የዶክተር በያን አሶባ ጆኒያ ሙሉ ውሸትና ዘረኛ የፈጠራ ታሪክ

(አቻምየለህ ታምሩ)

ቀደም ሲል የኦነግና አሁን ደግሞ የኦዴግ አመራር አባል የሆኑት ዶክተር በያን አሶባ በቅርቡ በአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ የአማርኛው ክፍል ቀርበው በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ «አከራካሪ ጉዳዮች ዙሪያ» ከፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌና ከዶክተር ብርሀኑ መንግስቱ ጋር በጋዜጠኛ ትዝታ በላቸው አጋፋሪነት ተከራክረው ነበር።

ዶክተር በያን አሶባ ለኦነግና ሌሎች ተገንጣይ የዘር ድርጅቶች ትግል መነሾ የሆናቸውን «የብሄረሰብ ጭቆና» ያሉትን ዋና ማሳያ ሲገልጹ «የአጼ ምኒልክ ወረራ ሁለት ህዝቦችን ነው ኢትዮጵያ ውስጥ የፈጠረው፤ ለዚህ መረጃ የመጀመሪያው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ህገ መንግስት ሲሰራ፤ ኢትዮጵያዊ ማነው? ለሚለው ጥያቄ የመጀመሪያው አንቀጽ ነው መልስ የሰጠው። ያ ህገ መንግስት. . . ምንድን ነው የሚለው ኢትዮጵያ ከሁለት ህዝቦች ነው የምትመሰረተው፤ በእንግሊዝኛ ቋንቋ Natives ከሚባሉትና subjects የሚባሉት በጋራ ነው የኢትዮጵያን ህዝብ የሚመሰርቱት ይላል» ይላሉ።

ዶክተር በያን አሶባ ቀጠል አድርገው «በአንድ አገር ውስጥ Native የሚለውን National ወይንም ዜጋ እንበለው፤ subjects የምንላቸው ደግሞ ዜጋ ያልሆኑ ወይንም ከዜጋ ያነሰ መብት ያላቸው እንደማለት ነው።» ይላሉ። ከዚያም ከጓዶቻቸው ጋር ሆነው ኦነግን መስርተው ለመገንጠል እንዲታገሉ ያደረጋቸውን መነሾ ሲያስረዱ «ይሄ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ህዝቦች ከመንግስት ጋር ያላቸው ግንኙነት [ህገ መንግስቱ ዜጋ የሆነና ዜጋ ያልሆነ ይላል ያሉትን ማለታቸው ነው]፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ያላቸው status [ደረጃ] ነው የሚያታግለን» ሲሉ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ህዝቦች ስለመጨቆናቸው ማስረጃው የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ህገ መንግስት አንቀጽ አንድ መሆኑንና የሚያታግላቸውም ይህ ዜጋ «የሆኑና ዜጋ ያልሆኑ» በሚል በህገ መንግስቱ የዘፈረው ጉዳይ እንደሆነ የፈጠራ ታሪክ ደርተው እንደ ታሪካዊ ሰነድ ይጠቅሳሉ።

ዶክተር በያን አሶባ የህግ «ምሁር» እንደሆኑ በቃለ መጠይቁ መግቢያ ላይ ተጠቅሷል። ሆኖም ግን በኛ አገር የግራ ፖለቲከኞች ዘንድ «ምሁርነት» ማለት ለፖለቲካ መጠቀሚያ የሚንጠለጠል ማዕረግ እንጂ ማገናዘብን፣ ማመሳከርንና ማጣራትን፤ ደግሞ ደጋግሞ መፈተሽን አይጨምርም። በአገራችን የግራ ፖለቲከኞች ዘንድ ምሁርነት የእንጀራ መበያ ካባና የህዝብ ማታለያ ጭንብል እንጂ የእውነት ማጣሪያ ልቀት [የexcellence ደረጃ] አይደለም። ያገራችን የግራ ፖለቲከኛ ምሁራን እግራቸውን አስንተው ሲዋሹ፤ የፈጠራ ታሪክ እያመረቱና መጽሀፍ ሲደርቱ ለፖለቲካ እስከ ጠቀማቸው ድረስ የህሊናም ሆነ የሞያዊ ስነ ምንግባር ልጓም የላቸውም።

ዶክተር በያን አሶባና የትግል ጓዶቻቸው ኦነጋውያን ላለፉት አርባ ሁለት አመታት ኦነግን እየመሩ ሲታገሉና ሲያታግሉ፤ የውሸት ሮፓጋንዳ ሲሰሩ የኖሩት «የኢትዮጵያ የመጀመሪያው ህገ መንግስት የኢትዮጵያን ህዝቦች ዜናጋ ዜጋ ያልሆኑ በሚል ስለሚከፍል፤ ኦሮሞ በህገ መንግስቱ የዜግነት status ስላልተሰጠው፤ የራሳቸውን አገር መስርተን ኦሮሞ የዜግነት status እንዲኖረው እናድርግ» በሚል ነው። ሰው እየተማረ ሲሄድ በአስተሳሰብና በስብዕው ላይ የአመዛዛኝነትና የኃላፊነት ስሜት ነው አብሮ እያደገ ይሄዳል። በግራ ፖለቲካ ኩሸት የተፈጠሩት የአገራችን የዘር ፖለቲከኞች ግን እየተማሩ ሲሄዱ የሚያገኙትን የዶክተርነትና ፕሮፌሰርነት ማዕረግ የአመዛዛኝነታቸው መለኪያ ሳይሆን የፈጠራ ታሪካቸው ለማስረጽ የሚጠለቅ ክታብ አድርገው ያንሱበታል።

እስቲ ዶሴው ይውጣና እውነቱ ዶክተር በያን አሶባ ካሉት አኳያ ይታይ። በ1923 ዓ.ም. የጸደቀው የኢትዮጵያ የመጀመሪያው ህገ መንግስት አንቀጽ አንድ እንደሚከተለው ይነበባል. . .

«የኢትዮጵያ መሬት፡ ከወሰን እስከ ወሰን በሙሉ የንጉሰ ነገስት መንግስት ነው። በንጉሰ ነገስት ግዛር ውስጥ በዜግነት የሚኖር የኢትዮጵያ ተወላጅ ሁሉ ባንድነት የኢትዮጵያ ህዝብ ነው።»

ዶክተር በያን አሶባ በ1923 ዓ.ም. የጸደቀው የኢትዮጵያ የመጀመሪያው ህገ መንግስት የኢትዮጵያን ህዝብ «ዜጋ የሆኑና ዜጋ ያልሆኑ» ወይንም «Native እና Subject» ይላል ያሉት የሳቸውና የኦነግ ፍጹም ፈጠራ እንጂ በህገ መንስግቱ የመጀመሪያው አንቀጽ ላይ እንደዚያ የሚል አገላለጽ የለም።

እኔ የሚገርመኝ የተማሩ ተብለው ዶክተርና ፕሮፌሰር እየተባሉ የሚጠሩ ፖለቲከኞች ሲናገሩና ሲጽፉ፤ እንደ ወረደ የሚቀበል እንጂ እያንዳንዷን ነገር በአንክሮ የሚከታተል፤ የሚመለከትንና የሚናገሩትንም ሆነ የሚጽፉትን ነገር የሚፈትሽ፤ መረጃና ማስረጃ አገላብጦ እውነቱን የሚያወጣና የሚሞግታቸው ሰው የሚኖር አይመስላቸውም።

እነዚህ የውሽት ታሪክ እየፈጠሩ የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ የሚሰሩ የዘር ፖለቲከኞች እስከ ዛሬ ድረስ እግራቸውን እያነሱ ለተከታዮቻቸው ሲዋሿቸውና ሲያታልሏቸው ሲኖሩ ከተከታዮቻቸው መካከል አንድም ሰው ተነስቶ እንደሚንቋቸውና እንዴት እንደደብ እንደሚዩዋቸው ተገንዝቦ ሲያጋልጣቸው አለማየቴ ሁል ጊዜ ይደንቀኛል።

ዶክተር በያን አሶባ እንደነገሩን ከትግል አጋሮቻቸው ጋር ሆነው ኦነግን መስርተው እንዲታገሉ ያስገደዳቸው በ1923 ዓ.ም. በአማርኛ ተጽፎ የጸደቀው የኢትዮጵያ የመጀመሪያው ህገ መንግስት የመጀመሪያው አንቀጽ ላይ የኢትዮጵያን ህዝብ «ዜጋ የሆነና ዜጋ ያልሆነ» ተብሎ «መለያየቱ» ነበር ካሉንና ከዚህ ሁኔታ ለመውጣት መፍትሔው የኦሮሞን ነጻ አገር መስርተው በአዲሱ አገር ውስጥ ኦሮሞን ዜጋ ለማድረግ መታገል ነው» ብለው ህዝቡን ካደረጁና ካታገሉ፤ « የትግላችን መንስዔ ነው» በማለት በ1923 ዓ.ም. የጸደቀው «የኢትዮጵያ የመጀመሪያው ህገ መንግስት የኢትዮጵያን ህዝብ «ዜጋ የሆኑና ዜጋ ያልሆኑ» ወይንም «Native እና Subject» ይከፍላል ያሉት ያልተጻፈ፣ ያልነበረና ደረቅ የፈጠራ ክስ ከሆነ ኦነግ የኦሮሞን መንግስት ለመመስረት የታገለው ራሱ በፈጠረው የውሸት ትርክት ላይ ተመስርቶ ነው ማለት ነው። የዶክተር በያን ንግግር በማስረጃ ሲፈተሽ የምንደርስበት ድምዳሜ ቢኖር ይህ ብቻ ነው።

ከታች ከታተመው በ1923 ዓ.ም. የጸደቀው የኢትዮጵያ የመጀመሪያው ህገ መንግስት ማየት እንደሚቻለው አንቀጽ አንድ ዶክተር በያን አሶባ እንደሚሉት የኢትዮጵያ ህዝብ «ዜጋ የሆኑና ዜጋ ያልሆኑ» ወይንም «Native እና Subject» ተብሎ አልተከፈለም።

የሌላ ታሪክ ፈጥሮ የኢትዮጵያ የመጀመሪያው ህገ መንግስት የኢትዮጵያን ህዝብ «ዜጋ የሆኑና ዜጋ ያልሆኑ» ወይንም «Native እና Subject» ይላል በማለት በፈጠራ ክስ አንድ ህዝብ ማታለልና መዋሸት የሚያሳየው ነገር ቢኖር ኦነጋውያን ለሚዋሹት ህዝብ ያላቸውን ንቀት ብቻ ነው። አንድ ህዝብን የሚያከብር ድርጅት ህዝብን አይዋሽም! ኦነግ ግን ያልተጻፈ የህገ መንግስት አንቀጽ እንደተጻፈ በማስመሰል በልብ ወለድ ፈጠራ ««የኢትዮጵያ የመጀመሪያው ህገ መንግስት የኢትዮጵያን ህዝቦች ዜናጋ ዜጋ ያልሆኑ በሚል የኢትዮጵያን ህዝብ ይከፍለዋል» ሲል ትውልዶችን አታሏል፤ አገርም አፍርሷል።
የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ህገ መንግስት ዶክተር በያን አሶባ እንደሚሉት ሳይሆን የኢትዮጵያን ህዝብ ሁሉ የአንድ ቤተሰብ እኩል ዜጋ ከማድረጉ ባሻገር ኦነግ ባወጣው የመሬት ላራሹ አዋጅ የመሬት ባለቤትነት መብቱ ተነጥቆ የደርግና የወያኔ ጭሰኛ ከመሆኑ በፊት የኢትዮጵያን ገበሬ የግል የመሬት ባለቤትነት ያረጋገጠና በኢትዮጵያ ታሪክ ከተጻፉት ህገ መንግስቶቹ ሁሉ በተራማጅነቱ ታይቶ የማይታወቅ ህገ መንግስት ነበር።

እነ ዶክተር በያን አሶባ ግን ሁለት ጸጉር አብቅለው፤ በዲግሪ ላይ ዲግሪ ደርበው፤ የሰሩትን ደባና ያጠፉትን ጥፋት ለመሸፈን ሲሉ ብቻ ንግግራቸውንና ጽሁፋቸውን የሚመረምር ሰው ያለ ስለማይመስላቸው ከ42 ዓመታት በፊት አጀንዳ ያላቸው ላላዋቂዎች የፈጠሩትንና በሐሰት የመሰረቱትን የፈጠራ ክስ አሁንም እያመነዠኩ ሲዋሹት የኖሩትን ትውልድ እንደ ጴጥሮስ ደግመው ደጋግመው ዛሬም ይክዱታል፣ ያታልሉታል፣ ይንቁታል፤ ክብር እንደሌላቸው በአደባባይ ያሳዩታል።

ዶክተር በያን አሶባና ድርጅታቸው ኦነግ የኢትዮጵያ የመጀመሪያው ህገ መንግስት የኢትዮጵያን ህዝብ «ዜጋ የሆኑና ዜጋ ያልሆኑ» ወይንም «Native እና Subject» ሲል ይከፍላል በማለት የፈጠሩትን የኃጢያት ክስ አንባቢ ያገናዝብ ዘንድ በእጄ ያለውን በ1923 ዓ.ም. የጸደቀው የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ህገ መንግስት ኦሪጅናል የአማርኛ ቅጂ የመጀመሪያ አንቀጽ «ኢትዮጵያዊ ማነው?» ለሚለው ጥያቄ የህገ መንግስቱን መልስ ወረድ ብዬ ባተምሁት የህገ መንግቱ የመጀመሪያ ገጽ ላይ በቀይ መስመር አስምሬበታለሁ። ይህንን የተሰመረበት የመጀመሪያ አንቀጽ ነው እንግዲህ ዶክተር በያን አሶባ « የኢትዮጵያ የመጀመሪያው ህገ መንግስት የኢትዮጵያን ህዝብ «ዜጋ የሆኑና ዜጋ ያልሆኑ» ወይንም «Native እና Subject» ይላል፤ የታገልነውም በዚህ ምክንያት ነው» ሲሉ የታገሉት በውሸት ታሪክ እንደሆነ በአደባባይ ራሳቸውን የሚያጋልጡት።

ገራሚው ነገርኮ የያ ትውልድ የግራ ፖለቲከኞች ዛሬም ድረስ ባልፉት 42 ዓመታት የፈጠሯቸውን የሀጢያት ታሪኮች መመርመር አለመጀመራቸው ነው። ምናልባት እንዲህ ዶሴው ሲገለጥ ዶክተርነታቸው ከብዷቸው የፈጠሩት የውሸት ታሪክ ፍጹም ልብ ወለድ እንደሆነ ተገንዝበው ለስህተታቸው ትውልዱን ይቅርታ በመጠየቅ ረገድ ዶክተር በያን አሶባ የመጀመሪያው ይሆኑ ይሆን?ሲሆን ለመስማትና ለማየት ያብቃን!

ዶክተር በያን አሶባ በንግግራቸው የተናገሯቸውን ሌሎች የኦነግ የፈጠራ ትርክቶች ወደፊት በማስረጃ ታግዘን በምናቀርባቸው ጽሁፎች እንመለሰባቸዋለን።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.