ምነው “ከኑግ የተገኘህ ስሊጥ አብረህ ተወቀጥ” አደረጉት? – ዓለም ባልከው

ዶክተር ጌታቸው ኃይሌ

“የሳባ ንግሥት ትሩፋትና የዶክተር ጌታቸው ኃይሌ ስህተት” የሚለውን ጽሁፍ አንብቤ አንዳንድ ጽሁፍዎት ውስጥ   የሰነዘሯቸው አስተያየቶች ላይ ተምርኩዤ ልጽፍ ወደድኩ። በአገራችን አበው የሚሉት አንድ አባባል አለ። እሱም “ከኑግ የተገኘህ ሰሊጥ አብረህ ተወቀጥ” የሚለው ነው። የእርስዎም ጽሁፍ ይሄንን አባባል ገላጭ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።\

የሳባ ንግሥት ትሩፋትና የዶክተር ጌታቸው ኃይሌ ስህተት። – ከሙሉጌታ ውዱ።

በመጀመሪያ ዶ/ር ዶን ሌቨን በብዙ ኢትዮጵያውያን ወዳጆቻቸው የሚጠሩት “ጋሼ ሊበን” በመባል ነው። ነፍሳቸውን ይማረውና በህይወት ስለሌሉ ምላሽ መስጠት አይችሉም ። ነገር ግን የዶ/ር ሌቨንን አስተዋጽዎ ለኢትዮጵያ ጥናት፣ ብዙ ኢትዮጵያዊ ወጣቶች ተጠቃሚ ለሆኑበት አዋሳ ክ/ሀገር በሽርክና ባቋቋሙት ድርጅት ውስጥ እንዲሁም ለብዙዎች (mentor) የቅርብ ምክር ሰጪ፣ የችግር ተካፋይ እና አስተማሪ በመሆን ያገለገሉ ናቸው። የእትዮጵያ ጉዳዮች ላይ ከአገራችን ዜጋ ባልተናነሰ ሁኔታ ለህዝባችን ድርሻ ያበረከቱ ስለነበሩ በጎ አድራጎታቸውንና ስለ ኢትዮጵያ ያላቸውን መውደድ ሳናነሳ ማለፍ የለብንም። በእርግጥ የኢትዮጵያን ባህሏን ፣ህዝቧን ታሪኳን ጠንቅቀው ስለሚያውቁ እርስዎ እንዳሉት ”የስለላ ሥራ“ ወይም ለአገራችው ውጭ ጉዳይ መረጃ ሰጪነትም ሆነ አማካሪነት የመጀመሪያ እጩ እንደሚሆኑ ማመን አያዳግትም።ዶ/ር ዶን ሌቨንን ከምዕራባዊያን አገር ታሪክ ቀማኛ፣ ገፋፊና፣ ከአገር ስም አጥፊ ጋር አብረው ይመደባሉ ብንል ተገቢ አይመስለኝም። እንደው ዶ/ር ሌቨን እተኙበት እንዳያገላብጣቸው ይቺን ያህል ካልኩ ወደ ሌላው አስተያየቴ ላምራ።

ከጽሁፍዎት እንደተረዳሁት የኢትዮጵያን ታሪክ በፈረንጅ መጻፍ አድናቂም ሆነ ትምህርቱን ፈላጊም አይመስሉም። በእርግጥ የአገራችን ታሪክ በእኛው ቢጻፍና ቢመረመር ሸጋ ነበር። የአገራችን ገዳማትና አድባራት ስንት ሚስጥሩ ያልተዳሰሰ የብራና ጽሁፎች አቧራና የሸረሪት ድር አድርቶባችው ግማሹንም ለአገር ጎብኚዎች ያለ ምንም ጥንቃቄ ስንት ዘመናትን ያሳለፉ ቅርሶቻችን እንደዋዛ በአስጎብኚውም ሆነ በጎበኚው ሲገላበጥ በዩቲዩብ (YouTube) እናያለን። እርስዎ የት እንዳሉ ባላውቅም እኔ የምኖርበት አገር ውስጥ የኢትዮጵያ የቆዩ ታሪኮችን የያዙ መጽሀፎች ወይም ጽሁፎች ለማንበብ ቤተ መጽሀፍቱ በቀጠሮና በትልቅ ጥንቃቄ ነው ማየት የምችለው። በተጨማሪ እድሜ የጠገቡትን መጽሃፍትና ሌሎች መረጃዎችን ተውሼ እንኳን ለመውሰድ አይፈቅዱም። እንደው በጥቂቱ Edward Ullendorff, ዶ/ር ጌታቸው ኃይሌ Dr Bill F Macomber የመሳሰሉት ባለሙያዎች የመጽሀፍት ዝርዝር ካታሎግ (Catalogue) በማዘጋጀት ለተመራማሪዎች፣ለተጠቃሚ ጉልህ ሥራ ሰርተዋል። በእርግጥ ፈረንጆቹ ብርቅዪ ለሆኑት ቅርሶቻችን እንክብካቤ የሚሰጡበት አላማው ለኛ በማሰብ ብቻ ሳይሆን የራሳቸውንም ሆነ የዓለምን ታሪክ ቋጠሮውን የሚፈልጉበት፣ የሚፈቱሹበት እና የሚመረምሩበት ነው።  ታዲያ ቋንቋውን፣ ባህሉንና ህዝቡን የማያውቀው ፈረንጅ ለአገራችን ቅርስ እንደዚህ አይነት እንክብካቤና ጥንቃቄ አድርጎ አቆይቶልናል። በዛው መጠንም በአገራችን ምድር ከእኛው ህብረተሰብ ውስጥ ያለው ቅርስ የአቧራና የሸረሪት ድር ለብሶ ሲታይ ምን ይመስልዎታል?ይሄንን ሳነሳ  እርስዎ ላይ ጫና መስጠቴ ሳይሆን ከፈረንጅ እና ከአጭበርባሪ የተረፈውን በአግባቡ እንያዘውና ፈረንጅ የሰጠውን ክብር ባንነፍገው ጥሩ ነበር ባይ ነኝ።

በእርግጥ ስለ አገራችን ታሪክ፣ ባህል፣ ስለማንነታችንና ስለ ነገሥቶቻችን የፈረንጅ አንባቢን ቀልብ እንዲስቡ ታስበው የቀረቡ መጽሃፍትና፣ ጽሁፎች ለዘመናት አንብበናል። አንዳንዱም ባህላችንን፣ ልማዳችንንና ህዝባችንን ጠንቅቆ ባለማወቅ የተነሳ ማመን እስኪያስቸግር አጋኖና በመሰለኝ የጻፈልንም አለ። በቋንቋ ትርጉም አለመግባባትም ትርጉሙ የማይሆን ፍቺ ይዞ የቀረበም አንዳለ ይታያል። በብዛትም አፍሪካን አህጉር ከስልጣኔ መስራችነት ጎራ ሙልጭ አድርገው ለማጥፋትና ለዓለም ስልጣኔ ምንም ዓይነት አስተዋጽዎ እንዳላደረገች አድርገው በዘር ተጽዕኖ የጥቁርን ታሪክ በመካድ ይተርኩልናል።  ታዲያ ይህንን ስል በዛው መጠንም ስለ አገራችን ታሪክ የጻፈ ፈረንጅ ሁሉ ለጥቅም ፍለጋ፣ ለተንኮል ወይም በተለምዶ ፈረንጅ ያለስለላ አገራችን ላይ ትኩረት የለውም ብለን በጥቅል መወንጀልም ተገቢ አይመስለኝም። ለአገራችን በተለያየ ታሪክ ላይ ያተኮረ ትልቅ የጽሁፍ አስተዋጽዎ ካደረጉት ፈረንጆች በጣም በጥቂቱ እንደነ ሪቸርድ ፐንክረስት፣ ስቨን ሩብንሰን፣ ከላይ የጠቀስኩት ዶን ሌቨን “ጋሼ ሊበን”፣ ሄጋ ኤልሪች፣ ሬይመንድ ጆናስ፣ሃሮልድ ማረከስ፣ ካርሎ ኮንቲ ሮዚኒ፣ክሪስት ፕራውቲ ሳይነሱ መታለፍ የሌለባቸው ናቸው። እገረ መንገዴን ክቡር አቶ ተክለ ጻዲቅ መኩሪያን የኢትዮጵያ ውድ ልጅ ቢሆኑም እንኳን፣ ቴክኖሎጂ ባልተስፋፋበትና በጊዜው የነበረውን መንግሥት እየለመኑ በብዙ ድካምና ባላቸው አቅም ተጠቅመው ላበረከቱልን የታሪክ ጽሁፎች ሳላነሳቸው ማለፍ አልፈልግም። የአቶ ተክለ ጻዲቅ መኩሪያና ሌሎችም የቀድሞ የኤትዮጵያ ታሪክ ጸሃፊዎች በኋላ ላይ ለመጡ የታሪክ ሊቆች መንደርደሪያ የሚሆናችውን መንገድ ጠርገውላቸዋል ብዬ እገምታለሁ። እንደው በነካ እጄ በውቅቱ ያሉትንም አንዳንዶቹን ባነሳም አይከፋም። በጥቂቱ ከማስታውሳቸው ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ፣ፕሮፌሰር ጳውሎስ ሚልኪያስ፣ዶ/ር ጌታቸው ኃይሌም ጥሩ አስተዋጽኦ ያደረጉና እያደረጉም ነው።

በእርግጥ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማቶች ለታሪክ ምርምርና ጥናት የገንዘብና ቁሳዊ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። ሆኖም በድሮ አንጋፋ የታሪክ ባለሙያዎችና ሊቃውንት የተሰሩትን እንመልሰዋለን፣ እንቀልሰዋለን እንጂ በአዲስ ወጥነት በኢትዮጵያውኖች ተሰርቶ የሚወጣ በታሪክ ላይ የተመሰረቱ ጽሁፎችን እምበዛም አላይም። መቼም ታሪክ ስንል ብዙ ነገሮችን ያጠቃልላል እና የአሁኑ ወጣት ተማሪዎቻችን የኢትዮጵያን ታሪክ መማር አቁመዋል፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፕሮግራማቸውን ዘግተዋል ሲሉኝ ጥልቅ ሀዘንና የሰማሁት እውን እንዳልሆነ ነው የምጸልየው። አንዳንድ ስራዎች አልፎ አልፎ ቢኖርም አንዳንዱ ጽሁፍ ውስጥ ካለ ዓጼ ዮሃንስ የአሁኗ ኢትዮጵያ ትኖር እንዳልነበር አድርገው ሲነግሩን፣ ሌሎቹ ደግሞ ጀግንነት የሚለውን ቃል ዓጼ ቴዎድሮስ ብቻ የፈጠሩ አስመስለው ያውጉናል፣ ሥለ እምዪ ሚኒሊክ የሚተረከውና የሚጻፈውን መስማት ወይም ማንበብ እጅግ የሚከብድ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።  በቅርቡ ያለፍንበትን መንግስቱ ሐ/ማሪያም እንኳን ስንት ህዝብ እንዳልገደለና እንዳልጨረሰ፣ በጦርነት ህዝቡን ፋታ ሳይሰጥ በእሳት እንዳልማገደ ያንን ወደ ጎን ትተን “አገር ወዳድ“ ነው እየተባለ ይወደሳል። የአገር ፍቅር አለው እየተባልን በህዝብ ላይ ያደረሰውን ሰቆቃና እልቂት በባንዲራችን ይሸፍኑለታል። በዓለም ታሪክ ጽሁፍ ውስጥ አድልዎ የተደረገባቸውን ጽሁፎች ማንበብ የተለመደ ነው። ሆኖም ለማለት የፈለኩት ነገር ፈረንጁ የጥቁር አህጉርን ህዝብ የሥልጣኔ ተሳትፎን እንደሚክድ ሁሉ የአገራችንም ጽሁፎች እውነትን በመካድ ወገንተኝነት አስመርኩዞ ለአንዱ ደጋፊ (ቲፎዞ) በመሆን ታሪኩን ይተረኩልናል።

ለፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ጽሁፍዎ ላይ የጠቆሙት “ስህተት“ በመጽሃፍ ቅዱስ ላይ የተመሰረተ ማሰረጃ ይመስላል። ስህተቱን እሳቸው እራሳቸው መልስ ይስጡበት እንጂ እኔ የለሁበትም። (ከፕ/ሮ ጌታቸውም ሆነ ሀሳባቸውን ከሚጋራ መልስ ካገኙ ግን ለማንበብ እወዳለሁ)። እዚህ ላይ በቅድሚያ ማንሳት የምፈልገው ግን  በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሃይማኖቴ መሰረት መጽሐፍ ቅዱስን የማነበው ታሪኩ ከአገሬ ኢትዮጵያ ጋር ስለተየያዘ ሳይሆን የእግዚአብሔር ቃል በመሆኑ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ኢትዮጵያ ተብሎ የተጻፉት ታሪኮች ሁሉ የአሁኗን አገሬን እትዮጵያ ነች ብዪ ነው እምገምተው። ማስረጃም ባይኖረኝም  በኢትዮጵያዊነቴ ለአገሬ አድልዎ በማድረግ ወገንተኝነትን እመርጣለሁ።  በአ አ አቆጣጠር 2004 Dr. Edwin Yamauchi (Japanese American historian, Christian. His wide scholarly interests, embracing Old and New Testament as well as ancient history and the history of the Early Church, and his expertise in many ancient languages) አፍሪካና መጽሃፍ ቅዱስ (Africa & the Bible)በሚለው መጽሃፋቸው ላይ ተመርኩዞ የሰጡትን ቃለ ምልልስ ክርስቲያኒቲ ዛሬ (Christianity Today) ድሀረ ገጽ ላይ ያነሱት ነጥቦች በጥቂቱ ይሄንን ይመስላል።

http://www.christianitytoday.com/ct/2004/mayweb-only/5-24-21.0.html

Dr Edwin Masao Yamauchi  የሚሉን ደግሞ የሙሴ ሚስት ከደቡብ ግብጽ ሱዳን እንደሆነች አድርገው ነው የሚነግሩን። የንጉስ ሰለሞንን ከአፍሪካ ጋር ያለውን ግኑኙነት ደግሞ በወርቅ ግኝት ላይ የተመሰረተ ሆኖ ይህም ግኝት የሚያመለክተው ምስራቅ አፍሪካ ወይም ምዕራባዊ አረቢያ እንደነበር ነው ። ንግስት ሳባንም ከደቡብ አረቢያ ከአሁኗ የመን ጋር ያደርጓታል። በግሪክ ቋንቋ ፍቺ የኢትዮጵያ ስሙ የሚያመለክተው የደቡብ ግብጽ እና  እንዲያውም ህንድንም ይጨምራል ይሉናል። ኢትዮጵያ የሚል ሥም ያገኘነው ከ20ኛው ክፍለ ዘመን በኋላ ስለሆነና ከዚያን በፊት የአሁኗ ኢትዮጵያ ትጠራ የነበረው አቢሲኒያ በሚለው ሥም ስለነበረ  ሌሎች ህዝቦችንም ሆነ እኛ ኢትዮጵያኖችን በመጽሃፍ ቅዱሱ ውስጥ ከተጠቀሰው ኢትዮጵያ ጋር  እንደሚያደናግር ጠቅሰዋል።

(በእርግጥ Edwin Yamauchi እንዳሉት ኢትዮጵያ ተብላ የተጠራችበትን እድሜዋን ቢያሳጥሩባትም ኢትዮጵያ ለመባላችን በርካታ አገራዊ የታሪክ ማሰረጃዎች አሉን ብዬ እኔም እንኳን የታሪክ ሙያው የሌለኝ እገምታለሁ።)

መቼም የታሪክ ምርምሩን ውጤት Dr, Yamauchi እንዳሉን ደቡብ ግብጽ (የአሁኗ ሱዳን) ወይም ምዕራባዊ አረብ (የአሁኗን የመን) በማለት ፈንታ ከአሁኗ ኢትዮጵያ አገሬ ጋር ቢያይዙት ሁሌም የምናውቀው ታሪክ ነው ብዪ ኩራት ይሰማኝ ነበር ። እዚህ ላይ እርስዎም Edwin Yamauchi ከላይ የጠቀስኩትን የምርምር ውጤት ሲመለከቱ ምን አልባት በጽሁፌ የነገርኩሽ ይህንኑ ክርክሬን የሚደግፍ ማስረጃ ሰጠሽኝ ይሉኝ ይሆናል እንዲያውም ከፈረንጅ ደህና ነገር አልጠብቅም ሊሉኝም ይችሉ ይሆናል።

Edwin Yamauchi ግን ከሌሎቹ ታሪክ አዋቂዎች ለየት የሚያደርጋቸው መጽሃፍ ቅዱሱን በቀጥታ ኢትዮጵያን በብቸኝነት ለይቶ በማውጣት ባያገናኙትም እንኳን ታሪኩን በሳቸው አገላለጽ ወደ ደቡብ ግብጽ (የአሁኗ ሱዳን) በማድረግ ወደ አህጉረ አፍሪካ በመሳብ የጥቁርን ህዝብ አስፈላጊነት አሳይተውናል። በዓለም ህበረተሰብ እጅ ውስጥ በሚገኘው ክቡር በሆነው የመጽሃፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ የምርምሩን ውጤት ሱዳን ላይ አመልክተው ቢነግሩንም ያው በአፍሪካዊ ጥቁርነታችን መሰረት ለዓለም ህብረተሰብ የታሪክ ተጋሪዎች ማድረግና ለስልጣኔም መምጣት አስተውጽዎ አድራጊዎች እንደሆንን አሳይተዋል። 

አስተያየቴን ከማጠቃለሌ በፊት ማንሳት የምፈልገው ነገር የተለያዩ የታሪክ ምንጮች እንደሚጠቁሙን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ መጽሃፍ ቅዱሳችን የተተረጎመው በተዋረድ ከሶሪያ ፣ግሪክ፣ አረብኛ  ብሎም ግዕዝ ስለሆነ በትርጉም ሂደት መዛነፍ ምክንያት ያጣነውም  ሆነ ያገኘነው ታሪክ ሊኖር ይችላል። በእርግጥ ይሄንን እርስዎ እንዴት እንደሚያስቡት አላውቅም። በተለያየ ጊዜ አዲስ ግኝት ብለው የሚያቀርቡልንን መላ ምት፣ ጥናቶችና ግኝቶች ታሪካችን ከእጃችን ተፈልቅቆ እንዳይወጣ ከፈለግን ተግቶ መመርመር፣ ማጥናትና በተጨባጭ ማሳየት እንዲሁም ማስተማር የባለታሪኮቹ ኢትዪጵያውያን ታሪክ ሊቃውንት ድርሻ ነው ብዪ እገምታለሁ። አስተታየቴን እዚህ ላይ ልግታና ጊዜዎትን ወስደው ስላነበቡ በቅድሚያ አመሰግናለሁ።

ሰላም ለሁላችን

ዓለም ባልከው

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.