.፣ በቅዱስ ሲኖዶስ በጸደቀው ሕገ ቤተ ክርቲያን ትርጓሜ መሠረት፣ “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሠራተኛ” ማለት፦ በቤተ ክርስቲያኒቱ መሥሪያ ቤቶች በቋሚነት ወይም በጊዜያዊነት ተመድቦ(ተቀጥሮ)፥ መንፈሳዊ፣ አስተዳደራዊ ወይም ሌላ ዓይነት አገልግሎት የሚያበረክት ሰው ነው፡፡

እንደ ሕገ ቤተ ክርቲያኑ ትርጓሜ፡– “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ” ማለት፦ በቅዳሴ ወይም በማሕሌት ወይም በሌላ መንፈሳዊ ግልጋሎት፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በቋሚነት ወይም በጊዜያዊነት ተመድቦ በክፍያ ወይም በነፃ መንፈሳዊ ግልጋሎት የሚሰጥ ሰው ማለት ነው፡፡

“ቤተ ሳይዳ” – የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአገልጋዮችና ሠራተኞች መረዳጃ ዕድር፣ ከአብነት ት/ቤቶች፣ ከመንፈሳውያን ኮሌጆች፣ ከካህናት ማሠልጠኛዎችና ከሰንበት ት/ቤቶች ተምረው በወጡና ቤተ ክርስቲያን በላከቻቸው፤ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት፣ የአድባራትና የገዳማት፣ የሰንበት ት/ቤቶች እና የመንፈሳውያን ማኅበራት መደበኛ እና የትሩፋት አገልጋዮች አነሣሽነት የተቋቋመ መኾኑ ተገልጧል፡፡

ክብረ ክህነታቸውን በብልሹ ምግባር ያዋረዱት የያቤሎ የ3ቱ አድባራት አለቃ ከሓላፊነታቸው ተነሡ፤ ወደ ሻኪሶ ሊቀ ካህንነት መዛወራቸውም እያወዛገበ ነው

 • ክህነታቸው እንዲሻር በማስረጃ የቀረበው አቤቱታ በቀኖናው እንዲወሰን በብርቱ እየተጠየቀ ነው
 • ምንኵስናቸውን በዝሙት አፍርሰዋል፤ በልቅ ዘማዊነታቸው ከየአድባራቱ በተደጋጋሚ ተባረዋል
 • መካኒቱን ስደስርብሽ ትወልጃለሽ ሲሉያባብላሉ፤ በመተት ያስፈራራሉ፤ ከዓላውያንም ይሰስናሉ
 • በመብል ፍቅር እየበሉ ይቀድሳሉ፤ ሲጠጡ ዕርቃናቸውን ጥለው ኃፍረታቸውን ገልጠው ያሳያሉ
 • በራሳቸው እና በልጆቻቸው ስም ያሠሯቸው አራት የከተማ ቤቶች ከፍተኛ ጥያቄ አሥነስተዋል
 • ከካህናቱ የመከሩበት ሊቀ ጳጳሱ፥“ዋናው መንሥኤ መጠጥ ነው” ሲሉ በዐውደ ምሕረት ገልጸዋል

*                    *                    *

 • ከአስተዳደርና ከክህነት አገልግሎት እንዲቆጠቡ ሊቀ ጳጳሱ ጊዜያዊ እገዳ አሳልፈውባቸው ነበር
 • መጽሐፋዊ፣ ቀኖናዊ እና ሰላማዊ ውሳኔ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚሰጡም ቃል ገብተው ነበር
 • እገዳው ያልከለከላቸው አለቃ መቅደስ ለመግባት ሲሞክሩ የተገቱት በከተማው ጸጥታ ዘርፍ ነው
 • ወደ ሻኪሶ ሊቀ ካህን ኾነው ቢዛወሩም፣ በእንቢተኝነት ሕዝቡን እያሳደሙና እየከፋፈሉ ይገኛሉ
 • ካህናት፣ ምእመናንና የሰንበት ት/ቤት ጉዳዩ ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ እንዳያመራ አሳስበዋል፤
 • ጉዳዩ በዝውውር ብቻ ሳይድበሰበስ መፍትሔ ያግኝ፤ ለቤተ ክርስቲያን ሰላምና ደኅንነት ሲባል!!

*                    *                    *

melake-birhanat-fisseha-tsion-kebede
እኚህ ሰው መልአከ ብርሃናት ፍሥሓ ጽዮን ከበደ ይባላሉ፡፡ በዝዋይ ገዳም አቋቋም እና ቅኔ ተምረዋል፤ በወላይታ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም መንኵሰው እንደነበርም ይነገራል፡፡ ከ14 ዓመት በፊት በጉጂ ቦረና እና ሊበን ዞኖች ሀገረ ስብከት ወደሚገኘው ሻኪሶ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ሲደርሱ ሥራ የጀመሩት የደብሩ መሪጌታ ኾነው ነበር፡፡

ከጥንቱም ባለባቸው የከፋ ምግባረ ቢስነት፣ በወቅቱ የደብሩ አስተዳዳሪ በኋላ ሊቀ ጳጳስና የወቅቱ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ ርምጃ ሲባረሩ ወደ ሜጋ ቅዱስ ሚካኤል አምርተዋል፡፡ ብዙም ሳይቆዩ በተጠናወታቸው የዝሙት ነውር ተከሠው ለኹለተኛ ጊዜ ሲባረሩ፣ አኹን ወዳሉበት የያቤሎ ከተማ ሦስቱ አድባራት(ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም፣ ደብረ ኢዮር እግዚአብሔር አብ ወአቡነ ሐራ ገዳምና ደብረ ብርሃን ቅዱስ ጊዮርጊስ) ይመጣሉ፡፡

በቅኔ ማሕሌቱ በትጋት አገልግለዋል፤ በሚል በአኹኑ የአድባራቱ ቄሰ ገበዝ በያኔው የያቤሎ ተልተሌና አሬሮ ወረዳዎች ሊቀ ካህን መልአከ ገነት ሐረገ ወይን ጥሩነህ ቦታም ይመደባሉ፡፡ የ3ቱ አድባራቱ አስተዳዳሪ መልአከ ጽዮን አባ ቃለ ወልድ ደስታ ሲያርፉም ሓላፊነቱን ደርበው በመያዝ፣ ሊቀ ካህናትም አለቃም ይኾናሉ፡፡ “ምዝበራውንና ዘማዊነቱን ያጧጧፈው ከዚኽ በኋላ ነው፤” ይላሉ ኹኔታውን በቁጭት የሚያወሱ የከተማው ምእመናን፡፡

በዝሙት ምክንያት ምንኵስናውን ከተዉት በኋላ፣ ትዳር መሥርተው ልጆች አፍርተዋል፡፡ በያቤሎ ከተማ አራት የግል ቤቶች አሠርተዋል፤ የተያዙትም በራሳቸውና በልጆቻቸው ስም ነው፡፡ የገንዘቡ ምንጭ፣ ተጠያቂነት የሌለበት ምዝበራቸው እንደኾነ በስፋት ይታመናል፡፡ ትዳር ቢመሥርቱም፣ የተነደፉበት የዝሙት ፆር ከጎልማሶች ሚስቶች እስከ ሴሰኞች አድርሷቸዋል፤ መካኒቱንም፣ “ከእኔ ብትገናኚ ትወልጃለሽ”  በሚል ማባበያ አልማሯትም፡፡ በመተት እያስፈራሩ ያነወሯቸውና የሌላ እምነት ተከታዮችም እንዳሉ ተነግሯል፡፡

ይህን ኹሉ አበሳቸውን እንዳላዩና እንዳልሰሙ የሸፈኑት የአድባራቱ ካህናትና ምእመናን፣ አንድ አጋጣሚ እስኪፈጠር የሚጠብቁ ይመስላል፡፡ ነሐሴ 29 ቀን 2008 ዓ.ም. በከተማው ሠርግ ኾነ፤ መልአከ ብርሃናት  ፍሥሓ ጽዮን ከበደም በዚያ እድምተኛ ነበሩ፡፡ አብሯቸው የኖረ ዓመል ነውና፣ በሥነ ሥርዓቱ ላይ ሲተነኳኩሱ ሚስቴን ቀምተኽኛል ያለ አንድ ጎበዝ፣ በእድምተኛው ፊት በቡጢ ነርቶ ዘረራቸው፡፡

የጠቡ መንሥኤ እድምተኛውን አላከራከረም፤ ተግባብቶ የጋራ አቋም ለመያዝም ጊዜ አልፈጀም፡፡ “ከዚያች ቀን ጀምሮ፣ ምእመኑ በራሱ ተነሣስቶ፣ ይኼ ምግባረ ቢስ፣ ሃይማኖታቸንን እያጠፋ ነው፤ ቤተ ክርስቲያናችንን እየዘረፈ ነው፤ ብለን ከሓላፊነቱ እንዲነሣ እንቅስቃሴ ጀመርን፤ ሥልጣነ ክህነቱም በቀኖና ቤተ ክርስቲያን እንዲመረመር አቤቱታ አቀረብን፤” ይላሉ – ምእመናኑ፡፡

አቤቱታውን የተቀበለው የሦስቱ አድባራት ሰበካ ጉባኤ፣ ከኹሉ አስቀድሞ የክህነታቸው ጉዳይ በአለቃው ንስሐ አባት በኩል እንዲታይ አድርጎ ችግር መኖሩ በሪፖርት ይገለጽለታል፡፡ ካህናት፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ወጣቶች ያሉበት በሰበካ ጉባኤው የተቋቋመ ኮሚቴም ይህንኑ የሚያረጋግጥ ማጣራት ያደርጋል፡፡ አለቃው መልአከ ብርሃናት ፍሥሓ ጽዮንም ተጠርተው የማጣራቱ ሪፖርት ይቀርብላቸዋል፡፡ እርሳቸውም፣ መቅደስ እንደማይገቡና የአስተዳደር ሓላፊነታቸውን በተመለከተበሰላም ለማስተካከል(በገዛ ፈቃዳቸው ለመልቀቅ) ተስማምተውና በቃለ ጉባኤው ላይ ፈርመው የኹለት ወራት ፈቃድ ይጠይቃሉ፡፡

yabelo-mariam
“የወሰዱትን ፈቃዳቸውን ሳይጨርሱ በቀን 29/01/2009 ዓ.ም. መቅደስ ገብተው ቃላቸውን አፍርሰዋል፤”
ይላል፣ በሦስቱ አድባራት ጸሐፊ ተፈርሞ ለክፍሉ ሊቀ ጳጳስ የተላከውና ችግሩ የመጨረሻ ውሳኔ እንዲሰጠው የሚጠይቀው ደብዳቤ፡፡ በዕለቱ፣ አለቃው መቅደስ ገብተው አገልግሎት ለመስጠት ሲጀምሩ ውዝግብ በመቀስቀሱ፣ ነገሩ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ከማምራቱ በፊት የተገታው በከተማው ጸጥታ ዘርፍ ትእዛዝና ጣልቃ ገብነት ነበር፡፡

አለቃው ቀደም ሲል ያመኑበትን በደላቸውን መሠረት አድርጎ ከተማው ሳይታወክ ሊቀ ጳጳሱ የመጨረሻ ውሳኔ እንዲሰጡ የሚጠይቅ 11 አባላት ያሉት የምእመናን የሰላም ኮሚቴ ባደረገው ጥረት፣ ኅዳር 3 ቀን በያቤሎ ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የተገኙት፣ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል፡- የሦስቱ አድባራት የአገልግሎት ክፍል(ቄሰ ገበዝ) እና የአለቃውን የመልአከ ብርሃናት ፍሥሓ ጽን ከበደን ንስሐ አባት ብቻቸውን በማናገር በቂ መረጃዎችን ተቀብለዋል፤ ከሦስቱ አድባራት ካህናት፣ ዲያቆናትና የስብከተ ወንጌል አባላት ጋር ባደረጉት ሰፊ ውይይትም በቂ ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል፡፡

በማግሥቱ ኅዳር 4 ቀን፣ በአለቃው በደል የደረሰባቸው ሴቶች ምስክርነታቸውን ሊሰጡ ሲቀርቡም፣ በቃኝ! ከዚኽ በላይ አያስፈልግም፤ በቂ መረጃዎችን ወስጃለኹ፤” ብለው መመለሳቸውን የአድባራቱ ጸሐፊ ደብዳቤ ያትታል፡፡ በዚኹ ዕለት በዐውደ ምሕረት ለምእመናን ባስተላለፉት ቃለ ምዕዳን፡- “ከደብሩ ካህናት ጋር ተነጋግረናል፤ ተወያይተናል፤ ኹሉንም ነገር ሰምተናል፤ አጣርተናል፤” ብለዋል፤ የችግሩ ኹሉ መንሥኤ መጠጥ መኾኑን የገለጹት ብፁዕነታቸው፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ በሕገ ቤተ ክርስቲያን መሠረት፥ ሰላማዊ፣ መጽሐፋዊ እና ቀኖናዊ ውሳኔ እንደሚሰጡ ተስፋ ሰጥተው ሕዝቡን ማሰናበታቸውን ደብዳቤው ጠቅሷል፤ በወረዳ ቤተ ክህነት ጽ/ቤትም ተገኝተው፣ ውሳኔውን በአስቸኳይ እንደሚልኩና፣ ይህን የሚቃወም ካለ ይሁዳ ነው፤ በማለት ሽማግሌዎችን መመረቃቸውን አውስቷል፡፡

ይህን ተከትሎም፣ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ፣ የአስተዳደር ሥራ እንዳይበደል ብለው ታኅሣሥ 3 ቀን በጻፉት ደብዳቤ፡- አለቃው መልአከ ብርሃናት ፍሥሓ ጽዮን ከበደ፣ ከአስተዳደር ሥራና ከውስጥ አገልግሎት ተቆጥበው እንዲቆዩና ሰበካ ጉባኤው በዋና ጸሐፊው፣ የውስጥ አገልግሎቱም በቄሰ ገበዙ እየተመራ እንዲቆይየባንክ ሒሳቡም በሌሎች ፈራሚዎች እንዲንቀሳቀስ በማዘዝ ጊዜያዊ እገዳ አሳልፈዋል፡፡
scan0022-1

ከዚኽ እገዳ በኋላ፣ በማስረጃና በማጣራት በተደረሰበት መሠረት ቀኖናዊና አስተዳደራዊ ውሳኔው ቢጠበቅም፣ scan0023እንደተባለው በአጭር ጊዜ ውስጥ ባለመድረሱ፣ መልአከ ብርሃናት ፍሥሓ ጽዮን ሕዝቡን በተለያዩ ውዥንብሮች ለማደናበር ጠቅሟቸዋል፡፡ “ለብፁዕነታቸው ይዤ እሔዳለኹ፤ ፈርሙልኝ” እያሉ ከያቤሎ እንዳይነሡ ድጋፍ ለማሰባሰብ ሞክረዋል፡፡ ይህም በማስረጃ ተረጋግጦ፣ ሲያስፈርሙ የነበሩ ኹለት ግለሰቦች በሕግ ቁጥጥር ሥር ውለዋል፤ የፈረሙ ጥቂቶችም በስሕተት እንደኾነ ቃላቸውን ሰጥተዋል፤ መልአከ ብርሃን ፍሥሓ ጽዮንም በከተማው አስተዳደር ፖሊስ ጣቢያ ተይዘው፣ ድርጊቱ ስሕተት መኾኑን ለከተማው ኮማንድ ፖስት አምነውና ፈርመው በመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ተለቀዋል፡፡

ኾኖም አለቃው፣ የብፁዕነታቸውን ትዕግሥት ተጠቅመው አማላጅ በመላክ፣ በልቅሶና በማሳዘን የውሳኔ ሐሳቦች እንዲቀያየሩና ርምጃው እንዲጓተት ከማድረግ አልተቆጠቡም፡፡ ይባስ ብለው፣ “ጉዳዩ በጓደኞቼ እንዲታይ አድርገዋለኹ” እያሉ መፎከራቸው ብዙኃኑን በማስቆጣቱ፥ ማኅበረ ምእመናን፣ አበው ካህናትና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች በሰፊው ከተወያዩበት በኋላ፣ ተወካዮችን ኹለት ጊዜ ወደ ሐዋሳ በመላክ፣ ለሕዝቡ ቃል በተገባው መሠረት የመጨረሻ ውሳኔ እንዲሰጣቸው በቃል ተማፅነዋል፤ በደብዳቤም ጠይቀዋል፡፡ የከተማው የፍትሕና ጸጥታ ጽ/ቤትም፣ አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጥ፣ በስልክም በደብዳቤም ብፁዕ ሊቀ ጳጳሱን በተደጋጋሚ መጠየቃቸው ተገልጧል፡፡

ከዚኽ ኹሉ በኋላ ግን፣ ታኅሣሥ 1 ቀን 2009 ዓ.ም.፣ ከሐዋሳ መንበረ ጵጵስና የተሰማው ውሳኔ፣ መልአከ ብርሃናት ፍሥሓ ጽዮን ከበደ፣ ከያቤሎ የሦስቱ አድባራት እልቅና ተነሥተው፣ ወደ ሻኪሶ ወረዳ ተዛውረው ሊቀ ካህናት/ሥራ አስኪያጅ/ ኾነው መመደባቸውን የሚገልጽ ብቻ ነበር፡፡

ምደባው፣ ከክህነት ይልቅ የአስተዳደር ሓላፊነትን ቢያመለክትም፣ የሥልጣነ ክህነታቸው ጉዳይ እልባት ሳያገኝ በዝውውር መመደባቸው ተገቢ አይደለም፤ በሚል ክፉኛ እየተተቸ ይገኛል፡፡ አለቃው መረን በለቀቀ ምግባረ ቢስነታቸው ክብረ ክህነታቸውን ያዋረዱ በመኾናቸው፣ በቀረቡት የማያወላዱ ማስረጃዎች መሠረት ሊቀጥሉ እንደማይችሉ ግልጽ ውሳኔ እንደሚተላለፍ ነበር የተጠበቀው፡፡

ዘግይቶ ከስፍራው እንደተሰማው ግን፣ መልአከ ብርሃናት ፍሥሓ ጽዮን፣ በክህነታቸው ምንም ችግር እንዳልተገኘባቸውና ከቀረቡባቸው አቤቱታዎች ነፃ መኾናቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ ከሊቀ ጳጳሱ ደርሷቸዋል፡፡ እርሳቸውም ደብዳቤውን እያዞሩ በማሳየት፣ ከሦስቱ አድባራት እልቅናቸው ላለመነሣት ካህናቱንና ምእመናኑን እያሳደሙና እየከፋፈሉ እንደሚገኙ ነው፣ የተዘገበው፡፡

በሌላ በኩል፣ የተመደቡበት የሻኪሶ ወረዳ፣ ቀደም ሲል በምግባረ ቢስነታቸው የሚታወቁበትና የተባረሩበት በመኾኑ፣ ዝውውራቸውን የሚቃወሙና እንዳይመጡብን የሚሉ አቤቱታዎች፣ ከወረዳው አገልጋዮችና ምእመናን ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጽ/ቤት እየደረሱ መኾኑን ለመረዳት ተችሏል፡፡

“የሐዋሳ መንበረ ጵጵስና ውሳኔ፣ በዚያም በዚኽም ላለችው አሐቲ ቤተ ክርስቲያን ፈተና ኾኖ ይቀጥላል፤ አርኣያነትም አይኖረውም፤” የሚሉት አገልጋዮቹና ምእመናኑ፣ በራሱ ጊዜ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ከማምራቱ በፊት፣ በቀረቡት ማስረጃዎችና በተደረጉት ማጣራቶች መሠረት ክብረ ክህነትን የሚያሳይና ለቤተ ክርስቲያን ሰላም የሚበጅ ቀኖናዊ ውሳኔ በአስቸኳይ እንዲሰጥ በጥብቅ አሳስበዋል፡፡

የካህናት ተልእኮ፣ ምእመናንን በመንፈሳዊ ሥነ ምግባር መምራት ነው፡፡ ይህን አገልግሎት ቸል በማለት ምንደኛ እረኛ ከኾኑና በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ሊጠብቁት የሚገባቸውን የማይጠብቁ፤ እንዳይሠሩ የተከለከለውን የሚሠሩ፤ ሕዝቡን በአርኣያነት የማያስተምሩና የማይመሩ ቀሳውስት ቢገኙ ከክህነታቸው እንደሚሻሩ በፍትሕ መንፈሳዊ ተደንግጓል፡፡


ቀሳውስት፣ በሕገ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ ጋብቻ ፈጽመው እያንዳንዳቸው በአንዲት የሕግ ሚስት ተወስነው ማገልገል ይገባቸዋል፡፡ በሕግ ተወስነው የመኖርን ጉዳይ ወደ ጎን በማለት ኹለት ጊዜ አግብተው ከኾነ ሥልጣነ ክህነታቸው ይሻራል፡፡

በሲሞን መሠሪ ሐሳብ ተጠምደው ጉቦ ሰጥተው የተሾሙ፣ በሐሰት የሚመሰክሩና የሚምሉ፣ የሚኮሩ፣ የክፋትን ሥራ የሚሠሩ፣ የሚሰክሩ፣ ኮከብ የሚቆጥሩ(የሚጠነቁሉ)፣ በአራጣ አብድረው አራጣ የሚቀበሉ፣ ከሴሰኛ ሴት የደረሱና ሲሰስኑ የተገኙ፣ የሚደባደቡ፣ የሰረቁ፣ የመናፍቃንን ቁርባን የተቀበሉ፣ አብረዋቸው የጸለዩ፣ አባለዘራቸውን በገዛ እጃቸው የሰለቡ፣ በገበያ መካከል የሚበሉ፣ በመሸታ ቤት የሚጠጡ፣ በአገልግሎት ምክንያት ሚስታቸውን የፈቱ፤ እመነኵሳለኹ፣ ተባሕትዎ እይዛለኹ ብለው ሚስታቸውን የተዉና ያሰናበቱ ካህናት ከሹመታቸው ይሻራሉ፡፡ (ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 6 ከገጽ 73 እስከ 74፤ 2ኛቀሌምንጦስ 4፤ 2ኛ ቀሌምንጦስ 5)

ቄስም ኾነ ዲያቆን ከሹመቱ ከተሻረ በኋላ ደፍሮ ለአገልግሎት ቢገባ፣ ከቤተ ክርስቲያን ተወግዞ ከአገልግሎት ይለያል፡፡ እያወቁ በዚኽ ድፍረት የተባበሩት ኹሉ ከምእመናን ይለያሉ፡፡ (ፍትሐ ነገሥት አን. 6 ረስጠብ 2፤ 2ኛቀሌምንጦስ 22)

ቄስ ታሞ በሚመረመርበትና በሚታከምበት ጊዜ ከአልኾነ በስተቀር በማንም ጊዜ ፈጽሞ ዕርቃኑን ሊጥልና ሊጋለጥ አይገባውም፡፡ “ወኢትዓረቅ ቀሲስ ግሙራ ቅድመ መኑሂ እምሰብእ ዘእንበለ በጊዜ ዐጸባ” (ፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 6 ክፍል 4 በስ. 53)

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.