ወያኔ የቆመበት አዲስ የኮንቬንሽናል ጦርነት ዋዜማ የለም፤ ለዋዜማ ሬዲዮ – መስቀሉ አየለ

ዋዜማ ራዲዮ፡ “የኢትዮጵያ መንግስት “የደህንነት አደጋ ደቅነውብኛል በሀገሪቱ ስላምና መረጋጋትን አናግተዋል” ያላቸውን ሀይሎች ለመፋለም እየተዘጋጀ መሆኑን በገዥው ፓርቲ ዙሪያ ላሉ ቁልፍ ሹማምንትና ለደህንነት አካላት ሹክ ብሏል።

ኢህአዴግ በተለይ በአማራና ኦሮምያ ክልሎች ተከስቶ የነበረው ህዝባዊ አመፅ እንዳይደገም ይረዱኛል ያላቸውን እርምጃዎች በሁለት ዘርፍ ከፍሎ ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰናዳ መሆኑንም ለዋዜማ የደረሰ መረጃ ያመለክታል። ከእርምጃዎቹ አንዱ በኤርትራ ላይ የሚከተለውን ፖሊሲ መለወጥና በአስመራ ላይ ስልታዊ እርምጃ መውሰድ እንዲሁም በውጪ ሀገር ያሉ ተቃዋሚዎችና ሚዲያዎችን በህግ ፊት ማቅረብና ማዘጋትን ያካትታል። አርበኞች ግንቦት ሰባትና ኦነግ እንዲሁም ኢሳትና ኦ ኤም ኤን የአዲሱ የመንግስት ጥቃት ኢላማ መሆናቸውን የመንግስት የቅርብ ምንጮች አረጋግጠዋል። በኤርትራ ላይ የተዘጋጀው አዲስ ዕቅድ በቅርቡ ለህዝብ ይፋ የሚደረግ ሲሆን በሌሎቹ ጉዳዮች ላይ አለማቀፍ አማካሪ ለመቅጠርና የምዕራባዉያንን ትብብር ለመጠየቅ ዕቅድ ተይዟልዕ ሲል በዚህ ሳምንት ዘግቧል።

ይህን ዘገባ ተከትሎ በማህበራዊ ድህረገጽ ላይ የተንሸራሸሩ የተለያዩ መላ ምቶችን የያን ሲሆን በጉዳዩ ላይ የተጨነቁም አልጠፉም። የብዙዎቹ የጭንቀት ምክንያት ግን በዋነኛነት የአዲሱ የትራምፕ አስተዳደር በባህሪው ነገሮችን የሚያይበት መንገድ ከተለመደው ወጣ ያለና ነጮቹ “አንፕሪዲክተብል” የሚሉት አይነት በመሆኑ ምናልባት በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የገባውን ቃል አጥፎ ከወያኔ ጋር መዳራቱን ከቀጠለ እንደ ገና በትራምፕ አስተዳደር ድጋፍ የእድሜ ማራዘሚያውን ትኬት በመቁረጥ ተጨማሪ የስቃይ አመታት እንገፋ ይሆናል ከሚል ስጋት ነው።

በኔ እምነት ግን እንዲህ ያሉ ነገሮች እንደወረዱ መታየት የለባቸውም ባይ ነኝ።ምክንያቱም በተደጋጋሚ እንደ ታየው ወያኔ ውጥረት ሲበዛበትና የፖለቲካው ዳይናሚክስ ወደየት እያመራ እንደሆነ ማሰብ ሲሳነው እንዲህ አይነት አጀንዳዎችን በመፍጠርና ወደ ሰው በመወርወር የህዝቡን ቀልብ ወደ አንድ አቅጣጫ የመሳብና ብዥታ የመፍጠር ስልት ይጠቀማል። የእሩቁን ትተን ባለፈው ሃምሌ ወር አካባቢ የነበረውን እንኳን ብናስታውስ አሁን ከነደፈው እቅድ የበለጠ የተጨበጠና የምር የሚመስል እቅድ ወጣ በተባለ በጥቂት ግዜ ውስጥ እቅዱን የእውነት ለማስመሰል በኤርትራ ድንበር በኩል ወረራ የሚመስል ነገር ለማካሄድ ሞክሮ እንደ ነበረ የሚታወስ ነው።
እቅዱም “የሻቢያን አከርካሪ እስከ መጨረሻው የሚሰብርና ሻቢያን በታማኝ ቡድኖች ለመተካት እንዲያስችል የሻቢያን ተቃዋሚዎች ያሳተፈና እግረ መንገዱንም በኤርትራ የመሸጉትን ጸረ ወያኔ ተቃዋሚዎች እግር ሳያወጡ በእንጭጩ ቆርጦ በማስቀረት አስተማማኝ ሰላም መፍጠር” የሚል አላማን የያዘ ነውም ተብሎ ነበረ። ይኽንን ነገር ተከትሎ በኢሳት ቴለቪዥን ጭምር ባለሙያዎች እየቀረቡ “ጦርነቱ ወይ አስመራ ወይንም አዲስ አበባ ይጠናቀቃል” የሚል ትንታኔ ሲስጡበት የነበረ ቢሆንም በሁለት የተለያየ ግንባር እጁን የሰደደው ወያኔ ለመጨበጥ የሞከረው አለሎ ምን ያህል አደገኛ እረመጥ እንደ ነበር እሳት ውስጥ እንደገባ ላስቲክ በጥቂት ግዜያት ውስጥ ተኮማትሮ የቀረው በመቶዎች የሚቆጠረው የአጋዚ ሰራዊት ማስረጃ ነው። ባጭሩ የትም ያልደረሰ ድንፋታ እንደነበርና ያ ሁሉ ዝርዝር ፕላን ባዶ ምኞቱን በወረቀት ላይ ከማስፈር በላይ ተሻግሮ የመሄድ ብቃትም ሆነ አላማ እንዳልነበረው አስመስክሮ ያለፈበት ዲስኩር እንደ ነበር ይልቁንም ወያኔ አሁን ያለበትን ቁመና ከፍቶ በማየት ይኽ የወጣው ሰነድ ዛሬም እንደ ትናንቱ ባዶ ፊኛ መሆኑን ድምዳሜ ላይ መድረስ ይቻላል:;

፩ በብዙ መመዘኛ ወያኔ ከአምናው ይልቅ ዘንድሮ የተዳከመ ቁመና ላይ መሆኑ እሙን ነው። ህዝባዊ እንቢተኝነቱ ወደ ህዝባዊ ተጋድሎ ተሸጋግሮ በብዙ የአማራው ከፍተኛ ቦታዎች አካባቢ ነውጡ በመሳሪያ ሃይል መታገዝ የጀመረበት፣
፪ ብዙ ገጠራማ ቦታዎች ከወያኔ ቁጥጥር ውጭ በመሆናቸው ስልጠናው በዚሁ አካባቢ ስልጠና የሚሰጠጥበት;
፫ ትግሉ እየበሰለ፣ ህዝቡ ይበልጥ ወደ በረሃ እየተመመና ለመረረ መስዋእትነት እራሱን እያዘጋጀ ያለበት;
፬ ቀሪውም ህዝብ ነጻ አውጭ ከመጠበቅ ይልቅ ትግሉ እቤቱ በር ላይ እስኪ ደርስለትና እራሱም የድርሻውን ለመወጣት በጥፍሩ ቆሞ የሚጠብቅበት
፭ ኢህአዴግ የሚባለው የወያኔ ጭምብል ወልቆ TPLF እርቃኑን የቆመበት ብቻ ሳይሆን እራሱ በአንጃ የተከፈለበትና ማእከላዊነት የጠፋበት;
፮ በአለም ላይ ይኽ ነው የሚባል የውጭ ፖሊሲ የሌለው መንግስት ቢኖር የወያኔ መንግስት እንደመሆኑ ለሩብ ምእተ ዓመት ያህል ኢትዮጵያን ታህል አግር እየገዛ ኢትዮጵያዊ መሆን ያልቻለና ከትግራይ ውጭ ማሰብ የተሳነው እና ለግዜው እስከጠቀመው ድረስ የአገሪቱን ብሔርዊ ጥቅም እጅ መንሻ ሲያደርግ መኖሩ ይልቁንም ከአገሪቱ መዳከም እጠቀማለሁ ብሎ በቆሻሻ ስሌት ውስጥ እንዳልኖረ ዛሬ ያ ሁሉ ኑፋቄ ተጠራቅሞ ወደ አንዳች መርገምት መቀየር የጀመረበትና የእጁን ለማፈስ የተቃረበበት አካባቢያዊ ሁኔታ መፈጠሩን የአለም መገናኛ ብዙሃን የዘገቡት ሃቅ ነው። እንደ ሴተኛ አዳሪ ቀሚሱን እየገለበ ከማንም ሴረኛ መንግስታት ጋር አንሶላ ሲጋፈፍበት የነበረበት ዘመን አልቆ በሶስት መቶ ዲግሪ ወታደራዊ ከበባ ላይ የወደቀው ወያኔ የትናንቱዋን ደቡብ ሱዳን እንኩዋን ማስፈራራት ያልቻለበት፤ብሎም አዲሱ የትራምፕ አስተዳደር ይወስዳል በሚባለው የበጀት ድጎማ ፖሊስ ስረዛ የተደናገጠበት፤
፯ በማይናወጽ አለት ላይ “በሁለት እግሩ ተከልነው” ሲሉት የነበረው “ህገ መንግስታችን” የሚሉት ድሪቶ አቅም አልባ ሆኖ አገሪቱ በአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ውስጥ ለመንፈቅ ያህል የቆየችበት ብቻ ሳይሆን ዛሬም ድረስ ድፍረት ኖሮት ይኽን አዋጅ ለማንሳት በራሱ ላይ እምነት ባጣበት በዚህ አጣብቂኝ ሰዓት በምን ስሌት ነው በሻቢያና በዚያው ምድር ላይ አሉ በሚላቸው የታጠቁ ጸረ ወያኔ ሃይላት ላይ ደፍሮ ጦር የሚሰብቀው?

በእርግጥ አንጻራዊ በሆነ መልኩ ወያኔ መለስ በነበረበት ግዜ ማእከላዊ አመራር የነበረው ሲሆን የፖለቲካውም ሃይል በስለላ ክንፉም ሆነ በወታደራዊው መዋቅር ላይ ከፍ ያለ ጉልበት እንደነበረው ያም ሆኖ ግን ሻቢያንም ሆነ ድንበር ተሻግሮ ተቃዋሚዎቹን ለመምታት የሚያስችል ቁመና እንዳልነበረ የሚያውቀው መለስ ከሻቢያ ጋር ለመታረቅ ሰባ ሁለት ግዜ ያህል አማላጅ መንግስታት፣ ታዋቂ የአገር ሽማግለዎችን እና በሚስጥር ደግሞ የታሸገ ፖስታ ለአትሌት ሃይሌ ገብረስላሴ በማስያዝ ናይሮቢ ለሚገኘው የኤርትራ ኤምባሲ መላኩን እናውቃለን።ያም ሆኖ ግን ያ ሁሉ ደጅ ጥናት ውሃ ነበረ የበላው።

ለማጠቃለል ያህል ወጣ የተባለው ዘገባ አሁንም እንደ ባለፈው ላንድ ሰሞን የፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ሆነ ተብሎ በሳሞራው አገዛዝ የተለቀቀ ባዶ ዲስኩር ብቻ ነው። ዛሬ የወያኔ የፖለቲካና የስለላ ክንፍ ከሳሞራ ተገንጥሎ በራሱ ዛቢያ በሚሽከረከርበት፣ ሳሞራ ከመከላከያ ቢሮ ባሻገር የአራት ኪሎውን ምንጣፍ መጎተት በጀመረበት ሁኔታ ድንበር ተሻጋሪ ጦርነት መክፈትና ያሰበውን ማሳካት ቀርቶ በሰላማዊ መንገድ ችግሮቹን ለመፍታት የሚያስችል አጀንዳ ለመቅረጽ አቅም እንደ ሌለው እግር ጥሎት ወያኔን የወረሰውን የቁምጥና ደዌ መጠኑን የታዘበ መንገደኛ ሁሉ ያውቀዋል። ወያኔ እኮ በባድመ ዘመቻ ወቅት በተሻለ የህዝብ ድጋፍና ቁመና አንድ ሆኖ ዘምቶ ሶስት ሆኖ ነበር የተመለሰው። ዛሬ ያ ቁመና ላይ አይደለም።ዛሬ ከውስጥም ከውጭም ምንነቱ እንደ ሽንፊላ ተገልብጦ እንደ እንዝርት ተፈርቅጦ የታወቀው ይሕ ቡድን መረብን መሻገርና ኮንቬንሽናል ጦርነት ማካሄድ ቀርቶ ከጎንደር ከተሞች ጥቂት ኪሎ ሜትሮች ወደ ውስጥ ገባ ብሎ የሚገዛው የገጠር ቀበሌ እንደሌለ ያውቀዋል። ዛሬም እንደ ባለፈው ሁሉ እንዲሁ አለሁ ለማለት ያህል ብቻ በባድመማን በጾረና ድንበር አካባቢ መጠነኛ ትንኮሳ ሊያደርግ ከሚችል በቀር።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.