‹‹ለጋራ አገራችን በጋራ እንወያይ የሚል ጥሪ ማቅረብ እፈልጋለሁ›› ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከወራት ፀጥታ በኋላ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ከሚዲያው ጋር ፊት ለፊት ተገናኝተዋል፡፡ የሰሞኑ ዋና የመወያያ ርዕስ የሆነውንና አገሪቱ ወደ ዓለም አቀፉ የቦንድ ገበያ ለመግባት ያደረገችውን ጥረት እንደተጠበቀው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያብራሩት ዋናው ጉዳይ ነበር፡፡

‹‹አገሪቱ ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ገበያው ገንዘብ ለማግኘት ብቁ ሳትሆን ቆይታለች…›› በማለት ጉዳዩን ያስረዱት አቶ ኃይለ ማርያም፣ በስኳር ፕሮጀክቶችና በኢንዱስትሪ ዞን ላይ ወጪ የሚደረገው ይህ ገንዘብ፣ ለህዳሴ ግድብ ግንባታ እንደማይውልና ግድቡም የገንዘብ ችግር እንዳላጋጠመው አትተዋል፡፡ ከውጭ ብድር በተጨማሪ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለያዩ የአገሪቱ ሜጋ ፕሮጀክቶች ላይ እየታየ ያለውን ግስጋሴ በዝርዝር አብራርተዋል፡፡ በተለይም በሰሞኑ የስኳርና የነዳጅ አቅርቦት መስተጓጐልን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ የስኳር ፕሮጀክቶችን ጉዳይ ከተከሰቱ ፈተናዎች ጋር በማያያዝ ተንትነዋል፡፡ በሌላ በኩል በአፍሪካ ቀንድ በተለይም በደቡብ ሱዳን፣ በሶማሊያና በጂቡቲ ላይ መንግሥት የያዘውን አቋም አስረድተዋል፡፡ መንግሥታቸው በመጪው ምርጫና ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ስላለው አጠቃላይ ሁኔታ አብራርተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአገር ውስጥ ጋዜጠኞች ጋር ካደረጉት ቆይታ የተቀነጨበው ምላሻቸው በፖለቲካ ገጽ ላይ ተስተናግዷል ይመልከቱ፡፡

Source:: Ethiopian Reporter