ስለ እናት! የእህት ሰሚራ ምሬትና “ወደ ሀገሬ አስገቡኝ ” ተማጽኖ – ከነብዩ ሲራክ

* በገና መባቻ
* የእህት ሰሚራ እናት
* የእህት ሰሚራ ምሬትና “ወደ ሀገሬ አስገቡኝ ” ተማጽኖ
* ዘባተሎው ፖለቲካ የሚያመጣው ጣጣ
* ትንታጉ አረቡ ብላቴና ስለ እናት

በገናን በዓል ከልጆቸና ከመላ ቤተሰቤ ጋር ባለሁበት ስደት እንደ አቅሜ አደማምቄ አከብር ዘንድ ምክንያቴ ዛሬም እናቴ ነበረች ። ያን ሰሞን በስልክ ስናዎራ በልጇ ናፍቆት የተጎዳች እናቴ በዓሉን በልጅ ልጆቿ ተከባ በማክበሯ የተሰማትን ጥልቅ ደስታ ስትነግረኝ ደስታየ በእቅፏ ያለሁትን ያህል ደስታ ፈጥሮልኝ ውሎ አድሯል 🙁 ተመስገን !

በገናው ዋዜማ ” ወደ ሀገሬ አስገቡኝ ” ስትል ተማጽኖዋን ያቀረብኩላችሁ እህት ሰሚራ በምዕራብ ሳውዲ ባንዷ ትንሽ ከተማ የመኪና አደጋ ደርሶባት በተኛችበት ሆስፒታል ሆና በእንባ እየታጠበች ያደረሰችኝ መልዕክት ” ነቢዩ እናት አለህ ፣ በእናትህ አትጨክንም ፣ እርዳኝ …የሚረዳኝ አፈላልግልኝ ፣ ጉዳዬን አንተ ካስተላለፍክበት ጊዜ ጀምሮ ያነጋገረኝ ሆስፒታሉ ብቻ ነው ፣ ከኢንባሲ የማጣም ሆነ ያነጋገረኝ የለም ፣ ድፍን አንድ አመት ያልጠየቁኝ የሀገሬ መንግስት የኢንባሲ ሰዎች በመኪና የገለበጠኝን ሰው አፈላልገው አሳስረው ፍትህ አገኛለሁ ብዬ ተስፋ አላደርግም። ስለዚህ ያለ አባት ካሳደገችኝ እናቴና ከቤተሰቤ ጋር እንድገናኝ እርዳኝ !” ስትል መላ አካሏ የተሰናከለችው እህት ሰሚራ በድጋሜ ደ ሀገሯ እንድትገባ ትብብር እንድጠይቅላት ተማጽናኛለች 🙁 እጅግ በጣም የሚያመው መልዕክቷ በእጄ ገብቷል ፣ እንደ አስፈላጊነቱ መልዕክቷን በቀጣይ ቀናት አቀርበዋለሁ !

ያለስጋት ወደ ሀገር እንዳንገባና እንዳንወጣ የሚያደርገን ዘባተሎው የአረኛ ሀገር ፖለቲካ በስደትም ሰላም ነስቶናል ፣ አሁን አሁን የጀመሩት ስውር ነቆራ ደግሞ ደስ አይልም ። ፖለቲከኞች ከድርጅት ፣ ዘርን መሰረት አድርገው ከተደራጁት ትላልቅ ማህበራት እስከ ትናንሿ የአብሮ አደግ እድርና መረዳጃ ማህበራት እጃቸውን እያስገቡ ያንገላቱን ይዘዋል ። ከምንም በላይ በሰው ደካማ ጎን እየወሸቁ ሰውኛ ሰብዕናን መሰረት አድርገው ስደተኛውን ከመርዳት ይልቅ ርዕዮታቸውን ለማሸከም መትጋቱን ስራ ብለው ይዘውታል ። የእኔ ቢጤ ደካሞች በጉልበታችን ሰርተን ገብተን ፣ እርስ በርስ ተደጋግፈን ስደቱን እንዳንገፋ እያናቆሩን ለመሆኑ ብዙ ማለት ይቻላል ። በተለይም ገና የሳውዲ ህግ ቀጠነ ፣ ወደ ሀገር መግባት አማራጭ የለውም በተባለ ቁጥር በቀቢጸ አልፎ አልፎ የሚመቻቸውን ወጣትና ጎልማሳ እተመለመሉ ፣ በማይጨ በጠው የተስፋው መንገድ እተነዷቸው መምልከት ይዘናል። በተለይም አምናና ዘንድሮ የሚያጠምቋቸው አዳዲስ ካድሬዎች ለመረዳዳት በተከፈቱ የመመካከሪያ ማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በመሰግሰግ አፋቸውን አሹለው እያየናቸው ነው ! …

በከተማችን ስውር ካድሬዎች ከወገንና ለሀገር የተነቃቃን መንፈስ ለማኮሰስ እንደ አሸን በፈሉበት ሰማይ ስር በአብሮ የአደጎች ምክክር እሰጣ ገባ መካከል ይህን የምትመለከቱትን መረጃ ተሰራጭቶ አገኘሁ ፣ ከንትርኩ ለመውጣት መረጃውን ተጭኘ አደመጥኩት ፣ በእርግጥም ፍጹም መንፈስ አዳሽ መረጃ ለመሆኑ ይህን ታዳጊ ወጣት አረብ ብላቴ ግጥም አድምጣችሁ ምስክርነት ስጡ ፣ ለእኔ ቀልቤን ስቦት ላጋራችሁ ፈቅጃለሁ … ከምንም በላይ የዚህ ብላቴና የግጥም ትረካ ቀልቤን የሳበው የእኔንም የሰሚራንም ፣ የሀኪም ስህተት 11 ዓመት ያለ ፍትህ ጅዳ ውስጥ አልጋ ላይ ያለው ብላቴናውን መሀመድንም እናት በግጥሙ ውስጥ አይቸበታለሁ ፣ ነፍሴ በተደበላለቀ ስሜት ተሰረቀ … ውስጤን አንዳች ነገር ነዘረው … ይህ ስሜት በደረቁ ሌሊት የተመለከት
ኩትን አረብ ታዳጊ መንፈስ ዘባተሎው ፖለቲካ ካመጣብንንና ከእሰጣ ገባው መንደር መንጥቆ አወጣኝ …!

ወጣቱ አረብ ብላቴና ስለ እናቱ ያቀረበው ግጥም ስንኞች ጥልቀት ከእናት ፍቅር አምጥቆ በተዋበ ሰረገላ ያንሸራሽራል ፣ ከሰውኛ እሳቤ በሀይማኖት ዳራው ሩቅ ወስዶ ይመልሳል ፣ ስንኞቹ ይጣፍጣሉ ፣ ያመራምራሉ ፣ የገሀዱ አለም እውነታ በብላቴናው ርቱዕ አንደበት የሚወረወሩት እያንዳንዱ ቃላት ጣፋች መአዛን የተሞሉ ናቸው ፣ ስለ እናት ፍቅር ከሚነገሩት እና ከሰማኋቸው እውነቶች በዚህ ግጥም ብዙው ተካቷል ፣ ይህ ትጉህ አረብ ወጣት ብላቴና ስለ እናቱ ፍቅር ቃላቱን እያቆላመጠ ሲተርከው ፣ ከመድረክ ወርዶ ወደ እናቱ ቀርቦም ከእናቱ ጎን ሆኖ በእጁ ትከሻዋን በፍቅር እየዳበሰና እያመላከተ በሚያንቆረቁረው ቅኔ ታዳሚውን አስደመመው ፣ እናት አነባች ፣ እኔንም ውስጤን አረካው ፣ እንዲያው በአጠቃላይ ግጥሙ ውስጣዊ ስሜትን ይኮረኩራል ፣ ይፈነቅላል ማለት ይቀለኛል !

ከእርካታው የደስታ ስሜት ውስጥ ሆኘ ግን በዙ አልቆየሁም 🙁 የእናትን ጥልቅ መውደድና ፍቅር እንዲህ ሲገለጽ ከማናችንም በላይ መላ አካሏ በአደጋ የደቀቀው የእህት ሰሚራ ተማጽኖ ልቤን ሰበረው ” ወደ ሀገሬ አስገቡኝ ፣ ያለ አባት ካሳደገችኝ እናቴ አገናኙኝ !” ብላኛለችና ዛሬም የሪያድ ኢንባሲም ሆነ የጅዳ ቆንስል ተወካዮች የዜጋዋን ድምጽ ሰምቶ ድፍን አንድ አመት ያልጎበኟትን እህት ሰሚራን እንዲጎበኟት ፣ እህት ሰሚራ በክትትል ማነስ ፣ በመብት አስከባሪ እጦት የጎደለባት ፍትህ እንዲከበር ፣ የጉዳት ካሳዋን አግኝታ ወደ ሀገሯ ፣ ወደ ናፈቀቻት እናቷ ትቀላቀል ተሰደርጓት ዘንድ አሁንም ለሚመለከታችሁ ሁሉ መልዕክቴን አስተላልፋለሁ !

ቸር ያሰማን !

ነቢዩ ሲራክ
ጥር 2 ቀን 2009 ዓም

1 COMMENT

  1. How is the cross erected by an individual related to TPLF? If you are Christian you have to be happy and if you are Muslim respect the faith of others.

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.