በጎንደር ችግር አለ – ብአዴን ህዝብን ሲያናግር፣ ሕወሃት ይተኩሳል – የሚሊዮኖች ድምጽ

 
ጎንደር ከተማ ከፍተኛ ተኩስ እንዳለ እየተገለጸ ነው። ጋዜጠኛ ሙሉቀን ተስፋው “ጎንደር ከተማ ቀበሌ 18 አካባቢ ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ፣ ከምሽተ 4.30 ጀምሮ መኖሩን መረጃዎች እየመጡ ነው። ከፍተኛ የሆነ ውጥረት ሲኖር መንገዶች ሁሉ ተዘግተዋል ተብሏል” ሲል ጦምሯል።
 
ከጥቂት ቀናት በፊት የብአዴን ከፍተኛ አመራር አባላት የከተማዋን ህዝብ በአክብሮት ማነጋገራቸውና ሕዝቡ አስተያየቱን በድፍረትና በወኔ መስጠቱን በተመለከተ በሰፊው መዘገቡ ይታወቃል። ሆኖም ግን፣ የብአዴን አመራሮች ሕዝቡን ለመስማት ባደረጉት ጥረት ያልተደሰቱት፣ ኮምንድ ፖስት ከሚባለው ጀርባ ያሉ የሕወሃት የደህነትና የመከላከያ ሃላፊዎች ” እነ ገዱ የፈለጉትን ስብሰባ ጠርተው ቢያወሩም ከኛ ዉጭ የትም አትሄዱም። ሃይሉ ያለው እኛ ጋር ነው” በሚል የደካሞችና የእብሪተኖችን መለስክት ለማስተላለፍ ፣ ሆን ብለው የጀመሩት ጠብ ጫሪነት ሊሆን እንደሚችል ተንታኞች ይናገራሉ።
 
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ታዉጆ፣ በርካታ ታጣቂዎች በመላክ አገዛዙ መረጋጋትን ለመፍጠር የሞከረ ቢሆንም፣ እንደ ጎንደር ከተማና ባህር ዳር፣ ካሉ ትላልቅ ከተሞች ዉጭ፣ በሌሎች ገጠራማ አካባቢዎች ከአገዛዙ ቁጥጥር ዉጭ እንደሆኑና በጎበዝ አለቃ የሚመሩ፣ ከሕዝቡ የተወጣጡ በርካታ ተዋጊዎች፣ የሚንቀሳቀሱባቸው እንደሆነ ለአካባቢው ቅርበት ያላቸው ይናገራሉ። አገዛዙ አካባቢውን ማረጋጋት ባለመቻሉም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በአማራው ክልል እንደገና ለሶስት ወራት ለማስተላለፍ እቅድ እንዳለውም ታውቄል።
 
መሳሪያ፣ ሃይል ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መፍትሄ እንዳላመጣና እንደማያመጣ የገለጹትአንድ የቀድሞ ዝነኛው የአንድነት ፓርቲ ክፍተኛ አመራር አባል ” ያ ሁሉ ወታደር ተሰማርቶ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታዉጆም፣ መረጋጋት ካልመጣ፣ ኢሕአዴግ ከሃይልና ከእልህ ፖለቲክ ያለፈ ተሻለ አማራጫን መቀበል አለበት ” ሲሉ አገዛዙ መሰረታዊ የአካሄድ ለዉጥ ካላመጣ የከፋ ችግር ዉስጥ እንደሚወድቅ ነው የተናገሩት። እኝህ የሰላማዊ ታጋይ ሲያክሉም አሁን ተጀመረ የተባለውን ድርድርን፣ ኢሕአዴግ ለሰላም፣ ለአገር ጥቅም ብቻ ሳይሆን ለራሱ ሲል እንዲጠቀምበት፣ በሕዝብ ተቀባይነት ያለው፣ የተጨበጠ ዉጤት የሚያመጣ ድርድር እንዲያደርገው ጠይቀዋል።
 
“ፍርሃት የወለደው ታጋሽነታችን ለብዙ ሕገ-ወጥ ድርጊት ጋብዞናል” የሚለው መፈክር በጎንደር ሲታይ የነበረ መፈክር ነበር። ” መንግስት ለኔ ሳይሆን በኔ ላይ ነው የቆመው” የሚል እምንት በዉስጡ ካዘለ፣ አገዛዙ የሚያወጣውን ሕግ በሙሉ አልቀበለም የሚል የእምቢተኝኘት አቋም መያዙ አይቀረም። ተጀምሯልም።
 
በመሆኑም አገዛዙ እንደከዚህ በፊቱ ሊቀጠል እንደማይችል ተገንዝቦ፣ የይስሙላን እና የማስመሰንልል የዉሸት “ተሃድሶዉን” ወደ ጎን ጥሎ፣ አንድ የጎንደር ነዋሪ እንዳሉት በድሪቶ ላይ ድሪቶ መደረቡን አቁሞ፣ ለትክክለኛና እዉነተኛ፡ለዉጥ ራሱን እንዲያዘጋጅ እንጠይቃለን።
 
ከተቃዋሚዎች ጋር የተጀመረዉ ድርድር እንደ አገር ከታሰርነበት ማነቋችን የምንወጣበት፣ የሰደዱ የሚመለሱትብት፣ ነፍጥ ያነሱ ነፍጥ የሚደፉበት፣ የታሰሩ የሚፈቱበት፣ የተጣሉ የሚታረቁበት፣ የተበተኑ የሚሰባሰቡበት፣ በዘር አድሎ ሳይኖር ሁሉም እንደ ኢትዮጵያዊ በዜግነቱ የሚከበርባትና ሁሉ በሁሉም የአገሪቷ ግዛቶች በሰላም የሚኖሩባት ኢትዮጵያ ትመጣ ዘንድ በሩን የሚከፍት ድርድር እንዲሆን ጸሎታችን ነው።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.