የጅቡቲ አፋሮች ትግል እንዴት ከሸፈ? (ከይገርማል) ክፍል 1 – ይገርማል ታሪኩ

መግቢያ

የጅቡቲ አፋሮችን ትግል መክሸፍ በተመለከተ ጽሁፍ ለማዘጋጀት ሳስብ ብዙ ጊዜ ሆኖኛል። ነገር ግን በተግባር ላውለው ሳይቻለኝ እስከአሁን ቆይቻለሁ። ለዚህም ምክንያት ነበረኝ። ምክንያቴ ደግሞ በጅቡቲ አፋሮች ትግል መኮላሸት የኢትዮጵያውያንም እጅ ስላለበት እንዴት አድርጌ ማቅረብ እንዳለብኝ ሳወጣ ሳወርድ ጊዜ በመውሰዴ ነበር። ከአፋሮች ጎን ተሰልፈው የግል ጥቅማቸውን ለማሳካት ሲያልሙ የነበሩ ኢትዮጵያውያንን ወደላይም ሆነ ወደታች ወይም ወደጎን ያለ የዘር ሀረጋቸውን ስሜት ላለመጉዳት በማሰብ ስም በመጥቀስና ባለመጥቀስ ላይ ብቻ እንኳ ከራሴ ጋር ደጋግሜ ተሟግቻለሁ። በመጨረሻ ላይ ኢትዮጵያዊነትን ክደው ነገር ግን በኢትዮጵያውያን መስዋዕትነት ፍላጎታቸውን ለማሳካት ሴራ ሲጠነስሱ የነበሩትን ሁለቱን ዋና አክተሮች በስም ጠቅሶ ዕውነቱን ይፋ ማድረግ የሞራልም የታሪክም ግዴታ አድርጌ ተቀብየ ይህንን ጽሁፍ አዘጋጀሁ።

በጽሁፌ ላይ ስለጅቡቲ ታሪካዊ መሰረትና ከፈረንሳይ ጋር እንዴት እንደተወዳጀች የሚያሳይ ቁንጽል መረጃ ቀርቧል። ሀገሪቱ ነጻነቷን ያገኘችበትን ሁኔታና የሶቪየት ሕብረት መበታተን በሶሻሊስት ሀገሮች ላይ የፈጠረው ተጽዕኖ፣ አልፎ ተርፎ የጅቡቲ አፋሮችን ትግል እንዴት እንደጎዳው ያነሳሳል። የታላቋ ሶማሊያ ህልመኞችና የደርግ ተፈናቃይ ወታደሮች ያሳረፉት አሻራም ተተርኳል። የጅቡቲ አፋሮች ትግል ከጀመሩበት ማግስት ጀምሮ ነጻ መሬታቸውን ለመንግሥት አስረክበው ለስደት እስከተዳረጉበት ድረስ ባለው ጊዜ እኔም የታሪኩ ተጋሪ ነበርሁ። እና እኔ እራሴ እንዴት ወደጅቡቲ ሄጀ የአፋሮችን ትግል እንደተቀላቀልሁ፣ በጅቡቲ የነበረኝን ቆይታና እስከፍጻሜው ድረስ ያሳለፍሁትን ህይወት ሳልሰስት “እንኩ” ብያለሁ። ከሀገራቸው ተሰደው በሰው ሀገር እየኖሩ በየተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ለህዝባቸው በጎ ነገር ለመስራት የሚደክሙ፣ ሀገራችን ምን አደረገችልን ሳይሉ “ለሀገራችን ምን እናድርግ!” ብለው የሚጨነቁ፣ ወገኖቻችንን ማሰብ ተገቢ ነው ብየ በማመኔ ያስታወስኋቸውን ጓዶቸን በስም ጠቅሸ አስተዋውቄያለሁ። በጅቡቲ አድርገው ወደአረብ ሀገር ለመሄድ የሚነሱ ኢትዮጵያውያን ዕጣ ፈንታ ምን እንደሆነ ትምህርት የምናገኝበት ቢሆን ብየ የማውቃቸውን ሰዎች በምሳሌነት ጠቅሻለሁ። የሆነው ሆኖ የላክሁለት ድረገጽ ጠቃሚ መስሎ ካልታየው ጽሁፌን ባያወጣው ቅሬታ አይኖረኝም።

ጅቡቲ ማን ናት?

ጅቡቲ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የምትገኝ በሰሜንና በምስራቅ ከኤርትራና ከቀይ ባህር በደቡብ ምስራቅ ከሶማሊያ በደቡብና በምዕራብ ከኢትዮጵያ በምስራቅ ከኤደን ባህረሰላጤ የምትዋሰን ከአንድ ሚሊዮን ያነሰ የሕዝብ ብዛት እና 23200 ስኩየር ኪሎሜትር የቆዳ ስፋት  ያላት በዋና ከተማዋ ስም የምትጠራ ትንሽዬ ሀገር ናት። የጅቡቲ የስራ ቋንቋ አረብኛና ፈረንሳይኛ ይሁን እንጅ አብዛኛው የሀገሪቱ ሕዝብ ሶማሊኛ እና አፋርኛ ተናጋሪ ነው። በሰሜኑ የሀገሪቱ አካባቢ የሚኖሩት አፋሮች ናቸው። ኢሳወቹ በደቡቡ የሀገሪቱ አካባቢ ይኖራሉ። ኢሳወች ሶማሊኛ ተናጋሪ ሕዝቦች ናቸው። ከአጠቃላይ የሀገሪቱ ሕዝብ ውስጥ 60% የሚሆነው ኢሳ፣ 35% የሚሆነው ደግሞ አፋር ነው። ቀሪው 5% የሚሆነው ሕዝብ ኢትዮጵያውያን፡ ፈረንሳውያን፡ አረቦችና ጣሊያናውያን ናቸው። 76% የሚሆነው የሀገሪቱ ሕዝብ የሚኖረው በከተሞች ውስጥ ሲሆን ቀሪው 24% የሚሆነው ሕዝብ አርብቶ አደር ነው። የጅቡቲ የኢኮኖሚ ምሰሶ የሰርቪሱ ሴክተር ነው። በንግድና በወደብ አገልግሎት የሚገኘው ገቢ የሀገሪቱ የኢኮኖሚ መሰረት ሆኖ ቀጥሏል። በጅቡቲ ወደብ የገቢና የወጪ ንግድ እንቅስቃሴ አገልግሎት 70% ተጠቃሚዋ ኢትዮጵያ ናት። አመታዊ የዝናብ መጠኑ እጅግ ውሱን በመሆኑ የምግብ ፍጆታዋን የምታሟላው በግዥ ነው። ጎዳ ተብሎ በሚጠራው ከታጁራ በስተምዕራብ በኩል ከሚገኘው ተራራ ላይ መጠነኛ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት ይመረታል። ያም ሆኖ የሀገሪቱን የአትክልትና ፍራፍሬ ፍላጎት የሚያሟላ አይደለም።

በጅቡቲ ታሪክ ላይ ኢትዮጵያውያንና አውሮፓውያን የተለያየ እይታ አላቸው። አውሮፓውያን የሚሉት ጅቡቲ ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ2500 ዓመተ ዓለም ጀምሮ ፑንትላንድ ተብሎ ይጠራ የነበረው የሰሜን ሱዳንን፡ ኤርትራንና የአሁኗን ጅቡቲን የሚያጠቃልለው የግብጽ አካል እንደነበረች ነው። በዝሆን ጥርስ በወርቅና በቆዳ ንግድ ትታወቅ የነበረችው ጅቡቲ ሕዝቧ ከጥንታዊቷ ግብጽ ጋር ጥብቅ ቁርኝት እንደነበረው ነው የሚናገሩት። ኢትዮጵያውያን የታሪክ ምሁራን የሚሉት ደግሞ በውል ስምምነት ለፈረንሳይ እስክትሰጥ ድረስ ጅቡቲ የኢትዮጵያ አካል ሆና እንደቆየች ነው፡ ራሷ ግብጽም ብትሆን በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ አካል እንደነበረች ነው።

የኢትዮጵያ የታሪክ መዛግብት እንደሚያስረዱት ጅቡቲ ከእናት ሀገሯ ኢትዮጵያ የተለየችው በ19ኛው ክፍለዘመን በአጼ ሚኒሊክ ዘመነ መንግሥት ነበር። ከአጼ ሚኒሊክ ዘመነመንግሥት በፊት ኢትዮጵያውያን በአዱሊስ በዘይላ በኦቦክና በታጁራ በኩል ከአውሮፓና ከእስያ ሀገራት ጋር የንግድ ግንኙነት ሲያደርጉ ኖረዋል። ይህን የንግድ እንቅስቃሴ የበለጠ ለማጠናከር ሲባል ከጅቡቲ እስከ አዲስ አበባ ድረስ የሚያዘልቅ የባቡር ሀዲድ መዘርጋት አስፈላጊ ነው ተብሎ በመታመኑ በአጼ ሚኒሊክ ዘመነ-መንግሥት ከፈረንሳይ ጋር ስምምነት ለማድረግ ተወሰነ። ምርቶችን ወደውጪ ለመላክም ሆነ ለሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት የባሕር ትራንስፖርት ቀዳሚ ተመራጭ በመሆኑ ጅቡቲ ላይ ዘመናዊ ወደብ ገንብቶ ከመላው አለም ጋር ፈጣንና ቀልጣፋ ግንኙነት ለማድረግ ከመሀል ሀገር ጋር የሚያገናኝ የባቡር አገልግሎት መኖር ወሳኝ ነበር። ለሀገራቸው ዕድገትና ለሕዝባቸው ስልጣኔ እረፍት አጥተው ይሰሩ የነበሩት ሚኒሊክ ጅቡቲን ለ99 ዓመታት በውል ለፈረንሳይ በማከራየት በምላሹ የፈረንሳይ መንግሥት ከጅቡቲ እስከአዲስአበባ የሚዘልቀውን የባቡር ሀዲድ ሰርቶ እንዲያስረክብ ስምምነት ፈጸሙ። በወቅቱ የጅቡቲ ከተማ ለኑሮ የማትመች ሰው-አልባ እንደነበረች ይታወቃል። የውጪ ኃይል በቀላሉ ወደ ሀገር እንዲመጣ መጋበዝ ይሆናል ብለው ያሰቡት ሚኒስትሮች የባቡር ግንባታውን በጽኑ የተቃወሙበት ሁኔታ እንደነበር ይታወቃል። ሌላው ቀርቶ የንጉሠነገሥቱ ባለቤት የነበሩት እቴጌ ጣይቱ እንኳ የግንባታውን ሥራ ለማስተጓጎል ብዙ ጥረት አድርገዋል። ይሁን እንጅ ሁሉም መሰናክል ታልፎ የጅቡቲ – አዲስ አበባ የባቡር መስመር ተሰርቶ አገልግሎት መስጠት ጀመረ።

የፈረንሳይና የጅቡቲ ግንኙነት

ፈረንሳይ ወደአፍሪካ ቀንድ እግሯን ያስገባችው መጀመሪያ በኦቦክ በኩል ነበር። በጊዜው አካባቢውን ያስተዳድሩ ከነበሩት የኢሳና የአፋር ሱልጣኖች ጋር እኤአ በ1862 ባደረገችው የወዳጅነትና የትብብር ስምምነት የኦቦክን ወደብ በግዥ ከእጇ ያስገባችው ፈረንሳይ ከ1883-1887 ድረስ ባደረገቻቸው ሌሎች ተጨማሪ ስምምነቶች ታጁራን ጭምር በአስተዳደሯ ስር በማዋል የአካባቢው የበላይ ጠባቂ ነኝ ለማለት በቃች። ይህ በእንዲህ እንዳለ ከጅቡቲ እስከ አዲስ አበባ የሚዘልቀውን የባቡር ሀዲድ ለመገንባት በኢትዮጵያና በፈረንሳይ መንግሥታት መሀል የተደረገውን ስምምነት ተከትሎ እ.ኤ.አ በ1894 ዓ.ም ፈረንሳይ በዋና ከተማነት ይታወቅ የነበረውን ኦቦክ ትታ ጅቡቲን ዋና ከተማ አደረገች። እ.ኤ.አ በ1897 ዓ.ም ኢትዮጵያና ፈረንሳይ በጅቡቲና በኢትዮጵያ መሀል የድንበር ማካለል ተግባር አከናወኑ። የወሰን ማካለሉ ተግባር ተፈጽሞ በመሬት ላይ ምልክቶች ከተቀመጡ በኋላ ፈረንሳይ አሁን ጅቡቲ በመባል የምትታወቀውን ሀገር French Somaliland ብላ ሰይማ እ.ኤ.አ እስከ 1967 ዓ.ም ድረስ ይዛት ቆየች። ከዚያም በኋላም ቢሆን በሦስተኛው ሕዝበ-ውሳኔ ጅቡቲ ነጻ ሀገርነቷን እስክታረጋግጥ ድረስ ላላ ባለ መልኩ በፈረንሳይ የበላይ ጠባቂነት ስር ቆይታለች። የወሰን ማጽናት ስምምነቱ በአጼ ኃ/ሥላሴ ዘመነ መንግሥትም ለሁለት ጊዜ ያህል በ1945 ዓ.ም እና በ1954 በሁለቱ ሀገሮች መሀል ተደርጓል። ጅቡቲ ከ1967 ዓ.ም ጀምሮ ነጻነቷን እስካገኘችበት 1977 ዓ.ም ድረስ ብዙ ነገሮችን በራሷ መፈጸም የሚያስችላት መብት ያገኘች ቢሆንም በፈረንሳይ የበላይ ጠባቂነት ስር ነበረች።

የመጀመሪያው የጅቡቲ ሕዝበውሳኔ

ሶማሊያ ነጻነቷን ከማግኘቷ ከሁለት አመታት አስቀድሞ እ. ኤ. አ በ1958 ዓ.ም የጅቡቲን እጣ ፈንታ ለመወሰን የሕዝበ ውሳኔ (ሪፈረንደም) ተደርጎ ነበር። ጅቡቲ ነጻ ከምትወጣዋ ሶማሌ ጋር አብራ አንድ ሀገር መመስረት አለባት ወይስ በፈረንሳይ ውስጥ መቀጠል በሚሉት ሁለት አማራጮች የተደረገው ሕዝበ ውሳኔ የተቋጨው ጅቡቲ በፈረንሳይ ስር ሆና መቀጠል አለባት በሚል የድምጽ ብልጫ ነበር። የፈረንሳይ ሶማሊላንድ (የአሁኗ ጅቡቲ) ም/ ፕሬዚደንት የነበረው ማህሙድ ሀርቢ ፋራህ ታላቋን ሶማሊያን ለመመስረት የመጀመሪያው አላሚ ነበር ማለት ይቻላል። ፋራህ ለአረብ መንግሥታት የተለያዩ ስጦታወችን በማበርከት ጅቡቲን ከሶማሊያ ጋር ለመቀላቀል ድጋፍ እንዲያደርጉለት ሲደክም ኖሯል። ከዚህም በተጨማሪ በሰሜን ሶማሊያ አካባቢ የሚኖረውን ሕዝብ ወደጅቡቲ እንዲገቡ በማድረግ በምርጫው አብላጫ ድምጽ አግኝቶ ጅቡቲን ወደፊት ነጻ ከምትወጣዋ ሶማሊያ ጋር ለመቀላቀል ብርቱ ጥረት አድርጓል። ይሁን እና ውጤቱ ፋራህ እንዳሰበው ሳይሆን ቀርቶ ጅቡቲ በፈረንሳይ ስር ሆና ትቀጥል የሚለው ድምጽ አሸናፊ ለመሆን በቃ። ጅቡቲ በፈረንሳይ ስር ሆና እንድትቀጥል ሰፊውን ድርሻ ያበረከቱት አፋሮችና በሀገሪቱ የሚኖሩ አውሮፓውያን ነበሩ። ሕዝበውሳኔ ተካሂዶ ብዙም ሳይቆይ በቅኝ ግዛት ስር ይተዳደሩ የነበሩ ሀገሮች ነጻ ይውጡ በሚል የተደረሰውን ስምምነት መሰረት በማድረግ ፈረንሳይ ጅቡቲን ለቃ እንድትወጣና ነጻ የጅቡቲ መንግስት እንዲቋቋም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጥሪ አቀረበ። ይሁንና ይህን የተባበሩት መንግሥታት ያሳለፈውን ውሳኔ ለመቀበል ፈረንሳይ ፈቃደኛ አልነበረችም።

ሁለተኛው የጅቡቲ ሕዝበውሳኔ

እ.ኤ.አ በ1966 ዓ.ም የፈረንሳይ ፕሬዚደንት ቻርልስ ዲ ጋውለ (Charles De Gaulle) ጅቡቲን ጎብኝተው ነበር። የፕሬዚደንቱን ጉብኝት ተከትሎ ጉብኝቱን የሚቃወምና የጅቡቲን ነጻነት የሚጠይቅ ሰላማዊ ሰልፍ በአመጻዊ እንቅስቃሴ ታጅቦ ተካሄደ። ይህን የሕዝብ ስሜት የተመለከቱት ቻርለስ በጅቡቲ ሁለተኛ ሪፈረንደም እንዲካሄድ ፈቀዱ። በዚህም መሰረት እ.ኤ.አ በ19.03.1967 ዓ.ም ጅቡቲ ሁለተኛውን ሕዝበውሳኔ አካሄደች። በዚህ የድምጽ አሰጣጥ ላይ እንደበፊቱ ሁሉ ኢሳወች ጅቡቲን ከሶማሊያ ጋር አንድ ለማድረግ ድምጽ ሲሰጡ አፋሮች ደግሞ በፈረንሳይ ስር ለመኖር ምርጫቸው አድርገዋል። ምርጫው ከሚካሄድበት ቀን ቀደም ብሎ በርካታ ኢሳወች የጅቡቲ መታወቂያ የላችሁም በማለት ከሶማሊያ የመጡ ናቸው ተብለው ተባረዋል። ኢትዮጵያ በበኩሏ የኢትዮጵያ አፋሮችን ወደፈረንሳይ ሶማሊላንድ በማስገባት ፈረንሳይ ሶማሊላንድ በፈረንሳይ ስር እንድትቆይ ድምጽ እንዲሰጥ አድርጋለች ተብላ ተወንጅላለች። ይህን ክስ የፈረንሳይ መንግሥት ሀሰት ነው ሲል አጣጥሎታል። ይሁን እንጅ ኢትዮጵያና ፈረንሳይ በአጼ ሚኒሊክ ዘ/መንግሥት የተፈራረሙትን ስምምነት ተግባራዊ በማድረግ ከ99 አመት ቆይታ በኋላ ጅቡቲን ለኢትዮጵያ ለመመለስ በሁለቱ ሀገሮች መሀል የውስጥ መግባባት እንደነበር የሚካድ አይደለም የሚሉ አሉ። የሁለተኛው ሕዝበ-ውሳኔ ፈረንሳይ ሶማሊላንድ በፈረንሳይ ስር ሆና እንድትቀጥል የሚል በመሆኑ በሀገሪቱ ደም አፋሳሽ የሆነ ግጭት አስከትሏል። ከግጭቱ በኋላ ፈረንሳይ በፈረንሳይ ሶማሊላንድ ላይ የነበራትን ወታደራዊ ኃይል አጠናከረች። ከዋና ከተማው ውጪ ያለውን የሀገሪቱን አካባቢም የአፋርና የኢሳ ክልል በሚል ከፈለች።

ሦስተኛው የጅቡቲ ሕዝበውሳኔ

ኢሳወች የሶማሌ የዘር ግንድ አካል ናቸው፡ ቋንቋቸውና ሀይማኖታቸውም አንድ ነው። ፍላጎታቸው አንዲት ታላቅ የሶማሌ ሀገር መመስረት ነው። የአፋሮች ፍላጎት ከኢሳወች ፍላጎት በእጅጉ ይለያል። አብዛኛው የአፋር ሕዝብ የሚኖረው በኢትዮጵያ ነው። ወደኢትዮጵያ ለመግባትና ለመውጣት ድንበር አያግዳቸውም። በዚህም ምክንያት ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸው ቁርኝት ከፍተኛ ነው። ከሁለተኛው ሕዝበ-ውሳኔ ወዲህ ኢሳወች ዝም ብለው አልተኙም። ከሶማሊያ እየሰረጉ የገቡት ሶማሌወች ቁጥር ዴሞግራፊውን በሚገርም ሁኔታ ቀይረውት ነበር። ይህ የሶማሌወች የቁጥር መብዛትና የአመጽ እንቅስቃሴው የፈጠረው ጫና ፈረንሳይ ሶማሊላንድን ለሦስተኛ ጊዜ ሕዝ-በውሳኔ እንድታደርግ አስገደዳት። በዚህ ሕዝበውሳኔ ላይ ዋና አክቲቪስት የነበሩት ሀሰን ጉሌድ አፕቲዶን ፈረንሳይ ሶማሊላንድ ራሷን ችላ እንደሀገር እንድትቀጥል ያደረጉት የቅስቀሳ ዘመቻ የሌሎች አክተሮች ድጋፍ የተቸረው ነበር። ሀሰን ጉሌድ ኦፕቲዶን በ1958ቱ ሪፈረንደም ወቅት ከጎሳ አባሎቻቸው አመለካከት ባፈነገጠ መልኩ ፈረንሳይ ሶማሊላንድ ከፈረንሳይ ጋር መቀጠል አለባት የሚል አቋም ሲያንጸባርቁ የነበሩ ሰው ናቸው። በሦስተኛው የሕዝበ-ውሳኔ ወቅት ሦስተኛ አማራጭ ሆኖ የቀረበው የፈረንሳይ ሶማሊላንድ ነጻነት ጉዳይ አመጹን ለማቀዝቀዝና በቀጠናው ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የተሻለ አማራጭ ነው ተብሎ ስለታሰበ ነበር ድጋፍ የተቸረው። እ.ኤ.አ በ27.06.1977 የተካሄደው ሦስተኛው ሕዝበ-ውሳኔ በሚገርም ሁኔታ በ98.8% ድምጽ የፈረንሳይ ሶማሊላንድን ነጻነት አበሰረ። ሐሰን ጉሌድ አፕቲዶን የመጀመሪያዋ የፈረንሳይ ሶማሊላንድ ፕሬዚደንት ሆነው ሲመረጡ የሀገሪቱ መጠሪያ ደግሞ በዋና ከተማዋ ስም የጅቡቲ ሪፐብሊክ በሚል እንዲጠራ ተወሰነ።

የጅቡቲ ጉዳይ በጅቡቲያውያን ምርጫ ከመወሰኑ በፊት በነበሩት ጊዚያት ፈረንሳይ፡ ሶማሊያ፡ የአረብ ሀገሮችና ኢትዮጵያ በግልጽና በስውር የመሻኮቻ አጀንዳ ሆኖ ቆይቷል። ጅቡቲ ነጻነቷን ከተቀዳጀች በኋላም ቢሆን ሁሉንም ለጅቡቲ ለራሷ ትተው አርፈው አልተቀመጡም። በነጻነት ማግስት the Front for the Restoration of Unity and Democracy (FRUD) የተባለ የአፋር ድርጅት ተቋቋመ። FRUD የሚለውን ምህጻረ ቃለ አፋሮች ፍሪድ ብለው ነው የሚጠሩት። ፍሪድ በአንድነትና ዴሞክራሲ ስም የተቋቋመ ድርጅት ይሁን እንጅ የሚታየው እንደአፋር ነጻ አውጪ ድርጅት ነበር። ስሙን የረሳሁት ከድርጅቱ መስራቾች አንዱ የነበረ ሰው በአንድ ወቅት እንዳጫወተኝ ድርጅቱ የተመሰረተው በኢትዮጵያ መንግሥት (በደርግ)እንደሆነና የመጀመሪያወቹ ተዋጊወቹ የሰለጠኑት በወሎ ክ/ሐገር ቃሉ አውራጃ ቀርሳ ከሚባል ቦታ እንደነበረ ነው። ይሁን እንጅ ደርግ በምስራቅ በሶማሊያ በሀገር ውስጥ ደግሞ በሻዕቢያ፡ በወያኔ፡ በኢሕአፓ፡ በኢዲዩ፡ በኦነግና በሌሎችም ጦርነት ተከፍቶበት ስለነበር ራሱን ከመከላከል አልፎ የጅቡቲ አፋሮችን ትግል ለማገዝ አቅሙ አልነበረውም።

የሶቪየት ሕብረት መበታተንና በሶሻሊስት ሀገሮች ላይ የፈጠረው ተጽዕኖ

በMarch 1985 የሶቪየት ሕብረት ኮሙኒስት ፓርቲ ዋና ጸሀፊ ሆኖ ወደስልጣን የመጣው ሚካኤል ጎርባቾቭ በዓለም ላይ ግዙፍ የሆነ የታሪክ ለውጥ እንዲከሰት አድርጓል። perestroika (ተሀድሶ) and glasnost (ግልጽነት) በሚሉ ሁለት መርሀ ግብሮች በአለም አቀፍ ግንኙነት፡ በፖለቲካና በኢኮኖሚ አዲስ ምዕራፍ እንዲከፈት አድርጓል። ጎርባቾቭ በስልጣን ላይ በቆየባቸው አምስት አመት ከዘጠኝ ወር የጊዜ ክልል ሀገሪቱ ገንብታው የነበረውን ኃያልነት አፈራረሰ። ሶቪየት ህብረት በምስራቅ አውሮፓ የነበራትን የበላይነት አነሳች። በዩኒየኑ ውስጥ ተጠቃለው የነበሩ አካባቢወችን በመልቀቅ 15 ነጻ መንግስታት እንዲመሰረቱ አደረገ። ይህን ተከትሎ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር የነበረው ፍጥጫ ማለትም የቀዝቃዛው ጦርነት አበቃ ተባለ። ሚካኤኢል ጎርባቾቭ ለአለምም ሆነ ለራሽያ ካስገኘው ጥቅም ይልቅ ያስከተለው ጉዳት እጅግ ከፍተኛ እንደሆነ ይታመናል። በመጀመሪያ ደረጃ ራሽያ ለከፍተኛ የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ ተዳርጋ ሕዝቧ በኑሮ ውድነት ቀላል የማይባል ችግር አሳልፏል። አንድ የአሜሪካ ዶላር እስከ 300 ሩብል ድረስ የተመነዘረበት ከፍተኛ የፋይናንስ ቀውስ አስከትሎ ብዙ ጉዳት አድርሷል። ፖለቲካዊና ማህበራዊ ቀውሱም እንዲህ በቀላሉ የሚነገር አይደለም። በዩኒየኑ ታቅፈው የነበሩት ትናንሽ አካባቢወች ነጻነታቸውን ሲጎናጸፉ ሕዝቦቻቸው ለአስከፊ ችግር ተጋለጡ። ዛሬ ላይ በአውሮፓ ሀገሮች የጥገኝነት ጠያቂወች ሆነው በየካምፑ ተጠልለው የሚኖሩ፣ በሌብነትና በማጭበርበር ርካሽ ተግባር ተሰማርተው የሚገኙ የነዚህ አካባቢ ሰዎች እጅግ ብዙ ናቸው። የሶቪየት ሕብረት መፈራረስ ሶቪየት ሕብረትን ተከትለው ሶሻሊዝምን መርሀቸው ያደረጉ ሌሎች ሀገሮችንም ከምንም በላይ የጎዳ ነበር። የሚካኤል ጎርባቾቭ የተሀድሶ መርሀ-ግብር ከአሜሪካ ጋር የነበረውን የቃዝቃዛ ጦርነት እንዲያከትም ሲያደርግ የሶቪየት ተከታይ ለነበሩት ሀገሮች ደግሞ መራር ጦርነት ፈጠረ። ዩጎዝላቪያ፡ ቸኮዝላቫኪያ፡ ቡልጋሪያ፡ ሩማኒያ፡ ሀንጋሪ፡ ምስራቅ ጀርመን የአሜሪካ የበቀል በትር አጎሳቁሏቸዋል። ኢራቅ ከሶቪየት ህብረት ጋር በነበራት ስትራቴጅካዊ ግንኙነት ምክንያት ለአስከፊ ቅጣት ተዳርጋለች። የኢስያና የአፍሪካ ሶሻሊስት ሀገሮች አይቀጡ ቅጣት ተቀጥተዋል። የመን ፍዳ እያየች ነው። ኤርትራ ከኢትዮጵያ እንድትገነጠል ተደርጎ ቀሪው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሀገሩና ለሕዝቡ ክብርና ፍቅር በሌለው ወያኔ ስር ውሎ እንዲቀጣ ተፈርዶበት በስቃይ እያነባ ነው። የሶቪየት ሕብረትን መፍረስ ተከትሎ በምስራቅ አፍሪካ የተፈጠረው ቀውስ በጅቡቲ አፋሮች ትግል ላይም የፈጠረው ተጽዕኖ አለ።

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.