ሕወሐት ደብረፂዮን ገ/ሚካኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ለማድረግ አቅዷል (ከኢየሩሳሌም አርአያ)

debretsionየጠቅላይ ሚኒስትር ስልጣን ወደ ሕወሐት ለመመለስ የፓርቲው ቁልፍ አመራሮች በምስጢር ሲመክሩ መስንበታቸውን የቅርብ ምንጮች አስታወቁ። በአቶ ደብረፂዮን ገ/ሚካኤል፣ አባይ ፀሐዬ፣ ጌታቸው አሰፋ፣ ጄ/ል ሳሞራ የኑስ፣ ፀጋይ በርሔ፣ አርከበ እቁባይና ስብሃት ነጋ የሚመራው የሕወሐት ከፍተኛ አመራሮች ከዚህ ቀደም ሲካሂዱት በነበረውና ህወሀት የጠ/ሚ/ ርነት ስልጣን መልሶ መያዝ ይኖርበታል፣ የሚለውን ምክክር ከዳር ለማድረስ አቋም መያዘያቸውን ያስታወቁት ምንጮቹ በተለይ በቅርቡ የተካሄደው የአራቱ ፓርቲዎች ጉባኤ ላይ በብአዴንና ኦህዴድ በኩል ቅሬታና ተቃውሞ እየበረታ በመምጣቱ የሕወሐት አመራሮች ስልጣኑን በእጃቸው ለማስገባት ቆርጠው መነሳታቸውን አስረድተዋል።

በብአዴን በኩል የአቶ በረከት ስሞን ከስልጣን መገፋት በደጋፊዎችቻቸውና አመራሩ በኩል ቅሬታ መፍጠሩን የጠቆሙት ምንጮቹ በረከት ስሞን የጠ/ሚ/ር ሃ/ማርያም አማካሪ ተብለው ቢሾሙም ነገር ግን በጠ/ሚ/ር ፅ/ቤት ቢሮ እንዳልተሰጣቸውና የተሰጣቸው ካዛንቺስ አካባቢ የሚገኘው የቀድሞ የደህንነት ቢሮ መሆኑን ምንጮቹ ገልፀው በዚህ ቢሮ ኩማ ደመቅሳ እንደሚገኙና በጠ/ሚ/ር ፅ/ቤት አዲስ ቢሮ ተገንብቶ ይሰጣችኋል የተባለው ተግባራዊ እንዳልሆነ አያይዘው አስረድተዋል።

በጠ/ሚ/ር ፅ/ቤት ቢሮ የተሰጣቸውና ከአቶ ሃ/ማርያም እያንዳንዷ እንቅስቃሴ ያልተለዩት አርከበ እቁባይ፣ አባይ ፀሐዬና ፀጋይ በርሄ ሲጠቀሱ በም/ጠ/ሚ/ር ቦታ ደብረፂዮን መኖራቸውን ምንጮቹ አመልክተዋል። ለሕወሐት አመራሮች ሌላው ራስ ምታት የሆነባቸው የኦህዴድ ፓርቲ ከሕወሐት እኩል መገዳደር እያሳየ መምጣቱ ነው ያሉት ምንጮቹ በተለይ ከአቶ መለስ ሞት በኋላ ኦህዴድ የተለያዩ የስልጣን ጥያቄዎች በማንሳት ድፍረት እያሳየ መጥቷል ብለዋል።

ሕወሐት የጠ/ሚ/ርነት ስልጣኑን መቆጣጠር የፈለገበት አንዱ ምክንያት ይህ መሆኑን ምንጮቹ አልሸሸጉም። በኦህዴድ በኩል የጠ/ሚ/ር ስልጣን ለኦሮሞ ይገባል በሚል ከዚህ ቀደም የነበረው የሕወሀት ስልጣንን አንሰራፍቶ የመያዝ አካሄድ መገታት አለበት የሚል አቋም እንደተያዘ ያስረዱት ምንጮቹ በተለይ የህወሀት አመራር የኦህዴድ አካሄድ እንዳልተዋጠለትና ከዚህ ቀደም ማን ጠ/ሚ/ር ስልጣን ይያዝ የሚለው የህወሀት ምክክር በእንጥልጥል ቆይቶ በቅርቡ ግን ዶ/ር ደብረፂዮን ገ/ሚካኤል ስልጣኑን መያዝ አለበት የሚል ውሳኔ ላይ መድረሱን ምንጮቹ አስገንዝበዋል። የደብረፂዮን ወደ ጠ/ሚ/ር ስልጣን የማምጣት እቅድ በተመለከተ አርከበ እቁባይ ተቃውሞ አሰምተው መከራከራቸውንና በመጨረሻ ግን ኦህዴድና ብአዴን ለመጨፍለቅ ሲባል አርከበ መቀበላቸውን ምንጮቹ አመልክተዋል። የህወሀት አመራሮች ከስምምነት የደረሱበትን ጉዳይ ከቀጣዩ ምርጫ በኋላ ጠ/ሚ/ር አቶ ሃ/ማርያም ደሳለኝን ከብቃት ማነስ ጋር በማያያዝ ከስልጣን ለማውረድና በምትካቸው የጠ/ሚ/ርነቱን ቦታ ለደብረፂዮን ለመስጠት መወሰናቸውን ምንጮቹ አጋልጠዋል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.