10 ቢሊዮን ብር በከንቱ ለባከነበት “የነፋስ ተርባይኖች” ቅሌት፣ ተጠያቂው ማን ነው?- አዲስ አድማስ

“ለነፋስ ተርባይኖች” ግዢ በሚል ሰበብ በየአመቱ እንደዘበት የሚባክነው የቢሊዮን ብሮች ሃብት ሲታይ፣ በእርግጥም በኢትዮጵያ ታሪክ አቻ የማይገኝለት ቅሌት ነው ማለት ይቻላል። በየትኛውም አገር ቢሆን፣ በበለፀጉት አገራትም ጭምር፣ ከፍተኛ ሃብት በከንቱ እንዲባክን ማድረግ አሳፋሪ ተግባር ነው። አብዛኛው ህዝብ ችግረኛ በሆነባት፣ ሩብ ያህሉ ካለምፅዋት ሕይወቱን ማቆየት በማይችልባትና ገና አንገቷን ቀና ለማድረግ በምትውተረተር ደሃ አገር ውስጥ፣ በፈቃደኝነት ሃብት እንደ ዘበት ሲባክንስ ምን ይባላል?
እስካሁን በመቀሌና በአዳማ ናዝሬት የተተከሉት የነፋስ ተርባይን ጣቢያዎች፤ እንዲሁም በቅርቡ በተፈረመው ውል አዳማ ላይ የሚጀመረው ሦስተኛ የነፋስ ተርባይን ጣቢያ፣ በድምሩ 770 ሚሊዮን ዶላር (15.4 ቢሊዮን ብር) ገደማ ይፈጃሉ። ከዚሁ ገንዘብ ውስጥ፣ ከአስር ቢሊዮን በላይ የሚሆነው ሃብት በከንቱ የባከነ ነው። ለምን ቢባል፤ የነፋስ ተርባይኖቹ ዋጋ እጅግ ውድ ነው፤ ኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅማቸው ደግሞ ደካማ! በሌላ አነጋገር፤ በአነስተኛ ወጪ የሃይል ማመንጫ ግድብ በመገንባት ከነፋስ ተርባይኖች በሶስት እጥፍ የሚበልጥ ኤሌክትሪክ ማመንጨት ይቻላል። ነገሩ ቀልድ አይደለም።
አንደኛ፤ ብክነቱን በአንዳች “አሳማኝ ምክንያት” በይቅርታ እንድናልፈው ለማድረግ ይቅርና፤ በአንዳች “ማመካኛ” ለማድበስበስም አይመችም። ያፈጠጠ ብክነትና ያገጠጠ ቅሌት መፈፀሙ አያከራክርም። ወዲህ ወዲያ የሚያስብል ማምለጫ የለውም። ማንም ሊክደው የማይችል፣ ጎልቶ የሚታይና በቁጥር የተሰላ ሃቅ ነው። ሁለተኛ ነገር፣ የብክነቱ መጠን ያስደነግጣል – ከአስር ቢሊዮን ብር በላይ የአገር ሃብት ነው በከንቱ የባከነው። ከ40ሺ እስከ 50ሺ ኮንዶሚኒዬም ቤቶችን ሊያስገነባ የሚችል ሃብት! ወይም ደግሞ ባለፉት አስር አመታት ለነዋሪዎች ከተላለፉት ኮንዶሚኒዬም ቤቶች መካከል ግማሽ ያህሉን እንደማፍረስ ቁጠሩት።
የዚህ ጉደኛ ቅሌት መንስኤ፣ ሙስና ይሁን ሌላ ወንጀል፣ እብደት ይሁን ሞኝነት ማጣራት፤ የዋና ኦዲተር፣ የፓርላማ፣ የፖሊስ፣ የአቃቤ ህግ ሥራ ቢሆንም፤ ያን ያህልም አስቸጋሪ አይደለም። ከብዙዎቹ ቅሌቶች በተለየ ሁኔታ፣ እርቃኑን በግላጭ የሚታይ ግዙፍ ዘግናኝ አገራዊ ቅሌት ነውና። እንደገና ለማረጋገጥ ከፈለጋችሁ መረጃዎቹን እንደገና አንድ በአንድ መመርመር ትችላላችሁ። አለበለዚያ ደግሞ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል የሰጠውን ምላሽ ተመልከቱ – እውነታው ቁልጭ ብሎ ይታያችኋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ባለፈው ሳምንት በአዲስ አድማስ በሰጠው ምላሽ፤ አገሪቱ በነፋስ ተርባይኖች ኪሳራ ደርሶባታል ተብሎ የቀረበው ዘገባ የተጋነነ ነው ብሏል። ግን፣ በደፈናው “ተጋኗል” ከማለት ውጭ፤ የትኛው መረጃ እንደተጋነነ አልገለፀም። “ይሄኛው ወይም ያኛው መረጃ ተሳስቷል፣ ይሄኛው ወይም ያኛው ቁጥር ተዛብቷል” በሚል አንዱንም መረጃ ለማስተባበል አልሞከረም። በቁጥር የተሰላው የሃብት ብክነት ላይ፤ ድርጅቱ አንዳችም የቁጥር ማረሚያ ወይም ማስተካከያ አላቀረብም። ሊያቀርብም አይችልም። ለምን በሉ። መረጃዎቹ ትክክል ስለሆኑና የሃብት ብክነቱንም በግልፅ ስለሚያረጋግጡ ለማስተባበል አይመቹም። እንዲያውም፣ ራሱ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል በሰጠው ምላሽ፣ “በእርግጥ ከውሃና ከነፋስ ሃይል፣ ውዱ የነፋስ ሃይል ነው” ብሏል። ይህም ብቻ አይደለም። “ቀደም ባሉት ዓመታት በአብዛኛው በውሃ ላይ አተኩረን የቆየነው፣ ውሃ በርካሽ የገንዘብ አቅም መልማት ስለሚችል ነው” ብሏል – ድርጅቱ። ቀደም ብዬ እንደነገርኳችሁ፣ በነፋስ ተርባይኖች እና በኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድብ መሃል ያለው ልዩነት፣ ፈፅሞ የሚያሻማ አይደለም። ጎልቶ የሚታይና በቁጥር የተሰላ ልዩነት ስለሆነ፣ ማንም ሊክደው አይችልም። የነፋስ ተርባይኖች በሙሉ፣ ኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅማቸው ደካማ መሆኑ ሳያንስ፤ ወጪያቸው ከፍተኛ ነው። እስካሁን ከ15 ቢሊዮን ብር በላይ የወጣባቸውን የነፋስ ተርባይኖች፤ እጅግ በዛ ቢባል 5 ቢሊዮን ብር በማይፈጅ የሃይል ማመንጫ ግድብ መተካት ይቻላል።
“መቼም፣ ሰዎች በጤና አይናቸው እያየ፣ ይህን ሁሉ ሃብት በከንቱ እንደዘበት ለነፋስ አይበትኑትም። አንዳች አሳማኝ ምክንያት ቢኖራቸው ነው” የሚል የቀቢፀ ተስፋ ምኞት ቢፈጠርባችሁ አይገርምም። አሳዛኙ ነገር፤ አንዳችም አሳማኝ ምክንያት የሚያቀርብላችሁ እንደማታገኙ በግልፅ እያያችሁት ይመስለኛል። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ድርጅት ይህንን እውነታ መካድ አልቻለም። እውነታው ምንድነው? የሃይል ማመንጫ ግድብ በመጠነኛ ወጪ የላቀ ውጤት ያስገኛል፤ የነፋስ ተርባይን በተቃራኒው ከፍተኛ ወጪ እየፈጀም ደካማ ነው!
ሃይል የማመንጨት ብቃታቸውን ለማነፃፀር ያህል፣ ባለፈው አመት ከሃይል ማመንጫ ግድቦችና ከነፋስ ተርባይኖች የተገኘውን የኤሌክትሪክ መጠን ተመልከቱ።

ከአሁን በፊት በተለያዩ አመታት መረጃዎችና በተለያዩ አገራት ጥናቶች እንደተረጋገጠው፣ የሃይል ማመንጫ ግድቦች ብቃት ከነፋስ ተርባይኖች ቢያንስ በ70 በመቶ ይበልጣል። የዘንድሮውን መረጃ ከሰንጠረዡ እንደምትመለከቱት ደግሞ፣ የሃይል ማመንጫ ግድቦች ብቃት ወደ ከነፋስ ተርባይኖቹ ወደ እጥፍ ገደማ ነው (በ100% ይበልጣል ማለት ነው)። በግንባታ ወጪ ስናወዳድራቸው ግን፣ በተገላቢጦሹ የነፋስ ተርባይኖች ግንባታ ለከፍተኛ ወጪ ይዳርጋሉ። የሃይል ማመንጫ ግድቦችን ለመገንባት ከሚወጣው ገንዘብ በእጥፍ የናረ ነው – የነፋስ ተርባይኖች ወጪ። ለአንድ ሜጋ ዋት የሚወጣውን ገንዘብ አነፃፅሩት።
በአጭሩ፤ ብቃታቸውን በቁጥር እናስተያይ ከተባለ፤ የሃይል ማመንጫ ግድብ ብቃት ከነፋስ ተርባይኖች ቢያንስ ቢያንስ በ70 በመቶ (ብዙውን ጊዜም በእጥፍ) ይልቃል። በወጪ ደግሞ በተቃራኒው፤ የነፋስ ተርባይኖች ከ100% በላይ (ከእጥፍ በላይ) ገንዘብ ይፈጃሉ። በድምር፤ የብቃትና የወጪ ልዩነታቸውን አዋህደን ስናነፃፅራቸው የሃይል ማመንጫ ግድቦች ውጤታማነት፣ አራት እጥፍ ያህል ነው – ከነፋስ ተርባይኖች ጋር ሲወዳደር።
በዚህ ስሌት ካሰብነው፣ እስካሁን ለተተከሉትና ውል ለተፈረመባቸው የነፋስ ተርባይኖች ከወጣው ወደ 16 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ውስጥ፣ 12 ቢሊዮን ያህሉ በከንቱ የባከነ ነው ማለት ይቻላል። ካሁን በፊት ባቀረብኩት ፅሁፍ ላይ ግን፣ የሃይል ማመንጫ ግድቦች ውጤታማነት ከሦስት እጥፍ በላይ መሆኑን፣ ለነፋስ ተርባይኖቹ የተመደበው ወጪም ከ15 ቢሊዮን ብር በላይ፤ በከንቱ የባከነው ደግሞ ከአስር ቢሊዮን ብር በላይ እንደሆነ ነው የገለፅኩት። ለምን? “ተጋኗል” የሚል ማስተባበል እንዳይመጣ ለመከላከል በማሰብ ነው – የማስተባበያ ሰበቦችን ለማጥፋት።
ከመነሻው፣ በፅሁፌ ላይ የቀረቡት መረጃዎቹ ከአንድ ተከራካሪ ወገን የተወሰዱ አይደሉም። በጭራሽ አያከራክሩም። በኤሌክትሪክ ሃይል ድርጅት ሰነዶችና ጥናቶች ላይ በተደጋጋሚ በቁጥር የተገለፁ መረጃዎች ናቸው።
ምን ለማለት ፈልጌ ነው? የትኛው እንደሚሻልና የትኛው ለብክነት እንደሚዳርግ በግልፅ እየታወቀ ነው፤ ያ ሁሉ ሃብት እንዲባክን የተደረገው። እኮ ለምን? ግራ ያጋባል አይደል!
በአምስት ቢሊዮን ብር ወጪ የሃይል ማመንጫ ግድብ መገንባትና ተመሳሳይ የኤሌክትሪክ መጠን ማመንጨት እየተቻለ፣ ለምን ከ15 ቢሊዮን ብር በላይ ሃብት ለነፋስ ተርባይኖች ወጪ ይደረጋል? 50ሺ ኮንዶሚኒየም ቤቶችን ሊያስገነባ የሚችል ከአስር ቢሊዮን ብር የበለጠ የአገር ሃብት በከንቱ ማባከን ለምን አስፈለገ?
የድርጅቱ ምላሽ እነሆ – “በውሃ ላይ አተኩረን የቆየነው፣ ውሃ በርካሽ የገንዘብ አቅም መልማት ስለሚችል ነው። አሁን ግን የሃገራችን ኢኮኖሚ በማደጉ…”
ምን ምን? “ቀደም ሲል ብዙ ገንዘብ ስላልነበረን፣ ያለንን ገንዘብ ለሃይል ማመንጫ ግድብ እናውለው ነበር። አሁን ግን ብዙ ገንዘብ ስላለን በከንቱ ቢባክን ችግር የለውም” ለማለት ነው? አስገራሚ ነው።
“እንዲያውም” ይላል ድርጅቱ፤ “እንዲያውም ‘ውዱን ጭምር ለማልማት የቻለች፣ እያደገች ያለች ኢትዮጵያ’ ብላችሁ ነው መዘገብ ያለባችሁ”።እንዴት ነው ነገሩ! አድናቆት መሆኑ ነው? “ሃብትን በከንቱ ማባከን የቻለች አገር!” እንደማለትኮ ነው። አማራጮቹ ግልፅ ናቸው። እስቲ በቀላል አገላለፅ ለማነፃፀር እንሞክር። “15 ቢሊዮን ብር ለምን ተግባር ይዋል?” የሚል ጥያቄ ቀረበ እንበል። ለጥያቄውም ሁለት አማራጮች መጥተዋል።

እንደገና ልድገመው። የብክነቱና የቅሌቱ ማስረጃ የተሟላና ግልፅ ስለሆነ፤ ወዲህ ወዲያ የሚያስብል ማምለጫ የለውም – ማንም ሊክደው የማይችል፣ ጎልቶ የሚታይና በቁጥር የተሰላ ሃቅ ነው።
የብክነቱና የቅሌቱ መጠን ደግሞ ያስደነግጣል – ከአስር ቢሊዮን ብር በላይ የአገር ሃብት ነው በከንቱ የባከነው።
ገና ምላሽ ያላገኙ ሁለት ጥያቄዎች ግን አሉ። የቅሌቱ መንስኤ ምንድነው? የብክነቱ ተጠያቂዎችና የቅሌቱ ተዋናዮችስ እነማን ናቸው?
=========================================

ከውሃ ግድቦች የመነጨ               ከነፋስ ተርባይኖች የመነጨ ሃይል
ሃይል (ባለ 1810 ሜዋ)                (ባለ 171 ሜዋ)

አንደኛ ሩብ ዓመት        (2,070 ጊዋሃ)                      (100 ጊዋሃ)
ሁለተኛ ሩብ ዓመት      2,030 ጊዋሃ                             103 ጊዋሃ
ሦስተኛ ሩብ ዓመት      2,070 ጊዋሃ                          109 ጊዋሃ
አራተኛ ሩብ ዓመት      2,170 ጊዋሃ                          88 ጊዋሃ
የዓመት ድምር          8,340 ጊዋሃ                         400 ጊዋሃ
ከ1 ሜዋ የተገኘ         4 ጊዋሃ                             2.3 ጊዋሃ
የማመንጨት          ብቃት 52.6%                               26.7%
==================================
ከአሁን በፊት በተለያዩ አመታት መረጃዎችና በተለያዩ አገራት ጥናቶች እንደተረጋገጠው፣ የሃይል ማመንጫ ግድቦች ብቃት ከነፋስ ተርባይኖች ቢያንስ በ70 በመቶ ይበልጣል። የዘንድሮውን መረጃ ከሰንጠረዡ እንደምትመለከቱት ደግሞ፣ የሃይል ማመንጫ ግድቦች ብቃት ወደ ከነፋስ ተርባይኖቹ ወደ እጥፍ ገደማ ነው (በ100% ይበልጣል ማለት ነው)። በግንባታ ወጪ ስናወዳድራቸው ግን፣ በተገላቢጦሹ የነፋስ ተርባይኖች ግንባታ ለከፍተኛ ወጪ ይዳርጋሉ። የሃይል ማመንጫ ግድቦችን ለመገንባት ከሚወጣው ገንዘብ በእጥፍ የናረ ነው – የነፋስ ተርባይኖች ወጪ። ለአንድ ሜጋ ዋት የሚወጣውን ገንዘብ አነፃፅሩት።

==================================
የውሃ ሃይል ማመንጫ     አቅም             ጠቅላላ ወጪ            የ1 ሜዋ ወጪ
ተከዜ                      300 ሜዋ          340 ሚ. ዶላር         1.16 ሚ. ዶላር
ጣና በለስ                 460 ሜዋ           600 ሚ. ዶላር        1.3 ሚ. ዶላር
ግልገል ጊቤ2               420 ሜዋ          540 ሚ ዶላር          1.3 ሚ ዶላር
ግልገል ጊቤ3                1870 ሜዋ        1.7 ቢ ዶላር            ከ1 ሚ. ዶላር በታች
ሕዳሴ                        6000 ሜዋ       5 ቢ ዶላር              ከ1 ሚ. ዶላር በታች
የውሃ ሃይል ማመንጫ         አቅም             ጠቅላላ ወጪ           የ1 ሜዋ ወጪ
መቀሌ አሸጎዳ                  120 ሜዋ         300 ሚ ዶላር         2.5 ሚ ዶላር
ናዝሬት አዳማ1                51 ሜዋ           120 ሚ ዶላር          2.3 ሚ ዶላር
ናዝሬት አዳማ2                  153 ሜዋ         345 ሚ ዶላር        2.3 ሚ ዶላር
==============================
የ1 ሜዋ ወጪ
የሃይል ማመንጫ ግድቦች አማካይ ወጪ             1.1 ሚ. ዶላር
የነፋስ ተርባይኖች አማካይ ወጪ                    2.3 ሚ. ዶላር

==========================
ከአሁን በፊት በተለያዩ አመታት መረጃዎችና በተለያዩ አገራት ጥናቶች እንደተረጋገጠው፣ የሃይል ማመንጫ ግድቦች ብቃት ከነፋስ ተርባይኖች ቢያንስ በ70 በመቶ ይበልጣል። የዘንድሮውን መረጃ ከሰንጠረዡ እንደምትመለከቱት ደግሞ፣ የሃይል ማመንጫ ግድቦች ብቃት ወደ ከነፋስ ተርባይኖቹ ወደ እጥፍ ገደማ ነው (በ100% ይበልጣል ማለት ነው)። በግንባታ ወጪ ስናወዳድራቸው ግን፣ በተገላቢጦሹ የነፋስ ተርባይኖች ግንባታ ለከፍተኛ ወጪ ይዳርጋሉ። የሃይል ማመንጫ ግድቦችን ለመገንባት ከሚወጣው ገንዘብ በእጥፍ የናረ ነው – የነፋስ ተርባይኖች ወጪ። ለአንድ ሜጋ ዋት የሚወጣውን ገንዘብ አነፃፅሩት።

ምንጭ – አዲስ አድማስ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.