ክቡር ሚኒስትሩ መኝታ ቤታቸው ሆነው የቡችላ ድምፅ ይሰሙና ጥበቃቸውን አስጠሩት

ክቡር ሚኒስትሩ

አንተ፡፡
አቤት ጋሼ፡፡
የምን ድምፅ ነው የምሰማው?
የት ጋሼ?
ግቢ ውስጥ ነዋ፡፡
እንግዲህ ወፎች ይጮሃሉ፣ የመኪና ድምፅ ይኖራል…
እሱን አይደለም የምልህ፡፡
ታዲያ የምን ድምፅ ሰምተው ነው?
የምን የቡችላ ድምፅ ነው የምሰማው?
አልሰሙም እንዴ ጋሼ?
ምኑን?
ወለደች እኮ፡፡
ማን?
የእኛ ውሻ ናታ፡፡
ምን?
እንዴ ጋሼ እርጉዝ ነበረች እኮ?
ከማን ነው ያረገዘችው?
ያስረገዛት አልታወቀም፡፡
እንዴት?
ከሰፈር ውሻ ነዋ ያረገዘችው፡፡
ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?
መድኃኒት ትወስድ ነበር እንዴ?
የምን መድኃኒት?
የእርግዝና መከላከያ፡፡
ማሾፍህ ነው?
አይ እንዴት ልታረግዝ ቻለች ሲሉኝ ነዋ?
እኔማ ማርገዟ አናዶኝ ነው፡፡
ለምን ክቡር ሚኒስትር?
ስማ በስንት መከራ ነው እኮ ያገኘኋት፡፡
ማለት ክቡር ሚኒስትር?
ምርጥ ዘር ናት፣ በብዙ ሺሕ ብር ነበር የገዛኋት፡፡
ዘር መቀላቀሏ ነው ያናደደዎት?
ታዲያስ፣ የቡችሎቹ አባት ራሱ አይታወቅም፡፡
እሱማ ዲቃላ ነው ያመጣችብን፡፡
አንተ ግን ይኼ ሲሆን የት ነበርክ?
የእኔ ሥራ እኮ ቤቱን መጠበቅ ነው፡፡
ውሻዋም እኮ ቤቱ ውስጥ ነበረች፡፡
እኮ በር ሲከፈት ወጥታ ነው አርግዛ የመጣችው፡፡
ስለዚህ ምን መደረግ እንዳለበት እኔ ነኝ የማውቀው፡፡
ምን ሊያደርጉ ነው ክቡር ሚኒስትር?
ሁሉም ውሾች መረሸን አለባቸው፡፡
የትኞቹ ውሾች?
የሰፈር ውሾች ናቸዋ፡፡
እነሱ ምን አጠፉ?
ይኸው ውሻዬን አስረገዟት አይደል እንዴ?
ያረገዘችው እኮ ራሷ ሄዳ ነው፡፡
ቢሆንም ጥፋቱ የእነሱ ነው፡፡
እዚህ ግቢ ገብተው አይደለም እኮ ያስረገዟት፡፡
አንተ ለእነሱ ተሟጋች ያደረገህ ማን ነው?
ከፈቀዱልኝ ግን አንድ ነገር ልናገር?
እሺ ተናገር፡፡
ሰው ፍትሕ አጣሁ እያለ የሚማረረው ለካ እውነት ነው፡፡
እንዴት ማለት?
እንዲህ ዓይነት ፍርድ ቢሮም የሚፈርዱ ከሆነ የሰው ምሬት ገባኝ፡፡
ያልተጠየቅከውን ለምን ትዘባርቃለህ?
ይቅርታ ክቡር ሚኒስትር፡፡
ለመሆኑ ስንት ቡችሎች ነው የወለደችው?
አምስት፡፡
ስለዚህ እናታቸው ቡችሎቹን ትጠርንፋቸው፡፡
በምን?
በአንድ ለአምስት!
[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ስልክ ተደወለላቸው]

ሄሎ ክቡር ሚኒስትር፡፡
ማን ልበል?
እኔን እንኳን አያውቁኝም፡፡
ታዲያ ለምን ደወልክ?
አንድ ነገር ልነግርዎት ነው፡፡
ምንድን ነው የምትነግረኝ?
ስለልጅዎት ነው፡፡
ምነው ልጄ ኪራይ ሰብሳቢ ሆነ እንዴ?
እንግዲህ እንደዚያ ሊሉት ይችላሉ፡፡
ከፀረ ልማቶች ጋር ገጥሟል እያልከኝ ነው?
ከወንጀል ጋር የተገናኘ ነው፡፡
ምን አልከኝ?
ወንጀል ነክ ጉዳይ ነው፡፡
የእኔ ልጅማ ወንጀለኛ አይደለም፡፡
እሱ ወደፊት የሚታይ ጉዳይ ይሆናል፡፡
ቆይ ምን አድርጎ ነው?
ሕገወጥ ዕቃዎችን ያዘዋውራል፡፡
ምን ዓይነት ሕገወጥ ዕቃ?
ሕገወጥ የሆኑ መድኃኒቶችን፡፡
ምን ዓይነት ሕገወጥ መድኃኒቶች?
እንዳይደነግጡ ግን ክቡር ሚኒስትር፡፡
ሰውዬ ለምን አትናገርም?
ሕገወጥ ዕፅ ያዘዋውራል፡፡
ምን አጠፋሪስ ምናምን ነው?
አይደለም ክቡር ሚኒስትር፡፡
ምን ዓይነት ዕፅ ነው ታዲያ?
ኮኬንና ኤክስተሲ!
[ክቡር ሚኒስትሩ ልጃቸውን አስጠሩት]

አቤት ዳዲ፡፡
ድድህን ማውለቅ ነበር፡፡
ምነው ዳዲ?
ምንድን ነው የምሰማው?
ምን ሰማህ ዳዲ?
ምን ዓይነት ሥራ ነው የምትሠራው?
ትምህርት እማራለሁ፣ በጐን ግን ቢዝነስም አለኝ፡፡
እኮ ምን ዓይነት ሥራ?
እንዴ ዳዲ ሁሉንም ነገር ለአንተ ማሳወቅ አለብኝ?
አባትህ ነኝ እኮ?
እሱማ አውቃለሁ፡፡
ስለዚህ የሰማሁት እውነት ነው ማለት ነው?
ምን ሰማህ ዳዲ?
ሕገወጥ መድኃኒት ታዘዋውራለህ እንዴ?
ሕገወጥ የሆነው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፡፡
እንዴት ማለት?
ውጭ በፕሪስክሪፕሽን የሚገዙ መድኃኒቶች ናቸው፡፡
ከማን ጋር ነው ይኼን የምትሠራው?
ከሌሎች የሚኒስትር ልጆች ጋር ነዋ፡፡
እንዴት እዚህ ሥራ ውስጥ ገባህ?
የዕድገቱ ውጤት ነዋ፡፡
የአገሪቷ ዕድገት ነው?
የአንተ ዕድገት ነው እንጂ፡፡
እኔ ወደ ምን አደግኩ?
ወደ ሚኒስትርነት!
[የክቡር ሚኒስትሩ መሥሪያ ቤት የ150 ሺሕ ኮምፒዩተሮች ጨረታ አውጥቷል፡፡ አንድ ተጫራች ደወለላቸው]

ሄሎ ክቡር ሚኒስትር፡፡
ማን ልበል?
ስልኬን አልያዙትም ማለት ነው ክቡር ሚኒስትር?
አላወቅኩህም ማን ልበል?
ባለፈው ተገናኝተን ነበር፡፡
ምን ፈልገህ ነው አሁን?
አይ ስለጨረታው እንድናወራ ብዬ ነው፡፡
ስለየቱ ጨረታ?
ስለኮምፒዩተሩ ጨረታ፡፡
የጨረታ ሰነድ ገዝተሃል?
ከዚያ በላይ ዋናው እርስዎ ነዎት፡፡
ምን እያልከኝ ነው?
ክቡር ሚኒስትር ይኼ ጨረታ የሁለታችንንም ሕይወት ይለውጠዋል፡፡
እንዴት ማለት?
ኮምፒዩተሮቹ የሚፈለጉት ለምን ዓላማ ነው?
ያው ለቢሮ ሥራ ነዋ፡፡
ስለዚህ ክቡር ሚኒስትር እኔ ከቻይና ላስመጣቸው እችላለሁ፡፡
እኛ ግን ብራንድ ዕቃ ነው የምንፈልገው፡፡
እኮ ዕቃውማ ብራንድ ነው፡፡
ከቻይና ነው የማስመጣው ስትለኝ?
ከውስጥ የቻይና ይሆንና ከውጭ ግን ብራንድ እናደርገዋለን፡፡
ዋናው ጉዳይ ለእኔ ምን ጥቅም አለው የሚለው ነው?
ክቡር ሚኒስትር ኮሚሽን አስባለሁ፡፡
በቃ የምንፈልገውን ስፔሲፊኬሽን አሁን እልክልሃለሁ፡፡
ቴንኪው ክቡር ሚኒስትር፡፡
ኮሚሽኔ ስንት ነው ግን?
በአንድ ኮምፒዩተር…
እ…
አምስት ዶላር!
[ለክቡር ሚኒስትሩ ሌላ ተጫራች ደወለላቸው]

ሄሎ ክቡር ሚኒስትር፡፡
ማን ልበል?
ስላወጣችሁት ጨረታ ለመነጋገር ነው፡፡
የቱ ጨረታ?
የኮምፒዩተሩን ጨረታ፡፡
ቅድም ተነጋግረን ጨረስን አይደል እንዴ?
ይቅርታ ከእኔ ጋር በዚህ ጉዳይ አልተነጋገርንም፡፡
አንተ ማን ነህ?
ቅድም ምሳ ላይ ተዋውቀን ነበር፡፡
ጨረታውን እኮ ተስማምቼ ጨርሻለሁ፡፡
በምንድን ነው የተስማሙት?
በኮምፒዩተር ሰባት ዶላር ነዋ፡፡
እንዴ ክቡር ሚኒስትር ይኼማ እርስዎንም አገሪቷንም መናቅ ነው?
እንዴት?
አገሪቷስ እኮ በሁለት ዲጂት እያደገች ነው፡፡
እሱማ ይታወቃል፡፡
እርስዎም ኮሚሽን መቀበል ያለብዎት እንደዚያው ነዋ፡፡
እንዴት?
በሁለት ዲጂት!
[የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪያቸው ቢሯቸው ገባ]

ላናግርዎት ፈልጌ ነበር ክቡር ሚኒስትር?
ስለምን ጉዳይ?
በቅርቡ ስላሠራነው ሕንፃ፡፡
ተሠርቶ ተመረቀ አይደል እንዴ?
አዎ ግን በሦስት ወሩ እየተሰነጣጠቀ ነው፡፡
ምን?
እንዲያውም ሊፈርስ ሁላ ይችላል፡፡
በሦስት ወሩ?
አዎን ክቡር ሚኒስትር?
ምን ሆኖ?
በጥራት አልተሠራም፡፡
ጨረታ አውጥተን አይደል እንዴ ያሠራነው?
ማውጣትማ አውጥተን ነበር፡፡
እና ምን ሆነ?
ጨረታው የተሰጠው ግን ለመንግሥት ድርጅት ነው፡፡
ለምን ተሰጠው?
የልማት አጋር ነው ተብሎ ነዋ፡፡
ስለዚህ በድጋሚ ጨረታ ይውጣና መልሶ ራሱ ድርጅት ይሥራዋ፡፡
ተመልሶ ለዚያው ድርጅት የሚሰጠው ከሆነ ለምን ጨረታ ይወጣል?
ለማሳየት ነዋ፡፡
ምኑን ክቡር ሚኒስትር?
የሥራችንን ግልጽነት!
[የክቡር ሚኒስትሩ መሥሪያ ቤት በድጋሚ ያወጣውን የሕንፃ ግንባታ ጨረታ የተለመከቱ ሌላ ሚኒስትር ደወሉላቸው]

ሰላም ክቡር ሚኒስትር፡፡
እንዴት ነህ ወዳጄ?
በቅርቡ አልነበር እንዴ ሕንፃ ያስገነባችሁት?
አዎን ልክ ነው፡፡
ታዲያ ለምንድን ነው የሕንፃ ጨረታ ያወጣችሁት?
ሕንፃው ስለፈረሰ ነው፡፡
በሦስት ወሩ ነው የፈረሰው?
ሆን ብለን ነው ያፈረስነው፡፡
ለምን ክቡር ሚኒስትር?
ሕንፃውም ያስፈልገው ነበር፡፡
ምን?
ጥልቅ ተሃድሶ!

ምንጭ – ሪፖርተር

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.