የኢትዮጵያ ሴቶች ፖለቲካዊ ተሳትፎ ትናንትና ዛሬ – ፋሲካ ገ/ጻዲቅ ወ/ሰንበት

ወ/ሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ የቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ተ/ምሊቀመንበር የነበሩትሰላም ክቡራትና ክቡራን ኢትዮጵያዊያን ወገኖቼ፤ በዛሬው ዕለት የምናገርበት ርእስ ስለሴቶች በብዛት ወደ ነጻነት ትግሉ ጎራ አለመቀላቀል ቢሆንም እግረመንገዴን በወንዶች የተመላው እና የሴት ያለህ የሚለው የትግል ጉዞአችን ለምን እንደሚጠየቀው ጾታዊ ስብጥር የለውም የሚለውን ሃሳቤን አካፍላችሁዋለሁ። እንደመንደመሪያ፤ የሴቶች ሚና በሃገራችን የታሪክ ሂደት ውስጥ ምን ይመስል እንደነበረ ጥቂት እውነታዎችን፤ እንዲሁም ባለፉት 25 ዓመታት በተደራጁትና ህወሃት መራሹን ስርዓት በሚቃወሙት ድርጅቶች ውስጥ፡ የሴቶች ተሳትፎ ለምን ሊበረታታ እንዳልቻለ የበኩሌን እይታ እገልጻለሁ። ዓላማዬም ካለፉት ድክመትና ጥንካሬዎቻችንን ተምረን ነገን ብሩህ ለማድረግ፤ ፍትህ እኩልነት፤ ሰብዓዊትና የዜግነት መብት የተከበረባት ኢትዮጵያን፡ እኔ እንደማልማት እንድታልሟት ራዕዬን ማካፈል ነው።

ሴት ልጅ በጡንቻ ካልሆነ በቀር በማንኛውም ነገር ከወንድ ልጅ አታንስም፤ እሱንም ስፖርት ካዘወተረች ትደርስበታለች። ሴት ልጅ ተፈጥሮዋ ሆኖ ሊሆን ይችላል፡ ትራራለች፤ ትሳሳለች፤ ላመነበችበት ዓላማ መስዋዕትነት ትከፍላለች፤ እጅግ ትታገሳለች፤ ሲበቃት ደግሞ አራስ ነብርን ታስንቃለች። ሴት ልጅ እቤት የምትውለው ሳታውቅ ቀርታ፤ ዝም የምትለው ፈርታ፤ አይዞህ የምትለው ሳይከፋት ቀርታ፤ ዝቅ የምትለው መከበር ጠልታ አይደለም። ኑሮዋን፤ ልጆችዋን፤ ዓላማዋን፤ ከፍ ሲልም የማህበረሰቧን ሰላምና ደህንነት ቅድሚያ ሰጥታ እንጂ።  በአንድ ወቅት በካናዳ የቀድሞዋ የሚሲሳጋ ከንቲባ ሄዘር ማካሊዮን፡ በቅጽል ስማቸው ኸሪኬን ሄዘር፤ 12 ጊዜ በህዝብ ተመርጠውና ለ36 ዓመታት በከንቲባነት አገልግለው በ93 አመታቸው በበቃኝ ለምርጫ መወዳደር ከማቆማቸው በፊት CBC ሬድዮ ላይ ቀርበው በስራ ዘመናቸው ከወንዶች በኩል ምን ያህል ፈተና እንደደረሰባቸው ሲጠየቁ የሰጡት መልስ፤ የሳቸውን የሃላፊነት ተግባር ለመቀበል የሚያንገራግሩት ከወንዶች ይልቅ ብዙ ጊዜ ሴቶች እንደነበሩ ተናግረው ነበር። እምነታችንም፤ ትምህርታችንም፤ ማህበረሰባችንም ስለ ሴት ልጅ ክብር፤ እኩልነትና አስተዋጽኦ እዚህም እዚያም

ቢጠቃቅስም፡ በተግባር ግን ሴት ከወንድ እኩል መሰለፍ መቻሏን ለመቀበል፡ ዲሞክራቲክ የሚባለው ካናዳ ውስጥ እንኳን መቸገራቸውን የኸሪኬን ሄዘር ተሞክሮ አንድ ምሳሌ ነው።

ወደ ሃገራችን ጉዳይ ስንመለስ፤ በኮ/ል አሌኸንድሮ ዴል ባዬ ተጽፎ በ ዶ/ር ተስፋዬ መኮንን ባይለየኝ በተተረጎመው ቀይ አንበሳ በሚባለው መጽሃፍ ውስጥ (1992፤ ገጽ 183፤84) ጸሃፊው የአለማየሁ ባሪያ ወይም “ማሚቴ” ብሎ እንደሚጠራት የትግራይ ሴት፤ በታሪካችን ሂደት ለሃገራቸው የተለያዩ አስተዋጽኦዎችን ያበረከቱ እንዲሁም ሃገራቸውን ከጠላት ወረራ  ለመታደግ በተደረጉ የጦርሜዳ ውሎዎች የተሳተፉ ነገር ግን ስማቸውን እንኳ በውል የማናውቃቸው ብዙ ባለውለታ ሴቶች ነበሯት፤ ዛሬም ከመጋረጃው ጀርባ  ብዙ ስራዎችን እንደሚሰሩ ጥርጥር የለኝም።

በአንጻሩ፤ ገድላቸው ከተከተበላቸው ነገስታት መሃከል፡ በቅድሚያ ንግስት እሌኒን ለማንሳት እወዳለሁ። ንግስት እሌኒ በፖለቲካና ዲፕሎማቲክ ብስለታቸው የሚደነቁ፡ በ16ኛው ክ/ዘመን ሊፈቱ የሞከሩት ችግር ዛሬም ያልተፈታ፡ የምስራቅ አፍሪካንና የመካከለኛው ምስራቅን አካባቢያዊ ቅራኔ እንዲሁም የአውሮፓዊያንን አሰላለፍ ያስተዋሉና የአለምአቀፍ ግንኙነት አካሄዱ ጠንቅቆ የገባቸው ሴት ነበሩ። ንግስት እሌኒ አባታቸው ገራድ አህመድ የተባሉ የደዋሮ ሰው ነበሩ። በዚያን ጊዜ ደዋሮ ተብሎ የሚጠራው ከሸዋ በስተምስራቅና በስተሰሜን፤ የዛሬውን አዳማን ጨምሮ፤ በስተምስራቅ ከአዳል ሡልጣናዊ ግዛት በኩል እያጠቃለለ የሚዋሰን የነበረው ስፍራ ሲሆን፤ አብዛኛው ህብረተሰብ የእስልምና  እምነት ተከታይ ነበረ ይሉናል አቶ ይልማ ደሬሳ (የኢትዮጵያ ታሪክ በአስራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን 1959፤ ገጽ 13፤14)።

እሌኒ አጼ በዕደ ማሪያምን አግብተው ንግስት የሆኑ ሲሆን፡ ባለቤታችው በሞት ከተለዩዋቸው በኋላ፡ ለዐጼ እስክንድርና አጼ ያዕቆብ በእንደራሴነት፤ ልጃቸው ዳግማዊ ዐምደ ጺዮን ነግሶ ህይወቱ ሲያልፍ ደግሞ፡ ለልጃቸው አጎት ለዐጼ ናዖድ የበላይ አማካሪ ሆነው በወቅቱ በቱርኮች የተቃጣውንና ለኢትዮጵያ ህልውና

አስጊ የነበረውን ሁኔታ፡ ፖርቹጋሎችን እርዳታ በመጠየቅ፤ ከአካባቢያችን አረብ ሃገሮች ጋር ጥሩ ጉርብትና  እንዲኖር በመስራት፤ እንዲሁም ከአዳል ሱልጣኔቶችና ከሌሎችም አሚሮች ጋር ቤተሰባዊ ዝምድና ስለነበራቸው፡ ከማዕከላዊ መንግስቱ ጋር የአስታራቂነትና የዲፕሎማቲክ ሚና በመጫወት፤ ለ400 አመታት የቆየን ግጭት ወደ ሰላማዊ ግንኙነት ለመቀየር አስችለዋል (ይልማ ደሬሳ የኢትዮጵያ ታሪክ በአስራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን 1959፤ ገጽ 18፤19፤21፤24፤25)። ንግስት እሌኒ የሃይማኖት ልዩነት ሳይበግራቸው እስላሙን፤ ኦርቶዶክስና ካቶሊክ ክርስቲያኖችን፤ ሃገራቸውን ከጎረቤት አፍሪካ ሃገሮችና ከአረቦች እንዲሁም ከአውሮፓዊያንን ጋር አግባብተው መስራት የቻሉ ተራማጅና፤ አርቆ አሳቢ ሴት ነበሩ።

በመቀጠል፡ የዐጼ  ባካፋ  ባለቤት የነበሩት የቋራ ተወላጅዋ እቴጌ ምንትዋብን ብንወስድ፡ በጣና ደሴት ላይ ዛሬ  የቱሪስት መስህብ የሆኑትን፡ የወንዶች ብቻ የሆነውን ክብራን ገብርኤልን ጨምሮ፤ ትልልቅ አድባራትና ገዳማትን ያሰሩ ሲሆን፤ በልጃቸው በዐጼ እያሱ ብርሀን ሰገድ ዘመንም በሞግዚትነት ነግሰው ትምህርት እንዲስፋፋ ለማድረግ ከአረቢኛ ወደ ግእዝ ያስተረጎሟቸውን መጽሃፍት፡ ተማሪዎች ከሸዋ፤ ከትግሬና ከጎንደር ወደ ደሴቷ መጥተው ለቀለባቸው ሳያስቡ ለዓመታት መጽሃፍቶቹን እንዲያጠኑ አስችለዋል (ተክለጻዲቅ መኩሪያ የኢትዮጵያ ታሪክ ከዐጼ ልብነድንግል እስከ ዐጼ ቴዎድሮስ 1961፤ 4ኛ ዕትም ገጽ 256 እና 281)።

በሌላ በኩል፤ እቴጌ ጣይቱም በበኩላቸው ከአድዋ  ጦርነት በፊት ኮንት አንቶኔሊን “ማን የሚደነግጥልህ አለ ጦርነቱን በፈቀድክ ጊዜ አድርገው እኛም ከዛው እንቆይሃለን” ብለው በመለሱለት መልስና በሌሎች ቆራጥና ብልህ ምክራቸው የበለጠ የሚወደሱ ቢሆንም፡ አፈወርቅ ገብረየሱስ እንደጻፉት፡ ኮንት አንቶኔሊ የውጫሌ ውል ተርጓሚውን ግራዝማች ዮሴፍን እፊታቸው መሳደቡን በመቃወም፤ ስህተት ካለ የመገሰጽ መብት የኢትዮጵያዊያን ብቻ መሆኑን ማስገንዘባቸው ስለዜጎች መብት ያላቸውን የህግ ግንዛቤ

ሲያሳይ፤ በአንጻሩ ደግሞ፡ ዛሬ በሃገራችን ለዜጎች መብት የሚቆም መንግስት አለመኖሩ ምን ያህል ጉዞአችን የኋልዮሽ እየሄደ እንደሆነ ያመለክተናል (አጤ ሚኒሊክ 1901፤ገጽ 76፤77)።

በተጨማሪም፤ ምንም እንኳ ከ1909-1922 በንግስና ቢቆዩም፡ እምብዛም ታሪካቸው ሲነገር የማንሰማው ንግስተ ነገስታት ዘውዲቱ፤ በ7 ዓመታቸው ለ12 ዓመቱ የአጼ ዮሃንስ ልጅ፡ ራስ አርአያ ዮሃንስ፡ ለሃገር አንድነትና ደህንነት ሲባል  ልጅነታቸው መስዋዕት ተደርጎ ነበር የተዳሩት። በንግስናቸውም ዘመን ዛሬ ለተለያዩ  የእምነት ተከታዮች አገልግሎት በቀብር ስፍራነቱ የሚታወቀውን የአዲስ አበባውን ዮሴፍ ቤተ ክርስቲያንን ጨምሮ እጅግ በርካታ አብያተ ክርስቲያናትን አሳንጸዋል። እንዲሁም ዘውዲቱ ሆስፒታልን የሴቶች ማዋለጃ አገልግሎት እንዲሰጥ ያሰሩትም እኒህ ንግስት ነበሩ። በዘመኑ የፊታውራሪ ሃ/ጊዮርጊስና የአልጋ ወራሽ ወገን እየተባባለ የነበረውን መካረር ሰላም ወዳዷ ንግስት ዘውዲቱ፡ በማስማማትና በታላቅ ትእግስት ያበርዱት እንደ ነበረ የዓይን ምስክርነት ቃላቸውን ደጃዝማች ከበደ ተሰማ በጽሁፍ አኑረዋል (የታሪክ ማስታወሻ  1962 ገጽ 31፤36፤39፤43)።

ሌላዋና፡ የሃገራችን የመጨረሻዋ ንግስት ሆነው ያለፉት እቴጌ መነን፤ በየካቲት 3 1938፤ የእቴጌ መነን የሴቶች ትምህርት ቤትን የመሰረት ድንጋይ በማኖር፡ የሃገራችን ሴቶች ዘመናዊ ትምህርትን እንድንቀስም የሚያበረታታ መሰረት ጥለዋል። በ1942 ደግሞ 14 ቅዱሳን መጽሃፍት እንዲተረጎሙ እና 3800 ቅጂዎች እንዲሸጡ አርገው $12 ሺህ ብር፡ አቅም ለሌላቸው ህጻናት መማሪያ እንዲሆን  ለቅዱስ ጳውሎስ የስዋስው ትምህርት ቤት አበርክተዋል። እቴጌ መነን በሃገራችን የመጀመሪያው የህክምና ትምህርት ቤት፤ ልእልት ጸሃይ ሆስፒታል እንዲሰራ፡ የእናታቸውን ርስት በስጦታ የሰጡ ሲሆን፤ ልጃቸው ልእልት ጸሃይ እንግሊዝ ሃገር የነርስነት ትምህርት ሲከታተሉ የተዋወቋቸው የኢትዮጵያ ባለውለታ ወ/ሮ ሲልቪያ ፓንክረስትም

ለሆስፒታሉ ገንዘብ በማሰባሰብ ተባብረዋቸው፤ የእቴጌዋ የበጎ አድራጎት ተግባር እንደታቀደው ሊከናወን ችሏል። በነገራችን ላይ የእቴጌ መነን እናት፡ የወ/ሮ ስህን አባት፡ ንጉስ ሚካኤል፤ የነቢዩ መሃመድ 5ኛ ትውልድ ከሆኑት ከአብዱላህ ቢን ሙሃመድ አል ባኪር የዘር ሃረጋቸውን እንደሚስቡ Anjahli Parnell ጽፈዋል (The Biography of Empress Menen Asfaw: The Mother of the Ethiopian Nation 2011፤ ገጽ 101፤105፤174)።

ሌላዋ ተደናቂ ሴት ወ/ሮ ሸዋረገድ ገድሌ ሲሆኑ፡ ወ/ሮዋ የጣሊያን ወታደሮችን ዕቅድ ለአርበኞች በማድረስ፤ የከተማ ውስጥ አርበኞችን በማስተባበር፤ ለአርበኞች ጠመንጃ፤ ጥይትና ስንቅ በማቀበል የታገሉ ስመ ጥር አርበኛ ሴት መሆናቸውን ጀ/ራል ጃጋማ ኬሎ መስክረውላቸዋል። ወ/ሮ ሸዋረገድ ገድሌ፡ በወቅቱ የሚናቀውን የንግድ ስራ በትጋት በማከናወን፡ የዘይት ማምረቻ፤ የአልኮል ፋብሪካ፤ የእንጨት ስራ፤ የአትክልትና  ፍራፍሬ ምርት በመሳሰሉ የንግድ ስራዎች ላይ በግላቸውም ሆነ  ከግሪኮች ጋር በሽርክና በመስራት፡ ስራ ፈጣሪ እና ባለሃብት ሴት መሆናቸውን ደራሲ ሺበሺ ለማ ጽፈዋል (ሸዋረገድ ገድሌ  የአኩሪ ገድላት ባለቤት የህይወት ታሪክ 1878-1942  2007፤ ገጽ 200፤201፤206፤207)።

እነዚህ የጠቀስኳቸው መልካም ስራን ሰርተው ያለፉ ኢትዮጵያዊያን ሴቶች ታሪክ እንደሚያሳየንም ሆነ፤ የሰላም ጥናት አባት ተብለው የሚወደሱት ኖርዌጂያዊው ዮሃን ገልታንግ እንደጻፉት፤ አርክቴክቶችና ኢንጅነሮች በትምህርትና በስልጠና የሚያገኙትን፡ ልዩነቶችን አቻችሎ፤ ቅራኔዎችን ፈቶ የማለፍን ጥበብ፤ ሴቶች ግን በተፈጥሮ እንደታደሉት ጽፈዋል (Peace, and Development: Theories and Methodologies 2015፤ ገጽ 31፤ 32) ። የቀደምት ሴቶች ኢትዮጵያዊያንን ገድል የዘረዘርኩት ለመመጻደቅ፤ ለመበላለጥና ከወንዶች ጋር ለመፎካከር ሳይሆን፡ የእኛም ሆኑ የሌሎች ዓለም ማህበረሰቦች፡

ይህንን የሴትን ልጅ ልዩ ክህሎትና ተፈጥሮ፡ የተሻለ፤ መፈቃቀርና መከባበር የነገሰባት ሰላማዊ ዓለም ለመገንባት አለመጠቀማችን፡ “ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣል” የሚለውን ብሂልን እንዲያስታውሰን ብዬ ነው።

         ወደ ዘመናችን የሴቶች ፖለቲካዊ ተሳትፎ ስንመጣ ደግሞ፡ ጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙ የኢህአዲግ ቀይ እስኪብርቶ በሚል ርዕስ በ2004 ዓም ባሳተመችው መጽሃፍ፤ የሴቶች ተሳትፎ በሃገራችን የፖለቲካ ማህበረሰብ ዘንድ፡ በህወሃትም ሆነ በተቃዋሚዎች መንደር ባዶ መሆኑን ጠቁማለች። ከዚህ በተለየ መልኩ የቀድሞው አንድነት ፓርቲ ብቻ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን ለፓርቲ ሊቀመንበርነት በመምረጥ ፈር ቀዳጅ ቢሆንም፤ ይኸው ፓርቲ በወቅቱ 20 ከሚሆኑት የስራ አመራሮቹ መሃል 2ቱ ብቻ ሴቶች እንደደሆኑ ጽፋለች (ገጽ 201፤202)። በበኩሌ የወያኔን ስርዓት መብት በመንፈግ የሚያክለው ባይኖርም፡ “የድርጅቱን” ሚስት፤ አዜብ መስፍንን ግን፡ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ እንድትነግስ ለክፉ ስራም ቢሆን ዕድል መስጠቱ፡ ከተቃዋሚዎች አሰላለፍ እጅግ በጥቂቱም ቢሆን ለየት ያደርገዋል እላለሁ። የኢትዮጵያን ፖለቲካ ነፍስ ካወቅኩባቸው አመታት ጀምሮ በርቀት፤ ላለፉት አስራ ሁለት ዓመታት ደግሞ በቅርበት እንዳስተዋልኩት፤ በነጻነት ጥማትና በአልገዛም ባይነት ትግል የማህበረሰባችንን ትብትብ አመለካከት ጥሰው ከወጡትና ከማደንቃቸው እህቶቼ፡ ጋዜጠኛ ሰርካለም ፋሲል እና ጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙ ውጪ፤ የዘመናችን የፖለቲካ ማህበረሰብ አበረታቶ፤ መርጦ፤ እደጉ ተመንደጉ ብሎና ፈቅዶ ያፈራቸው፡ ለሌሎቻችን አርአያ የሚሆኑ፤ ትውልዱን ሊቀርጹ የሚችሉ ሴቶችን፡ ለመቁጠር ብፈልግ እምብዛም ላገኝ አልቻልኩም።

ለዚህም ምክንያቱ ምን ይሆን ብዬ ራሴን ስጠይቅ ያገኘሁት መልስ፤ በህወሃትም ሆነ በተቃዋሚ ጎራ ያላችሁት “አብላጫዎቹ” ወንዶቻችን የኋላውን አሰራራችንን ሁሉ ኋላቀር ብላችሁ፤ በዘመናዊ ትምህርት ጫና ከበጎ ባህላችን ጋር ጭምር ቅራኔ ውስጥ ገብታችሁ፤ ራሳችሁም ገና ከአውሮፓዊያን የበላይና የበታች

አስተምህሮ ነጻ ስላልወጣችሁና የሃገራችሁን ነባር የአስተዳደር ጥበብ፤ ባህልና አሰራር፡ በተወሳሰበና መተማመን በጎደለው፡ የፓርቲና የድርጅት የተውሶ አወቃቀር፤ ሙሉ በሙሉ በመተካታቹ ነው። በሌላ በኩል ማህበረሰባዊ ፍትህንና እኩልነትን ለማስፈን፤ ነጻ አስተሳሰብና አመለካከት መጀመሪያ ከራስ፡ ብሎም ከቤታችን ይጀምራል። ለሌሎች መብት ለመጮህ፡ መጀመሪያ የግል ህይወታችን የሰው ልጆችን ሁሉ መብት በማክበር ጽንሰ ሃሳብ የተዋቀረ ሊሆን ይገባዋል። በየግል ህይወታችን ከሰዎች ጋር ያለን ግንኙነት ቅጥፈት፤ ተንኮልና አድሎ የተመላበት ከሆነ፤ በሸንጎ ስለፍትህ ብንመክር፡ በአደባባይ ስለ መብት ብንጯጯህ፤ ባዶ የመንፈስ ርካታን ካልሆነ በቀር፡ ማህበራዊ ፍትህንና እኩልነትን አያጎናጽፈንም። የሃገራችን የፖለቲካ መድረክ እኔነትና ራስወዳድነት የነገሰበት የዓለማችን ነጸብራቅ ነውና ወደ ማንነታችን ካልተመለስን ችግራችን ይቀጥላል። ከአውሮፓ በፊት ስልጣኔን ያጣጣመች፤ የነሉሲ መገኛ፤ የአክሱም፤ የላሊበላ፤ የፋሲለደስና፤ የሶፍ ሁመር ዋሻ ባለቤቷ ኢትዮጵያ ውስጥ፤ ለዛሬ ትውልድ የሚበጅ የአስተዳደር ጥበብ ተፈልጎ ይጠፋል ብዬ አላምንም።

በዚህ አጋጣሚ ይልማ ደሬሳ በገዳ ስርዓት መሰረት፡ የኦሮሞ ሴቶች ካገቡ በኋላ እንደ ወንድ በፈረስ ተቀምጠው እንደሚሄዱና ሃሳባቸውንም በነጻነት ሲናገሩ ተደማጭነት እንደሚያገኙ፤ በባላቸውም ትዳር የማዘዝና የማስተዳደር መብት እንዳላቸው ጽፈዋል (የኢትዮጵያ ታሪክ በአስራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን 1959፤ ገጽ 247)። ዛሬ በዘመናችን የፖለቲካ ፈረስ ላይ የሚቀመጡ፡ በርካታ የኦሮሞ ሴት ወይዛዝርትን ማየት እፈልጋለሁ። የሃገር ውስጥና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሮቻችን የደዋሮ ሴቶች ሆነው ማየትን እመኛለሁ። የእርዳታ ማስተባበሪያ ተቋም ወይም ትምህርት ሚኒስቴር ውስጥ ብዙ መነኖችን ለማየት እፈልጋለሁ። ኢትዮጵያን፤ ኤርትራን፤ ሱማሌን፤ ጅቡቲን፤ 2ቱን ሱዳኖች፤ ግብጽንና ኬኒያን አዋደው እና የተቃቃረውን አስማምተው፤ ለዓለማችን የሰላምን ዘር የሚዘሩ እሌኒዎችን ማየት ህልሜ ነው።

ለሃገራችን ጥቅምና አንድነት፤ ለዓለማችን ደህንነትና ሰላም፤ ለምድራችን ልምላሜና በረከት ሴቶች ከማጀታቸው እየወጡ አደባባዩን እንዲሞሉት ወንዶችም ሴቶችም ማገዝ፤ ማበረታታት፤ ጓዳቸው  እንዳይጎድል ዘመድ ወዳጅ እንዳይሰላች መተጋገዝ ይገባናል። በተመሳሳዩም ወንዶች ለሃገራዊ ጉዳይ አደባባይ ስትውሉ ሴቶችም ሆንን ሌሎች ወንዶች ለቤተሰባችሁ ልንሳሳላችሁ ይገባል። ውጤት አለመስዋዕትነት እንደማይገኝ የታወቀ ነው፤ ነገርግን አንዳንዴ መስዋዕትነቱ የግል፡ ወይም የቤተሰብ፤ ከፍ ሲልም የማህበረሰቡ ሊሆን ይችላል። ዳንኤል ፖ የተባሉ ጸሃፊ ሚሼል ናር ኦቤድ ስለተባለችው የሃገሯ የአሜሪካን መንግስት በውጪ ሃገራት የሚያደርገውን ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት አምርራ ስለምትቃወመው ሴት ሲጽፉ፤ ሚሼል ማህበረሰባችን የእናትነትን ሚና ለእናት ብቻ  የሚተወውን አስተሳሰብ፤ ለጋራ ጥቅም ሲባል ሃላፊነትን በመውሰድ ለጎጆዋ ብቻ  ልታውለው የምትችለውን ልጇን በሰላምና በእንክብካቤ የማሳደግ እናታዊ ተግባር፡ ለፍጥረት ሁሉ አለኝታ ለመሆን፡ እየታሰረች እየተፈታች ስለ ዓለም ሰላም ስትታገል፤ በአንጻሩ ባሏና ማህበረሰቧ ሴት ልጇን ለማሳደግ እናታዊ ሚናን በጋራ በመወጣት ከዓላማዋ እንዳትደናቀፍ እንደተባበሯት ጽፈዋል (Danielle Poe “Woman, Mother, and Nonviolent Activism.” Positive Peace: Reflections on  Peace Education, Nonviolence, and Social Change 2010 P. 119, 130-31).

ስለዚህ ጥያቄው ሴቶች ለምን ከትግል ጎራ ታጡ ሳይሆን፡ ወደ ትግሉ ጎራ ሲወጡ በቂ ድጋፍ እንዲኖራቸው ማህበረሰባችንን ለማንቃት፤ ለማስተማር ምን ስራ ተሰርቷል? የትግሉ ጎራ እንደ ኮርማ  መጎሻሸሚያ መሆኑ፡ እንኳን ሴቶችን ወንዶችንም ስለሚያሸሽ፤ ለሃገር ጥቅም ሲባል ክብሬ ኩራቴ ተነካ በማለት መጎሻሸሙን ለማስቀረት በእናንተ ዘንድ ፈቃደኝነቱ አለ ወይ? ወደ ትግሉ ጎራ እንደምንም የመጡትንስ ሴቶች ከጓዳ ስራ ሌላ፤ ለማማከርና የመሪነት ድርሻ  እንዲኖራቸው ለማብቃት ዝግጁ ናችሁ

ወይ? ለሃገራችንስ ከህወሃት የተለየ ሴቶችን፤ ወጣቶችንና አነስተኛ የብሄር ቁጥር ያላቸውን የማህበረሰባችንን ክፍሎች የሚያሳትፍ ራዕይ ሰንቃችኋል ወይ? ራዕዩ ሲጠነሰስስ የሁሉም የህብረተሰብ አካላት ተሳትፎ አለበት ወይስ ለይስሙላና ብቻ ነው ተሳትፏችን የሚፈለገው?

ዶ/ር ታደሰ ወ/ጊዮርጊስ፤ “ኅብረተሰብ የሚፈጠረው፡ ኅብረተሰብ የሚደራጀው፤ የኅብረተሰቡ ግማሽ አካል የሆኑት ሴቶች በኅብረተሰቡ እንቅስቃሴ ውስጥ በእኩልነት ደረጃ ሲሳተፉ ነው” ብለው ጽፈዋል (የምዕራባውያን ሥልጣኔና ኢትዮጵያዊያን በአሜሪካ ማህበራዊ እና ስነ ልቡናዊ ትንተና  2006፤ ገጽ 235)። “ዘመናዊ” ትምህርት ተምረናል በምንልበት በዚህ ዘመን፤ ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት የነበሩ ቀደምቶቻችንን ያህል እንኳን አስተውለን፤ ሴቶች በተፈጥሮ የተቸራቸውን የማማከር፤ የማግባባት፤ አርቆ የማየት ጥበብ ጥቅም ላይ ስናውለው አላየሁም። ፕ/ር ሃይሌ ገሪማ  እንዳሉት፡ “የኢትዮጵያ ጉዞ ሶስት ሺህ ዘመን ወደኋላ፤ ወደኋላ፤ ወደኋላ ሆኗል”። በሌላ በኩል ቴዲ አፍሮ “የኋላው ከሌለ የለም የፊቱ” ቢለንም፤ ወደኋላ የምናየው ከበጎውም ከመጥፎውም ታሪካችን ለመማር እንጂ የነበረንና የገነባውን ሁሉ እያፈረስን የኋልዮሽ በመሄድ፤ አፍርሰን ለመስራት መሆን የለበትም። ስለዚህ፡ ምንም እንኳ ሴቶች ወደ ትግሉ ጎራ እንዳይገቡ ሌሎች ሴቶችም ሊያዳክሙ እንደሚችሉ ቢገለጽም፤ የዘመናችን የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምህዳር የተጥለቀለቀው ግን በወንዶች ስለሆነ፤ የሴቶች ፖለቲካዊ ተሳትፎ እንዲጨምርና የኋልዮሽ ጉዞአችን እንዲቆም እናንተስ ምን አቅዳችኋል? ብዬ ጥያቄውን ወደ ወንዶቻችን መልሸዋለሁ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.