እንኳን ለከተራ ክብረ በዓል በሰላም እና በጤና አደረሳችሁ! – ለመሆኑ… ከተራ ምን ማለት ነው? – ኤድዋርዶ በይሮኖ

“ከተራ” በአጼ ይኩኑ አምላክ መንግስት በ12ኛው ክፍለ ዘመን የተጀመረው እና በአጼ ገብረ መስቀል መንግስት በ15ኛው ክፍለ ዘመን በአደባባይ እንዲከበር የታወጀው የጥምቀት ክብረ በዓል ከመከበሩ አንድ ቀን ቀደም ብሎ የሚከበር ራሱን የቻለ ሰፋ ያለ እምነታዊ ታሪክ ያለው በጥንታዊት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ምዕመናን በደመቀ ሁኔታ የሚከበር ክብረ በዓል ነው ።

“ ከተራ” ከተረ ከሚለው የግዕዝ ቃል የተወረሰ ሲሆን አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ “ከተረ” ፣ ወሃ ገደበ፣ ውሃ አገደ፣ ውሃ ዘጋ በማለት ወደ አማርኛ ተርጉመውታል ።

ታዲያ በየአመቱ ጥር 10 የጥምቀት ዋዜማ ዕለት ጀምበር ከመጥለቋ በፊት ቀደም ብለው የቤት ክህነት አገልጋዮች ተሰባስበው ጊዜዊ ውሃ ማጠራቀሚያ ገንዳ በመቆፈር ወይም በአቅራቢያቸው ያለውን ጅረት በመገደብ ለሚቀጥለው ጥር 11 የጥምቀትን ክብረ በዓል ለማክበር የሚሰበሰቡት ምዕመናን እንዲጠመቁ የመጠመቂያ ስፋራ የሚያዘጋጁበት ዕለት ነው።

በተጨማሪ በአቅራቢያ የሚገኙት ቤተክርስቲያናት ተሰብስበው ከዚሁ ከተቆፈረው ገንዳ ወይም ከተገደበው ጅረት አጠገብ ዳስ ወይም ድንኳን ጥለው ታቦቶቻቸውን ያሳድራሉ።

ቅዱሳን አባቶቻችንም በየአመቱ በከተራ ዕለት በዚሁ በአዘጋጁት የመጠመቂያ ስፋራ አጠገብ በጣሉት ጊዚያዊ ዳስ ወይም ድንኳን ውስጥ አንድ ላይ ተሰባስበው እየጸለዩ በማደር እግዚአብሔር ለነብዩ ሙሴ “የታቦት መኖር የእኔ ከአናንተ ጋር የመኖሬ ምልክት ነው” ብሎ የገለጸለትን ቃል ይፈጽማሉ።

የተባረከ ዕለተ ከተራ (የጥምቀት ዋዜማ) ይሁንላችሁ።

Eduardo Byrono

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.