?… ዴሞክራሲን – ለመቼ?!- ከሥርጉተ ሥላሴ

ከሥርጉተ ሥላሴ 08.02.2017 (ዙሪክ – ሲዊዘርላንድ)
„የድሆች ምክር አስፈራችሁ፥ እግዚአብሄር ግን ተስፋቸው ነው።“ ( መዝሙር ምዕራፍ ፲፫ ቁጥር ፱)

ዴሞክራሲን ለማዬት ወይንም ለማግኘት ቀጠሮ – አያስፈልግም። ቅድመ ሁኔታም አይሻም። አሁን በእጅ ባሉት መድረኮች፤ ሚዲያዎች፤ ጆሮዎች፤ ስብሰባዎች፤ ጉባኤዎች ዴሞክራሲን ሥራ ላይ ለማዋል ውጪ ሃገር ምን ዬሚያግድ፥ ምንስ ዬሚገድ ነገር አለና ነው ማዕቀቡ ዘርፈ ብዙ ዬሆነው????

በወያኔ ሃርነት ትግራይ ሥር አንጋጦ ዴሞክራሲን ከመለመን፤ ውጪ ሀገር ያለውም ዬኢትዮዽያ ልጅ በመሆኑ ለሃሳቡ፤ ለዕይታው፤ ለራዕዩ፤ ለፍላጎቱ፤ ለህሊና ብቃቱ፤ ለሙሉ አቅሙ፤ ለተለዬ ስሜቱ በመጠራቅቅ  ወይንም በጠላትነት በመፈረጅ ወይንም በመሰረዝ ወይንም ተቋርጦ እንዲቀር በማድረግ ወይንም ሰብዕናውን በማክሰል የማይዋከብበት መድረክ  ይኑረው። ዲስኩሩ ሁሉ ላም አለኝ በሰማይ ወተቷን የማላይ ነው ለእኔ ተጨባጩና ዕውነቱ ዬሚነግረኝ። ስደቱ ላይበቃው ተቆርቋሪ ሆኖ ሁለመናውን ለሚሰጥ ቅን እና ተቆርቋሪን ዜጋ ከወያኔ ሃርነት ትግራይ ባልተናነሰ ሁኔታ በቡድን ተደራጅቶ ሲያሳድዱ ተውሎ እዬታደረ የነገን ሁሉን አሳታፊ ሀገር ዴሞክራሲያዊ ኢትዮዽያንማሰብ ዬህልም እንጀራ ነው  – ለእኔ።

ዴሞክራሲ ለማንፌስቶ ለአደሩት ከተገኘ እነሱው – ያውቁታል። እኔ የማንፌስቶ ቤተኛ ስላልሆንኩ ሁነቱን አላውቀውም። ባለቤት ለሌላቸው፤ ዬማንፌስቶ አምላኪ መሆንን ላልፈቀዱ ሴቶች፤ ወጣቶች፤ ጸሐፍት፤ ከያንያን፤ ያልተማሩ ዜጎች ማህይም¡ የምንባለውን እኔን ጨምሮ“  ዬተማሩትም፤ ሃይማኖት ያላቸው ሆነ ዬሌላቸው፤ ዬህሊና አቅማቸው ብቁ ዬሆኑ ሙሁራን ወይንም የተለያዩ ሙያያት ሊቃናት፤ ከውጭ ዜጋ ጋር የተወለዱ የትውልደ – ኢትዮዽውያን ዬደም ዝርያ ያላቸው ሁሉ ሰብሳቢ፤ አስተዋሽ፤ ተቆርቋሪ ዬላቸውም።

ውጪ ሀገር ተወልደው የሚያድጉት የነገ ወርቅ አንባር ተስፋዎችን ህፃናትና ታዳጊ ወጣቶችንማ ቀድሞ ነገር ስለመፈጠራቸውም ሆነ ስለወደፊት ዬተስፋ ሀገራቸው ዬተዘለለ አምክንዮ ነው። ዛሬ ዬወያኔ ሃርነት ትግራይ ሥልጣን ላይ ቢኖርም፤  ለነገ የተስፋ ጉዞ ባለቤት እኔ ነኝ ዬሚል የወያኔ ሃርነት ትግራይ ተፎካካሪ ፖርቲ ሁሉ፤ ቢያንስ የድርሻውን መጀመር ያለበት ነገ ሳይሆን ዛሬ መሆን አለበት። አቦ ሌንጮ ለታ ሲዊዲን ህዝባዊ ስብሰባ ላይ የተናገሩት በኸረ ቁም ነገር ነበር ከዚህ ያላገኘሁትን ዴሞክራሲ ነገ አልጠብቀውም“  ዬሚል መልዕክት ነበረው – ዕድምታው። ዕውነት ነው። እኔም ይህን የሃቅ እንክብል እጋራዋለሁ።

ዴሞክራሲ ፈቅዶ ማግኘትና ፈቅዶ ማጣት ማለት ነው። የሌላውን አሸናፊ ሃሳብ ሲቀበሉት ደግሞ ተቀባዩ ፈቅዶ የሚያጣው ይኖረዋል፤ የሃሳብ አሸናፊ የሆነውም ቢሆን ፈቅዶ የራሱን አሸናፊ ሃሳብ ሲቀበለው ወደ ዬብዙኃን ኪዳናዊ  መንፈስ ይሁንታ ባለአደራ ይሆናል። የዴሞክራሲ ባለአደራነት ስክነትናን ሆደ ሰፊነትን ብቻ ሳይሆን፤ የህግ ተገዢነትን ውስጣዊ የሰብዕዊነት ባህሪን ይጠይቃል። ባለ ሚዛን መሆን። አሸናፊው – ለተሸናፊው ሃሳብ የበዛውን ፍቅር፤ አክብሮትና ዕውቅና መስጠትን ይጠይቃል። በቂ የባለቤትነት ሙሉ ስሜት ሊኖር ግድ ይላል – በማለት ሳይሆን በመሆን መክበር አለበት። ዴሞክራሲ የጓሮ መንገደኝነት አይደለምና። ገጥ – ለገጥ መከወን አለበት – ይሁንታው።  የነገረ ዲሞክራሲ መርህ ይሄው ነው፤ ማንዳለጥ ወይንም ማዳዳጥ የተፈጥሮው ተፃራሪዎች ናቸው። በሌላ በኩል አቅሙ ቢኖር ዴሞክራሲ ማለት ሰባዕዊነት ነው። ለሰውነት ህልውና አየር መስጠት። በጠላት ወረዳ ታጡ የሚባሉት ሁሉ ከስብዕነት ክብርና ልዕልና ጋር የተያያዙ ናቸው።

ዛሬ እኔ ውጪ ሀገር  እማዬው ዴሞክራሲ የጨዋታ ወይንም የዲስኩር ወይንም የንግግር  ማሟያ ብቻ ሆኖ ነው። ከአምና ከታች አምናው ፈቅ ያለ የተግባር ቡቃያ አልታየበትም። ዛሬም ማን ደፍሮን፤ ዛሬም ማን ተናግሮን እኛ የብጹዐን የተራራው ህግጋት ነን ነው። ይህ ደግሞ በዚህ ግሎባላይዜሽን ዘመን ቋት የማይገፋ ነው። ይልቁንም መታመንን ይሸረሽራል። ደንበር ሰራሽ መብት ክፍሉ አይደለም የዴሞክራሲ መርሁ። የዴሞክራሲ መርሁ ከጥሩ ተናጋሪነት ይልቅ ብቁ አድማጭነትና ድርጊተኝነትን ይጠይቃል። የታረመ ሙሉ ሥነ-ምግባርንም ይጠይቃል፤ ከላይ እስከታች ባለው መዋቅር ብቻ ሳይሆን አባላቱን በብቃት በመልካም ባህሬ ማነጽ ይጠይቃል፤ ህዝብ ለመምራት በተፎካካሪነት ከተሰለፉ። ስለዚህም ነው ጋራ – ለጋራ ማገናኘት ያልተቻለው ከመርሁ ጋር ውል የማሰሪያው ድፍረቱና ፈቃዱ ጭንጫማ በመሆኑ ነው።

ኢትዮዽያ ከላቀ ደረጃ ሊያደርሷት የሚችሉ ሊቀ – ሊቃናት ያሏት ዲታ ሀገር ናት። ግን በየት ታልፎ፤ ውጪ ሀገር እንዲደመጥ የሚፈለገው አመክንዮ ብቻ ነው „ነፃነት“ ያለው። እንዲደመጥ ዬማይፈለገው ደግሞ ካቴና ብቻ ሳይሆን በዘመቻ ውግዝ ከአርዮስ ነው። ዴሞክራሲ የሚሉን ይሄን ነው። በአፈና፤ በማሳደድ፤ በአድማ፤ በመቧደንና በማንፌስቶ ማህበርተኝነት ብቻ ዴሞክራሲ የሚገለጥ ከሆነ ለእኔ በአፍንጫየ ይውጣ። በዚህ ዘርፍ ለአብነት ዬሚጠቀስ ተቋም አለን ከማለት በሃሳብ ለጥንስስነት ቢታሰብ እንኳን እንደ መታደል – በተቆጠረ።  የዜጎቹ የሃሳብ ነፃነት ሲገፋና ሲገፈተር፤ ዜጎች በስደት ላይ ለሌላ ስደት ሲጋለጡ፤ ዬተስፋ ማጣት ህመምተኛ ቢሆኑ ባይሆኑ ጉዳዩ አይደለም ለዴሞክራሲ ነው የምታገለው የሚለው ድርጅት ሁሉ። ለመማት እንጂ ለማድመጥ ዬሚያቅድ – የሚቀድምም የለም። በየዘርፋ አቅም ያላቸው፤ ሞግተው የሚረቱ የፋክት ኃብታትን አንገት እያስደፉ እና እያዋከቡ ዴሞክራሲ ቢሉ ልግጫ ነው ለእኔ። ዴሞክራሲ የማይታይ የማይጨበጥ ረቂቅ መናፍስት አይደለም ወይንም በስማበለው ዬሚመለክበትም ጣኦት አይደለም።

ዴሞክራሲ የውስጥ ፈቃድን ይጠይቃል። በታሰረ ውስጥነት ዴሞክራሲ አይፈጠርም። በተዘጋ ቤት የቤቱን ውስጥ ውበት ሆነ ጉድለት ማየት አይቻልም። ዴሞክራሲ ጣዕሙ መራራውን ነገር አዳምጦ ወደ የጋራ ጣፋጭነት መስመር በመለወጥ „ከእኔ“ ከሚለው ዬግል ሃሳብ አውጥቶ „የእኛ የጋራችን“ እንዲሆን አስማምቶና አቻችሎ የሃሳቡን ህይወት ወይንም ነፍስ መልክ ሰጥቶ በመቅረጽ ህዝበ ጠቀም ማድረግ ነው። በተጨማሪም እንዲቀጥል ዬተፈቀደለት ሃሳብን በተሸናፊ ሃሳብ ላይ ተጫኝ እንዳይሆን በፈቃድዮሽ ዬሁሉዬሽ ዬማድረግ የሥልጡን አመራር የጥበብ ሂደት ነው። አሸናፊውን ሃሳብ በስምምነት ለሁሉም ጌጥ፤ ውበት ማድረግ ማለት ነው ለእኔ እስከሚገባኝ ድረስ። ስለሆነም የሃሳብን ምላጭ ወይንም ቃታ ያልደፈረ፤ የቀላሃ ጉዞውንም ይደፍረዋል ብየ አላስብም። ሃሳብን ያልደፈረ ባሩድን የሚደፍር ነፃነት ይኖራል ብዬም አላምንም!

በኢትዮዽያ ፖለቲካ እንደ ዕውነት እንደ ጦር ዬሚፈራ አመክንዮ የለም። ሃቅና ሃቅን አፋትጎ፤ አቅምና አቅምን ማጋባት ሲቻል፤ ሃሳብን በመሸሽ ከወያኔ ሃርነት ትግራይ አባልተኝነት ጋር ማዳበል ብላሽነት ነው – ለእኔ። በጣም ጥቂት በግለሰብ ደረጃ ያሉ ካልሆነ በስተቀር፤ ከወያኔ ጋር ሊሰሩ ያልፈቀዱ ድርጅቶች ሆኑ ግለሰቦች ጥቂቶች ናቸው፤ በመቀናጀት ሁነ በህብረት፤ በግንባር ይሁን በንቅናቄ – ሁሉም አብሮ ለመስራት ሞክሮታል። ሲበቃው በቃኝ ያለው ሁሉ በእኩል ሚዛን ሊለካ ሲገባ፤ አንዱ ዬነፃነት ትግሉ ቤተኛ ሌላው ደግሞ የእንጀራ ልጅ በማድረግ ነው ዬውጭ ሀገሩ ዴሞክራሲ ተክለ ሰውነቱን የሚገልጽልን።

ዴሞክራሲ በማንፌስቶ አምልኮ አይፈተንም ወይንም ዴሞክራሲ በቀለም ምርጫ አይመተርም። ዴሞክራሲ ሆኖ በማሳዬት ብቻ ይገለጣልተጨባጭ ነገር ነው – ነፍሱ። ግልጽነትና ቀጥተኝነት ነው – ትንፋሹ። ብቁ አድማጭነት ነውደሙ። ሰዎች በነፃነት ሃሳባቸውን ሲገልፁ ሊጎረብጥ አይገባም። ሰዎች በፈለጉትና ጊዜና ሁኔታ እንደራጃለን ቢሉ ደጅ ጥናት አይሻቸውም። ወቅትም ሊወሰንባቸው ወይንም ሊገደብባቸው አይገባም። የሀገር ባለድርሻነት እኩልነት ነው። የዜግነት እኩሌታነት የለም!

ሰዎች የመታገያ አርማቸውን ይሁን ዓላማና ተግባራቸውን በመግለጽ ሆነ በማስፋፋት ማዕቀብ ሊጣልባቸው አይገባም። ሰዎች ነኝም አይደለሁምም“ በሚሉት ዬህሊና ነፃነታቸው ላይ ማንም መብት የለውም- ለመሰረዝ ይሁን ለመደፍጠጥ። ይልቅ መልካሙ ነገር መፋትና መገለል የሚያመጡት ቀውሶች ከአቅም በላይ ሆነው እንዳይሄዱ ከተፈለግ – ደፋሩን ውይይት ማድረግ ብቻ ነው መፍትሄው። ዛሬ የዘውግ ነው። ነገ ዬሴቶች ማዕበል ይነሳል። ዬሴትነት ማንነት ደግሞ ከቤት ስለሚነሳ አደጋው ሰፊ ነው። ወንድምን፤ ትዳርን፤ አባትን፤ አጎትን፤ ያጠቃልላል። አሁን እኔ ድንቅ ዬሚባሉ ዬሴት ሊቃናትን በየትኛውም ሚዲያ ማዕቀብ እንደለባቸው አያለሁ። ይህ ለሴቶች ብቃት ዕውቅና ያለመስጠት ዕምቅ ቁስል አንድ ቀን ደግሞ feminism  ሊያፈነዳ ይችል ይሆናል። ቁስል ዕብጠቱ መተንፈሻ ካልሠሩለት መግሉን ካለፈሰሱት ትንፋሽ – አይሰበሰብም።

በዚህ ላይ ሁለት አንስቶችን ለናሙና ማንሳት እሻለሁ። በእኛ ትውልድና በቀደመው ትውልድ የእኔን የፆታ ማንነት በትክክል ይወክሉልኛል የምላቸውን። ዕንቋዋ ወጣት ብሎገሪስት ሶልያና ሽመልስ የሚገርም ብቃት ነው ያላት። እንዲያውም እኔ ሰማያዊ ዬተለዬ ጸጋም ያላት የዓይን አንጎል ሆና ነው ያገኘኋት። ተደምጣ የማትጠገብ፤ የሁለገብ ብቃት ትንታግ። ወጣት ጸሐፊ፤ ወጣት ጋዜጠኛ፤ ወጣት ሴት። ከየትኛውም አቅም አለኝ ከሚል ፖለቲከኛ በላይ በፋክት ላይ የተመሰረት ሙሉ አቅምና ሰብዕናን የታደለች ልዩ መክሊት ናት። እሷን በዲቤት ማሸነፍ የሚል አይመስለኝም። እያንዳንዱን ሀገራዊ አጀንዳ ማስተር አድርጋዋለች። ሳዳምጣት ልጄ ብትሆኝ ዋጥ አደርግሽ ነበር እላለሁ። ዬድንቅነት እመቤት። ለእሷስ እንኳንም አፌን ሞልቼ መሰከርኩላት።

ልባም ከሆኑ የኢትዮዽያ የፖለቲካ ሊቃናት፤ ለዛም ከተበቃ ግንባር ቀደም ተሟጋች መሆን ያለባት ጋዜጠኛ ሶሊያና ሽመልስ መሆን ይኖርባታል። ከእሷ ዘንድ የሚያመልጥ ምንም የወያኔ ሃርነት ትግራይ ሴራ አይኖርም። አንቀጽ በአንቀጽ ሞግታ ሴራውን የምትንደው በብቃቷ ዕውነትነት ይሆናል። ዕውነትም እንደ ሥሟ „ሽህ መልስ“ ናት! ይህቺ ዕንቡጥ ጽጌረዳ ክብራችን ናት! የራሷ ጌታ መሆኗ እራሱ አሸናፊነቷን ካለምንም ቅድመ ሁኔታ ያውጃል። ሁላችን በእኩልነት የመወከል ውስጥነት አላትና። አብሶ ለባለቤት አልቦሾቹ ለእኔና ለእኔ መሰሎች ዋቢያችን ናት። ድምፃችን ናት!

ሁለተኛዋ ከኢትዮዽያ ዬፖለቲካ ሊቀ – ሊቃናት ውስጥ ለሀገር መሪነትም በሙሉ ብቃትና በጉልህነት መፎካከር አቅም ያላቸው ዶር. አበባ ፈቃደ ናቸው። የኢትዮዽያ እናቶች ድምጽ አልባ ግን ለግዴታ መከረኞች ናቸው። ከ42 ዓመት በላይ አልቅሰዋል። መንፈሳቸው ተሰብሯል። ማህጸናቸው በአሳራቸው ብዛት አሯል። ሥነ – ልቦናቸው ደቋል። አስተዋሽ የላቸውም። ሰብሳቢ የላቸውም። ጉዳታቸውን የሚጋራ ሁነኛ የላቸውም። ለዚህ መዳህኒቱና ፈውሱ የፆታ አጋራቸው መድረኩን አግኝታ ድምፃቸውን ማሰማት ስትችል ብቻ ነው። ዕንባቸውን በቅርብ ተገኝታ – ተጋርታ በመሆን ስትደባብሳቸው ብቻ ነው፤ ያ የዘመናት ማድያት የለበሰው ውስጥ የሚፈወሰው። ለሌላውም ቢሆን ብልህነትና ልቅና፤ እናትነትና ርህርህና፤ አዛኝነትና ኃላፊነትን በመወጣት ለሴቶች የሚገድ አንዳችም ነገር የለም። እናትየ ለሁሉም ናት። ዥንጉርጉሩን እፍን ክብክብ አድርጋ የምትይዝ።

ስለሆነም ሁለቱም ለእኔ መድረክ ያላገኙ፤ አቅማቸው ዬተፈራ ግን ሁሉ ያላቸው ብቁ የሴቶች የድርጊት ፈርጦች  ናቸው። ዴሞክራሲው ካለ እስኪ ዬኢትዮዽያ ሴቶችን ያላባራ ዕንባ እና ስለወደፊቱ የኢትዮዽያ መልካም ራዕይ ድምፃችን እንዲያሰሙ መድረኩ እስኪ-  ይመቻች። እዚህ አሳዩን እስኪ – ስለ አምስት ፊደላት ጥምረት ቃል ዓመት ይዞ እስከ ዓመት ተመሳሳይ ነገር አድምጡ – ከምትሉን። ዬዴሞክራሲን የቃሉን ምት ብቻ በህልማችሁ ዳዊት ድገሙ፤ ድርሳኑን በምናብ አድርሱ ከምንባል። እስኪ ቀለሙን ቀዬር ለማድረግ ድፍረቱን እንይ። የአንድ ሀገር ዴሞክራሲ ልኩ ለሴቶች በሚሰጠው ዬነጻነት መጠን ወይንም በሚፈጥረው መጠራቅቅ ይወሰናል። ይሄ ሳይንስ ነው ለድድር የማይቀርብ።

ነጻ ሃሳብ – ብዕርና ብራና ተሸሽቶ የነገ የቀና ቀን ማሰብ አይቻልም – ራዕዩ የጉም ሽንት ነው የሚሆነው። አቅም ለማመንጨት አቅም ያላቸውን የማይመሳሰሉ ሃሳቦችን አፋጭቶ ብርሃን መፍጠር መቻል ነው ዬዴሞክራሲ ዶክተሪን። ዴሞክራሲ በትክክል ቢተገበር አቅም ሲሰበሰብ እንጂ በየጊዜው እንዲህ ሲናድ ባልታየ ነበር። አየር የሚፈልገው ሁሉ መተንፈሻውን ፍለጋ በሚያደርገው ጉዞ ከእጅ እያመለጠ ነው። ይህ ለፖለቲከኞች አይታያቸውም። ሚዲያዎችም ቢሆኑ ተከትሏቸው ፖለቲከኞችን እንጂ የተሻለ መስመርና አቅጣጫ ለመንደፍ አልቻሉም፤  ሚዲያ ስል  VOA  እና DW ይጨምራል። ምንአልባት ዬታሰሩበት ነገር ሊኖር ይችላል – በጠንቀኛው ዬፖለቲካ ማኒፌስቶ። ባለ አቅማቸውና ችሎታቸው ሃብታቸውን ጥቅም ላይ ለማዋል በተናጠል እንዳሉ ብቃቶች የእኔ የሚሉት የውስጥ ነፃነት ይኑራቸው አይኑራቸው የሚታወቅ ነገር የለም። ምክንያቱም የሚታይ አዲስ የዴሞክራሲ የመስፋት ሆነ የማደግ ሁኔታ አይታይም። ድግግሞሽ  ብቻ። በወርድምም በቁመትም እንደ አምናውና እንደ ታች አምናው ወርደ ጠባብ – ዘንድሮም።

ዬበሰለ ትንተናና አቅጣጫ አመልካች ሁነቶች በመፍጠር እረገድም ቢሆን አቅምና ችሎታ ያላቸው፤ ክህሎቱና ተመክሮው፤  የለማ መክሊት ያላቸውን ሊቃናት ዕውቀታቸውን በመጠቀም እረገድ ያላው ዝንባሌም ከፖለቲካዊ ፍላጎት ሊያመልጥ አልቻለም። ስለዚህም የህዝቡ ማህበራዊ ንቃተ ህሊና ከፖለቲካ መሪዎች ይልቅ ቀድሞና ልቆ መሪውን ተመሪ፤ ተመሪውን ደግሞ መሪ እያደረገው ነው ይህም የሚያሳየው የተወሰነ ሰው ብቻ ከአቅሙ በላይ  ሊያመጣው ዬሚችለው የለሌ መሆኑን ነው። ያልቃል ወይንም ይሰወራል።

ስም ማንሳት አልፈልግም አቶ „ለ“ ልበለው እንደ ህግ የትምህርት ክ/ ጊዜ ሥነ – ልቦና እንዳይጎዳ ስለምሻ አሁን አቶ ሁሴን ያሲን  የመሰለ ሊቅ እንዴት ባለ ሁኔታ የዛን መሰል ጮርቃ የአቶ „ለን“ ፖለቲካዊ ትንታኔ ታዳሚ የሚሆነው። በምን ስሌት? ፖለቲካዊ ሊቀ-  ሊቃውንታትን ገና ቆባ ላይ ያለን ጅምር አዳምጥ ብሎ ማሰብ ኢትዮዽያ ያላትን የሊቀ – ሊቃንት አቅም ከመናቅ ወይንም ካለማወቅ የሚመነጭ ይመስለኛል። እኔ ሊቀ – ሊቃውንቱን አቶ ሁሴን ያሲን ለናሙናነት አቀረብኩ እንጂ፤ ትውልዱን በተመክሮ ሊገነቡ የሚችሉ እጅግ በጣም ብዙ ሊቀ – ሊቃናት አሏት ኢትዮዽያ።

የሃሳብ ልዩነቱ ነው ለዴሞክራሲ ጌጡ፥ ውበቱ፤ ማርዳው፤ ዝባዱ። …. እና ? ዴሞክራሲ መቼ ነው ዬሚመጣው??? ወይንም ተሰማይ እንደ መና ለኢትዮዽውያን ዱብ የሚልልን ይሆን? … ከቅንጅት በፊት በነበረኝ የመደበኛ የጋዜጠኝነት ተግባራት በርካቶችን የፖለቲካ ሊቃናት በአካል አውቃቸዋለሁ። የሰከነ ሰብዕና ያላቸው፤ በምን ሁኔታ በዛ ወጣትነት ዕድሜ ለፕሮፌሰርነት ደረጃ እንደደረሱም ለማወቅ እስኪቸግር ድረስ ውስጣቸው ሰብል የሆኑ ሙሁራንንም ለመተዋወቅ ዕድሉ ነበረኝ። ህብረትን የመሰለ በርካታ ዬፖለቲካ ድርጅቶችን በወልዮሽ ያሰባሰበ ድርጅት ፈርጀ ብዙ የብቃት ማሳ እንደነበርም አውቃለሁ። ህብረት ዓለም ዓቀፍ የፖለቲካ ድርጅት ነው የነበረው። ኢትዮዽያን ጨምሮ በሁሉንም አህጉራት የነበሩትን የፖለቲካ ድርጅቶች ያቀፈ ነበር። ቀሪዎች ጥቂት ነበሩ።

ዛሬ በቆረጣ ይሁን በአለመታደል ዛሬ ሌላ ነው፤ መልክም ፎርም የለሽ ጠፍጣፋ ነገር። ሁለገብ ልምድና ተመክሮ ያላቸው ሊቃናትና ለትውልዱ ለማካፈል ዝግ መሆን  ያማል። ሚዛኑን የጠበቀ ግንዛቤ ለማፍለቅ ዛሬ ካልተቻለ ዴሞክራሲ ቃሉ ከወረቀት ነብርነት አያልፍም። ዴሞክራሲ ለፈቃጅና ለነሺ ሰጊድ ለኪ ዬሚል አመክንዮ አይለም። ዴሞክራሲ ዬህሊናን ነፃነት ሥራ ላይ ለመዋል ነፃነትን ካለ ተዕቅቦ የሚያጎናጽፍ የፖለቲካ ባህል ነው።

በዴሞክራሲ ባህል ውስጥ በመርህ መተዳደር እንጂ የጌታና የሎሌ፤ የምርጥ ዘርና የመናኛ ዘር ቤተኝነት የለም። በሁሉም የሚሠራው ስለሁሉም ይሠራል። በእኩልነት አሸናፊው ሃሳብ ተሸናፊውን ሃሳብ ተረግጦ ሳይሆን መንፈሱን ውስጡ አስርፆ በፍቅር ገብያ መገናኛ መስመር መዘርጋት ነው አስተምህሮቱ።

እኔ ፖለቲከኞች ዴሞክራሲ የሚሉትን ቃል ባይጠቀሙ ምንኛ ጥሩ በሆነ ነበር። በቃላት መንፈስን መግዛት አይቻልም። በህይወቱ እኮ እየተኖር ነው። የሌለውን እናመጣለን ባይሉን ይመረጣል። ባለቤት ለልለን ስደተኛ ዜጎች፤ ለማንፌስቶ ለማንገዛ በሃገራችን ጉዳይ እንደ እንጀራ ልጅ ለምንታይ ምንዱባኖች – ያቆስላል እራሱ በየስብሰባው ቃሉን መስማቱ። በየስብሰባው ሺ ሚሊዮን ጊዜ ዓላማችን „ዴሞክራሲያዊት ኢትዮዽያን መገንባት“ የሚለው ሸበላ መንፈስ ህሊና ውስጥ ለውጥ አምጥቶ ባለው ያለውን ለማካፈል አልተቻለም። የደመረው ነገር የለም። አክሽን ላይ አልተገኘም።

መጀመሪያ አቅሙ ካላችሁ በስደት ለሚሰቃየው ወገናችሁ በእጃችሁ ያለውን የዴሞክራሲ እንጀራ ለማካፈል ቸር ሁኑ። ኃላፊነት ማለት ሁሉንም በእኩል ማየት ነው። ይህን ደግሞ አልዘረጋችሁም።  ለመዘርጋትም ፈቃደኞች አይደላችሁም። ታዲያ እንዴት ተብሎ ይሆን 100,000,000 ሚሊዮን ህዝብ ዴሞክራሲ እንደ ጸበል ዕድሉ ቢኖር ኢትዮዽያ ውስጥ የሚረጨው። መቼስ 100,000,000 ሚሊዎን ህዝብ የፓርቲ ማኒፌስቶ አምላኪ አይሆን ነገር። አለመደገፍም መብት ነው አይደለም  እንኳንስ አባል መሆን።

ሙያቸውም ሆነ ሰብዕናቸው የማይፈቅድላቸውም አሉ ዬህግ ባለሙያዎች ሆኑ ጋዜጠኞች። በተጨማሪም እንደ እኔ ፈንገጥ ብለው የተፈጠሩም አሉ። ሁሎችም ዜጎች ናቸው። እትብቱ ዕውን የሀገር ልጅነት ከሆነ መሩሁም በዚህው መወራረድ አለብት። ሌላ ታፔላ ወይንም ማለያ ሳያስፈልገው። ውጪ ሀገር እኮ የፓርቲ ማኒፌስቶ አምላኪ አለመሆን መብት መሆኑ ቀርቶ ዜግነት የሚያስቀማ ፈሊጥ ወይንም ፍልጥ እኮ ነው። ብታውቁት ለህዝብ መብት ጥበቃ አደርጋለሁ የሚል የነፃነት ጉዞ በእርቦና በሲሶ ጉዞ አይታሰብም ነበር።

በዴሞክራሲ ትርጓሜ አያያዝ ሆነ አመራር አራዊታዊውን የወያኔ ሃርነትን ከማብጠልጠል በፊት፤ ወያኔ ሃርነት ትግራይን ሊያስተምር የሚችል የተግባር ቀበቶ ያስፈልጋል። ለጠራችሁት ስብሰባ ሄደን ስንት ዕንባ አፈሰን እንደምንመጣ ቤተሰቦቻችን ያውቃሉ። ተገፍተን፣ ባይታዋርነት ተሰምቶን ነው የምንመለሰው። ብዙ ዬኦሮሞ ወንድሞቼ ሁሉ ነገር „አማራ አማራ“ ይላል ይላሉ። ውስጤ በጣም ነው የሚያዝነው። አዎን! የሚያሸበርቀው በምወደው የኢትዮዽያ ሰንደቅ ዓላማ ነው። የስብሰባው ቋንቋ አማርኛ ነው። ግን ይህ መሆኑ የእኔን የፖለቲካ አቋምና የግል ውሳኔዬን የሚያከርና ዕውቅና የሚሰጥ አይደለም። ቢያንስ ሰው መሆኔን ቢያከብር ምንኛ ዕድለኛ በሆንኩ።

ዕውነት ለመናገር ስብሰባ እሄድ የነበረው ለቅጣት ነበር። ታምሜ ነው የምመለሰው። በገንዘቤ በሽታ ገዝቼ። ከእንግዲህ ግን አይሞከርም። ለሚሄዱትም አዝናለሁ። እንደ እኔ ባለቤት ለሌላቸውና ቤተኛ ላልሆኑት ማለቴ ነው። የሆነ ሆኖ የምንታገለው ለዲሞክራሲ ነው ማለቱ መብት ቢሆንም፤ መሬት ላይ ያለው ነገር ባዕድ ነው።

አለ ስለሚባለው ዴሞክራሲ ህይወቱን ከእነ አንጀት ጉበቱ ዘረጋግፈን ለምንፈትሸው ሆነ ሂደቱ ለሚገባን ምንም ነው። የፈሰሰ ነገር ነው። ምንአልባት የውስጥ ምሬቱ መርምሮ ከኖርንበት የገደል ማሚቶ ኩነት የማያዳግም እርምጃ ተወስዶ በደንበር፤ በክልል ያለው ፍረጃና ማሳደድ ተግ ብሎ ወደ የሚባልለት ዴሞክራሲ ሽግግሩ  ካለ ቅንነትን ለተስፋ ቀልበን – እንጠብቃለን። የእስከዛሬው ግን አልተደፈረመ።

ይከወን።

አንድ ፓርቲ በአባላት ምልመላ ወቅት ከቁስ ይልቅ የሰብዕና መለኪያ ቢኖረው መልካም ነው። አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ቢያንስ በየጊዜው የህዝብን ቅሬታ እያዳመጠ ሊያስተካክል፤ አባላቶቹን በሥነ-ምግባር ሊገራ ካልቻለ ኢትዮዽያዊ ማንዴላ ፕሮፌሰር ዶር መራራ ጉዲና እንዳሉት ውጪ ሀገርም መሪዎችን የሚባላ የነውጥ እንቅስቃሴ አውሎ አይቀሬ ነው!“  በገለልተኝነት ሙሉ ድጋፍ በመስጠት የኖረውም ቢሆን ጥረቱ ካላፈራ፤ ልቡን ቀርቶ ጀርባውንም ይነፍጋል። ሁሉም ሥልጣኑ ቢኖረው ምን ያደረግ ይሆን? መልስ ያላገኘ ሞጋች አመክንዮ!

ዴሞክራሲ ማለት ሰባዕዊነት ነው!

ዴሞክራሲ መነሻው ሆነ መድረሻው ለሰው ልጆች ሁሉ ሰብዕዊ ነፃነትን ማጎናጸፍ ነው!

መሸቢያ ጊዜ፤ እግዚአብሄር ይስጥልኝ።

 

 

 

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.