የተከሰሰው መረራ ብቻውን ነው! አታምታቱ ጀዋርና ብርሀኑ የሉበትም! – ሰርፀ ደስታ

ሰሞኑን የወያኔ ቡድን ኢትዮጵያዊውን እውነተኛ የሕዝብ ልጅ ፕ/ሮ መረራ ጉዲናን ከአክራሪ እስልምና አቀንቃኙ ከጀዋርና (ክርስቲያንን ሁሉ በሜጫ ቢከትፈው የሚመኝ) በሻቢያ በኩል ኢትዮጵያን ነጻ አወጣለሁ እያለ የሚያላግጥብንን ብርሀኑ በአንድ ላይ ከሰሰ በሚል የወያኔ ሚዲያዎች ማናፈሳቸው ሳያንስ ሌሎችም ይህንን ተቀብለው እያዛመቱለት ነው፡፡ እውነታው ግን ከመረራ በቀር ለወያኔ በአሁኑ ወቅት አደገኛ ሆኖ የታያት የለም፡፡ እውነታው ጀዋርና ተከታዮቹ ባይኖሩ ወያኔ አደጋ ላይ በወደቀ ነበር፡፡ ጀዋርና ተከታዮቹ ለወያኔ የጠቀሟትን ያህል አለኝ የምትለው አጋዚም አልጠቀማትም፡፡ ጀዋርና ተከታዮቹ መስለውኝ ሕዝብ ወሳኝ ተጋድሎ ላይ እያለ ኢትዮጵያን ማፍረስ ሚናቸው እንደሆነ ከወያኔ የተሰጣቸውን ሥራ ለንደን ላይ ሲናገሩ የሰማናቸው፡፡ ጀዋርና ተከታዮቹ እኮ መሰሉኝ በወሳኝ የትግል ወቅት የሕዝብን ትኩረት ወደሌላ ለመቀየር አትላንታ ላይ የኦሮሞ ቻርተር በሚል ልዩ ሕዝብን የሚከልስ ሥራ ሲሰሩ የነበሩ፡፡ የለንደኑም ንግግር የአትላንታውም ጉባዔ እኮ እንደተባለውም ከምር አልነበረም፡፡ ሆን ተብሎ ወያኔ የገባችበትን አጣብቂኝ ፋታ እንዲሰጣት ትኩረት ለማስቀየር እንጂ፡፡ ለመሆኑ ጀዋር ከመቼ ወዲህ ነው የወያኔ ጠላት የሆነው፡፡ ከተከሰስ ለምን ድሮ አልተከሰሰም፡፡ ዛሬ ከመረራ ጋር ጀዋርን መክሰስ ለምን ተፈለገ; የወያኔው ቡድን ጀዋር በሕዝብ ዘንድ እንደተጠላ ስለተረዳ እንደገና የወያኔ ጠላት በማስመሰል የሕዝብ ትኩረት እንዲያገኝ ስለሚፈልግ ነው፡፡  ምክነያቱም ገና ብዙ ለወያኔ የሚሰራላት ሥራ አለውና ነው፡፡ ይህ ግለሰብ እያደረገ ያለውን ብዙ የኦሮሞ ልጆች ዛሬ ላይ ነቅተውበታል፡፡ እሱና ቡድኑ ወሳኝ የወያኔ የቁርጥ ቀን  ተዋናይ ናቸው፡፡ እባብ ሞኝን ሁለት ጊዜ ነደፈው ይባላል፡፡ ድሮ የኦነግ ባለስልጣናት ከወያኔ ጋር እየሰሩ የኦሮሞ ልጅ ኦነግ ነህ እየተባለ ሥንቱ የደረሰበት እንኳን ሳይታወቅ ቀርቷል፡፡ አሁን የኦነግ ባለሥልጣናት ብዙም ሚና የላቸውም፡፡ ወያኔ ትብብሯ ትልቅ ሚና አላቸው ከተባሉት ከእነጀዋርና ቡድኑ ጋር ነው፡፡ አስተውሉ ጀዋርና ቡድኑ ምን እያደረጉ እንዳለ፡፡ ዛሬ ጀዋርና ቡድኑ የአረጀውንና ከሕዝብም ትኩረት እየደበዘዘ የመጣውን ኦነግን በአዲስ መልክ እንዲያስቀጥሉት ወያኔ ትፈልጋለች፡፡ ይህ ከአልሆነ የኦሮሞ ሕዝብ ከእጇ መውጣቱ ነው፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ አመለጠ ማለት ደግሞ በቃ ሁሉም ነገር አከተመ፡፡ እነ መረራ ዛሬ ላይ እንዲህ ሥጋት የሆኑባት ወያኔ ኦነጋውያን ጥሩ ሥም በነበራቸው ጊዜ እንደምንም አልቆጠረቻቸውም ነበር፡፡ ዛሬ ላይ ከጥቂት የጀዋር ተከታይ የሙስሊም አክራሪ ኦሮሞዎች በቀር የኦሮሞ ሕዝብ ትኩረቱን ወደነመረራ አዙሯል፡፡ ይህ ወያኔን ከአስደነገጣት ነገር አንዱ ነው፡፡ በእርግጥም እነጀዋርንም እጅግ አስደንግጧል፡፡ ዛሬ የኦሮሞ አክቲቪስት ነን የሚሉት እንዲህ አቅላቸውን የጣሉ እስከሚመስል ድረስ የሚያንቀዠቅዣቸው ይሄው የኦሮሞ ሕዝብ ኦነጋውያኑን(የዛሬዎቹ አክቲቪስት ተብዬዎቹ እነጀዋር) ገሸሽ አድርጎ መረራንና ቡድኑ መመልከቱ ነው፡፡ ለዘመናት መረራን ሊያደምጥ የፈለገ አልነበረም፡፡ እንደውም የነፍጠኛ ተላላኪ በሚል ሥም ጭራሽ በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት እንዳይኖረው ተደርጓል፡፡ ሌላ ቀርቶ እነ ተስፋዬ ገብረዓብም እነሱ ከመረራ በላይ ኦሮሞ ሆነው በመረራ ሲያፌዙ ነበር፡፡ በአንድ ፕ/ር ሕዝቅዬል የመድረክ መሪ በሆነበት የኦሮሞ ዲያስፖራ ጉባዔ ላይ ሕዝቅኤልና መሰሎቹ የሰጡትን ኦሮሞነት ተሰፋዬ ሲጠቀምበት መረራን በመንቀፍ አፉን ሲያሟሽ የተደረገለት ጭብጨባ እናስታውሳለን፡፡  ዛሬ ላይ መረራን በኦሮሞ ሕዝብ ፊት አንዳች ክፉ መናገር አይቻልም! ዘግይቶም ቢሆን ሕዝብ አሁን ገብቶታል!

ወያኔ አሁን እያደረገች ያለችው ይህን አፍጥጦ የመጣባትን የመረራና ቡድኑ የኢትዮጵያዊነትና ኦሮሞነት ፍልስፍና እንዲምታታ ሥለፈለገች ነው የኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ጠላት የሆኑትን እንደነጀዋር የመሳሰሉትን ከመረራ ጎራ ያደረገቻቸው፡፡ ወያኔን ከኢትዮጵያዊነት በላይ የሚያስፈራት የለም፡፡ ይህ ኢትዮጵያዊነት በሙሉ ወኔ ወደ ኦሮሞ ሕዝብ ገባ ማለት ነገሩ ሁሉ ያበቃል፡፡ እንኳን አዲስ አበባ ወያኔ ተነሳሁበት የምትለው ደደቢትም ከዚያ በኋላ መመሸጊያዋ አይሆንም፡፡ ይህችን አገር የሠሯት ባለቤቶቿ በግዛታቸው የባንዳ ልጆች መጨረሻቸው ነው፡፡ ዛሬ የኦሮሞ ጀግኖች ልዮ ታሪክ የሆነውን የሚኒሊክን ታሪክ ጥላሸት ለመቀባት የሚዘመትበት ቁልፍ ሚስጥሩም ይሄው ነው፡፡ እነ የኦሮሞ አክቲቪስት ነን የሚሉ የወያኔ ቅጥረኞች እድል አግኝተው ያልተፈጠረ ታሪክ እየፈጠሩ የሚያወሩበት ሚስጢር ይሄ ነው፡፡ እምዬ ሚኒሊክ ሲባል ሁሉም ይበረግጋል፡፡ ጀግኖቹ ኦሮሞዎች ሚኒሊክ የልብ ወዳጃቸው ነው፡፡ የሚኒሊክ ታሪክ አደዋ ቢቻም አደለም፡፡ እወነት ነው ሚኒሊክና ኦሮሞዎች ብል ይቀለኛል እሽ ያለውን በውድ እምቢ ያለውን በግድ አስገብረው ኢትዮጵያ የምትባልን አገር ከዘመናት መፍረስ በኋላ መልሰዋታል፡፡ የኦሮሞ አክቲቪስቶችን ይህ ታሪክ የሚያስፈራቸው ከባንዳዎቹ ጋር ባላቸው ወዳጅነት እንጂ አንድም እነሱ የሚሉት ታሪክ በሚኒሊክ ተፈጽሞ አደለም፡፡ እንነጋገር ከተባለ በአፍሪካ አደለም በአለም ላይ ሥኬታማና ልዩ ታሪክ ፈጣሪ የነበረው ኦሮሞዎች በዋናነት የተሳተፉበት የሚኒሊክ ሥርዓት ነው! አገርን አንድ ማድረግ፣ አገርን በእድገት ጎዳና በታላቅ ፍጥነት ማስገስገሰ፣ ዓለም በወቅቱ ያልደፈራቸውን ቅኝ ገዥዎችን ማሸነፍና የአገርን ዳር ድንበር ማስጠበቅ ለየትኛውም የአለም መሪ አልተሳካለትም፡፡ ሊያውም አፍሪካዊነት በራሱ ታላቅ ክብደት በሆነበት ወቅት፡፡

ሰሞኑን የሄው ጀዋር የሚባለው ግለሰብ በሚመራው ሚዲያ የኦሮሞ ምሁር ነን የሚሉት ሶስት ግለሰቦች ፕ/ር ሕዝቅኤል ገቢሳ፣ ዶ/ር አባስና ሀብቴ ኢታና ለሚኒሊክ ኃጥያት የሚሆን የውሸት ታሪክ በመፍጠር እውነተኛውን የማየወዱት ሳይቀሩ እየመረራቸውም ቢሆን የተጎነጩትን የአደዋን ታሪክ በማጥላላትና በማኮሰስ ሊነግሩን ብቅ ብለው ነበር፡፡ ምሁርነት በራሱ ትልቅ ሀላፊነት ነው፣ እድሜ ሌላው ትልቁ ሀላፊነት ነው፣ ከዚያ በተረፈ ግን ማንኛውም ተራ ሕጻን እንኳን  ቢሆን ሕሊናን የሚያጎድፍ ወሸት መናገር ውርደት ነው፡፡ ጥሩነቱ የኦሮሞ አክራሪዎቹ የሚይዙት የሚጨብጡት ስላጡ አሁን አሁን ማንነታቸውን እየገለጡት መሆኑ ነው፡፡ ለበርካታ ጊዜ የኢትዮጵያን ጉዳይ ዋና ተንታኝ የነበረው እሱ ራሱን እንደገለጸው “ዶ/ር” (ይቅርታ የሰውን ማዕረግ ለማሳነስ ሳይሆን ገና የ ዶክተሬት ተማሪ እንጂ ዶ/ር አደለም የሚል መረጃ ስላለ ነው) ጸጋዬ አራርሳ  የማንነት ጭምብሉ ሲወጣ ሲገለጥ ነው ዛሬ የምንሰማውን የጥላቻና የበቀል ንግግሮቹን መንዛት የጀመረው፡፡ እስከ ዛሬ ተደብቆ ነበርና፡፡ ልብ በሉ ጸጋዬ ግን በወያኔ የሲቪል ሰርቪስ ኮሌች የወያኔ ካድሬዎች አሰልጣኝ ነበር፡፡ ጀዋርና መላው የኦሮሞ አክቲቪስት ነኝ የሚለውን ወያኔ ሕዝብ እንዲቀበላቸው ትፈልጋለች፡፡ መረራን ከጀዋር ጋር የከሰሰችበት ዋና ምክነያቷ የመረራን ፍልስፍና ለመበረዝ ነው፡፡ የመረራ ፍልስፍና ከምንም በላይ ለወያኔ አደገኛ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት፣ ነፍጠኛ ከተባለ የኦሮሞም ነፍጠኛ ነበር ብሎ የሚናገረው ለዘመናት ተቀባይነት ያጣው የመረራ ፍልስፍና፡፡ ኢትዮጵያ ከማንም በላይ በኦሮሞ ልጆች ደም የተገነባች አገር ነች ብሎ የሚናገረው መረራና ጀዋር ናቸው እንግዲህ በአንድ ወንጀል የሚከሰሱት፡፡ ጀዋር ቢከሰስ እንኳን ምን አልባት ወደፊት ክርስቲያንን በሜጫ ጨርሶ እስላማዊ መንግስት ለመመስረት ምኞት እንዳለው ተጠርጥሮ ሊከሰስ ይችላል፡፡ ዛሬ እሱን የሚከሰው የለም፡፡ ዛሬ ግን  ጀዋር  አዲስ አበባ ቢሄድ ሻራተን ሶስት ቀን ቆይቶ ምን አልባት የታሰረ ወገን ካለው አስፈትቶ ሊመለስ ይችላል የቀድሞው የኦነግ መሪዎች እንዲህ እንደነበሩ እናስታውሳለንና፡፡ ሥንቱ የደሀ ልጅ ግን በኦነግ ሥም አልቋል፡፡ በአጭሩ ሌሎቻችሁ ደግሞ አታምታቱ ወይም አትጃጃሉ የተከሰሰው መረራ ብቻ ነው እንጂ ጀዋር እየተደረገለት ያለው ያጣውን የሕዝብ ድጋፍ እንዲያገኝ ፕሮፓጋንዳ ነው፡፡ ባይሆን ጀዋር ትንሽ ቀሪ ደጋፊዎች ካሉት አገር ቤት ለወያኔ ፕሮፓጋንዳ የሚመች ሕዝብ የሚያልቀበትን የጎዳና አመጽ ያውጅ ይሆናል፡፡ ለእሱም ወሬ ያገኛል፡፡ እሱ የሚመራው ሚዲያ ይሄ ዛሬ ላይ በየቦታው የምንሰማው የኦሮሞ ሕዝብ ልጆች ሥቃይ ከአበቃ ወሬም ላይኖረው ነው፡፡ ሰሞኑን በሶማሊ ክልል ታጣቂዎች የሚደርሰው ግፍ ጥሩ ወሬ ሆኖለታል፡፡ እኛን ግን ያመናል፡ ይቆጫል፣ ያንገበግባል! ዛሬ ማንነቱን አጥቶ መክኖ አቅም ያጣው የኦሮሞ ሕዝብ ለጦርነት ለሌሎችም ጦርነትን ያስተማረ ነው፡፡ እድሜ ለወያኔና ኦነጋውያን፡፡ አሁን የነቃው የኦሮሞ ሕዝብ ፊቱን ወደነመረራ ማዘንበሉ ግን ከምንም በላይ ለወያኔና ኦነጋውያን(የዛሬዎቹ አክቲቪስቶች) ስጋት ነው፡፡  ይህ ነው እውነታው! አታምታቱ!

ሌላው በሻቢያ በኩል ኢትዮጵያን ነጻ አወጣለሁ ሲን ስንጃጃልለት የኖርነው ዶ/ር ብርሀኑ ነጋ የተባለው ግለሰብ ነው፡፡ ድርጊቱ ሁሉ አንድም ቦታ ከኢትዮጵያ ሕዝብ የነጻነት ትግል ጋር የሚመስል እንደሌለ ብናይም ብዙ ደጋፊ ስለነበረው ግራ ተጋብተን ቆይተናል፡፡ ለነጻነት እታገላለሁ የሚልን መደገፍ መልካም ሊሆን ይችላል፡፡ ግን አንዳች የሚመስል ነገር የሌለውን መደገፍ በራሱ ሌላ ግራ መጋባት ነው፡፡ ዲያስፖራ ተብዬው በእርግጥ እንደነዱት የሚነዳ እንጂ ማስተዋል ያለው አይመስልም፡፡ ልብ በሉ ለነጻነት እዋጋለሁ የሚለው የብርሀኑ ቡድን የወያኔ የቁርጥ ቀን ወዳጅ በሆነው በሻቢያ በኩል ነው፡፡ ለመሆኑ ይሄ ቡድን አማራጭ አጥቶ ነው ወይ ብለን ስንጠይቅ መልስ የለም፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያ ከዳር እዳር ሕዝቧ አፈንግጦ እያለ ሻቢያ ጋር መልከስከስ ምንድነው; ብለን መጠየቅ ፈርተናል ወይም አዚም ተደርጎብናል፡፡ ባይሆን እንኳን ከምንም በላይ ደቡብ ሱዳን ጥሩ አማራጭ ነበር፡፡ ከሕዝብ ወጥተው ዛሬ እየታገሉ ያሉት ወገኖች እኮ ያሉበት እነ አርማጮ መሳሪያ የሚያገኙት ከሱዳን ነው፡፡ ያጠራቸው ገንዘብ እንጂ የተኛውንም አይነት መሣሪያ ሊያስገቡ እንደሚችሉ እናውቃለን፡፡ ማን ከልክሏቸው በገዛ መሬታቸው፡፡ የብርሀኑ ቡድን ግን ስንት አመቱ ነው;   ከባለፈው ዐመት የተሻለስ ትክክለኛ የነጻነት ታጋይ ከሆን ምን እድል ነበረው; ልብ ያለው ልብ ይበል ከማለት ውጭ አሁን ላይ ሰው ሊያምነው የማይቻለውን ነገር ብንናገር ማን ቢሰማ፡፡ ብርሀኑ ከመረራ ጋር የተከሰሰበት ሂደት ግን ጀዋርን ከመረራ ጋር ከተከሰሰበት የተለየ አደለም፡፡ እነ በቀለ ገርባ ከታሰሩ ጀምሮ መረራን የሚያስሩበት ምክነያት እየፈለጉ ነበር፡፡ ከምንም በላይ ሕዝብን ሊያመው የሚገባው መረራ መታሰሩ ብቻም ሳይሆን እንደገና ከሕዝብ ጠላቶች ጋር ተባባሪ እንደሆነ ለማሳየት የተሞከረበት ሂደት ነው፡፡ ወያኔና ወዳጆቹ የመረራን ከእነዚህ ሁለት ግለሰቦች ጋር መከሰሱን አጉልተው ሊያወሩት ይፈልጋሉ ይሄ በትክክልም አጀንዳቸው ነውና፡፡ ሌሎች ግን አይምታታባችሁ፡፡ በዚህ ልዩ ክስ  ወያኔን የከሰሰቸው መረራና መረራ ብቻ ነው፡፡ ጀዋር ብርሀኑ የምትሏቸው ወያኔ ሕዝብ ትኩረት እንዲሰጣቸው ስለፈለገች ነው ከመረራ ጋር የደባለቀቻቸው፡፡ ዲያስፖራ ሆይ ተምታቶብህ ሌሎችን አታምታታ፡፡ ሁሉንም ቆይተህ ታየዋለህ፡፡   ዲያስፖራን ሌላ የታዘብነው አለ መረራ ሲታሰር አንድም እንቅስቃሴ አለማድረጉ የዲያስፖራው ነገር የተያዘው በነጋዴዎች እንጂ በእውነተኛ የሕዝብ አጋሮች እንዳልሆነ ነው፡፡

 

እግዚአብሔር ማስተዋሉን ይስጠን!

 

 

ልዑል እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይጠብቅ! አሜን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.