የማለዳ ወግ …” አትደናገር ፣ ኢትዮጵያ እንደሁ አትጠፋም ” – ነቢዩ ሲራክ

====================================
* “ዓድዋ በህብረት አሸንፈናል ፣ ማይጨው ላይ ተለያይተን ተሸንፈናል”
* ” ኢትዮጵያ ባንተ አልተጀመረችም ፣ ባንተ አትጠፋም !”
* ” በእኔ ኢትዮጵያዊነት ችግር ካለብህ ያንተ ነው ችግሩ ”
ፕሮፊሰር ኃይሌ ገሪማ

ትናንት 121 ኛውን የዓድዋ የነጻነት ድል በአል በታላቅ ክብር አዘክረን ሸኝተነዋል ። አድዋን ስናዘክር በኢህአዴግ የአገዛዝ ዘመን አኩሪ ታሪካችን ለምን አኮሰስነው? በሚለው ዙሪያ ብዙ ተብሎ ብዙ መላ ምቶችን ተናግረን ሰምተናል ! ዘንድሮ ለአድዋ ዝካሬ ቀርበው ቀልቤን ከሳቡት ዝግጅቶች መካከል እንደ ፕሮፊ ኃይሌ ገሪማ ምስክርነት አስተምሮት መንፈሴን ያረካው አላገኘሁም ! እናም ራሴን መወቃቀሴ አልቀረም ….

እውነት ነው ላለፉት በርካታ ዓመታት የቀደመውን የአባቶች የነጻነት ተጋድሎ ገለል አድረገነዋል ፣ አለም ያወቀው ፣ ጸሐይ የሞቀውን አንጸባራቂውን ክቡር የአባቶች ቀደም መስዋዕትነት አረክስነዋል … የሀገሬ ህዘብ ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ምኒሊክን ተከትሎ ዘር ሐይማኖት ሳይለይ ለአንዲት ሰንደቅ የተዋደቁላትን ሀገር የዛሬ ትውልዶች አኩሪ ገድላችን በክብር ማዘከር ገዶናል … ለሀገራቸው ደማቸውን ላፈሰሱ አጥንታቸውን ለከሰከሱት ለጀግና አርበኞቻች ሐውልት ማቆምያ አንድ ክንድ መሬት ነፍግናቸዋል ! እውነቱና ውሎ አዳራችን ይህ ደረቅ እውነት ሆኖ እንደ ዜጋ ታመን ከርመናል ፣ የሌለ ቀለም እየቀባን ፣ መላ የለሽ ሆነን ታሪክ እያዳፈንን ባጅተናል ። ቢያንስ እኔና መሰሎች በምናውቀው ድፍን 25 የኢህአዴግ አገዛዝ አመታት የሆነው ይህ ነው 🙁 አጃኢብ !!!

የሚሆነው እያስፈራን እያጠፋንም ፣ መደናገራችን አልቀረም … ከሁሉ አስቀድሞ ባሳለፍነው ሩብ ክፍለ ዘመን የተዳፈነው አኩሪ የትውልድ ታሪካችን አሸራ ለአዲሱ ትውልድ የማድረስ ቅብብሉ በጊዜ ብዛት እንዳይኮላሽ ሰግተን ተደናግረናል…ከሩብ አመት ሽሽት በኋላ 121 ኛው አድዋ የነጻነት ቀን ምኒሊክ በገነቡት ቤተመንግሰት ሆነው የሚያስተዳድሩን ገዥዎቻችን መልካም ፈቃድ ሆኖ ዓድዋ ዘንድሮ ደምቆ መከበር ሲጀምር በአርምሞ ከመመልክት ባለፈ ተደስተናል … መንግስት ካለፉት 25 አመታት ዝካሬ ዓድዋ በቅጡ አለማክበሩን አምኖ ፣ ምክንያቱ ሳይነገረን ሲቀር ግን ተደናግረናል ! … ግራ የተጋባን እኛ እንደተደናገርን አለን .. ” ደግሞስ ዘንድሮ ምን አዲስ ነገር ተገኘ ” ብለን አውጥተን አውርደናል … ጠይቀን መልስ አጥተናል … ተደናግረው እያደናግረውናል !

በመጽሐፍ ቅዱስ ” ኢትዮጵያ እጆቿን ትዘረጋለች ” ብሎ ተጽፏልና በተስፋዋ ምድር የተጨበጠ ተስፋ በምናሸትበት ደመና ስር ሆነን ተስፋችን ጨርሶ አልጠፋም ! የሙስሊማን የመጀመሪያው ስደትን ” ሂጅራ ” ከምዕተ አመታት አስቀድሞ ያስተናገደችው የሀበሾች ታሪካችን ታሪክ አልባ በሚያደርጉ ስንኩሎች እየተገፋን መከራችን የከፋ ሆኗል ፣ ቢሆንም ቅዱስ ቅርአን ሁሉን እኩል የሚያስተዳድር መንግስት እነደነበረ የመሰከረላት ሀገር የወደፊትም ተስፋ ሰንቀን መጓዝ ግድ ሆኖብናል !

እርግጥ ነው ፣ ከሀገራችን ሆነንም ከሀገር ወጠን ፣ ልባችን የተሰደደ በሀገራችን ላይ የሸፈትን ህዝቦች ሆነናል 🙁 ወይ እኛ አልተመቸን ወይ እሷ አልተመቻት ስንል በመልካም አስተዳደር እጦጥ በሙስና ብንማረር የታሪክ አሻራችን ጉድፍ እየበተኑበት ተስፋ ወደ መቁረጡ ተዘፍቀን ተደናግረናል … ኢትዮጵያ ሰው አታጣም፣ በመደናገሩ መካከል ” ኢትዮጵያ ባንተ አልተጀመረችም ፣ ባንተ አትጠፋም ! … በእኔ ኢትዮጵያዊነት ችግር ካለብህ ያንተ ነው ችግሩ …ዓድዋ በህብረት አሸንፈናል ፣ ማይጨው ላይ ስለተበታተንን ስለ ተለያይተን ተሸንፈናል … ኢትዮጵያ ብዙ ስቃይና መከራ ያሳለፈችው ሀገር ናት ስቃይ መከራው ይበዛባት ይሆናል እንጅ አትጠፋም !” ሲሉ እንዳንደናገር ይመክሩናል … ታሪክ መርማሪው ፣ እውቁ የስነ ፊልም ባለሙያና ደራሲው ፕሮፊ ኃይሌ ገሪማ ታፈረ … !

እናም በክፍል በክፍል እያቀናበርኩ ከማቀርብላችሁ መካከል እንደኔ የተደናገራችሁ ” አትደናገር ፣ ኢትዮጵያ አትጠፋም ” የሚለውን የፕሮፊ ኃይሌ ድንቅ ምክር የዛሬ ምርጫ አስተምሮት አድርጌ ስጋብዛችሁ ለፕሮ ያለኝን ታላቅ አክብሮት በመግለጽ ጭምር ነው !

ክብር ለአርበኛ ሰማዕታት !

ነቢዩ ሲራክ
የካቲት 24 ቀን 2009 ዓም

-6:28

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.