የማለዳ ወግ…ኢትዮ የሞት ፍርደኞች ” ነጻ ” ተብለዋል ፣ ይፈታሉም!- ነቢዩ ሲራክ

• የጅዳ ቆንስል ጉዳዩን ተከታትሎታል ፣ ይለቀቁ ዘንድ ጠይቋል
* ጉዳዩን በቅርብ የተከታተሉት ዲፕሎማት ይመሰገናሉ
* የጅዳ ቆንሰልም ድጋፍ እየሰጠ ነው ፣ ይበረታታል
የሁሴንና ጓደኞቹ የግድያ ወንጀል ጅዳ ፈይሰልያ በተባለ አካባቢ ሲከወን ከሀበሾች አልፎ ያንድ ሰሞን የሳውዲ መገናኛ ብዙሃን መነጋገሪያ ርዕስ ነበር ። ጉዳዩ ሲቦካ ፣ ሀበሾች ” ሳውዲ ወጣት ገደሉ! ” በሚል ከተናፈሰው መረጃ ጀርባ የነበረው እውነት ግን ሌላ ነበር ። ከስራ መጥተው በቤታቸው ውስጥ የነበሩ የሁሴን ቤተሰቦችን ለመዝረፍ የመጡ ሳውዲ ጎረምሳዎች ” ሸባቦች ” ከዝርፊያ አልፈው ሴቶችን እንድፈር ሲሉ አንባጓሮ ተነሳ። ወንዶችን ሴቶችን ለየብቻ ክፍል ውስጥ ዘግተው ስለት ይዘው ከመዝረፍ ወደ ሴቶችን መድፈር ሲያመሩ ነገር ተበላሸ ።
ሟች በያዘው ስለት እያስፈራራ እንደዘረፈ የሁሴንን ሚስት ሊደፍር ሲሞክር ሚስቱ ” ድረስልኝ ” ብላው ሁሴን ደረሰላት ፣ በጩቤ አስፈራርቶ ሊደፍር ይታገል የነበረውን ሳውዲ ጎረምሳ በያዘው ስለት ወግቶ ጣለው ። እናም ሁሴንና ጓደኞቹ ታፍሰው ዘብጥያ ወረዱ ።
ለአመታት በተደረገው ማጣራት ሁሴን በዋና ገዳይነት ፣ ወንድሙና ጓደኞቹ በተባባሪነት ወንጀል በሞት ፍርደኞች መካከል ሆነው ፍርዳቸውን ሲከታተሉ ከርመው ነበር። ከወራት በፊት ፍ/ቤቱ ባሳለፈው ውሳኔ እነ ሁሴን ሚስቱን ከመደፈር ለመከላከል ሲል በእጁ የሰው ህይዎት የጠፋበት ሁሴንና ጓደኞቹ በነጻ እንዲለቀቁ ወስኗል ። ሁሴንና ጓደኞቹ በጅዳ ቆንስል ጉዳያቸውን አስረጅ ጠበቃ አቆሞላቸው ክርክር ባይደረግላቸውም ከአንድ አመት ወዲህ ዲፕሎማት አቶ ያለለት በተደጋጋሚ ወደ ፍርድ ቤቱ በመሄድ ያደረጉትን ክትትል ሳላደንቅና ሳላመሰግን አላልፍም ።
” ነጻ ” ከተባሉ ወዲህ የጅዳ ቆንስል ሁሴንና ጓደኞቹን ዋስ በመሆን ካሉበት የብሪማን እስር ቤት ለማስወጣት ፍላጎቱን ለፍርድ ቤት ማቅረቡን ሰምቻለሁ ! ይህ ከዚህ ቀደም ያልነበረ ፣ ከአመት ወዲህ ያየነው ሊበረታታ የሚገባ ድጋፍ ነው ። እዚህ ላይ በተመሳሳይ ሁኔታ በሞት ፍርድ ተራ የሚጠብቁ ዜጎቻችን ሞልተው ተርፈዋል ። ተመሳሳይ ብቻ ሳይሆን ጠበቃ እስከመቅጠር የደረሰ ድጋፍ ሊደረግላቸው ይግባል ። ህጉ ገደለ ተብሎ ብቻ ይገደል እንደማይል የእነሁሴን ጉዳይ አስረጅ ይመስለኛል ። በተለያየ እጅግ ፈታኝ በሆነ የአእምሮ ፈተናና ጭርቀት ውስጥ ወድቀው ግድያ የፈጸሙ ዜጎች ቢያንስ ሊደመጡ ይገባል ። ፍርዱን ከግምት ውስጥ በማስገባት ወደ ወህኒ ጎራ በማለት ዜጎችን በማወያየትና በማማከር ቆንስልና የኢንባሲ መ/ቤቶች አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ለዜጎች ድጋፍ ያድርጉ ዘንድ ዛሬም እንማጸናለን ! ከታሳሪዎች ባለፈ በተለያየ ምክንያት ጉዳት ደርሶባቸውና ተሰናክለው በየሆስፒታሉ የሚገኙ ዜጎች ዛሬም በለቅሶ የመንግሰት ተወካዮችን ድጋፍ እየተማጸኑ ይገኛሉ ፣ እኒህም ዜጎች ናቸውና በዋናነት የመንግስት ተወካዮች መብታቸውን ከማስከበር ጀምሮ ወደ ሀገር ቤት እስከመላክ የደረሰ ድጋፍ በማድረግ ሊታደጓቸው ይገባል ! እኒህም ድምጻቸውን ሰሚ ያጡ ዜጎች ናቸውና !
ከሁሴን ጋር ያደረግኩት ቃለ ምልልስ እንደ አስፈላጊነቱ አቀርበዋለሁ!
ቸር ያሰማን !
ነቢዩ ሲራክ
የካቲት 1 ቀን 2009 ዓም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.