የጅቡቲ አፋሮች ትግል እንዴት ከሸፈ? ክፍል 6 (ከይገርማል)

በሻምበሎች የተፈጸመ ክህደት

ከራንዳወች ምንም ነገር ሳንሰማ ቀን ቀንን ሣምንት ሣምንትን እየተኩ ነጎዱ። ለምን ድምጻቸውን እንዳጠፉ ሊገባኝ አልቻለም። ሀሳብ እያብሰለሰለኝ ሳወጣ ሳወርድ የሆነ ተባራሪ ወሬ መሰማት ጀመረ። እንደወሬው ከሆነ በራንዳና በጦር ግምባር ያሉት ኢትዮጵያውያን ተሰባስበው ኮሚቴ መርጠዋል። ቀስ በቀስ ወሬው እየጠራ ዕውነትነቱ ተረጋገጠ። የሆነ ነገር ጭንቅላቴን ሲወቅረኝ ተሰማኝ። እኛ እንዳናውቀው የተፈለገበት አንድ ተንኮል ቢኖር ነው ብየ መጠራጠር ጀመርሁ።

አንድ ቀን ማንነቱን የማላስታውሰው ሰው ሻምበል ኪሮስና ሻምበል የሱፍ ወደዶራ መምጣታቸውን ነገረኝ። ታይተዋል ወደተባለበት ቦታ ስሄድ ሻምበል ኪሮስን ብቻውን አገኘሁት። በከተማው ውስጥ ካለችው ብቸኛ ምግብ ቤት ምሣ በልቶ እየወጣ ነበር። ከዚህ በፊት በአካል ተገናኝተን አናውቅም፤ ራንዳ በሄድሁ ጊዜም አላገኘሁትም። ጠይም መልክ፣ ቀጠን ብሎ በመጠኑ ረዘም ያለ ቁመና አለው።
ገና ከሩቅ ሲያየኝ ፈገግ ብሎ ወደኔ አመራ። ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ እራሴን ለማስተዋወቅ ስሞክር “ስለአንተ ብዙ ሰምቻለሁ። ማስተዋወቅ አይጠበቅብህም” አለኝ። ስለእኔ ተክለቁመና ከሻምበል የሱፍ ወይም እኔን ከሚያውቁኝ ሰዎች መረጃ አግኝቶ ሊሆን ይችላል ስል አሰብሁ። “ማንነቴን ማስተዋወቅ ያለብኝ እኔ ነኝ። እርግጠኛ ነኝ ስለእኔ ብዙ መረጃ የለህም። ለማንኛውም ሻምበል ኪሮስ አበራ እባላለሁ። በአባቴ ጎንደሬ ነኝ። እናቴ የትግራይ ሰው ናት። በውትድርና ሙያ ከሰለጠንሁ በኋላ አብዛኛውን ጊዜ ያገለገልሁት ሁአሠ በሚል ይታወቅ በነበረው በሁለተኛው አብዮታዊ ሠራዊት ውስጥ ኤርትራ ነው። በደርግ የመጨረሻ ዓመታት ወደሦስተኛው አብዮታዊ ሠራዊት ተዛውሬ በዘመቻ መኮንንነት አገልግያለሁ። ኢሕአዴግ አዲስ አበባን ሲቆጣጠር በስደት ወደዚህ መጣሁ” አለኝ።
ምላሱ ምላጭ ወይም ጤፍ የሚቆላ የሚባል አይነት ሰው ነው። ከአነጋገሩ እምነት ሊጣልበት የሚከብድ ብልጥ መሆኑን መረዳት ብዙም አይከብድም።

“ተሰባስባችሁ ኮሚቴ እንደመረጣችሁ ሰማሁ” ስለው ከአፌ ነጥቆ “አዎ ጊዚያዊ ኮሚቴ አቋቁመናል። ከመጀመሪያው ጀምሮ አፋሮች የሚያውቁትን የአየር ወለድ ሃምሣ ዓለቃ የኮሚቴው ሰብሳቢ አድርገነዋል። እዚህ ያላችሁትንም የሚያጠቃልል ስብሰባ ወደፊት እናካሂዳለን ብለን አስበናል። በዚያን ወቅት ቋሚ አመራሮችን እናስመርጣለን” አለኝ። “ግን እኮ ከሻምበል የሱፍ ጋር የተነጋገርነው እንደዚህ አልነበረም። እዚያ ያላችሁት ተነጋግራችሁ በምትወስኑት ቀን መጥተን በጋራ ኮሚቴውን እንደምናቋቁም ነበር የተነጋገርነው። የምታከናወኗቸውን ተግባራት በሚመለከትም መረጃ እንደምትሰጡን ሻምበል የሱፍ ቃል ገብቶልኝ ነበር። እንዴት እንዲህ ሊሆን እንደቻለ አልገባኝም!” አልሁት።

ሻምበል ኪሮስ ፊቱን በፈገግታ አስውቦ “እንደነገርሁህ ያቋቋምነው ኮሚቴ ጊዚያዊ ነው። የአንተ ሀሳብ ቀላል የማይባል መነሳሳት ፈጥሮልናል። ጊዚያዊ ኮሚቴው በአጭር ጊዜ ብዙ ስራወችን ሰርቷል። በመጀመሪያ ደረጃ ኢትዮጵያውያኖች ተሰባስበን ድርጅት ለመመስረት ያለንን ፍላጎት ገልጸን ከፍሪድ አመራሮች ጋር ባደረግነው ድርድር ከስምምነት ላይ ደርሰናል። የእኛ መሰባሰብና መጠናከር ለነርሱ ጠቃሚ መሆኑን አምነውበታል። በዚህም መሠረት ራሳችንን በወታደራዊ ኃይል እንድናጠናክር ሠላሣ ሽህ ብር ተፈቅዶልን ወደኢትዮጵያ እየሄድን ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ለጥቂት ሣምንታት እንቆያለን። የምንሄድበት ዋናው ዓላማ የሰው ኃይል መልምለን ወደዚህ ለመላክ ነው። ጨርሰን ስንመለስ አጠቃላይ ስብሰባ ጠርተን የድርጅቱን አመራሮች እናስመርጥና የድርጅታችንን ምስረታ ዕውን እናደርጋለን። የጊዚያዊ ኮሚቴው የስራ ድርሻ የሚያበቃው ቋሚ አመራር ስንመሰርት ይሆናል። ከዚያ በኋላ ያለውን ሁኔታ የድርጅቱ አመራሮች የሚወስኑት ይሆናል። ኢትዮጵያውያንን በአንድ ዕዝ አሰባስበን እንደሰው ኃይላችን መጠን ምደባ አድርገን በራሳችን ወታደራዊ አመራሮች እንዲመሩ እናደርጋለን የሚል ነው ህልማችን። ከፍሪድ ጋር ሊኖረን የሚችለውን ግንኙነትና የመተባበር ወሰን በተመለከተ የስምምነት ሰነድ መፈራረም አግባብ እንደሆነ አምናለሁ። ይህ ሊሆን የሚችለው በጊዚያዊ ኮሚቴው አይደለም። ስለዚህ የድርጅቱ አመራሮች አንድ የሥራ ድርሻ ሆኖ ወደፊት የሚፈጸም ይሆናል። ሀሳባችን ይኸው ነው” አለኝ።
ሲናገር አልፎ አልፎ እያመለጠው ‘ሊሆን የማይችል ነገር ይዠ የምንገታገት የቀን ህልመኛ እንደሆንሁ አድርጎ የሚያሳይ’ የሹፈት ፈገግታ የፊቱን ገጽ ያላብሰዋል። እየተናገረው ያለው ነገር ባይጥመኝም መጨረሻውን ለማየት በትዕግስት መጠበቅ ይሻላል ብየ ራሴን አሳምኘ ምንም አይነት ጥርጣሬ እንዳላደረብኝ ለመምሰል መጣር ያዝሁ። ሻምበል የሱፍ ዐይኔን ሊያይ እንዳልፈለገ ገብቶኛል። ለዚያም ነው የጠፋው ስል አሰብሁ። ቢሆንም ላለማስነቃት ስል “ሻምበል የሱፍ የት ሄደ?” ስል ኪሮስን ጠየቅሁት። “ከጥቂት ደቂቃወች በፊት አብረን ነበርን። ወዴት እንደሄደ እንጃ” አለኝ።
የሆነ የተደበቀ ነገር እንዳለ ሰውነቴ ይነግረኛል። እንዴት ማውጣጣት እንዳለብኝ ግራ ገብቶኝ ዙሪያ ጥምዝ ስዞር ቆየሁ። ሰውየው ግን የሚቀመስ አልነበረም። ነገር ግን ያች አልፋ አልፋ ብልጭ የምትለዋ የሹፈት ፈገግታ የተቋጠረ ተንኮል እንዳለ የምትጠቁም ነበረች።

ከሻንበል የሱፍ ጋር በተገናኘንበት ጊዜ እንዳደረግሁት ስለአርበኞቻችን ገድል፣ ስለኢትዮጵያዊነት ኩራት፣ ዓላማ ለሌለው ነገር ደም ማፍሰስ እንደማይኖርብን ልተርክ ሳኮበኩብ “ብዙ መጨነቅ አያስፈልግህም። ስለሀገርና ስለሕዝብ ከሆነ ከአንተ የበለጠ ሀላፊነት ያለብኝ እኔ ነኝ። ኢትዮጵያዊ በመሆኔ ልክ እንዳንተው የሀገሬና የህዝቤ ጉዳይ ይመለከተኛል። ከዚያ በተጨማሪ ወታደር ነኝ። በውትድርና ሙያ ሰልጥኘ መለዮ ሳደርግ የሀገሬን ሉአላዊነት ለማስከበርና የሕዝቤን ሰላምና አንድነት ለማስጠበቅ ቃለ-መሀላ ፈጽሜአለሁ። የማልሁት መሀላ ከላየ ላይ የሚወርደው ቃሌን ሳከብር ነው። የቃል ባለዕዳ ነኝ እያልሁህ ነው። ይህን ተረዳልኝ” አለኝ በስሜት እየተናጠ።

በዕውነት! መስሎ ለመጫወት የሚችል የተዋጣለት አርቲስት ነው። ወደቤት ሄደን አረፍ እንድንል ጋብዠው ነበር፤ ፈቃደኛ አልሆነም። አብሬው እንድቆይም አልፈለገም። የሆዳችንን በሆዳችን አድርገን ስንሰነባበት ሲመለሱ እንደሚጠይቁኝ ቃል ገባልኝ።

በሻምበሎች እየተደረገ ያለውን ሽፍጥ የማጋለጥ ቅስቀሳ

ከጥቂት ቀናት በኋላ ምልምል ናቸው የተባሉ ኢትዮጵያውያን ወደዶራ መምጣት ጀመሩ። ወደራንዳ ከማለፋቸው በፊት ከእኛ ወታደራዊ ካምፕ (ገሶ) እንዲሰባሰቡ ስለተፈለገ ነበር ወደዚህ እንዲመጡ የተደረጉት። ይህ አጋጣሚ ከምልምሎች ጋር ውይይት ለማድረግ ምቹ ሁኔታ ፈጠረልን። አብዛወቹ ስለውትድርና ምንም የማያውቁ በቀን ሥራ ሲተዳደሩ የነበሩ ወጣቶች ናቸው። ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ከኤሊዳርና ከሎጊያ ነው የተገኙት። ወደዚህ በረሀ የመጡት ሁለቱ ሻምበሎች ስላታለሏቸው ነበር። ጅቡቲ ውስጥ ሥራ አለ ብለው እስከማንዳ ድረስ የትራንስፖርት ከፍለው ነው የላኳቸው። በራሳቸው ወጪ የመጡም ነበሩ። ከማንዳ ወደቡያ የሚመራቸው ሰው ተዘጋጅቶ ስለነበር ወደጅቡቲ ለመዝለቅ ችግር አልነበረባቸውም። ሁለቱ ሻምበሎች ኤሊዳር ላይ ጠጥተው ሰክረው ከሰው ጋር ተጋጭተው እነደነበረ ልጆቹ ነገሩን። በዚያን ጊዜ ሠላሳ ሽህ ብር በጣም ብዙ ገንዘብ ነበር። ግማሹን እንኳ አስተርፈው ተካፍለውት ከሆነ ራሳቸውን ሊያቋቁሙበት ይችላሉ። ለውትድርና ተመልምለው የመጡትን ወጣቶች ለምን ወደዚህ እንደመጡ ስንነግራቸው ከልብ አዘኑ፤ ተጨነቁ። ሁሉም ማለት ይቻላል ወደሀገራቸው ለመመለስ ጥያቄ አቀረቡ። አፋሮች ግን ይህን ለማድረግ ቀርቶ ለማሰብ እንኳ ፈቃደኞች አልነበሩም። የድሀ ጥሪታቸውን አሟጠው ሠላሳ ሽህ ብር ያወጡት ለቀልድ እንዳልሆነ በቁጣ ጭምር ነበር የገለጹት።

እኔና አብዱራህማን ምን ማድረግ እንዳለብን ትኩረት ሰጥተን ቁጭ ብለን መምከር ያዝን። ነገሮች ከቁጥጥራችን እየወጡ ነው። ሻምበሎችና የአየርወለዱ ሃምሣ ዓለቃ እንደሸወዱን ብቻ ሳይሆን እንደሸጡንም ተገንዝበናል። በፍሪድ ማሕጸን ድርጅት ለመመስረት የነበረን ህልም በነዚህ ሰዎች ሴራ ሳይጀመር እንደከሸፈ እርግጠኞች ሆነናል። እኒህ ሦስት ሰዎች ኢትዮጵያውያኑ በሚከፍሉት ደምና አጥንት ኑሯቸውን ሊመሰርቱ እንዳሰቡ፣ ክብርና ዝና ሊገነቡ እንደቋመጡ እርግጠኞች ሆነናል። ነገር ግን ይህን እንዲያደርጉ ማን ይፈቅድላቸዋል? ዓላማ ለሌለው ነገር ወገኖቻችን መስዋእትነት ሊከፍሉ እንደማይገባ ሁለታችንም ቁርጠኛ አቋም ያዝን።

ከዶራ ተነስቶ ወደኢትዮጵያ ለመጓዝ በቡያ ወይም በበልሆ በኩል ማለፍ ግድ ይላል። ከነዚህ መተላለፊያወች ውጪ ያለው በሙሉ የድንጋይ ክምር ነው። በሁለቱ መተላለፊያወች በኩል ደግሞ ሰው ሳያይ ለማለፍ የሚታሰብ አይደለም። በዚያ ላይ ከራሳቸው ከአፋሮች ሌላ አካባቢውን የሚያውቅ መንገድ መሪ ለማግኘት የሚቻል አይደለም። ያለው ብቸኛ አማራጭ ልጆቹን መቀስቀስ ነበር። ከተመልማዮቹ ጋር የምናደርገው ግንኙነት ከታወቀ ለእኛም አደገኛ እንደሚሆን እናውቃለን። ስለዚህ እንዳይነቃብን ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ጀመርን። ለቅስቀሳው ከፍተኛውን ድርሻ የወሰደው መቶ ዓለቃ አብዱራህማን ነበር። የተወሰኑ ሰዎችን በተናጠል በመያዝ ለኢትዮጵያ የማይጠቅም መስዋዕትነት ሊኖር እንደማይገባ፣ ኢትዮጵያውያኖች ተሰባስበው በራሳቸው ወታደራዊ አመራር እየተመሩ በአንድ ግምባር እንዲሰለፉ ጥያቄ እንዲያቀርቡ፣ ድርጅት እንዲመሰረት ግፊት እንዲያደርጉ፣ ሁሉም ኢትዮጵያውያን በመሀላቸው ክፍተት እንዳይፈጠር ዘግተው ለመብታቸው እንዲቆሙ የመቀስቀሱ ሥራ ተጠናክሮ ቀጠለ። አንዱ ከሌላው እየተቀባበለ እየተንጠባጠቡ ወደገሶው ለሚገቡት ሁሉ መረጃ የማቀበሉ ሥራ በብቃት ተሠራ። ከሣምንታት ቆይታ በኋላ ሻምበሎቹ ወደራንዳ መመለሳቸውን ሰማን። ያለፉት በዶራ በኩል ቢሆንም ሊያገኙን አልፈለጉም ነበር ማለት ነው።

አዲሶቹ ምልምሎች ወደራንዳ የተጓጓዙት ቀስ በቀስ ነበር። ከዚያ በኋላ አልፎ አልፎ ከምንሰማው ተባራሪ ወሬ በስተቀር ለብዙ ሳምንታት ዕውነተኛ መረጃ የምናገኝበት መንገድ አልነበረም። ዘግይተን እንዳረጋገጥነው መሰረታዊ የመሣሪያ አጠቃቀም ትምህርት የሰጣቸው ሻምበል የሱፍ ነበር። ከስልጠናው በኋላ “ለውትድርና ብቁ ናችሁ” ተብለው የልብስና የመሳሪያ እደላ ተደርጎ ወደግምባር ተልከዋል። አጠቃላይ የኢትዮጵያውያኑ ወታደሮች ቁጥር 300 አካባቢ ሲሆን ሻምበል የሱፍ የበላይ ኃላፊያቸው ሆኖ ተመድቧል። ዶራወች ወሬ ማነፍነፋችንን ቀጥለናል። በተለይ እኔ የወንጀለኛነት ስሜት እየተሰማኝ መብከንከን ይዣለሁ። እነዚህ ልጆች ወደዚህ መጥተው በማይመለከታቸው ጉዳይ መስዋዕትነት እንዲከፍሉ ምክንያት የሆንሁት እኔ ነበርሁ። ተደራጅተን ለሀገራችንና ለህዝባችን የሆነ በጐ አስተዋጽዖ እናበረክታለን ብየ ያቀረብሁት ሀሳብ እርባና ለሌለው ነገር የወገኖቼ መጥፊያ ሊሆን ነው። የተቀደሰ ነው ብየ ያቀረብሁት ሀሳብ በሦስት ራስ ወዳዶች ተጠልፎ ለግል ፍላጎታቸው መጠቀሚያ እየዋለ ነው።
የኢትዮጵያውያን ወታደሮች አድማ

የእኔና የአብዱራህማን ቅስቀሳ መስራት የጀመረው ብዙም ሳይቆይ ነበር። ወደውጊያ ወረዳ እንዲገቡ የተጠየቁት ወታደሮች እምቢ አሻፈረን አንዋጋም ብለው በአንድ ድምጽ አቋም እንደያዙ ይወራ ጀመር። የወታደሮቹ ጥያቄ “ዶራ ያሉት ሰዎች ወደዚህ መጥተው ያነጋግሩን” የሚል ነበር። በዚህ ቢባሉ በዚያ ማንንም አንሰማም የሚል አቋም ያዙ። ብቸኛው አማራጭ እኔ ወደግምባር ሄጀ እንዳነጋግራቸው ማድረግ ነበር። በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ የታሸ ብዙ የተብላላ ነገር ሊኖር ይችላል። በመጨረሻ ግን የኢትዮጵያውያኑን አቋም ያለዝባል በሚል ስሌት ወደግምባር ሄጀ እንዳነጋግራቸው ተፈቀደልኝ። በዚህ መሠረት ከወታደሮች ጋር የምገናኝበትን ሰዓት ተወስኖ ሁሉም እንዲያውቀው መደረጉ ተነግሮኝ ወደራንዳ ተጓዝሁ። ራንዳ ስደርስ መቶ ዓለቃ መኮንን እየጠበቀኝ ነበር። መኮንን ብዙ ጊዜ ይታመማል። የምን እንደሆነ ባላውቅም መርፌ ይወጋ ነበር። “አንተ መድከም አያስፈልግህም፤ ሌላ ሰው ይዞኝ ሊሄድ ይችላል” ብየው ነበር፤ እሺ አላለኝም። የሆነውን ሁሉ እያጫወተኝ ወደአቡሌ ራንዳ ተጓዝን።

የአየር ወለዱና ሁለቱ ሻምበሎች ከፍሪድ ባለስልጣኖች ጋር የተስማሙት የጅቡቲን መንግሥት በኃይል አሸንፈው እንዳስወገዱ በውጊያ ለተሳተፉት ኢትዮጵያውያን ዜግነት እንዲሰጧቸው ነበር። ከፍሪድ ባለስልጣናት ጋር በተካሄደ ውይይት ከድል በኋላ የጅቡቲ ወታደር ሆናችሁ እንድትቀጥሉ ስምምነት ላይ የተደረሰ በመሆኑ እንኳን ደስ ያላችሁ ተብለዋል ኢትዮጵያውያኑ። የጅቡቲ ወታደር ወርሀዊ ደመወዝ እጅግ ከፍተኛ ነው፤ ለወደፊቱ ጣፋጭ ህይወታችሁ ስትሉ ተዋጉ ተብለው ተቀስቅሰዋል። ያሳምናቸዋል፣ ያማልላቸዋል የተባለው ሁሉ እየተነሳ ብዙ ተደስኩሯል። ዶራወች የረጩትን መርዝ ለማርከስ ተብሎ ብዙ እንደተደከመ ተረዳሁ። ከዚያ ሁሉ ድካም በኋላ ግን ኢትዮጵያዊያኖቹ አንድ ነገር ተናገሩ፤ ዶራ ያሉት ሰዎች መጥተው ካላነጋገሩን ለውጊያ አንሰለፍም ብለው።

ሻምበሎቹ የወታደሮችን ልብ ለማሸነፍ ያላደረጉት ነገር አልነበረም። “ዶራ ያለው ሰው ከመዐሕድ የተላከ ነው። አላማው የመዐሕድ የሽምቅ ተዋጊ ኃይል በጅቡቲ ምድር ለመመስረት ነው። ይህን የምንቀበለው አይደለም። በመጀመሪያ ደረጃ ወያኔም ሆነ ኢሕአዴግ የእኛ ጠላት አይደሉም። ጠላታችሁ ማን ነው ካላችሁን ጠላታችን የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። ወያኔን እያበላ፣ እያጠጣና እየመራ ለዚህ ያበቃቸው ማንም ሳይሆን የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። መረጃ እየሰጠ፣ ያለንበትን እየጠቆመ ለሽንፈት የዳረገን የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። እኛ የሀገራችንን ሉአላዊነትና አንድነት ለማስጠበቅ ስንዋደቅ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነበር ከወያኔ ጎን ሆኖ የወጋን። የወያኔን ቁስለኞች ሲደብቅና ሲረዳ እኛን ግን እያጋለጠ ሲሰጠን ነበር። በውጊያ ተሸንፈን ተበታትነን ስናፈገፍግ እያናጠለ የፈጀን የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። መሳሪያችንን እየገፈፈ፣ ልብሳችንን እያስወለቀ፣ ኪሳችንን እያራገፈ ራቁታችንን የለቀቀን የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። እኛ ለሀገራችንና ለሕዝባችን ብለን ያለንን ሳንሰስት ስንሰጥ እየሞትንለት ነው የምንለው ሕዝብ ግን እንደጠላት ጦር ቆጥሮን ግፍ ፈጽሞብናል። ወያኔ ጨፍጫፊ ከሆነ እሰየው ነው፤ ደግሞ ደጋግሞ ያድርገው። ሀገሪቷም ብትሆን ብትፈልግ አንድ ትሁን አሊያም ትበታተን። በሕዝቧ ላይ እየደረሰ ነው የሚባል መከራ ካለም ሲያንስ ነው፤ ይበለው። ስለኢትዮጵያና ስለሕዝቧ ከናንተ ይልቅ እኛ ብዙ እናውቃለን። አሁን ጊዜው ተለውጧል። ሁሉም ያዋጣናል የሚለውን መንገድ ተከትሎ ልቡ የፈቀደውን እያደረገ ነው። እኛም ከእንግዲህ በኋላ የምንቆስለውም ሆነ የምንሞተው ለማንም ሳይሆን ለራሳችን ነው። የኢትዮጵያና የሕዝቧ ጉዳይ አይመለከተንም፤ በቅቶናል” በሚል ሊያሳምኑ ጥረዋል። ኢትዮጵያውያኑ ግን ቃላቸውን ሳያጥፉ “ለማንኛውም ዶራወች ይምጡና የሚሉንን እንስማ” በሚለው አቋማቸው ጸኑ።

አቡሌራንዳ ከሆነች ደሳሳ ጎጆ አርፈን በበነጋታው ጠዋት የጅቡቲ መንግሥት ወታደሮችና የፍሪድ አማጽያን የተፋጠጡበትን ግምባር ሊያሳየኝ ወደታጁራ መስመር ትንሽ ተጓዝን። አንድ ቦታ ላይ ስንደርስ “በቃ እንቁም!” ከዚህ ካለፍን ያዩናል አለኝ። አንድ ሰው እንኳ ካዩ መድፍ ከመተኮስ እንደማይመለሱ የነገረኝ እሱ ነው። በሁለቱ ኃይሎች መሀል ረባዳ መሬት አለ። በታጁራ ግምባር ካለው ጉብታ ላይ ነው የመንግሥት ወታደሮች ያሉት። አካባቢውን ለማየት ብዙ መቆየት አላስፈለገንም። ለጥቃት እንዳንጋለጥ ሰባራውን መሬት ይዘን ወደኋላ ተመልሰን የቀጠሮውን ሰዓት መጠበቅ ያዝን።
የቀጠሮው ሰዓት ሲቃረብ ወደስብሰባው ቦታ አመራን። ከቦታው ስንደርስ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 3ኛ ዓመት ላይ አቋርጦ የመጣ ነው የተባለ አንድ ጠይም ወጣት ተቀበለን። ፈንጠር ብሎ ከሜዳ ላይ ወደተቀመጡት ሰዎች እያመለከተን “ያው እየጠበቋችሁ ነው” አለን። ምን ያህል እንደሆኑ ባላውቅም ስብሰባውን ለመካፈል የመጡት ወታደሮች በርካታ ናቸው። የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ነበር የተባለው ወጣት ለተሰብሳቢው አስተዋውቆኝ ሲያበቃ “እንኳን በሰላም መጣህ!” ብሎ መድረኩን ለቀቀልኝ።

ወደፊት ቀረብ ብየ ንግግር ለማድረግ ስዘጋጅ አንድ መኪና በከፍተኛ ፍጥነት እየበረረች መጥታ ካጠገባችን ስትደርስ ቆመች። ሻምበል የሱፍ ጋቢናውን ከፍቶ ወጣና በቀጥታ ወደእኔ መጥቶ “አቶ ዓሊ መኪ ሊያነጋግርህ ይፈልጋል፤ ሾፌሩን አታስጠብቀው ሂድ” አለኝ። የተሸበረና የተጣደፈ ይመስላል። ወታደሮች የማጉረምረም ድምጽ ማሰማት ሲጀምሩ “ከአቶ ዓሊ መኪ ጋር ከተነጋገረ በኋላ ተመልሶ ይመጣል” በማለት ሊያረጋጋቸው ሞከረ። ዐሊ መኪ ማለት የፍሪድ ወታደራዊ ኃይል የበላይ ሹም ነው።

ለጥቂት ጊዜ ከራሴ ጋር ተማክሬ ከአፋሮች ጋር የሚኖረንን ግንኙነት ላለማበላሸት ስል መሄድ እንዳለብኝ ወሰንሁ። በሻምበሎች የተሸረበውን ተንኮል ለማክሸፍ፣ የተረጨውን መርዝ ለማርከስ አጋጣሚው ጥሩ ነው ስል አሰብሁ። ሾፌሩ የጋቤናውን በር ከፍቶ እንድገባ በምልክት ሲያሳየኝ ገባሁና ተመቻችቸ ቁጭ አልሁ። ወዲያው ስሜቴ መዘበራረቅ ያዘ። የወሰንሁት ውሳኔ ትክክል ስለመሆኑ መጠራጠር ጀመርሁ። ምን እንደማስብ ግራ ይገባኝ ጀመር። መያዣ መጨበጫ የሌለው ድብልቅልቅ ያለ ሁኔታ እየተሰማኝ ነው። ልውረድ አልውረድ እያልሁ ከራሴ ጋር ሙግት በገጠምሁበት ሰዐት ሳላስበው ክላክሱን ተጭኜ ይዠው ኖሯል። ሾፌሩ የመኪናውን በር ከፍቶ ክላክሱን እንድለቀው ሲነግረኝ ነበር ተጭኘ ይዠው እንደነበር ያወቅሁት። በመጨረሻ ከፍሪድ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ሊያገናኘኝ የመጣልኝን ዕድል መግፋት አግባብ አይደለም የሚለውን አማራጭ ይዠ ባለሁበት ጸናሁ። ወዲያው ሾፌሩ ሞተሩን አስነስቶ እኔን ብቻ ይዞ ወደራንዳ ማሽከርከሩን ቀጠለ። ሻምበል የሱፍ ከወታደሮች ጋር የቀረው የሆነ ያልሆነውን እያነሳ ሊያሳምናቸው አስቦ እንደሆነ ገብቶኛል።

ራንዳ ስንድረስ ከመኪና ወርደን ዓሊ መኪ ወደሚገኝበት ቤት ገባን። በቤቱ ውስጥ ከፍተኛ ኃላፊወች ተሰባስበዋል። በምን አጀንዳ ላይ እየተነጋገሩ እንደሆነ ባላውቅም ግማሽ ክብ ሰርተው በፍራሽ ላይ ተቀምጠው በተመስጦ እየተወያዩ ነበር። ባዶ ቦታ ፈልጌ ቁጭ ብየ የሚሆነውን መከታተል ያዝሁ። ሰላምታ ያቀረበልኝ ወይም ያነጋገረኝ ማንም አልነበረም። እነርሱ ለእኔ ምንም ትኩረት ባለመስጠት ወጋቸውን ቀጥለዋል። መቀመጡ ሲሰለቸኝ ብድግ ብየ ወጣሁ። ከውጪ የመቶ መሪ ነኝ ያለኝ አንድ ጠይም ኢትዮጵያዊ ወጣት ቆሞ ሲጠብቀኝ አገኘሁት። አፋሮች ሊጐዱት ይችላሉ በሚል ያለሁበትን ሁኔታ ለማጣራት ተልኰ ጥቂት ወታደሮችን አስከትሎ እንደመጣ ነው የነገረኝ። በግምባር ስላለው ሁኔታ ስጠይቀው “ሻምበል የሱፍና ወታደሮች ሊግባቡ አልቻሉም። እንዲያውም ከወታደሮች አንዱ መሳሪያ አዙሮበት ነበር” አለኝ። አሃ! አደጋ ውስጥ ነኝ ማለት ነው! ደርግን የጣሉ አምታቾች እዚህም ችግር እየፈጠሩ ነበር።

የኡጉጉሙ ጦርና የጅቡቲ አፋሮች በምን ምክንያት እንደሆነ ባላውቅም ፊት እንደተዟዟሩ ሰምቻለሁ። አባስ ዶራ የሚኖር የኡጉጉሙ ሰው ነበር። ባለቤቱ አሚና የምትባል ኢትዮጵያዊት ናት። ከነዚህ ሰዎች ጋር በጣም ተቀራርበን እንደሀገራችን እየተጠራራን ቡና እንጠጣ ነበር። በርሱ ምክንያት ከኡጉጉሙ የበላይ ኃላፊወች ጋር ተዋውቄአለሁ።

የኡጉጉሙ የበላይ ኃላፊ ነው ብሎ አባስ ያስተዋወቀኝን ሰው ራንዳ ሳገኘው በጣም ደስ አለኝ። ያለኝ አማራጭ ኡጉጉሙን ከጎናችን እንዲሰለፍ ዲፕሎማሲያዊ ሥራ መስራት ነበር። ከኃላፊው ጋር በአስተርጓሚ ብዙ አወራን። የእኔ ሀሳብ ምን እንደሆነ ዘርዝሬ አስረዳሁት። ሰውየው ስለሁሉም ነገር በግልጽ እንደሚያውቅ ነገረኝ። “ችግሩ የፍሪድ ሰዎች አይደለም የናንተ ሰዎች ነው” አለኝ። “የኢትዮጵያን መንግሥት የሚቃወም ድርጅት የሚመሰረት ከሆነ ከኢትዮጵያ ጋር ያቃቅራችኋል። መቃቃሩን ተከትሎ ከኢትዮጵያ ጋር የሚያገናኘን መውጫ መግቢያ ይዘጋል። ከኢትዮጵያ ጋር የሚያገናኘን መስመር ከተዘጋ ደግሞ ሳንወድ በግድ እጃችንን ሰጠን ማለት ነው። ቀለብን ጨምሮ ማንኛውንም ነገር የምናስገባው ከኢትዮጵያ ነው፤ ከኢትዮጵያ ጋር ቅራኔ መፍጠር ማለት ራስን በራስ ማጥፋት ማለት ነው ብለው ዐዕምሯቸውን የቀየሩት የናንተ ሻምበሎች ናቸው” አለኝ።

የዚህ ሀሳብ ጠንሳሽ ሻምበል ኪሮስ እንደሚሆን አልጠራጠርም። የአየር ወለዱን ሃምሣ ዓለቃ ባላውቀውም ያን ያህል ነገር የማወሳሰብ አቅም እንደሌለው በቅርብ ከሚያውቁት ሰዎች ተረድቻለሁ። ከመጀመሪያ ጀምሮ ነገር ሲያበላሽ የነበረው ይኸው ኪሮስ የሚባለው ሰው መሆን አለበት። ሻምበል የሱፍ የዋህ ግን የማመዛዘን ችግር ያለበት፣ የነገሩትን በቀላሉ የሚቀበል ዋዣቂ እንደሆነ ነው የተረዳሁት። ማንም እንደፈለገው ሊያሾረው የሚችል ከጭንቅላቱ ይልቅ ጉልበቱን የሚጠቀም፣ ከፊቱ የቆመውን ሁሉ የሚወጋ የስፔይን በሬ መሆኑ ነበር የተገለጸልኝ። ሻምበል ኪሮስ የሱፍን እየተጠቀመበት ነበር። ኪሮስ ምናልባት የወያኔን ተልዕኮ ይዞ የመጣ ሊሆን ይችላል።

ከኡጉጉሙ ኃላፊ ጋር የነበረንን ውይይት እንደጨረስሁ ደህንነቴን እንዲከታተሉ ከተላኩት ወንድሞቸ ጋር ተገናኝተን ትንሽ አወራን። የኡጉጉሙ ኃይል ከጎናችን እንደሚቆም ኃላፊው አረጋግጦልኛል። ሁላችንም ኢትዮጵያውያን መሆናችንን አትርሳ ብሎኛል። ተመልሸ ወደአቡሌ ራንዳ ለመሄድ የማይታሰብ ነበር። ከልጆቹ ጋር የተመካከርነው ወደዶራ እንድመለስ ስለነበር መኪና አፈላልገው አሳፈሩኝ። ዶራ ስደርስ የሆነውን ሁሉ እዚያ ላሉት ነግሪያቸው ሁላችንም መጠንቀቅ እንደሚኖርብን ተስማማን።

የዶራ አፋሮች በሙሉ ሴት ወንድ፣ ትንሽ ትልቅ ሳይሉ ፊታቸውን አዞሩብኝ። ሜሪቶ ራሱ ምክንያት እየፈጠረ ይገላምጠኝ፣ ፊቱን ይቋጥርብኝ ያዘ። በየወሩ እየተሰፈረ ይሰጠኝ የነበረው ቀለብ ተቋረጠ። በቃላቸው መሰረት ከጎኔ መሆናቸውን ያስመሰከሩት ኡጉጉሙወች ለወር የሚያስፈልገኝን ቀለብ ከተሰጣቸው ቀንሰው በአባስ በኩል እንዲደርሰኝ አደረጉ።

በግምባር የተሰለፉት የእኛ ልጆች የሚሞቱት ሞት ትርጉም አልባ እንደሆነ ገብቷቸዋል። ውጊያ ውስጥ ከተገባ ሞት ይኖራል። የሞተ ሰው ከጅቡቲ ነጻነት ሊያገኘው የሚችለው ጥቅም ምንድን ነው? ለሀገራችን የማይጠቅም ኢትዮጵያዊ ደም ከእንግዲህ በኋላ በጅቡቲ ምድር አይፈስም የሚል አቋም ይዘው ውጊያ ላለመግባት እምቢኝ አሉ። ሁሉም ማለት ይቻላል የእኛን ትንፋሽ ማዳመጣቸውን ቀጠሉ። ከዚያው ከግምባር ካሉት ወጣቶች መሀል የወሎ ቦረናው ልጅ ከሀገር ቤት ያመጣውን በአቶ ተ/ጻዲቅ መኩሪያ የተጻፈውን የአጼ ቴወድሮስ የታሪክ መጽሀፍ ከሽፋኑ ቀጥሎ ባለው ገጽ ላይ ፊርማውንና ቀኑን አስቀምጦ በስጦታ መልክ ላከልኝ። ይኸ ለእኔ ከአቅሜ በላይ የሆነ፣ የማልችለው ትልቅ ሸክም ነበር።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.