ሕገ ወጥ የባንክ ሒሳብ ፈራሚ መድበው ኹለት ደመወዝ በመውሰድ የተጠየቁት: የመቐለ ሀ/ስብከት ሥራ አስኪያጅ ከሓላፊነታቸው ተነሡ

  • የፈጸሟቸው አስተዳደራዊ በደሎች፣ የሀ/ስብከቱን ሰላማዊ እንቅስቃሴ አውኳል፤
  • በጠ/ጽ/ቤቱ አጣሪ ቢመደብም፣ በጉቦ ለመደለል ሞክረዋል፤ ሒደቱም ታጉሏል፤
  • የቀድሞው የጅግጅጋ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ፣ በጊዜአዊነት ተመድበዋል፤\

ሐራ ዘተዋሕዶ

እናት ቤተ ክርስቲያናችን፣ በየጊዜው በከፍተኛ መንፈሳዊና አስተዳደራዊ አካሏ ከምትስዳቸው አቋሞችና ከምታወጣቸው መግለጫዎች እንደምንረዳው፣ ወቅታዊ ትኩረትን የሚሹት ዐበይት ችግሮቻችን፦ የመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ የሙስና መስፋፋት፣ የሚወሰኑ ውሳኔዎች አስፈጻሚ ማጣት፣ የቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጥሰት እና የእናድሳለን ባዮች ውስጣዊ ሤራ ናቸው፡፡

በተለይም፣ በመልካም አስተዳደር ዕጦትና በአማሳኝነት የሚፈጸሙ በደሎች፣ በአንድ ገጻቸው፣ ለምእመናን ኅሊና ዕንቅፋት እየኾኑና አገልጋዮችንም የሥራ ዋስትናና ከለላ እያሳጡ ሲያርቋቸው፤ በሌላ ገጻቸው ደግሞ፣ ለመናፍቃንና ለፀራውያን ሰርጎ ገብነት ክፍተት በመፍጠራቸው፣ ለቤተ ክርስቲያናችን የወደፊት ህልውና ከፍተኛ ስጋት እንደኾኑ ታምኖበታል፡፡

መልካም አስተዳደር ሰፍኖ፥ አድልዎ፣ ጭቅጭቅ፣ ንትርክ፣ መለያየት በአጠቃላይ ከመንፈሳዊነት ጋራ የማይጣጣም አስተሳሰብና አሠራር ተወግዶ የተስተካከለ ሥርዓትን ማየትን እንሻለን፡፡ ለዚኽም፥ ለኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖታችን ክብርና ህልውና ከልብ የሚቆረቆሩ፣ መልካምሥነ ምግባርና የተስተካከለ ሰብእና ያላቸው፤ እንዲኹም፣ በኑሮአቸው ኹሉ ለሕዝበ ክርስቲያኑ እንደ አርኣያ የሚጠቀሱ የውሉደ ክህነት ሠራተኞች አመራር፣ በእጅጉ ወቅታዊ መኾኑን ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በየቃለ ምዕዳናቸው እያሳሰቡ ነው፡፡

የአስተዳደራችን ማእከልና ርእስ የኾነው ጠቅላይ ቤተ ክህነት፣ ዋና ባለሥልጣን የኾኑት ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁም፥ ሥራንና ሠራተኛን በማገናኘት ላይ ያተኮረ፤ በሚለኩና ሊገመገሙ በሚችሉ ወጪ ቆጣቢ ዕቅዶች ላይ በተመሠረተ፤ የቤተ ክርስቲያንን መብቶችና ጥቅሞች አስጠብቆ በማወያየትና በማሳመን መሥራትን ማእከል ባደረገ አኳኋን፥ ተጠያቂነትን ለማስፈንና ሕግን ለማስከበር፤ የሙስናና የመልካም አስተዳደር ችግሮችንም ለመቅረፍ ጥረት በማድረግ ላይ እንዳሉ ይገለጻል፡፡

መላው አህጉረ ስብከት፣ በተሳተፉበት የዘንድሮው 35ኛ ዓመታዊ አጠቃላይ ጉባኤ፥ በየደረጃው ያለውን የመልካም አስተዳደር መስተጓጎልና ያለመሟላት ክፍተት በሚገባ ፈትሾ በማስተካከል፣ ከቤተ ክርስቲያናችን የሚጠበቅ አስተዳደራዊ ሥርዓት ለማስፈን በአርኣያነት እንደሚሠሩ ባወጡት የጋራ መግለጫ ቃል ገብተዋል፤ ሲኖዶሳዊና ማዕከላዊ የኾነውን አሠራር በሚቃረን መልኩ የሚፈጸመውን አስተዳደር ነክ የሕግ ጥሰት ለመከላከል፣ ቅዱስ ሲኖዶስ ዝርዝር መመሪያ በማውጣት እንዲከታተለው በማሳሰብ፣ መዋቅርን በመጠበቅ በሕገ ቤተ ክርስቲያንና በቃለ ዐዋዲው ለመሥራት ቃል ገብተዋል፡፡

የፋይናንስ አያያዙን ለማጠናከርና ዘመናዊ ለማድረግ በተዘረጋው የኹለትዮሽ የሒሳብ አመዘጋገብ፣ በግልጽነትና በተጠያቂነት በመሥራት፣ ምእመኑ፥ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎትና ለሃይማኖት መጠበቂያ ብሎ በእምነት የሚለግሰው ገንዘብና ንብረት ከምዝበራ ተጠብቆ ለታለመለት ዓላማ ብቻ እንዲውል ለመሥራት ቃል ገብተዋል፡፡ የኦዲትና ኢንስፔክሽን አሠራሩም በሠለጠኑ ባለሞያዎች ምደባ ተጠናክሮ እንዲፈጸም አሳስበዋል፡፡

የአህጉረ ስብከቱን አጠቃላይ ጉባኤው የጋራ መግለጫና የውሳኔ ሐሳብ በማዳበር የበጀት ዓመቱ የሥራ መመሪያ እንዲኾን ያጸደቀው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤም፥ በቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ቀልጣፋና ቅንነት የሰፈነበት አሠራር እንዲኖር፤ በየደረጃው የተዘረጉት የልማት አውታሮች የበለጠ ውጤት እንዲኖራቸው ለማስቻል ከመንበረ ፓትርያርክ ሥራ አስኪያጅ ጀምሮ ኹሎችም የየአህጉረ ስብከቱ ሊቃነ ጳጳሳት ሓላፊነት ያለባቸው ስለኾነ ተከታትለው እየሠሩ እንዲያሠሩ ከፍተኛ ውሳኔ ወስኗል፡፡

በሀገር ውስጥ ካሉን 50 ያኽል አህጉረ ስብከት አንዱ በኾነው፥ በክልል ትግራይ – የመቐለ ሀገረ ስብከት፣ ከ2005 ዓ.ም. ጀምሮ ሲፈጸሙ የቆዩ የአስተዳደር በደሎችና የጥቅመኝነት ተግባራት፣ በአህጉረ ስብከቱ የጋራ መግለጫና በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የተወሰነውን የሚፃረር ኢ-ሕገ ቤተ ክርስቲያናዊ በመኾኑ፣ ሰሞኑን፣ መዋቅርንና ሕግን የማስከበር ርምጃ በጠቅላይ ጽ/ቤቱ ተወስዷል፤ ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት የሚበቃ ማጣራት እንዲካሔድም ቀጣይ አቅጣጫ ተሰጥቷል፡፡ ሌሎችም አህጉረ ስብከት በተመሳሳይ መልኩ መዳሰስ የሚገባቸው ሲኾን፤ ከሓላፊነት በሚነሡትና በቦታቸው በሚተኩት ሹሞችም የተጠያቂነቱና የአርኣያነቱ ጉዳይ በጥብቅ ሊታሰብበት ያስፈልጋል፡፡


(ሰንደቅ፤ 12ኛ ዓመትቁጥር 600፤ ረቡዕ፣ የካቲት 29 ቀን 2009 ዓ.ም.)

ሥልጣናቸውን መከታ በማድረግ፣ ከሌሎች የክፍል ሓላፊዎች ጋራ፣ ከሕግና መመሪያ ውጭ ኹለት ወርኃዊ ደመወዝ የሚወስዱት፣ የመቐሌ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ፥ መልአከ ብርሃናት ገብረ ሥላሴ ሕሸ፣ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ውሳኔ ከሓላፊነታቸው ተነሡ፡፡

መልአከ ብርሃናት ገብረ ሥላሴ ሕሸ፥ ሕገ ቤተ ክርስቲያንንና ቃለ ዐዋዲውን በመጣስ ከበላይ አካል የተላለፉ ውሳኔዎችንና መመሪያዎችን ባለማስፈጸም እንቢታ ሲያሳዩ መቆየታቸውን በውሳኔው የጠቀሰው ጠቅላይ ጽ/ቤቱ፤ በሀገረ ስብከቱ የፈጠሩት አስተዳደራዊ ችግር ተጣርቶ የመጨረሻ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ፣ ከየካቲት 20 ቀን ጀምሮ፣ በሥራ አስኪያጅነት የሥራ መደብ የሚያገኙትን ወርኃዊ ደመወዝ ብቻ እንደያዙ፣ ከሓላፊነታቸው ተነሥተውና ወደ ዋናው መ/ቤት ተዛውረው የመንፈሳዊ ፍርድ ቤት አባል ኾነው እንዲሠሩ መመደባቸውን አስታውቋል፡፡

የተጣለባቸውን የሥራ ሓላፊነት ወደ ጎን በመተውና ሥልጣናቸውን መከታ በማድረግ የፈጸሟቸውን መተላለፎችና በደሎችም ውሳኔው በስድስት ነጥቦች ለይቶ ዘርዝሯል፡፡ የመጀመሪያው፣ በሥራ አስኪያጅነት ሓላፊነታቸው ከሚያገኙት በተጨማሪ፣ ከሌሎች የሀገረ ስብከቱ ሠራተኞች ጋራ ኹለት ደመወዝ ሲወስዱ መቆየታቸው ነው፡፡

ለዚኽም፣ ሥራ አስኪያጁ፣ ከ6 ወራት በፊት በሞት በተለዩት ሒሳብ ሹም ምትክ፣ ከዋናው መ/ቤት ዕውቅና ውጭ በራሳቸው የባንክ ፈራሚ በመመደብ ለሕገ ወጥነታቸው አመቺ ኹኔታ መፍጠራቸው ተመልክቷል፡፡ የኹሉም አህጉረ ስብከት የባንክ ሒሳብ ፈራሚዎች የሚመደቡት በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ደብዳቤ እንደኾነ የጠቀሰው ውሳኔውም፤ ሥራ አስኪያጁ፣ ከሕግና መመሪያ ውጭ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ ካልፈቀደለት ሠራተኛ ጋራ በጣምራ ፊርማ የባንክ ሒሳብ ሲያንቀሳቀሱ መቆየታቸውን አስረድቷል፡፡

የሀገረ ስብከቱ ምንጮች እንደገለጹት፣ ሥራ አስኪያጁ፣ ራሳቸውን በጽርሐ ኣርያም ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል አስተዳዳሪነት በመሠየም የእልቅናውን ደመወዝ ይወስዳሉ፤ በሕገ ወጥ መንገድ የተመደቡት የሀገረ ስብከቱ ሒሳብ ሹምና ዋና ጸሐፊም፣ በጽ/ቤቱና በአድባራት ደራርበው በያዟቸው ሓላፊነቶች፣ በአንድ ተቋም የተለያዩ የሥራ መደቦች ኹለትና ከዚያ በላይ ወርኃዊ ደመወዝ እንደሚያገኙ ተጠቁሟል፡፡

የጠቅላይ ጽ/ቤቱ ውሳኔ፥ በኹለተኛና በሦስተኛ ደረጃ ያስቀመጠው፣ ከወረዳ ቤተ ክህነት ሠራተኞችና ከአድባራት ለሚቀርቡ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች፣ በሥራ አስኪያጁ ወቅታዊ ምላሽ ባለመሰጠቱ ባለጉዳዮች ላልተገባ ወጪና እንግልት መዳረጋቸውን ነው፡፡

ለአብነት ያኽል፦ የዓይናለም ደብረ ኃይል ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ማኅበረ ካህናትና ምእመናን የደረሰባቸውን በደል በመዘርዘር ላቀረቡት አቤቱታ፣ ሀገረ ስብከቱ በአስተዳደር ጉባኤ አይቶ ውሳኔ እንዲሰጥበት፣ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ መመሪያ ቢሰጥም፣ በማንአለብኝነት ሳይፈጸም ቀርቷል፤ ባለጉዳዮቹም፣ በድጋሚ ለኹለተኛ ጊዜ አቤቱታ ለማቅረብ በመገደዳቸው ላልተገባ ወጭና እንግልት ተዳርገዋል፡፡

እንዲኹም፣ የሦስት ወረዳ አብያተ ክህነት ጽ/ቤቶች ሠራተኞች፣ የደረሰባቸውን አስተዳደራዊ በደል በመግለጽ በጻፉት ማመልከቻ ያቀረቡትን አቤቱታ፣ ሀገረ ስብከቱ ደረጃውን ጠበቆ በአስተዳደር ጉባኤ ውሳኔ እንዲሰጥበት ከዋናው መሥሪያ ቤት በተጻፈ ደብዳቤ መመሪያ ቢተላለፍም ሳይፈጸም ቀርቷል፡፡ ሌሎችም በርካታ መሰል ጉዳዮች እንዲኹም የቋሚ ሲኖዶስንና የፍርድ ቤት ውሳኔዎችን ጭምር ባለማስፈጸም፣ ሥራ አስኪያጁ፣ ለቤተ ክርስቲያናችን ሲኖዶሳዊና ማዕከላዊ አስተዳደር ባለመታዘዝና ተገዥ ባለመኾን እንቢታ ሲያሳዩ መቆየታቸው ታውቋል፡፡

በብልሹ አሠራርና በጥቅመኝነት የተፈጠረው ችግር፣ ከሀገረ ስብከቱ አልፎ ለክልላዊ መንግሥቱና ለመቐለ ከተማ አስተዳደር ጭምር የደረሰ ሲኾን፤ በአግባቡ አጣርቶ ኹነኛ የውሳኔ ሐሳብ የሚያቀርብ ሦስት አባላት ያሉት የጠቅላይ ጽ/ቤቱ ልኡክ፣ ባለፈው ጥር 29 ቀን 2009 ዓ.ም. ወደዚያው ተልኮ እንደነበር ውሳኔው አውስቷል፡፡

ልኡኩ በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት እንደደረሰ፣ የሚጣሩትን ጉዳዮች በመለየትና በአካሔዱም ላይ ከሥራ አስኪያጁ ጋራ በመነጋገር ተግባብቶ የነበረ ቢኾንም፣ ተግባሩን ለመጀመር በሚዘጋጅበት ዕለት ግን፣ ሥራ አስኪያጁ በፈጠሯቸው ማሰናከያዎች ምክንያት ተልእኮውን ሳያሳካ መመለሱ ተገልጿል፡፡

በመጀመሪያ፥ “ነገሩን አለሳልሱት፤ አስተኙት፤ የምትጠይቁትን እንከፍላለን፤ እንሰጣችኋለን፤” በሚል ልኡኩን በጉቦ ለመደለል ሞክረዋል፤ በገንዘብ የማጣራቱን ሒደት የማዳፈን መላ፣ ችግሩ ከተፈጠረበት ከ2005 ዓ.ም. ጀምሮ በሚላኩት የጠቅላይ ጽ/ቤቱ ልኡካን ላይ የለመዱት ቢኾንም፣ በአኹኑ ግን አልያዘላቸውም፡፡ ይህን ሲረዱም፣ ሊቀ ጳጳሱን በመገፋፋት እንዲኹም፣ በማጣራቱ እንዲሳተፉ ከጅምሩ ስምምነት የተደረሰባቸውን አቤቱታ አቅራቢዎችን ስም በማጥፋት አላስፈላጊ ቅስቀሳ በማካሔድ ሥራው በተያዘለት መርሐ ግብር እንዳይከናወን መሰናክል ፈጥረዋል፡፡

ልኡኩም፣ ያጋጠመውን መሰናክል በሪፖርት ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ በመረጃ ደረጃ ደግሞ ለከተማው ከንቲባ በማሳወቁ፣ በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ አንቀጽ 51 ንኡስ ቁጥር 6 ድንጋጌ መሠረት፣ የሀገረ ስብከቱ ዋና ጽ/ቤት ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጽ/ቤት እንደ መኾኑ መጠን፣ ሥራ አስኪያጁ ማጣራቱን ማስተጓጎል እንደማይችል የሚገልጽና ሒደቱ ከቆመበት እንዲቀጥል የሚያዝ ጥብቅ መመሪያ በደብዳቤ ቢያስተላልፍም፣ በማንአለብኝነት መመሪያው ሳይፈጸም መቅረቱን በውሳኔው አስፍሯል፡፡

ይህም ተደማምሮ፣ ከመልካም አስተዳደር ዕጦት በላይ የሀገረ ስብከቱን አጠቃላይ ሰላማዊ የሥራ እንቅስቃሴ የሚያኮላሽ በመኾኑ፣ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ፣ የካቲት 10 ቀን 2009 ዓ.ም.፣ በቁጥር 2956/19/2009 በጻፈው ደብዳቤ፣ሥራ አስኪያጁ፣ የሀገረ ስብከቱን ሒሳብ በስማቸው እንዳያንቀሳቅሱ ከማገዱም በላይ፣ ከሥራና ከደመወዝም አግዶ፣ እስከ የካቲት 17 ቀን 2009 ዓ.ም. ወደ ዐዲስ አበባ መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ሔደው ሪፖርት እንዲያደርጉ አዟቸዋል፡፡

ሥራ አስኪያጁም፣ በትእዛዙ መሠረት፣ ወደ ዐዲስ አበባ ከመጡ በኋላ፣ የሀገረ ስብከቱ ኹለንተናዊ ችግሮች ቀድሞ በተመደበው አጣሪ ልኡክ ተጣርቶ የመጨረሻ ውሳኔ እስከሚሰጥ ድረስ፣ ለሀገረ ስብከቱ ወቅታዊ ሰላም ሲባል፣ ከየካቲት 20 ቀን ጀምሮ ከሥራ አስኪያጅነት አንሥቶ ወደ መንፈሳዊ ፍ/ቤት በማዛወር መመደቡን አስታውቋል፡፡

በተያያዘ ዜና፣ የጠቅላይ ጽ/ቤቱ አስተዳደር ጉባኤ፣ ትላንት ማክሰኞ፣ የካቲት 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ባካሔደው ሳምንታዊ መደበኛ ስብሰባው፣ ከሓላፊነት በተነሡት መልአከ ብርሃናት ገብረ ሥላሴ ሕሸ ምትክ፣ በቤቶችና ሕንፃዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት በጠቅላላ አገልግሎት ሓላፊነት የሚሠሩት፣ መልአከ መዊዕ ሰሎሞን ዓባይ፣ ሀገረ ስብከቱን በሥራ አስኪያጅነት እንዲመሩ በጊዜአዊነት መድቧል፤ የአሠራር ክፍተቶችንና አስተዳደራዊ በደሎችን የማጣራቱ ተግባርም፣ ቀደም ሲል በተመደበው ልኡክ፣ ከቀጣዩ ሳምንት ጀምሮ እንዲቀጥል ወስኗል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.