ህወሃትና ብአዴን ደኢህዴንን እየተቀራመቱ ነው -ገለታ ጋሞ

ብአዴን ኃይለማሪያም ደሳለኝን በመያዝ፣ ህወሃት ደግሞ ሽፈራው ሽጉጤን በመያዝ የደቡቡ ድጋፍ ለማግኘት ግብግብ ውስጥ ገብተዋል።

ሽፈራው ሽጉጤ በሙስናና በወንጀል ኔትዎርክ የያዛቸውና ወላይታዎችን በጠላትነት የሚያዩ የሲዳማ ተወላጆች በስተቀር በደቡብ ውስጥ ብዙም ድጋፍ የለውም። ኃይለማሪያማ ደሳለኝ ግን በፕሮቴስታንት ቤተክርስቲያኗና በቀጥታ በራሱ በፈጠረው ኔትዎርክ አማካኝነት ደኢህዴን ውስጥ የተሻለ ድጋፍ አለው።

ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ዓምና ያተረፈው የኢትዮጵያ መርከብና ትራንስፖርት ድርጅት ስራ አስኪያጁ ሲነሳ ሃይለማሪያማ ደሳለኝ የጋሞ ተወላጅ በሆነውና ቀድሞ የንግድ ሚኒስቴር በነበረው ያዕቆብ ያላ ቢተካውም ህወሃት በሽፈርዋ ሽጉጤ አምካኝነት ወድያውኑ አስነስቶታል።
በትግራይ ተወላጆች የተደረገው የልማት ባንክ ዘረፋን ለማስቆም ኃይለማሪያም ደሳለኝ ያደረገውን ሙከራም ህወሃት ሽፈራው ሽጉጤን በመጠቀም ለጊዜውም ቢሆን አክሽፏል።

ሰሞኑን ገዱ አንዳርጋቸው፣ ደመቀ መኮንንና ኃይለማሪያም ደሳለኝ የወልዲያ ስታዲዮምን ለመመረቅ ሰበብ ቆቦን መጎብኘታቸውና፣ በአማራ ክልል ውስጥ ያለው የራያ አካባቢ በተሻለ ሲለማ በትግራይ በግድ የተጠቃለለው የራያ አካባቢ በኢኮኖሚ ወድቀቅን አጉልቶ ያሳየ ሁኔታ በምሆኑ፣ ይህንን ጉብኝት ህወሃቶችና ደጋፊዎቻቸው በትግራይ ላይ እንደተቃጣ አድርገው በማናፈስ ላይ ናቸው።

የህወሃቱ ንዋይ ገብረአብ ኃይለማሪያምን ይቆጣጠርበት ከነበረበት ቦታ በብአዴን ድጋፍ መባረሩ ሃይለማሪያም ኃይል እያገኘ መሆኑንም አመልካች ነው።

ምንም እንኳን የጦር ሃይሉና የስለላ መዋቅሩ በህወሃት ቁጥጥር ውስጥ መሆን ለሃይለማሪያአም ደሳለኝ አደጋ ቢሆንም የነብር ጅራት ከያዙ ነውና ሃይለማሪያምም ሆነ እን ደጉ አንዳርጋቸው ወደ ኋላ መመለስ ወደማይችሉበት ሁኔታ ላይ ደርሰዋል።
ጀነራሎቹ በሃይለማሪያም ደሳለኝ ላይ ኩዴታ እስካላካሄዱ ድረስ ሃይለማሪያም ደሳለኝ ምናልባትም በያዘው መንገድ ሳይቀጥል አይቀርም። የሚቀጥለው ታርጌቱም ደብረጽዮን ሳይሆን እንደማይቀር ነው። ደብረጽዮን ሃገሪቱን የግር ብረት አስሮ ያለ ሰው ነው። የዚህ ሰው ከቦታው መነሳት ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ለውጥ በአገሪቱ ያመጣል የሚል ግምት አለ። ከቻይኖች ጋር ባለው የጠበቀ ግንኙነት ማንሳቱ አስቸጋሪ ሊሆን ቢችልም ህወሃት እንዳይንሰራራ ተደርጎ በኢሃድግ ውስጥ መመታት የሚታወቀው ኃይለማሪያም ደብረጽዮንን ማንሳት ከቻለ ነው።

ከጀነራሎቹ የኩዴታ አደጋ ቢኖርም የኢሃድግ ምክር ቤትን በበላይነት እስካልተቆጣጠሩ ዓለም አቀፍ ውግዘትና መገለልን ስለሚያስከትልባቸው አይሞክሩት ይሆናል።

የኃይለማሪያም ደሳለኝ በኢሃድግ ውስጥ ተጽዕኖ ማየል የህዝባዊው ተቃውሞው ቀጥተኛ ውጤት ነው። የህወሃትም በሽፈርው ሽጉጤ አማካኝነት ተቃዋሚዎችን የመቅረብ ሙከራ የዚሁ ሽኩቻ አካል ሲነው።

ተቃዋሚዎች ኢሃድግ ውስጥ አሁን የተፈጠረውን ቅራኔ በመጠቀም ህወሃትን ከጨዋታው ውጪ ለማድረግ መስራት ይችላሉ። የህወሃት ተጽዕኖ ፈጣሪነት ከተዳከመ ብቻ ነው ሰላማዊ ሽግግር ሊታለም የሚችለው። ያ ካልሆነ የርስ በርስ ጦርነት አደጋው በአገሪቱ ውስጥ እንደተደገነ ነው።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.