ሃይ ባይ ያጣው የሊዝ መሬት ሻሞ – ረፖርተር

ረፖርተር

ምርጫ 1997 የፈጠረውን እሳት ለማጥፋት መንግሥት በአቶ ብርሃነ ደሬሳ የሚመራ ጊዜያዊ ባለአደራ አስተዳደር ሰይሞ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ይህ ባለአደራ አስተዳደር ለሦስት ዓመታት ካስተዳደረ በኋላ፣ ኢሕአዴግ   የምርጫ ካርድ የነፈገውን የአዲስ አበባ ሕዝብ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት በአቶ ኩማ ደመቅሳ የሚመራ ካቢኔ መሾሙም የሚዘነጋ አይደለም፡፡ 

3c9e3a3fff3ae99bc1a5094c9e66003d_Lበአቶ ኩማ ካቢኔ ውስጥ፣ በተለይ በመሬት ጉዳዮች ትልቅ ቦታ የነበራቸው አቶ መኩሪያ ኃይሌ ናቸው፡፡ የከንቲባ ባህሪ የተላበሱት አቶ መኩሪያ በዚያ ወቅት የከተማው ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው በመሬት ጉዳዮች መሠረታዊ ለውጦችን ያመጡ የሕግ ማዕቀፎችና ስትራቴጂዎችን በመንደፍ ለተግባራዊነታቸው ሠርተዋል፡፡

አቶ መኩሪያ የከተማው ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው በተሾሙበት በ2000 ዓ.ም. ለጨረታ ለቀረበ ቦታ መሬት በካሬ ሜትር 22 ሺሕ ብር ቀርቦ ነበር፡፡ ይህ ዋጋ በከተማው ታሪክ ተሰምቶም፣ ይሆናልም ተብሎ ታስቦ ስላልነበር፣ በወቅቱ ከፍተኛ የመነጋገሪያ ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ ነበር፡፡

በወቅቱ ሪፖርተር የከተማው የመሬት ዋጋ እየናረ እንደመጣና መንግሥት የመሬት ዋጋ እንዲወጣ ይፈልግ እንደሆነ ለአቶ መኩሪያ ጥያቄ አቅርቦላቸው ነበር፡፡ አቶ መኩሪያ ሲመልሱ፣ በፍፁም መንግሥት የመሬት ዋጋ እንዲጨምር ፍላጎት እንደሌለውና ይልቁኑ በርካታ ቦታዎችን ለአልሚዎች በጨረታ በማቅረብ ዋጋው እንዲቀንስ፣ ብሎም አልሚዎች ያላቸውን ካፒታል መሬት ላይ ሳይሆን ልማቱ ላይ እንዲያውሉት ይደረጋል ብለው ነበር፡፡

አቶ መኩሪያ የከተማ ልማት ቤቶችና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ሆነው ከተሾሙ በኋላ በተለይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በልደታ ክፍለ ከተማ በገነባቸው ኮንዶሚኒየም ቤቶች ሥር ባሉ ሱቆች ግብይት ላይ ከፍተኛ ዋጋ ቀርቦ ነበር፡፡

በወቅቱ ለጨረታ ለቀረቡ ሱቆች በካሬ ሜትር 56 ሺሕ ብር ቀርቦ ነበር፡፡ ይህ ሁኔታም በወቅቱ ከፍተኛ የመነጋገሪያ ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ ነበር፡፡ ከዚህ በኋላም በዚሁ አካባቢ በካሬ ሜትር ከ70 ሺሕ ብር በላይ ቀርቧል፡፡

ይህን ጉዳይ በሚመለከት ሪፖርተር አቶ መኩሪያን አነጋግሮ ነበር፡፡ አቶ መኩሪያ በወቅቱ ሲመልሱ ‹‹እኛ መፍትሔ እናስቀምጣለን፡፡ ይህንን የዋጋ አቅርቦት እንዴት እንደምንሰብር እናውቃለን፡፡ በእርግጠኝነት የምናውቀው ሱቆቹ እንደሚያስፈልጉ ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሱቆችን በስፋት እንሠራለን፡፡ አቅርቦትና ፍላጎት በሚጣረስበት ጊዜ፣ በፍላጐት ልክ አቅርቦት በሚያንስበት ወቅት፣ ለምን ዋጋ ወጣ ብለን አይደለም የምንጨነቀው፡፡ አቅርቦትን በመጨመር ነው ችግሩን የምንቀርፈው፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ነገር ግን አቶ መኩሪያ ያሉትን ታሳቢ በማድረግ ከዓመታት በኋላ የመሬት፣ የቤቶችና የሱቆችን ግብይት ስንመለከት ታሪኩ ሌላ ሆኖ ይገኛል፡፡

ከአምስት ዓመት በፊት በካሬ ሜትር 22 ሺሕ ብር ሲሸጥ ‹‹ጉድ›› ያለው የአዲስ አበባ ሕዝብ ባለፈው ሳምንት ደግሞ ‹‹ወዴት እየሄድን ነው?›› ብሏል፡፡

ኅዳር 25 ቀን 2007 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ባህል አዳራሽ አሥራ አንደኛው ዙር ሊዝ ጨረታ ተከፍቶ ነበር፡፡ በዚህ ጨረታ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ፣ በርበሬ ተራ አካባቢ ለቢዝነስ አገልግሎት የቀረበው 449 ካሬ ሜትር ቦታ አስገራሚና አስደናቂ ዋጋ ቀርቦለታል፡፡

ለዚህ መሬት በካሬ ሜት 305 ሺሕ ብር የቀረበ ሲሆን ይህንን ገንዘብ ያቀረበው  ዝዋይ ትሬዲንግ ነው፡፡ በወቅቱ ለብዙዎች አነጋጋሪ ጉዳይ የሆነው ለዚህ መሬት የተወዳዳረው ሁለተኛው ኩባንያ 288 ሺሕ ብር ማቅረቡ ነው፡፡

ይህንን ገንዘብ ያቀረበው ኤንኤስኬ የተሰኘ ኩባንያ ነው፡፡ በአንደኛ ደረጃ የቀረበው ዋጋ በመሬቱ ስፋት ሲሰላ 136.9 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ነው፡፡ ይህ ኩባንያ የዚህን ገንዘብ 20 በመቶ (27 ሚሊዮን ብር) መክፈል ይጠበቅበታል፡፡ የተቀረውን ዋጋ በ30 ዓመት ተከፍሎ የሚያልቅ በመሆኑ፣ ከ9.6 በመቶ ወለድ ጋር ተደምሮ የመሬቱ ዋጋ ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ያደርሰዋል፡፡

ይህ ትልቅ ገንዘብ ለ449 ካሬ ሜትር ቦታ መዋል ይጠበቅበታል ወይ የሚለው አጠያያቂ ከመሆኑ ባሻገር፣ በዚህ መሬት ላይ የሚገነባው ስድስትና ሰባት ፎቅ ሕንፃ ለመሬቱ ከወጣው አንፃር የሚያስገባው ገቢ በራሱ እያነጋገረ ይገኛል፡፡

ከዚህ 11ኛው ዙር ጨረታ ቀደም ብሎ ወጥቶ በነበረው ስምንተኛው ሊዝ ጨረታ የዚህን ያህል የተጋነነ ባይሆንም ለአዲስ አበባ መሬት ግን እንዲሁ ከፍተኛ ዋጋ ቀርቦ ነበር፡፡

ቦሌ ክፍለ ከተማ ከኤድና ሞል ዝቅ ብሎ ወደ ደሳለኝ ሆቴል በሚወስደው መንገድ ለጨረታ በቀረበው 158 ካሬ ሜትር ቦታ፣ በካሬ ሜትር 65 ሺሕ ብር ነው የቀረበው፡፡ ይህንን ገንዘብ ያቀረበው ኤስኤንአይ ትሬዲንግ ነው፡፡

ይህንን ቦታ ለመግዛት 59 ተጫራቾች ሲቀርቡ ጨረታው በተከፈተበት ዕለት የተገኙ ባለሙያዎችን አስገርሞ የነበረው፣ ይህንኑ ቦታ ለመግዛት ጨረታ ውስጥ ገብቶ ሁለተኛ የወጣው ኤኤንኤ ኮንስትራክሽን ለዚህ ቦታ በካሬ ሜትር 64 ሺሕ ብር ማቅረቡ ነው፡፡

ከዚህ ጨረታ በኋላ ቦሌ ክፍለ ከተማ ሚሊኒየም ጀርባ በካሬ ሜትር 51 ሺሕ፣ 55 ሺሕ፣ 57 ሺሕ ብር የቀረበላቸው ቦታዎች ነበሩ፡፡

በተለይ ከእነዚህ ጨረታዎች በፊትም በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሁለት ወሎ ሰፈር አካባቢ ለሚገኝ ቦታ 32 ሺሕ ብር ቀርቦለታል፡፡ ሞም ፕሮፐርቲ ዴቨሎፕመንት ኩባንያ በወቅቱ ያቀረበው ይህ ገንዘብ ትልቅ መነጋገሪያ ጉዳይ ነበር፡፡ ለከተማው መሬት እየቀረበ ያለው ዋጋ መረጋጋት የማይታይበትና ቀጥታ በፍጥነት መውጣቱን ቀጥሏል፡፡ ንረቱም ጤናማ እንዳልሆነ ባለሙያዎች እየተናገሩ ይገኛል፡፡

አቶ መኩሪያ በቅርቡ ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢብኮ) ጋር ባደረጉት ቆይታ ‹‹አቶ መኩሪያ በካሬ ሜትር እየቀረበ ያለው ዋጋ ጤነኛ አካሄድ ነው ብለው ያምናሉ?›› የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር፡፡ ሲመልሱም፣ ‹‹ትክክል አይደለም፡፡ መስተካከል አለበት፡፡ አሁን እንግዲህ ከአቅርቦት ጋር መዝነን ማየት አለብን፡፡ ለትምህርት፣ ለጤናና ለኮንዶሚኒየም የሚቀርበው [መሬት]፣ ለመሠረተ ልማት የሚቀርበው ሁሉ መዘንጋት የለበትም፡፡ እሱን ዕውቅና መንፈግ አይገባም፡፡ በግብይት የሚቀርበው ዋጋ ግን ጤነኛ አይደለም፡፡ ለእኛም የስኬት መገለጫ አይደለም፡፡ ዋጋው እየጨመረ መሄድ የለበትም፡፡ ምክንያቱም መሬት የሕዝብና የመንግሥት መሆን አለበት የተባለበት መሠረታዊ ይዘቱ ባለሀብት ለመሬት የሚያወጣውን ገንዘብ ለፋብሪካ ያውጣው፡፡ ለመሬት ያወጣ የነበረውን ገንዘብ ለሪል ስቴት ያወጣው፡፡ መሬት የጋራ ሀብት ስለሆነ መሬቱን ይውሰድና ልማቱን ያፋጥነው የሚለው ጉዳይ ነው ቁም ነገሩ፤›› ብለው ነበር፡፡

ነገር ግን አሁንም ቢሆን የመሬት ዋጋ አቶ መኩሪያ ባስቀመጡት መንገድ እየሄደ አይደለም፡፡ አቶ መኩሪያ ይህን ምላሽ ከሰጡ ከቀናት በኋላ በተከፈተው ሊዝ ጨረታ ከፍተኛ ንረት ታይቷል፡፡ አሥራ አንደኛው ዙር ሊዝ ጨረታ እጅግ ከመክረሩ የተነሳ ከዚህ ቀደም ብዙም ትኩረት ባላገኙ ቦታዎች ለምሳሌ በአቃቂ ቃሊቲ ቂሊንጦ አካባቢ በቦሌ ክፍለ ከተማ አራብሳ አካባቢ ቀድሞ ከ500 እና ከ600 ብር በካሬ አልፎ የማያውቅ መሬት ከ10 ሺሕ እስከ 14 ሺሕ ብር ቀርቦለታል፡፡

የሊዝ ዋጋ እያደገ መምጣት ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ ማሳደሩ እንደማይቀር ከሚያምኑ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች መካከል አንዱ አቶ አድምጥ ዘሪሁን ናቸው፡፡

አቶ አድምጥ ከጥቂት ዓመታት በፊት በአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት በአዲስ አበባ ከተማ የሊዝ ሥሪት ዙሪያ ጥናት ካደረጉ ባለሙያዎች መካከል አንዱ ናቸው፡፡ አቶ አድምጥ ለአንድ ካሬ ሜትር ቦታ 305 ሺሕ ብር ተሰጠ ሲባል ኢንቨስትመንቱ ስንት ቢያወጣ ነው የሚል ጥያቄ እንደጫረባቸው ይገልጻሉ፡፡ እንዲህ ያሉ የተጋነኑ ዋጋዎች ለምን ተሰጡ ተብሎ መፈተሽ እንዳለበት፣ የተሰጠውን ዋጋ የሚስተካከል ኢንቨስትመንትስ ይካሄድበታል ወይ ብሎ መፈተሸም ተገቢ መሆኑንም ያመለክታሉ፡፡

‹‹እንዲህ ያሉ ዋጋዎች መንግሥትን ጭምር የሚጐዱ ናቸው፤›› የሚሉት አቶ አድምጥ፣ መንግሥት በተጋነነ የሊዝ ዋጋ በተሰጠው ቦታ ላይ ከሚካሄደው ኢንቨስትመንት ውስጥ ቢያንስ 30 በመቶ ድርሻ እንዳለው ማሰብ እንደሚኖርበት ገልጸዋል፡፡

ምክንያቱም ከቦታው ላይ ከሚደረግ ኢንቨስትመንት ከሚገኘው ትርፍ 30 በመቶው የትርፍ ድርሻ ግብር የመንግሥት በመሆኑ ከኢንቨስትመንት ወጪው የበለጠ ለመሬት የተሰጠው ዋጋ ብልጫ ከታየበትና ኢንቨስተሩ ኢንቨስት አድርጌያለሁ ብሎ የሚያገኘውን ገቢ ለመሬት ዋጋው የሚከፍል ከሆነ መንግሥት ከትርፍ ሊያገኝ የሚገባውን ገቢ የሚያሳጣው እንደሆነም ይጠቅሳሉ፡፡ ስለዚህ ከኢንቨስትመንቱ ጋር ሊጣጣሙ የማይችሉ ዋጋዎች ሲሰጡ መንግሥት ይሁንታ እየሰጠ መቀጠል እንደማይኖርበትም ይመክራሉ፡፡

እንዲህ ያሉ የተጋነኑ ዋጋዎች ሲሰጡ መንግሥት ተጠቃሚ ይሆናል የሚል አመለካከት ሊኖር ይችላል የሚሉት ዶ/ር በክሪ የሱፍ የሊዝ ኤክስፐርት ሲሆኑ፣ ይህ አመለካከት ግን ከእውነት የራቀ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ምክንያቱም አስተዳደሩ ከሚያገኘው ጠቅላላ ዓመታዊ ገቢ ከሊዝ ተገኘ ተብሎ የሚጠቀሰው ገቢ መጠን እጅግ አነስተኛ በመሆኑ ነው፡፡

ስለዚህ መንግሥት ከሊዝ ከሚያገኘው ገቢ ይልቅ በሊዝ ከተሰጠው ቦታ ላይ ከሚሠራው ኢንቨስትመንት የሚያገኘው የትርፍ ግብር ብልጫ ያለው በመሆኑ፣ አስተዳደሩ የሊዝ ገቢን ዋነኛ ዓላማው አድርጐ መውሰድ እንደማይኖርበት መክረዋል፡፡

ይህ ከሆነ ደግሞ የተጋነኑ የሊዝ የጨረታ ዋጋን ሊቆጣጠርበት የሚችል ስልት እስካልተዘረጋ ድረስ የመሬት ሊዝ ዋጋ ተገቢ ያልሆነ ዋጋ እየተሰጠው ሊቀጥል ይችላል የሚል ሥጋት አላቸው፡፡

ዶ/ር በክሪ ሰሞኑን ለአንድ ካሬ ሜትር ቦታ የተሰጠውን ዋጋ እጅግ አስገራሚ ብለውታል፡፡ ‹‹መሬት መዋል ያለበት ለልማት ነው፡፡ ትክክለኛው መንገድ ለልማት እንዲውል ከተፈለ ደግሞ ለአልሚዎች የሚውል መሬት ዋጋው ተመጣጣኝ መሆን አለበት፡፡ ይህ ካልሆነ በተጋነነ የሊዝ ዋጋ የሚታይ ከሆነ ነገሩ አልሚን ማባረር ሆነ ማለት ነው፤›› በማለትም ገልጸውታል፡፡

በመሆኑም የሊዝ ዋጋ ሥሪት ዋና ዓላማው ልማትን ማራመድ እስከሆነ ድረስ እንዲህ ያሉ የተጋነኑ የሊዝ ዋጋዎች የግድ የመቆጣጠሪያ ስልት ሊኖራቸው እንደሚገባ ዶ/ር በክሪ ገልጸዋል፡፡ ዶ/ር በክሪ ከሙያ ባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን ከጥቂት ዓመታት በፊት በአዲስ አበባ የመሬት ሊዝ አሠራር የዋጋ ተመንና ጥቅል ይዘትን በተመለከተ ያደረጉት ጥናት ላይ እንደ አንድ ክፍተት የተመለከቱት የጨረታ ሒደቱን እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡

በወቅቱ ለጨረታ የሚቀርቡ ቦታዎች በመነሻ ዋጋቸውና መጨረሻ ላይ ለቦታው በሚሰጠው ከፍተኛ ዋጋ መካከል እጅግ ከፍተኛ የሆነ ልዩነት ታይቷል፡፡

የዋጋ ልዩነቱ ደግሞ እንዲህ ቀላል እንዳልነበርና ከሺዎችና ከመቶዎች በላይ ብልጫ ይታይበት እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡

ዶ/ር በክሪ ይህ መሬት በሊዝ ለጨረታ የሚቀርብበትን ዋነኛ ዓላማ ያፋልሳል ብለዋል፡፡ ይህም የከተማ አስተዳደሩ የጨረታ ሒደት ቁጥጥር የማይደረግበት መሆኑን ያሳየ በመሆኑ፣ እንዲህ ዓይነት የተጋነኑ ዋጋዎች እንዳይቀርቡ የመነሻ ዋጋው ተቀምጦ የተጋነነ ዋጋ እንዳይሰጥ የሚያደርግ አሠራር እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡

ለምሳሌ አንድ በጨረታ የቀረበ አንድ ካሬ ቦታ መነሻው 50 ብር ከሆነና ተጫራቹ 5,000 ብር ካመጡ የዋጋው አመጣጥ ጤነኛ አለመሆኑን በመገንዘብ ውድቅ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

ይህ የአስተዳደሩ ሥራ መሆን አለበት የሚሉት ዶ/ር በክሪ፣ መሆን አለበት ብለው እንደ መፍትሔ ያስቀመጡት የጨረታ መነሻ የሚባል ዋጋን ማስቀረት ነው፡፡

አስተዳደሩ በጨረታ የሚስማማውን ቦታ የገበያ ዋጋ የሚያመላክት መረጃ ይዞ በተለይ ለጨረታ ቢያቀርብና የሚሰጠውን የጨረታ ዋጋ እርሱ በጥራት ይህንን ያህል ሊያለማ ይችላል ብሎ በቅድሚያ ካስቀመጠው ዋጋ ጋር በማናበብ የጨረታ ውጤቱን ማፅደቅ ወይም መሰረዝ በሚችልበት አሠራር ሊኖረው እንደሚገባ ያስረዳሉ፡፡

እንደ እርሳቸው አባባል አስተዳደሩ በወቅቱ ሊያዋጣ ይችላል የሚለውን ዋጋ በቦታው ላይ ሊሠራ ከሚችለው ቢዝነስ ጋር በማጣጣም ለቦታው የሰጡት የዋጋ ግምት ተጫራቾች ከሰጡት ዋጋ ጋር ከተወሰነ መቶኛ በላይ ከሄዱ ወይም ከተወሰነ መቶኛ በላይ ካነሳ ውጤቱን ውድቅ ለማድረግ የሚችልበት አሠራር ተግባራዊ ሊደረግ ይገባል፡፡

እንዲህ ዓይነቱ አሠራር በኮንስትራክክሽን የጨረታ አሠጣጥ ላይ የሚታይ በመሆኑ፣ ይህንኑ የአሠራር ዘዴ በሊዝ ጨረታ ላይ መጠቀም እንደሚችል አመልክተዋል፡፡

በኮንስትራክሽን ጨረታ የግንባታው ባለቤት ግንባታው ሊያቀርቡ የሚችለውን በዚህ አግባብ ከሠራ በኋላ ሥራውን ለማሠራት ጨረታ ሲያወጣ ኮንትራክተሩ ያቀረበው ዋጋ ግንባታው ይፈጃል ተብሎ ከተገመተው ዋጋ 20 በመቶ ዝቅ ያለ ወይም ከ20 በመቶ የበለጠ ተጫራች ያቀረበ ተጫራች ወዲያው ይሰረዛል፡፡ ለሊዝ ጨረታም እንዲህ ዓይነቱን አሠራር መከተሉ ተገቢ መሆኑንም ይጠቁማሉ፡፡ በጥናታቸው ውስጥ ሊሠሩ ይገባል ተብሎ ከቀረቡ ሐሳቦች መካከል አንዱ መሆኑንም ያስታውሳሉ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ሊዝ ጉዳይ እጅግ ውድ ከተማ እያደረጋት በመሆኑ ሁለት ጉዳዮች ጐልተው እየተነሱ ይገኛሉ፡፡

የመጀመሪያው ጉዳይ አዲስ አበባ ዝቅተኛ ገቢ ያለው የኅብረተሰብ ክፍል መሀል ከተማ ላይ ኑሮውን መግፋት የሚችልበት ሁኔታ አለ ወይ? የሚለው ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የከተማው ኢኮኖሚ ጤነኛ ነው ወይ? የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገርም ባለሀብቶች እሴት ከማይጨመርበት ዘርፍ ይልቅ እሴት መጨመር በሚፈልጉ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እንዲሰማሩ ለማድረግ የታቀደው ዕቅድ ተግባራዊነት አዲስ አበባ ከተማ ከሌሎች አቻ ከተሞች ለየት የሚያደርጋት ከፍተኛ ገቢ ያለውና ዝቅተኛ ገቢ ያለው የኅብረተሰብ ክፍል በጋራ ተቀላቅሎ የሚኖር መሆኑ ነው፡፡

ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ግን ይህ መስተጋብር ቀስ እያለ እየተሸረሸረ የሄደ መስሏል፡፡ ለዚህ ማሳያዎቹ የመሬት ሊዝ ዋጋ ንረት፣ የመልሶ ማልማትና የኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታ ናቸው፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ያሉ ቦታዎች በሦስት ደረጃ ይከፈላሉ፡፡ የከተማው ወቅታዊ የሊዝ መነሻ ዋጋ መረጃ እንደሚያሳየው የመጀመርያው ማዕከላዊ የንግድ ቀጣና ሲሆን፣ በዚህ ሥር አምስት ደረጃዎች አሉት፡፡ ደረጃ አንዱ 1,686 ብር ሲሆን አምስተኛው 894 ብር ነው፡፡

ደረጃ ሁለት የሽግግር ዞን የተባለው ሲሆን፣ ይህም ከአምስት መነሻ ዋጋዎች  ተቀምጦለታል፡፡ ደረጃ ሁለት ሥር አንደኛ የሚባለው ቦታ 1,035 ብር በካሬ ሲሆን፣ አምስተኛው የሚባለው ቦታ ደግሞ 555 ብር ነው፡፡

ማስፋፊያ ቦታ አራት ደረጃ ያለው ሲሆን የመጀመሪያው 355 ብር፣ ከፍተኛው ደግሞ 191 ብር ነው፡፡

አስተዳደሩ እነዚህን ደረጃዎች የሚጠቀምባቸው ግን ለጨረታ መነሻ ዋጋ እንዲሆኑ ሳይሆን ለተለያዩ ቅጣቶች፣ በአካባቢ ዋጋ ለሚሰጣቸው ማኑፋክቸሪንግ፣ እንዲሁም ሕገወጥ ግንባታዎች ሕጋዊ ለማድረግና ለመሳሰሉት ነው፡፡

ትልቁ ሥጋት ከፍተኛ ዋጋ እየቀረበላቸው የሚገኙ ቦታዎች ቀጣይ ጨረታ በሚወጣበት ጊዜ አማካኙ ዋጋ ተወስዶ በቀጣይነት የጨረታ መነሻ ዋጋ ሆነው ማገልገላቸው ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በመኖሪያና በንግድ ሕንፃዎች ግብይት ላይ ደላሎች የጨረታ ዋጋዎችን በመጥቀስ የአካባቢውን ዋጋ በመተመን ሽያጭ እንዲካሄድ ማድረጋቸው ነው፡፡

ይህ የተያያዘ የሊዝ ዋጋ ንረት የከተማዋን ኢኮኖሚ በመሬት ላይ ብቻ እንዲፈስ የሚያደርግ በመሆኑ፣ መንግሥት ባለሀብቶች ወደ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እንዲገቡ የቀየሰውን ዕቅድ የሚፃረር እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የመሬት ባለሙያ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በካሬ 305 ሺሕ ብር የተከፈለበት መሬት ፍሬ ዋጋው 136.9 ሚሊዮን ብር ነው፡፡ በ30 ዓመታት ተከፍሎ እስኪጠናቀቅ አጠቃላይ ዋጋው ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ይሆናል፡፡ መሬቱን የገዛው ኩባንያ ግን ሕንፃውን የሚገነባው በ30 ሚሊዮን ብር ነው ቢባል ተሸንሽኖ ሲካራይ አሁን ባለው የኪራይ ዋጋ ኩባንያው የወጣውን ወጪ መልሶ ሕንፃውን ገቢ ማስገኘት የሚጀምረው ከ40 ዓመት በኋላ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

ይህ የሚያሳየው ከተማው ያመነጨው ኢኮኖሚ በመሬት ላይ የሚያርፍ በመሆኑ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ዕቅድ ሕልም ሆኖ እንደሚቀር ነው፡፡ አንድ የኢኮኖሚ ባለሙያ በዚህ ላይ ጨምረው እንደገለጹት፣ አካሄዱ በሒደት የከተማው ኢኮኖሚ ዕድገት ሊገታው ይችላል፡፡ የሚፈጠር እሴት ካለመኖሩም በላይ መንግሥት ኪራይ ሰብሳቢነት የሚለውን ዘርፍ ያስፋፋል ሲሉም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በሁለተኛ ደረጃ የተቀመጠው የመልሶ ማልማት ፕሮግራም በከተማው ውስጥ አደገኛ ሁኔታ ይዞ መምጣቱ ነው፡፡ በቀጣይነት አዲስ አበባ ከተማ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ቦታ እንዳይኖራት ያደርጋታል የሚል ነው፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ በ1996 ዓ.ም. የመልሶ ማልማት ፕሮግራም መጀመሩ ይታወሳል፡፡ ከዚሁ ፕሮግራም ጎን ለጎን የኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታ በማካሄድ ነዋሪውን ተጠቃሚ ለማድረግ ሥራዎች ተጀምረዋል፡፡ ነገር ግን ይህ ሐሳብ በአጭር የተኮላሸ ሲሆን፣ ሰፋፊ ኮንዶሚኒየም ቤቶች በአዲስ አበባና ኦሮሚያ ልዩ ዞን ድንበር ላይ ተገንብተዋል፡፡

ለዚህ ምሳሌ ኮዬ ፈጨ፣ ቱሉ ዲምቱ፣ አባዶ፣ አራብሳና የመሳሰሉ ቦታዎች ላይ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ኮንዶሚኒየም ቤቶች መገንባታቸው ነው፡፡

በመሀል ከተማ ይኖር የነበረ ሕዝብ በልማት ምክንያት እየተነሳ ከተማ ዳር መኖር የጀመረ ሲሆን፣ በልማት ምክንያት ነፃ የሆነው ቦታ በጨረታ አልያም መንግሥት በሚያካሂደው ልማት አማካኝነት ከፍተኛ ገቢ ላለው የኅብረተሰብ ክፍል እየተዛወረ ይገኛል፡፡

በመሀል ከተማ የተገነቡ አፓርታማ ቤቶች በካሬ ሜትር 30 ሺሕ ብር እየቀረበላቸው ሲሆን፣ እንደ ልደታ ባሉ አካባቢዎች ደግሞ በኮንዶሚኒየም ሕንፃ ሥር ለተገነቡ ንግድ ቤቶች 70 ሺሕ ብር በላይ ተሰጥቷል፡፡

ቁጥሮች በሙሉ እየተናገሩ የሚገኙት አዲስ አበባ ዝቅተኛ ገቢ ላለው ወይም ለድሃ የማትመች መሆኗን እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

ይህ ቀመር ቀደም ባሉት ጊዜያት ድሃና ባለፀጋ ተሰባጥሮ ይኖር የነበረ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት የመሬትና የሕንፃ ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ በመጨመሩ ልዩነቱ በግልጽ  እየተፈጠረና እየሰፋ መምጣቱ እየታየ ነው፡፡

ከፍተኛ ገቢ ያለው የኅብረተሰብ ክፍል ወደ መሀል ከተማ ሲያቀና፣ ድሃው ሕዝብ ዳር አገር እየተመመ ይገኛል፡፡

ለዘመናት ተሰባጥሮ ይኖር የነበረን ማኅበረሰብ መለያየቱ አግባብ እንዳልሆነ የሚናገሩት የመረጃ ምንጮች፣ ይህ ማኅበራዊ እሴት ለሌሎች አገሮች ተምሳሌት እንደነበር ይገልጻሉ፡፡ ነገር ግን ይህ እሴት በአሁኑ ወቅት እየተሸረሸረ መምጣቱ አደገኛ ሁኔታ ሊፈጥር ይችላል የሚሉ አሉ፡፡

ባለሙያዎች እንደሚሉት መንግሥት እነዚህን ክስተቶች ከግምት በማስገባት የሊዝ ዋጋ ላይ ገደብ በመጣል የዋጋ መቆጣጠሪያ ዘዴ ሊቀይስ ይገባል ይላሉ፡፡ በእርግጥ የሊዝ መሬት ግብይት የፈጸሙ ባለሀብቶች በገቡት ውል መሠረት ክፍያቸውን ይፈጽማሉ ወይ በማለት የሚጠይቁም አሉ፡፡  ከንቲባ ድሪባ ኩማ በቅርቡ ለከተማው ምክር ቤት ባቀረቡት ሪፖርት ከሊዝ መሰብሰብ ያለበት ገንዘብ እየተሰበሰበ እንዳልሆነና ይህንንም ማስተካከል እንደሚገባ አስምረውበት ነበር፡፡ ከአብዛኛዎቹ የሊዝ መሬት ተጠቃሚ ባለሀብቶቸ ከፍተኛ ውዝፍ ዕዳ እንዳለባቸው የአስተዳደሩ ምንጮች ይናገራሉ፡፡ ከዚህ በመነሳት ከፍተኛ ገንዘብ ለመሬት እንዲሰጥ ከማድረግ ይልቅ አስተዳደሩ ማግኘት ያለበትን ገንዘብ በወቅቱ ማግኘት እንዲችል ማድረግ ይገባል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ መንግሥት ያለ ገደብ ለመሬትና ለመሬት ነክ ንብረቶች የሚወጡ ገንዘቦች ምንጭ ምን እንደሆነ ያውቃል ወይ? የገንዘብ ምንጭ ከሕገወጥ ተግባራት የፀዳ ነው ወይ? በማለት ጥርጣሬያቸውን በጥያቄ የሚያቀርቡም አሉ፡፡ ባለሙያዎች እንደሚሉት አዲስ አበባን በተለይም መካከለኛውን የከተማውን ክፍል ለባለፀጋውም ለድሃውም እኩል ማድረግ ሲታሰብ የመልሶ ማልማት ፕሮግራም በድጋሚ ሊከለስ ይገባል፡፡ ለልማት ነዋሪዎችን ማንሳት እንዳለ ሁሉ፣ ከልማቱ በኋላ ጊዜያዊ ቦታ የተነሳውን ነዋሪ መልሶ ማስፈር ይገባል የሚሉ ሙግቶችም እየቀረቡ ነው፡፡

አቶ መኩሪያ በግልጽ ያስቀመጧቸው ሐሳቦች ተግባራዊ ማድረግ እንዳለ ሆኖ ከላይ የተሰጡት ሐሳቦችም ተግባራዊ ሊደረጉ የሚገባቸው በመሆናቸው መንግሥት በዚህ ጉዳይ ላይ ቆም ብሎ ማሰብ እንዳለበትም እየተገለጸ ነው፡፡

(ለዚህ ዘገባ ዳዊት ታዬ አስተዋጽኦ አድርጓል)

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.