የጅቡቲ አፋሮች ትግል እንዴት ከሸፈ? ክፍል 4 (ከይገርማል)

የኢትዮጵያውያን ዕጣ ፈንታ በጅቡቲ በረሀ

የአፋር በረሀ የኢትዮጵያውያን የቅጣት ቦታ ነው ቢባል ሀሰት የሚል ይኖር ይሆን! በተለያየ ምክንያት በሀገሩ ለመኖር ያልቻለው ኢትዮጵያዊ ወደውጪ ከሚወጣባቸው በሮች ውስጥ አንዱ ጅቡቲ ነው። አብዛኛወቹ ወደአረብ ሀገር ለመሻገር ፍላጎት ያላቸው ወገኖች የጅቡቲን መስመር ይመርጡታል። ይሁን እንጅ እንዳሰቡት ቀይባህርን ተሻግረው መሄድ ይቅርና ጅቡቲና ታጁራ ሳይደርሱ በአፋሮች ተይዘው በበረሀ ቀልጠው የሚቀሩ ብዙ ናቸው። አንዲት የአዲስ አበባ ወጣት በያዛት አፋር በግዳጅ ሚስት ሆና ልጆች ወልዳ ፍየልና ግመል ጠባቂ ሆና እንደቀረች ሰምቻለሁ። የሀበሻን ሴት በግዳጅ ከቤት ማስቀመጥ እንደነውር አይታይም። ለነገሩ ሀበሾችን እንደሰው የሚቆጥሩም አይመስለኝም። የሀበሻ ሴቶች በአፋሮች ዘንድ የክብር ቦታ የላቸውም። ለወሲባዊ ፍላጎት ማርኪያ የሚያገለግሉ መብትም ክብርም የሌላቸው ተደርገው ነው የሚታዩት። እምባቸው፣ ስቃያቸው ምንም ማለት አይደለም። ክብር ተሰጥቷቸው የአፋር ወንዶችን ያገቡ ቢኖሩም ጋብቻውን የፈጸሙት ግን በፍላጎታቸው ላይሆን ይችላል። አልፎ አልፎ የአፋሮችን ባህልና ደካማ ጎናቸውን ጠንቅቀው የሚያውቁ ብልህ ሴቶች የአፋር ወንዶችን ደባብሰው ኮማ ውስጥ ካስገቧቸው በኋላ የበላይነቱን ይዘው ለሚፈልጉት አላማ እንደመሳሪያ ይጠቀሙባቸዋል።
በጅቡቲ ቆይታየ የኢትዮጵያውያንን መብት ለማስከበር ብዙ ታግያለሁ። በዚህ ጥረቴ ሁለት ሴት ኢትዮጵያውያንን ነጻ ለማውጣት ችያለሁ። ከጎናቸው ቆሜ ከተከራከርሁላቸው ሰዎች መሀል አንዷ ብርቱካን ናት። እንደነገረችን ከሆነ ብርቱካን የሸዋ ሮቢት ልጅ ናት። እንደነገረችን ከሆነ የምለው ወድጀ አይደለም። ብዙ ኢትዮጵያውያን አይደለም ከሀገር ወጥተው ይቅርና በሀገራቸው ውስጥ የቦታ ለውጥ ሲያደርጉ እንኳ ስማቸውን እንደሚቀይሩ ስለማውቅ ነው። ብርቱካን ደማቅ ቀይና ደመግቡ ወይዘሮ ናት። ይህችን እህታችንን ወደጅቡቲ አሻግርሻለሁ ብሎ ይዟት የመጣው አፋር አልለቅም ብሎ እያሰቃያት ነበር። የሚረዳት ሰው ትፈልግ ኖሮ ሰዎችን አጠያይቃ ከቤቴ መጣች። የህይወት ታሪኳን ከነገረችን በኋላ በግዳጅ ከያዛት ሰው እንድታደጋት በእንባ ተማጸነችኝ። ነፍሴ ከስጋየ ካልተለየች በስተቀር የሀገሬን ልጅ እምባ ረግጨ ‘ስራሽ ያውጣሽ’ ለማለት የሚቻለኝ አልነበረም።

የአፋሩ ጎረምሳ ያለችበትን አጠያይቆ ሲመጣ ብርቱካን ቤተኛ ሆና በነጻነት ከባለቤቴ ጋር በቤት ውስጥ ጉድ ጉድ እያለች ነበር። እንደደምቡ ሰላምታ ሰጥቶን ከቤት ገብቶ ትንሽ ከተቀመጠ በኋላ “ኡጉት!” አላት፤ ተነሽ ለማለት። ሰማይ ዝቅ ምድር ከፍ ቢል ከዚህ ቤት አልወጣም ብላ እምቢ አለች። አፋሩ እንድትነሳ እየጎተታት በንዴት ይገሰላ ጀመር። ከፍላጎቷ ውጪ አስገድዶ ሊወስዳት እንደማይችል ስነግረው ይበልጥ አበደ። እሷን መጎተቱን አቁሞ ወደ እኔ እየተንደረደረ ሲመጣ ዝም ብየ ጠበቅሁት። ክርክሩ መልኩን ቀይሮ ግብግቡ በእኔና በእሱ መሀል ሆነ። ዐይኔን ሊያወጣኝ ምንም ያህል አልቀረውም። እግዚአብሔር ይስጣቸውና ጫጫታውን ሰምተው የመጡ ሰዎች በመሀል ገብተው ባያገላግሉን ኖሮ የምጎዳው እኔ እሆን ነበር።

ከጥቂት ደቂቃወች በኋላ መረጃው የደረሳቸው እነሜሪቶና የአካባቢው ሽማግሌወች ጉዳያችንን ለማየት ተሰባስበው እኔና እሱ ተጠርተን ከፊታቸው ቀረብን። ተከራካሪየ ከኢትዮጵያ ይዞ ያመጣትን ሴት ከቤቴ አስቀምጨ ልሰጠው ፈቃደኛ አለመሆኔ መረን የለቀቀ ትልቅ ወንጀል እንደሆነ በንዴት እየተወራጨ ተናገረ። ካሳ ክሶ ባስቸኳይ ይመስልኝ ሲል ደነፋ። እኔ በተራየ ይህችን የእኔ ናት የሚላትን ሴት ወደጅቡቲ አሻግርሻለሁ ብሎ አታሎ ያመጣት ተጠቂ እንደሆነች በመግለጽ አልፈልገውም ለምትለው ሰው ተላልፋ ልትሰጥ አይገባም፤ ሰው በመሆኗ የሰውነት ክብር ይሰጣት ስል መከራከሪያ አቀረብሁ። በዚህ ቢባል በዚያ እኔም ሆንሁ እሱ ከያዝነው አቋም መለሳለስ አላሳይ አልን። ሽምግልናው ካለስምምነት ከተጠናቀቀ በኋላ ከአንዴ ሁለቴ ከቤት እየመጣ ሊያባብላት ሞክሮ ነበር። ያሰበው አልሳካለት ሲል አካባቢውን ጥሎ ጠፋ። ብርቱካን ለጥቂት ወራት አብራን ከቆየች በኋላ አግብቸ ወደታጁራ ልውሰድሽ የሚል የአፋር ባል መጣላት። የመጀመሪያ ፍላጎቷም ወደታጁራ ለመሄድ ስለነበር የመጣላትን ባል እንድታገባ ፍቃድ እንድሰጣት ጠየቀችኝ። ፍቃዷን ተቀብየ በጋብቻ ውል አፈራርሚያት ወደታጁራ አቀናች።

ሌላዋ ተጠቂ ሶፊያ ትባላለች። ሶፊያ የደሴ ልጅ ናት። ወደታጁራ ለመሻገር ነበር እሷም የመጣችው። ፍተሻ ላይ አሊ በረጎይታ ይዟት ወደቤቱ ወስዶ ያስቀምጣታል። የልጅቷን ስቃይ የሰሙ ኢትዮጵያውያን ሳይሆኑ አይቀሩም የነገሩኝ። ሰተት ብየ ከአሊ በረጎይታ ቤት ሄጀ እንዲለቃት ነገርሁት። አሊ ብዙም አልተከራከረኝም። ሶፊያ እስከመጨረሻው ድረስ አብራን ቆይታ ወደኢትዮጵያ ስንመለስ ከምታውቃቸው ሰዎች ዘንድ ኤሊዳር ቀረች።

አንድ ስሟን የማላስታውሳት ሴት ነጻ አውጪ ድርጅቱን ለመቀላቀል ትምህርታቸውን አቋርጠው ከጅቡቲ በመጡ ልጆች የቡድን ጥቃት እየተፈጸመባት እንደሆነ በመስማቴ ልጆቹ ከሚኖሩበት ት/ቤት ከነበረው አንድ ክፍል ሄጀ አነጋገርኋት። ልጆቹ የከተማዋን ሕጻናት ሰብስበው የሚያስተምሩ የወቅቱ መምህራን ናቸው። እኔ ደግሞ እነርሱን አልፎ አልፎ በማስጠናት አግዛቸው ስለነበር ከማክበር አልፈው ከሚያገኟት ነገር ሁሉ ያካፍሉኝ ነበር። ለምሳሌ አንድ ቀን ከተላኩላቸው የፍየል ግልገሎች ውስጥ አንዷን ለእኔ ሰጥተውኛል። የፍየልና የበግ ግልገሎች በከል ተብለው ይጠራሉ። በከሏ የአንድ ወር ዕድሜ ያላት ስለመሆኗ እንጃ። የምንሰጣትን ከእጃችን ጎርሳ እንደልጅ እየቦረቀች ቤታችንን አድምቃልን የቆየችው ለጥቂት ቀናት ብቻ ነው። አርደን ጠባብሰን እየበላናት እያለ ነበር ያ ፍንጥዝያዋ ትዝ ብሎኝ ለምን አረድኋት ብየ የተጸጸትሁኝ። ከተማሪ አስተማሪወች ቤት ስገባ ሁሉም በአክብሮት ብድግ ብለው ተቀበሉኝ። ከነርሱ ጋር ትንሽ ሳወራ ከቆየሁ በኋላ ከፍላጎቷ ውጪ በግዳጅ አብራቸው እንድትኖር ተደርጋ እንደሆነ እንድትነግረኝ ልጅቷን ጠየኳት። በምን እንዳታለሏት አላውቅም፤ ምንም ችግር እንዳላጋጠማትና አብራቸው የምትኖረውም በፍላጎቷ እንደሆነ ነገረችኝ። ሳትፈራ እውነቱን እንድትነግረኝ ደጋግሜ ወተወትኋት፤ መልሷ ያው ነበር።

የሴቶችን ያህል አይሁን እንጅ በወንዶች ላይም ቢሆን በደል ይፈጸማል። ስድቡና ማንቋሸሹ እንደተራ ነገር ነው የሚታየው። ጉልበት አለኝ ብሎ ጥቃት መሰንዘር አደጋ አለው። አፋሮች የተለያዩ ቢመስሉም አንድ ናቸው። አንዱ አፋር ቢጠቃ ሌሎች ደም ለመመለስ ታጥቀው ይነሳሉ። እና በጉልበቱ ያነሰ አፋር ጡንቻማውን ሀበሻ ሊማታ ቢነሳ መፍትሄው ሮጦ ማምለጥ ወይም እያሳሳቁ መገላገል ነው። ከአፋሮች ጎን በግምባር ተሰልፈው ሲዋጉ ከነበሩት መሀል አንድ ሰው ታርዶ እንደተገኘ አንድ ሰሞን ሲወራ ሰምቻለሁ። ሻምበል ኪሮስ አበራ የሚባል የቀድሞ የኢትዮጵያ ወታደራዊ መኮንን ለጅቡቲ መንግሥት ይሰልላል በሚል ጥርጣሬ ሙልጭ ተደርጎ ተገርፏል። ኪሱ ሲበረበር ብዙ የአሜሪካ ዶላር እንደተገኘበት ሲወራም ነበር። በደረሰበት ድብደባ ትክሻው አካባቢ አጥንቱ ተጎድቶ ለብዙ ጊዜ ተሰቃይቷል።
አፋሮች አዘውትረው የሚሳደቧት ስድብ “ኩታ” የምትለዋ ናት። ኩታ ማለት ውሻ ማለት ነው። ስድቡን ከበድ ሲያደርጉት “ኩቲ በራው!” ይላሉ የውሻ ልጅ ለማለት። ከኢትዮጵያውያን ጋር ሲጣሉ “ጋላይቱ በራው” ብለው ይሳደባሉ። ይኸ የመጨረሻው አስከፊው ስድብ መሆኑ ነው። ጋላይቱ በራው ማለት የጋላ ልጅ ማለት ነው። ከኢትዮጵያ የሄደ ሁሉ ጋላ ነው። ሲያሻሽሉት ሀበሻ ለማለት ሀበሽታ ብለው ይጠሩናል።

አንድ ቀን አደን የሚባል የኢትዮጵያ አፋርና አብዱራህማን በምን እንደሆነ እንጃ ሲጣሉ እዚያው ነበርሁ። አደን በጣም ተናዶ ‘ጋላይቱ በራው’ አለና አብዱራህማንን ሰደበው። ችግሩ ሳይከፋ በቦታው የነበሩ ወታደሮች በመሀል ገብተው ሁለቱንም ተቆጥተው ነገሩን አበረዱት። ከሰዓታት በኋላ አደን ሌሎች አፋሮችን አስከትሎ ከእኔ ቤት መጣ። አማረኛ ለመግባቢያ ያህል ይችላል፤ ኧረ አስተርጓሚያችንም እሱ ነው! “አጥፍቻለሁ፣ በጣም ይቅርታ አድርግልኝ” አለኝ። አጥፍቻለሁ የሚለኝ እኔ ባለሁበት አብዱራህማንን ጋላይቱ በራው ብሎ በመሳደቡ ነበር። ከሌሎች ጋር እንደተወያዩበት ገብቶኛል። ለማንኛውም ተመስገን ነው፤ እኔ የተከበርሁ ጋላ ነኝ ማለትም አይደል! በዕውነትም አክብረውኛል፤ ለዚህም እግዚዓብሔር ውለታቸውን ይመልስልኝ። አፋሮች ካመኑ ከራሳቸው ሰው በላይ አክብረው ይይዛሉ። ክብር የተቸረው ሰው የሚናገረው ይደመጣል፤ ትልቅ ትንሹ ይታዘዝዋል። የሆነች እንከን ከተገኘችበት በአንዲት ቀን አዳር የገነባው ማንነት ፈራርሶ ተራና መናኛ ተደርጎ ይቆጠራል።

አንዳንድ የኢትዮጵያ አፋር ወጣቶች ለምን እንደሆነ ባይገባኝም ኢብራሂምን (ሶልሶልን) አይወዱትም። እርሱም ሁልጊዜ ተጠንቅቆ ነው የሚኖር። አንድ ቀን ሲያቀብጠኝ አንድ ስሙን የረሳሁትን የአፋር ወጣትና ኢብራሂምን አደን እንሂድ ብየ ጠየቅኋቸው። የአፋሩ ወጣት የራሱ ክላሽ አለው። ኢብራሂም እኔን አምኖ የአፋሩ ወጣትም አክብሮኝ ጥያቄየን ተቀብለው ወደቡያ በሚወስደው መንገድ አድርገን ወደቆጥቋጦወች አመራን። ወደውስጥ እየራቅን ስንሄድ የሆነ የተለየ ነገር ማስተዋል ጀመርሁ። ኢብራሂም ከፊት ሆኖ ሲመራ የአፋሩ ወጣት ቀስ እያለ ከኋላችን ሆኖ ይከተል ጀመር። በእራቁት ገላ የባና ብርድልብስ የለበስሁ ይመስል ሰውነቴን ኮሰኮሰኝ፤ ልቤን ፍርሀት ፍርሀት አለኝ። ወደኋላ ዞር ብየ ሳይ የአፋሩ ጓደኛችን ፊት ላይ ከእኔ የባሰ ጭንቀት አየሁበት። ፊቱ በላብ ወርዝቷል። የሆነ ነገር ለመወሰን አቅቶት በሀሳብ እየተንገላታ እንደሆነ ገመትሁ። መላ አካሌን ለጉድ ውርር አደረገኝ። ጠበንጃውን ልቀበለው እያጫወትሁና እያሳሳቅሁ ስቀርበው ምንም አይነት ተቃውሞ አላሰማም። “አምጣው እስቲ እኔ ደግሞ ልያዘው” ስለው ከትክሻው አውርዶ አቀበለኝ። የምናድነው አውሬ አጥተን ስንመለስ ከመንገድ ላይ ኢላማ ተኩስ ስንወዳደር ካልሆነ በስተቀር ጠበንጃውን ከእጄ ሳላወጣ ተመልሰን መጣን። የተፈጠረብኝ ስሜት ዝም ብሎ ከስጋት የመነጨ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ያችን ቀን ባሰብኋት ቁጥር አሁንም ቢሆን ሰውነቴን ይሰቀጥጠኛል፤ አፌን ደም ደም ይለኛል።

ቀንና ወሩን በትክክል ባላስታውሰውም በ1985 ዓ.ም አንድ ፈታኝ ነገር ገጠመኝ። ፈተናው የሁለት ትግሬወች በቁጥጥር ስር መዋል ነበር። ሁለቱ ሰዎች እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ በጅቡቲ አልፈው ወደአረብ ሀገር ለመሻገር ሲሉ የተያዙ ነበሩ። አፋሮች እንደቀላል ነገር ሊያልፉት አልፈለጉም። በዚያ ላይ በትግራዩ ወያኔ ተበትነው ለስደት የተዳረጉ የቀድሞ ኢትዮጵያውያን ወታደሮች ግፊት ነበር። ሁለቱ ትግሬወች ከኢትዮጵያ መንግሥት ተልከው የመጡ ሰላዮች ናቸው ተብሎ ታምኗል። እና ሁሉም እርምጃ እንዲወሰድባቸው እየጎተጎቱ ነው። ወያኔ የላካቸው ሰላዮች በቁጥጥር ስር እንደዋሉ ስሰማ ላያቸው ተጣደፍሁ። ሰዎቹ በገሶው በር በቀኝ ጫፍ፣ ከውጪ በኩል ከግምቡ ጋር ተያይዛ በድንጋይ ከተሰራችዋ ጠባብ ክፍል ውስጥ ተዘግቶባቸዋል። በሩ የንፋስ መግቢያ ሰፋፊ ቀዳዳወች ስላሉት ከውስጥ ወድውጪ፣ ከውጪም ወደውስጥ ማየት ያስችላል። አንገቴን ሰገግ አድርጌ አየኋቸው። ከወገባቸው በላይ ራቁታቸውን ሆነው በዚያ ትንፋሽ በሚያሳጣ ወበቅ እየነፈሩ ጭብጥ ብለው በፍርሀት ተቀምጠዋል። አንዳች ታምር ፈጥሬ ከዚያ መአት እንዳወጣቸው በዐይኖቻቸው የተማጸኑኝ መሰለኝ። በግሌ የትግሬወች ውለታ አለብኝ።

ወርቅ አንጣሪው ግደይ ሲበዛ ጓደኛየ ነበር። ግደይ ቁርሱን እንኳ ከእኔ ተለይቶ መብላት አይወድም ነበር። ብዙውን ጊዜ በርሱ ወጪ ስለምጋበዝ “የአባትሽን ስም ቀይሪ” እያለ ይቀልድብኝ ነበር። ከሚስቱ ቢጣላ ሽማግሌ ሆኜ ሰላም በር ድረስ ሄጃለሁ።

ሌላ አንድ የትግራይ ሰው ደግሞ በጨነቀኝ ጊዜ ደርሶልኛል። ነገሩ እንዲህ ነው። ከደቡብ ተዛውሬ ወደአዲሱ የስራ ቦታየ ስመጣ ገንዘብ አልነበረኝም። በዚያ ላይ ደመወዜን ሰጥተውኝ ቶሎ እመለሳለሁ ብየ በማሰብ የክረምት ኮርሱን አቋርጨ ነበር የሄድሁት። ተስፋየ የሚባለው የአስተዳደር ይሁን የሰው ኃይል አላፊ እንጃ ደመወዜ በስሜ ከገንዘብ ሚ/ር ተጠይቆ እንዲሰጠኝ በማመልከቻየ ላይ መራበት። ይህ ደግሞ ብዙ ቀናትን ይወስዳል። ችግሬን ዘርዝሬ፣ ከካዝና ይሰጠኝና በኋላ ከደመወዜ ተኩት ብየ ማመልከቻየን መልሸ ሰጠሁት። አቶ ተስፋየ ማመልከቻየን ወርውሮ ወደበሩ እያሳየ “ውጣ!” አለኝ።
በኪሴ ምንም ነገር አልነበረም። የአልጋ አልከፈልሁም፤ ምግብም አልበላሁም። ከሆዴ ይልቅ ያሳሰበኝ የመኝታየ ጉዳይ ነበር። ሥራ የሚያበቃበት አስር ሰዓት እየደረሰ ነው። ቢሮው አካባቢ በተስፋ መቁረጥ ወዲያ ወዲህ ስል አብራኝ የተማረች ካሰች ዐሊ የምትባል ልጅ አገኘሁ። ካሰችን ሳያት መፍትሄ ይዛልኝ ከሰማይ የወረደች ያህል ነበር የተሰማኝ። ሰላምታ ከተሰጣጠን በኋላ ቀጥታ ወደችግሬ ገባሁ። የምትኖረው ራቅ ካለ ቦታ እንደሆነና በእጇ ምንም ገንዘብ እንዳልያዘች ነግራኝ ማዘኗን በከንፈር መጠጣ ገለጸችልኝ።

ገንዘብ ልታበድረኝ ፍላጎቱ አልነበራትም ወይም እንዳለችው በእጇ ገንዘብ አልያዘችም። ምን ማድረግ እንዳለብኝ እያሰላሰልሁ እያለሁ ባለቤቷ መጣ። “የትምህርት ቤት ጓደኛየ ነው፤ ተዋወቁ!” ብላ ካስተዋወቀችን በኋላ እኔ የነገርኋትን ችግሬን ለርሱ ነገረችው። “ስንት ነው ደመወዝህ?” ሲል ጠየቀኝ ባለቤቷ፤ ነገርሁት። ከኪሱ ያበጠ ቦርሳ አወጣና አንድ ሁለት ብሎ ቆጥሮ “እንካ” አለኝ። ካሰች የደመወዜን ግማሹን ብቻ እንዲሰጠኝ ፈልጋ ነበር። እርሱ ግን፣ ምንም አይደል ኮርሱን ጨርሶ ሲመጣ ይመልስልናል አላት። በሆነ ወረዳ የግብርና ጽ/ቤት ሰራተኛ ሆኖ የሚያገለግል የትግራይ ሰው እንደሆነ ስንተዋወቅ ነግሮኛል። ምን ማለት እንዳለብኝ ማወቅ ተሳነኝ። ቢቸግረኝ “ወደቢሮ እንግባና ደመወዜን ለአንተ እንዲሰጡህ ልፈርምልህ” አልሁት። እሱ ግን “ይልቅ የአውቶቡስ ቲኬት ሳያልቅብህ ሂድና ቁረጥ። ደህና ሁን!” ብሎ አሰናበተኝ።

ዕውነት አልመስል አለኝ። ካሁን ካሁን ተመለስ ይለኛል ብየ እየሰጋሁ እግሬ ስብር ስብር እያለ ከግቢው ወጣሁ። ከግቢው እንደወጣሁ በሩጫ ተሰወርሁ። ከዚያ በኋላ አንድ የታወቀ ምግብ ቤት ገብቸ ክትፎ አዝዠ ዘና ብየ ርሀቤን አስታገስሁ። ይህን ውለታ አቅልሎ የሚያይ ካለ በዚያች ቀን የተሰማኝን ስሜት ሊረዳልኝ ያልቻለ ወይም ያልፈቀደ መሆን አለበት። ደግሞስ የውለታ ትንሽ አለው! ስንት ሀጢያት የሰራው ሰው እንኳ በጥም ለተቸገረ ጉሮሮ ማርጠቢያ ጥርኝ ውሀ በመስጠቱ ሀጢያቱን ይቅር ተብሏል አይደል!

ውለታ ባይኖርብኝስ! እንኳን የሀገሬን ልጆች ሌላስ ቢሆን ባልተጣራ ሁኔታ ለሞት ሲዳረጉ ዝም ብየ ማየት አለብኝ? ሊወጋን ጠበንጃ ይዞ የመጣን ጠላት ተኩሰው ቢገድሉት አግባብ ነው። እኒህ ሰዎች እኮ የጠላት መልዕክተኛ መሆናቸው ያልተረጋገጠ፣ በእጃቸው ምንም ነገር ያልተገኘ፣ በዘራቸው ብቻ ተጠርጥረው የተያዙ ሰዎች ናቸው። በዚያ ላይ ከዚያ መዐት የሚያወጣቸው ፍለጋ በጭንቀት የሚንከባለሉ ዐይኖቻቸው የአውሬ ባህሪ ላልተጸናወተው ሰብአዊነት ለሚሰማው ሰው በቀላሉ የሚታለፉ አልነበሩም። እንዲህ አይነት ጭካኔ በዘሬ የለም። አባቶቻችን በውጊያ ላይ የማረኳቸውን እንኳ አክመው፣ አብልተውና አጠጥተው፣ መክረውና ገስጸው የሚለቁ እንደነበሩ ነው የምናውቀው። በጅምላ ለመጥላትና በጅምላ ለመግደል ወያኔ ወይም ኦነግ መሆን ያስፈልጋል። እኔ ደግሞ ሁለቱንም አይደለሁም። ስለዚህ አንድ ነገር ማድረግ ነበረብኝ።

የቀጠናውን ኃላፊ፣ የገሶውን ኃላፊና ሌሎች ጥቂት ትላልቅ ሰዎች ከእኔ ቤት ጫት ልጋብዛቸው ስጠራቸው ለምን እንደሆነ ባለቤቴ እንኳ አታውቅም ነበር። ከማንም በላይ ሚስጥረኛየ ባለቤቴ ናት። እርሷ የማታውቀው ትልቅ ነገር ቢኖር ይኸ ብቻ ሳይሆን አይቀርም። ለምን እንደሆነ እንጃ ለእርሷ እንኳ ለመናገር ድፍረቱ አልነበረኝም።

እንግዶቸ ጥሪየን አክብረው በሰዐቱ ተገኝተውልኛል፤ ሳይጋበዙ የተገኙም ነበሩ መሰል። ከፀሀይዋ በተቃራኒ፣ ጥላ ካጠላበት የቤቱ ጥግ፣ ከተዘጋጀው ቦታ ላይ ቁጭ ብለን ኮካኮላ እየተጠጣ ጫት እየተቃመ ስለጦርነቱ ወግ ተጀመረ። ሁሉም አፋር ማለት ይቻላል የጦርነቱን አሰላለፍና የመሬቱን አቀማመጥ የሚያስረዳው በካርታ ነው። ሽርጡን ጎነፍ አድርጎ ቁጢጥ ይልና በመሬት ላይ በስንጥር እየጫረ ካርታ እየሰራ “እንዲህ ነው!” ብሎ ያሳያል። ሜሪቶ ጦርነቱን የተመለከተ በካርታ የተደገፈ ገለጻ አድርጎልን ሲያበቃ ሰላይ ናቸው ተብለው ስለታሰሩት ጉዳይ አነሳሁ። ብዙ አወራን፤ ብዙ አወጣን፤ ብዙ አወረድን። ሜሪቶ ባያግዘኝ ኖሮ የእኒያ ሰዎች ዕጣ ፈንታ የበረሀ አሸዋ ለብሶ መቅረት ይሆን ነበር። ባደረገው በጎ ተግባር ሜሪቶን መቸም ቢሆን አልረሳውም። በመጨረሻ እኒህን ሰዎች መግደሉ ምንም ጥቅም የለውም በሚል በሜሪቶ ብርቱ ድጋፍ ሌሎችን ተጭነን ማለት ይቻላል ማንም ሳያይ ከኢትዮጵያና ከጅቡቲ ድንበር ወስደው ለቀቋቸው። ያችን ቀን በህይወቴ ከምደሰትባቸው ቀናት አንዷ አድርጌ አስባታለሁ።
የአፋሮች ባህል

ሁለት የማይተዋወቁ አፋሮች ከመንገድ ከተገናኙ እንዲሁ በቀላሉ አይተላለፉም። መጀመሪያ እጅ ለእጅ ይጨባበጡና አይበሉባ የሚባለውን የእጅ መዳፎቻቸውን ጀርባ አንዱ የሌላውን ተራ በተራ ደጋግመው ይስማሉ። ከዚያ ዳጉ ይጀምራል። ዳጉ ማለት ዜና ወይም ወሬ እንደማለት ነው። “አኒናይ!” ይላል አንደኛው፤ ሌላው “ነጊያ ወላህ፣ ሳህሌ ወላህ፣ አማና፣ መስቡቱ” እያለ ምላሽ ይሰጣል። የመጀመሪያው ጠያቂ በየመሀሉ “እ፣ እ፣ እ” እያለ ምላሹን ያዳምጣል። ይህም ማለት የመጀመሪያው ጠያቂ አኒናይ ሲል መላሹ ነጋያ የሚል መልስ ቢሰጥ የመጀመሪያው ሰው “እ” ይላል ቀጥል እንደማለት ወይም “ደግ” እንደማለት። ‘ሳህሌ ወላህ’ ይላል መላሹ፤ እ – ‘አማና’ እ- መስቡቱ እያለ ይቀጥላል ማለት ነው። አኒናይ ማለት እንደምን አለህ እንደማለት ሲሆን አማና ማለት ደግሞ አማን ነኝ እንደማለት ነው። በዚህ መልኩ የመጀመሪያው ጠያቂ እያናገረው ያለውን ሰው ማንነት፣ ጎሣውን፣ የሚኖርበትን አካባቢ ሁኔታ፣ ፍየሉን ግመሉን ሳይቀር ጠይቆ መልስ ካገኘ በኋላ ተጠያቂ የነበረው ሰው በተመሳሳይ ሁኔታ ሲጠይቀው ለነበረው ሰው በተራው ጥያቄ ያቀርብለታል። በዚህ መልክ መረጃ ተለዋውጠው ሲያበቁ ይሰነባበታሉ። አፋሮች መረጃ የሚለዋወጡበት ዳጉ የህብረተሰቡ ባህላዊ መገናኛ (network) በመሆን በክልሉ የሚከሰቱ አዳዲስ ነገሮችን ከጫፍ ጫፍ በማዳረስ ግንዛቤ ያስጨብጣል።

አፋር ማህበራዊ ቁርኝቱ ከፍተኛ ነው። በቤተሰብ ወይም በጎሣ ብቻ ሳይሆን በአፋርነት መሀል ያለው ትስስር ጠንካራ ነው። ጥቃትን በጋራ መከላከልና መበቀል ዋናው መለያቸው ነው። ከኢሳወች ጋር አይዋደዱም። የመንግሥትን ጦር የኢሳ ጦር ነው ብለው ነው የሚሉት። የጅቡቲ ጦር በአንድ በኩል ጥቃት ከከፈተ “ኢሲ ይመቴ” ማለት ኢሳ መጣ በማለት በጩኸት ይጠራራሉ።
ጅቡቲ ጫት አብቃይ ባትሆንም ጫት ተጠቃሚው ግን በጣም ብዙ ነው። ጫት የሚመጣው በአብዛኛው ከባቲ፣ ከገርባና ከደጋን አካባቢ ነው። በወቅቱ አንድ እስር ጫት (አንድ ዙርባ) በጅቡቲ ፍራንክ ስንት እንደነበረ ባላስታውስም በኢትዮጵያ ገንዘብ ሃያ ብር ያወጣ ነበር። ሁሉም ባይሆኑም አብዛኛወቹ አፋሮች ጫት ካጡ ያቅበጠብጣቸዋል፤ የሚሆኑትን ያሳጣቸዋል። ጫት ለብዙ አገልግሎት ይመረጣል። ጫት ተይዞ ሽምግልና ይካሄዳል፤ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ውይይቶች ይደረጋሉ፤ ገበያው ጥጋብ፣ ሀገሩ አማን እንዲሆን ይጸለይበታል፤ የታመመ እንዲድን ፈጣሪን ይለምኑበታል። ቅሚያ ላይ ሲሆኑ ሰውነትን ዘና አድርጎ ትንፋሽ የሚያሳጥረው ሙቀት ይረሳል።

ከምግብ ሩዝ ይወዳሉ። ከከብት ወተት ይልቅ የፍየልና የግመል ወተት ይመርጣሉ። የተሻለ ኑሮ ያላቸው ለምግብ ማጣፈጫ አዘውትረው የሚጠቀሙት የፍየል ቅቤ ነው።
ግመል የአፋሮች ሁሉ ነገራቸው ነው። ለዕቃ መጫኛና ለሰው ማጓጓዣ የሚጠቀሙት ግመሎቻቸውን ነው። ከአንድ አካባቢ ነቅለው ወደሌላ ሲሄዱ ቤቶቻቸውን አፈራርሰው የሚጭኑት በግመሎቻቸው ነው። ወተታቸው ለመጠጥ ስጋቸው ለምግብነት ይውላል። ተኛ ሲሉት የሚተኛ፣ ተነሳ ሲሉት የሚነሳ ታዛዥ እንስሳ ነው ግመል። ተኛ ተብሎ ይጫናል ወይም ጭነቱ ይራገፋል፤ ተነስ ተብሎ ሸክሙን ይዞ ወደመሩት ይጓዛል። ግመል እምባ አውጥቶ እንደሚያለቅስ ይነገራል። “ተኛ!” ብለው አስተኝተው ተመልሶ እንዳይነሳ የታጠፉ እግሮቹን ጥፍንግ አድርገው አስረው ቢለዋ ሲስሉ ሲያይ እምባውን እያፈሰሰ ድምጽ አውጥቶ ያለቅሳል ይባላል። አንዳንዱ ግመል ግን አመለኛ፣ ነውጠኛ ነው። በእንክሻ አንገትን ጨምድዶ ይዞ ከመሬት ሊመታ ወይም ሊገድል ይችላል፡ በተለይ ወዛቸውን ያልለመዳቸውን ሰዎች። ሴት ግመሎች ልጅ ስለሚወልዱና ስለሚታለቡ ብዙውን ጊዜ የመታረድ ስጋት የለባቸውም።

በአፋሮች ባህል የሰው ሚስት የሚነካ ቀርቶ የሚያስብ የለም። በዐይኑ አይቶ በልቡ የተመኘ እንዳመነዘረ ይቆጠራል የሚለው መጽሀፍቅዱሳዊ ህግ የሚሰራው እዚህ ሳይሆን አይቀርም። የወንድ ሚስትን ቀርቦ ለፍቅር ጨዋታ ለማናገር ይቅርና ቀና ብሎ ለማየት የሚደፍር የለም። የወንድ ሚስት ደፍሮ የተገኘ ሰው ቅጣቱ እጅግ ከባድ ነው። ያለ የሌለውን ግመልና ፍየል ከፍሎ የማይወጣው ችግር ውስጥ ይወድቃል። ስለዚህ ባለትዳር ሴትን ደፍሮ ለፍቅር ጨዋታ ለመጠጋት ቀርቶ ለማሰብ ወኔ አይገኝም።
አፋሮች ሁሉም አንድ የዘር ሀረግ ያላቸው የእስልምና ተከታይ ይሁኑ እንጅ በውስጣቸው የተለያዩ ጎሳወች አሏቸው። ጎሳወች ከሚከባበሩባቸው መንገዶች ውስጥ አንዱ በየግል ጉዳዮቻቸው ጣልቃ አለመግባት ነው። ለምሳሌ አንዱ የአፋር ሰው የሀበሻ ሴትን ጠልፎ ከቤቱ ቢያስቀምጥ ሌሎች ተቃውመው እንዲለቃት ማድረግ አይችሉም። ይህን ለማድረግ ቢሞክሩ ጠባቸው ከጠላፊው ጋር ብቻ ሳይሆን ከጎሳውም ጭምር ይሆናል። ስለዚህ የመንግሥት ባለስልጣኖች ራሳቸው ወደ ጎሳ መሪወች ሄደው እነሱን በማሳመን ነው ብዙውን ጊዜ የሚፈልጉትን ነገር የሚያስፈጽሙት።
ሰዎች ስንባል ራስ ወዳዶች ነን። የራሳችንን ነውር ደብቀን ሌሎችን ስናጣጥል እንገኛለን። የሰዎችን ደካማ ጎን ለማወቅ የማናደርገው ጥረት ይለም። ይህን የምናደርገው ለበጎ ነገር ቢሆን ጥሩ በሆነ። የሌለንን ስምና ክብር ለራሳችን ሸልመን ሌላውን እናናንቃለን። አንዳንድ የከፋ ባህሪ የተጸናወታቸው ደግሞ ማንንም ይሁን ማንን በደግ ማንሳት አይወዱም። ስለሰዎች ደግነት ከተናገሩ ለራሳቸው የሚተርፋቸው በጎ መጠሪያ የሚያልቅባቸው ይመስላቸዋል። እና ማንንም ኩስ ሲቀቡ ነው የሚገኙት። እንዲህ ሲያደርጉ ራሳቸው ከፍ ብለው የሚታዩ ይመስላቸዋል። የጅቡቲ አፋሮችና የኢትዮጵያ አፋሮችም ይናናቃሉ። የጅቡቲ አፋሮች የኢትዮጵያ አፋሮችን “ሞያ መሌ” ይሏቸዋል። ጭንቅላት የላቸውም፤ አያስቡም ለማለት። የኢትዮጵያ አፋሮች በተራቸው ልብ የላቸውም ሲሉ የጅቡቲ አፋሮችን ይንቋቸዋል፤ ፈሪወች ናቸው ብለው ያጣጥሏቸዋል።
አፋሮች ራሳቸውን ከማንም በላይ ጀግና እንደሆኑ አድርገው ያምናሉ። አንድ ቀን ሰብሰብ ብለን ስንጫወት ስለዚሁ ጉዳይ እያወሩ ነበር። በመሀል እንደሌሎች ሁሉ ለእኔም የእስላም ስም ይውጣለት ተብየ ከብዙ አማራጮች ውስጥ በስምምነት አብዱልቃድር የሚለው ስም ተመረጠልኝ። አስተርጓሚያችን አደን ነው። ‘ጥሩ ነው ይሁን’ ተባለና አብዱልቃድር ሆንሁ። ከስም ማውጣት ሥነስርአቱ በኋላ በግድግዳው ጥግ ለጥግ ተቀጣጥለው በተነጠፉ ፍራሾች ላይ ተደላድለን ተቀምጠን ጫቱ እየተቃመ ሻዩ እየተጠጣ ወሬያችንን ቀጠልን። ሁሉም የሚያስቡት የአፋር ሕዝብ አንድ ላይ ከሆነ ለዓለም የሚያሰጋ ይሆናል ተብሎ በመታመኑ የዓለም መንግሥታት ተነጋግረው በሦስት ሀገር ውስጥ እንዲከፋፈል እንደተደረገ ነው። የሁሉም አመለካከት መሆኑን እርግጠኛ አይደለሁም እንጅ በሦስቱ ሀገሮች ማለትም በጅቡቲ በኢትዮጵያና በኤርትራ የሚኖሩትን የአፋር አካባቢወች ያጠቃለለ ኃያል የአፋር ሀገር ለመመስረት እንደሚፈልጉ አንዳንዶች ሲያወሩ ነበር።

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.