የአንድነት የምርጫ ዘመቻ ዕቅድና የተሻሻለው የፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ

ረፖርተር

ሊካሄድ የወራት ዕድሜ የቀሩት አምስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ ዋዜማ ላይ፣ በምርጫው የሚሳተፉ የተለያዩ ፓርቲዎች ምርጫውን አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት ወይም የኢሕአዴግ ዋነኛ ተገዳዳሪ ለመሆን የተለያዩ የአደራጃጀት ሥራዎችንና እንቅስቃሴዎችን በማከናወን ላይ  ይገኛሉ፡፡ 

77aba07f18af23d32321ef3cef492d7c_Lምንም እንኳን ምርጫው ሊካሄድ ከቀረው አጭር ጊዜ አንፃር የአብዛኛዎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንቅስቃሴና ሕዝቡ ውስጥ ሰርፀው ያላቸውን የፖሊሲና የስትራቴጂ አማራጮች ከማስተዋወቅ አኳያ የተቀዛቀዘ ቢመስልም፣ የተወሰኑ ፓርቲዎች ሕዝባዊ ስብሰባዎችን ማድረግና ከሕዝቡ ጋር ለመወያየት የተለያዩ አማራጮችን ለመጠቀም የሚያካሄዱትን እንቅስቃሴ መመልከት ይቻላል፡፡

ከእነዚህ እንቅስቃሴዎች መካከል በዘጠኝ ፓርቲዎች አማካይነት የተቋቋመው የፓርቲዎች ትብብር ለማድረግ አቅዶት የነበረውና በውዝግብ የተቋጨው የአዳር ሕዝባዊ ሠልፍ፣ እንዲሁም በባህር ዳርና በመቐለ ከተሞች የተደረጉት የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ሕዝባዊ ስብሰባና ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ጠቅላላ ጉባዔውን አከናውኖ መተዳደሪያ ደንቡን ያሻሻለው የአንድነት ፓርቲ እንቅስቃሴ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ሌሎች ፓርቲዎችም በዚህ ዓመት የሚካሄደው ምርጫ ላይ የራሳቸውን ወሳኝ ሚና ለመጫወት እየሠሩ እንደሆነ በተለያዩ ጊዜያት በሚያወጧቸው መግለጫዎች ሲገልጹ ተስተውሏል፡፡ ምንም እንኳን አብዛኛዎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች መንግሥት ከምንጊዜውም በላይ የተጠናከረ ጫና እየሳደረብን ነው በማለት የሚከሱ ቢሆንም፣ ለምርጫው የሚያደርጉትን ዝግጅት ግን አጠናክረው መቀጠላቸውን ይገልጻሉ፡፡

የአብዛኛዎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሠልፍና የሕዝባዊ ስብሰባ ጥያቄዎች በከፊል ሲመለሱና ሲስተጓጎሉ የተስተዋለ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም ባሉ ጊዜያት የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት የሚል ሕዝባዊ ስብሰባዎችና ሠልፎችን ያከናወነው አንድነትም ለመጪዎቹ ወራት የሚዘልቅና በተለይ ምርጫውን ዓላማ ያደረገ ‹‹ተደራጅ 2007 ለለውጥ›› የሚል የማደራጀትና የቅስቀሳ ዘመቻ ሊጀምር ነው፡፡ ዘመቻውን ለማስጀመር የሚያስችለውን ዕቅድና ዝግጅት ማጠናቀቁን ታኅሣሥ 7 ቀን 2007 ዓ.ም. ቀበና አካባቢ ከሚገኘው የፓርቲው ዋና ጽሕፈት ቤት በፓርቲው የድርጅት ጉዳይ፣ የሕዝብ ግንኙነትና የውጭ ግንኙነት ኃላፊዎች በጋራ በሰጡት መግለጫ ይፋ አድርጓል፡፡

ይህ ለወራት ይዘልቃል የተባለው እንቅስቃሴ የሚያካትታቸው በርካታ አጀንዳዎችን ሲሆን፣ በዋነኛነት የምርጫ 2007 ጉዳይ ዓብይ አጀንዳው እንደሚሆን ኃላፊዎቹ አስረድተዋል፡፡

ይህን አጠቃላይ የምርጫ እንቅስቃሴ ዕቅዱን አንድነት ፓርቲ ከማሳወቁ በፊት ግን፣ ባለፈው ሳምንት ዓርብና ቅዳሜ ጠቅላላ ጉባዔውን ሲያከናውን ባለፉት ጊዜያት ሲጠቀምበት የነበረውን መተዳደርያ ደንቡን ማሻሻሉ ታውቋል፡፡

የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ አቶ ዘካርያስ የማነብርሃን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የፓርቲውን መተዳደርያ ደንብ ማሻሻል ያስፈለገበት ዋነኛ ምክንያት ‹‹አንድነት ፓርቲ ከሌሎች ፓርቲ በተለየ ሁኔታ የምርጫ ቦርድ በመተዳደርያ ደንባችሁ ላይ የጠቅላላ ጉባዔ አባላትን ምልዓተ ጉባዔ አስቀምጡ ብሎ ስላዘዘን ነው፤›› በማለት፣ ለመተዳደርያ ደንቡ መሻሻል ዋነኛ ምክንያት ከምርጫ ቦርድ በተሰጠ ትዕዛዝ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ምንም እንኳን በምርጫ ቦርድ ትዕዛዝ መሠረት እንዲስተካከል የተፈለገው የመተዳደርያ ደንቡ እንዲያካትት የተፈለገው ከምልዓተ ጉባዔ ጋር የተያያዘ ነጥብ ቢሆንም፣ እንደ አቶ ዘካርያስ ማብራሪያ ግን በዚህ ምክንያት ፓርቲው ሌሎች አንቀጾችን አካትቶ የተደራጀ መተዳደሪያ ደንብ ማዘጋጀቱን ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

‹‹የምርጫ ቦርድ እንዲስተካከል ባዘዘው መሠረት የጠቅላላ ጉባዔ አባላትን በተመለከተ የጠቅላላ ጉባዔ አባላት ብዛት 320 መሆኑን በተሻሻለው ደንብ ተካቷል፤›› በማለት አቶ ዘካርያስ የገለጹ ሲሆን፣ ‹‹በዚህም መሠረት 161 ወይም 50+ አባላት ከተገኙ ደግሞ ምልዓተ ጉባዔው እንደተሟላ ይቆጠራል የሚለውን በግልፅ አስቀምጠናል፤›› በማለት አብራርተዋል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘም የተሻሻለው የፓርቲው መተዳደርያ ደንብ አንቀጽ 10 ንዑስ አንቀፍ 6 እና 7 ይህንኑ ጉዳይ አካተው ተዘጋጅተዋል፡፡ በተሻሻለው የመተዳደሪያ ደንብ ላይ ይህን የጠቅላላ ጉባዔ አባላትን ጉዳይ በተመለከተ የጠቅላላ ጉባዔውን ጥንቅርና አደረጃጀት ብቻ የሚዘረዝር ሲሆን፣ በዚህ በአዲሱ የመተዳደርያ ደንብ ላይ ግን የመዋቅሩ ጥንቅርና ቁጥር ተቀምጧል፡፡

በፓርቲው አደረጃጀት መሠረት ይህ ጠቅላላ ጉባዔ የሚባለው አካል በየሦስት ዓመቱ የሚሰበሰብና የፓርቲው ከፍተኛው የሥልጣን አካል ሲሆን፣ ሕጋዊ የሆኑ ማንኛቸውንም ውሳኔዎች ለመወሰን የሚያስችል ሥልጣን የተሰጠው አካል ነው፡፡ በዚህም መሠረት ይህ የሥልጣን አካል ከተሰጡት ሥልጣኖች መካከል የሚከተሉት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ የፓርቲውን ስያሜ፣ ዓርማ፣ ፕሮግራም፣ ደንብና ፖሊሲዎች ማፅደቅ፣ መሻርና ማሻሻል፣ የፓርቲውን ፕሬዚዳንት፣ የብሔራዊ ምክር ቤትና የኦዲትና የቁጥጥር ኮሚቴ አባላትን መምረጥና መሻር የሚሉት ይገኙበታል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በተሻሻለው የመተዳደሪያ ደንብ መሠረት ከዚህ ቀደም ያልተካተቱ አዳዲስ ሥልጣኖችና ኃላፊነቶች ለተለያዩ የፓርቲው የሥራ አስፈጻሚ አካላት የተሰጠ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል ከፓርቲው ፕሬዚዳንት ሥልጣን ጋር የተያያዘው ዋነኛ ተጠቃሽ ነው፡፡

በዚህም መሠረት ከዚህ ቀደም የፓርቲው ብሔራዊ ምክር ቤት ሥልጣንና ተግባር ላይ ያልነበረና የተጨመረው አንቀጽ የፓርቲው መሪ ከሕግ፣ ከፓርቲው ፕሮግራምና ደንብ ውጪ ተንቀሳቅሷል ብሎ ሲያምን በ2/3ኛ ድምፅ ሥራውን አግዶ ከአንድ ወር በማይበልጥ ጊዜ እንደገና ብሔራዊ ምክር ቤቱ ተሰብስቦ ከምክር ቤቱ አባላት መካከል ሌላ ፕሬዚዳንት ይመረጣል የሚለው ነው፡፡ ምርጫው እስኪደረግ ድረስ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ተክቶ ይሠራል ይላል፡፡ ምንም እንኳን ይህ አሠራር ቀደም ሲል ሲሠራበት በነበረው መተዳደሪያ ደንብ ላይ በብሔራዊ ምክር ቤት ሥልጣንና ተግባር በሚለው ሥር የተካተተ ቢሆንም፣ በቀድሞው ደንብ ላይ በደፈናው የብሐራዊ ምክር ቤት አባላት የዲሲፒሊን ጉድለት መፈጸማቸው ሲረጋገጥ ምክር ቤቱ በ2/3ኛ ድምፅ እነሱን በመሻር ተለዋጭ አባላት መተካት ይችላል የሚል ነበር፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በዚህ በተሻሻለው መተዳደርያ ደንብ ግን ከዚህ ቀደም ያልነበረ ሥልጣንና ተግባር ለብሔራዊ ምክር ቤቱ ተሰጥቷል፡፡ እርሱም የፓርቲው ፕሬዚዳንት በራሱ ፈቃድ ኃላፊነቱን ቢለቅ ወይም በሞት ቢለይ፣ ወይም ከአገር ውጪ በመውጣት የማይመለስ መሆኑ በብሔራዊ ምክር ቤቱ ቢረጋገጥ፣ ወይም በሥራ ምክንያት ወደ ተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ቢሄድና ፓርቲውን መምራት የማይችል መሆኑን በጽሑፍ ለብሔራዊ ምክር ቤቱ ቢያቀርብ፣ ቀጣዩ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ እስከሚደረግ ድረስ ብሔራዊ ምክር ቤቱ ተሰብስቦ በምክር ቤቱ አባላት ሌላ ፕሬዚዳንት ይመረጣል በማለት ቀደም ሲል ብሔራዊ ምክር ቤቱ ከነበረው በተጨማሪ ይህን ሥልጣን ሰጥቶታል፡፡

ከዚህ ቀደም ፓርቲው ሲሠራበት የነበረው የመተዳደሪያ ደንብ በአጠቃላይ የነበሩት አንቀጾች ብዛት 54 የነበሩ ሲሆን፣ በዚህ በተሻሻለው የመተዳደሪያ ደንብ መሠረት ግን አጠቃላይ የአንቀጾቹ ብዛት ወደ 28 ዝቅ ብለዋል፡፡ ይህ እንዴት ሊከሰት እንደቻለና የወጡ አንቀጾች አሉ ወይ በማለት ሪፖርተር ጥያቄ ያቀረበላቸው አቶ ዘካርያስ፣ ‹‹የወጡ አንቀጾች አሉ ማለት አይቻልም፡፡ ነገር ግን በአንቀጽ ቁጥር ደረጃ ይህን ያህል ልዩነቶች የተፈጠረው ብዙዎቹ በአንድ አንቀጽ ውስጥ እየተሰገሰጉ በመካተታቸው ባሉት አንቀጾች ውስጥ ሽግሽግ ሲደረግ የአንቀጾቹ ቁጥር ሊቀንስ ችሏል፤›› በማለት መልሰዋል፡፡

በአንቀጾች መካከል የተደረገ ሽግሽግ መኖሩን ኃላፊው ቢገልጹም ቀድሞ በነበረው የመተዳደሪያ ደንብ ላይ የነበሩ ነገር ግን ወደ የትኛው የሥልጣን አካል እንደተሸጋሸጉ ያልተገለጹ የሥራ ዘርፎች አሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል በምሳሌነት ለመጥቀስ የህል ቀድሞ ሲሠራበት በነበረው ደንብ ላይ የብሔራዊ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ዝርዝር መካከል የጥናትና ምርምር ጉዳይ ኃላፊ፣ የምርጫ ጉዳይ ኃላፊና የዕቅድና ስትራቴጂ ጉዳይ ኃላፊ የሚሉ የአባላት ዝርዝር በተሻሻለው መተዳደሪያ ደንብ ውስጥ በግልጽ አልተቀመጡም ወይም በየትኛው ሥር እንደተካተቱ አልተገለጸም፡፡

ምንም እንኳን ኃላፊው የአንቀጾች ሽግሽግ የተደረገ መሆኑን የገለጹ ቢሆንም፣ በመጪው ግንቦት ከሚካሄደው አገር አቀፍ ምርጫ አንፃር የምርጫ ጉዳይ ኃላፊ በተናጠል ራሱን ችሎ ሥራውንና ዝርዝር ተግባሩ ቢካተት የተሻለ ነበር የሚሉ አሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የጥናትና ምርምር ጉዳይ ኃላፊም እንዲሁ ከዚህ ቀደም በነበረው መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ራሱን ችሎ ቢዋቀር ፓርቲው ለሚያቀርባቸው የፖሊሲና የስትራቴጂ አማራጮች የግብዓት ምንጭ ሆኖ ሊሠራ ይችላል ከሚል ታሳቢነት ራሱን ችሎ ቢዋቀር እንዲሁ መልካም እንደሚሆን የሚገልጹ አሉ፡፡

በብሔራዊ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት መካከል በተሻሻለው ደንብ መሠረት አዲስ አባል የተካተተ ሲሆን ይህም የአዲስ አበባ አንድነት ፓርቲ ሰብሳቢ ነው፡፡ በዚህ በተሻሻለው ደንብ መሠረት ከዚህ ቀደም ያልነበሩ የአዲስ አበባ መዋቅርን በተመለከተ ከስምንት ሥራ አስፈጻሚ አባላት ወደ ዘጠኝ እንዲያድግ፣ የሕግና የሰብዓዊ መብት ኃላፊ ዝርዝር የሥልጣንና ተግባር እንዲካተት፣ እንዲሁም የሴቶች ጉዳይና የወጣቶች ጉዳይ ኃላፊዎች የሥራ ኃላፊነት ተግባር በዝርዝር ተቀምጧል፡፡ በቀድሞው ደንብ ላይ የነበረው የወጣቶች ጉዳይ ኃላፊ ዝርዝር የሥራ ተግባር ብቻ የነበረ መሆኑንም አቶ ዘካርያስ ገልጸዋል፡፡

‹‹ተደራጅ 2007 ለለውጥ››

ፓርቲው ጠቅላላ ጉባዔውን ባካሄደ ማግሥት በጠራው መግለጫ ላይ እንዳስታወቀው ከዚህ ቀደም በተከታታይ የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት፣ የሚሊዮኖች ድምፅ ለመሬት ባለቤትነትና የሚሊዮኖች ድምፅ ለህሊና እስረኞች የቅስቀሳ ዘመቻ ማካሄዱን አስታውሷል፡፡ የዚሁ ዘመቻ የመጨረሻ ምዕራፍ የሆነውን የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃና ፍትሐዊ ምርጫ በሚል ዓብይ ርዕስ ሥር በመጪዎቹ ወራት እንደሚያካሂድ የፓርቲው የውጭ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዳንኤል ተፈራ ገልጸዋል፡፡

የዚህ ዘመቻ መሪ ቃል ‹‹ተደራጅ 2007 ለለውጥ›› የሚል እንደሆነ የገለጹት አቶ ዳንኤል፣ ዘመቻውም በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች በሚደረጉ ሕዝባዊ ስብሰባዎችና ሰላማዊ ሠልፎች የሚካሄድ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ደግሞ በተለያዩ ማኅበራዊ ድረ ገጾችና የመገናኛ ብዙኃን አማካይነት ሰፊ ቅስቀሳ ለማድረግ ማቀዳቸውን አክለው አብራርተዋል፡፡

‹‹የዚህ ዘመቻ ዋነኛ ዓላማም ዜጎች በዚህ ዓመት ግንቦት ወር ላይ በሚደረገው አገራዊ ምርጫ በንቃት እንዲሳተፉ በማድረግ በምርጫው አሸናፊ ሆኖ በመውጣት የኢትዮጵያን ሕዝብ የሥልጣን ባለቤት እንዲሆን ማድረግ ነው፤›› በማለት አቶ ዳንኤል ዓላማውን ገልጸዋል፡፡

የተሻሻለ መተዳደሪያ ደንብ በማዘጋጀት የተጠናቀቀው የፓርቲው ጠቅላላ ጉባዔ በምርጫው በንቃት ለመሳተፍ መወሰኑ የተገለጸ ሲሆን፣ ለዚህም ሕዝቡ በአጠቃላይ በምርጫው ሒደት ላይ ሙሉ ለሙሉ ተሳታፊ እንዲሆንና በነቂስ ወጥቶ ካርድ እንዲወስድ፣ እንዲመርጥና ድምፁን እንዳይቀማ ተደራጅቶ እንዲጠብቅ የሚያስችል ስትራቴጂ አውጥቶ እየሠራ እንደሆነም ተገልጿል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.