የትግል አቅጣጫ አመላካች መግለጫ – ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት  

ሰኞ ታኅሳስ ፲፯ ቀን ፪ሺህ፱ .. ቅፅ ቁጥር

ከዚህ ወዴት? እንዴት?

የትግል አቅጣጫ አመላካች መግለጫ  - ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት   1 ንገተኛ ጎርፍ አምጥቷቸው የጀግንነት ከበሮ ሲደልቁ የቆዩት ወያኔዎች እራሳቸው ተደልቀው የታሪክ ትቢያ የመሆናቸው ጊዜ  ብዙ ያዘግማል የሚል ግምት የለም። እነዚህ ጎጠኞች የዘሩት የጎጥ ዘር እራሱ ሊጠራርጋቸው አፉን ከፍቷል። ወትሮውንም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ብሄረሰቦች ባሉበት አገር እንኳን እንደወያኔ ያለው የለየለት ዘረኛ ጉጅሌ ይቅርና አናሳዎች ፤ስልጣን ላይ ሲወጡ እምነት በማጣት ሌሊት ተቀን ሲባንኑ ፣ሲገድሉ ፣ ንጹሃንን ወደ ወህኒ ማጋዝ ስራቸው እንደሆነ ይታወቃል።

በቅርብ የተቀጣጠለው ጠንካራ የሕዝብ አመጽ ወያኔዎችን እንደልብ እንዳይቦርቁ ገትቷቸዋል። ይሁን እንጂ ወጣቶች በሰሜኑም ሆነ በምዕራቡ ኢትዮጵያ ያሳዩት የዐማራውና የኦሮሞው የደምና የትስስር አንድነት መፈክር የአናሳዎችን የቁም ቅዠት እጅግ አባብሶታል። አመጹ ወያኔን እየከበበውና እየዋጠው ቢሆንም ባንድ ሌሊት ይተናል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው። ይህ የሁለቱ ብሄረሰቦች የተባበረ እንቅስቃሴ ቀድሞውንም ለኢትዮጵያ መሰረት መሆኑ ግልጽ ነው። አሁንም ለጸናች ኢትዮጵያ መቀጠል ወሳኝነት አለው ።

ይሁን እንጂ በወጣቱ መካከል የሚታየው ይህ ተስፈኝነትና ትግል በሁለቱ ብሄረሰቦች ምሁራንና ፓለቲከኞች ስልታዊ ሕብረት ሲታገዝ አይታይም። የተጠናከረና የተቀናጀ ተግባራዊ የትግል ስልት ባጭር ጊዜ ውስጥ ምድር ላይ ሊታይ በተገባውም ነበር። የተያዘው ድል ቀላል ባይሆንም ቀጣዩ ትግል ነው የመጨረሻውን ምዕራፍ ለመደምደም የሚያበቃው። የጦርነት አበቃ ድል እወጃ ቅርብ አለመሆኑን መረዳት መዘናጋትን ያስቀራል። ባንዳንድ ወገኖች የሚታይ የድል ባለቤትነት ይገባኛል ሽሚያም  ወቅቱ አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን ትግሉን አያግዝም ። በዚያውም ላይ ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማም እንዳይሆን ያሰጋል።

ወያኔዎችና እነሱ የቀፈቀፏቸው ሌሎች መንደረተኛ ጽንፈኞች ዐማራውን ቃል መግለጽ በማይችለው መንገድ አሰቃይተው ፈጅተውታል። የችግሩ ክፋት የዐማሮችን ትዕግስት ገደብ ጥሶት፤ ቢያረፍድም ባነናል።ከዚህ ወዲህ ወደ ኋላ ላንመለስ መነሳታችን ብቻ ሳይሆን አቅላቻው የከዳቸውን ነፍሰ ገዳዮች የወይራ ዝንጣፊ ይዘን እንደማንጠብቃቸው ጠንቅቀው ሊረዱ ይገባል።

በሌላ በኩልም በዘር መደራጀት ወያኔ በቀደደው ቦይ መፍሰስ ነው የሚሉ ወግ አራቂዎች አሁንም አደብ አልገዙም። የኢሃዴግ የዘር ፓለቲካ እና የዐማራው መደራጀት ጭራሽ አይገናኙም ። ዱባና ቅል ለየቅል አሉ። እነዚህ የቅቤ አንጓቾች የማይመልሱት፣  መሰረታዊ ጥያቄ ለሚሞት፣ለሚሰደድ፣ለሚፈናቀለው፣በሃገሪቱ ዳርቻ ለሚዋከበው ዐማራ ማን ይቁምለት? እጣ ፋንታውስ ምን ይሁን ? የሚለው ነው፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነየሁላችንም የሆነችውን ኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ማስጠበቅ ለዐማራው ብቻ የሚሰጥ ሃላፊነት አድርጎ የማሰቡ ነገር ልክ ካለመሆኑም ባሻገር ለኢትዮጵያብሄርተኝነት መለምለም ሲባል ዐማራው ሲሞት ዝም ብሎ መታየት አለበት ለማለት የሚቃጣው ነው፡፡

የዐማራውን ሰቆቃ ለዘነጉት ወይንም አውቀው ለሚያድበሰብሱት በጥቂቱ እናስታውሳቸው። በዘመን የተለያዩ ፤በስፍራ የተራራቁ አያሌ ውጣ ውረዶች ዐማራውን ገጥሞታል። ይሁን እንጂ አሁን የገጠመው በአይነቱም ሆነ በይዘቱ የታሪክ አቻ የለውም። ሕይወትን ማቆየት ሕይወትን የሚያስከፍል ግጥምጥም የሆነበት ቀን የከዳው ሕዝብ ሆኗል።  ማንነታቸውን ሳይመርጡ አፍቅረውና ተፈቅረው በኖሩበት አካባቢ በጠራራ ፀሃይ ሕይወታቸውን እንደዋዛ አጥተዋል። ዐማራው መከራን በፀጋ መቀበል እጣ ፋንታው ይመስል ስጋው በእዋፋትና አራዊት ከርስ ውስጥ አዳሪ እንዲሆኑ ተደርጓል።የጃን አሞራው ጀግና ልጅ ለጥምብ አንሳ ግብር እንዲውል አድርገውታል። የባህልን አጥር ጥሶ ለዘመናት ሁሉም ቤቴ ብሎ የኖረው ዐማራ እንደጸጉረ ልውጥ ተቆጥሮ ባይተዋር ሆነ።የሰርክ ማንነቱን እንዲጥል ዐይኑን ባይኑ እንዳያይ አመከኑት። በዘረኞች እኩይ ቅስቀሳ የተነሳ በያካባቢው  ሕዝቡ በ«እንኳን ደህና መጣህ»ልቡን ከፍቶ ፤ፊቱን ፈትቶ፤እጁን ዘርግቶ መቀበሉ ቀርቶ የእንሰሳ እንኳን ማዕረግ ነፈገው። ይህ መከራ የተጫነው ሕዝብ ለዘመናት ለሁሉም እንዳልሞተ ሁሉም ዘመቱበት። የእርጥብ ፓለቲከኞች መሳለቂያ ሆነ። ብላቴና እህቶቻችን ወደ የአረቡ አለም እየተጋዙ የዝሙታን ርኳቤ ማስታገሻ ሆኑ።

 እነዚህ ጉብል ወጣቶች በተናጥልና በስውር የሚገጥማቸውን መሪር መከራ መጋፈጥ የአዘቦት የኑሮ እጣፋንታ ሆናቸው። ልዕለ ተፈጥራዊና-ልእለ ሰብአዊ መብታቸው ተገሰሰ። የዛሬዋ የወያኔ ኢትዮጵያ ለዐማራው ጓጉቶና ጎምዥቶ ዳሩ ግን ፈርቶና ሸሽቶ የሚኖርባት እንግዳ ምድር ሆነችበት።

ይህን ሁሉ ወደጎን በመተው ለአገራችንና ለሕዝባችን ቅድሚያ በመስጠት በብሔራዊ አጀንዳ ዙሪያ ለመስራት ፈቃደኝነታችንን አሳይተናል። ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት ቀደም ሲል የትግል የጋራ ትብብር አስፈላጊ መሆኑን በመገንዘብ በኢትዮጵያዊነታቸው ለሚያምኑ ወገኖች ሁሉ የትብብር ጥሪ ማድረጉ ይታወሳል። የተናጥልና የፊና ትግል ውጤቱ የወያኔን መንግስት ዕድሜ ርዝማን እገዛ ነው። ኦሮሞና ዐማራ ትግሉን ማጦዝ ይዟል። ሁሉም በታየውና በተቻለው መንገድ ትንንቁን ቀጥሏል። አሁን የምንዘናጋበትና የየራስ ሚናችንን እና ያስከተለውን ውጤት የምናውጅበት ወቅት ሳይሆን በጋራ የወያኔን ሃይል ማዋከብ የምንቀጥልበት ወቅት ነው። ዐማራ ዘንድ ጋብ አለ ሲባል ኦሮሞ ውስጥ ሲጦፍ ኦሮሞ ዘንድ ጋብ አለ ሲባል ዐማራ ትግሉን ሲያጋግለው የዘረኛውን መንግስት ጉልበት እየተብረከረከና ብሎም መንኮታኮት ይይዛል። ዳሩ ግን ሁኔታውን ሁነኛ በሆነ መንገድ ያልገመገሙ አንዳንድ ጽንፈኞች ይህንን የተጀመረ የጋራ ትግል አዳክመውና ለግላቸው ሚና የተጋነነ ድርሻ ገምድለው በመስጠት ሰልፉን ያበላሹ እለት የባሰ የትግል አቀበት የመግጠሙ ጉዳይ አያጠራጥርም። አንድ ግልጽ መሆን ያለበት ዐማራው ሞቷል። ተባሯል ተግዟል። ይህ ግን ይቆማል። ዐማራው ከዚህ በኋላ ዝምብሎ መሞት እንደለሌለ እቅጩን ተናግሯል። ስለሆነም ሁኔታው ያታለላቸው አንዳንድ የዋህ ወገኖች ሌላ ቅዠት ውስጥ እንዳይገቡ በጽኑ ልናስጠነቅቅ እንወዳለን።

ይህ ፳፭ ዓመት ለማንም ህሊና ላለው ሁሉ የሚያስተምረው ነገር አለ። ይሀውም ማንም ብቻውን ኢትዮጵያ ውስጥ ከዚህ በኋላ ስልጣን መፈናጠጥ እንደማይችል። «ጦርነት እንሰራለን» እያሉ ሲመጻደቁ የነበሩት የትግራይ ሽፍቶች ሳይቀሩ በወጣቶች ድንጋይ እየተፍረከረኩና መላው እየጠፋቸው ነው። ዱሮውንስ የጊዜ እንጂ የሰው ጀግና የለውም ተብሎስ የለ።

በየጊዜው የሚነሱ የፓለቲካ አለመረጋጋቶችንና ግብግቦችን  እያጀቡ የወጀብ አጃቢ ከመሆን በተቀናጀ መንገድ የፓለቲካውን ወጀብ ፈጣሪ ሃይል መሆንን የፓለቲካው ጉዞ የሚጠይቀው መሰረታዊ ጉዳይ ነው። ደግሞስ እስከመቼ ነው ንቁና ብቁ የሆኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችን ለሞት፤ለእስራት፤ ለስደት እየገበርን የምንቀጥለው? እስከመቼ ነው ወያኔ አንድ ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሌላ ጊዜ ኮማንድ ፓስት እያቋቋመ ዐማሮችንና ኦሮሞዎችን የሚጨፈጭፈው? ወያኔ የምርጫ ኮሮጆ በገለበጠበት የ1997 ምርጫ ማግስት በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ጀግኖች ኢትዮጵያውያንን ገብረናል።ብዙ አካለስንኩላንን አፍርተናል። ወደ አረቡ አለም ተሰደው የበረሃ ሲሳይ ሆነዋል። አሁንም እየሆነ ያለው ይሀው ነው።

ያለፈው ታሪክ ለትምህርታችን ያሁኑ ለጋራ ሕይወታችን ቀጣዩ ለመጪው ትውልድ መሆኑን ተረድተን በብልሃትና በጋራ አገራችንን ልንመራ ነባራዊው ሁኔታ ግድ ይለናል። ይህ ካልሆነ መሪነትን ለራስና ጽንፈኝነትን እንደግብና መታገያ ስልት አድርገን ከያዝን ነገም በተራችን አመጽ ጊዜውን ጠብቆ የምናገፈጠው ጭራቅ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው።ላንዴና ለመጨረሻ የዲሞክራሲን ስርአት ተክለን ሕዝባችንን ቀጣይነት ያለው እፎይታ እናጎናጽፈው።

የድርጅቶች የነጠላ ፓለቲካ ጉዞ የሰለቸው የኢትዮጵያ ሕዝብ በ 1997 ምርጫ ወቅት «ተባበሩ ወይም ተሰባበሩ» ማለቱን እናስታውሳለን። አሁንም ያልተመለሰው ጥያቄ ይሀው የተባበሩ ጉዳይ ነው። በውስጥ ያሉት የፓለቲካ ድርጅቶች በወያኔ ደህንነትና ፍርፋሬ ተቋዳሾች ለትብብር ስንክሳር ቢበዛባቸው አይገርምም። ከውጭ ያለነውን ወደ ሃላ የጎተተን ምን ይሆን? በሰለጠነው አለም እየኖርን በጠረፔዛ ዙሪያ ሆነን መነጋገርን ማን? ምን? ከለከለን። ለመሆኑ የባቢሎን ግንብ የሆነብን ቅጥር ምን ይሆን?

ለትብብርና አገርን ለማዳን በጋራ ለመስራት የተዘጋጀነውን ያህል ዐማራውን ካፈናቀሉ ፤ዘመን ሊቀየር እንደሚችል ዘንግተው ከወያኔዎች ጋር ወግነው ዐማራውን ካጠፉት ጋር መተባበር ሳይሆን ሁኔታዎች በሚፈቅዱ ወቅት ለፍርድ የምናቀርባቸው መሆኑ መታወቅ ያለበት መሆኑን ሞረሽ ወገኔ ከውዲሁ ያስገንዝባል።

ዐማራን ከፈጽሞ ጥፋት እንታደጋለን!

ድል ምንጊዜም የሕዝብ ነው!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.