ወመኑ ዘይደምሮ ብርሃን ውስተ ጽልመት : ዳሸን ቢራን በፋሲል ከነማ ላይ መደረት – መስቀሉ አየለ

ዳጎን የተባለውን ጣኦት በታቦተ ጽዮን ላይ የመጫን ያህል ነው።ይኽን እብሪት የተፈለገውን ያህል መንገድ ተጉዞ ወደኋላ መመለስ የማይቻል ግድ ይለዋል፤ ካልሆነ ግን ዘመነ ሚጠት እስኪመጣ ደጋፊው ስደት ላይ መሆኑን ማመን አለበት፤ስለሆነም የጋንግሪኖቹ ሴራቸው ስጋና ደም እንዳይገዛ የቻለ ንቁ ሆኖ ወደ እርስቱ የሚመልሰውን ዛሩባቤልን ከመሃሉ ይፈልግ፤ ያልቻለ ደግሞ እንደ ባሮክና አቤሚሊክ ስልሳ ስድት አመት ይተኛና ዘመነ ሚጠት በደረሰ ግዜ የሶስተኛው ነጋሪት ድምጽ እንዲቀሰቅሰው ይሁን። ከዛ በመለስ የቀረበው ምርጫ ግን የጣኦቱን መስዋት በልቶ እንደ ሶሎሞን ከክብር መውረድ ነው። እርሱ የማርያም መንገድ አይሆንም።

በሮማን ኤምፓየር ዘመን ፈርኦኖቹ የሚዝናኑበት እስታዲዩም ነበር፤ዛሬም ድረስ በሮምና በወቅቱ የነርሱ ሁለተኛ መናገሻ በነበረችው በዛሬዋ ፓልሜራ (ሲሪያ) ውስጥ ይገኛሉ። የጨዋታውም አይነት በነገስታቶቹ ፊት የተመረጡና ጉልበት ያላቸው ባሮች “ፋያቲንግ ቱ ዴዝ” መጫወት ነበር። እድል ያልቀናው በወኔና በጭብጫ ገብቶ በጥቂት ደቂቃወች ውስጥ አስከሬን ሆኖ ይወጣል። ንጉሱ ከፈለገና ይበልጥ መደሰት ከፈለገ ደግሞ የጨዋታው አይነት ባሪያ ለባሪያ መሆኑ ቀርቶ ፍልሚያው ከአንበሳ ጋር ሊሆንለት ይችላል። ባሪያው በራሱ ላይ መብት የለውምና ባለቤቱን ለማስደሰት እስከ ተፈለገ ድረስ ሁን የተባለውን መሆን የምርጫው ነገር አይደለም። መንፈሱ ያልተሰበረ; ከሰውነት ተራ ወርዶ ወደ እቃነት ያልተለወጠና በነፍሱ ጭምር ለማሰብ አቅም ያለው ሰው ሲሆን ግን እንዲህ አይነቱን ውርደት ፈጽሞ አይሸከምም ነበር። “ለመሞት-ለመሞት ከነ ክብሬ ልሙት እንጅ በኔ ሲቃይ ሌላው ቁጭ ብሎ የእረፍት ቀኑን የሚዝናናብኝ ማነው?” ብሎ የሞቱን ጽዋ በራሱ እጅ እንዲወስዳት የሚያስችለው ከፍ ያለ የሞራል አቅም የገነባ ነበር ማለት ነው።

ዛሬ የአባይ ወልዱ ጭፍሮች ፋሲል ከነማን “ወርሰነዋል” ሲሉ ማሳየት የፈለጉት ይህንኑ ነው፣ “ጎንደሬ ምን ታመጣለህ፤ ስትፈልግ ይኽንን ሁሉ ተጨዋች ከሰውነት ተራ አውርደን የራሳችን ግላዲያተር ማድረግም እንችላለን” ነው ዋናው መልእክት። “ከእንግዲህ አርማኽ ቢሆን የዳሸን ቢራ መሆኑን እንድታውቀው ይሁን” ነው መልእቱ፤ አጼ ቲዎድሮስ የኮሶ ሻጭ ልጅ ብሎ የሰደበውን ሰው ባሊ ሙሉ ኮሶ ግቶ እንደገደለው ዛሬም ጋንግሪኖቹ ድፍን ጎንደሬን ባሊ ሙሉ ኮሶ ለመጋት መፈለጋቸውን ነው የሚያሳየው። ይህ ሁሉ እንግዲህ በዙሪያቸው እንደ አርተሌ እሳተ ጋሞራ የሚንቀለቀለው የጸረ ወያኔ ብሄርተኝነት ገንፍሎ ሳያጠፋቸው በፊት ውሃ ሊያፈሱበት እና የህዝቡንም መንፈስ አኮላሽቶ ህዝቡን ለለየለት ባርነት ማዘጋጀት ነው አለማው።

አንድ የአገዛዙን እውነተኛ ገጽታ የሚያሳይ የቀልድ ክሊፕ አይቸ ነበረ። ሰውየው ኑሮ ቢከብደው ሚስቱን ተሰናብቶ እራሱን ሊያጠፋ በአካባቢው ወደ ሚገኝ እረጅም ድልድይ ይሄዳል፤ ጫፉ ላይ ቆሞ ሃሳቡን ለመሰብሰብ ሲታገል አጋዚው ያገኘውና “እዚህ ምን ታደርጋለህ” ሲል ይጠይቀዋል። ሰውየው ደግሞ “ኑሮ ቢከብድብኝ መከራ ቢወድቅብኝ ሚስቴን ተሰናብቸ እራሴን ላጠፋ መጣሁ” ሲል ይመልስለታል፤ አጋዚው ቢሆን ግን ምክንያቱን ከሰማ ቦሃላ “እዚህ እራስህን ማጥፋት አትችልም፤ ከፈለክ ሌላ ቦታ ፈልግ” ይለዋል፤ ሰውየው ግራ በመጋባት ለምን ብሎ ቢጠይቀው የአጋዚው መልስ እንዲህ የሚል ነበር።”ቦታውን በሊዝ ገዝተነዋል” የሚል ነበር።

ዛሬ ከፋሲል ተጨዋቾች ውስጥ ማነው የነገሩ ስሌት የገባው ይሆን። ጥቂቶቹ ቀርተው አንዱ እንኩዋን “አርማየን አልሰጥም፤ማተቤን አልበጥስም” ብሎ ወደታች አርማጮሆ ወርዶ የጎቤን ሱሪ መውረሱን ቢያውጅ በእግር ኳስ ተጨዋቾች ታሪክ የመጀሪያው ሃውልት ሆኖ ይጻፋል። ክልቡን ከደመወዝ በላይ አሻግሮ ማየት የቻለ፤ ፋሲል ከነማ በዚህ የአብዮት መባቻ ወቅት ፈክቶ በመውጣቱ የጸረ ውያኔ ትግሉ ማኒፌስቴሽን መሆን መቻሉ ጋንግሪኖቹን እንቅልፍ እንደ ነሳቸው ያወቀ፤ ኳስ ማንቀርቀቡንና በጥይት ማንጠርጠሩን እኩል የሚያውቅ፤ የክፉ ግዜ ሰልፈኛ የደግ ግዜ ሰላምተኛ; “ደመዛችሁን ውሰዱ እንጅ ማተቤ ላይ መብት የላችሁም” የሚል ማን ይሆን ?፤ በላይ ዘለቀ ሚስቱንና ልጁን ላፈነበት እና “ሰይፍህን ወደ ሰገባው መልስ፣ እጅህንም ለኛ ስጥ” ብሎ ለላከበት የፋሽስት ሰላቶ የመለሰውን መልስ ልብ ብሎ የሰማ የዘመናችን በላይ ማን ይሆን ?፤ “ኳስ ለምኔ፤ ጠመንጃ ምርኩዜ!” ብሎ ግዳይ የሚወጣ የወንድ ቁና የቱ ይሆን..

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.