የእማሆይ ነገር ! – ይድነቃቸው ከበደ

አንዲት መነኩሴ በታላቁ ኩዳዴ ጾም እንቁላል ያምራቸውና ፣ አንድ እንቁላል ይዘው ከገዳማቸው ወጣ ወዳ አለ ስፍራ ይሄዱሉ፡፡ የጋለ ድንጋይ ፈልገው እንቁላሉን ድንጋዩ ላይ ያፈርጡታል ።ብዙም ሳይቆይ፤ አንድ የገዳም አባት በዛ በኩል ለጉዳይ ብቅ ሲሉ፤ እማሆይ ድንጋይ ላይ እንቁላል ለመጥበስ ፀሀይን እና ድንጋይን ለማገናኘት ሲባክኑ ያገኙዋቸዋል፡፡ የገዳሙ አባት መነኩሴዎን ምነው እማሆይ ? ቢሏቸው “ሠይጣን አሳስቶኝ” ሲሉ። ሠይጣንም ቁጭ ብሎ ከእሟሆይ ሙያ እየተማረ ነበርና ብሽቅ ብሎት፤ “ የእውነት ይህን ዓይነት እንቁላል አጠባበስ ያለዛሬም አላዩሁት አለ” ይባላል፡፡

የማይገባንን ግን የምንፈልገውን ለማግኘት ደፋ ቀና ስንል፣ ለማይገባን ነገር መባከናችንን ታዝቦ ፤ እንዴትስ ይሆናል ? ብሎ ለሚጠይቀ የምንፈጥረው ሰበብ እና አላስፈላጊ ምክንያት ፤ መቼም ማለቂያ የለውም ። ምን ይሄ ብቻ የምንፈጥረው ሰበብ ወይም ምክንያት ፤ ሰበብ ወይም ምክንያት የምናደርገው ነገር ተሰምቶ ፣ ታይቶ የማይታወቅ ምን አልባትም ወደፊትም የማይኖር ጭምር ሊሆን ይችላል ። እማሆይ ሊበሉት ያሰብት እንቁላል ከምንም በላይ ደግሞ ያጠባበስ ዘዴያቸው ፤ እማሆይ ሰበብ ያደረጉት ሰበበኛው እራሱ አያውቀውም ፤ እንዳሁኹም ሰበበኛው ሰይጣን ቁጭ ብሎ ከእማሆይ ሙያ እየተማረ ነበር ። እሱም “ የእውነት ይህን ዓይነት እንቁላል አጠባበስ ያለዛሬም አላዩሁት አለ መባሉ ለዚህም አይደለ ። ሰኔ እና ሰኞ አይነት ሆነና ነገሩ ፣ ይህ ጽሁፍ እና የእማሆይ ነገር ! በኩዳዴ ጾም ገጠመ።


ከሰሞኑ የሚፃፈው ፣የሚወራው ለጉድ ነው። አንዱ ሌላውን ለመደገፈ እና ለመቃወም የሚወረወረው የነገር አንካሴ ፣የወርዋሪው ልክ-የለሽ ድፍረት ፍንትው አድርጎ የሚያስይ ነው። የራስ የሆነውን ነውርን ለሌላው ለመስጠት የምናመካኘው ሰበቡ ሲታይ ፣ እዚህ ላይ ፈጣሪ ጠብቀኝ የሚያስብል ነው ። ሌላውን መስደብ እና ማዋረድ፣ የተሳዳቢውን ጨዋነት የሚያረጋግጥ የሚመመስለን በዝተን መታየታችን አይጣል ነው። ይበልጥ ደግሞ ሰለ-ሚባለው ነገር ፣ ግራ ቀኙን መዝኖ የራስ የሆነ አቋም ለመያዝ ከመሞከር ይልቅ ፤ “ወሬ ሲንግሩህ ሃሳብ ጨምርበት” ይሉት አይነት ነገር ፣ ይሄን ሰሞን ወዲህ እና ወዲያ የሳይበር (የማህበራዊ ድረ-ገጽ) እና የመገናኛ ብዙሃን ሹኩቻው ለጉድ ነው።

ልብ ያልን እንደሆነ ፤ሰዎች ስለሌላው ጥሩ ነገር ሲነግሩን ፣ ደግመን ደጋግመን ማረጋገጫ እንፈልጋለ። ከዚያም የዛ ሰውን ጥሩነት ወይም ስኬት ቀስ ብለን ማንሻኮክ ሥራ ሆኖብን ምንዳ እንጠብቃለን ። ሆኖም ግን አንዱ ስለ ሌላው መጥፎነት ሲነግረን ምን አይነት ማረጋገጫ ሳያስፈልገን ፤ “ወሬ ሲነግሩህ ሃሳብ ጨምርበት” እንደሚባለው የራሳችንን ግምት ጨምረንበት ፍጽም ከእውነት የራቀውን የሐሰት ወሬ በመጮህ ለማሰማት እንሞክራለን ። ይህም አልበቃ ብሎን ለመቅበር ጉድጎድ እንምሳለን፣ በቆፈርነው ጉድጎዳ ማን ይቅደም ሳናውቅ። ይህ ሁሉ የአብዛኞቻችን ችግር ነው። ለዚህም የሚሻለው በጎ ልቦና ፈጣሪ እንዲሰጠን መጸለይ እና እራስንም ለበጎ ነገር ማትጋት ነው።

በጎ ልቦና ይታገሳል፣ በጎ ልቦና ይቅር ባይ ነው፣ በጎ ልቦና የተከለከለ እና የተፈቀደን ለይቶ ያመላክታል፣ በጎ ልቦና በእራስ ላይ እንዲሆን የማይፈለግ በሌላው ላይ እንዳይሆን ያስጠነቅቃል፣ በጎ ልቦና የወደቅውን ለማንሳት እንጂ የቆመውን ለመጣል አይባዝንም፣ በጎ ልቦና ለስህተት ሣይሆን ከስህተት ለመውጣት ምክንያት ይፈልጋል፣በጎ ልቦና ትላንት፣ዛሬ እና ነገን ያስባል፣ በጎ ልቦና ከፀብ እና ከሐሜት ይልቅ ፍቅርን ፣ሰላምን እና ተግሳጽን ያስቀድማል ፣ በጎ ልቦና የእማሆይ ነገር አስታውሶ ከሰበብ ይጠብቀናል። ምን ይሄ ብቻ ከዚህ በላይ የሆነውን ለማሰብና ለማድረግ የበጎ ልቦና አሰተዋአዖኦ ቀላል አይደለም ። እናም ፈጣሪ በጎ ልቦና ይስጠን፤ አሜን!!!

(ይድነቃቸው ከበደ)

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር፤ አሜን!!!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.