በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የኢህአዴግ አባላት አስቸኳይ ስብሰባ የተጠሩበት ግምገማ ያለውጤት ተበተነ

ብርሃኑ አየለ

ትናንት ምሽት በጽሁፍ በተላለፈ አስቸኳይ ስብሰባ ዛሬ ቅዳሜ ታህሳስ 22 ቀን ከጠዋቱ 2 ሰዓት ጀምሮ እስከ ቀኑ 7 ሰዓት በየቀበሌው በተካሄደው የኢህአደግ ስብሰባ የተሳተፉት የህዝብ ተወካይ ተብለው በህወሃት እንዲደራጁ የተደረጉ የየቀበሌውና ክፍለ ከተማው ምክር ቤት አባላት፤ የሴቶች፤ የወጣቶችና በተለያዩ ስሞች የተደራጁ ፎረሞች ጠቅላላ አባላት እንደሆኑ ታውቆአል። በመላው አገሪቱ የሚገኙ የኢህአደግ ከፍተኛ አመራሮችና የክልል መስተዳድር ሃላፊዎች እንዲሁም ካድሬዎች ከ24 ሰዓት ባነሰ ጊዜ በተላለፈላቸው አስቸኳይ ጥሪ አዲስ አበባ ውስጥ ተገናኝተው ስብሰባ መቀመጣቸው በተዘገበ ማግስት አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ያሉትን አባላት በሙሉ በተመሳሳይ መንገድ በአስቸኳይ ስብሰባ ጥሪ መሰብሰብ ለምን እንዳስፈለገ ጥያቄ የፈጠረባቸው ምንጮች እንደሚሉት ለውይይት የቀረበው አጀንዳ የተለመደው የግምገማ ጉዳይ ብቻ መሆኑ የበለጠ ግራ እንዳጋባቸው ገልጸዋል።

ዛሬ በተደረገው በዚህ አስቸኳይ ስብሰባ ኢህአደግ ሁለት ትላልቅ ፈተናዎች እንደገጠሙት ለአባላቱ የገለጸ ሲሆን እነርሱም በራሱ በድርጅቱ ውስጥ የሰፈነው ኪራይ ሰብሳቢነት፣ ጠባብነትና ትምክህተኝነት ናቸው ተብሎአል። እነዚህን ሁለቱን ፈተናዎች ለመዋጋትና ድርጅቱ የገጠመውን መሰናክል ለማለፍ  ጥልቅ ተሃድሶ ማካሄድ አስፈላጊ መሆኑን በአስቸኳይ ስብሰባ ለተጠሩት አባላቱ የገለጸው ኢህአደግ፣ ሁሉም አባላቱ እራሳቸውን እንዲገመግሙና እርስ በርስም እንዲገማገሙ አዞአል። ሆኖም ግን እርስ በርስ በይፋ ተገማገሙ የሚለው ትዕዛዝ ማን በማን ላይ ትችት እንዳቀረበ እንዲታወቅ በማድረግ ምናልባት እንዳይነኩ በሚፈለጉ ሰዎች ላይ ሊሰጥ የሚችለው አስተያየት ለተለመደው ጥቃት እንዳይዳርጋቸው ስጋታቸውን በመግለጽ በሚስጥር በሚሰጥ ጽሁፍ ካልሆነ በቀር ግምገማ አናደርግም እንዲሉ እንዳደረጋቸዋል። በዚህም የተነሳ የዛሬው ስብሰባው ያለ ውጤት እንዲበተን እንደተደረገ ምንጮች ተናግረዋል። በዚህ ያልተጠበቀ የአባላት እምቢተኝነት ግራ የተጋቡ የውይይቱ መሪዎች፣ ስብሰባው ለነገ ዕሁድ ታህሳስ 23 እንዲተላለፍና የተባለው የምስጢር ግምገማ እንዲካሄድ የበላይ አለቆቻቸውን ፈቃድ ይዘው እንደሚመለሱ በመግለጽ ተለያይተዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ዛሬ ተካሂዶ በነበረው የኢህአደግ አባላት ስብሰባ ላይ ተቃውሞ ያስከተለው ሌላው ጉዳይ የአባላቱ አስተያየትና ድጋፍ ሳይጠየቅ ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ የተደረጉ፣ ለሹመት የታጩና ወደሌላ ሃላፊነት እንዲዛወሩ የተደረጉ አስተዳደርና የካቢኔ አባላት ስም ዝርዝር ለግምገማ ቀርቦ ደምጽ ማግኘት አለመቻሉ ነው። እናንተው እራሳችሁ ግምገማችሁ ለሹመት ካጫችሁ፣ ለዝውውር ከመደባችሁና ከቦታ ለማስነሳት ከወሰናችሁ በኋላ የኛን አስተያየት መጠየቅ ተገቢ አይደለም ያሉ አባላት ያቀረቡዋቸው የሰላ ትቺትና ያሳዩት የጠነከረ ተቃውሞ ለአወያይነት የተላኩትን ሃላፊውች ክፉኛ  እንዳስደነገጠም ተያይዞ የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

በመላው አገሪቱ በተነሳው ህዝባዊ ተቃውሞ የበታች ሹማምንቶችንና የመንደር ካድሬዎቹን በአቅም ማነስና በሙስና በማባረር ጥልቅ ተሃድሶ አድርጌአለሁ ብሎ እንደ አዲስ የንግሥና ዕድሜውን ለማራዘም ደፋ ቀና እያለ ያለው ህወሃት በአብዛኛው አባላቶቹ ዘንድ ጭምር ትዝብት ውስጥ እየገባ እንደሆነና አሜኔታ እያጣ እንደመጣ ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ የተደረገው የአባላት ስብሰባ ማሳያ ነው ሲሉ መረጃውን ያደረሱን ገልጸዋል።

ኢህአዴግ ለነገ ባስተላለፈው የአባላት ስብሰባ የሚደረገውን ግምገማ ውጤት ካዳመጠና ለሹመት ያዘጋጃቸውን አባላት እንዲያጸድቁለት ካደረገ በኋላ ህብረተሰቡን ለሰኞ ታህሳስ 24 ጠዋት ጠርቶ በማወያየት ብሶታቸውን ለመስማትና ጭዳ ሊያደርጋቸው ያዘጋጃቸውን አባላቱን በማባረር ወይም ወደ እስር ቤት በመላክ ጥልቅ ተሃድሶ እንዳደረገ ለማብሰር በዝግጅት ላይ እንደሚገኝም እነዚሁ ምንጮች አስረድተዋል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.