ኦሮሞ ማህበረሰብ ላይ የተመዘዘዉ የወያኔ የበቀል በትር? – ሸንቁጥ አየለ

ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል እየተነሳ ከ12 በላይ በሚሆኑ የኦሮሚያ ወረዳዎች ላይ የጥቃት እርምጃ ስለሚወስደዉ እና ወረዳዎቹን ስለሚወረዉ ህገወጥ ሀይል የጀርመን ድምጽ ሰፊ ዘገባ አቅርቧል:: የጀርመን ድምጽ የኦሮሚያ ክልል ባለስልጣኖችን እያነጋገር ለመስማት የሚዘገንኑ ሀቆችን ሲያቀርብ ያደመጠ ኢትዮጵያዊ ሁሉ በወያኔ በቀልተኛ እርምጃ መበሳጨቱም መገረሙም አይቀርም:: ይሄ ከሶማሌ ክልል የሚነሳዉ ወራሪ ሀይል በኦሮሚያ ክልል ያለዉን ማህበረሰብ የማፈናቀል: ወረዳዎችን የመዉረር ብሎም ወረዳዎቹን የሶማሌ ክልል ናቸዉ ብሎ የሶማሌ ክልል ባንዲራን በወረራቸዉ ወረዳዎች ላይ የማዉለብለብ እርምጃ እየወሰደ እንደሚገኝ ተብራርቶ ቀርቧል::

ይሄዉ ህገወጥ ሀይል የኦሮሚያ ወረዳዎች የሶማሌ ወረዳዎች ናቸዉ የሚል መግለጫ እየሰጠ ኦሮሞዉን እያፈናቀለ ወረዳዎቹንም በቁጥጥሩ ስር እያደረገም እንደሆነ ያደመጠ ሁሉ ወያኔ በቀጣይነት ኢትዮጵያዉያንን እርስ በርሳቸዉ በክልል ግዛት ጉዳይ ሊያጫርሳቸዉ በሰፊዉ እንዴት እንዳቀደ ግልጽ ይሆንለታል::የሚያሳዝነዉ ደግሞ የፌደራል መንግስቱ እና የሶማሌ ክልል መንግስት በኦሮሚያ ክልል መንግስት አገላለጽ መሰረት ይሄ ከሶማሌ እየተነሳ ኦሮሞዉን እየፈጀ ስላለዉ ሀይል ሲጠየቁ ይሄ ሀይል ከመንግስት ቁጥጥር ዉጭ ነዉ እያሉ የፌዝ መልስ እየሰጡ ነዉ:: ሆኖም የኦሮሚያ ባለስልጣናት በመረጃ ለጀርመን ድምጽ እንዳቀረቡት ይሄ ከሶማሌ ክልል የሚነሳዉ ህገወጥ ሀይል የሰለጠነዉ እና የሚታዘዘዉ በህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ /ህዉሃት/ ነዉ::

የዚህ ሁሉ ዋና ማጠንጠኛዉ ግብ በቀል ነዉ::ኦሮሞው ለምን የዲሞክራሲያዊ መብቴ ይከበር የሚል ጥያቄ አነሳ የሚል ታሳቢ ነዉ::ወያኔ ስልጣን የያዘ አመታት ዉስጥ አንድ ሸዉራራ ታሳቢን አንግቦ ነበር ወደ ስልጣን የወጣዉ::ይሄዉም ኦሮሞዉን እያሞኘሁና እያስፈራራሁ ዘላለሜን እጋልበዋለሁ: አማራዉን ደግሞ በሌሎች ብሄሮች እያስቀጠቀጥሁና አከርካሪዉን ሰብሬ ለዘላለም እገዛዋለሁ የሚል ቀመርን ይዞ ነበር የተነሳዉ::

በወያኔ ቀመር መሰረት እነዚህን ሁለት ትልልቅ ብሄረሰቦች እርስ በእርስ ከፋፍለህ ግዛዉ ከተቆጣጠራቸዉ ሌላዉ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ አስቸግሮም አያስቸግረዉም:: ሆኖም ወያኔ ያሰበዉ እና የቀመረዉ ስትራቴጅ ስህት መሆኑን ሀያ አምስት አመታት ሙሉ የኦሮሞ ህዝብ ወያኔን ተጋፍጦ ስለዲሞክራሲያዊ መብቱ እየሞገተዉ ይገኛል::በተለይም በመላዉ ኦሮሚያ ተነስቶ የነበረዉ የኦሮሞ ተቃዉሞ ወያኔን በኦሮሞ ማህበረሰብ ላይ የበቀል በትሩን እንዲያነሳ አድርጎታል::አንዱ የበቀል በትሩም ኦሮሞዉን ከሶማሌ ክልል በሚነሳ ህገወጥ ሀይል ማስቀጥቀጥ ማፈናቀል እና ማስጨረስ ሆኖ ተከስቷል::

ወያኔ ምናልባትም የኦሮሞን ማህበረሰብ በአራቱም አቅጣጫ ከልዩ ልዩ የሀገሪቱ ማህበረሰቦች ጋር በማጋጨት እና በማስጨረስ የመጨረሻዉን የበቀል እርምጃ ሊወስድበትም እየተዘጋጀ ሊሆን ይችላል::

የኢትዮጵያን ህዝብ በአጠቃላይ ለመታደግ እና ለመፈወስ ኢትዮጵያዉያን የተቃዉሞ ሀይላት አንዱ የአንድነት ሀይል: ሌላዉ የብሄር ሀይል ተባብለዉ ለዬብቻ ሳይሮጡ ቁጭ ብለዉ በጥበብ እና በሰከነ መልክ ቢመክሩ ብቻ ለሁሉም የምትመች እና ሁሉም የሚስማማባትን ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ መፍጠር ይቻላሉ:: የኦሮሞ ተቃዉሞ ሀያላትም ከወንድሞቻቸዉ የአማራ ተቃዉሞ ሀይላት ጋር ያለባቸዉን የልዩነት መሰረት ለሁለቱም ማህበረሰብ በሚበጅ መልክ ፈትተዉ እንዲሁም መላዉ የኢትዮጵያን ህዝብ በሚጠቅም መልክ ኢትዮጵያን ለማዳን ከአንድነት ሀይሉም ጋር ተባብረዉ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን መፍጠር ላይ ቢተጉ መልካም ይመስለኛል::

ኢትዮጵያዉያን ሁሉ በደንብ ሊረዱት የሚገባዉ የዲሞክራሲያዊነት ምርጫ እና የመጻኢዉ ጊዜ ምልዓታዊ የማህበረሰብ ብልጽግና ሁሉ በራሳቸዉ እጅ ብቻ እንደሚገኝ ቢረዱት መልካም ነዉ::ከዚያ ዉጭ ድጋፍ ከዚያ ወይም ከዚህ የዉጭ ሀይል ወይም ከዚህኛዉ ወገን ለዚህኛዉ ማህበረሰብ ተብሎ የሚሰጥ ድጋፍ ሁሉ ሁሉንም ማህበረሰብ የማያድን ስለሚሆን የመጨረሻዉ ጉዞ ወደ ጥልቁ መርዛማ ባህር ነዉ::መፍትሄዉ ኢትዮጵያዉያን ብቻቸዉን ቁጭ ብለዉ የማንንም የዉጭ ሀይል እጅ ሳያስገቡ ይነጋገሩ: ይመካከሩ: መወቃቀስም ካስፈለገ ይወቃቀሱ: ሀይለኛ እና ፍጹም የአማራጭ ሀሳቦች ላይ ይከራከሩ::

በመጨረሻም ለሁሉ ወገን የሚበጀዉን የተሻለ አማካይ እና አካታች መስመር በመከተል አንዲት ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን በመፍጠር በመላዉ ኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ብቻ ሳይሆን በጎረቤት ህዝብ ላይ እየተፈጠረ ያለዉን ያለመረጋጋት እና የመከራ አዙሪት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስቀረት ይስሩ:: ኢትዮጵያዉያን ከተባበሩ ወያኔን አንድም በድርድር ወይም በሀይል ከወንበሩ የማንሳት ስራም የሳምንታት ስራ ብቻ ይሆናል:: ሌላዉ ምርጫ ሁሉ የጨላማ ጉዞ ብቻ ሳይሆን ጥልቅ አዙሪት ነዉ::

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.