ስለባንዳዎቹ እውነቱን ከጠየቃችሁማ ይሄው (ኤርሚያስ ቶኩማ)

ጀግናው ራስ አሉላ

ኢትዮጵያውያንን ለዘመናት ከውጭ ወራሪዎች እየመጡ እንደፈለጉ ህዝቧን እንዲጨፈጭፉ ታሪካዊ ቅርሶቿን እንደፈለጉ እንዲዘርፉ ረዳት በመሆን ያገለገለው ከተከዜ በስተሰሜን ይገኙ የነበሩ ባላባቶች በተለይም ነገስታቱ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ከተከዜ ማዶ ነገስታቶች መካከል አጤ ዮሐንስ ፣ ልጃቸው ራስ መንገሻ፣ ጀግናውን ራስ አሉላን የገደለው የተምቤኑ ራስ ሐጎስ እና ኃይለስላሴ ጉግሳ ዋነኞቹ ናቸው፡፡ እነዚህ ባላባቶችና ነገስታት ከ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ ጀምሮ ኢትዮጵያን ከውጭ ወራሪዎች ጋር በመሆን ያወደሙ ብዙም ያልተወራላቸው ባንዳዎች ናቸው ቢወራም ስለኃይለስላሴ ጉግሳ እንጂ ስለሌሎቹ ብዙም አይፃፍም አንድነትን ይጎዳል ተብሎ ስለሚታሰብም እንዲወራ አይፈልግም፡፡

አጤ ዮሐንስ የሌላኛው ባንዳ የእንደርታው ገዢ የራስ አርአያ እህት ወይዘሮ ወለተ ሥላሴ ልጅ ናቸው፡፡ አጤ ዮሐንስ በወቅቱ የኢትዮጵያ ንጉስ የነበሩትን አጤ ቴዎድሮስን ከስልጣን አስወግደው የኢትዮጵያ ንጉስ ለመሆን ያልሞከሩት ነገር የለም ከእነዚህም ውስጥ የተሳካላቸው የኢትዮጵያና የእንግሊዝን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መቋረጥ በመጠቀም ለእንግሊዞች በማደር የሠሜኑ የኢትዮጵያ ክፍልን ለእንግሊዝ ወታደሮች ክፍት በማደረግ አጤ ቴዎድሮስ የሚገኙበት መቅደላ ድረስ የሚሸኙ ሰዎችን በማዘጋጀትና ወታደሮቹን መንገድ እንዲመሩ በማድረግ መቅደላ ድረስ ከአፍ እስከገደፉ የታጠቀውን የእንግሊዝ ወታደሮች ወስደው አጤ ቴዎድሮስ አማራጭ እንዲያጡና እራሳቸውን እንዲያጠፉ በማድረግ ከእንግሊዞች የተገባላቸውን ቃል ተቀብለው አክሱም ላይ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገስት ተብለው የተሾሙ ናቸው፡፡ አስገራሚው ነገር በንግስና ቀናቸው ለእንግሊዝ ወታደሮች እና መንግስት ምስጋናቸውን ያቀረቡ ናቸው ለእንግሊዝ መንግስት የጻፉት ደብዳቤ አጤ ቴዎድሮስን ለመውጋት በመጣው ጦር ውስጥ የተሳተፉት ዌልሄምሰን በፃፉት የታሪክ ማስታወሻ ላይ ይገኛል፡፡ እንግሊዞችም ለአጤ ዮሐንስ ውለታ ኢትዮጵያውያንን ለመውጋት ይዘውት መጥተው የነበሩትን መሳሪያዎች ለንጉሱ ሠጥተው ሄደዋል፡፡

ሌላኛው ባንዳ የአጤ ዮሐንስ ልጅ የሆነው የትግሬው ገዢ ራስ መንገሻ ነው፡፡ ራስ መንገሻ የአድዋ ጦርነት ሊካሄዱ ወራቶች ሲቀሩት ከጣልያኖች ጋር በመስማማት የትግራይ ህዝብ ከኢትዮጵያ ጦር በተቃራኒ እንዲቆምና ለጣልያን እንዲያድር ጣልያንን የጠላ ጠላቴ በማለት የፋሺሽት ጣልያን ወታደሮች ከበሮ እየተደለቀላቸው ወደኢትዮጵያ ድንበር እንዲገቡ ምክንያት የነበረ ሰው ነው፡፡ ይህ ታሪኩ ግን ብዙም አይወራም የማይወራበት ምክንያት ሃሰቡን ቀይሮ የፈፀመው መልካም ተግባር ስላለ ሳይሆን ቢወራ እና እውነታው ቢታወቅ ህዝቦችን ከማራራቅ በተለየ ሊፈጠር የሚችል ነገር ስለማይኖር እውነታው እንዲደበቅ ተደርጓል፡፡

ሶስተኛው ባንዳ የተንቤን ተወላጁን ጀግናውን የእንግዳ እቁበን ልጅ የራስ አሉላን ህይወት የነጠቀው የተምቤን ገዢ የነበረው ራስ ሐጎስ ነው፡፡ ይህ ግለሰብ ከጣልያኖች ብዙ ድጋፍና እርዳታ ይደረግለት የነበረ እና ራስ አሉላን እንዲበቀል ከፋሽሽት ኢጣልያ ትዕዛዝ የተሠጠው ህሊናው በገንዘብና በጥቅም የታወረ ግለሠብ ነበረ፡፡ ራስ አሉላ ከአድዋ ድል በኋላ ሐገር ሰላም ብለው በተቀመጡበት ወቅት ይህ ባንዳ ራስ ሐጎስ የሚባል የጣልያን ተላላኪ ወታደሮችን አዘጋጅቶ የራስ አሉላ ጦር ባልተዘጋጀበት ሁኔታ ጦርነት በመክፈት የራስ አሉላን እግር በጥይት በመምታት ጀግናው የኢትዮጵያ ባለውለታ ራስ አሉላ አባነጋ እንደ አውሮፓውያኑ የዘመን አቆጣጠር የካቲት 15 1897 ህይወታቸው እንዲያልፉ ያደረገ ታሪክ ሊረሳው የማይገባው የጣልያን ተላላኪ ነበረ፡፡

አራተኛው ባንዳ ብዙዎቻችን የምናውቀው ኃይለስላሴ ጉግሳ ነው፡፡ ኃይለስላሴ ጉግሳ የአጤ ዮሐንስ የልጅ ልጅ ነው፡፡ ይህ ባንዳ ከራስ ስዩም ጋር በመሆን ትግራይን ለሁለት ከፍሎ ሲመራ የነበረ ግለሠብ ሲሆን በወቅቱ የኢትዮጵያ ንጉስ የነበሩት አጤ ኃይለስላሴ ልጃቸውን ዘነበወርቅን ገና በ13 ዓመት እድሜዋ የዳሩለት ግለሰብ ነው፡፡ ይህ እንሰሳ የ13 ዓመት ልጅ የነበረችውን ዘነበወርቅ በማስረገዝ በወሊድ ምክንያት ህይወቷ እንዲያልፍ ያደረገ ነውረኛ ግለሠብ ነው፡፡ ባንዳው ኃይለስላሴ ጉግሳ እንደቀደምቶቹ ኢትዮጵያን ለመካድ ከነበረው ፍላጎት የተነሳ አጤ ኃይለስላሴን የምገዛው መሬት ስላነሰኝ ግዛት ይጨመርልኝ በማለት ቁርሾውን ከጀመረ በኋላ የ2ኛው የጣልያን ወረራ ሊነሳ አቅራቢያ መስከረም 28 ቀን ከአዲስ አበባ ጋር የሚገናኘውን የስልክ መስመር በሙሉ በጣጥሶ በወታደሮቹ ታጅቦ አስመራ በመግባት ለጣልያን ለማደር የተስማማ ነው፡፡ እዚህ ጋር እጅግ ልብ የሚነካው ተግባር የእርሱ ወታደሮች የፈፀሙት ተግባር ነው፡፡ ኃይለስላሴ ጉግሳ 12000 ወታደሮች የነበሩት ሲሆን ባንዳ ለመሆን መስማማቱን ሲያውቁ አስመራ ድረስ አብረውት ለመሄድ የተስማሙት አንድ ሺህ ብቻ መሆናቸውን ደቦና በመፅሃፉ ገልጧል፡፡ ኃይለስላሴ ጉግሳ ከባንዳነቱ በተጨማሪ አንዳንድ የትግራይ ሹማምንት ለኢጣልያ እንዲያድሩ በማድረግ ጣልያኖች በነፃነት የትግራይ ምድር ላይ እንዲጨፍሩና የትግራይ ህዝብ ላይ እንደፈለጋቸው እንዲፈነጩ ያደረገ ባንዳ ነበረ፡፡
ደንቆሮን ደንቆሮ ካላልከው ደንቆሮነቱን ሊረዳ አይችልም ይላሉ አባቶቻችን እውነት ነው ደንቆሮን ደንቆሮ ልንለው ይገባል ችግሩ የዘንድሮዎቹ ደንቆሮዎች ደንቆሮ ብንላቸውም ሊሠሙን አልቻሉም ምክንያቱም ደንቆሮ መስማት አይችልምና ሆኖም እውነታውን አሁንም ቢጠቅምም ባይጠቅምም ከዚህ በኋላም መፃፋችንን እንቀጥላለን፡፡

ቸር ያገናኘን
#ኤርሚያስ_ቶኩማ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.