በህወሓት የበላይነት ስር የሚገኘው የኣገር መከላከያ ሠራዊት ከ25 ዓመታት በኋላ በድጋሚ ሲፈተሽ

(በአርበኞች ግንቦት 7 ጥናትና ምርምር ቡድን የተዘጀ)
ታህሳስ 2009 ዓ.ም.
መግቢያ

የዛሬ  ሰባት አመት (እ.ኤአ. 2009) ያኔ “ግንቦት 7- የፍትህ፤ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ” ይባል የነበረውና አሁን አርበኞች ግንቦት 7: የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ ውስጥ የተጠቃለለው ድርጅት በዘር የተደራጀዉን የወያኔ መከላከያ ተቋም አደረጃጀት ምን እንደሚመስል በመረጃ አስደግፎ ለኢትዮጵያ ብሎም ለዓለም ማኅበረሰብ ማቅረቡ የሚታወስ ነዉ። ያ ጥናታዊ ሪፓርት ለዓለም ዓቀፍ ማኅበረሰብም ቀርቶ አገዛዙን ትዝብት ላይ በመጣሉ “የመካከያ ሠራዊታችንን ብሄራዊ ተዋጽዖ እናመጣጠንን ነው” የሚል ፕሮፖጋንዳ የወያኔ ኣገዛዝ መንዛት ተጀመረ።

በዝቅተኛና በተራ ውትድርና ደረጃ መመጣጠን መኖሩ ድሮም ጥያቄ ተነስቶበት አያውቅም። ድሮም አሁንም ጥያቄው ያለው በሠራዊቱ አመራር ላይ ያሉት እነማን ናቸው የሚለው ላይ ነው። በዚህ ረገድ በእርግጥ እንደሚባለው ለውጥ አለን? ይህ ጽሁፍ ይህንን ጥያቄ ለመመለስ የተደረገ ጥናት ውጤት ነው።

የጥናቱ ውጤት እንደሚያሳየው የአገዛዙ ሠራዊት አመራሮች የብሄር ተዋጽዖ በተመለከተ ዛሬ ሰባት ዓመት ከነበረው እጅግም የተሻለ ነገር የለም። በህወሓት ስር የሚገኘው የሀገር መከላከያ ሠራዊት የፓለቲካ ሥርዓት ለውጥ ከተደረገ  ከሃያ አምስት ዓመታት በኋላም 6% ብቻ የሆነውን የትግራይን ሕዝብን አንወክለዋለን በማለት በሚነግዱ የትግራይ ብሄር ተወላጆች  የበላይ ኃላፊነት፣ እዝና ቁጥጥር ስር ወድቆ እናገኛለን። ይህ ጥናት እንደሚያሳየው የኣሮሞና የኣማራ ብሄሮችም ሆኑ ሌሎችሁ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች በመከላከያ ሠራዊቱ የኃላፊነትና የእዝ ቦታዎች ላይ  እጅግ ዝቅተኛ ወይንም ከነኣካቴው ምንም እይነት የኃላፊነት ድርሻ የላቸውም። ይህ ያገጠጠ ኢ-ፍትሃዊነት  ኣንድምታው ህሊና ላለው ኢትዮጵያዊ  ሁሉ ምን ማለት መሆኑ ግልጽ ነው ብለን እንገምታለን። ዛሬም እንደትናቱ ኢትዮጵያ ዉስጥ ወያኔ ለፈጠረዉ ዘረኛ ስርዐት ብቸኛ ምሳሌ ሆኖ መቅረብ የሚችለዉ በቀድሞዋ ደቡብ አፍሪካ ዉስጥ ነጮች ፈጥረውት የነበረው ዘረኛ (Apartheid) ስርዐት ብቻ ነዉ።

በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ዉስጥ በተለይ በቁጥሩ ከፍተኛ ብልጫ ያለዉና ትግርኛ ተናጋሪ ያልሆነዉ ሠራዊት እጅግ ያኮረፈ፤ የተቆጣና ያመረረ ሠራዊት ከመሆኑ የተነሳ እራሱን የሚመለከተዉ እንደ አገር መከላከያ ሠራዊት አባል ሳይሆን አንደ ህወሓት የቤት ዉስጥ አገልጋይ ባሪያ ነዉ።  ይህ የህወሓት ዘረኞች በሠራዊቱ ላይ የፈጠሩት የመገዛትና የበታችነት ስሜት በየቀኑ ከፍተኛ ቁጣና የውስጥ ለውስጥ ተቃውሞ የሚገጥመዉ ቢሆንም ህወሓት በዘረጋዉ ከፍተኛ የአፈና መረብ የተነሳ የሕዝብ መነጋገሪያ አርዕስት መሆን አልቻለም። የህወሓት መሪዎችም ቢሆኑ ይህንን ቁጣና ተቃዉሞ በሚገባ ስለሚያዉቁ “ግምገማ” እያሉ በሚያዘጋጇቸዉ መድረኮች ላይ እንደነዚህ አይነቶቹን የህወሓትን የበላይነት ላይ የሚነሱ ጥያቄዎችን ማስተናገድ ቀርቶ ጥያቄዎቹ እንዲነሱም አይፈቅዱም። አንዳንዴ ደፍረዉ እነዚህን ጥያቄዎች የሚያነሱ ግለሰቦች ሽብርተኛ፤ የደርግ ስርዐት ናፋቂዎች፤ ጠባብ ብሄረተኞች ወይም የጥላቻ ፖለቲካ አራማጆች የሚል ተቀጥላ ስም ይሰጣቸዋል። ዛሬ ዕድሜ ልክ እስራት ተፈርዶባቸዉ በተለያዩ የወያኔ እስር ቤቶች ዉስጥ የሚሰቃዩት ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች ለዚህ አሳዛኝ ሁኔታ የበቁት በመከላከያ ተቋሞች ዉስጥ ሠራዊቱን በዬትኛዉም እርከን የሚመሩ መኮንኖች አመዳደብ ወታደራዊ አመራር ችሎታን፤ ልምድንና የብሄር ስብጥርን ያካተተ መሆን አለበት ብለዉ ደፍረዉ በመናገራቸዉ ነዉ።

የወያኔን መከላከያ ሠራዊት እየለቀቁም ሆነ ትግሉን አየተቀላቀሉ  የመከላከያ ሠራዊት ኣባላት ቁጥር ቁጥር በየቀኑ እየጨመረ በመሄድ ላይ ይገኛል። እነዚህ ወታደራዊ መሪዎች፤ የበታች መኮንኖች፤ ባለሌላ ማዕረጎቸችና ተራ ወታደሮች ከጠላት እንከላከላን ብለዉ የማሉላትን እናት አገራቸዉን እየለቀቁ የሚወጡት በወያኔ ጦር ዉስጥ ስር የሰደደዉ ዘረኝነትና በዚህ ዘረኝነት ላይ የተመሰረተዉ አመራር የሚያደርስባቸዉ በደል አንገፍግፏቸዉ ነዉ። ዛሬም  አንደትናቱ በየጎረቤቱ አገር ተሰድደዉ በችግር ላይ የሚገኙ ምርጥ የኢትዮጵያ የሚሊታሪ ሳይንስ አዋቂዎች ሁሉም በአንድ ድምፅ የሚናገሩት ሠራዊቱ ዉስጥ ይድርስባቸዉ የነበረዉ ንቀትና ዉርደት የሰዉ ልጅ መሸከም ከሚችለዉ በላይ መሆኑን ነዉ።

በኢትዮጵያ ውስጥ ወያኔ በገነባዉ መከላከያ ሠራዊት ውስጥ የዕዝ፤ የክፍለጦርና የመምሪያዎች አዛዥ ለመሆን ዋነኛዉ መለኪያ የህወሓት አባል መሆን ነዉ እንጂ ችሎታ፤ ልምድ፤ ብቃትና የወታደራዊ ሳይንስ ክህሎት አይደለም። ችሎታ፤ ልምድና ብቃት መመዘኛ ሆነዉ የሚቀርቡት በመጀመሪያ ለሹመት የታጨዉ መኮንን ህወሓትነት ከተረጋገጠ በኋላ ብቻ ነዉ። በህግ የመከላከያ ሠራዊት አባላት የፓለቲካ ድርጅት አባላት አይሆኑም፤ በተግባር ግን ለሹመት የሚያሳጨው የፓርቲ አባልነት ነው።

አንደሚታወቀው የህወሓት የስልጣን ሞኖፖሊ በወታደራዊ ደህንነት ተቋሞች ላይ ብቻ ተወስኖ አያበቃም። አብዛኛዉን የአገሪቱ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ተቋሞችም ወይ ከላይ አለዚያም ከታች ሆነዉ ይቆጣጠራሉ። ዛሬ ኢትዮጵያ ዉስጥ ለይስሙላ የተቀመጠና ከተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች የመጡ ሰዎች የሚገኝበት መንግስት አለ፤ በዚህ መንግስት ዉስጥ ደግሞ አገሪቱን ወዳሰኘዉ አቅጣጫ በዘፈቀደ የሚዘዉረዉና ከትግርኛ ተናጋሪዎች ዉጭ ሌሎች የማይገኙበት በመንግስት ዉስጥ ሌላ መንግስት አለ። የሚገርመዉ ዛሬ እነ ኃ/ማሪያም ደሳለኝ፤ አባዱላ ገመዳና ደመቀ መኮንንን የመሳሰሉ ምስለኔዎች ስልጣን ላይ የተቀመጡ ነገር ግን ህወሓት ጌቶቻቸዉ ከሚነግሯቸዉ ዉጭ በራሳቸዉ ምንም ዓይነት ትዕዛዝ መስጠት የማይችሉ አሻንጉሊቶች መሆናቸዉን እነሱ አራሳቸዉም የተገነዘቡት ይመስላል።

በዚህ በወቅታዊ መርጃዎች ላይ በመመስረት በኣርበኞች ግንቦት 7 የወታደራዊ ጥናት ቡድን ተሻሽሎና ታድሶ በኣዳዲስ መረጃዎች በተጠናቀረው ጥናት ቀጥሎ የሚቀርበዉ ሠንጠረዥ የተለያዪ የመከላከያ ተቋም የኃላፊነትና የእዝና ቁጥጥር ቦታዎችን፤ በእነዚህም  ቦታዎችን እነ ማን እንደተቀመጡና  የተወለዱበት ብሄረሰብ  ያሳያል።

በዚህ ሠንጠረዥ ያልተመለከተ ሌላ አቢይ ጉዳይም አለ። ይህም በእስር ላይ ከሚገኙ የሠራዊቱ መኮንኖች ውስጥ እጅግ የበዙት የአማራና የኦሮሞ ተወላጆች የመሆናቸው ሀቅ ነው። በጄኔራል ተፈራ ማሞና ጄኔራል አሳምነው ጽጌ ጋር በተያያዘ እነሱን ጭምሮ በርካታ ባለከፍተኛ ማዕረግ የአማራ ተወላጆች ታስረዋል፤ ከዚህ በቁጥር የበዙት ከሠራዊቱ ተባረዋል። ከጄኔራል ከማል ገልቹና ጄኔራል ኃይሉ ጎንፋ ጋር ተያይዞ እንደነዚ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የኦሮሞ ተወላጅ መኮንኖች ታስረዋል፣ ተባረዋል። አገዛዙ ውስጥ ችግር በደረሰ ቁጥር የችግር መወጫ የሚሆኑን የአማራ፣ የኦሮሚያና የሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች ተወላጅ የሆኑ መኮንኖች ናቸው።

[ሙሉውን ለማንበብ እዚህ ይጫኑ]

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.