የፕሮፈሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ጂክሳ መጽሐፍ በላስ ቬጋስ – ውብሸት ወንድሙ

ታህሳስ ፲፱ ቀን ፪ሺ፱ ዓ/ም (DECEMBER 28,2016) ከአሜሪካን ታዋቂ ከሚባሉ ከተሞች መካከል አንዷ በሆነችው በላስ ቬጋስ ከተማ አገርህን እወቃት ከጠላትም ጠብቃት በሚል መሪ ቃልና ቅስቀሳ የታደሙው የከተማው ነዋሪ ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳን በከፍተኛ ጭብጨባና ከፍ ባለ አክብሮት ወደ አዳራሹ ሲገቡ ተቀብሏቸዋል።

ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ጂክሳ ከሰሯቸው ስራዎች መካከል /ፒ. ኤች.ዲ/ ገጣሚ፣ ጸሐፊ ተውኔት እና ከ፷ (60) በላይ መጽሐፎችንና መጣጥፎችን በአማርኛ፣ በጀርመንኛ እና በእንግሊዘኛ ቋንቋዎች አሳትመው ለንባብ ማብቃታቸውን፤  በጀርመን እና በአሜሪካ በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ ማስተማራቸውን፤ በተጨማሪም የተወሰኑ ስራዎቻቸውን በአሜሪካ እና በኢትዮጵያ ለመድረክ ማብቃታቸውን፤ ከፍትኛ አድናቆትን ያገኙ የፊልም ስራዎቻቸውም ከብዙ በጥቂቱ ለታዳሚው ተገልጿል።

በአዘጋጆቹ በተያዘው መርሃግብር መሰረት ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ  ለአገርና ለወገን ከሰሯቸው ከቀደምት ስራዎቻቸው መካከል ለአብነት ያክል ለመጀመሪያ ጊዜ በአማርኛ ቋንቋ በዚሁ በአሜሪካን አገር በካሊፎርኒያ ግዛት ውስጥ ስለአቋቋሙት የቴሌቭዥን ጣቢያ ፤እንደዚሁም ለማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወላጅ ማስተማሪያና ምሳሌ የሚሆነውን የኢትዮጵያን ባሕል፣ ቋንቋና ታሪክ ለልጆቻቸው ሲያስተምሩ የሚያሳይ ድንቅ ስራዎቻቸው በቪዲዮ ለሕዝቡ ቀርቧል።

ለጥቆም ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ” የኦሮሞ እና የአማራ እውነተኛ የዘር ምንጭ” መጽሐፍ እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ልብን በሚመስጥ ምሁራዊ ትንተና አቅርበዋል። ከነዚህም መካከል ኢትዮጵያ የሚለውን ስም መቼ እንደተሰጠን፤ ኢትዮጵያ ማለት ምን ማለት አንደሆነና አገራችን ለምን ኢትዮጵያ እንደተባለች፤ በታሪክ የአማራ ገዢ መደብ የሚባል እንዳልነበረ፤ የኦሮሞውም ሆን የአማራው የሁሉም ኢትዮጵያዊ  ዘር ከአንድ እናትና አባት እንደተገኘን፤ምኒሊክ በጦርነት ላይ ጡት ቆርጠዋል የተባለው ምንም ዓይነት መረጃም ሆን ማስረጃ የሌለው መሰረተቢስ ወሬ እንደሆነ፤ ምኒሊክ በባህሪያቸው ተበቃይ እንዳልነበሩ እንደውም በጣም እሩህሩህና ይቅር ባይ ከመሆናቸውም በላይ ጥሩ ክርስቲያን እንደነበሩ፤ ሕወሃት ከፋፍሎ መግዛት እንደቻለው ሁሉ ይህንን ዕድሜውን ለማራዘምም እንዲመቸው እንደነ ሙክታር ከድርና ተስፋዬ ገብረአብ ያሉትን እና የመሳሰሉትን  እንደመሳሪያ ተጠቅሞ ሁለቱን ታላላቅ ሕዝቦች ኦሮሞና አማራውን በማያባራ ቂም እና ጥላቻ ውስጥ ለማቆየት ሲባል በብዙ ሚሊዮን ብር “የአኖሌን” ሃውልት እንዳቆመ፣ ለዚህ የጥላቻ ሃውልት የፈሰሰው በርካታ ሚሊዮን ብር ብዙ ትምህርት ቤቶችን፣ የጤና ጣቢያዎችንና የመሳሰሉትን እንደሚሰራ ከበቂ መረጃ ጋር አብራርትዋል።

ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ቀደም ሲል ሰለዚህ መጽሐፋቸው እዚህ ላስ ቬጋስ ውስጥ በሚገኝውና “ሕሊና ራዲዮ የኢትዮጵያውያን ድምጽ” በተሰኘው የዘወትር እሁድ የራዲዮ መርሃግብር ላይ ቀርበው ለከተማው ነዋሪ ያስረዱ ከመሆናቸውም  ባሻገር በዕለቱ ከታደመው ሕዝብ መካከል ከ፶ (50 )በላይ የሚሆነው ሕዝብ በቅድሚያ መጽሐፉን በማስመጣት አንብቦት ስለነበር ሕዝባዊ ውይይቱ የተሟላ ከመሆኑም በላይ የሞቀ፣ የደመቀና የሚጣፍጥ ነበር። ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳም ለተጠየቁት ጠንካራና ፈታኝ ጥያቄዎች አጥጋቢ የሆነ መልስ በመስጠት ታዳሚውን በማስደሰታቸው ውይይቱ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው በጭብጨባ የተሞላ ነበር።

በዕለቱም ከተሰጡት አስተያየቶች መካከል ይህ መጽሃፍ ከ፳፭ (25) ዓመታት በፊት ተጽፎ ቢሆን ኖሮ አገራችንና ሕዝባችን እዚህ ሁሉ መከራ ውስጥ ባልወደቅን ነበር በማለት ከእንባና ከለቅሶ ጋር በቁጭት የተሰጠው አስተያየት ውይይቱ በታዳሚው አዕምሮ ተቀርጾ እንዲኖር ያደረግ አጋጣሚ ነበር።

ሌላው ደግሞ ባለፉት ፳፭ (25) ዓመታት ውስጥ በአገር ውስጥም ሆን በስደት የሚገኙት የኦሮሞ ወጣቶች የተማሩት የቀኝ ገዥዎች ቋንቋ  መጻፊያ በሆነው በላቲን ፊደል ስለሆነና ኢሕአዴግና መሰሎቹ ከዘረኝነት በከፋና አጥፊ በሆነ መርዝ ቁጥሩ ቀላል የማይባለውን ሕዝብ ስለመረዙ፤ (ምንም እንኳ ከመጽሃፉ ዓላማ ውጭ ቢሆንም ) ለማስተማር እስከ ጠቀመ ድረስ እንደዚሁም የኦሮሞ ወጣትም የተማረው በዚሁ በላቲን ፊደል (በቁቤ)ስለሆነ ይህ የኦሮሞ እና የአማራ እውነተኛ የዘር ምንጭ መጽሃፍ በኦሮምኛ ማለትም በላቲን ፊደል( በቁቤ)ተተርጉሞ በአገር ቤትም ሆነ በውጭ ቢሰራጭ ብዙ ወጣቶችንና ጎልማሶችን ለመረዛቸው የዘረኝነት መርዝ ማርከሻና ማደሻ ሊሆን ይችላል ተብሎ ስለታመነበት መጽሐፉ  እነዲተረጎም ፕሮፌሰር ፍቅሬን ሕዝቡ በአጽንዎት ጠይቋል። ፕሮፌሰር ፍቅሬም ሙሉ ፈቃደኝነታቸውን በመግለጽ ” ትርጉሙ ቀደም ብሎ በአገር ቤት ተጀምሮ እንደነበረና ተርጓሚው በዚሁ ምክንያት ለእስር በመዳረጉ እንደተቋረጠ ሆናም በሌላ ብቁ ሰው ሊተረጎም በዝግጅት ላይ እንደሆነ ” አስረድተዋል።

ከዚህ ጋር በተያያዘም ከ፪፻ (200 )ዓመታት በፊት አባ ገመቺስ (አናትሞስ ነሲብ ) የተባሉ አባት አስቴር ጋኖ ከምትባል እንስት ጋር መጽሐፍ ቅዱስን በኦሮምኛ ነገር ግን  በግዕዝ ፊደል ተርጉመው ሕዝቡ ይገለገሉበት እንደነበረ፣ የጥንቱ በሬሳ ጋዜጣ እየታተመ በሰፊው ይሰራጭ የነበረው በዚሁ በኦሮምኛ  ቋንቋ ነገር ግን በሳብ ወይም በግእዝ ፈደል እንደነበር፤ እንዲሁም በመሰረተ ትምህርት እስከ ፭ኛ (5ኛ  ) ክፍል ድረስ የትምህርት መማርያ (ካሪኩለም) ተቀርጾለት በኦሮምኛ ቋንቋ ነገር ግን በሳብ ወይም በግእዝ ፈደል ተጽፎ ይሰራበት እንደነበር ፤ የመሬት ላራሹ አዋጅ  በዚሁ በኦሮምኛ የሳባ ፊደል ወይም በግእዝ ተተርጉሞ በተቀላጠፈ ሁኔታ ያለምንም ችግር ይሰራበት  እንደነበር በፕሮፌሰር ፍቅሬ ማብራሪያ ተሰጥቷል።  “በአንጻሩ ከቁቤ ወይም ከላቲን ፊደል ይልቅ የሳባ ወይም የግእዝ ፊደል ጊዜን እና ገንዘብን ይቆጥባል ለምሳሌ በኦሮምኛ ነገር ግን በሳባ ወይም በግእዝ ፊደል ፪ (2) ገጽ የተጻፈን ፅሑፍ በኦሮምኛ ቁቤ ሲጻፍ ፮ (6)ገጽ ይፈጃል በዚያ ላይ ለአናባቢ (ፕሮናውንሴሽን )የግእዙ ኦሮምኛ ሲባዛ ይቀላል” ሲሉ ፕሮፌሰር ፍቅሬ አስረድተዋል።አክለውም የሳባ ወይም የግእዝ ፊደል የአማራ፣ የኦሮሞ፣ የትግሬ ወይም የማንም ፊደል አይደለም የኢትዮጵያ ፊደል ነው። ይህን ፊደል ኤርትራ እንኳ ስትገነጠል ይዛው ነው የሄደችው ለምን ጥቅሙን ስላወቀች ከዚህም አልፎ ፈረንጆቹ በዩኒቭርስቲ ደርጃ የግእዝ ቋንቋን ማጥናት ከጀመሩ ቆይተዋል በዚህ ብቸኛና አፍሪካዊ በሆነ ቋንቋ ልንኮራበትና ልንማረው ይገባል እንጂ እንደ ጠላት ልናየው አይገባም ሲሉ ገፋ አድርገው ምክር አዘል ትምህርት የሰጡበት ሲሆን ይኸው የኦሮሞ እና “የአማራ እውነተኛ የዘር ምንጭ ያሉትንም መጽሐፋቸውን እንደጥንት አባቶቻቸን በኦሮምኛ ቋንቋ ነገር ግን በሳባ ወይም በግእዝ ፊደል ይታተማል ሲሉ አብስረዋል።

በመጨረሻም ፕሮፌሰር ፍቅሬን ይዘን በመላው ዓለም ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር በመተባበርና በመቀናጀት ከፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ያገኘነውን እውቀት በማስፋትና በማዳበር ወደ ተግባር ለመቀየር ይቻል ዘንድ መጽሐፉም የያዘውን ፍቱን መድሃኒት ለሁሉም ይዳረስ ዘንድ ፯ (7) አባላት ያሉት ቻፕተር በማቋቋምና በመጽሐፋቸው ላይ የክብር ፊርማቸውን በመፈረም ከ፫ (3) ሰዓታት በላይ የወሰደው ውይይት እጅግ ባማረ እና በደመቀ ሁኔታ ተጠናቋል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.