በባህርዳር ኬላ ላይ ለሁለተኛ ቀን ከባድ ፍተሻ እየተካሄደ ነው

ጥር ፳፬ (ሃያ አራት)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የፌደራል ፖሊሶች ከትናንት ማክሰኞ ጀምሮ እስካ ዛሬ ድረስ የተጠናከረ ፍተሻ በማድረግ ላይ ሲሆኑ፣ በርካታ ተሽከርካሪዎች የመፈተሽ ተራ እስከሚደርሳቸው ረጃጅም ሰልፎችን ሰርተው ለሰዓታት ቆመው መዋላቸውን የአይን እማኞች ገልጸዋል።

ዋናው ፍተሻ የሚካሄደው በመራዊ አቅጣጫ ባለው የአዲስ አበባ ባህርዳር መስመር ላይ ሲሆን፣ ወደ ከተማው የሚገቡና የሚወጡ መኪኖች ጥብቅ ፍተሻ ይደረግባቸዋል። በአካባቢው በርካታ የፌደራል ፖሊሶች እየተንቀሳቀሱ መሆኑንም የአይን እማኞች ገልጸዋል።

መንገደኞች በፍተሻው በእጅጉ መማረራቸውንም በስፍራው ለሚገኝው ዘጋቢያችን ተናግረዋል ተመሳሳይ ፍተሻ እና ክትትል በመተሃራና ወለንጭቲ መሃከል ባሉ ቦታዎች እየተካሄደ መሆኑንም መረጃዎች ደርሰውናል። የፌደራል ፖሊሶች ከጅቡቲ በሚመለሱ መኪኖች በተለይም በነዳጅ ጫኝ ተሽከርካሪዎች ላይ ከፍተኛ ጥበቃ እያደረጉ ሲሆን፣ ፍተሻው ዛቻና ማስፈራሪያዎች እየጨመሩ ከመምጣታቸው ጋር የሚያያዝ መሆኑን ምንጮች ይናገራሉ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በመላው ኢትዮጵያ በተነሳው ሕዝባዊ አመጽ የተደናገጠው የህወሃት ኢህአዴግ አገዛዝ በመቶ ሽዎች የሚቆጠሩ ስርዓቱን በመቃወም ድምጻቸውን ያሰሙ ዜጎችን በገፍ ወደ ማሰቃያ እስር ቤቶችና ወታደራዊ ካምፖች ወስዶ በማጎር ኢሰብዓዊ የሆነ ሰቆቃ ሲፈጽምባቸው ከቆየ በሁዋላ የተወሰኑትን እንደሚፈታ አስታውቋል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ ከሕግ አግባብ ውጪ ዜጎችን የመግደል፣ ንብረታቸውን የመውረስና ሰቆቃ የመፈፀም ልዩ ስልጣን የተሰጠው ኮማንድ ፖስቱ፣ በቁጥጥር ስር ያዋላቸውን የተወሰኑ እስረኞችን መልቀቅ ጀምሯል። ሰብዓዊ ክብራቸውን በመጣስና ፀጉራቸውን ላጭተው አይደገምም የሚል ቲሸርት በማልበስ ባለፈው ወር ቁጥራቸው 9 ሺህ 800 የሚሆኑትን መልቀቃቸው ይታወሳል::
በሰንቀሌ፣ ይርጋለም፣ ጦላይ እና ብር ሸለቆ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ካንፖች ውስጥ ሲሰቃዩ ከርመው በህይወት ከተረፉት ውስጥ ደግሞ ኮማንድ ፖስቱ 11 ሺህ 352 የሚሆኑትን ለመልቀቅ መወሰኑን የህወሃት ልሳን የሆነው ፋና ዘግቧል።

የአስቸኳይ የጊዜ አዋጁ ከታወጀበት ካለፉት ሶስት ወራቶች ጀምሮ በመላው ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ እስረኞች ቁጥር እስከ 70 ሺ እንደሚደርስ የሚገመት ሲሆን፣ ዛሬ የሚፈቱትን ጨምሮ 21 ሺህ 152 ይለቀቃሉ።

በተመሳሳይ ዜና ፋይናንሻል ታይምስ የገዢውን ፓርቲ ቃል አቀባይ አቶ ነገሪ ሌንጮን በመጥቀስ ባወጣው ዘገባ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መቼ እንደሚነሳ አይታወቅም ብሎአል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መንግስትን ለመለወጥ ቆርጠው የተነሱትን የታጠቁ ሃይሎችና አሸባሪዎች አመጽ እንዳይቀሰቅሱ ረድቷል ሲሉ ቃል አቀባዩ ገልጸዋል። አገዛዙ ከተቃዋሚዎች ጋር በመደራደር እንዲሁም ወጣቶችን በማሰርና ስለ ህገመንግስቱ በማስተማር ድጋሜ የፖለቲካ አመጽ እንዳይነሳ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ቃል አቀባዩ ቢጠቅሱም፣ ተቀማጭነታቸው አዲስ አበባ የሆኑ ዲፕሎማቶች ግን አባባላቸውን አጣጥለውታል። የአገሪቱ ዋና ዋና ተቃዋሚዎች ያልተሳተፉበት ውይይት ለውጥ አያመጣም በማለት አገዛዙ ከተቃዋሚዎች ጋር ድርድር ጀምሬአለሁ በሚል የሚያራግበውን ወሬም ዲፕሎማቶቹ ውድቅ አድርገውታል። አገዛዙ መሰረታዊ የሆነ ለውጥ ለማምጣት ፍላጎት እንደሌለው ፣ አንድ ኢንች ቢሰጥ ሊቆጣጠረው የማይችለው ነገር እንደሚፈጠር ዲፕሎማቱን ጠቅሶ ጋዜጣው ዘግቧል።
ህዝባዊ አመጹ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ እድገት ልፈፋ እንደጎዳውና ይህን ተከትሎም ኢንቨስተሮች እምነት እያጡ መመምጣታቸውን ጋዜጣው አክሎ ዘግቧል።

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.