የማለዳ ወግ … የዲፕሎማሲያችን ክሽፈት ! [ነቢዩ ሲራክ]

* የከሸፈው የኢራን ዲፕሎማሲ
* የከሸፈው የእኛ ዲፕሎማሲ የእኔ ማስታወሻ

ነቢዩ ሲራክ
ነቢዩ ሲራክ

ቀዳሚ የወጌ ማጠንጠኛ የሳውዲና የኢራን ጉዳይ ከቶ አልነበረም ። ዳሩ ግን ትኩሱን መረጃ ነካክቸ ልለፈው በሚል የከሸፈው የኢራን ዲፕሎማሲያዊ የሚል መግቢያ ቢጤ መሞነጫጨርን ወደድኩ …
ቀጠልኩበት !

ሳውዲ የኢራንን ኤምባሲ መዝጋቷን ተከትሎ ባህሬንና ሱዳን በተመሳሳይ ሁኔታ ከኢራን ጋር ግንኙነት ማቋረጣቸውን እየሰማን ነው ። ኢራን ለሳውዲ ኤምባሲ መቃጠል ለተባበሩት በላከችው ደብዳቤ ይቅርታ ብትጠይቅም ያቀጣጠለችው እሳት ከኢራን አልፎ ወደ ባግዳድና ባህሬን እየተሰራጨ ነው ። በኢራቅ የሸአ እምነት ተከታዮች ሳውዲን ተቃውመው ሰልፍ ወጥተዋል ። በላዩ ላይ የሱኒ እስልምና ተከታዮች መስጊድ ተቃጥሏል ። አየሩ ደስ አይልም !

የሰመረ ግንኙነት ሊኖራቸው የሚገባ ሁለት ጉልበታም ሐገራት በከፋ ፍጥጫ ላይ መሆናቸው እውነት ሆኖ የፖለቲካና ርዕዮቱ ዳራ መጨበጫ ጠፍቶታል ። በዚህ መንገድ በከሸፈ ግንኙነት ላለፉት ግማሽ ክፍለ ዘመናት የዘለቁት ሳውዲና ኢራን ዛሬም በለየለት የቃላት ጦርነት ተጠምደዋል ። እኛም የቃላት ጦርነት ጩኸት ሁከቱን ተከትለን በአገራችን ፖለቲካ እንደተለያየነው “ኢራን ልክ ናት ሳውዲ ልክ ናት! ” ጎራ ለይተን ላንግባባ በሰው ሀገር ጉዳይ እንድንፈተፍት ግድ ሆኗል። ለዚህ ሁሉ ለምንሰማው የቃላት ጅምር ጦርነትም ከሳውዲ የሞት ቅጣት የተተገበረ ብይል በላይ የኢራን ፖለቲከኞች ሸአው የሀይማኖት መሪ መገደል ምክንያት አድርገው በኢራቅ ፣ በየመን ፣ በባህሬን በሶርያ በቀሩት ሐገራት ያልሰመረው እጅ አዙር ትንኮሳ አጋግለው ያራግቡት ይዘዋል። በሀገሪቱ ምስራቃዊ ክፍል የሚገኙ የሸአ እምነት ተከታዮችን ለአመጽ የሚያነሳሳ አስተምሮት በላይ የሳውዲን ንጉሳዊ ቤተሰብ ለማስዎገድ በመቀስቀሳቸው የሞት ፍርድ የተሰጣቸውን የሳውዲ ሸአ የሃይማኖት አባት ምክንያት ያደረገው የዛሬ ፍጥጫ ቆስቋሿ ኢራን ለመሆኗ ብዙ ማሳያዎችን ማቅረብ ይቻላል።

የሽብር ተጠቂው ጋዜጠኛና የሟቹ ቤተሰቦች ቃል …
====================

በሳውዲ መንግሥት አንገታቸው ከተቀሉት 47 ሰዎች የሽብር ጥቃት ብዙ ንጹሃን ተገድለዋል ። ዛሬ ለማጣቀሻ ማነሳው ጋዜጠኞቹን ይሆናል ። በሳውዲ በሞት ከተቀጡት መካከል በ2004 ሪያድ ውስጥ በዘገባው ላይ የነበሩትን የቢቢሲውን ዘጋቢ ፍራንክ ጋርደነር Frank Gardner በስድስት ጥይት አቁስሎ የ36 አመት ጎልማሳውን አይርሻዊ ሳይመን ኩምበርስን Simon Cumbers ነፍስ የቀጠፈው የአልቃኢዳ ነፍሰ ገዳይ አድል አል ዱበይቲ ይገኝበታል …
ዛሬ በደረሰበት ጥቃት የአካል ጉዳተኛ ሆኖ በሕይወት ያለው የቢቢሲ ጋዜጠኛው ገዳዩን እንዲያገኘው ተጠይቆ የዱበልቲ ቤተሰቦች ደብዳቤ ጽፈው ይቅርታ እንዳደርግለት የጠየቁኝን ያህል እኔን አሰናክሎ ጓደኛዬን የገደለው አል ዱበይቲ በፈጸመው ወንጀል ተጸጽቶ ይቅርታ ያልጠየቀውን ክፉ ሰው ማየት አልፈልግም ። ለምን አየዋለሁ ? ምንስ ለማግኘት? እሱ እንደሁ በቁሙ ነፍሱን ያጣ የሞተ ሰው ነው !” ሲል ልብ በሚነካ መንገድ ምላሽ መስጠቱ ይጠቀሳል ። ዛሬ ፍርዱ በተሰጠ መባቻ ጋዜጠኛ ፍራንክ ተጠይቆ ስለ ግድያው አስተያየት እንደማይሰጥ አስታውቋል ።

የሳይመን ቤተሰቦች የልጃችን ገዳይ መግደሉ ካልተረጋገጠ እንዲገደል ፍላጎት እንደሌላቸው በ2009 በሰጡት አስተያየት አስታውቀው ነበር። ከቀናት በፊት አድልዎ አል ዱበይቲ ጉዳዩ ተጣርቶ የሞት ፍርዱ እንደተሰጠው ሲሰሙ አንድ የዜና አውታር እንዲህ አሉ ” በውሳኔው የተምታታ ስሜት ነው ያለኝ ፣ በአድል ዱበልቲ ግድያ ምንም የምናገኘው ጥቅም ባይኖርም ለረዥም ጊዜ ልባችን ተሰብሮ ስንጠብቀው የነበረው ጉዳይ እልባት አግኝቷልና ደስታ ይሰማኛል ፣ እኔና ባለቤቴ ያዘንነው እንደ እኛ በልጃቸው ሞት ስለተጎዱት የቡርጋቲ ቤተሰቦች ጥልቅ ሐዘን ግን እናዝናለን! ” ነበር ያሉት …ልብን ሰቅዞ በሚይዝ ትህትና …

በዚህ ዙሪያ የምለው በቀጣዩ የቀለም ቀንድ ማስታዎሻ ዳሰሳየ ይሆናል! እዚያ እስክንደርስ በራሳችን ጉዳይ አትኩሮት እንሰጥ ዘንድ በዛሬው የቀለም ቀንድ ጋዜጣ መረጃ ቋት ያስተላለፍኩትን መረጃ በጨረፍታ ላስቀኛችሁ !

አቅምን ያላገናዘበው የእኛ መንግሰት እርምጃ …
===================

የታኅሣሥ ወር ከገባ ወዲህ የጀዳና የቀረው ሳውዲ ዐረቢያ የሚያቃጥል የበረሐ ሐሩር በረድ ማለት ይዟል። የገና ጀንበር በጊዜ ከመግባቷ ሌሊቱም አጭር መሆኑን ያስታዎስኩት ዘንድሮ ነው። ታኅሣሥ 19 ቀን 2008 ዓ.ም. ማለዳ ‹‹የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዲሱን የውጭ አገራት የሥራ ስምሪት ዐዋጅ አጸደቀ›› በሚል የተሰራጨው መረጃ እንዳበገነኝ አጭሩ ሌሊት ተገፋና ማለዳው ከተፍ አለ። ታኅሣሥ 19 ቀን 2008 ዓ.ም. ማምሻውን የሳውዲ ሜትሮሎጅ ጅዳና አካባቢው ከበድ ያለ ዝናብ ስለሚጥል ትምህርት ቤት የመዘጋቱ መረጃ ደርሶኝ ነበርና ተፍ ተፍ ብየ ከእንቅልፍ ተነሰቸ በመስኮት ሰማዩን አየሁት። ደመና አለ፤ ዝናብም ያካፋ ይዟል …

… ባንዱ ማለዳ እንደለመድኩት ማልጀ ተነስቸ ከቤቴ ሳሎን ባንዱ ወንበር ላይ ቁጭ ብየ በመስኮት የሚያካፋውን ዝናብ በቆረጣ እያየሁ የሳውዲ ጋዜጦችን የማለዳ ዜና መቃኘት ያዝኩ። ዐረብ ኒውስ ጋዜጣ የሲሪላንካ መንግሥት ሳውዲ ውስጥ ሞት የተፈረደባትን ዜጋቸውን ሕይወት ተከራክረው ማትረፋቸውን የሚያትተው ዝርዝር መረጃ ይዞ ተመለከትኩ። ቀልቤን ጨምድዶ ያዘውና ሙሉውን ካነበብኩት። ብዙም ሳልቆይ በቁጭት እየደበንኩ ከቀናት በፊት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያጸደቀውን የውጭ አገራት የሥራ ስምሪት ዐዋጅን አስታዎስኩ። በዚህ ዙሪያ አዲስ መረጃ ባልጠብቅም ያነበብኩት የሲሪላንካ መንግሥትና ዲፕሎማቶቹ የመብት ጥበቃ ትጋት ወንዝ ከማያሻግሩት የእኛ አገር ዲፕሎማቶች ጋር እያገናኘሁ ‹‹ምን ብንረገም ነው ለእኛ መብት አስከባሪ ያጣነው? ምንስ ብናጠፋ ነው ተቆርቋሪ መንግሥት ያጣነው?›› ስል ራሴን በራሴ ጠይቄ አጉተመተምኩ።

ሳውዲ ዐረቢያ ሪያድ ውስጥ የኢትዮጵያ ኢምባሲ፣ በጅዳ ቆንስልና በቀሩት ዐረብ አገራት ያሉት የዲፕሎማቲክ መሥሪያ ቤቶች ክህሎት ባላቸው በቂ የሰው ኃይል ሳይደራጁ በአዲሱ ስምምነት ወደ ዐረብ አገራት የሚመጡት ዜጎች ፈታኝ ጊዜያት ከፊቴ ድቅን አለብኝ። ሕጉ ጸድቆ ወደ ተግባር ሲገባም የሚመጡትን በሽዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞችን ቀርቶ በቆየው ነዋሪ ላይ የመብት ገፈፋ ሲፈጸምም ሆነ በተላያየ ወንጀል ስንወነጀልና ስንከሰስ ጠያቂ ስለሌለን ዜጎች ጥቂት ማሳያ የሚሆን መረጃ ከማስታዎሻየ መፈታተሽ ጀመርኩ። መረጃውን አላጣሁም። የሩቁን ሳይሆን የቀረበውን ጉዳይ እያሳየሁ ስለመብታችን ስለ ማይተጉ ዲፕሎማቶቻችን ከሌሎች አገራት የዜጎች ጋር በንጽጽር የሚሆን ሁለት ሦስት ጉዳዮችን ላነሳ ወደድኩ። በአንጻሩ ባሳለፍናቸው ጥቂት ወራት በታዋቂ የሳውዲ ዐረቢያ ጋዜጦች የወጡ መረጃዎችን የሌላ አገር ዲፕሎማቶች ሳውዲ ዐረቢያ ላይ ለተገፉት ሳይሆን የሳውዲን ሕግ መጣሳቸው ተረጋግጦ የተፈረደባቸውን ዜጎቻቸውን መብት ለማስከበር ስለሚሄዱት ርቀት ያለው መብት ማስከበር ሁለት ጥሩ ማሳያዎችን ላሳያችሁ ፈቅጃለሁ።

በተሳካው ዲፕሎማሲ ዜጎችን ሲታደጉ …
================
የሲሪላንካ ዲፕሎማቶች በሳውዲ በድንጋይ ተወቅራ እንድትገደለባት የተፈረደባት ሲሪላንካዊን ከሞት ቅጣት ሲታደጓት እንመለከታለን ! የብሪታንያ ዲፕሎማቶችም ከ350 ጅራፍ ግርፊያና እስራት የተደረሰበትን ዜጋቸውን ስለታደጉበት አንደምታ በጨረፍታ እናየዋለን … በንጽጽር የእኛን ጉዳይ እናያለን …

ሞት የተፈረደባት ኢትዮጵያዊት …
==============

ከዓመታት በፊት አንዲት ኢትዮጵያዊት አሰሪዋን ገድላ ለፍርድ ቀርባ ውሳኔው ሲነገራት በቦታው የነበር ወዳጀ አስተርጉም ተብሎ ቀርቦ ያየውና የሆነውን አጫውቶኛል። …

ሚስቱን ላለማስደፈር ሲታገል ነፍስ ያጠፋው ኢትዮጵያዊ …
========================

ከአንድ ዓመት በፊት ጅዳ ውስጥ ፈይሰልያ በሚባል መንደር ሳውዲ ዐረቢያ ጎረምሶች የአንድ ሐበሻን ቤት ዘለው ገብተው ከዘረፉ በኋላ ወንዶችና ሴቶን ለየብቻ ያግቷቸዋል። ብዙም ሳይቆይ ሚስቱን አውጥተው ሊደፍሯት ሲታገሉ የድረሱልኝ ድምጽ የሰማው ወንድም የተዘጋበትን በር ሰበሮ በመውጣት ቀበቶውን ፈትቶ ሚስቱን ሊደፍር ከተዘጋጀው ወሮበላ ጋር ይተናነቃል። ባደረገው ግብግብ ቤት ዘራፊና ደፋሪው ወጣት ይዞት በመጣው ጩቤ ይወጋዋል።

ሐና ገዳይዋ ማነው ?
=========
ጅዳ ውስጥ ‹‹ሀየል ሰፋ›› በተባለ መንደር አንዲትን ኢትዮጵያዊ ከገደሉ በኋላ ጥቁር አበያና መነጽር ካለበሱ በኋላ በበሽተኛ ጋሪ አድርገው ወደ ቤቷ አምጥተው ጥለዋት ይሄዳሉ። ” ምን በሽተኛ አምጥተው ጣሉብን ?” በማለት መነጽር ያደረገችውን ከጋሪው ላይ የተቀመጠች እህት ቢያናግሯት አትሰማም። ትንሽ ቆይተው ሞታ እያለ ልክ እንዳልሞተች ለማስመሰል ከጋሪው ጋር አስረው ያመጧትን እህት ሬሳ መሆኑን ተገነዘቡ። ወዲያው ቤቱን ጥለው ሲሄዱ ሬሳው እዚያ ቤት አምጥተው እንደተጣለባቸው ቤቱን የተከራየው ኢትዮጵያዊ ለፖሊስ ባሳወቀው መሠረት ሬሳው ተነሳ …

10 ዓመት ፍትህን ፍለጋ …
===========
ምናልባት ከላይ የጠቀስኳቸው ከበድ ከበድ ያሉ ናቸው ቢባል በሐኪሞች ስህተት 10 ዓመት የተኛው ብላቴናው መሐመድ አብድልአዚዝ ሲንገላታ ምን ዓይነት የመብት ጥበቃ ተደረገ? ሌላው ቀርቶ ጤና ጥበቃ ያሳለፈውን ውሳኔ ይዞ፣ በመሳሪያ የሚንቀሳቀሰውን መሐመድ ይዛችሁ ካልወጣችሁ የተፈረደውን ካሳ አልሰጥም ያለውን ሆስፒታል ጉዳይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ለማስገባት ለምን አልተቻለም? ጠበቃ ቀርቦ የውጭ ጉዳይ የሕግ ምክር አልመጣም ተብሎ ጉዳዩ የሚጎተትበት እንቆቅልሽ ሊገባን አልቻለም …

የእኛ ዲፕሎማሲ…
========
… ዋና ሥራቸው የዜጎችን መብት ማስጠበቅ መርህ ያደረጉት በመንግሥት የተሰየሙት ተወካዮቻችን ዲፕሎማቶች ባልተረጋገጡ ወንጀሎች እጃቸውን አስገብተው የተያዙ ወንጀለኞችን መብት ይከራከሩና ነጻ ያውጡልን። ምህረት ያሰጡ ያለም የለም። የተረጋገጡ መረጃና ማስረጃ የተያዘባቸውን በደሎቻችን ግን ለከፍተኛ የሳውዲ ዐረቢያ መንግሥት ኃላፊዎች ያቅርቡልን እያልን መማጸናችን ግን ግድ ነው። የተለያዩ አገር ዜጎች ዜጎቻቸው ማናቸውም በደልና የመብት ጥሰት ሲፈጸምባቸው በሕግ አንጻር አስፈላጊውን ሁሉ እርምጃ ወስደው፣ ተበዳይ፣ በዳይ ታሳሪዎችን በማማከርና ጠበቃ ድረስ በመቅጠር መብታቸውን ሲያስከብሩላቸው ተመልክተናል።

… እኛ በዜጎች መብት ማስከበር ዲፕሎማሲ ስለከሸፈብን አንድምታ ሁሉንም በጥልቀትና በመረጃ ንጽጽር ሐገር ቤት በምትታተመው የቀለም ቀንድ ጋዜጣ አቅርቤዋለሁ ! ቀለም ቀንድ ዛሬ በገበያ ትውላለች ። ያንብቧት ፣ ከቀለም ቀንድ የመረጃ ቋት ሁሉንም ያገኙታል …

መረጃ ሕይወት ነው !

ነቢዩ ሲራክ
ታህሣሥ 26 ቀን 2008

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.