ፍረጃን የስህተት መሸፈኛ ያደረገው የተቃውሞ ጎራ (ምላሽ ለኢንጂነር ይልቃል)- ግሬስ አባተ

ኢ/ር ይልቃል ከSBS Amharic ጋር ያደረጉትን ቆይታ አደመጥኩት፤ በከዚህ ቀደም ፅሁፌ እንዳልኩት ‹በኢትዮጵያ የተቃውሞ ጎራ ፖለቲካ ውስጥ ለሚሰሩ ስህተቶች ሌሎችን ‹‹ወያኔ›› ማለት እራስን ከስህተት ነፃ የሚያድርግ ነው፡፡ ኢ/ር ይልቃል 22 ደቂቃዎችን በፈጀው ቆይታቸው ሌላው ሁሉ ቀርቶ በመሪነታቸው የነበራቸውን መድረኮች በመጠቀም ችግሮችን ለምን መፍታት እንዳልቻሉ እንኳ ትንፍሽ ሳይሉ ሌሎችን በባንዳነት መፈረጅ መርጠዋል፡፡ ይህ ብዙ የሚገርም አይደለም፡፡ የፓርቲው የስነስርአት ኮሚቴ እሳቸውን ጨምሮ ሌሎች አራት አባላትን የመጠየቅ አቅም መፍጠሩ በአፍራሽነት ነው ያስፈረጀው፡፡


ይህን አሮጌ የፍረጃ ፖለቲካ የሙጥኝ ብለው በዛው አንደበታቸው እንዲህ ይላሉ ‹‹ዋና ከምላቸው የሰማያዊ ፓርቲ አስተዋፅኦዎች ይህን ትውልድ ከ60ዎቹ ትውልድ ፖለቲካ አላቆ አዲስ እርሾ እንዲሆን አድርጓል›› ከዚህ በላይ ፌዝ የለም፡፡ ቁምነገሩ እኮ የተዋናዮቹ የእድሜ ለውጥ አይደለም፡፡ የአስተሳሰብና የተግባር ነው፡፡ ዛሬም ተቀናቃኝ የሆነውን አካል በጠላትነት እያዩ፣የሃሳብ ልዩነትን ከፍረጃ ተሻግረው ማስተናገድ እንኳ ሳይችሉ፣ተጠያቂነት ሲነሳ አሮጌውን ፍረጃ እየደገሙ ከ60ዎቹ ትውልድ ፖለቲካ ተላቀናል ይሉናል፡፡

ኢ/ሩ አሮጌውን ፍረጃቸውን ለማስረዳት አንድነት፣ቅንጅት፣ኦብኮ፣መኢአድ ላይ የሆነውን በድፍኑ እንደምሳሌ አቅርበዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ በሰማያዊና በመኢአድ ላይ የሆነው አንድ አይነት አይደለም፡፡ መቼም ሰርተፍኬቱን ለሰማያዊ ምርጫ ቦርድ ለመኢአድ ጤና ጥበቃ ይስጥ ካልተባለ በስተቀር፡፡ ሰርተፍኬት ሰጪው አካል አንድ በመሆኑ የሰማያዊ ሁኔታ የሌሎች ተመሳሳይ እንደሆነ የፍረጃው ሞተሮችን ማሳመን ይቻል ይሆናል፡፡ ሂደቱን የተከታተለ ሰው ግን የ’ካፈርኩ አይመልሰኝ ፖለቲካ አስቀያሚ ምሳሌ መሆኑን አይስተውም፡፡ ገና ድርድሩ ሳይጀመር ቅድመ ውይይቱን አስመልክቶ በጥርጣሬ አይን የሚታይ እንደሆነ ስለሚያውቁ ብቻ ያን ለማጠንከር በተለይ የሰማያዊ እና መኢአድ እውቅና ከዛ ጋር እንደሚያያዝ ለማሳየት የሞከሩበት አገላለፅ በፍረጃ ተጠልሎ ለማለፍ የሚሞክሩበትን እርቀት ያሳያል፡፡

የሆነው ሆኖ የኔ ክርክር የግለሰቦች ጉዳይ አይደልም፡፡ ቁም ነገሬ በአመራር ደረጃ ላይ ያሉ ሰዎች በሚፈፅሙት ስህተት የሚፈጠሩትን ችግሮች እስከመቼ በፍረጃና በገዢዎች እያሳበብንና ስህተት የሰሩትን ነፃ እያደረግን እንቀጥላለን? ይህ ለተቃውሞ ጎራው ተዋናዮች የስህተት መደበቂያ ዋሻ ሆኖ አላገለገለም ወይ? እዚህ አገር በተለይ ፓርቲዎች ከመቋቋም ጀምሮ በገዢዎች ተፅእኖ እንደሚደርስባቸው እሙን ነው፡፡ ይህ ከሆነ ለዚህ መሻገሪያውን መንገድ ማዘጋጀት የእነሱ ተግባር አይደለም ወይ? ለዚህ ሀላፊነቱን መወሰድ የለባቸውም ወይ? ይህን ሳንመልስ አለባብሰን አሮጌውን ፖለቲካ መከተል የትም የማያደርስ ብቻም ሳይሆን አንድ እግር ወደፊት አንድ እግር ወደኋላ አይነት ነው፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.