ከጥር 5 እስከ 6 ቀን 2009 ዓ፡ም (ጃንዋሪ 13-14) በዋሽንግተን ዲሲ የተካሄደው ሁሉን አቀፍ የምክክር ጉባኤ በተሳካ ሁኔታ ተጠናቀቀ!

የአገር አድን የቀውጢ ጊዜ ግብረ ኃይል ተቋቋመ፤ ሁነኛ የአንድነት ኃይሎች አማራጭ በአጭር ጊዜ የማውጣት ሂደት ላይ

ስምምነት ተደረሰ!

 

አዘጋጅ የሆኑት ሶስት ድርጅቶች (ሸንጎ፣ የሽግግር ምክር ቤትና የወጣቶች ንቅናቄ) ቀደም ሲል ሲያደርጉት የነበረውን ግንኙነት በማደስ ላለፉት 7 ወራት ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር ተከታታይ የሁለትዮሽ፤ የወል ግንኙነቶችን እና ጥረቶችን በማድረግ ከቆዩ በኋላ፤ በአገራችን ጉዳይ ላይ ባለ ድርሻ ለሆኑ ለሁሉም የፖለቲካና የሲቪክ ድርጅቶች ኦፊሽያል ጥሪ በማድረግ እንደሚገኙ በደብዳቤ ካረጋገጡት 10 ድርጅቶች መካከል 9ኙ በጥር 5 እና 6 ቀን 2009 ዓ፡ም  (ጃንዋሪ 13 – 14 ቀን 2017) ተገኝተው የተሳካ ጉባዔ በዋሺንግተን ዲሲ አካሂደዋል፡፡

 

ይህ ጉባዔ የተከፈተው በስደት የሚገኘው ሕጋዊው ሲኖዶስ ተወካይና የዋሽንግተን ዲሲና የአካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ  ብፁዕ አቡነ ሣሙኤል በሰጡት ቡራኬና ፀሎት ሲሆን፤ በተጨማሪም ጉባዔው ለአገርና ለሕዝብ የሚበጅ አንድ ውጤት ላይ እንዲደርስ ልባዊ ተማጽኖ አቅርበዋል፡፡

 

በጉባዔው የመጀመሪያ ቀን የተገኙት 9ኙ ድርጅቶች በተመደበላቸው ሰዓት የአንድነት ኃይሉን ትብብርና ሁነኛ የአማራጭ ኃይል የማውጣት ሂደት ላይ ያላቸውን ራዕይ አቅርበዋል፡፡ እንዲሁም የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን የሆኑት ፕሮፌሰር ጌታቸው መታፈሪያና ዶክተር ተድላ ወልደ ዮሐንስ በተያያዥ አርዕስቶች ዙሪያ ጥናታዊ ፅሁፍ አቅርበዋል፡፡ ከላይ የተዘረዘሩትን የመክፈቻ ቀን ዝግጅቶች በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች በቀጥታ ስርጭት እንዲከታተሉት ተደርጓል፡፡

 

በጉባዔው ሁለተኛ ቀን የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር ተወካይ ተገኝተው የጉባዔው ተሳታፊ ድርጅቶች ተባብሮ የሚያሰራቸው ውሳኔ ሃሳብ ላይ በመድረስ ጉባዔው ውጤታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ያላቸውን በጎ ምኞት በመግለጽ፤ ለወደፊት ድርጅታቸው አብሮ ለመስራት ያላቸውን ፍላጎት አረጋግጠዋል፡፡ በዕለቱም በ9ኙ ድርጅቶች መካከል ዝግ የሆነ ጥልቅ ውይይት ከተካሄደ በኋላ ከዚህ በታች በተዘረዘሩት ዋና ዋና ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ በመጨረሻም ሁለት ቀን የፈጀው የምክክር ጉባዔ ከተለያዩ ጋዜጠኞችና የመገናኛ ብዙኃን አባላት ጋር በተደረገ ጋዜጣዊ መግለጫ ተጠናቋል፡፡

 

የጉባዔው ዝርዝር ሪፖርትና የቪዲዮ ቅንብር በቅርብ ቀናት ለሁሉም ይፋ እንደምናደርግ ልንገልጽ እንወዳለን፡፡

 

 

 

 

 

የጉባዔው ዋና ዋና የስምምነት ነጥቦች

 

 1. ከጥር 5-6 ቀን 2009ዓም በዋሽንግተን ዲሲ የተሰባሰቡ የተለያዩ የአንድነት ኃይሎች የአገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ በዝርዝርና በጥልቀት በመመርመር የጋራ ግንዛቤ ላይ ተደርሷል። አገዛዙ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚያደርሰውን የግድያ፣ የአፈና፣ የመፈናቀልና የሽብር ዘመቻ በአጽንኦት እየኮነነ፤ እየተካሄደ ያለውን ሕዝባዊ እምቢተኛነትና ተጋድሎ አገር አቀፍ አድማሱን አስፍቶ እንዲቀጥል የሚቻለንን ሁሉ ለማድረግ ስምምነት ላይ ተደርሷል።

 

 1. ከዚህ የጋራ ግንዛቤ በመነሳትና የኢትዮጵያ ችግር በኢትዮጵያውያን ብቻ መፈታት እንዳለበት በማመን ከዚህ በታች በተዘረዘሩት መሰረታዊ የእምነት መርሆዎች ላይም ስምምነት ላይ ተደርሷል።

 

 • በኢትዮጵያ ግዛታዊ አንድነት፤ የሕዝቡ የሥልጣን ባለቤትነትና ሉዑላዊነት እንዲሁም በሃገሪቱ የግዛት አንድነት ላይ ግልጽና የማያወላውል ዕምነት መኖር፤
 • የማንኛውም የኢትዮጵያዊ ግለሰብ ዲሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶችን ማክበር፤
 • በድርጅቶች ውስጥና በምንሰባሰብበት የጋራ ማዕቀፍ ዲሞክራሲያዊ ግንኙነቶችንና አሰራሮችን ለማስፈን መስራት፤
 • በኢትዮጵያ ውስጥ የህግ የበላይነት እንዲኖር መታገል፤
 • በኢትዮጵያ ህዝብ መካከል ምንም ዓይነት አድሏዊነት እንዳይኖር፤ ሁሉም በሕግ ፊት እኩል ዜጎች መሆናቸውንና ማንም ከህግ በላይ ያለመሆኑን ማመንና በተግባር ማስረገጥ፤
 • የህወሓት/ኢህአዲግ ስርዓት ዘረኝነት የተጠናወተው፣ ግፈኛ፤ አፋኝና መሰሪ ስርዓት በመሆኑ መለወጥና በዲሞክራሲያዊ አስተዳደር መተካት እንዳለበት ማመን
 • እውነተኛና ዘላቂ የሆነ የዲሞክራሲያዊ ስርአት ለመገንባት አግላይ ያልሆነ፤ ሁሉን አቀፍ የሽግግር ሂደት እንዲኖር ከባለድርሻ አካሎች ጋር ቅድመ-ሁኔታዎችን ለማመቻቸት፤ በጋራ መስራት ናቸው።

 

 1. ለአገራችን መሰረታዊና ወቅታዊ ውስብስብ ችግሮች በጋራ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ የመፍትሔ ህሳቦች ላይ ተደርሷል።

 

 1. ከላይ የተጠቀሱት የጋራ ግንዛቤዎችን መሰረት በማድረግ ሁለት የተግባር አካላት እንዲመሰረቱ ተወስኗል። በዚህም መሰረት፤

 

ሀ. በአሁኑ ወቅት በአገራችን ሁለንተናዊ መብቶችን ለማስከበር ለሚደረገው ሕዝባዊ ትግል በሁሉም ዘርፍ ትብብርና እርዳታ ለማድረግ ይቻል ዘንድ አንድ ኃላፊነቱን ወስዶ የሚሠራ ሀገር አድን የቀውጢ ጊዜ ግብረ ኃይል ተቋቁሟል።

 

ለ. የአገሪቱን ውስብስብ ችግሮች ባገናዘበ መልኩ የተፈጠረውን የሁነኛ ብሔራዊ አማራጭ ክፍተት ለመድፈን ሕዝባችን የሕገ መንግስታዊ   ዴሞክራሲያዊ ስርአት ባለቤት ለመሆን የሚያደርገውን ትግል ለአዎንታዊ ውጤት ለማብቃት መሰረቱን ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ላይ የጣለ አዲስ የኃይል አሰላለፍ እንዲፈጠር ስምምነት ላይ ተደርሷል። ይህንን ተልእኮ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ ለማድረግ ይቻል ዘንድ ኃላፊነት የተሰጠው አንድ ልዩ ኮሚቴ ተሰይሟል።

 

 

በሁለት ቀን ጉባኤው በመሳተፍ ስምምነት ላይ የደርሱት ድርጅቶች ዝርዝር፤

 

1.የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ (ሸንጎ)

2.የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሽግግር ምክር ቤት (ሽግግር ም/ቤት)

3.የኢትዮጵያ ወጣቶች ብሄራዊ ንቅናቄ

4.ሞረሽ ወገኔ የአማራ ድርጅት

5.የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ኅብረት ህብረሕዝብ

6.ዳግማዊ አርበኞች ንቅናቄ

7.የአዲስቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ

8.ቱሳ የኢትዮጵያ ትንሳኤ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት

9.የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ሰላማዊ ንቅናቄ ደጋፊዎች ህብረት

 

ድል ለ ኢትዮጵያ ህዝብ!

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.