የኦሮሞ እና የአማራ የዘር ምንጭ ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳን ለምን አስጨነቃቸው!? – ከተስፋዬ ባልቻ

ከተስፋዬ  ባልቻ
ብሬመን፣ ጀርመን

“የኦሮሞ እና የአማራ እውነተኛው የዘር ምንጭ” በሚል ስያሜ ለገበያ የበቃዉን መጽሐፍ እና ከዚያም ይህንኑ መጽሐፍ ካነበቡ የታሪክ ተመራማሪዎችና መሁራን እንዲሁም ሌሎች አንባብያን ያቀረቡትን ጽሑፎች በትኩረከት ተከታትያለሁ። በተለይም የኢትዮጵያ ታሪክ ጽሑፍ ውስጥ ስማቸው የማይዘነጉትን ከሌሉ የመጽሐፉ አንባቢያን ለምን እንዳልተጠቀሱም ብሎ ራሱን የሚጠይቅበት ሁኔታ እንዳለ የታሪክ አንባቢያን ያውቃሉ። ከነዚህ የታሪክና የቋንቋ ተመራማሪዎች እንዲሁም ሌሎችም ሙሑራኖች ከላይ የተጠቀሰዉን መጽሐፍ መርምረው መጽሐፉ ውስጥ ያገኟቸውን በቁጥር ከፍ ያሉ ስህተቶችንና የመረጃ ጐደለቶችን አስመልክቶ ለደራሲው በርከት ያሉ ጥያቄዎችንና የጉድለት ዝርዝሮችን በሥርዓቱ ለደራሲው ዘርዝረው ገልጸዋል። ደራሲው ከአንባብያን ላገኙቸው ትችቶችና እርምቶች እንዲሁም አስተያየቶች አመስግነው ለመጽሐፉ ዕርምታ ወደፊት ሊጠቀሙበት ሲችሉና ለደረሷቸውም ጥያቄዎች መልስ መስጠት ሲገባቸው፣ ተቺዎቹን በንትርክና ጭብጥ በሌለው አሉ-ባልታ ገጥመዋቸዋል። ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ መጽሐፋቸውን ሀ ብለው ሲጀምሩ፣ የኢትዮጵያ ሙሑራን ተብየዎች የውጭ ሙሑራን በኢትዮጰያ ባላቸው የተዛባ አስተያየትና የግንዛቤ ጉድለት የታነፁ በመሆናቸው ስለ ሀገራቸው እና ስለ ሕዝባቸው በተሳሳተ እምነት የታነጹና የሚመሩ ሲሉ ይነቅፏቸዋል። ስለዚህም ሀገራችንን ለማወቅና ትክክለኛ ማንነታችንን ለመገንዘብ ጥናት ማካሄድ ይኖርብናል ይሉናል። በመሆኑም ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ የኢትዮጵያን ታሪክ ለአራት አንዳንዴም ለአምስት አመት መርምሬአለሁ፣ የኢትዮጵያን ታሪክ እስከ 3500 ዓመታት አለያም 5500 ዓመታት ወደ ኋላ ዘርግተው የገዢዎችን የአስተዳዳር ዘዴና “ጥበብ” ዘርዝሮ የኢትዮጵያ/ኢትዮፒ ግዛት ከየት የት ይደርስ እንደነበር ዘርግተውልናል። አንባቢያንን እውነተኛ ታሪካችሁ ጠርቶ እንዲታያችሁ ፓውዛ አብርቼላችኋለሁ ያሉ ይመስላሉ። መጽሐፉ ላይ ባለው የመረጃ ጉድለትና በተለይም የታሪክ ባለሙያዎች ባቀረቡት በርካታ ጉደለቶች፣ ደራሲው የተነሱበት ዓላማ ላይ አለመድረሳቸውን ዝርዝር በቀረቡት ትችቶች መጽሐፉን በታሪክ መጽሐፍነት  ለመቀበል ያለኝን መቆጠብ ሊቀንሰው አልቻለም። ከዚህ አንፃር ደራሲው ለኢትዮጵያ ታሪክ ግንዛቤ፣ እንኳን ፓውዛ ኩራዝ አብርቷል ለማለት አያስደፍርም እላለሁ።

በተመሳሳይ ከአምስት እና ከስድስት ሳምንታት በፊት ስለዚሁ መጽሐፉ የተገነዘብኩትን እንዲሁም የተሰማኝን፣ ለአንባብያን ለመግለጽ ኢትዮሜዲያ ላይ ጽሑፌን አቅርቤ ነበር። ዛሬ ግን የተነሳሁበት፣ መጽሐፉ ምክንያት ቢሆነኝም ዋናው ትኩረቴ ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ በመጽሐፋቸው ተቺዎች ላይ የሚያደርሱትን የቃላት ግድፈት ሳነብና ስሰማ የተሰማኝን፣ ብሎም ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ እራሳቸውን ለማስተዋወቅ በመጽሐፋቸውና እንዲሁም በሌላ ዜዴዎች የሚያሰራጯቸውን መልክቶች ከብዙው በጥቂቱ ላይ ላቶኩር ሲሆን፣ በተለይ ደግሞ የኢትዮጵያ “ታሪክ” በባዕዳንና በብሔር ድርጅቶች ደጋፊዎች ትብብር ሲታነፅና ሲቀረጽ በወቅቱ ለምን  ደራሲው እንደ አልቆረቆራቸውና እንደ አላመማቸው ለመጠየቅ ነው።በተጨማሪም ከጊዜ ወደ ጊዜ በተለያዩ የሶሻል ሚድያዎች የሚሰጧቸውን ከእውነት የራቁ መረጃዎች ስላሳሰበኝ፣ ለአድማጮችና ለአንባብያን እውነታውን ለማስገንዘብ ነው፡፡ በተለይ አሁን አሁን ከፍተኛ ትምህርት ተምረናል በሚሉና የዶክትሬት እና የፕሮፌሰር ማዕረጋቸውን እንደሽፋን በመጠቀም የራሳቸውን ፍላጎት (የፖለቲካ ዓላማም ሊሆን ይችላል) ለማሳካት የሚጥሩ ግለሰቦችን መመልከት እየተለመደ ስለመጣ የታሪክ ተመራማሪ ወይም ባለሙያ ባልሆንም እንደ አንድ የአትዮጵያ ትውልድ ለአገሩና ለታሪኳ እንደሚቆረቆር ዜጋ በግሌ የተሰማኝን አስተያየት ለመስጠት እና አንባብያን የራሳቸውን ግንዛቤ እንዲዎስዱ የተወሰኑ መረጃዎችን ለመስጠት ነው፡፡

 

ለምን የኦሮሞና  የአማራ ሕዝቦች ዝምድና ዛሬ ለጥያቄ ቀረበ?

ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ የኦሮሞና የአማራ ሕዝቦች ወንድማማችነት/እህትማማችነት ትዝ ሲላቸው ለምን እነዚህ ሕዝቦች እሳቸው በዘረጉላቸው “የታሪክ” ዘመናት እናም አስተዳደር እንዴት ይኖሩ እንደነበረ፣ አስተዳዳሩ በነሱ ሕይወት ምንስ ሚና ተጯውቶአል፣ ምንስ አይነት ስኬትን፣ ምቾትን፣ ዕውቀትን ወዘተ አጐናጽፏቸዋል? ከዚህስ ዘልቆ ዛሬ ምን ላይ ተደርሶአል? ገዢዎች በሕዝብ ላይ  ያደረሱትንና የሚያደርሱትን ግድያ፣ እስራት፣ መሰደድ፣ ርሃብ፣ ወዘተ በምን ያህል ቀነሰ ወይም ጨመረ የሚሉትን የምርምር ትኩረታቸው ቢዘረጉ ኖሮ ምን ያህል ባስተማሩን ነበር። ኦሮሞና አማራ ከአንድ ቤተሰብ ተወለዱ ወንድማማቾች ናቸው ሲሉን፣ በቀላሉ የተቀበሉትና በጐ ሀሳብ ነው ብለው እምነታቸዉን ለደራሲው የለገሱዋቸው፣ የነዚህን ወንድማማች ሕዝቦች እናትና አባት ብሎም የትውልድ ቦታቸውም  ተረት ተረት ቢመስልም ወንድማማችነታቸውን እሳቸውም ሆኑ ሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝበች ለዘመናት አብረው በመኖራቸው መዛመዳቸው የሚካድ አይመስለኝም። በተረጋገጠው የታሪክ ዘመናት (3000 ዓመታት) ውስጥ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብሮ በመኖሩ በጋብቻ ተዋልዶ፣ ባሕሉን ተወራርሶ፣ በማሕበራዊ ኑሮው ተሳስሮ፣ ጠላት ሲያጠቃው ለነፃነቱ በጋራ ታግሎና ታጋድሎ፣ በፅናት ተቆራኝቶ ለዘመናት አንዱ ትውልድ ለመጭው ትውልድ አስተላልፎአል። አንዱ ወገን ሌላዉን ወገን የተዋጋበትና በቅኝ ግዛት የያዘበትና ያስተዳደረበት ጊዜ በኢትዮጵያ ነበር፣ ብሎ በአስተማማኝ ማስረጃና መረጃ ሕዝብ አውቆት፣ ተወያይቶበት፣ የስነልቦና ውሳኔ የወሰደበት ጊዜ የለም። ቢጠቀስ እንኳ ፍርድ በመጓደሉ ገዢዎችና ባለሥልጣናት የግል ፍላጎታቸውን ለማራመድና ለማስፋፋት ወይም ለዘረፋ የአንድን አካባቢ ሕዝብ ወግተውታል አፈናቅለውታል፣ ነገር ግን አንዱ ሕዝብ ተነስቶ ሌላውን ሕዝብ ወግቶ የገዛበት ጊዜ ነበር፣ ለማለት አያስደፍርም። በማንኛውም ጊዜ አብዛኛው የሕዝብ ክፍል፣ ለምሳሌ አማራ ኦሮሞን፣ ወይም በተገላቢጦሽ ኦሮሞ አማራን ይጠላል፤ አማራ ትግሬን ይጠላል ብባል ስህተትና ሀሰት ነው። ስለዚህ ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ የተነሱበት ሃሳብ መሠረተ ቢስ ነው ብል ስህተት አይሆንም። እንዲያውም ሰሞኑን ይባስ ብለውም የጻፍኩት መጽሐፍ ሰላምና ፍቅርን እያስፋፋ ነው፣ የሚለው የድፍረታቸው ከእውነት የራቀ ባዶ ቃላቶችን እያሰራጩ መሆኑን እንገነዘባለን። ለመሆኑ ጎንደር ላይ  የኦሮሞ ደም የኔም ደም ነው፣ የተባለውንና በኦሮሚያ ውስጥም የአማራ ደም የኔም ደም ነው የተባለውን፣ እሱ ጆሮ አልደረሰም ማለት ነውን? ምናልባት አማሮች ከኦሮሞ እና ከደቡብ ሕዝቦች አካባቢ ተዘርፈው እና ተገፍተው እንዲወጡ ለተገደዱበት የአስተዳደርና የፍትህ ጉድለትን ሽፋን ሰጥቶ ባለስልጣኖችን ከተጠያቂነት ነፃ ሊያደርጓቸው ይሆን? ወይንስ የኦሮሞና የደቡብ ሕዝቦች ከአማራ ሕዝብ ጋር ያለውን ወንድማማችነት ዘንግተው ወግቶ አባረራቸው ሊሉን ይሆን? ወይስ የሳቸው መጽሐፍ ከመውጣቱ በፊት፣ በመሀላቸው ባለው ጥላቻ ይጋደሉ ነበር ሊለን ነው?

የታሪክ ተመራማሪዎችና ሌሎችም ሙሁራኖች በደራሲው መጽሐፍ ላይ በደረሱበት ድምዳሜና ባገኙት በርካታ ስህተቶች የመጽሐፉን ይዘት ከተረት ተረት ወይም ከሚት (myth) አልፎ መጽሐፉ የታሪክነት ይዘትን ተቀባይነትን አሁንም አላገኘም። ይህንን ደራሲው መቀበል እንደ ተሳናቸውና በተለያዩ ዘዴዎች በግለሰቦች ላይ የሚያሰራጩትን አላስፈላጊ ቃላቶች፣ ለሰሚና ለአንባቢያን በጣም የሚከብዱ ናቸው። እኔም ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳን ጀርመን በኖሩበት ወቅት ስለ ማውቃቸው፣ አሜሪካ ከገቡም በኋላ አልፎ አልፎ በሚናገሯቸውና በሚጽፏቸው ስለምገረም፣ አሁንም ደግሞ በዚህ አነጋጋሪ በሆነው መጽሐፋቸው ምክንያት ያነበብኩትና የሰማሁት ስለከበደኝ፣ በተለይም መነጋገሪያው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ አገራችን እና ታሪካችን በመሆናቸው፣ ታዝቤ ማለፍ ባለመቻሌ ዛሬ ደግሞ ይህንን ጽሑፍ ለአንባቢያንና ለዶ/ር ፍቅሬ እንድጽፍ ግድ ብሎኛል።

 

በደራሲው መጽሐፍ ዙሪያ የተዋስዖ ሂደት ምን ይመስላል?

የተለያዩ አንባቢያንና ታዛቢያን በመጽሐፉ ላይ ስለሚካሄደው የቃላት ልውውጥ የተከፉና ያዘኑ መሆናቸውን በተለያዩ መንገዶች ይገልጻሉ፣ ይህን አስመልክቶ ተዋናይዮችን ከቃላቶቻቸው  እንዲቆጠቡ በጽሑፍ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል። ይህንን ጥሪ ተከትለውም ባሁኑ ጊዜ ከደራሲው ጋር የነበራቸውን የምሑራዊ ተዋስዖ (discourse) ሂደቱን ያቋረጡ አሉ። ነገር ግን ይህ ጥሪ ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ ጋ አለመድረሱን በቅርቡ ደራሲው ለፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ በጻፉላቸው ደብዳቤና እንዲሁም ”በመሬት ኢትዮጵያ እስራኤል ድምፅ” ሬዲዮ ላይ በተካሄደው ቃለመጠየቅ፣ ደረሲው ለጥሪው ጆሮ እንዳልሰጡና በተለይም ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌን እና ፕሮፌሰር ጳውሎስን አስመልክቶ በማይጥሙና አስከፊ ቃላቶችን እንደተለመደው በመጠቀም ሀሳባቸውን ማንሸራሸራቸውን ቀጥለውበታል። ይህን ከአንድ የስነጽሑፍ ምሁር ነኝ ባይ፣ በማሕበራዊ ሳይንስ ትምሕርትና ምርመር ሥራ አካሄዳለሁ ከሚሉ ሰው የማይጠበቅ ነው። ለምሳሌ ስለ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ የጻፉላቸውን ሁለት ደብዳቤዎች ስንመለከት የሚሰነዝሯቸው ቃላቶች በጣም ያስከፋል፤ ያሳዝናል። ደራሲው ስለ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ እንደ መጣላቸው ብዙ ብለዋል። ነገር ግን በምንም መስፈርት ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ በነዚህ ቃላቶችና አመለካከቶች የሚታዩና የሚገመቱ ሰው አይደሉም። ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ የዕውቀታቸው ሥፋትና ጥልቀት፣ ያካበቱት የሥራ ልምድ እና ግንዛቤ፣ በአገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ አዋቂዎችና ተደናቂዎች ተርታ የሚያስጠራቸው ብቻ ሳይሆን በዓለምም ደረጃ የተመሰከረላቸው ሰው መሆናቸው ይታወቃል። በምርምር ሥራቸው፣ ስለ ሃገራችን፣ ስለ ቋንቋችን፣ ስለ ኢትዮጵያ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንም ያበረከቱት አስተዋጿ ለአሁኑ ትውልድ ብቻ ሳይሆን ለመጭውም ትውልድ የሚዘልቅ ነው። ለኢትዮጵያ የሚሰጡት ትኩረትና ፍቅር እንዲሁም ለረዥም ጊዜ በሀገራችን የለውጥ ጥረት ላይ ያላቸው ተካፍሎ ያደረጉትን  አሰተዋፆ አንተ ማን ነህ፤ ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር የወገንክ ነህ፣ ተብለው አያስፈርጃቸውም፤ የሚያውቋቸው በጥሩ ሥራቸውና ድርጊታቸው ይወዷቸዋል፤ ያከብሯቸዋል። በሞያ ውጤታቸው ብቻ ሳይሆነ የሕይወትን ውጣ ውረድም እስከ ዛሬ አሳክተው  የዕድሜ ባለፀጋነታቸውም በምሳሌነት ከሚጠቀሱት ተርታ ይውላሉ። ይህንን ከግል አድናቆቴ ባሻገር ከባሕላችንም ወንድማዊ አክብሮት ደንብ ቦታ የሚሰጠው ነው።

ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ የደራሲውን መጽሐፍ ከታሪክ መረጃ፣ ብሎም ከቃላት ትርጉም ጥራት ጉድለቱ አንፃር መርምረው ሙሑራዊ ትችታቸውን ለደረሲውና ለአነባቢያን ጠቁመዋል። እነዚህንም ጉድለቶች ለማስወገድ ደራሲው በመጽሐፋቸው ወስጥ ለእርማት  ያገለግሏቸው ዘንድ ምክርም ለግሰዋቸዋል። በተለይም ደራሲው በዋናነት የተጠቀሙበትን የመሪራስ አማን በላይን ግኝቶችን አስፈላጊውን ምርመራ ለማድረግ ፈቃደኝነታቸውን ገልፀውላቸዋል። ነገሩ ባጭሩ ይሄ ሁኖ ሣለ ከደራሲው በኩል የሚደርስባቸው፣ ነቀፌታዎችና ውንጀላዎች እንደቀጠሉ ናቸው።

ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ በተመሳሳይ መንገድ ፕሮፌሰር ጳውሎስ መልኪሳንም መጽሐፋቸውን ስለ ተቹና ለታሪክ መጽሐፍነት፣ ማረጋገጫ በርከት ያሉ መረጃዎችን ስለጠየቁ እና መጽሐፉ ባለበት ሁኔታ ለትምህርትም ሆነ ለምርምር ሥራ ለማገልገል ብቃት የሚጎለው፣ መሆኑን ገለጸው፣ ቀጥሎም መጽሐፉ ያለ እርማት፣ ለአገልግሎት ቢውል የሚያስከትለው ጉዳት ከፍ ያለ መሆኑን፣ በዝርዝር አብራርተው፣ ደራሲው ያለባቸውን ሀላፊነት ይወጡ ዘንድ በአጽኖት አስገንዝበዋል። ከዚህም ሌላ ደራሲው በምርምር ሥራቸው የሳይንሳዊ አሠራርን ደንብ እነዳልተከተሉ ያመላክታሉ።

በተጨማሪም በዚህ ላይ ሳልጠቅስ ማለፍ የማልፈልገው የዶ/ር ከፍያለው አባተን ጽሑፍ ሲሆን፣ ያገኙትን ጉድለቶች ዘርዝረው፣ ለአንባቢያን የደራሲውን መነሻና መድረሻ እንዲገነዘቡ ዋና ዋና ፍሬ ነገሮችን በሳይንሣዊ መንገድ እንዲረዱና እንዲከታተሉ፣ በምሳሌዎች አብራርተዋል። በዚህ ሂደታቸው የደራሲዉን በጐ ሃሳብ ያሰምሩበታል። ሆኖም፣ ተቀባይነት ያገኘ ታሪክን ለመሻር የሚያጠራጥሩትን ሌላ አማራጭ ማስረጃ ከደራሲው መቅረብ ያስፈልገዋል፣ ሲሉ ትችታቸዉን ደምድመው፣  ከብዙ ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል ብለው አራት አንኳር ናቸው ያሉትን ነጥቦችን በዝርዝር አቅርበዋል። ዶ/ር ከፍያለው አባተ የዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳን ድምዳሜና መረጃዎች ለመቀበልና ለመከተል ቢያስቸግራቸውም፣ በትዕግሥትና በጥሞና ደራሲው ውጤቴ ነው የሚሉትን በርካታ ጥያቄዎችን ሰንዝረውባቸዋል።

ከላይ ከተጠቀሱት ሙሁሮች ባሸገር ሌሎችም በመጽሐፉ ላይ ያገኙትን ጉድለቶች አውጥተው እንዲሁም የመጽሐፉን የጥራት ጉድለት አስመልክተው በዝርዝር ጽፈዋል። በተለይ ፕሮፌሰር ባይሩ ተፍላ የደራሲውን የአማራና የኦሮሞ ታሪክ መነሻ ያደረጉትን ታሪክ (theory) ለመጽሐፉ መሠረት የማይሰጥ መሆኑን አስመልክቶ፣ ደራሲው ለዚህ መረጃ እንደማይሰጥ ጠቁመዋል። እንዲሁም ደራሲው ተጠቅመውባቸውም መጽሐፉ ውስጥ ያልመዘገባቸውን መጽሐፍቶችንንና ደራሲያንን የማይዘግቡ መሆናቸውን እንዲህ ሲል ይጠቁመናል፡-

“Have not the books of Nebura’ed Ermias Kebede and Abraham Kinfe told the same stories in almost the same wording years ago? Unfortunately I do not find their names in the so-called sources.”

ይህ ግኝትና ትችት የመጽሐፉን ደራሲ ለከባድ ጥያቄና እንዲሁም ለሕጋዊ ተጠያቂነትም የሚዳርግ ነገር ሆኖ ሳለ፤ ደራሲው ስማቸው ከላይ የተጠቀሱትን ደራሲያን ጹሑፎችን መጽሐፎቶችን የጻፉትን ግለሰቦች ስም መጽሐፉ ውስጥ ሣይመዘግቧቸው ገፆቻቸውን ግን ቃልበቃል ገልብጠው በመጠቀማቸው (plagiarism) ሕጋዊ ክትትልን እንደሚያስከትልባቸው ጠንቅቀው ማወቃቸውን ከላይ በጠቀስኩት ራዲዮ ላይም ስለ ጽሑፍ አጠቃቀም ያላቸውን ግንዛቤ  አንዱ አካል ሆኖ ማብራሪያ ሰጥተውበታል። ስለዚህ  ተጠያቂነት መኖሩን ደራሲው ጠንቅቆ ስለሚያውቁና የራሳቸውም መጽሐፍ ውስጥ የደራሲው “ሁሉ ሕጋዊ መብቶች የተጠበቁ All Rights Reserved” ናቸው ሲሉ አንባቢያንን ያስጠነቅቃሉ። የራስን መብት እንዲጠበቅ አስጠንቅቆ የሌላዉን መብት ለመጣሳቸው፣ ደረሲዉ ምን ትርጉም እንደሚሰጡት ለመገመት ያዳግታል፤ ስለዚህ ጉዳይ እስከ ዛሬ አንድም ቃል አላሰሙም።

ከላይ የተጠቀሱት ሙሑራን የሚሰማቸውን የሞያዊና የሀገራዊ ግዴታቸውን ፍላጎታቸውን ለመወጣት በሚያደረጉት ትብብር የሚደርስባቸው ተራ ነቀፌታዎችንና ዉንጀላዎችን ሰምቶ ማለፍ ከባድ ነው፣ በተለይም በጋራ ታሪክ ላይ። ብዙ ግዜ እንደምንገነዘበው ጸሐፊያን ትችቶችን ለመጽሐፋቸው እነደሚቀበሉ በተለይም -የሣይንሣዊ ምርመር ውጤትን- በሙሑራን ዘንድ መተቻቸትና መተራረም ብሎም የእርማት ጥቆማን ማግኘት የአብዛኛው ጸሐፊያን ምኞትና ደስታ ሆኖ ሳለ፣ ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ መጽሐፋቸውን አድንቀው የሚቀበሉትን በደስታ ሲቀበሉ፣ ተችዎችን ለተንኮል የተነሱባቸው አድርገው ይመለከትና ጭብጥ በሌለው ክርክር ይገጥሟቸዋል። ይህ ደራሲው ላይ ከፍ ያለ የአንባቢያንን ትዝብት አስከትሎባቸዋል፣ መጸሐፋቸውም ላይ ከፍ ያለ ጥርጣሬን ጥሎ ይገኛል።

ከላይ በስም ከጠቀስኳቸው ተቺዎች ባሻገር ሌሎችም የመጽሐፉን ይዘትና ውጤት ለመቀበል የተቸገሩ እንደ አሉም፣ በሌላ መልኩ ደግሞ የደራሲውን መነሻና መድረሻ በአድናቆትም የተቀበሉ አሉ። በተለይም የደራሲውን ነጥቦችን በመጥቀስ፣ ፕሮፌሰሩ እንደአስተማሩን፣ ግልጽ እንደአደረጉልን፣ ሌሎች ያልደረሱበትን የታሪክ አድማስ በማለት፣ ገደብ የሌለዉ አድናቆታቸዉን ለደራሲው ይገልጻሉ። በተቃራኒ ስለ ተቺ ሙሁራኖች ያላቸዉን አስተያየት፣ በደራሲው ላይ አላቸው  የሚሉትን የቅናት፣ የተንኮል፣ የአልበለጥ ባይነት ይሉና መፍትሄውም ሁሉም በችሎታውና ለሃገሪቷ በላቸው ተነሳሽነት፣ ታሪክን ይጻፉ ብለው ድምዳሜ ላይ  ይደርሳሉ። ነገር ግን ታሪክ በዚህ ሂደት ከተፃፈ የሚያስከትለውን ጉዳትና ጉድለት ተገንዝበውት ይሆን?

ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ የታሪክና የቋንቋ ሙሁራን በመጽሐፋቸው ዙሪያ የሚያነሱትን የመረጃ ጉድለቶችን፣ አጠራጣሪ ውጤቶችን በሚመለከት፣ ለተጠየቁት ጥያቄዎችም እስከ ዛሬ መልስ አልሰጡበትም፣ ለመስጠትም ፈቃደኚነቱን አላሳዩም። በተደጋጋሚ መልሱ ይህን አስመልክቶ መጽሐፌ ውስጥ በርካታ ማጣቀሻ ያደረኳቸው የመጣጥፍና የመጽሐፎቶች ዝርዝር ሰፍሮአል፤ አንባቢያንና ተቺዎች ጐደለ ለሚሉት፣ መፍቴሄን ከመጽሐፌ ሊያገኙ ይችላሉ ብሎ ይደመድማል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም በአሁኑ ወቅት የሚነሱ ጥያቄዎች አሉ። ይሄዉም መጽሐፉ በታወቁ የታሪክና የቋንቋ ሙሑራን ትችቶችና ግምጋሜዎች የታሪክ መጽሐፍነት  ደረጃ ሊደርስ አለመቻሉን፣ በርከት ባሉ አንባብያን ዘንድ የመወያያ አርእስት ሆኖ ሳለ፣ ደራሲው ለአንባብያን በአምስት ዓመት የሥራ ጊዜ የታሪክ መጽሐፍ አቅርቤአለሁ ይሉናል። እነዚህ ድምዳሜዎች ተቃራኒ በመሆናቸው ከመጽሐፉ ገዥዎች አንጻር የህግ ባለሞያዎች ይህንን እንዴት ይመለከቱታል? ከዚህ ጋር ተያይዞ በጣም አጠያያቂና አነጋጋሪ የሆነው የመጽሐፉ ምንነት ነው። መጽሐፉ በባለሞያዎች በተረጋገጡት የስህተቶች ብዛትና በሚጎድሉትም መረጃዎች የታሪክ መጽሐፍትነቱ ተቀባይነት እንደሌለው እየተገነዘብን ነው። መጽሐፉ ባለው ጉድለት፣ እነዲሁም ያቀራረብ፣ የቃላት ጥራትና ያጠራረዝ ጉድለቱ፣ ለምሳሌ መጸሐፉ ወስጥ የቀረቡት ሰንጠረዦች በመበታተናቸው፣ ለመረጃነት የቀረቡት ኮፒዎች መነበብ ባለመቻላቸው፣ ገጾች በአጭር ጊዜ መበታተናቸው ገዥ ለከፈለው ዋጋ ተመጣጣኝ  መጽሐፍን አላገኘም ማለት ይቻላል። ለዚህ ኪሳራ ማን ተጠያቂ ይሆናል?

 

ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ! -ምን ለማለት ይሆን?

በአለፈው አንድ ዓመት ውስጥ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለለውጥ ያለዉን ፍላጐትና ለኑሮ ያለውን ችግር ለአስተዳደር አካላት ድምፄ ይሰማ ብሎ መንገድ ላይ ሲወጣ፣ ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ ይህንን አነጋጋሪ የሆነዉን መጽሐፋቸውን በአጭር ጊዜ አርቅቆውና አሣትመው ኢትዮጵያ ተገኝቶ በተለያዩ ወሳኝ በሚሏቸው ቦታዎች መጽሐፋቸውን አስተዋውቀዋል። መጽሐፋቸውን እና እራሳቸውን በሚያስተዋውቁበት ጊዜ፣ ሌሎች ሙሑራን ተሣናቸው የሚሉትን የታሪክ ምርምር በአራትና በአምስት ዓመታት ጊዜ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያበረከቱት ሃገር ወዳድ፣ እውነትን ፈልፍሎ አውጪ፣ የቁርጥ ቀን ልጅ፣ ምንጊዜም ከሕዝብ ጐን የሚቆሙ፣ የሚሏቸዉን ቃላቶች እሳቸውና የዛሬ አድናቂዎቻቸው በአፅኖት ባገኙት ዕድል ያሰምሩበታል። መጽሐፋቸውን ለገበያ ለማብቃት የወሰደባቸው ጊዜ ከበርካታ ጉድለቶች፣ የመረጃ እጥረቶች፣ ብሎም የህትመትና የጥረዛ ግድፈቶችን አስመልክቶ ለፍጻሜ የወሰደባቸው የጊዜ እርዝመት፣ በጣም ያጠራጥራል። ዶ/ር ፍቅሬ  ሙሑራን ተብየዎች የሚላቸው ሙሑራኖች እሳቸው መጽሐፍ ውስጥ ያሉትን ጉድለቶች፣ ፈለፍለው በማውጣታቸው ብቃታቸውን ለአንባቢያን አረጋግጠዋል። ይህ ለሳቸው በማንኛውም መልኩ የማይጥማቸውና የማይመቻቸው ሆኖ ስለ አገኟቸው፣ መፍቴሄ አድርገው የያዙት የትራምፕን ዘዴ ነው፣ ማለትም ሀሰት “በእውነትነት” ተቀባይነት እስክሚያገኝ፣ ያንኑ ሀሰትና ውንጀላን መደጋገም ይሆናል። መጽሐፉ ግን የተተቸበትን ጉድለት ይዞ የኢትዮጵያ ብር 200 ሲሸጥ፣ ትንሽ ቆይቶ ደግሞ 120 ብር ከመጽሐፉ ገዢዎች መሰብሰቡ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በአማካኝ በዓመት $590 US. ለሚተዳዳር ቤተሰብ፣ ማለትም ከወር መተዳደሪያው ወደ 20% ለመጽሐፉ ሲያውል ምን ያህል የኑሮ ተጽእኖ እንደሚደርስበት፣ ደራሲው ከግንዛቤያቸው አስገብተውት ይሆን? ለመገመት የሚያዳግት ነው! ኢትዮጵያ ለሚኖሩት ብቻ ሳይሆን ውጭ ሀገር ለሚኖሩትም በኢትዮጵያ ዋጋ ተቀነባብሮ ተመርቶ በ$25 US ሲሸጥላቸው የሚገርም ነገር ነው።

ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ በአሁኑ ወቅት ከመጽሐፋቸው ጋር አያይዘው የኢትዮጵያ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ለኢትዮጵያ ታሪክ ያላትን አሻራ ጠቅሰው፣ በሱዳን በረሃ በድንጋይ ሳጥን ውስጥ ተገኘ ያሉትን የብራና ጽሑፍ ባያዩትም በዋናነት ያብራራሉ። ከዚህም ጋር አያይዘው መሪራስ አማን በላይ ስለ አላቸው የቤተክህነት ትምህርትና እውቀት በአድናቆትና በአጽንፆት ይገልጻሉ። አያይዘውም ቤተክህነቷ ለኢትዮጵያ ታሪክ ያላትን ሚና ያሰምሩበታል። ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ  ብሬመን ከተማ በነበሩበት ወቅት ኢትዮጵያውያንን እየሰበሰቡ ችግራችሁ መፍትሄ ያገኛል፣ መሄድ፣ ማየት ወዘተ የተሳናችሁ፣ ህመምም ያጠቃችሁ፣ ትፈወሳላችሁ እያሉ በጀርመን ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን እንዲሰባሰቡ ያበረታቱ ነበር። ከተወሰነ ጊዜ  በኋላ ግን እሳቸውም ሆኑ አብዛኛው የሰበሰቧቸው፣ ለቤተክርስቲያኑ ጀርባቸውን ሰጡ። ይህ መዋዠቅ ለእምነቱ ብቻ ሳይሆን ለግለሰቦችም ባላቸው ግንኙነት ጎልቶ የሚታይ ነበር።

ሌላው እጅ እና እግር የሌለው በተለያዩ መንገዶች ሠራሁ እወቁልኝ የሚሏቸው ነገሮችንም ከዚሁ  መጽሐፍ ጋር አያይዘው ያቀርባሉ። ጀርመን በነበርኩበት ወቅት የኢትዮጵያ ባሕልን፣ ማሕበራዊ ኑሮዋን፣ ጊዚያዊና ታሪካዊ ሂደቷን የጀርመን ሕዝብ እንዲገነዘብ አደርጌአለሁ ይሉናል። አክለውም በብሬመን ዩኒቨርሲቲ አስተምሪያለሁ ይሉናል። ለዚህ አባባል ብሬመን ውስጥ ያለው ትዝብት ፍጹም የተለየ ነው። ዶ/ር ፍቅሬ ይህንን ሊያደርጉ ምኞቱ ቢኖራቸውም፣ ካላቸው የጀርመን ቋንቋ ምጥንነትና ከሕብረተሰቡም ስውር ዘረኝነት አንጻር፣ ተግባር ላይ ማዋሉ ቀላል አይደለም። ለዚህ ማብራሪያ በዝርዝር ካስፈለገም ወደፊት ሊገለጽ ይቻላል። የኢትዮጵያን የሙዚቃ ጥበብ በአንድ ወቅት በሬድዮ እንዲተላላፍ ያደረጉት ሙከራ “በባንቱስታን ሙዚቃ” ተፈርጆ የጀርመኖች መሳቂያና መሳለቂያ ሆኖ፣ በአጭር ጊዜ ተቋረጠ። ሆኖም ከዚህ በላይ ለተጠቀሱት ቁምነገሮች ሊውሉ ይችሉ የነበሩ ሠፊ ሁኔታዎችንና እድሎችን በትጋትና በቆራጥነት ተነስተው ጥረት ቢያደርጉ ኖሮ ከግብ ሊያደርሱ ይችሉ ነበር። ነገር ግን ሳይጠቀሙባቸው ቀርተዋል፣ ለምሳሌ በዩኒቨርሲቲው፣ በሙዚየሙ፣ እንዲሁም በሌሎች የሕዝብ መገናኛ አዳራሾች ውስጥ የኢትዮጵያን ስነጽሁፍ፣ ፍልስፍና፣ ሐይማኖቶችን እንዲሁም በወቅቱ አነጋጋሪ የነበረውን ታሪኳን አለኝ በሚሉት ሙያ አቀነባብረው ለጀርመን ሕዝብ ሊያቀርቡና ሊያስተዋውቁ ይችሉ ነበር። ይህ ግን በወቅቱ አልታያቸውም ወይም አስፈላጊ ሁኖ አላገኙትም። ለዚህ በብሔር ድርጅቶች ረዳትነት የተሰለፉትን ለአላማቸው መሳካት ጥረታቸውን እንደ ምሳሌ ሊያዩ ይችላሉ ነበር።

ወደ አሜሪካን ከመሄዳቸው በፊት አሥር ዓመት ገደማ የኖሩት ጀርመን፣ ብሬመን ከተማ ሲሆን፣ የፒ.ኤች.ዲ. ምርምራቸውን ብሬመን ዩኒቨርሲቲ ውስጥ አጠናቀዋል። ነገር ግን በምንም ጊዜ የዩኒቨርሰቲው ቋሚ ተቀጣሪ ሆነው በሞያቸውና በሥራ ገቢያቸው የተስተዳደሩበት ጊዜ የለም። ለዚህም ተጨማሪ ማብራሪያ ካስፈለገ ወደፊት እንዳአስፈላግነቱ ሊገለጥ ይችላል። መንግሥት ለረጅም ጊዜ ለሥራፈቶች በሚያመቻቸው መንገዶች ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳም ኡበርዜ-ሙዝዩም ብሬመን  (Übersee – Museum Bremen) የሚባለው፣ የጀርመን ቅኝ ግዛት ሃገሮች ቆሳቁሶች ተሰብስበው የሚታይበት ውስጥ ለአንድ ዓመት ሠርቶዋል። ከአንድ ዓመት የሥራ ጊዜ በኋላ ከድርጅቱ ተሰናብተዋል። ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ ለረጂም ጊዜ በስደተኛነት ብሬመን ከተማ ውስጥ ከቆዩ በኋላ “እልፍ ሲሉ እልፍ ይገኛል” እንደሚባለው ጀርመንን ለቀው ወደ አሜሪካ ማቅናታቸው ይታወቃል። አሜሪካን አገር ሆነው፣ ጀርመን አገር በነበሩበት ጊዜ ኢትዮጵያን አስተዋወኩ፣ በአስተማሪነትና በስነ ጽሑፍ ሥራዬ ታዋቂነት አትርፌአለሁ፣ የሚባለው ከተለመደው “በሬ ወለደ” ዓይነት ተረት የማያልፍ ነው። ይህንን ጋዜጠኛ አበበ ገላው ባለው ጥበብና ልምድ የዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳንም ዝና፣ የሌሎችን ሲያደርግ እንደነበረው ቢመረምረው መልካም ነበር፣ እላለሁ።

ሆኖም ሳልጠቅስ የማላልፈው በጎ ተግባር ዶ/ር ፍቅሬ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ብለው ከኢትዮጵያውያኖች ጎን አንድ ጊዜ የተሰለፉበትን ወቅት ነው። በ 1984/85 ኢትዮጵያ ውስጥ በተከሰተው ርሀብ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሲረግፍ፣ ብሬመን የሚኖሩ የኢትዮጵያ ተወላጆች የሀገሩን ሕዝብ ለእርዳታ ጠርተው፣ ስለ ርሀቡና ምክንያቱ ገልፀው፣ እርዳታ ሲያሰባስቡ ዶ/ር ፍቅሬም ከተባባሪው አካል አንዱ ነበሩ። ከዚህም ሌላ አንድ ወንድማችን በአደጋ ምክንያት ተጎድቶ ሆስፒታል በነበረበት ወቅት አሜሪካ ካለው ወንድሙ ጋር ግንኙነት አድርገው ወንድምየው መጥቶ እንዲይየው አሳክተዋል።

ከላይ ከተዘረዘሩት ባሻገር ዛሬ ኢትዮጵያ የምትገኝበትን በተለይም በዚህ መጽሐፍ ዙሪያ የሚነሱትን በርካታ ጉዳዮች መነሻ ምንጫቸው ምን ነበር፣ በወደፊት ሂደትስ ውስጥ ምን ያህል ትኩረት ያገኛሉ? ይህ አመለካከት በግልም ሆነ በድርጅታዊ አስተሳሰብና ተግባር ትኩረትና እምነት እንደሚገባው አልጠራጠርም። ከዚህ በመነሳት የኢትዮጵያ የመቶ ዓመት ታሪክ የተባለውን. አነሳስና ስርሰደድነት፣ እንዲሁም ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳን አስመልክቶ ባጭሩ እጠቅሳለሁ።

 

የኢትዮጵያ ”የመቶ” ዓመት ታሪክ አፍንጫችን ስር ሲታነጽና ሲቀረጽ ዶ/ር ፍቅሬ  የት ነበሩ?

ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ የላስቬጋስ ከተማ ነዋሪዎች ከፍ ባለ አድናቆትና አክብሮት ተቀብለዋቸውና አስተናግደዋቸው እንደ ነበር፣ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። በዚህ ወቅት በርካታ ሰዎች ተገኝተው የመጽሐፉን አቅርቦት ታዳሚዎች ሁነው በትኩረት እንደተከታታሉትና እንዲሁም ባለፉት 25 ዓመታት የኢትዮጵያ ታሪክ በመቶ ዓመት ተመጥኖ የሚወራበትም ተነስቶ ታዳሚና የዕለቱ ዕንግዳ በለቅሶና በእንባ የተራጩበት እንደነበር ተብራርቶ በጽሑፍ ቀርቧል። የኢትዮጵያ የመቶ ዓመት ታሪክ ሲነሳ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሚያመው፣ እንደሚያበሳጨውና እንደሚቆጨውም የማይካድ ነው። ነገር ግን ዶ/ር ፍቅሬ የዚህ ሕዝብ አካል አድርጐ እራሳቸውን መመልከትና የሃዘኑ ተካፋይ ሁነው መቅረባቸው፣ በራሱ በጣም የሚደንቅና የሚያሳዝን ነገር ነው።

ይህንን የመቶ ዓመት የኢትዮጵያ ታሪክ የተባለዉን ፕሮፌሰር ኃይሌ ላሬቦ በቅርቡ በኢሳት (ESAT) ቃለ-ምልልስ ላይ የጀርመን ቅዠት ብለው ጠቅሰውታል። ይህ ታሪክ ጀርመን ውስጥ ታስቦ፣ ተቀርጾ ከ1980 ዎቹ እስከ 1990 ዎቹ መጀመሪያ ድረስ መሰረቱ የታነፀበት፣ ተጠናክሮና ቅርፅ ይዞ የወጣበት ጊዜ ነው። በወቅቱ የብሔር ድርጅቶች ብሔረሰቦቻችን ከኢትዮጵያ የቅኝ አገዛዝ ቀንበር ነፃ እናወጣለን ብለው በፍልሚያ (በትጥቅ ትግል) ለዓላማቸው ይታገሉ በነበሩበት ወቅት ነበር። የዚህ ታሪክ አፍላቂዎችና ኮትኳቾች በዋናነትና ግንባር ቀደም ሁነው የሀሳቡ መሪና ዘዋሪ በመሆን የሚጠቀሱት ዶ/ር ሃስልብላት የበርሊን ሚሲዮን-ቨርክ ባልደረባ (Hasselblatt, Berlin Missionswerk)፣ ጉንተር ሽራኤደር (Günther Schröder) እና ቫልተር ሚሸልስ (Walter Michels) የሚባሉ 3 ጀርመኖች ናቸው። የበርሊኑ ሚሲዮንስ-ቨርክ በ2008 በአሳተመው “ኢትዮጵያ” በሚለው ፅሑፍ  እንድህ ሲል መዝግቦታል:-

 

„Jüngste Geschichte

Das heutige Äthiopien mit seinen mehr als 80 verschiedenen Völkern ist im wesentlichen ein koloniales Gebilde des 19. Jahrhunderts und der damaligen expansiven Machtpolitik von Kaiser Menelik II., König der Shoa-Amharen (1889 – 1913). Vor 1889 war Äthiopien als Königreich „Abessinien“ bekannt. Als 1884/85 in Berlin die europäischen Kolonialmächte Afrika unter sich aufteilten, saß als einziger Afrikaner ein Vertreter des abessinischen Kaiserreiches mit am Tisch. Mit der Erlaubnis der Berliner „Kongo“-Konferenz und mit Hilfe der damaligen Kolonial-mächte (England, Italien und Frankreich) eroberte die kaiserlich-abessinische Armee daraufhin die westlichen, südlichen und östlichen Nachbarvölker. Das so durch Eroberung geschaffene Großreich war nunmehr doppelt so groß wie vorher und wurde fortan „Äthiopien“ genannt. 1880 – 1913 Vergrößerung des Kaiserreiches um das Dreifache durch Kolonialeroberungen im Westen, Süden und Osten. Addis Abeba entsteht als neue Hauptstadt dieses Reiches.“ [1]

ትርጉም:-

“የቅርብ ግዜ ታሪክ

የዛሬዋ ኢትዮዽያ ከ 80 በላይ የሚሆኑ የተለያዩ ሕዝቦችን ያቀፈች የ19 ኛው ክፍለ ዘመን በዋናነት በኃይል መስፋፋት የቅኝ ግዛት አካል እና በወቅቱ በኃይል የመስፋፋትን  ፖለቲካ ይከተል የነበረው  ንጉሥ  ሚኒልክ II፣ የሸዋ – አማራ ንጉሥ (1889 -1913) ግዛት ናት። ከ 1889 በፊት በኑጉሠ ነገሥታት ስትተዳደር በ”አቢሲኒያነት” ትታወቅ ነበር። በ 1884/85 የአውሮፓ ቅኝ ገዥ ኃይሎች በርሊን ወስጥ ተሰብስበው አፍሪካን ሲከፋፈሉ፣ ከመሀላቸው የተገኘው ብቸኛው አፍሪካዊ የአቢሲኒያው ንጉሠ ነገሥት ተወካይ በጠረጴዛው ዙሪያ አብሮ ተቀምጦ ነበር። በበርሊኑ “ኮንጎ” ከንፈረንስ ፈቃድ እና በዚያን ጊዜ የቅኝ ገዥ ኃይሎች (ኢንግላንድ፣ ጣሊያን እና ፈረንሳይ) እርዳታ የአቢሲኒያው ንጉሥ ወታደሮች ይህን በመጠቀም የምዕራቡን፣ የደቡቡን እና የምስራቁን ጎረቤት ሕዝቦችን ወረሩ። በዝህ ወረራ የታነጸችው ትልቋ ንጉሣዊ ቅኝ ግዛት አሁን የጥንቱን እጥፍ ሆና “ኢትዮዽያ” በመባል ትጠራለች። 1880-1913 በንጉሣዊ  ቅኝ ግዛት መስፋፋት ወደ ምዕራብ፣ ደቡብና ምስራቅ ዛሬ ሶስት እጅ እጥፍ ዕድገት ደርሳለች። አዲስ አበባ የዚህ ንጉሣዊ ግዛት እነደ አዲስ ሁና ከተማ ተመሰረተች።”

 

ዶ/ር ሃስልብላት በአፄ ኃይለ ሥላሴ አስተዳደር ኢትዮጵያ ውስጥ በሃይማኖቶች ዙሪያ ይሠራ የነበረ የጀርመን ቤተክርስትያን የዕርዳታ ተላኮ ነበር። ሌሎቹ ግን የብሔር ድርጂቶችን ሻዕቢያ፣ ሕወሃትና ኦነግ ከኢትዮጵያ ቅኝ አገዛዝ “ሕዝባችንን” ነፃ እናወጣለን በሚል አላማ የተነሱትን፣ ደጋፊዎች ነበሩ። በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ያደረሰው ለውጥ፣ ክስረትና ጉዳት በተለያየ መልኩ ዛሬም የውይይት አርእስት ሁኖ ይንፀባረቃል።

በዚህ ጊዜ እነዚህን የብሔር ድርጂቶችን ለመርዳትና ለማስተዋወቅ በግንባር ቀደምትነት የሚንቀሳቀሱትና የሚመሩት ከላይ የጠቀስኳቸው 3 ሰዎች ሲሆኑ በወቅቱ የጀርመን ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን በግብረ ሠናይ ድርጂቶች አካባቢ እንዲሁም በግለሰቦች ታጅቦ “ነፃ አውጪ” ድርጂቶቹን የሚረዷቸው ቁጥሩ ከፍ ያለ የጀርመን ተወላጆች ነበሯቸው። ይህ ክስተት የደርግን አስተዳደር ስለ አሰጋው ዶ/ር ሃሰልብላትን በግድያ ለማስወገድ ሁለት ቦንብ አጥማጆችን ወደ ጀርመን፣ በርሊን ከተማ ላከ። ተልኮዎቹ ባረፉበት ሆቴል ቦንቡን ሲያዘጋጁ ፈንድቶባቸው አንዱ ሲሞት ሌላው ከባድ ጉዳት ደርሶበት ከዳነ በኋሏ፣ የተልኮ ሚሥጢሩን ይፋ አደረገ። ይህ በመታወቁ የዶ/ር ሃሰልብላት የትግል ኃይል ተሰሚነቱና ጠላትነቱ ተጠናክሮ ቀጠለ።

በወቅቱ የብሬመን ከተማ አስተዳደር በአፍሪካ ተማሪዎች አነሳሺነት ጀርመን የኰሎንያል ታሪክን ማረም አለባት በሚል መርሆ እንቅስቃሴ የተካሄደበት ወቅት ሁኖ፣ ትግሉም ለቅኝ ግዛት ሀገሮች ለሚያካሄዱት የነጻነት ትግል ዕርዳታ ኢንዲሰጣቸውና በዓለምም ላይ ድጋፍ እነዲያገኙ የብሬመን መንግሥት ትብብር ይሰጣቸው ዘንድ ጥሪ የተላለፈበት ወቅት ነበር።

የናሚቢያ ሕዝብ በስዋፖ መሪነት እያየለ ሲመጣና በዓለም ደረጃ እራሳቸዉን አስተዋውቀው፣ ታዋቂነታቸው እየጐላ ሲመጣ፣ የብሬመን አስተዳዳር የቅኝ ግዛት ታሪኳን ለማስተካከል ስዋፖን የሚረዳ ፕሮጄክት ብሬመን ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ቀርጾ፣ ሥራ ጀመረ። በዚህን ጊዜ ብሬመን እና አካባቢዋ ይማሩ፣ ይኖሩ የነበሩ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚካሄደዉን የብሔር እንቅስቃሴ እንደግፋለን የጥቁርን ኰሎንያሊዝም እንዋጋለን ሲሉ የእርዳታ ጥሪያቸዉን አስፋፍተው ተነሱ። ይህን ጥሪ ተከትለው የተለያዩ ድጋፍ የሚሰጧቸው ቁጥራቸው እየጨመረ ተሰሚነታቸው እየጠነከረ መጣ። በዚህ ሂደት ውስጥ ከላይ የጠቀስኳቸው ስሞች የጀርመን ተወላጆች ቀላል የማይባል ሚና ነበራቸው። ለዓላማቸው ሕዝቡ ውስጥ ሰርፀው ለመግባት በየሳምንቱ መጨረሻ ላይ የምሺት ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት ከላይ በጠቀስኳቸው የብሔር ድርጂቶች የሚመሩትን ሕዝቦች አናኗር፣ የኢትዮጵያ የ19ኛው ክፈለ ዘመን መስፋፋትና ጥቁር በጥቁር ላይ የሚፈጽመውን ኰሎኒያል አገዛዝ በሚል ተቀነባብሮ ይቀርብ ነበር። ለዚህ ፕሮግራም የሚመጣው የሃገሬው ሕዝብ በኢትዮጵያ የባሕል ምግብ በብሔሮች ሙዚቃና ጭፈራ ሲሰተናገድ በትርኢቱም ላይ የገንዘብ ስበሰባ ይካሄድ ነበር።

ይህ ሂደት በጀርመን፣ ብሬመን ከተማ ውስጥ አድናቆት እያገኘና እየተስፋፋ ሲሄድ፣ ለኢትዮጵያ አንድነት የሚታገለው የሰው ብዛት አነስተኛ በመሆኑ፣ በችግር ተውጦን በየአደባባዩ ወጥቶ የኢትዮጵያን ማንነትና ኢትዮጵያ ለዘመናት የተፈራረቁባትን፣ ነፃነቷን የተፈታተኗትን በመጥቀስ፣ ኢትዮጵያ ግዛቷን ባላት ኃይል ከወራሪ ኃይሎች ተከላክላ ነጻነቷን ከማስከበር አልፋ፣ በምንም ወቅት የግዛት ማስፋፊያ ፖለቲካ እንዳልተከተለች፣ ለማሰማትና ለማሳወቅ በተለያዩ ሁኔታዎች ትግል አድርገናል። ለዚህም ትብብር ኢተዮዽያውያንን ከሌላ የጀርመን ከተሞች፣ እነዲሁም ከሆላነድ፣ ከፈረንሳይ ከእንግሊዝ ከጣሊያን ድረስ መጥተው ረድተውን በጥሩ ውጤት ተሳክቶልናል።

ይህንን ትግል ብሬመን ባለነው ኢትዮጵያውያንና በአጭር ጊዜ ዝግጅት አድርገን ሕዝቡን ለኛ ጉዳይ ለማሳመን ወዳጆች የምንላቸውን ሁሉ አነጋግረናል። ከነዚህ አንዱም ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ ነበሩ። ኢትዮጵያ ያለችበትን ሁኔታ እያየንና እየሰማን በዝምታ ማለፍ የለብንም፣ ይህንን ሂደት በቻልነው መንገድ፣ ለሃገሬው ሕዝብ፣ ለአፍሪካ ተማሪዎች ድምፃችንን እናሰማ ብለን በመጥራትና ለትግሉም አጋር እንዲሆን ከመጎትጎት አልተቆጠብንም። ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ ለጥሪው እንቢ ባይሉም በወቅቱና በዝግጅቱ  ከላይ የተጠቀሱትን የኢትዮጵያ አንድነት ተቃዋሚዎችና ጠላት የሆኑትን የሃሰት ፕሮፖጋንዳቸውን ወይም ሚት/myth ተቃውሞ ከሌሎች ለኢትዮጵያ አንድነት ታጋዮች ጐን ተገኝተው የተቃወሙበት እና የታገሉበት ጊዜ የለም። በዛን ቀውጢ ጊዜ ሁኔታዎችን በመናቅና ትኩረት ባለመስጠታቸው ከጥቂቶቹ የኢትዮጵያ የአንድነት ስብስብ አካል ትችትንና ነቀፌታን አስከትሎባቸዋል። በተለይም በጊዜያዊነት በሚሠሩበት በብሬመን ከተማ፣ የኰሎኒያል ሙዝየም አዳራሽ ውስጥ ኢትዮጵያን የመበታተን ፖለቲካ ሲካሄድበት አንድም ቀን ድምጻቸውን ሳያሰሙ በዝምታ አልፈውታል።

ይህ ሆኖ ሳለ ዛሬ የኢትዮጵያ ታሪክ በመቶ ዓመት ታሪክነት በጀርመን አገር በተለይም ብሬመን ከተማ ውስጥ ተጸንሶ፣ ታንጾና ተጠናክሮ ወጥቶ፣ ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ የ 25 ዓመት እድሜን ተጐናጽፎአል። ይህንን ዛሬ በተለያዩ ዓለም ከተማዎች ዶ/ር ፍቅሬ እየተዘዋወሩ የኢትዮጵያን ታሪክ፣ በእግር የተረገጠበት እሳቸውን ለማያውቁት ቢያወሩ የሃዘንተኞቹ አስተዛዛኝ ቢሆኑ፣ ታሪኩን ለምናውቀው “ከአዞ እንባነት” ያለፈ ትርጉም አይሰጠውም። ይህ ሰው ነው እንግዲህ፣ ዛሬ በኢትዮጵያ ተቆርቋሪነት እራሰቸውን እየካቡ ለብሔር “ነጻነት“ እንታገላለን የሚሉትንም በጠላትነት እየወነጀሉ፣ አላማቸው መሠረተ ቢስ እያሉ የሚነቅፏቸው፣ የሚከሳቸው። እሳቸው ግን ለኢትዮጵያ ተቆርቋሪ ሆኖው፣ የሳቸውን መንገድ ለማይከተሉት ኢትዮጵያውያንን ከሃዲ አድርገው የሚከሷቸው።

ከ30 እና 35 ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ መሠረቷ ሲናጋ ተዋናይ ከነበሩት ድርጂቶችም ሆኑ ግለሰቦች በወቅቱ አምነው የተከተሉትን አላማቸዉን ሽረው ላደረጉት ፀፀታቸውን አሰምተው ዛሬ በዝምተኛነት ወይም በአዲስ መድረክ ላይ ወጥተው ለኢትዮጵያ አንድነት የሚታገሉ መኖራቸው አይካድም። ዶ/ር ፍቅሬ ግን እስከ ዛሬ ባደረጉት በደርግ ሥርዓትና ደርግ እስኪ ወድቅ በነበረው ጊዜ ውስጥ አደረግሁ የሚሏቸው ስፍር ቁጥር የለውም። ነግር ግን የኢትዮጵያ ገፅታዋና ታሪኳ እንደ አልሆነ ሲደረግ እራሳቸውን አሸዋ ወስጥ ቀብረው አላየሁም፣ አልሰማሁም ሊሉን ነውን? የውጭ ወራሪ ኢትዮጵያን ሲወሩና ሲወጉ ከነሱ ጋር ተባብረው ሕዝብን የወጉትን ባንዳ የባንዳ ልጅ ተብለዋል፤ በቅርቡ ታሪካችን ሲሰረዝ ሀገራችን ስትፈርስ፣ ስትጎዳ ስትደማ በዝምታ አሳልፈው ዛሬ የሀገር አርበኞ ነኝ ሲሉን ምን እንበላቸው?

ከዚህ ሁኔታ ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ በፋሽስት ጣሊያን የደረሰባትን ጉዳትና የሕዝብ ዕልቂት አስመልክቶ ሰሞኑን ኢትዮሜዲያ ላይ ለንባብ የቀረበው የዶ/ር መላኩ በያን አርበኝነት ትዝ አለኝ። ኢትዮጵያ ውስጥ ለሕዝብ አገልግሎት መስጠት ላይ ሳሉ በጦርነቱ መከሰት ምክንያት ወደ አሜሪካ ተሰደው ለሕዝባቸው ባለውለታ ሁነው አልፈዋል። ለኢትዮጵያ ሕዝብ ድምፅ ሆነው የሚከተለው ተግባር አቀነባበሩ፡-

“Dr. Malaku Bayen reached the United States in September 1936, and Harlem in New York City became his base of operation. Immediately, the young physician introduced a very valuable review “The Voice of Ethiopia” and soon established an organization called “The Ethiopian World Federation.”  Dr. Malaku assembled prominent African Americans who devoted time and resources to assist actively Ethiopian patriots in action and to stand firmly in opposition to those who rushed to endorse fascist aggression against Ethiopia.  The supporters of his cause included leaders like W.E.B. Du Bois, Rev. Lloyd Imes, Mildred Houston, Lorenzo King and a cross-section of individuals and organizations in the Caribbean, America and Europe. Dr. Malaku proclaimed that his organization was pledged to continue the struggle for the liberation of the entire black race and he encouraged his collaborators never to slow down their efforts to dismantle Mussolini and his fascist soldiers and send them back home before they committed further destruction.  In the 1940’s, there was hope. Ethiopians began to see the giant fascist colonial castle collapsing.”

ባለፉት 50 ዓመታት ኢትዮጵያ ለደረሰባት ጉዳት ሕዝቧ በጋራ መነሳት ስለ ተሳነው በግል ወይም በጥቂቶች በታቀፈ ቡድን መንቀሳቀሱን እነደ መፍቴሄ ተያይዞታል። የዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳም ፍልስፍናም በዚህ ላይ ያለመ ይመስላል፤ ከዚህም ባሻገር ያለፈውን የግድየለሽነቱን ጊዜ ለማካካስ፣ ከላይ በተጠቀሰው መጽሐፋቸው የኢትዮጵያን ሕዝብ ታሪክህን እስከ 5500 ዓመት ወደ ኋላ ሂጄ መረመርኩልህ፣ የቆዳ ስፋቷን እስከ ግብፅና ሊቢያ ዘረጋሁልህ፣ መዘገብኩልህ፣ እና ትልቋ  ኢትዮጵያን በዚህ ካስኳት ያሉ ይመስላል። ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ ያቀረቡት መጽሐፍ ባለው የመረጃ ጉድለቶች እንዲሁም በርካታ ስህተቶች በኢትዮጵያ ታሪክነት መሠረት ሊጥል አልቻለም። በተለይም በዚህ መጽሐፍ ውስጥ፣ ኢትዮጵያ እስከ ሊብያ፣ ግብፅ፣ ሱዳን፣ ወዘተ ታስተዳድር ነበር የሚለው በመቶ ዓመቱ ታሪክ ውስጥ ኢትዮጵያ ለምትከሰስበት “የመስፋፋት ፖለቲካን” ለሀገር ተቀናቃኞችና ለውጭ ጠላቶቻችን በአማሳካሪነት ማገልገሉ አይቀሬ ነው። ስለዚህ ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ እስከ ዘሬ ለደረሶትና ወደፊትም ለሚደርሶት ትችቶችና እርማቶች ትኩረት ሰጥተው መጽሐፎን ለታሪክ መጽሐፍትነት ማብቃቱ የርሶ ሀላፊነት ነው። አየይዤም እውነት የታሪክ ምርምር ሥራ መሰረት እነደ መሆኑ ትኩረት ዘንድ ልጦቅም ወዳለሁ። ከዚህም ጋር በኑቢያ በረሀ ተገኘ የተባለውን፣ የታሪክ ቅርስ የኢትዮዽያ ሕዝብ የታሪክ ንብረት እንደመሆኑ በሚመለከተው መንግሥታዊ መሥሪያ ቤት ወይም በቤተ ክሕነት ቁጥጥር ስር መዋል ስለሚገባው፣ ድርሻዎን ይወጡ። ይህ ጉዳይ የያንዳንዱ ኢትዮዽያዊ ቅድመ ትኩረትም መሆን አለበት።

—————————————————————————————————————————–

በዚህ ጽሑፍ የተጠቀሱ ግለሰቦችም ሆኑ ጽሑፎች ከዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ መጽሐፍ ጋር ተያይዞ ከመሀል ታህሣሥ እስከ መሀል የካቲት ድረስ  ኢትዮሜዲያ ላይ ለንባብ የቀረቡ ናቸው

[1] Äthiopien,  Ein Arbeitsheft für die Arbeit mit Kindern, Jugendlichen und Erwachsenen, Berliner                  Missionswerk, 2008

 

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.