እንዲህ አይነት ግፍ በአገረ ኢትዮጵያ አይደገምም!!! – ከተማ ዋቅጅራ

ገዢው ህወሓት ውጥረት ሲበዛበት እና መፈናፈኛ ሲያጣ ሃሳብ ማስቀየሻ የሚመስል ነገር ግን አሰልቺ ውሸቶችን በየግዜው በመፈብረክ በEBC ላይ  በተደጋጋሚ በማቅረብ የኢትዮጵያን ህዝብ ውሸት በመሰልቸቱ ምክንያት EBCን ማመን ዘግቶ ነው እስከ ማለት የደረሰበት ደረጃ ላይ እንዳለ የሚታወቅ ሃቅ ነው። ህዝቡ በገዢው ፓርቲ የሚደርስበትን ዘርፈ ብዙ በደሎች እና ግፎች እንዳይደገም ጥያቄውን በሰላማዊ መንገድ ቢያቀርብም የሚሰጠው ምላሽ የተገላቢጦሽ ስለሆነ በግድ አፍኖ ለመግዛት የሚፈልግ ሁሉንም ነገር በሃይል ጨፍልቆ ማስተዳደር የሚፈልገው  አገዛዝ ሃይልን በሃይል በሚል መርህ መሰረት አስገዳጁን አስገድዶ ለመጣል ብረት ያነሱ ኢትዮጵያኖች ፍልሚያውን ከጀመሩ ሰነባብተዋል። በዚህም አመርቂ ውጤት እየተመዘገበ  እና ለነጻነት የሚታገሉ ታጋዮች ቁጥር እጅግ መብዛቱ   አይቀሬው ለውጥ መምጣቱ ገዢው ፓርቲ ስጋት ላይ መውደቁ እና ጭንቀት ውስጥ መግባቱ  እያየን ነው። ህዝብን ታግሎ ያሸነፈ በአለም ላይ እንደሌለ  ሁሉ የኢትዮጵያ  ህዝብ ከተጣለበት የጭቆና  ቀንበር መላቀቂያው ግዜ  እየመጣ ስለሆነ ህወሓት ያስቀመጠው የግፍ አሻራ ከፍተኛ  ዋጋ እንዳያስከፍለው አይደገም ብለን የምንጠይቀው ጥያቄ ለገዚው ፓርቲ እናቀርባለን።

 

ገዢው ፓርቲ ስህተትን በስህተት ማረም ሊያስከፍለው የሚችለውን ዋጋ  በቀላሉ ሊገመት እንደማይችል እሙን  ነው። አጥፊዎቹ ሳይቀጡ ያላጠፋውን ህዝብ መቅጣት አርፎ የተኛን በሬ እየነካኩ አውሬ ማድረግ ነውና በህዝብ ላይ የሚወሰደውን ማንኛውንም እርምጃ በአፋጣኝ በማቆም የታሰሩትንም የህሊና  እሰረኞችን በሙሉ በመፍታት፡-  ህዝብን የገደሉ ህዝብን ያፈናቀሉ እና  ያሰሩ እንዲሁም ያሰቃዩ ለፍርድ በማቅረብ ከላይ ተቀምጠው አገርን የሚያተራምሱ  ስህተታቸውን እንዳይደግሙ ቅጣታቸውን መቀበል ይገባቸዋል እንጂ መገፋቱን፣ መበደሉን፣ መረገጡን፣ ነጻነቱን መነጠቁን፣ በአገሩ የመኖር መብት የተነፈገን ህዝብ የጠየቀውን ጥያቄ እንደ ስህተት በመቁጠር የተለያየ  ነገር በመለጠፍ  የኢትዮጵያን ህዝብ በሙሉ ስህተተኛ  በማድረግ አይደገምም በሚል በEBC ላይ የተሰራው አሰልቺ የውሸት ድራማ ህዝቡን ወደ በለጠ ቁጣ  እና  ትግል ይጋብዘዋል እንጂ የሚፈይደው አንዳች ነገር የለም።  አይደገምም የምትለውን ቃል ትክክለኛ አጥፊዎችን በመቅጣት ቢሆን ኖሮ ሊመጣ  ያለውን አደጋ  ይቀንሰዋል።

 

አይደገምምን ካነሳን ገዢው ፓርቲ የሚከተለው ፖሊሲ በጣም አደገኛ  በመሆኑ ስህተቶችን ከወዲሁ አርሞ ወደ ህዝቡ ሃሳብና ጥያቄ ወደመመለሱ ካልሄደ በያዘው አቋም አፍኜ እና  ረግጬ አንዱን ከሌላው አለያይቼ እና  አጣልቼ ስልጣኔን አራዝማለው የሚለው አካሄድ አደገኛነቱ ማን ላይ እንደሚከፋ የታወቀ ስለሆነ ሰሚ ጆሮ ካለ ይስማ  አስተዋይ ልቦና ካለ ወረድ ብሎ ያስተውል ገዢው ፓርቲ የሚከተለው አጥፊና የተሳሳተ ፖሊሲ እንዳይደገም አድርጎ  በማጥፋት እውነትን ይዞ መጓዙ የሚጠቅመው ለገዢው አካል ነው።

 

ወደ ላይ የወጣው ሹመኛ  በሚንስቴር ደረጃ ይሁን በአንባሳደር፣ በመከላከያ ሰራዊት ይሁን በሲቢል ተቋም፣ በአየር መንገድ ይሁን በመንገድ ትራንስፖርት፤ በአጠቃላይ በስልጣን ወንበር ላይ የተቀመጡት በሙሉ መሾም ያለባቸው በእውቀታቸው ሆኖ ለአገር እና  ለህዝብ ታማኝ አገልጋይ መሆን የተገባቸው ሲሆን በዘመነ  ኢህአዴግ የሚሾሙት ሹመኛ  በሙሉ የፓርቲ አገልጋይ የሆነ  ብቻ እና  ብቻ  ነው። ስልጣንም ሆነ የተለያዩ  የእድገት እርከኖችና ማእረጎች የሚሰጣቸው ለአገር እና  ለህዝብ ላበረከቱት አስተዋጽኦ ሳይሆን ፓሪቲያቸውን በታማኝነት በደንብ በማገልገላቸው ሙያቸው ከሚፈቅድላቸው ውጪ የሰውን ማንነት በመሰለል መረጃ  በመስጠት የሚተጉትን በሹመት ላይ ሹመት በማእረግ ላይ መአረግ በሃብት ላይ ሃብት ይምነሸነሻሉ እንጂ ለሚሰሩት ጥፋት የሚጠይቃቸው ማንም የለም። ታዲያ  ይሄንን ሁሉ ጉድ ህዝባችን ጠንቅቆ  ያውቀዋል ይሄንን እያወቀ  ጥያቄውን በሰላማዊ መንገድ እየጠየቀ ነው። የአንድ ፓርቲ የበላይነት ይብቃ፣ ህወሓት ከአሁን በኋላ አያስተዳድረንም በማለት ግልጽ እና  ዲሞክራሲያዊ ጥያቄዎችን በመጠየቅ ላይ ናቸው። የተሰጣቸው መልስ ግን ዝም በሉ በሚል መንፈስ ከፍተኛ  ኃይል በመጠቀም የመጨረሻ መፍጨርጨር እያደረጉ ይገኛሉ ። ተዉ ተመከሩ ከተመከራችሁ እና  ስልጣንን ለህዝብ ካስረከባችሁ ለአገርም ለህዝቡም ሰላም ይነግሳል የለም የምትሉ ከሆነ  መከራ እራሱ ጠራርጎ ያጠፋችኋል ይሄ ከመሆኑ በፊት ማምሻም እድሜ ነውና  በቀራችሁ ጥቂት ግዜ ከሰራችሁት ታሪክ ከማይረሳው ስህተት ለመውጣት ስልጣንን ለህዝብ በማስረከብ በእውቀት በእውነት እና በቅንነት አገርን እና ህዝብን የሚያገለግል መሪዎችን ወደ ላይ በማምጣት ስህተተኞችን ኣና ግፍ የፈጸሙትን ለሰሩት ጥፋት ተመጣጣኝ ቅጣት በመስጠት በኢትዮጵያ  ምድር ማንም ሰው ከሰራው ጥፋት ከቅጣት አያመልጥም አገር እና  ህዝብን የሚበድል መሪም ሆነ  ባለስልጣን በሰራው በደል አይጠየቅም ወይንም የፈለገውን ማድረግ ይችላል የሚለው አሰራር ወይንም ህግ በማጥፋት አጥፊዎችን የማይቀጡባት ፈጽሞ በኢትዮጵያ  ምድር አይደገምም የሚለውን አሰራር መስራት ተገቢ ነው።

 

ሳጠቃልለው፡ በራስህ እንዲደረግብህ የምትጠላውን ነገር በሌላው ላይ አታድርግ። አገርን የሚያጠፋ እና ህዝቡን ወደ መከራ  የሚያስገባ ስራን በመስራት ማንም ይሁን ማን በአገር ቤትም ሆነ  በውጪም የሚንቀሳቀሱ ኢትዮጵያን ለአደጋ  የሚያጋልጥ  ስራ  የሚሰሩ እና  ህዝቦቿንም ለከፋ  መከራ ለመዳረግ የሚንቀሳቀሱ በሙሉ የኢትዮጵያ  ህዝብ እና  የኢትዮጵያ  አምላክ እንዳይደገም አድርጎ ቅጣታቸውን እንደሚሰጣቸው ቅንጣት ያህል አልጠራጠርም። ላይደገሙ የሚጠፉ የህዝብ እና  የአገር ጠላት ቢኖሩም በግንባር ቀደም ግን አሁን በስልጣን ላይ ያለው ገዢው ፓርቲ ነው። አበቃው።

 

ከተማ ዋቅጅራ

28.12.2016

Email- waqjirak@yahoo.com

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.