ቢጫ ንቅናቄዎች (Yellow movements) ችግር አቅላይ ወይስ ችግር ፈጣሪ? – ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

የዛሬ አራት ዓመት አካባቢ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ (መካነ ትምህርት) ሴት ተማሪዎች ግቢ ውስጥ የሚገጥሟቸውን ዘርፈ ብዙ ችግር ለማቅለልና ለመቅረፍ አሰብን ያሉ ሴት ተማሪዎች “Yellow movement!” የሚል እንግሊዝኛ ሥያሜ ለራሳቸው በማውጣት ንቅናቄያቸውን መሠረቱና መንቀሳቀስ ጀመሩ፡፡ ከሚናገሩት መረዳት እንደሚቻለው የንቅናቄው ዓላማ የተቀደሰ ነበር፡፡ በአንድ እጃቸው የገነቡትን በሌላኛው እጃቸው የሚያፈርሱ መሆኑ እንጅ ክፋቱ፡፡

ስማቸውን ቢጫ ንቅናቄ በማለት ወደ አማርኛ እንመልሰውና (ምክንያቱም እነሱ ቢዘነጉትም የራሳችን ቋንቋ አንድ ብቻም ሳይሆን በርካታ ቋንቋዎች ያለን ሕዝብ ነንና ቢጫ ንቅናቄ እያልን እንቀጥል) እናም እነኝህ ቢጫ ንቅናቄዎች ሴቶች በተለያዩ ምክንያቶች ግቢ ውስጥ የሚገጥሟቸውን ችግሮች ለመፍታት ገንዘብ የግድ አስፈለጊ ሆኖ ስላገኙት ገቢ ሊያገኙ የሚችሉበት መንገድ ሲያፈላልጉ በቫላንታይንስ (በፍቅረኞች) ቀን አበባ በመሸጥ ገቢ ማግኘት እንደሚችሉ አሰቡና ባደረጉት ጥረት በመጀመሪያው ዓመት አራት ሽህ ብር አግኝተው አምና ደግሞ ከመቶ ሽህ ብር በላይ ለማግኘት ችለዋል፡፡ ዘንድሮ ደግሞ ከሁለት መቶ ሽህ ብር በላይ ለማግኘት ተስፋ አድርገዋል፡፡
እንግዲህ ይህ “ገቢ የማግኛ መንገዳችን ነው!” ብለው የመረጡት ቀን ነው “ልናስተካክለው እንፈልጋለን!” ብለው የሚያስቡትን አፍራሽ የሚያደርጋቸው፡፡ እነሱ ግን ለጠየቋቸው የብዙኃን መገናኛው ሁሉ ይሄንን ገብዘብ የማግኛን ሐሳባቸውን ብሪሊያንት (አስደናቂ) በማለት ይመኩበታል፡፡ እኛ ግን ይሄንን ሐሳብ በሦስት ምክንያቶች ምን ያህል ውዳቂ፣ አጥፊና ከአንድ የተማረ ዜጋ ሊፈልቅ የማይገባ እንደሆነ እናያለን፡፡

1ኛ. ቢጫ ንቅናቄዎች ዝም ብለው በስሜት ላይላዩን እንጅ በትክክል ደረጃውን በጠበቀ አግባብነትና ብቃት ባለው አሠራር ሴት ተማሪዎች የከፍተኛ ትምህርታቸውን በተገቢው መንገድ ተከታትለው በጥሩ ውጤት ይሄም ቢቀር እንዲያው ብቻ ለመመረቅ እንዳይበቁ የሚያደርጓቸው ፈተናዎች “ምን ምን ናቸው?” ብለው መርምረው አጥንተው “እንዴት ሊቀረፉ ይችላሉ?” በማለት መፍትሔ የሆኑትን ነጥቦች ለይተው አውጥተው በሱ ላይ የሚሠሩ እንዳልሆኑ ከሚያሳብቁባቸው ነጥቦች አንዱና ዋነኛው ሴቶቻችን እንዳማረባቸው ትልቅ ተስፋ ተጥሎባቸው ግቢ እንደገቡ ሁሉ ተመርቀው እንዳይወጡ የሚያደርጋቸው ትልቁ ችግር ግቢ ውስጥ በፍቅር ስም የሚጀመረው የተቃራኒ ፆታ ግንኙነት መሆኑ ነው፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ የተደረገ ጥናት ባላገኝም ሴቶችን ከከፍተኛ ትምህርታቸው አሰናክለው ከሚያስቀሩ ችግሮች በፍቅር ስም በሚመሠረት ግንኙነት ሳቢያ የሚከሰተው ችግር ከ90 በመቶ በላዩን እንደሚይዝ ከሚታዩና ከሚሰሙ ነገሮች በመነሣት መገመት ይቻላል፡፡ በፍቅር ስም የሚመሠረተው ግንኙነት ወሲብን ማካተቱ ውጤቱ እንዲከፋ አደረገው እንጅ ወዳጅነቱ ወሲብን ባያካትትና አንዳንዶቹ ብልሆች እንደሚያደርጉት የትዳር አጋርን ለማግኛ መጠናኛ መንገድ አድርገው የሚጠቀሙበት ቢሆን ኖሮ ውጤቱ የሚታየውን ያህል የከፋ ባልሆነም ነበር፡፡ ይህ በፍቅር ስም የሚመሠረተው ግንኙነት ግን ዓላማው የሚፈታተንን የወሲብ ፍላጎት ከማርካት ያላለፈ በመሆኑ የችግሩ ጉዳት ሴቶች ላይጎልቶ እንዲታይ አድርጎታል፡፡ ወንዶቹ ሴቶቹን የሚፈልጓቸው ለጊዜያዊ ስሜታቸው በመሆኑ በመሀል ለሚከሰቱ ችግሮች ወንዶቹ በፍጹም ኃላፊነት መውሰድ የሚፈልጉ አይደሉም፡፡ እነኝሁ ኃላፊነት የሚባል ነገር ጨርሶ የማይሰማቸው ወንዶች ባንድም በሌላም ምክንያት እንዲጠቀሙባቸው የፈቀዱ ሴቶች ግንኙነቱ በሚያመጣባቸው ፈተናና ጫና ተሰናክለው ውጤት ተበላሽቶባቸው ከመባረራቸው በፊት እንደቆይታቸው መጠን ከአንድ በላይ በሆኑ ወንዶች እጅ እየተላለፉ ኢሞራላዊ በሆነ ሁኔታ መጠቀሚያ ለመሆን ይገደዳሉ፡፡ በመጀመሪያቸው ግንኙነት በተፈጠረ ችግር ተሰናክለው የሚቀሩም አሉ፡፡

ከዓመታት በፊት ጤና ቢሮው (መሥሪያ ቤቱ) ጥናታዊ ግምገማ ለመውሰድ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ (መካነ ትምህርት) ተማሪዎችን የHIV የደም ምርመራ እንዲያደርጉ አግባብቶ ምርመራው ተደርጎ ነበር፡፡ ውጤቱ እጅግ አስደንጋጭ መሆኑ አፈትልኮ የወጣ መረጃ አረጋገጠ፡፡ ውጤቱ የሚበዛው ተማሪ HIV ቫይረስ (ተሕዋስ) በደሙ እንዳለበት ያረጋገጠ ነበር፡፡ መረጃውም ተማሪዎች ዘንድ ስለደረሰ በተማሪው ላይ ጭንቀት ፈጥሮ የመማር የማስተማሩን ሒደት ክፉኛ አወከው፡፡ የዚህ ችግር አደገኝነት ሲታይ ተማሪዎችን ከጭንቀት ለማውጣት ተብሎ “የወጣው መረጃ ሐሰተኛ ነው ተረጋግታቹህ ትምህርታቹህን ተማሩ!” የሚል ማስተባበያ ተሰጠ፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ጤና ቢሮውም “ውጤታቹህን ውሰዱ!” አላለ፤ ተማሪዎችም ደፍረው “የምርመራ ውጤታችን ይሰጠን!” ብለው አልጠየቁ በዚያው ተደባብሶ ቀረ፡፡

ይሄንን ያነሣሁበት ምክንያት ቢጫ ንቅናቄዎች “የሴት ተማሪዎች ጉዳት ያሳስበናል፣ በግቢ ቆይታቸው ውጤታማ ሆነው ለመመረቅ እንዲበቁ ለመርዳት እንፈልጋለን እንሠራለን!” ካሉ ሊያደርጉት የሚገባው ዋነኛው ነገር ችግሮችንና ፈተናዎችን አግተልትሎ እያመጣ ከትምህርት ገበታቸው አሰናክሎ እንዲወጡ ከሚያደርጋቸው በፍቅር ስም ከሚመሠረት ፆታዊ ግንኙነት እንዲርቁ፣ ለማሳሳት ከወንዶች ከሚመጡ አታካች ውትወታና ንዝነዛ (harassment) ሊጠበቁ የሚችሉባቸውን አሠራሮችን (mechanisms) ከትምህርት ተቋማቱ ጋር ነድፎ ሴቶችን ከጥቃት፣ ከመሳሳት፣ ከመታለል ተጠብቀው የዋልጌ ወንዶች መጠቀሚያ እንዳይሆኑ፣ ከፍተኛ ትምህርትንና “ፍቅርን” አንድ ላይ አስኪዶ ጥሩው ውጤት ቀርቶ ተንጠላጥለው ለመመረቅ እንኳ ፈጽሞ የማይቻል ነው ባይባልም እጅግ አስቸጋሪ በመሆኑ መንገዳቸውን በፈተና የተሞላ ከሚያደርጉት ፍቅርን ከትምህርት በኋላ በትክክለኛው ሰዓት የሚደርስና የራሱ ጊዜ ያለው መሆኑን በማስረዳት አሁን ግን ያልተከፋፈለ ያልተበረዘ ያልተረበሸ ሙሉ ትኩረትና ጥረትን በሚፈልገው ትምህርታቸው ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መሥራት ሲገባው ጭራሽ “በእሳት ላይ ነዳጅ!” እንዲሉ “Happy Valentine’s day!” እያሉ ግቢ ውስጥና የተለያዩ ቦታዎች አበባ መሸጥ ሴት ተማሪዎችን ወደ ችግር ጉድጓድ ውስጥ ገፍትሮ መወርወር እንጅ በፍጹም ችግራቸውን ማቅለል አይደለምና “ብሪሊያንት የሆነ ሐሳብ አፈለቅን!” ባይ የቢጫ ንቅናቄ አባላት እኅቶቻችን ስሕተታቹህን አውቃቹህ ታረሙ፡፡

2ኛ. ለአንዲት ሀገር ሰላምና ደኅንነት፣ ማንነት፣ ባሕል፣ ታሪክ፣ ቅርስና አጠቃላይ እሴቶች መጠበቅ ትልቁን ሚና የሚጫወተው የተማረው ዜጋዋ ነው፡፡ ይህ የተማረ የተባለው ኃይል ጠባቂ መሆኑን ትቶ እንዲህ አጥቂ ሆኖ ከተገኘ “ትልቁ ዳቦ ሊጥ ሆነ!” እንል እንደሆነ ነው እንጅ እንዴት ብለን የተማረ፣ የተመራመረ፣ የዜግነት ኃላፊነቱንና ግዴታውን የሚያውቅና የሚወጣ ልንል የምንችለው? ተማረ፣ ሠለጠነ የሚባለው ክፍል ለሚጠቅምና ከሞራል (ከቅስም) ድንጋጌዎች አኳያ ልዕልና ላላቸው የምእራባውያን እሴቶች እጅ ሰጥቶ የዚህ አስተሳሰብና ባሕል ተከታይ ቢሆንኮ ምንም ባልከፋ ነበር፡፡

ሲሆን የምናየው ግን እጅግ በጣም ትንግርት ሊያሰኝ በሚችል ሁኔታ እጅ ሰጥተው የገዛ ሀገራቸውን ባሕልና አስተሳሰብ ጥለውና አጥፍተው ሲከተሉት የምናየው የምዕራባውያኑ እሴት ጭራሽ ከሰውነት ደረጃም አውርዶ ወደ እንስሳነት አንዳንዴም ከዚህም በታች አውርዶ የሚያስፈርጀውን ነውረኛ ተግባርን ነው፡፡ ተማርን ሠለጠንን ብለው ግብረሰዶምን ከምዕራቡ በማምጣት በሀገራችን ሕጋዊ ዕውቅና ካላገኘ ብለው የሚሟገቱና ጥረት እያደረጉ ያሉ መኖራቸውን ልብ ይሏል፡፡
እነኝሁ ቢጫ ንቅናቄዎች ራሳቸው ግቢ ውስጥ “ሴት ልጅ የፈለገችውን፣ መስሎ የታያትን ዓይነት አለባበስ መጠቀም ትችላለች! መብቷ ነው! ለመጠቃቷ ምክንያት ሊሆን አይገባም!” እያሉ ኢሞራላዊ፣ ፀረባሕልና ርካሽ በሆነ ክርክራቸው የተማሪውን ልብ ያወልቁ እንደነበር አሁንም እንደሚያወልቁ አውቃለሁ፡፡ የሚያስከብረውና ኃላፊነት የሚሰማው አካል ጠፋ እንጅ የወንጀለኛ መቅጫ ሕጋችን “ከሕዝቡ ባሕል ጋራ ተቃርኖ ያለውንና ወሲባዊ ስሜትን የሚቀሰቅስ አለባበስን ተጠቅሞ በአደባባይ መታየት በሕግ የሚያስጠይቅ ወንጀል ነው!” ይል አልነበር እንዴ!

እና እንግዲህ ተማርን፣ ሠለጠንን የሚሉ ወገኖች እንዲህ ሆነው እያየን እንዴት ነው ኃላፊነት የሚሰማቸው፣ የነቁ፣ ያወቁ፣ የጠነቀቁ፣ ለችግሮቻችን መፍትሔ አፍላቂ ልንላቸው የምንችለው? ርካሽ የምዕራቡን ዓለም ባሕልና እሴት አምጥተው እየጫኑ ትውልዱ ወደከፋ ችግር የሚገባበትን ጉድጓድ ቆፋሪ ሆነው እያለ እንዴት ብለን ኃላፊነታቸውን የሚያውቁና የአኩሪ እሴቶቻችን ጠባቂ አስጠባቂ፣ ጠበቆች ልንላቸው የምንችለው? አናም በዚህ በዚህ ምክንያት ቢጫ ንቅናቄ በያዘው አሠራሩ የችግራችን አካል እንጅ የመፍትሔ አካል ሊሆን አይችልም፡፡ ምን? ለምን? እንዴት? መቸ? መሠራት እንዳለበት የሚያውቁ ሆነው አይታዩምና መልካም የመሥራት ቅን ፍላጎቱ ካላቸው እነኝህን ነገሮች ግምት ውስጥ በማስገባት እራሳቹህን አስተካክሉ፡፡

3ኛ. ቢጫ ንቅናቄዎች የፍቅረኞች ቀንን ገቢ ለማስገኛነት ሁነኛ ቀን ሆኖ አግኚተውት ቀኑን የመረጡት አይመስለኝም፡፡ እራሳቸውን ለምዕራባውያኑ ቀጥረው ቫላንታይንስ ዴይን (የፍቅረኞች ቀንን) ለማስተዋወቅና እኛ ላይ ለመጫን አስበው እንጅ፡፡ ምክንያቱም በምንም መመዘኛ ብናየው ይህ ቀን ከሌሎች በዓላቶቻችን በተሻለ በርካታ ሕዝብ የሚያከብረውና ከዚህም የተነሣ ጥሩ ገቢ ያስገኛል ተብሎ የሚገመት ቀን ባለመሆኑ፡፡ ልጆቹ ከቅጥረኛነታቸው የተነሣ ካልሆነ በስተቀር ጥሩ ገቢ ሊያገኙ የሚችሉበትን የሞቀ የደመቀ በዓል ቢያስቡ ቢያንሰላስሉ ጥምቀትን፣ መስቀልን እንቁጣጣሽን ወይም ሌላ በዓላቶቻችንን ያስቡ ነበር እንጅ የሞቁ የደመቁ በዓላቶቻችንን ትተው ማንም የማያውቀውን አዲስና እንግዳ የምዕራባውያኑን በዓል ቫላንታይንስ ዴይን (የፍቅረኞች ቀንን) እንዲያስቡ የሚያደርጋቸው አንድም የሚታይ ምክንያት የለምና፡፡
ልጆቹ ኢትዮጵያዊነቱ የማይሰማቸው ስለሆኑና የማንነት ቀውስ የሚንጣቸው ብኩኖች ባይሆኑ ኖሮ “በእንቁጣጣሽ ቀን የእንቁጣጣሽ አበባን ይዘን ታዋቂና ታላላቅ ሰዎች ዘንድና በመዝናኛ ቦታዎችና በሌሎች ቦታዎች እየዞርን ዓላማችንን በማስረዳት ገቢ ለማግኘት እንጣር!” ይሉ ነበር እንጅ “በጥምቀት በዓል ወጥተን ተፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ይዘን ብንቀርብ ዓላማችንን ሕዝብ ስለሚደግፈው ጠቀም ያለ ገቢ ልናገኝ እንችላለን!” ይሉ ነበር እንጅ በሌሎችም በዓላቶቻችን “እንዲህ እንዲህ ብናደርግ!” ብለው ያስቡ ነበር እንጅ በምንም ተዓምር ቫላንታይን አይታያቸውም ነበር፡፡

ሲሆን ሲሆን እንደዛሬው ባለው የሠማዕታት ቀን የካቲት 12፣ በአድዋ ድል የካቲት 23 ወይም አርበኞቻችን ፋሽስት ጣሊያንን አባረው በገቡበት የድል በዓል ሚያዚያ 27 “ምን ብናደርግ ታሪካችንን በመዘከር ገቢ አግኝተን በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ልናገኝ እንችላለን?” ብለው ማሰብ ነበረባቸው፡፡ ይሄኔ ነበር “ብሪሊያንት (አስደናቂ) ሐሳብ አፈለቅን!” ማለት ይችሉ የነበረው፡፡ እውነታው ግን እነሱ የሚያውቁት ቫላንታይንስ ቀን መቸ እንደሆነ እንጅ እነኝህ የማንነታችን መሠረት የሆኑ በዓላት መቸ እንደሆኑና ለምን እንደሚታሰቡ አንዱንም አያውቁም፡፡ ለአንድ ሀገር ከዚህ በላይ ኪሳራ አለ? ታዲያ እነኝህ ናቸው ሀገሪቱ የጣለችባቸውን አደራ የሚወጡ የተማሩ ዜጎች የሚባሉት?
በአንድ ሕዝብ ሰፊ ተቀባይነት አግኝቶ ስኬታማ ሥራ መሥራት ካስፈለገ ትልቁ ስልት እራሱን መስሎ መቅረብ ነው፡፡ ይሄኔ ከላይ የጠቀስኳቸውን እንቁጣጣሽን ወይም ጥምቀትን ተጠቅመው ቢሆን ኖሮ ምን ያህል የሞቀ ምላሽ ከሕዝብ ባገኙ እነሱም ባገኙት ነገር የሕሊና እርካታ ባገኙ ነበር፡፡ ሌላው ቀርቶ በታላቁ ሩጫ ቀን በሩጫው ለሚሳተፉ ከሰላሣና አርባ ሽህ በላይ ለሆነ ተሳታፊ የታሸገ ውኃን በሽያጭ ማቅረብ ቢችሉ ራሱ ብዙ ጊዜ እጥፍ የተሻለ ገቢ ማግኘት በቻሉ ነበር፡፡

አሁንም ቢጫ ንቅናቄዎች ይሄን ይሄን ልብ ካለማለት፣ መሳሳታቸውን ካለማስተዋል ከሆነ ይሄንን እያደረጉ ያሉት ወደ ማስተዋላቸው መጥተው አረማመዳቸውን እንዲያስተካክሉ እንጠይቃለን፡፡ እንዲህ ተጨባጭ የሆኑ አመክንዮአዊ ነገሮች ቀርበውላቸው ለመስተካከል ለመታረም የማይፈቅዱ ከሆነ ግን ያኔ ቅጥረኝነታቸውን በግልጽ የምናውቅ ይሆናል፡፡ ምናልባት ለዛ ይሆን እንቅስቃሴያቸውን ሲያደርጉ የእንግሊዝና የአሜሪካ ኤምባሲዎችም (የመንግሥት እንደራሴ መሥሪያ ቤቶችም) አድራሻዎቻቸው ሊሆኑ የቻሉት፡፡

አዎ ለመታረም ካልፈቀዱ “ሴት ተማሪዎችን መርዳት!” የሚለው የተቀደሰ ዓላማ ለሽፋን የተጠቀሙበት ምክንያት መሆኑን እንረዳለን፡፡ በሰፊው እያጠፉ በጥቂቱ መገንባት ብሎ ነገር የለምና፣ አበባ ሸጠውም ተለግሰውም ያመጡትን ለጥቂት ተማሪዎች የጽሕፈት መሣሪያና የወር አበባ መቀበያ በመስጠት “ሴቶች ተማሪዎችን ለመርዳት ነው የተቋቋምነው!” ይበሉ እንጅ አስቀድሞ እንዳየነው እያደረጉት ያሉት ግን ተማሪዎችን አሳስቶ መቀመቅ የሚከት በመሆኑ፣ ማንነትን ማጥፋትና መበረዝ በመሆኑ፡፡ ያኔ እራሳቸውን ግልጽ አድርገዋልና እኛም በይፋ የምንዋጋቸው ይሆናል፡፡ እንዲያው የአስተሳሰባቸው ሰንካላነት አደገኛ በመሆኑ ነገ ሰፊ ተቀባይነት ቢያገኙ አሳሳቢ አደጋ ሊጋርጡ ይችላሉ ከሚል ሥጋት ነው እንጅ አሁን ባሉበት ሁኔታ እኮ ቁጥራቸው በጣም ጥቂትና ተማሪው እንኳ ያልተቀበላቸውና በጥርጣሬ የሚያያቸው በመሆናቸው አሁን ባሉበት ሁኔታ ሥጋት ሆነውም አልነበረም እነሱን በተመለከተ ልጽፍ የቻልኩት፡፡ ቆይ ግን እናንተ ይሄም የወያኔ እጅ ይኖርበት ይሆን? ኧረ እንጠርጥር!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
amsalugkidan@gmail.com

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.