ብትፋቀሩ ይሻላል ጎሳ እየለያችሁ ከምትጣሉ – እቴጌ ጣይቱ

#ግርማ_ካሳ

አቻሜለህ ታምሩ የሚከተለውን ለጥፎ አነበብኩ። ምስጋንዬን ለዚህ ወጣት አክቲቪስት። ከዚህ በፊት አንብቤ የማላውቀው መነበብ ያለበት የእትጌ ጣይቱ እጹብ ድንቅ ግሩም ደብዳቤ ። እቴጌ ጣይቱ ከአንድ መቶ አመት በፊት የነበሩ ታላቅ ሴት ነበሩ። ከየጁ ኦሮሞ ግንድ ናቸው። እንግዲህ አስቡት ያኔ የነበሩ አባቶቻችን እና እናቶቻችን ምን ያህል የበሰሉና ፣ የሰለጠኑ እንደነበሩ።

“እናንተ ብትስማሙ እርስ በርሳችሁ ብትፋቀሩ አንድነትችሁን ብታፀኑ ይሻላል እንጂ ትግሬ የብቻ ነው፣ ሸዋ የብቻ ነው፣ ቤገምድር ጎጃም የብቻ ነው እያላችሁ ጎሣ እየለያችሁ ብትጣሉ ምን ትረባላችሁ” ሲሉ ነበር እቴጌይቱ የጻፊት።

የአሁኖቹ ዘረኛ መሪዎች የ እቴጌ ጣይቱ አንድ አሥረኛ እንኳን ብስለት ቢኖራቸው ኖሮ አገር አሁን ያለችበት ደረጃ አትደርስም ነበር።

የእቴጌ ደብዳቤ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ይነበባል፤
__________________
የራስጌ ማኅተም፡ ዝማኅተም ዘእቴጌ ጣይቱ ብርሃን ዘኢትዮጵያ የተላከ ከእቴጌ ጣይቱ ብርሃን ዘኢትዮጵያ፤ ይድረስ ከማህበረ ዴር ሥልጣን ወደብረ ገነት ዘኢየሩሳሌም፣ እንዴት ሰንብታችኋል፡ እኔ እግዚአብሔር ይመስገን ደህና ነኝ።

እናንተ ብትስማሙ እርስ በርሳችሁ ብትፋቀሩ አንድነትችሁን ብታፀኑ ይሻላል እንጂ ትግሬ የብቻ ነው፣ ሸዋ የብቻ ነው፣ ቤገምድር ጎጃም የብቻ ነው እያላችሁ ጎሣ እየለያችሁ ብትጣሉ ምን ትረባላችሁ።

እኛስ በኢየሩሳሌም ነገር ይህንን ያህል መድከማችን ያነን ያህል ብር ባንክ አግብተን የዚያን ወለድና ከቤቱ የሚወጣውን ክራይ መስጠታችን እንዳትቸገሩ የሰው ፊት እንዳታዩ ያነን እየበላችሁ ለኛም የጌታችን ደም ከፈሰሰበት ላይ ዳዊት እንድትደግሙልን እንድታዝኑልን እናንተም ፩ነታችሁ እንዲጸና ብለን ነው እንጂ ገንዘቡ ተርፎ ባገራችን በኢትዮጵያ ለምንሰጠው ሰው አጥተን አይደለም።
አሁንም ስለ እግዚአብሔር ብላችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተፋቀሩ፡ ለኛም ዳዊት ድገሙልን እዘኑልኝ። ሳትቸገሩ እንዴት የድፍን አውሮፓ መሳቂያ ትሆናላችሁ። አሁንም ይኸው እማሆይ ወለተ ተክሌ መቃብሬ ከዚያው ይሁን ብላ መጥታለችና አደራችሁን ምኑም በምኑም ነገር እንዳታስቀይሟት። እንግዲህ እሷ እንዲህ አደረጉኝ ብላ የላከችብኝ እንደሆነ እናንተንም እጣላችኋለሁ እኔንም እንዳታስቀይሙኝ።
ሰኔ ፳፱ [29] ቀን ፲፱፻ [1900] ዓመት አዲስ አበባ ከተማ ተጻፈ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.