የማለዳ ወግ …ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በጠና ታሟል ! – ነቢዩ ሲራክ

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ

ዛሬ በጠና የመታመሙን መረጃ የሰማነው ከብርቱው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝን ጋር ከአራት ዓመት በፊት በአዲሱ አመት ዋዜማ የአዲስ ዓመት ተገናኝተን የውስጥ ረመጥ ስሜትና ፍላጎቱን አጋርቶኝ ነበር ” … ነብዬ ወንድሜ፡- ሰው ነኝና ብዙ ነገር ይናፍቀኛል፣ ብዙ ነገር ያምረኛል፣ ፊት ለፊቴ ከሚታዩ ብዙ ነገሮችም ልቤ የፈቀደውን የራሴ ለማድረገ አስብና ‹‹ሰው ሰራሹ›› አጥር ያግደኛል፡፡ ከሚናፍቁኝም አንዱ እንደ አንተ አይነት ወዳጆቼ ጋር ያለ ስጋት ማውጋት ነው፡፡ ግና ምን ዋጋ አለው ዕድለኞች አይደለንምና ‹‹ለአቅመ ወግ›› አልታደልንም፡፡ … ” ብሎኝ ነበር … ዛሬ ከእኔ ጋር ቀርቶ ከወላጅ እናቱ ጋር እንዳሻው ማውጋትና መገናኘት ታግዷል ፣ ታሞ እንኳ እናቱና ቤተሰቡ እንዳያዩት ታግደው ቤተሰቡ በሰቀቀን ስቃይ ፣ እኛ አፍቃሪዎቹ በምሬት እዚህም እዚያም እያነባን እንገኛለን :

ይህ ሰላም ናፋቂ ወንድም ሀገሩን መወወደዱና ” ሀገሬን አልለቅም ፣ አልሰደድም !” ብሎ ከግል ጥቅሙ በፊት ስለ ሀገሩ የወደፊት ያለውን ራዕይ በመጻፍና በመናገሩ የግንባር ስጋ ሆኖ ግፍ እየተፈጸመበት ነው ። … ስለጻፈ ወንጄለኛ ተብሎ ተፈርዶበታል ። ይህ ም ይሁን ቢባል ፣ አመክሮው እንደ ታሳሪ ቢከለከል እግረ ሙቅ ገብቶበት ከጨለማ ክፍል ወዳልታወቀ ቦታ ፣ ካልታወቀው ቦታ ሲመለስ ጠያቂ ቤተሰብና በተለይም የእድሜ ባለጸጋዋ ጉስቁል እናቱ እንዳያዩት ተደርጓል ፣ እነሆ ባለፉት ቀናት ደግሞ ተሜ በጠና ታሞ ሐኪም ቤት የመተኛቱን የሚያም መረጃ እያማን ነው ! ይህ ሁሉ የግፍ በቀል እየተፋጸመበት ለመሆኑ የሀገሪቱ ህገ መንግስት የእስረኞች አያያዝ ህግ አንቀጽ 21 ተጥሶ ተመስገን እንደ ህግ እስረኛ በቤተሰብ ፣ በሀኪም ፣ በጠነቃና በሀይማኖት አባቶች ቀርቶ አምጣ በወለደች እናቱ እንዳይጠየቅ መከልከሉን መጥቀስ በቂ ነው ባይ ነኝ ፣ ይህ በጋዜጠኛ ተመስገን ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ እንደሱ የበረቱ ሀገር ወዳዶች በሀገሪቱ ሰማይ ስር ብቅ እንዳይሉ ፣ ካሉም ድምጻቸውን አጥፍተው አድርባይ አጎብዳጅ ሆነው እንዲኖሩ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ እንደ መቀጣጫ ለማድግ ታስቦ ከሆነ ከታሪክ አለመማር ይመስለኛል ፣ የታፈነ የህዝን ድምጽን እውነት እስካለው ድረስ በግለሰቦች ላይ በሚፈጸም ጭካኔ የተሞላሸት አያያዝ ትውልድን የማኮላሸት በቀል በየትኛው መንገድ ፣ በየትኛው ሃገር ሰርቶ እንደማያውቅ አሳሪዎች ሊገነዘቡት ይገባል ! …

ይህን ካልኩ ዘንዳ ለወዳጄ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ምህረቱን እየተመኘሁ በቋጠርኳት ስንኝ ልሰናበት !

አይዞህ …ተሜ !
===========
የተባው ሾተል ብዕርህ ፣
አላላውስ ቢላቸው
የእንቢ ላገሬ ስሜትህ ፣
ነዲዱ ወላፈን ሲገርፋቸው
ሃገሬን አልቀም ማለትህ፣
እንቅልፍ ሰላም ቢነሳቸው
እውነትክን እውሸት ማለት ፣
ሰላማዊው ሙግትህ ቢያቅታቸው
“አሸበረ ” ብለው መረጃ ማቅረብ ፣
ተሜን ማኮላሸቱ ቢገዳቸው
ብዕርክን ነውጠኛ ብለው አስገቡህ፣
መያዣ መጨበጫ ቢጠፋቸው !
ዳሩ ግና …
እጅና እግርን በካቴና እንደማሰር ፣
ህሊናን ማሰር አይቀልም ፣ አይቻልም!

እናም …
አይዞህ ወዳጀ ፣
ቀን አያልፍም ፣ ያልፋል
የደፈረሰው ጠርቶ ፣
የተሸፈነው ይገለጣል
የተንኳሰሰው ይነሳል ፣
አንኳሳሽ የእጁን ያገኛል
ግፍ በግፍ ባይመለስም ፣
ጨቋኝ በታሪክ ይወቀሳል
በሰፈረው ቁና ባይሰፈር ፣
የውርድትን ካባ ይለብሳታል
የጊዜ ወቅት ጉዳይ እንጅ ፣
ይህ አይቀርም ይፈጸማል
የጀግና እናት ካልመከነ ፣
ይህ ይፈጸማል ይሆንማል!

ተሜ … አይዞህ …

የቀራንዮ ጉዞህ ቢያምም ፣
የእማማን አንገት አስደፍቶ አይቀርም
“የኢትዮጵያን እናድን ” ጩኽትህ ፣
“ለእኔ አታልቅሱ !” ቃልህ ይሰምራልም
“ለትንሳኤው ተሰማሩ !” ሰላማዊ ጥሪህ ፣
ከወገንህ እዝነ ልቦና ተኖ አይጠፋም
ጊዜ እስኪያል ያልፋህ እንጅ ፣
ተገፍቶ ተረግጦ መኖርህ አይዘልቅም
ስማኝ ተሜ ! እውነቴ ነው የምለህ ፣
ዛሬ ከፍቶ ጊዜው ዘንበል ቢልብንም
በቀል ህመሙን አበርተቶብህ ፣
ልባችን መስበሩ ባይካድም
የድህነተየ ቀን ቅርብ ነው ፣
ከህመሙ ስቃዩ መዳንህ ግን ከቶ አይቀርም
የኢትዮጵያ አምላክ ጥሎ አይጥለንም ፣
የእማማ ጸሎት ምህላዋ አይከሽፍም
እስኪያልፍ መልፋትህ ዘልቆ ቢያምም
በቁጭት ቢያነደን ብንበግንም
ቀኑ ቅርብ ነው ይመጣል ፣
የኢትዮጵያ ትንሳኤ እንደሁ አይቀርም !
አይዞህ ተሜ ቆፍጣናው ፣
ኢትዮጵያ ሃገርህ ሰው አታጣም
እውነት እያደር ሲጠራ ፣
የአርበኝነት ክብርን አታጣም !

ነቢዩ ሲራክ
ታህሣሥ 19 ቀን 2009

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.