በቅዱስ ፍሬምናጦስ እና በቅድስት ሥላሴ ኮሌጆች: በኑፋቄና የምግባር ብልሽት አምስት ደቀ መዛሙርት ተባረሩ

  • በክህነት ባወቁትና ሊጠብቁት በሚገባው ምስጢረ ቤተ ክርስቲያን ተሣልቀዋል፤
  • ለዲቁና የማይገባ ማታለልና ኃይል አሳይተዋል፤ ከመናፍቃንም ጋራ ጸልየዋል፤
  • የኑፋቄን ስውር ተልእኮ፣ ከቴዎሎጂ ኮሌጆቻችን የማጥራት ቀጣይ አካል ነው፤

ሐራ ዘተዋሕዶ

በሚያፈሩት የተማረ የሰው ኃይል፣ በቤተ ክርስቲያናችን የዛሬና የወደፊት የአገልግሎት አቅጣጫ ላይ ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው የሚታመንባቸውን መንፈሳውያን ኮሌጆቻችንን፣ ከመናፍቃን ተጽዕኖ የመከላከልና ከኅቡእ ምንደኞቻቸው የማጽዳቱ እንቅስቃሴ በተጠናከረ ኹኔታ ቀጥሏል፡፡

በመቐለ፥ የቅዱስ ፍሬምናጦስ አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጅ እና በዐዲስ አበባ፥ አንጋፋው የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ፣ ሰሞኑን በወሰዱት አስተዳደራዊ ርምጃ፣ በእምነት አቋማቸውና በሥነ ምግባራቸው ከባድ ኑፋቄና መተላለፍ የተገኘባቸውን አምስት ተማሪዎች፣ ሙሉ በሙሉ ከደቀ መዝሙርነት አሰናብተዋል፡፡

አምነው በተቀበሉት ኑፋቄ የተነሣ፣ በማዕርገ ክህነታቸው ያወቁትንና ሊጠብቁት የሚገባውን ምስጢረ ቤተ ክርስቲያን ማቃለላቸው በማስረጃ የተረጋገጠባቸው ሦስት ተማሪዎች፣ ባለፈው ሳምንት ዓርብ፣ የካቲት 24 ቀን 2009 ዓ.ም.፣ ከቅዱስ ፍሬምናጦስ አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጅ ተባረዋል፡፡

በመንፈሳዊ ኮሌጁ፣ የተማሪዎች መማክርት እና የዲስፕሊን ኮሚቴ በየደረጃው ተረጋግጦ፣ ለአስተዳደር ጉባኤው ውሳኔ የቀረበው ማስረጃ እንደሚገልጸው፦ ሦስቱ ተማሪዎች፣ ኾነ ብለውና መክረው በደቀ መዛሙርት ፊት በድራማ መልክ ባሳዩት ትዕይንት፣ በሥጋ ወደሙ ታላቅነት ላይ ተሣልቀዋል፤ የክርስቶስን አማናዊ ቅዱስ ሥጋ አማናዊ ክቡር ደም የምንቀበልበት ምስጢረ ቊርባን፥ “የማይመረመር ምስጢር” የመኾኑን ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ እየነቀፉና እያቃለሉ፣ የፕሮቴስታንታዊውን “ተራ ኅብስት” አስተሳሰብ የመዝራት ተልእኳቸውን ለመፈጸም ተንቀሳቅሰዋል፡፡

ስመ ደቀ መዛሙርቱ፣ በተማሪዎች መማክርቱ ሲጠየቁ፣ ጥፋታቸውን በግልጽ ያመኑ ሲኾን፤ ጉዳዩ በዲስፕሊን ኮሚቴው ዘንድ በታየበት ወቅት ግን ለመካድ ሞክረው እንደነበር ተመልክቷል፡፡ ይኹንና ተደግፎ የቀረበው ማስረጃና የዓይን እማኞች ምስክርነት በአስተዳደር ጉባኤው ተመርምሮ ጥፋተኝነታቸው በማያሻማ ኹኔታ በመረጋገጡ፣ ሙሉ በሙሉ ከኮሌጁ እንዲሰናበቱ መወሰኑ ታውቋል፡፡ የስም ዝርዝራቸውና የተላኩበት አህጉረ ስብከትም፡-

  1. ታደለ ለገሰ፤ ከደቡብ ምዕራብ ሸዋ – ወሊሶ ሀገረ ስብከት የተላከና በመጀመሪያ ዲግሪ የሦስተኛ ዓመት ተማሪ የነበረ፤
  2. ሃይማኖት ገረመው፤ ከቤንች ማጂ ዞን ሀገረ ስብከት የተላከና በመጀመሪያ ዲግሪ የአራተኛ ዓመት ተማሪ የነበረ፤
  3. ሰሎሞን ገብረ ሕይወት፤ ከሲዳሞ ሀገረ ስብከት የተላከና በመጀመሪያ ዲግሪ የአምስተኛ ዓመት ተማሪ የነበረ ናቸው፡፡

በሌላ በኩል፣ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ፣ ትላንት ረቡዕ፣ የካቲት 29 ቀን 2009 ዓ.ም.፣ ከፍተኛ የሥነ ምግባር ግድፈት የታየባቸውን ኹለት የቀን መደበኛ ደቀ መዛሙርት ከኮሌጁ አሰናብቷል፡፡ ለክህነታቸው በማይገባና የደቀ መዝሙርነት ዲስፕሊንን በሚፃረር መልኩ፥ ኃይልና ጉልበት በማሳየት መምህራንን ሲጣሉና ሲሳደቡ እንደነበር የተገለጸ ሲኾን፣ በፈተና ወቅትም በመኮራረጅ እጅ ከፍንጅ መያዛቸው ተነግሯል፡፡

ኹለቱም በመጀመሪያ ዲግሪ የሦስተኛ ዓመት የቀን ተማሪዎች የነበሩ ሲኾን፦ ብርሃኑ ተስፋዬከወሊሶ ሀገረ ስብከት እና ኃይሉ አየለከጅማ ሀገረ ስብከት የተላኩ መኾናቸው ታውቋል፡፡ መጽሐፍ በጻፈበት ስሙ “ናዝራዊ” ብሎ ራሱን የሚጠራው ኃይሉ አየለ፥ በቅርቡ በኑፋቄ ከተባረሩት ስምንት ተማሪዎች መካከል፣ ስሜነህ መኰንን ከተባለው ጋራ ጥብቅ ግንኙነት እንዳለውና በተለይም በአንደኛ ዓመት ደቀ መዛሙርት ላይ በማተኮር፥ “ኮርስ እናሠለጥናችኋለን” በሚል በኅቡእ እየመለመለ በየመንደሩ የሚወስድ የኑፋቄው አስፈጻሚ እንደነበር በመረጃው ተጠቅሷል፡፡

ከኹለቱም ኮሌጆች የተሰናበቱት የስም ደቀ መዛሙርት፣ ክህነታቸውም እንደ አንድ መስፈርት ታይቶ የገቡ እንደመኾናቸው፣ በቅዱስ ሲኖዶስ ደረጃም መታየት የሚገባቸው ቀኖናዊ ጉዳዮች በመኖራቸው፣ ሥልጣነ ክህነታቸውን በተመለከተ ቀጣይ ውሳኔዎችም ይጠበቃሉ፡፡

ከሦስቱ ከፍተኛ መዓርጋተ ክህነት የመጀመሪያ የኾነው ዲቁና፣ ለጳጳሱና ለቄሱ የመላላክ፣ ምእመናንን የማንቃት ተልእኮ የሚፈጸምበት ነውና በመዓልትም በሌሊትም በሥነ ምግባር ላቅ ብሎ መገኘትን ይጠይቃል፡፡ ከኃጢአት ንጹሕ ኾኖ መልካም አገልግሎት የሚያገለግል ዲያቆን፥ ይረባል፤ ይጠቅማል፤ በጎ ዕድል ፈንታ ያገኛል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህን ሲያስረዳ፦ “እንዲኹም ዲያቆናት ጭምቶች፣ በኸለት ቃል የማይናገሩ፣ ለብዙ የወይን ጠጅ የማይጎመጁ፣ ነውርና ረብ የማይወዱ፣ በንጹሕ ኅሊና የሃይማኖትን ምሥጢር የሚይዙ ሊኾኑ ይገባቸዋል፤” ብሏል፡፡ (1ጢሞ. 3፥ 8-13)

ዲያቆናት፥ ትሑት ኾኖ የማገልገልን ክርስቶሳዊ አርኣያነት ወደ ጎን በመተው በሰው ላይ መታበይ፣ ኃይልን ማሳየት፣ ሰውን መማታት፣ በሐሰት መመስከር በመሳሰሉት ተመክረው የማይመለሱ ኾነው ሲገኙ ከክህነታቸው ይሻራሉ፡፡

ከምንም በላይ ደግሞ፣ ለሕገ ቤተ ክርስቲያን ተገዥና ሕገ ቤተ ክርስቲያንን አክብረው የሚያስከብሩ መኾን አለባቸው፡፡ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለሚገኙ፣ ከንዋያተ ቅድሳቱ ጀምረው እስከ አንድ ቆቆር ዕጣን ድረስ ዋጋ የሚሰጡ መኾን አለባቸው፡፡ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን እየነቀፉና እያቃለሉ ጥርጣሬ እየዘሩ በአገልግሎታቸው እንዲቀጥሉ አይፈቀድላቸውም፡፡

በመኾኑም አንድ ዲያቆን፥ ቤተ ክርስቲያንን ትቶ ከሔደ በኋላ የተመለሰ፣ ከመናፍቃን የተጠመቀ፣ ቊርባናቸውን የተቀበለ፣ ከመናፍቃን ጋራ የጸለየ፣ ቤተ ክርስቲያንን ትቶ ወደ ሌላ ቤተ እምነት ከሔደ ከዲቁናው ይሻራል፡፡ በእምነቱ ኑፋቄ ከተገኘበት፣ ንስሐ ቢገባም፣ በምእመንነቱ ይቀጥላል እንጂ፣ በሥልጣነ ክህነቱ ማገልገል አይችልም፡፡ /ፍትሐ መንፈሳዊ አንቀጽ 7 ክፍል 5/

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.