“ተቃዋሚዎቹ ያለገለልተኛ ታዛቢና ያለሚዲያ ተሳትፎ ወደ ድርድሩ እንዲገቡ አይመከርም” – አስራት አብርሃም

 

የሐበሻ ወግ፦  በዚህ ጊዜ ኢህአዴግ ግምገማ፣ ተሃድሶ ከዚያም ሲያልፍ ከተቃዋሚዎች ጋር ድርድር ሂደት ላይ ይገኛል። ይህ ስርዓቱ በለውጥ መንገድ ላይ ስለመሆኑ አመላካች ሊሆን ይችላል?

አስራት አብርሃም
አስራት አብርሃም

አቶ አስራት አብርሃም፦ ያለፈን ነገር እየረሳን ነው እንጂ ነገሮች ሁሉ አዲስ የሚመስሉን፣ በኢህአዴግ ቤት ግምገማም ተሃድሶም ጠፍቶ አያውቅም። ሁሌ ነው ግምገማ አድርገናል የሚባለው ጠብ ያለ ለውጥ ግን እስካሁን አላየንም። ስለተሃድሶ ካነሳን ድርጅቱ በ1993 ዓም የአቶ መለስ ዜናዊን ስልጣን መገዳደር የጀመሩ የድርጅቱ አመራሮች በህገ ወጥ መንገድ በማባረር በስብሰን ነበር አሁን ታድሰዋል እልል በሉ ተብሎ ነበር። አንድ ነገር ሁለቴ የሚታደስ አይመስለኝም። አንድ ያረጀ ነገር መታደስ የሚችለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው፤ ከዚህ በላይ ላድስህ ብትለው ድሪቶ ነው የሚሆነው። ስለዚህ ራሴን ገምግሜ ጥልቅ ተሃድሶ እያካሄደኩ ነኝ የሚለው ነገር ህዝቡን ለማረጋጋት ተብሎ ለሚዲያ ፍጆታ ተብሎ የሚነገር እንጂ በኢህአዴግ ቤት ምንም ዓይነት ግምገማም ሆነ ተሃድሶ የለም። ግምገማ ከነበረ ድሮ ህወሃት ጫካ እያለ ነበር፣ ስልጣን ከያዙ በኋላ የሚያደርጉት ግምገማ ዝም ብሎ ለይምሰል የሚደረግ ነው። ምክንያቱም የግምገማው ውጤት በተገምጋሚው ህይወትና ኑሮ ላይ ከፍተኛ ችግር የሚያስከትል በመሆኑ የምር መገማገም እየቀረ መጥቷል። ጫካ እያሉ አንድ ሰው ተገምግሞ ጥፋተኛ ነው ቢባል፣ የሚቀጣው ቅጣት ውሀ ወንዝ ሄዶ መቅዳት ወይም እንጨት መልቀም ወይም ምግብ ማብሰል ሊሆን ይችላል። በእርግጥ የሚታሰርም ይኖራል። ህይወቱን ሊሰጥ ለወጣ ታጋይ፣ በእግር ጉዞና በጦርነት ሙሉ ጊዜው ለሚያሳልፍ ታጋይ መታሰር ጥሩ ባይሆንም በግል ህይወቱ ግን የሚያመጣለት ለውጥ አልነበረም። ስልጣን ከተያዘ በኋላ ግን ግምገማ ስልጣን የሚያሳጣ ወይም የሚያሰጥ ጥቅማጥቅም የሚያስቀማ ወይም የሚያስገኝ በመሆኑ በቀላሉ የሚታይ አልሆነም። ስለዚህ በኢህአዴግ ቤት ግምገማም ተሃድሶም የለም።

ከተቃዋሚዎች ጋር ሊደረግ የታሰበው ድርድርም ቢሆን፣ እኔ ውጤታማ ይሆናል ብዬ አላስብም። ግምቴ ስህተት ሆኖ ኢህአዴግ ለእውነተኛ ለውጥ ቢደራደር ከሁሉም በላይ ደስተኛ የምሆነው እኔ ነኝ። ግን አይመስለኝም። እውነተኛ የለውጥ አቅጣጫ እያየሁ አይደለም። እንደ ኢህአዴግም በአሁኑ ሰዓት አንድነት ያላቸው አይመስለኝም። አንድ እንዳልሆኑ የሚያሳዩ ልዩ ልዩ ምልክቶች አሉ። ለምሳሌ እኔ ባለኝ መረጃ በጎንደርና አከባቢው የሚኖሩት የትግራይ ተወላጆች ላይ የደረሰው ጥቃት በዋናነት ያስተባበሩት የብአዴን ሰዎች ናቸው። በኦሮሚያ የነበረው ህዝባዊ ተቃውሞ የኦህዴድ ከፍተኛና ዝቅተኛ አመራሮች ተሳትፈውበታል ነው የሚባለው። ከሁሉም በላይ የሚገርመው ደግሞ በሶማሌ ክልል እየሆነ ያለው ነው። የክልሉ ልዩ ኃይል ይሁን ሌላ ታጣቂ ኃይል የኦሮሚያን ክልል መሬት በጦር መሳሪያ እየተደገፈ ወረራ አካሄዶ የክልሉ ባንዴራ በኃይል በሚቆጣጠራቸው ቦታዎች ላይ እየሰቀለ እንደሆነ የኦሮሞያ ክልላዊ መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ ለአዲስ አድማስ በሰጡት ቃለ መጠየቅ ተናግሯል።

ይሄ በራሱ እንግዳ የሆነ ነገር አለው፣ ሚሊሻዎችና ህብረተሰቡ በጋራ ራስን የመከላል ስራ እየሰሩ እንደሆነ ነው ኃላፊው የተናገሩት፣ ፌዴራል መንግስት ወይም መከላኪያ አላሉም። ይሄ ስርዓት የሚያስይዝና ስርዓት አልይዝ ያለውን ደግሞ አደብ የሚያስገዛ መንግስት እንዳለ የሚያመላክት አይደለም። በህወሓትና በሶማሌ ክልል ገዥ ፓርቲ መካከል እየተስተዋለ ያለው ገንፎ እስከ መጎራረስ የደረሰ ፍቅርም፣ በኢህአዴግ ውስጥ የህወሓት መዳከምና በግንባሩ ላይ ባሉት እኩዮቹ እምነት ማጣትና ሌላ አጋር ፍለጋ ወደ አጋር ድርጅቶች መውረድን ነው የሚያሳየው። ሌላው ከተቃዋሚዎች ጋር ሊደረግ በታሰበው ድርድር ላይ ከየፓርቲው የሚወከሉ ሰዎች አራት እንዲሆኑ መጠየቁ በራሱ ከኢህአዴግ አባል ድርጅቶች አንዳንድ ሰው የመመደብ ፍላጎት እንዳለ የሚያመላክት ነው።  ይሄ ደግሞ ኢህአዴግ እንደከዚህ በፊቱ በአንድ አቋም ለመቅረብ እንዳልቻለ ነው የሚያሳየው። ከዚህ እውነታ ስንነሳ ኢህአዴግ ከተቃዋሚዎች ጋር ለመደራደር ከመነሳቱ በፊት በመጀመሪያ በውስጡ ያሉትን ድርጅቶች ቢያደራድር ነው የተሻለ የሚሆነው። እነርሱ እርስ በራስ ሳይግባቡ እንዴት ነው ከተቀዋዎች ጋር መደራደርና መግባባት የሚችሉት!

የሐበሻ ወግ፦ ገዥው ፓርቲ ከ21 ፓርቲዎች ጋር ድርድር ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ ነው። በዚህ ጉዳይ እንደ አንድ ፖለቲከኛ ምን ይላሉ?

አቶ አስራት አብርሃም፦ ከላይ ለመግለፅ እንደሞከርኩት ኢህአዴግ በውስጡ ያለውን ችግር ሳይፈታ ስለሆነ ወደ ድርድሩ እየገባ ያለው ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ሊደረግ የታሰበው ድርድርም ውጤት ይኖረዋል ብዬ አልጠብቅም። ይሄ ከማየው ነገር ተነስቼ ነው እየተናገርኩ ያሉት፣ እያሟረትኩ አይደለም። አንደኛ 21 የሚባል እውነተኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በዚህ ሀገር የሉም። እውነተኛ ተቃዋሚዎች አሉ ወይ ብለህ ስትነሳ ቁጥራቸው አንድ ጣት እንኳን አይሞላም። ሌሎቹ ኢህአዴግ በምርጫ ቦርድ ከተመደበለት ገንዘብ ሳይቀር የሚዶግማቸው፣ ኢህአዴግ ለሚፈልገው የማስመስል ዓላማ ካልሆነ በስተቀር ምንም ዓይነት ህዝባዊም ሆነ ሀገራዊ ግብ የሌላቸው ናቸው። የእነዚህ ዓይነቶቹ መሪዎች ማየት ትችላለህ፣ ፖለቲካን ለኢኮኖሚ ያሉ ናችው፣ ህብረተሰባዊ ክብር የላቸውም፣ እነርሱም እንጀራ ፈልገው እንጂ ክብር ፈልገው ዓላማ ይዘው ወደ ፖለቲካው የመጡ ናቸው። ከእነዚህ ጋር ምን ዓይነት ፖለቲካ ነው የምትሰራው። አይደለም ለእውነተኛ ተቃዋሚዎች ለኢህአዴግ ለራሱ እኮ ከእነዚህ ጋር ቁጭ ብሎ መምከር የሚያሳፍር ነው። ለኢህአዴግ ጉዳዩ ህልውና ጉዳይ ስለሆነ ማፈሪያው ቁጥም አድርጎ በልቶት ሊሆን ይችላል። ለእውነተኛ ታጋች ግን ይሄ እጅግ የሚያሳፍር ነገር ነው።

ከዚህ ውጪ ያሉት እዚህ ግባ የሚባል አቅም የሌላቸው። ግን ደግሞ በሀገር ጉዳይ ላይ መቼም ቢሆን ተስፋ መቅረጥ ስለማይግባ፣ ድርድሩ ቢሳካ ብለን እናስብና በተቃዋሚ ፓርቲዎች በኩል መደረግ ያለባቸው ነገሮች ላይ የተወሰነ ነገር ልበል። በመጀመሪያ እውነተኛ የሆኑ ተቃዋሚዎች ለብቻቸው ነው ተነጥለው መቅረብ ያለባቸው። ኢህአዴግም የእውነት የመደራደር ፍላጎት ካለው ከእነዚህ ጋር ነው መነጋር ያለበት። ከእነ አየለ ጫሚሶ እና ከእነ ትዕግስቱ አወሉ ጋር ድሮውም ልዩነት የለውም፣ ጠብም የላቸውም።

ድርድሩ ምን መሆን አለበት? በምን መልኩ ይካሄድ ለሚለው ደግሞ (ይሄ ሀሳብ የእኔ ብቻ ላይሆን ይችላል፣ ከተወሰኑ ጓደኞቼ ጋር ቁጭ ብለን የተነጋገርንባቸው ናቸው።) አንድኛ ይሄ ፖለቲካዊ ድርድር እንጂ የፖሊሲ ክርክር እንዳልሆነ ሁሉም ተደራዳሪ ወገኖች ከግንዛቤ የሚያስገቡት ነገር መሆን አለበት። የፖሊሲ ክርክር የሚኖረው ከድርድሩ በኋላ፣ ነገሮች ሁሉ ተስተካክለው ወደ ምርጫ ቅስቀሳ ሲገባ ነው። አለበለዚያ ከፈረሱ ጋሪው ማስቀደም ነው የሚሆነው። የድርድሩ ይዘት በተመለከተ ደግሞ በዋነኝነት የተበላሸውን የፖለቲካ ምህዳር ማስተካከል ላይ ያተኮረ ነው መሆን ያለበት። ይህም፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሀገሪቱን ህግ አክብረው በሰላማዊ መንገድ እንደፈለጉ እንዲንቀሳቀሱ፣ አባላት እንዲያደራችሁ፣ ፕሮግራሞቻቸውን በሚዲያ፣ በስብሰባ በልዩ ልዩ መንገድ ለህዝቡ በነፃነት እንዲያስተዋውቁ መንግስት ተገቢውን ኃላፊነት ለመወጣት መፈረም አለበት። የፖለቲካ እና የህሊና እስረኞች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ፣ ከዚህም በኋላ ሰው በፖለቲካና በእምነቱ ምክንያት እንዳይታሰር፣ በተለያየ ጊዜ የወጡት አፋኝ ህጎችና አዋጆች እንዲሻሩ ወይም እንዲሻሻሉ ማድረግ፣ (የምርጫ ስርዓቱ ይቀየራል፣ ፓርቲዎች ባገኙት ድምፅ ልክ ተመጣጣኝ ውክልና ይኖራል የሚል ነገር አለ) ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ህገ መንግስቱን ማሻሻል ይጠበቅበታል። ብእርግጥ ህገ መንግስቱ የሚሻሻል ከሆነ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ህዝቡ መክሮበት የሚጨመር ተጨምሮ የሚቀነስ ተቀንሶ ነው መሻሻል ያለበት። የመንግስት ተቋማት፣ የፍትህ አካላት ከፖለቲካዊ ተፅዕኖ ነፃ ሆነው የሚሰሩበት ሁኔታ መፈጠር አለበት። ከሁለም በላይ ደግሞ እውነተኛ የስርዓት ለውጥና ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር በዚህ ሀገር እንዲኖር ከተፈለገ አሁን ያለው ምርጫ ቦርድ ሙሉ ለሙሉ ፈርሶ ሁሉም ተደራዳሪ ፓርቲዎች የተስማሙበት ከፖለቲካዊ ተፅዕኖ ነፃ የሆነ አዲስ ምርጫ ቦርድ መቋቋም አለበት። መንግስት ለፖለቲካ ፓርቲዎች የሚመድበው ገንዘብ በፍትሀዊ መንገድ መከፋፈል፣ በመንግስትና ልዩ ልዩ ሚዲያዎች ላይ ሁሉም በእኩልነት የመጠቀም መብት መከበር፣ ፓርቲዎች በነፃነት ፐሮግራሞቻቸውን እንዲያስተዋውቁ ሁሉም ሚዲያዎች ማተሚያ ቤቶች ጭምር ክፍት እንዲሆኑ ማድረግ፣ ምንም ነገር በስልክ በልዩ ልዩ መንገድ የሚደረግ ማንኛውም ተጽዕኖ ማስፈራራት መቆም አለበት።በፅሁፍ ካልሆነ በቃል የሚደረግ ትዕዛዝም ሆነ እገዳ በግልጽ መከልከል፣ ይሄ በድርድሩ መጨረሻ ላይ በሚወጣው አዋጅ በግልፅና በማሻማ መልኩ መደንገግ አለበት። ድርድሩ በዋናነት በእነዚህ ወሳኝ ጉዳዮች ላይ ነው መሆን ያለበት።

የሐበሻ ወግ፦ ድርድሩ የህዝብ ተቃውሞ እንቅስቃሴ ውጤት እንደሆነ ብዙዎችን ያስማማል። ከዚህ አንፃር ከዚህ ድርድር የህዝቡ ጥያቄና ፍላጎት ምላሽ ያገኛል ብሎ ማሰብ ይችላል?

አቶ አስራት አብርሃም፦ ስርዓቱ ለእውነተኛ ለውጥ ከተነሳና ከላይ ያስቀመጥኳቸው ነጥቦች ላይ ስምምነት ላይ መድረስ ከተቻለ የህዝብ ጥያቄ ይመለሳል፤ ፍላጎቱም ቢሆን ይሟላል ብዬ ነው የማስበው። እንዲያ ከሆነ ደግሞ እውነትም ኢህአዴግ ተቀይሯል ማለት ነው። ስለዚህ ነገር ሳስብ አንድ ነገር ነው ትዝ የሚለኝ። አንዲት የዘመዴ ሚስት ነበረች። በሆነ ጊዜ “አቡነ አረጋዊ በራዕይ ታዩኝ፣ የዚህ ዓለም ኑሮ በቃሽ፣ ከዚህ በኋላ ለነፍስሽ እደሪ” ብለውኛል ብላ ባሏንም ልጆቿንም ትታ መነነች፣ ገዳም ገብታ ቆብ ደፋች። ከቄሶቹም፣ ከሰባኪዎቹም በላይ ሆኗ በንግሱ ቤቱ እየዞረች “ንስሀ ግቡ” ስትል ከረመች። በመሀል ነገርዬው ስታስበው ቆጫት መሰለኝ አሁንም “አቡነ አረጋዊ በራዕይ ታዩኝ፣ ገና የምትወልጂው ልጅ አለሽ፣ ከገዳም ውጪ” አሉኝ ብላ ቆቡን ጣለችና ጋሜ ተስርታ ሌላ ጎረምሳ አገባች፣ ወለደችም። የመጀመሪያ በሏ ሌላ አግብቶ ትዳር ይዞ ስለነበር ወደ እርሱ መመለስ አልቻለችም። የኢህአዴግም ነገር እንደዚያው ነው። የሆነ ነገር ያምረውና ማድረግ ይፈልጋል። የሚያደርገው ነገር ስልጣኑን የሚያሳጠው መስሎ ከተሰማው ደግሞ ቀድሞ ወደ ነበረበት ዓይኑን በጨው አጥቦ ይመለሳል።

የሐበሻ ወግ፦  ፓርቲዎቹ ወደ ዋናው ድርድር ከመገባቱ በፊት እያንፀባረቁት ያለው ሀሳብ በርካታ ነው። ከዚህ አንፃር በድርድሩ እነዚህ ፓርቲዎች  በኢህአዴግ ላይ ተፅዕኖ ለማሳረፍ አይቸገሩም?

አቶ አስራት አብርሃም፦ በጣም ይቸገራሉ እንጂ ከላይ እኮ ገልጨዋለሁ። አንዳንዶቹ ምንም ዓይነት የህዝብ ዓላማ የሌላቸው የእንጀራ ድርጅቶች ናቸው፣ መሪዎቻቸውም ከኢህአዴግ ጎን ቁጭ ብለው በቲቪ ሲያወሩ ነው መታየት የሚፈልጉት፣ የሆነ ሊያበሽቁት የፈለጉት ሰው ያለ ነው የሚያስመስልባቸው፣ በቅርብ ሊያገኙት ስለማይችሉ በቲቪ መስኮት ወደ ሳሎኑ ዘው ብለው ገብተው ያን ሻጋታ ሀሳባቸው ሲናገሩ እንዲሰማቸው ይፈልጋሉ። ነገሩ ብሽሽቅ ነው የሚመስለው፣ ህዝብ ለማብሸቅ ቆርጦ መነሳት ግን አሳፋሪ ነው። ስለዚህ ኢህአዴግ እውነተኛ ድርድር ለማድረግ ከተነሳ የህዝብ አጀንዳ ካላቸው ብቻ ድርድሩ እንዲካሄድ ነው መስማማት ያለበት። አለበዚያ ግን እርሱና የእርሱ ጥላዎች በተጋበዙበት ሁኔታ ድርድር መቀመጥ ፋይዳ ያለው ነገር አይደለም።ድርድሩ በዚህ መልኩ ከሚካሄድ ቢቀር ነው የሚሻለው፣ እውነተኛ ፓርቲዎች በዚህ መልኩ የሚደረግ ድርድር የህዝብ ጥያቄ ስለማይመልስ ከድርድሩ ነው ራሳቸው ማግለል ያለባቸው። ኢህአዴግ የእውነት መደራደር ካልፈለገ እዚያ ከህዝብ ጥያቄ ጋር ፊት ለፊት እንዲጋፈጥ መተው ያለበት። ለእውነተኛ ድርድር የራስን ስራ እያከናወኑ መጠበቅ ከሁሉም የተሻለ አማራጭ ነው የሚሆነው። መጨረሻው ውጤት ላይኖር ጊዜ መግደል አያስፈልግም።

የሐበሻ ወግ፦  ለድርድሩ ህዝብ እውቅና እንደሰጠው በምን ማወቅ የሚቻል ይመስሎታል?

አቶ አስራት አብርሃም፦ ህዝቡ ለውጥ ይፈልጋል። ያሉበትን ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እንዲፈቱለት ይፈልጋል። ኢህአዴግ እነዚህ ነገሮች በራሱ ጊዜ ሊፈታቸው እንዳልቻለ ደግሞ የታወቀ ነገር ነው። ስለዚህ ከዚህ ድርድር ከሚገኘው ውጤት እሱን ተከትሎ ከሚደረግ ለውጥ መፍትሄ ይጠብቃል። ሲቀጥል ደግሞ እውነተኛ የሆነ ሰላማዊ ውድድር በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ኖሮ፣ ፓርቲዎቹ በፕራግራሞቻቸውና በፖሊሲዎቻቸው ላይ ተከራክረው፣ ህዝቡን ቀስቅሰው በምርጫ ተውዳድረው ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር እንዲኖር ህዝቡ ይመኛል። ስለዚህ አሁን ለድርድሩ እውቅና ሰጥቶታል ወይስ አልሰጠውም የሚለው ነገር ለማወቅ አስቸጋሪ ቢሆንም ድርድሩ እውነተኛ መፍትሄ የሚያመጣ ከሆነ ህዝቡ ድጋፍ የማይሰጥበት ምንም ዓይነት ምክንያት አይኖርም።

የሐበሻ ወግ፦  ድርድሩ የመገናኛ ብዙሃን እየተከታተሉ ህዝብ ጋር እንዳይደርስ ከወዲሁ ሀሳቦች እየቀረቡ ነው። ፓርቲዎቹ ድርድሩ ከሚዲያ ውጪ ለማድረግ የፈለጉት ለምን ይመስሎታል?

አቶ አስራት አብርሃም፦ በመሰረተ ሀሳቡ የጉዳዩ ባለቤት ህዝብ በመሆኑ የድርድሩን ሂደት ከህዝብ ዓይና ጆሮ ውጭ እንዲሆን የመፈለግ ነገር ካለ ጤናማ ፍላጎት አይመስለኝም። በሌላ በኩል ካየነው ደግሞ ከአሁን በፊት ከነበረው ልምድ አንፃር በቅንጅት እና በኢህአዴግ መካከል ተጀምሮ በነበረው ድርድር ላይ ሚዲያዎቹ ፓርላማ አትግቡ የሚለውን ሀሳብ ያራግቡ ስለነበር በድርድሩ ሂደት ላይ አሉታዊ ሚና አልነበራቸውም ማለት አይቻልም። የሆነ ሆኖ ሚዲያዎቹ የድርድሩን ሂደት እንዳይከታተሉ ከመዝጋት ይልቅ ግንቢ ሚና እንዲጫወቱ መምከርና ማሳሰቢያ መስጠት ነው የተሻለ የሚሆነው። በተለይ ለተቃዋሚዎቹ ያለገለልተኛ ታዛቢና ያለሚዲያ ተሳትፎ ወደ ድርድሩ እንዲገቡ አይመከርም። አቋሞቻቸው የህዝብ ጉዳይ እስከሆኑ ድረስ የድርድሩን ሂደት ከህዝብ እንዲሰወር መስማማት የለባቸውም። ኢህአዴግ በስውርም በግልፅም ሂደቱን ከመቅረፅ ወደኋላ ይላል ተብሎ አይታሰብም። እንዲያውም በሆነ ምክንያት ድርድሩ ቢቋረጥ ወይም በመጨረሻ ላይ ስምምነት ላይ ሳይደረስ ቢቀር በብቸኝነት በሚይዘው የድርድሩ ቀረፃ ነው ፕሮፓጋንዳ የሚሰራባቸው። እንዲያም እኔ የምመክረው ከሚዲያዎቹም በተጨማሪ ራሳቸው ፓርቲዎቹ የድርድሩን ሂደት በሙሉ በድምፅና በምስል መቅረፅ፣ በሰነድ መያዝ ነው ያለባችው። ይሄ ታሪክም ነው።

የሐበሻ ወግ፦  ይህ ሚዲያን የማቀብ ሀሳብ ከተቃዋሚዎች ሲመጣ ደግሞ አንድምታው እንዴት ይገለፃል?

አቶ አስራት አብርሃም፦ እኔ እስካሁን በተቃዋሚዎች በኩል ሚዲያ አይኑር የሚል ነገር አልሰማሁም። አንድ የተቃዋሚ ተወካይ ብቻ እንዲያ እንዳሉ አዲስ አድማስ ዘግቦት አይቻለሁ። ይህም ቢሆን የአፍ ወለምታ ነው የሚሆነው። የእውነት እንደዚያ የሚፈልጉ ከሆነ ግን ነገርዬ አስገራሚ ነው የሚሆነው። እንግዲህ አንድ ጉልበታም ጎረምሳ እና አንዲት ኮረዳ “ያለታዛቢ ቤት ዘግተን ነው መጫወት የምንፈልገው” ካሉ፤ ከሁሉም በላይ በኮረዳዋ ብሶ “ማንም እንዲኖር አልፈልግም” ካለች ምን ማለት ይቻላል። ወይ ከእርሱ ጋር ሌላ ነገር ለማድረግ አስባለች ማለት ነው ወይም “ከዘመዶቿ” በላይ እርሱን አምነዋለች ማለት ነው።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.